Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮም በሐዲስ ተፈጥሮም ከእርሱ ጋር አስተካክለን
ጥንተ ተፈጥሮ አዳም በመጀመሪያ ከፍጥረታት ሁሉ ጋር የተገኘበት ተፈጥሮ ነው፡፡ ሐዲስ ተፈጥሮ ጌታችን በዕለተ ዓርብ በመሠረታት ጥምቀት ዳግመኛ ከእግዚአብሔር የምንወለደው የልጅነት ተፈጥሮ ነው፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ይህን ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ ሲፈጥረው በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ ካለ በኋላ በዚህ ቀን ይህን ፈጠረ በዚህ ቀን ይህን ፈጠረ ዘፍ. 1:1-25 እያለ ሂዶ "እግዚአብሔርም አለ ሰውን በአርአያችንና በአምሳላችን እንፍጠር... ሁሉን ይግዛ ብሎ እግዚአብሔር ሰውን በእግዚአብሔር አምሳል ፈጠረ" ዘፍ. 1:26-27 ይላል፡፡

ዳግመኛ ይህን በዝርዝር የተናገረውን ሥነ ፍጥረት በመጽሐፈ ኩፋሌ ጠቅለል አድርጎ

"ሁሉም ሃያ ሁለት ዓይነት ፍጥረት ሆነ በስድስተኛዪቱም ቀን በሰማይና በምድር በባሕሩና በጥልቁ ውስጥ በብርሃንና በጨለማ መካከል በሁሉም ላይ ያለውን ፍጥረት ሁሉ ፈጥሮ ፈጸመ ኩፋ. 3:2 ብሎአል፡፡ ሃያ ሁለተኛው አዳም ነው፡፡

ሃያ ሁለት ዓይነት ፍጥረት ሆነ ሲባል ግን እያንዳንዱ በዝርዝር ተቈጥሮ አይደለም ብዙውን አንድ እያሉ በጥቅል ሲቈጠር ነው ለምሳሌ ከዋክብት ስፍር ቁጥር የላቸውም ልበ አምላክ ዳዊት

"ከዋክብትን በመላው የሚቈጥራቸው በየስማቸውም የሚጠራቸው እግዚአብሔር ታላቅ ነው ለጥበቡም ቁጥር የለውም" መዝ. 146:4-5

እንዳለው ከፈጠራቸው ከእግዚአብሔር በስተቀር ሊቈጥራቸው የሚችል የለም፡፡

መላእክትም ምንም እንኳ እንደ ከዋክብት ተደርድረው ባይታዩም ቁጥራቸው ከከዋክብት ሊበልጥ እንደሚችል ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ ታዲያ እነዚህና እንደ እነዚህ ብዛት ያላቸው ሁሉ በጅምላ አንድ እየተባሉ ተቈጥረው ነው ሃያ ሁለት ዓይነት ፍጥረት ሆነ የተባለው፡፡ ይሁን እንጂ ከእነዚህ ስፍር ቁጥር ከሌላቸው ፍጥረታት ሁሉ በእግዚአብሔር ምሳሌና መልክ የተፈጠረ የሰው ልጅ ብቻ ነው ዘፍ. 1:26-27 ዳግመኛ እንደ እግዚአብሔር ሁሉን እንዲገዛ የከበረ ዕድል የተሰጠው ለሰው ልጅ ብቻ ነው፡፡
ሦስተኛ በአፍንጫው እፍ ብሎ አርአያ እግዚአብሔርን ያደለው ሰውን ብቻ ነው፡፡

"እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ" ዘፍ. 2:7፡፡

ይህች የሕይወት እስትንፋስ የተባለች ሕያውነት ለባዊነትና ነባቢነት ያላት ፍጹምነት አርአያ እግዚአብሔር ወይም እግዚአብሔርን መምሰል ያላት ልጅነት ናት፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ሰውን በዚህ መልኩ ራሱን አስመስሎ በመፍጠር አክብሮና አልቆ አስቀምጦት ነበር "ወረስዮ ርኡሰ ወስሉጠ" አማርኛ ገዥና አለቃ አደረገው" መቅድመ ወንጌል፡፡ ነገር ግን ሰው የተሰጠውን ጸጋ ጠብቆ ሊኖር አልቻለም የጠላት ምክር ሰምቶ አምላክነት ሽቶ አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስ በመብላት ከፈጣሪው ተጣልቶ ከክብሩ ተዋረደ ከገነት ተባረረ ዘፍ. 3:1-24
ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት

"ሰው ግን ክቡር ሲሆን አላወቀም ልብ እንደሌላቸው እንስሶችም ሆነ መሰላቸው" መዝ. 48:12-20

እንዳለ በዚህ ጊዜ አዳምና ሔዋን እግዚአብሔርን ያዩበት የነበረ መልካሙ ዐይነ ልቡናቸው ታውሮ ከፉውን ነገር ሁሉ የሚያዩበት ዐይነ ሥጋቸው ተገለጠ ዕራቁታቸውን እንደሆኑ ዐወቁ" ዘፍ. 3:1-7 ልጅነታቸው ተገፈፈ ጸጋ እግዚአብሔር፣ ረድኤተ እግዚአብሔር ራቀቸው በአንጻሩ ፍራት፣ መንቀጥቀጥ፣ ድንጋጤ፣ ሽብር፣ እፍረት ያዛቸው ከዚህም የተነሣ የበለስን ቅጠል ሰፍተው ዕርቃናቸውን ሰወሩ ያም አልበቃ ብሎ በገነት ዛፎች ውስጥ ተሸሽጉ፡፡ ዘፍ. 3:8
ከዚያች ሰዓት ጀምሮ አዳም ከገነት መውጣቱ ሳያንስ በተጨማሪ ከእግዚአብሔር ጋር ከመኖር ከሰይጣን ጋር ወደ መኖር ከእረፍት ወደ ድካም ከደስታ ወደ ኀዘን ከሕይወት ወደ ሞት ተሸጋገረ "በዚህ ምክንያት ሞት በሰው ልጅ ላይ ሠለጠነ ስለዚህ ነው

"እግዚአብሔርስ ሞትን አልፈጠረም ነዋሪ ይሆን ዘንድ ፍጥረትን ፈጠሮአልና የሰዎች ጥፋት ደስ አያሰኘውምና ለመቃብርም በዚህ ዓለም ግዛት አልነበረውምና እግዚአብሔርን የዘነጉ ሰዎች ግን በቃል ጠሩት ባልንጀራም አደረጉት በዚህም ጠፉ" ጥበ.1:13-15:16

ከዚህም ጋር የሰው ልጅ የሰይጣን ተገዥ ሆነ፡፡
አዳም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አክብሮ ሥርዓቱን ጠብቆ ሲኖር የሁሉ ገዢ አደርጐታልና ሁሉ ያከበረው ሁሉ ይፈራው ነበረ ለአብነት ዛሬ ብዙ ቱሪስቶች ጊዜያቸውን ሠውተው ብዙ ገንዘብ አውጥተው አገር ለአገር ጫካ ለጫካ እየኳተኑ በአድናቆት የሚጐበኙአቸውን የዱር እንስሳትና አራዊት ሁሉ በእግዚአብሔር ፈቃድ ስም እንዲያወጣላቸው ዘወተር ወደ እርሱ እየሄዱ ከማዝናናታቸውም በላይ አልበህ ጠጣን አርደህ ብላን እያሉ ለእርሱ ያላቸውን አክብሮት ይገልጹ ነበር ዘፍ. 3:19-20 ሰይጣንም አይቀርበውም ነበር፡፡


ከእግዚአብሔር ጋር ከተጣላ በኋላ ግን ሁሉም ተጣላው እንስሳትም ሸሹት መልሰውም የሚተናኰሉትና የሚያጠቁት ሆኑ ይፈሩት የነበሩ አጋንንትም በነፍስ በሥጋው ገዢዎቹ ሆኑ፡፡
ስለዚህም ነው ታላቁ አባት ሐዋርያዊ አትናቴዎስ "ሰብእሰ እንዘ ንጉሥ ውእቱ ኢያአመረ አኅሠረ ርእሶ በፈቃዱ ወኮነ ገብረ ወመለክዎ እለ ኢኮኑ አማልክተ" አማርኛ ሰውስ ንጉሥ ሲሆን አላወቀም በፈቃዱም ራሱን አዋረደ ተገዢም ሆነ ገዢዎች ያልሆኑም ሠለጠኑበት" ቅዳሴ አትናቴዎስ ቁጥር 21

ከሞት ለማምልጥ የተደረገ ጥረት

ሰዎች በመሸሽ፣ በመደበቅ ወዘተ በመሳሰለ ከሞት ለመዳን ጥረት ያደርጋሉ በኲረ ፍጥረት አዳም ግን ከመሮጥ ማንጋጠጥ እንዲሉ የእግዚአብሔርን መሐሪነት አምኖና ተስፋ አደርጎ ከሞት ለመዳን በጾም በጸሎት እግዚአብሔርን መማፀን ነው የመረጠው፡፡ ስለሆነም "ለጸለየ ሰው የጸሎቱን ዋጋ ይሰጠዋል" ሳሙ 2:9 እንዲል እግዚአብሔር ልመናውን ሰምቶ አምስት ሺህ ከአምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንኀለሁ በማለት ፍጹም ተስፋ ያለው ቀጠሮ ሰጠው ይኸውም የማይዛባ ቀጠሮ ነው፡፡
የሰዎች ቀጠሮ በብዙ መልኩ ሊዛባ ይችላል የእግዚአብሔር ቀጠሮ ግን በምንም ዓይነት አይዛባም በመሆኑም አምስት ሺህ ከአምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም አድንኀለሁ ባለው መሠረት አንዲት ሰዓት ወይም አንዲት ሰኰንድ ሳያጓድል "ነገር ግን ቀጠሮው በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከ ከሴትም ተወለደ የኦሪትንም ሕግ ፈጸመ" ገላ. 4:4 ተብሎ እንደተነገረ ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍስዋ ነፍስን ነሥቶ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ በመሆን በመስቀሉ ላይ ባፈሰሰው ደሙ ሞትን አጥፍቶ በአዳም የሄደች ልጅነትን መልሶ በሐዲስ ተፈጥሮ ፈጠረን በዚህም በሐዲስ ተፈጥሮ ከእርሱ ጋር አስተካክለን "እኔም የሰጠኸኝን ክብር ሰጠኋቸው እኛ አንድ እንደሆን እነርሱም እንደኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ፡፡ እኛ የእግዚአብሔር ልጆች ከሆነ ወራሾቹ ነን ወራሾቹ ከሆንም የክርስቶስ ወራሾች ነን በመከራ ከመሰልነውም በክብር እንመስለዋለን፡፡ በቸርነቱ ብዛት ከእርሱ ጋር አስተካከለን ተብሎ እንደተጻፈ ዮሐ. 17:22 ሮሜ. 8:17 ገላ. 4:7 2ኛ ጢሞ.2:11 የዓርብ ውዳሴ ማርያም ዮሐ. 17:11 1ኛ ዮሐ. 1:3 3:1 2:5

የከበረ መታሰቢያ

በዓለም ብዙ ዓይነት መታሰቢያ አለ ሰዎች አስፈላጊ ላልሆነ ርካሽና ተራ ነገር ሁሉ መታሰቢያ ያደርጋሉ ቤተ ክርስቲያን ግን ሁሉን ለፈጠረ ለኀያሉ አምላክና ለወዳጆቹ ቅዱሳን የከበረ መታሰቢያ ታደርጋለች፡፡
በዚህ መሠረት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዌው ከሠራቸው ጐላ ጐላ ያሉትን ዘጠኝ ዐበይት በዓላትን ዘጠኝ ንዑሳን በዓላትን ታከብራለች ከፍ ያለ መታሰቢያ ታደርጋለች ከእነዚህም መካከል ግንባር ቀደም የሆነው በአገራችን ብቻ ሳይሆን በውጭ ዓለም ጭምር በከፍተኛ ደረጃ የሚከበረው በዓለ ልደቱ ነው፡፡


በዓለ ልደት ሀ/ለዓለም ሁሉ የሚሆን ታላቅ የምሥራች የተነገረበት ነው ሉቃ. 2:10
ለ/ ሰዎችና መላእክት በአንድነት የዘመሩበት ነው ሉቃ 2:11 – 17
ሐ/ ሁል ጊዜ እስራኤልን ለማጥፋት ወደ ኢየሩሳሌም ይዘምቱ የነበሩ አሦራውያን (ሰብአ ሰገል) የከበረ እጅ መንሻቸውን ይዘው በሰላም የተገኙበት የሰላምና የፍጹም ደስታ በዓል ነው ማቴ. 2: 1-12 ስለሆነም ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ከአንድ ሺህ ሦስት መቶ ዓመታት በላይ በሰላም ሲከበር ኑሮአል፡፡

ከዐሥራ አራተኛ መቶ አጋማሽ ወዲህ ግን እብሪተኞች ነገሥታት ማለትም የሮሙ ንጉሥ ዮስጣትያኖስና የሀገራችን ንጉሥ ዓምደ ጽዮን በፈጠሩት ችግር የጠብና የክርክር መደረክ ሁኖ ይገኛል ይኸውም በተለይ በዘመነ ዮሐንስ ጾመ ልደት ግማሹ ከኅዳር ዐሥራ አራት ቀን ጀምረን እንጹም ሲሉ እኩሌቶቹ ምን ጊዜም ከዐሥራ አምስት ቀን ጀምረን ነው መጾም ያለብን በማለት በዓለ ልደቱንም አንዱ ክፍል በሃያ ስምንት እናክብር ሲሉ ሌሎቹ ምን ጊዜም በሃያ ዘጠኝ ነው መከበር ያለበት በሚል ነው ሰጥ አገባው የነገሠው፡፡

ይህ ችግር እንዴት ተጀመረ ቢሉ ዮስጣትያኖስ ስሙን ለማስጠራት ከሐዋርያት ዘመን አንሥቶ በሃያ ዘጠኝ ይከበር የነበረውን የጌታችንና የመድኃኒታችን በዓለ ልደት በየዓመቱ በሃያ ስምንት እንዲከበር አዋጅ አስነገረ ካህናቱና ሕዝበ ክርስቲያኑ የማይቀበሉት ቢሆን ያለ ርኅራኄ በጭካኔ አስጨፈጨፋቸው የብዙኃኑን ደም በከንቱ አፈሰሰ፡፡

ከብዙ እልቂት በኋላ ችግሩ ያሳስባቸው ሰዎች የክርስቲያን ደም ለምን በከንቱ ይፈሳል፡፡ ይህ ሥርዓት እንጂ ሃይማኖት አይደለም ደግሞም ሌላው ንጉሥ መልሶ እንደነበረው ሊያስተካክለው ይችላል፡፡ ስለዚህ በሦስቱ ወንጌላውያን እንደነበረው በሃያ ዘጠኝ እንዲከበር ሁኖ በዘመነ ዮሐንስ ብቻ በሃያ ስምንት እንዲከበር ይሁን የሚል አስታራቂ ሐሳብ አቀረቡ

ንጉሥና ከፊል ሕብረተሰቡ ስለተቀበሉት ቀሪውም በውድም በግድም ቀስ በቀስ እየተቀበለው መጣና የሮም ብሔራዊ ሥርዓት ሆነ ይላል ዜና ምእመናን ወዐላውያን፡፡

ይህ የተዛባ ሥርዓት ወደ አገራችን እንዴት መጣ

ከጉባኤ ኬልቄዶን በኋላ የሮም ቤተ ክርስቲያን ከኦርቶዶክሶች ይልቁንም አንድ አካል አንድ ባሕርይ ከሚሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ ከአምስቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት በሃይማኖትም በሥርዓትም የተለየች ናት ይህ በሮም የተፈጠረው ብልሹ ሥርዓት ወደኛ ቤተ ክርስቲያን እንዴት ሊመጣ ቻለ ቢሉ ወደ አገራችን የገባው በፖለቲካ ምክንያት ነው፡፡

ከ1297 – 1327 ዓ.ም በኢትዮጵያ የነገሥው የመጀመሪያው (1) ዓምደ ጽዮን ጠላት በበረታበት ጊዜ ከሮም መንግሥት ወታደራዊ ርዳታ ቢጠይቅ የሮም መንግሥት በዘመነ ዮሐንስ የጌታችን በዓለ ልደት እንደሮም አገር በሃያ ስምንት ቀን እንዲከበር ለማድረግ ፈቃደኛ ካልሆነ ርዳታውን እንደማያገኝ ሲነገረው በግድ እንዲቀበለው ሁኖአል፡፡

ከዚህ በኋላ ንጉሡ ይህን ተገዶ የተቀበለውን የተሳሳተ ሥርዓት በሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ ለመጫን ታጥቆ ተነሣ ይሁን እንጂ ጥቂት አድርባዮች ሲደግፉት አብዛኛዎቹ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች በጽኑ ተቃውሙት ከተቃወሙት መካከል የደብረ ሊባኖሱ ሦስተኛው ዕጨጌ አቡነ ፊልጶስ ኢትዮጵያን ከዐሥራ ሁለት ተካፋለው ለማስተማር የተመደቡ ዐሥራ ሁለቱ ንቡራነእድና ግብጻዊ ጳጳስ አቡነ ያዕቆብ በግንባር ቀደም ይጠቀሳሉ፡፡

ንጉሥ ዓምደ ጽዮን ከዘመነ ሐዋርያት አንሥቶ እርሱ እስከ ነገሠ ከሺህ ዓመታት በላይ ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ ቀን ሲከበር የኖረውን በዓለ ልደት ከማዛባቱም ባሻገር የአባቱን ዕቅብት አግብቶ ስለነበረ አቡነ ፊልጶስና መስሎቻቸው እነዚህን ሁለት ስሕተቶች ካላስተካከልህ መንግሥት አይገባህም ከቤተ ክርስቲያንም የተለየህ ነህ ብለው አወገዙት

እርሱም በግርፋት በእሥራት አንዳንዶቹንም በሞት ከቀጣ በኋላ ዕጨጌውን አቡነ ፊሊጶስን አጋዘቸው፡፡ በዚያ ወቅት ጳጳሱ አቡነ ያዕቆብ ከአገራቸው እንደመጡ የደብረ ሊባኖስን ዕጨጌ ጥሩልኝ ሲሉ እርሳቸውማ ከንጉሡ ጋር እንዲህ ባለ ነገር ተጣልተው ተግዘዋል አሏቸው ጳጳሱም ዕጨጌው ትክክለኛ ነው እኔም እንዲህ ካለ ንጉሥ ጋር አልሠራም ወደ አገሬ እሄዳለሁ ብለው ወደ አገራቸው ሊሄዱ ተነሡ

ንጉሡ ይህን ሲሰማ በመደናገጥ እጨጌውን እፈታለሁ የምትሰጡኝንም መመሪያ እቀበላለሁ በማለት ጳጳሱን ተለማምጦ አስቀራቸው ዕጨጌውንም ለጊዜው ፈታቸው ነገር ግን ንጉሡ ስሕተቱን ባለማረሙ ዕጨጌው መልሰው አወገዙት እርሱም ዕጨጌውንና ተከታዮቻቸውን ገፍፎና ገርፎ ዕራቁታቸውን በከተማ እየተጐተቱ እንዲዘበትባቸው አደረገ፡፡ ከዚህ በኋላ እጨጌውን አጋዛቸው ጳጳሱ አቡነ ያዕቆብም ተቆጥተው ወደ አገራቸው ሄዱ ይላል ገድለ ፊሊጶስ፡፡

በገድለ ፊሊጶስና ከይኲኖ አምላክ እስከ ልብነ ድንግል በሚለው በኢትዮጵያ ታሪክ ተጽፎ እንደሚገኝ ዕጨጌውና ተከታዮቻቸው በተገረፉ ጊዜ ከእነርሱ የፈሰሰው ደም እሳት ሁኖ ከተማውን እንደአቃጠለው ይነግራል፡፡ከዚህም የተነሣ ሕብረተሰቡ በሙሉ ተባብሮ ንጉሡን ተቃውመው ጳጳሱን መልሶ እንዲያመጣቸው ዕጨጌውንም እንዲፈታ አስገደዱት እርሱም ጳጳሱን ፊትም በገንዘቤ ነው ገዝቼ ያመጣሁት አሁንም በገንዘቤ ገዝቼ አመጣዋለሁ ብሎ በመመጻደቅ ተገዶ ጳጳሱን አመጣቸው ዕጨጌውንም ፈታ፡፡

የማይገባና የሚገባ ውርስ

ወላጆች ለልጆቻቸው የሚገባውንም የማይገባውንም ያወርሳሉ፡፡

የማይገባ ውርስ ጥንቈላ፣ ሟርት፣ አምልኮ ባዕድ ስርቆት፣ ዝሙት፣ስካር ክፉ ሥራና ያልቀና ሃይማኖት ነው፡፡የሚገባ ውርስ ሀብት፣ ንብረት፣ ርስት ጒልት መልካም ሥነ ምግባር የቀና ሃይማኖት...ነው፡፡

በዚህ መሠረት ዓምደ ጽዮን ለልጁ ለሰይፈ አርዕድ የማይገባ ክፉ ሥነ ምግባር አውርሶት አልፎአል ይኸውም ከዚህ ቀጥለን እንደምናየው ዓምደ ጽዮን ተገድዶ ሁለቱን አባቶች ወደየቦታቸው ከመለሰ በኋላ ብዙ ሳይቈይ ወዲያው ስለአረፈ ልጁ ሰይፈ አርዕድ ነገሠ ይሁን እንጂ ሰይፈ አርዕድ ሥልጣን እስኪይዝ ድረስ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት እመራለሁ ቃላችሁንም አከብራለሁ በማለት ጳጳሱንና ዕጨጌውን አታልሎ ከነገሠ በኋላ ገድለ ፊልጶስ ጠንቋልያን ካህናተ ደብተራ የሚላቸው ሆድ አምላኩ የሆኑ ካህናት ድጋፍ እየሰጡት

ሀ/ እንደ አባቱ ሁለት ሚስቶችን አገባ
ለ/ እንደ አባቱ ወይም ከአባቱ በወረሰው ትውፊት በዘመነ ዮሐንስ በዓለ ልደት በሃያ ስምንት እንዲከበር አደረገ
ሐ/ አባቱ በሁለቱ አባቶች ያደርሰው የነበረውን ግፍ እርሱም አጠንክሮ ቀጠለበት፡፡ በመሆኑም ጳጳሱን ለሁለተኛ ጊዜ ወደ አገራቸው እንዲሄዱ ዕጨጌውን በደቡብ ጎንደር ስማዳ በሚባል ቦታ እንዲጋዙ አደረገ ንጉሡ በአንድ ቦታ እንዲጋዙ ቢያደርግም ዕጨጌው ግን በጣና ዙሪያ ሁሉ እየተዘዋወሩ ስብከተ ወንጌልን በስፋት ያከናውኑ እንደነበር ከላይ የተጠቀሰው የኢትዮጵያ ታሪክ በሚገባ ያስረዳል፡፡

ከዚህ ሁሉ ተጋድሎ በኋላ በፍጻሜ ዘመናቸው ስማዳ ውስጥ በምትገኘው በደብረ ዕንቊ ገዳም አርፈው ከብዙ ዘመናት በኋላ አፅማቸው ወደ ደብረ ሊባኖስ እንደፈለሰ ብዙ መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡

በዚህ መልኩ ግፈኞቹ ነገሥታት ክፉ አሻራቸውን ደጋጉ አባቶች ደግሞ ለሁሉ አርአያ የሚሆን በጎ ሥነ ምግባራቸውን ትተው አልፈዋል ነገሥታቱ ጥለውት ያለፉ ስሕተት ግን እስከ ዛሬ ቤተ ክርስቲያንን ክፉኛ እየጎዳት ይገኛል፡፡

ይኸውም ሥልጣናቸውን መከታ አድርገው በዘመነ ዮሐንስ በዓለ ልደት በሃያ ስምንት እንዲከበር በማድረጋቸው ነው፡፡ ለምሳሌ ከነገሥታቱ ባለሟል አንዱ በዘመነ ዮሐንስ ሊቃውንቱ በሃያ ስምንት አይደገፉም ነበረና በማርገጃው አርዶና አወራርዶ ሁሉም ተገድዶ በግብዣው እንዲቀመጥ ካደረገ በኋላ ጐራዴውን ታጥቆ እየተንጎራደደ እያንዳንድህ ትበላ እንደሆነ ብላ አለዚያ በሰይፌ አወራርድሃለሁ እያለ ሲያስፈራራቸው ከተገዳጆቹ አንዱ ስሙን ጠርተው ለኛ ብለህ በፀሐይ መንጠራራቱ ስትንጎራራድ ምች ያዳብንሃል አሉት ይባላል፡፡

ከዚህ ሌላ የደረሰባቸውን ችግር ሁሉ እየተቋቋሙ በአለማቸው የጸኑትን ጸጋ፣ ቅብዓት ናቸው እያሉ በሐሰት ስማቸውን በማጥፋት እንዲሸማቀቁና ሁሉ እንዲጠላቸው ለማድረግ የማይፈነቀሉት ድንጊያ የለም ነበር፡፡ እውነታው ሲመረመር ግን
1. ይህ የበዓል መዛባት የመጣ በዐሥራ አራተኛ ምእት የጸጋና የቅብዓት ሃይማኖት የመጣ ከብዙ ዘመን በኋላ በዐሥራ ስድስተኛው ምእት ዓመት ስለሆነ ፍጹም ግንኙነት የሌለው ነው፡፡

2. አክብሮ በዓል ሥርዓት እንጂ ሃይማኖት ስላልሆነ ጸጋና ቅብዓት ሊያስኝ አይችልም
3. የልደት በዓል ማዛባት ከሮም ነው የመጣው ጸጋና ቅብዓትም የተፈጠሩ ከዚያው ማለትም በሱስንዮስ ዘመነ መንግሥት ከሮም በመጣ ጳጳስ በአልፎንሱ ነው ስለዚህ የበዓል ሥርዓት ጸጋና ቀብዓት ያሰኛል፡፡ ከተባለም የሚቃረቡ የሮም ልጆች ነገሥታቱና የነገሥታቱ ደጋፊዎች ይጠሩበት እንጂ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ግን ከጉባኤ ኬልቄዶን በኋላ ቀረቤታ ስለሌላቸው ወላፈኑም አይነካቸውም ውንጀላውም ከንቱ ጒንጭ አልፋ ነው የሚሆነው፡፡

በአንባ ገነኖች ነገሥታት የተፈጠረው የሥርዓተ በዓል መዛባት ችግር በአሁኑ ሰዓት በምን ደረጃ ይገኛል ቢባል የበዓሉ ችግር እንዳለ ሁኖ በአሁኑ ጊዜ ችግሩ በጣም ጉልቶ የሚታየው በጾሙ መግቢያ ወቅት ነው ቅዱስ ሲኖዶስ መጽሐፍ በሚያዝዘው መሠረት በየዓመቱ ከኅዳር ዐሥራ አምስት ቀን ጀምሮ እንዲጾም መወሰኑ ይታወቃል ነገር ግን አብዛኛው አማኝ በሦስቱ ወንጌላውያን በተወሰነው በዐሥራ አምስት ቀን ሲጀምር በዘመነ ዮሐንስ ግን የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ሳይጠብቅ ከዐሥራ አራት ጀምሮ መጾም አለብን ሲል ሌላው ክፍል ምን ጊዜም የልደት ጾም ከኅዳር ዐሥራ አምስት ቀን አንሥቶ ነው መጾም ያለብን በማለቱ በየአራት ዓመቱ ከፍተኛ ረብሻ ይነሣል፡፡

ከዚህም የተነሣ ዘወትር በሕዝቡ መካከል እየተገኙ በየጊዜው የሚገጥማቸውን ጥያቄ ለመመለስና ጐራ ለይተው የሚፋለሙትን ወገኖች ለማስማማት ባለመቻላቸው የተቸገሩ ንስሐ አባቶችና ሰባክያነ ወንጌል በቅዱስ ሲኖዶስና በሊቃውንት ጉባኤ በኲል ለምን መፍትሔ አይደረግለትም በማለት ከፍተኛ ሮሮ እያሰሙ ይገኛሉ፡፡

አባባላቸው እውነታ ያለው ሙሉ በሙሉ የሚደገፍ ነው ቅዱስ ሲኖዶስ በሕዝቡ ያለውን ችግር መፈታት የሊቃውንት ጉባኤም የሲኖዶሱ ጠባቂ እንደመሆኑ መጠን ችግሮችን አጣርቶ ማቅረብ ይገባልና፡፡ "በጎንደር ዘመነ መንግሥት ዐቃቤ ሰዓት የሚባል የመንግሥት አካል የሆነ ባለሥልጣን ነበር የዚህ ባለሥልጣን ዋና ተግባር ንጉሡን መጠበቅ ነው፡፡ ንጉሡን የሚጠብቀው በእርሱ አደጋ እንዲደርስበት አይደለም ንጉሡ በሕዝቡ ላይ ችግር እንዳያደርስ መጠበቅ ነው እንጂ ይኸውም ስሕተት ከተፈጸመ በኋላ ፍርድ ተጓደለ ድሀ ተበደለ እያሉ ከማሳጣት ያለ ልክ በልቶና ወጥቶ ችግር እንዳያመጣ አስቀድሞ ለመከላከል በሚበላበትና በሚጠጣበት ሰዓት ዐቃቤ ሰዓቱ ድምጽ ያለውን ዘንግ ይዞ ከንጉሡ አጠገብ ይቆማል፡፡ ንጉሡ ከተወሰነለት በላይ ለመጨመር እጁን ሲሰድ ዐቃቤ ሰዓቱ ዘንጉን ገጭ በማድረግ ድምፅ ያሰማል ንጉሡም እጁን ይሰበስባል፡፡ በመጠጡም ጊዜ እንደዚሁ ነው፡፡

በፍርድ ጊዜም በመጀመሪያ አራት ወንበሮች የሚባሉ ሹሞች ነበሩ ፈርድ የሚሰጥበት ጉዳይ ሁሉ እነርሱ አጣርተው ለንጉሡና ለዐቃቤ ሰዓቱ በዋዜማው ያሰማሉ ንጉሡም በነጋታው ለፍርድ ይሠየማል ዐቃቤ ሰዓቱም ያችን ዘንግ ይዞ በተወሰነለት ቦታ ይቆማል የተዛባ ፍርድ ሲሰጥ ዘንጓን ገጭ ያደርጋታል፡፡ ንጉሡም በይደር እንዲታይ ይላል ማታ ከፍርድ መልስ እነዚያ አራቱ ወንበሮች ንጉሡና ዐቃቤ ሰዓቱ ስድስቱ አንድ ላይ ሁነው ጥፋቱ ከንጉሡም እንደሆነ ከዐቃቤ ሰዓቱም እንደሆነ ከወንበሮቹም እንደሆነ ሁሉም ፍትሐ ነገሥትን ጠንቅቀው የሚያውቁ ምሁራን ሊቃውንት ስለሆኑ ሊቃውንት ቢጣሉ መጻሕፍት ያስታርቋቸዋል መጻሕፍት ቢጣሉ ሊቃውንት ያስታርቋቸዋል እንደተባለ ፍትሐ ነገሥት የተባለውን መጽሐፍ በድጋሚ መርምረው በግልጽ ተወያይተውና ትክክለኛውን ፍርድ አጣርተው ያን ጊዜ ወረቀት ስለሌለ ለንጉሡ በቃል ይነግረዋል፡፡ እርሱም በልቡናው መዝግቦ አድሮ የሚገባውን ብይን ይሰጠዋል፡፡ ከዚህ ሊታለፍ የማይገባና በጉልህ ሊሠመርበት የሚገባ ትልቁ ቁምነገር የዚያን ጊዜ ባለሥልጣኖች በዚህ ሁኔታ በግልጽ እየተወያዩ ሕዝባቸውን በቅንነት ያገለግሉ ነበር ስለሆነም ይህንን ወርቃማ አሠራር በዘመናቸችን ያሉ ባለሥልጣኖች ባለመለያየት በግልጽነትና በመግባባት እየተወያዩ ለሚመሩት ሕዝብ የሚበጀውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

መለያየት የሚያመጣው ጒዳት

የአንዲት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርቲያን ልጆች በሁሉ ነገር አንድ ሲሆኑ በጾመ ልደትና በበዓለ ልደት ብቻ ለምን ይለያያሉ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔስ ለምን ይጥሳሉ ምክንያቱም አንዱ ክፍል በዘመነ ዮሐንስ በኅዳር ዐሥራ አምስት ቀን ጀምረው ሲጾሙ ሁለተኛው ክፍል ኅዳር ዐሥራ አራት ቀን ጀምረው ሲጾሙ ይታያሉ፡፡

በዓለ ልደቱንም በዘመነ ዮሐንስ እኩሉ በታኅሣሥ ሃያ ስምንት ሲያከብሩ እኩሉ በሃያ ዘጠኝ ቀን ሲያከብሩ ይታያሉ ይህ ለምን ሆነ ቢሉ፡፡በዘመነ ዮሐንስ ጾመ ልደትን በኅዳር ዐሥራ አራት ጀምረው በዓለ ልደቱን ታኅሣሥ ሃያ ስምንት ለማክበር ምክንያታቸው ጳጉሜን ስድስት ስለምትሆን ነው ይላሉ ይሁን እንጂ ከዚህ ቀጥለን በምናያቸው ማስረጃዎች ትክክል እንዳልሆኑ እንገነዘባለን፡

1. ጳጉሜን በዘመነ ዮሐንስ ስድስት ስለምትሆን ነው ይበሉ እንጂ ጳጉሜን ስድስት የምትሆን በዘመነ ሉቃስ ነው፡፡

2. አባባላቸው ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የተከተለ ቢሆን ኑሮ ግዝረቱ ጥምቀቱ ቃና ዘገሊላ ሁሉ ይሸጋሸጉ ነበር፡፡

3. ድሜጥሮስ ለበዓለትና ለአጽዋማት ሁሉ ኢየዐርግንና ኢይወርድን ሲሠራ ለዚህም ይሠራለት ነበር

4. ቅዱስ ያሬድም ለብዙ በዓላት ለእመ ኮነ ሲሠራ ለዚህም ይሠራለት ነበር

5. በቅዱሳት መጻሕፍት ፈጽሞ ድጋፍ የለውም ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ ከተጻፈ ስንክሣር በቀር ቅዱሳት መጻሕፍት በሙሉ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት ምንጊዜም ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ ቀን ብቻ እንደሚውል፤ ነው በአጽንዖት የሚናገሩት ከቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃዎች ጐላ ጐላ ያሉትን ከዚህ ቀጥለን እንመለከታለን፡፡

ሀ/ ሲኖዶስ ዘሐዋርያት ዘጸሐፈ ቀሌምንጦስ ትእዛዝ "ሰመንቱ ወይ ግበሩ በዓለ ልደቱ ለእግዚእነ አመ ዐሥራ ወተስዑ ለታኅሣሥ እስመ ውእቱ ርእሰ በዓላት" አማርኛ የሐዋርያት ሲኖዶስ ቀሌምንጦስ በጻፈው "በስምንተኛው ትእዛዝ የጌታችንን በዓለ ልደት ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ ቀን ያክብሩ እርሱ የበዓላት ራስ ነውና" ብለዋል፡፡

ለ/ ዲድስቅልያ አንቀጽ ዕሥራ ወተስዐቱ "ኦፍቁራኒሁ ለእግዚአብሔር ዕቀቡ እንከ ዕለተ በዓላት ቀዳሚ በዓል ዘውእቱ ዕለተ ልደቱ ለክርስቶስ አመ ዕሥራ ወኀሙሱ ለታስዕ ወርኅ" በኁልቈ ዕብራውያን ወበሐሳበ ግብጻውያን አመ ዕሥራ ወተሰዑ ለራብዕ ወርኅ አማርኛ፡- በዲድስቅልያ በሃያ ዘጠነኛው አንቀጽ "የእግዚአብሔር ወዳጆች ሆይ እንግዲህ የበዓላትን ቀን ጠብቁ ይኸውም በዕብራውያን አቈጣጠር በዘጠነኛው ወር በሃያ አምስተኛው ቀን በግብጻውን አቈጣጠር በአራተኛው ወር በሃያ ዘጠነኛው ቀን የሚውል የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕለተ ልደት የመጀመሪያው በዓል ነው" ይላል፡፡

ሐ/ ሠለስቱ ምእትም በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ዐሠርቱ ወተስዐቱ ኦአኀዊነ ተዐቀቡ በመዋዕለ በዓላት ዘውእቱ በዓለ ልደቱ ለእግዚእነ ወግበሩ አመ ዕሥራ ወኀሙሱ ለታስዕ ወርኅ በዕብራውያን ወበግብጻውያን አመ ዕሥራ ወተስዑ ለራብዕ ወርኅ አማርኛ በፍትሐ ነገሥት በዐሥራ ዘጠነኛው አንቀጽ "ወንድሞች ሆይ በበዓላት ቀን ተጠበቁ፣ ይኸውም በዕብራውያን አቈጣጠር በዘጠነኛው ወር በሃያ አምስተኛው ቀን በግብጻውያን አቈጣጠር በዘጠነኛው ወር በሃያ አምስተኛ ቀን የሚሆን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት አክብሩ" ብለዋል፡፡

መ. ዳግመኛ ሠለስቱ ምእት በዐሥራ ስምንተኛው አንቀጽ ታኀሣሥ ሃያ ስምንት ቀን ድራረ ጾም (ገሀድ አድርገው እስከ ሠርክ ጹሙ ብለዋል፡፡ ስለዚህ ጾሙን ሽሮ በተቃራኒው በዓል አድርጎ ሲበሉ ሲጠጡ መዋል ታላቅ ስሕተት ነው፡፡

ከዚህ በኋላ ይህን የሐዋርያትንና የሠለስቱ ምእትን ትእዛዝ መሠረት አደርገው ብዙ ሊቃውንት እነጊዮርጊስ ወልደ አሚድ እነ ሰዒድ ወልደ በጥሪቅ እነ አቡሻኸር ወዘተ ከዐሥር በላይ የሚሆኑ ሊቃውንት የጌታችን በዓለ ልደት ምን ጊዜም ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ ቀን ብቻ መከበር እንዳለበት በሚገባ ጽፈዋል፡፡ ቀሪውን ጥቅስ "በጾመ ልደት ከመለያየት ወደ አንድነት በሚለው ጽሑፌ መመልከት ይቻላል"፡፡

ነገር ግን ነገሥታት ይህን ሁሉ የመጽሐፍ ቃል ከግምት ሳያስገቡ ፍላጎታቸውን ብቻ በመከተል በዓለ ልደቱ እንዲዛባ ማድረጋቸውና ይልቁንም አድርባይ የሆኑ ካህናት እነ ርሱን መደገፋቸው የሚደንቅ ነው፡፡

በተለይ በአሁኑ ጊዜ ይህን በስሕተት የተፈጠረውን ሥርዓት ሲደግፉ መገኘት በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ ምነው ቢባል የቀደሙ ሰዎች ሥርዓቱን የሚከተሉበት በተለያየ ምክንያት ነው፡፡ አንዱ ክፍል በጥቅማ ጥቅም በአድር ባይነት ሁለተኛው ክፍል ወዮውልህ ስለሚባል በፍራቻ ነው፡፡ ሦስተኛ "ኅሡ ትርአዩ ውስተ መጻሕፍት እስመቦቶን ይመስለክሙ ዘትረክቡ ሕይወተ ዘለዓለም ወእማንቱ ሰማዕትየ"

አማርኛ "ትረዱ ዘንድ መጻሕፍትን መርምሩ በእነሱ የዘለዓለም ሕይወትን የምታገኙ ይመስላችኋልና እነርሱም የኔ ምስክሮች ናቸው ዮሐ. 5፡39" ባለው መሠረት ትክክለኛውን መንገድ ለመከተል መጻሕፍትን ባለማግኘታቸው ነው፡፡

የዛሬ ዘመን ሰዎች ግን ከሁሉ ነገር ነፃ ናቸው ደገፉም አልደገፉም የሚያገኙት ሆነ የሚያጡት ጥቅም የለም የፈለጉትን ቢከተሉም ወዮልህ የሚላቸው የለም መጻሕፍትም በየቋንቋው ተተርጉመው በየቦታው የሚገኙበት ወቅት ስለሆነ የመጽሐፍ ችግር የለባቸውም አንብበው አለመረዳታቸው ለምን ይሆን አሁንም እነርሱም እንዳይጐዱ ቤተ ክርስቲያናችንም በየአራት ዓመቱ ከሚገጥማት እሰጥ አገባ ነፃ እንድትሆን መጽሐፍቱን አንብበው አቋማቸውን እንዲያስተካክሉ ሰፊ ዕድል አላቸው፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍትም ማስረጃ ሊሆኑ የሚችሉት ከሁለት በላይ ተባብረው ሲገኙ ነው፡፡

1. "በሁለት ወይም በሦስት ምስክሮች ሞት የሚገባቸው ይገድሉ በአንድ ምስክር ግን አይገደሉም ዘዳ. 17፡6

2. ስለበደል ሁሉ ክፉ በማድረግም ስለሚሠራት ኃጢአት ሁሉ በማንም ላይ አንድ ምስክር አይሁን በሁለት ምስክሮች ወይም በሦስት ምስክሮች ቃል ነገር ሁሉ ይጸናል ዘዳ. 19፡15

3. "ባይሰማህ ግን በሁለተኛ ጊዜ ከአንተ ጋር አንድ ወይም ሁለት ምስክር ያዝ ነገር ሁሉ በሁለት ወይም በሦስት ቃል ይጸናል" ማቴ. 18፡16

4. እኔ ብፈርድ እውነት እፈርዳለሁ እኔና የላከኝ አብ ነን እንጂ አንድ ብቻዬ አይደለሁምና የሁለት ሰዎች ምስክርነት የታመነ እንደሆነ በሕጋችሁ ተጽፎአልና እኔ ስለራሴ ምስክር ነኝ የላከኝ አብም ይመሰክርኛል" ዮሐ. 8፡16 -18

5. ሁለት ወይም ሦስት ምስክሮች ባይመሰክሩበት በሽማግሌው ላይ ነገር አትሰማ" 1ኛ ጢሞ. 5፡10 ከዚህ በላይ የቀረቡ ጥቅሶች በሙሉ ተቀባይነት የሚኖረው ከሁለት በላይ የሆነ ምስክርነት ነው እንጂ አንድ ምስክር ሊያድንም ሊገድልም እንደማይችል ወይም ዋጋ እንደሌለው በማያሻማ ሁኔታ ያስረዳሉ፡፡

በዚህ አንጻር የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት ምንጊዜም የማይናወፅ ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ ቀን ነው፡፡ የሚለው ክፍል ቀደም ሲል እንደተገለጸው ከዐሥር በላይ የሚሆኑ ማስረጃዎችንና ምክንያቶችን ያቀርባል በዘመነ ዮሐንስ ታኅሣሥ በሃያ ስምንት ቀን መከበር አለበት የሚለው ክፍል ግን ማስረጃው አንድ መጽሐፈ ስንክሣር ብቻ ነው ያውም አባ ዘገየ የተባሉ ሊቅ በጥናት የደረሱበትን በመጽሐፈ መድብላቸው እንዲህ የሚል ጽፈዋል፡፡ ከግራኝ ወዲህ የተጻፈ ስንክሣር ነው እንጂ ከዚያ በፊት የነበረ ስንክሣር ታኅሣሥ በሃያ ስምንት ቀን አክብሩ አይልም ከማለታቸውም በላይ ይህንን አባባላቸውንም እውን የሚያደርጉላቸው የሦስት አብያተ ክርስቲያን ማለት የጐንደር ደብረ ብርሃን ሥላሴን የመሐል ዘጌ ጊዮርጊስን ስንክሳሮችን ጠቅሰዋል ይህም ዓምደ ጽዮን ይህንን ችግር ከመጣ በኋላ በእንቅርት ላይ እንዲሉ ግራኝ ተነሥቶ አብያተ ክርስቲያናትን ስላቃጠለና መጻሕፍትን ስለአጠፋ ከዚያ በኋላ በነገሥታቱ ተፅዕኖ የተጻፈ ነው እንጂ ታኅሣሥ ሃያ ስምንት ቀን በዓለ ልደት የሚባለው እውነታና መሠረት የሌለው ከንቱ ፈጠራ እንደሆነ እገነዘባለን፡፡

ማጠቃለያ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ የተወለደው ልደቱ ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ ቀን አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ይህንንም አባቶችን ሐዋርያት
ሀ/ በሲኖዶሱ ትእዛዝ ስምንት
ለ/ በዲድስቅልያ አንቀጽ ሃያ ዘጠኝ
ሐ/ አባቶቻችን ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ሊቃውንትም በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ዐሥራ ዘጠኝ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ ቀን ብቻ እንድናከብር ግልጽ በሆነ ቃል ደጋግመው አዝዘውናል፡፡
እንደዚሁም ግብፃዊው ጳጳስ አቡነ ያዕቆብ የደብረ ሊባኖስ ሦስተኛ ዕጨጌ አቡነ ፊሊጶስና ያንጊዜ የነበሩ አበው ገዳማውያን በመታሰር በመገረፍ በመሰደድና እስከሕይወት መሥዋዕትነት ድረስ በመክፈል በዓለ ልደቱ ከሃያ ዘጠኝ እንዳይወጣ ከፍተኛ ተጋድሎ ፈጽመዋል፡፡ስለሆነም የሐዋርያትን የሠለስቱ ምእትን ትእዛዝ ማክበር ከጳጳሱ ጀምሮ የአበው መነኰሳትን ፈለግ መከተል ግድ ይላል፡፡

ከዚያም በኋላ ብዙ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በዘመነ ዮሐንስ ልደት በሃያ ስምንት ቀን በሚከበርበት ጊዜ ሃያ ስምንትን ቀን በጾም እያሳለፉ ሃያ ዘጠኝን ቀን በማክበር በግልጽም በድብቅም ተቃውሞአቸውን ከመግለጻቸው ባሻገር በዓለ ልደት ከታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ ቀን የማይፋለስ መሆኑን በየድርሳኖቻቸው እየዘገቡ አልፈዋል፡፡

ከብዙዎቹም አንዱ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የዝዋይ ካህናት ማሰልጠኛ ሓላፊ የነበሩት ስመ ጥር ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ "ልደት የሚከበረው ታሣሥ ሃያ ዘጠኝ ቀን ነው በዘመነ ዮሐንስ ጳጉሜን ስድሰት ስትሆን ግን ታኅሣሥ ሃያ ስምንት ቀን ይሆናል ይህም የተጀመረው በዐፄ ዓምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት ነው ሁለት ቀን ልደት ማለት ግን ጥሩ አይደለም ከዚያስ ሃያ ዘጠኝን መያዙ ይሻላል በዚህ የቀን ስሌትም ብዙ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ሲጣሉበት ኑረዋል ለወደፊቱም ይህን ለማስተካከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቅዱስ ሲኖዶስ መሉ መብት አለው" ብለዋል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሰኔ 1991

ታዲያ በአሁኑ ጊዜ ችግሩ ከምን ጊዜውም እጅግ በከፋ መልኩ ሰፍቶና ጐልቶ ይታያል፡፡ ምክንያቱም ቀደሞ ሰጥ አገባው በካህናቱና በምሁራኑ ዙሪያ የተወሰነ ነበር ምእመኑ "የዋህ ሰው ነገርን ሁሉ ያምናል" ምሳ. 1315 እንዳለው ጠቢቡ ሰሎሞን የነገሩት ሁሉ በየዋህነት ተቀብሎ ይሄዳል እንጂ ተመልሶ አይከራከርም ነበር፡፡

የዘመናችን ምእመን ግን ሁሉ አንባቢና ተመራማሪ በመሆኑና ከካህኑ በላይ አልፎ ስለሄደ ለጠየቀው ጥያቄ መልስ ቢሰጠው እንኳ ለምን ሆነ በምን ምክንያት ወዘተ እያለ በጥያቄ ላይ ጥያቄ እያስከተለ ግራ ያጋባል ከዚህ ሌላ መልስ የማይገኝላቸው ጥያቄዎች በዚህ ዙሪያ ይነሣሉ ለምሳሌ


1. ጾመ ልደት ሁልግዜ ከኅዳር ዐሥራ አምስት ቀን ጀምሮ ሲጾም ጾሙ በሦስቱ ወንጌላውያን አርባ አራት ቀን በዘመነ ዮሐንስ አርባ ሦስት ቀን ይሆናል፡፡ለምን ቢባል መልስ የለም
2. አካላዊ ቃል የኛን ባሕርይ ነሣ ፍጹም ሰው ሆነ እያልን ከሰው ባሕርይ በተለየ ሁኔታ ሁለት ጊዜ ተወለደ ሲባል ከሰው የተለየ ነው የኛን ባሕርይ አልነሣም አያሰኝም ወይ ለሚለው ጥያቄ መልስ የለውም በመሆኑም ተጠያቂው ያፍራል ይሸማቀቃል ጠያቂውም ተስፋይቈርጣል የሚይዘው የሚጨብጠውን ያጣል በሁለቱም ከፍተኛ ጉዳት ይደርሳል፡፡

ለአብነት በዚህ ምክንያት ችግር ከደረሰባቸው መካከል አምርረው የነገሩኝ የአንዱን አባት ገጠመኝን እንመልከት ይህ አባት በቤተ ክርስቲያን ሞያ የአንዱ ክፍል መምህር ናቸው እሳቸው እንደረገሩኝ ከዕለታት በአንዳቸው በባስ ሲጓዙ ወቅቱ በዘመነ ዮሐንስ የጾመ ልደት መግቢያ ነበረና ከተሳፊሪዎች ውስጥ ሁለት ሰዎች ስለጾመ ልደት መግቢያ አንሥተው ሲነጋገሩ አንዱ ዘንድሮ በሃያ ስምንት ስለሚገደፍ ጾመ ልደት የሚገባ በዓሥራ አራት ቀን ነው ይላል ሁለተኛ የለም በዐሥራ አምስት ነው ይላል በዚህ ጊዜ ይህ ጥያቄ ወደኔ ላመጣው ብዬ ፈራሁ እንደፈራሁም አልቀረም ጠየቁኝ ነገር ግን ፊቴን አዙሬ ዝም አልሁ ደግመው ቢጠይቁኝም አሁንም ዝም አልሁ በመጨረሻ አጥብቀው ያዙኝ ጠይቄ እነግራችኃላሁ ብዬ ተሸማቅቄ ወጣሁ ችግሩ በዚህ አላበቃም በዐሥራ አራት ቀን ባለቤቴ ለቅበላ ከልኳንዳ ሥጋ ገዝታ ስትመጣ ስለታየች ቄሱ ከነቤተሰባቸው ጾም ሻሩ እየተባልን መነጋገሪያ ከመሆናችንም ባሻገር በአካባቢው ኅብረተሰብ እንደርኩሳን ተቈጠርን ተገለልን ከዚህም የተነሣ ባለቤቴ ምነው የዚያች ቀን ሥጋ በቀረችብን እያለች ታዝናለች ሲሉ በምህረት አጫውተውኛል፡፡

ስለዚህ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ እንዳሉት መፍትሔው ያለው በቅዱስ ሲኖስ እጅ ነውና የቅዱስ ሲኖዶስ መልካም ፈቃድ ሁኖ በዚህ መጽሐፍ እንደተገለጸው ቅዱሳን ሐዋርያት አበው ሠለስቱ ምእት በአዘዙት መሠረት በዓለ ልደት እንደጥንቱ ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ ቀን ብቻ እንዲከበር ቢያደርግ፡፡

የቤተ ክርስቲያን ልጆች በሙሉ ጾሙን ኅዳር ዐሥራ አምስት ቀን እየጀመሩ በዓለ ልደቱን ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ ቀን በማክበር ያለ ጭቅጭቅና ያለመሸማቀቅ በሰላም ለመኖር ይችላሉና በሥራ ይተረጐም ዘንድ እየተመኘሁ ለመነሻ እንድትሆን በጠባብዋ ዕውቀቴ ይህችን አነስተኛ ጽሑፍ ሳቀርብ በታላቅ ትሕትና ነው፡፡


ለሁሉም "ያለኔ ፈቃድ ምንም ማድረግ አትችሉም ብሎአልና" የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርሰቶስ መልካም ፈቃድ ይሁንልን፡፡ አሜን 


ሊቀ ማእምራን ብርሃነ መስቀል አጠና
መላውን ጽሑፍ ፎቶ ኮፒ እያነሣ ለሚወስድ ሁሉ ይፈቃዳል

የፎንት ልክ መቀየሪያ