Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

"ፍልሰታ ለማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ"

በመምህር ሙሴ ኃይሉ

ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ "ወአመ በፅሐ ዕድሜሁ እግዚአብሔር ፈነወ ወልዶ ወተወልደ እምብእሲት፡- ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ" /ገላ. 4፡4/ በማለት እንደገለጸልን ፍጠረኝ ሳይለው ከብዝሐ ፍቅሩ የተነሳ የፈጠረው የሰው ልጅ በፈጸመው ስሕተት ወይ በደል ተጸጽቶ፣ በዕንባና በለቅሶ ተሞልቶ፣ ማቅ ለብሶና አመድ ነስንሶ በንስሐ ሕይወት ተሞልቶ ፈጣሪውን ማረኝ ብሎ በመለመኑ ምክንያት ምሕረት የባሕርይ ገንዘቡ የሆነ ርህሩህ አምላክ እጅግ አብዝቶ ራራለት፣ አዘነለት፣ ጸሎቱም ሰማና "ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ" ብሎ የምስጢረ ድኅነት የተስፋ ቃል ኪዳን ሰጠው፡፡

የሰው ልጆችም ይህንኑ አምላካዊ የድኅነት /የማዳን ቃል ኪዳን/ ተስፋ በማድረግ ምንም ጽድቅ ቢሠሩና ጻድቃን ቢባሉም ቅሉ ከሞተ ሥጋ ከሞተ ነፍስ፣ ከመርገመ ሥጋ ከመርገመ ነፍስ መዳን ስላልቻሉ ወደ ፈጣሪያቸው አብዝተው ይማጸኑ፣ ይለምኑና ይጮኹ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል፡፡

 • "ሁላችንም እንደ ድቦች እንጮኻለን፤ እንደ ርግብ እንለቃቀሳለን ፍርድን በተስፋ እንጠባበቅ ነበር፤ እርሱም የለም፤ መዳንም ከእኛ ዘንድ ርቆአል" ኢሳ.59፡11

 • "ሁላችንም እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፤ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤ ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፤ በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል ስምህም የሚጠራ አንተንም ሊይዝ የሚያስብ የለም፣ ፊትህንም ከእኛ ሰውረሃል፤ በኃጢአታችንም አጥፍተኸናል" ኢሳ.64፡6-7

 • "ሰማዮችን ቀድደህ ምነው ብትወርድ፤ ተራሮችም ምነው ቢናወጡ፤ እሳት ጭራሮውን እንደሚያቃጥል እሳትም ውኃውን እንደሚያፈላ ስምህ ለጠላቶችህ ይገለጽ ዘንድ" ኢሳ.64፡1-2

 • "ፈኑ እዴከ እም አርያም፡- እጅህን ከአርያም ላክ" መዝ.144፡7 እንዲል

ዓለምን ፈጥሮ የሚያስተዳድር እግዚአብሔር በንጹሕ ልብ ሆነው የለመኑትን የማይነሳ፣ አስቀድሞ የገባውን ቃል ኪዳን ፈጽሞ የማይረሳ አምላክ ስለሆነ ወደ ሕዝቡ ልመናና ጸሎት ተመለከተ፡፡ በዚህም በገባው ቃል ኪዳን መሠረት "ተስፋ አዳም" ከሆነችው ከዳግሚት ሔዋን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ዘመን የማይቆጠርለት አምላክ ሲሆን ዘመን የሚቆጠርለት ሰውም ሆኖ በተዋሕዶ ምስጢር ከብሮ መወለድ ግድ ሆነ፡፡ "ለይኩን" ብሎ ለፈጠራት አምላክ "ይኩነኒ" በሚል ቃለ ተአዝዞ ወቃለ አሚን ፈጣሪዋ ሰው ሆኖ እንዲወለድ ምክንያት የሆነች ድንግል በመሆንዋ ምስጢረ ተዋሕዶ የተፈጸመባት፣ የተከወነባት አማናዊት መቅደስ ቅድስተ ቅዱሳን፣ ንጽሕተ ንጹሐን ስለሆነች ተቀዳሚ ተከታይ የሌላት የአምላክ እናት ለመሆን በቃች፡፡

ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ለአዳም የተሰጡች እውነተኛ ተስፋ መሆንዋን የቅዳሴዋ ጣዕም የበዛለት ቅዱስ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም አንቀጹ "አንቲ ውእቱ ተስፋሁ ለአዳም አመ ይሰደድ እምገነት፡- አዳም ከገነት በተሰደደ ጊዜ ተስፋው አንቺ ነበርሽ" (ቅዳሴ፡ ዘእግዝእትነ ማርያም) በማለት አመስጥሮታል፡፡

በተጨማሪም፡- "ተፈጸመ ተስፋ አበው በማርያም ድንግል

ወበቀራንዮ ተተክለ መድኃኒት መስቀል፤ /መልክዓ ሥላሴ፡ ለኩልያቲክሙ/

የአባቶች ተስፋ በማርያም ድንግል ተፈጸመ፤ በቀራንዮም መድኃኒት መስቀል ተተከለ በማለት ተስፋ አበው የተፈጸመባት አማናዊት የሰው ልጆች ተስፋ መሆንዋን በዚህ መልኩ ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት ያራቅቃሉ፡፡

ይህች አማናዊት የሰው ልጆች ተስፋ ድንግል ማርያም እንዲሁ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደውሃ ፈሳሽ ሆና በድንገት የተገኘች ሳትሆን ከዘመነ አበው ጀምራ በተለያዩ ሕብረ አምሳልና ሕብረ ትንቢት እየተገለጸችና እየተነገረች የመጣች ስለመሆንዋ መጽሐፍ ቅዱስ መሠረት በማድረግ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በሰፊው ያትታሉ፣ ይተነትናሉ፡፡ ከዘመነ አበው /ከሕገ ልቡና/ እስከ ዘመነ ሐዲስ /ዘመነ ወንጌል/ ድረስ ያለውን የወላዲተ አምላክ ምሳሌያዊ ትምህርት በሌላ ጊዜ ዘርዘር በማድረግ የምንማረው ይሆናል፡፡

የወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ሕይወት ታሪክ ከነበራት ሱታፌ ድኅነት አኳያ በማነጻጸር ራሱ የቻለ ሰፊ ምስጢራዊ አስተምህሮ ያካተተ የሥነ መለኮት ትምህርት አንዱ ክፍል ነው፡፡ እዚህ ጽሑፋችን ላይ ግን ለመግቢያ ያህል በአጭሩ ድንግል ማርያም በቅዱስ ጋብቻ ጸንተው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው፣ በምግባር በትሩፋት ተጠምደው፣ እግዚአብሔርን አምነውና በእርሱም ታምነው ይኖሩ ከነበሩት ቅዱሳን ቤተሰብ "ሐና እና ኢያቄም" የተገኘች ፍጽምተ ሥጋ ወነፍስ ናት፡፡ አባትና እናትዋ መካናት ስለነበሩ በማሕበረሰቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ዘንድ እንደተረገሙ ይቆጠሩ ስለነበሩ ፍጻሜው ለወንጌላውያን ሁላችንም ቢሆንም ለጊዜው ግን ለወላጆቿ ጸጋና ሃብት በመሆን የተሰጠች የደስታችን ምንጭ ናት፡፡ በመሆኑም ነሐሴ ሰባት ቀን ከእነዚህ ደጋግ ቤተሰብ አብራክ ልትገኝ ተጸነሰች፡፡ በየዓመቱ ነሐሴ ሰባት ቀን ፅንሰታ ለማርያም ተብሎ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በታላቅ መንፈሳዊ አገልግሎት ይከበራል፡፡

ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ሰዎች በማኅፀን ሊቆዩ በእግዚአብሔር የተፈቀደላቸውን ዘመን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ከጨረሰች በኋላ ግንቦት አንድ ቀን ተወለደች፡፡ የብፅዓን ወይም የስእለት ልጅ ስለነበረች በሦስት ዓመቷ ታሕሳስ ሦስት ቀን ወደ ቤተመቅደስ ገባች፡፡ ይህ ቀንም "በዓታ ለማርያም" በማለት በቤተክርስቲያናችን በታላቅ መንፈሳዊ አገልግሎት ይከበራል፡፡ ከዓበይት በዓላተ ድንግል ውስጥ አንዱ ነውና፡፡ አስራ ሁለት ዓመታት ያህል ከቤተመቅደስ ውስጥ ከኖረች በኋላ ጠቅላላ ዕድሜዋ አስራ አምስት ዓመት ሲሞላት ወደ ቤተ ዮሴፍ ተዛወረች፡፡

ዘመነ ምሕረት ማለትም እግዚአብሔር ይቅርታ የሚያደርግበትን ዘመን ስለ ደረሰ ብርሃናዌ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ልኮ በቃለ ውዳሴ በቃለ ስባሔ ለተዋሕዶ ምስጢር ማደሪያ እንደምትሆን ተነገራት፡፡

በመሆኑም ሰማይና ምድር እንዲሁም ሱራፌልና ኪሩቤል ሊሸከሙት የማይቻላቸው ረቂቅ መለኮት በማኅፀኗ በማሳደር ወልዳ አሳደገች፡፡ በቤተልሔም ተወልዶ በቀራንዮ ጎልጎታ እስከሞተ ድረስ ጌታችን በተገኘበት ሁሉ እየተገኘች በተከፈለው የቤዛነት ምስጢር የፈጸመችው ሱታፌም ከፍተኛ ስለሆነ ሊቃውንት አባቶቻችን እንዳስተማሩን ሰማይ ወረቀት ሆኖ የክረምት ዝናብ ደግሞ ቀለም ቢሆን ተጽፎ አያልቅም፡፡

በመሆኑም ከቤተልሔም እስከ ቀራንዮ ጎልጎታ ድረስ ወላዲተ አምላክ የሌለችበት ምስጢር ፈጽሞ አይገኝም፡፡ የወላዲተ አምላክ ሕይወት ታሪክና በነገረ ድኅነት የነበራት ሱታፌ በተመለከተም ራሱ የቻለ ሰፊ የትምህርት ዘርፍ በመሆኑ ለጊዜው ይቆየንና ወደ ፍልሰታ ለማርያም እንመለስ፡፡

ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አንድ ልጇ በሐሰት አወንጅለው በሐሰት መስክረው፣ እውነተኛ ፍርድ አጓድለው ጸሐፍት ፈሪሳውያን ከሮማውያን ወታደሮች ጋር በመሆን ሰቅለው ከገደሉት በኋላ "በጊዜ ስቅለቱ ወሞቱ" በስቅለቱና በሞቱ ጊዜ ከእግረ መስቀሉ ዘንድ ተገኝታ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለውን መከራ ሁሉንም በአይኗ ስለ አየች ይህንኑ የልጇ ሥነ ስቅለት በልቧ ፈጽሞ ስለተሳለ ልጇ ተሰቅሎ ከተቀበረበትና ሙስና መቃብር አጥፍቶ ከተነሳበት ቅዱስ ስፍራ በመገኘት መላ ዘመንዋን ስለ ኃጥአን እየጸለየች ትኖር ነበር፡፡

የባሕርይ አምላክ ከሆነ ልጇ ኃጥአን ሊያስምር የሚችል የምሕረት ቃል ኪዳን ከተቀበለች በኋላ በ64 ዓመትዋ ከዚህ ዓለም በሞት ምክንያት ወደ ሚበልጠው፣ ወደ ተሸለው ዓለም አንድትሸጋገር እግዚአብሔር ፈቀደ፡፡

ኢትዮጵያዊ ሊቅ ቅዱስ ያሬድም "ፍርድ፣ ፍትሕ ሳያጓድል መስጠት የባሕርዩ የሆነ ክርስቶስ ለሥጋ እናቱ እንኳ ሳያዳላ ሞት ሲፈርድ ተመልከቱ" በማለት የወላዲተ አምላክ ሞት በጣም አስደናቂ መሆኑን በምስጋናዊ ዜማ አመስጥሮልን ይገኛል፡፡ በመሆኑም ድንግል ማርያም የዚህ ዓለም መንፈሳዊ ተልዕኮዋን በሚገባ አጠናቅቃ በ64 ዓመቷ ጥር 21 ቀን አረፈች፡፡

"ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ

ሞታ ለድንግል የዓፅብ ለኩሉ"..... እንዲል፡፡

እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መካሪ ሆነው በጾም በጸሎት እየተጉ የተሰጣቸውን ወንጌል የመስበክ አገልግሎት ለመፈፀም ይፋጠኑ የነበሩ አባቶቻችን ሐዋርያትም ማረፍዋን ካረጋገጡ በኋላ በጌቴሰማኒ መካነ መቃብር አዘጋጅተው ሊቀብሯት በመዘጋጀት ላይ እንዳሉ አይሁድ በበኩላቸው በክፋት መመካከር ጀመሩ፡፡ ምቀኝነትና ተንኮል አንድ ጊዜ ፈፅመው ገንዘብ ያደረጉ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ተሰባስበው "ከዚህ ቀደም ሕዝባችንና ሀገራችን ያወከ ልጇ ሰቅለን በገደልነው ጊዜ፤ ሰቅለው ቢገድሉትም በሦስተኛ ቀኑ ከሞት ተነስቷል፤ በዓርባኛው ቀንም ወደ ሰማይ አርገዋል... እያሉ ስማችንን በማጥፋት ሥራችንም በማጋለጥ ላይ ናቸው፡፡ ባይበዙም የተወሰኑትም ቢሆኑ እያሳመኑ ወደ እነርሱ ሃይማኖት እያስገቡ ይገኛሉ፡፡ አሁንም ደግሞ እናቱ ስለሆነች ሞተች፣ ተነሣች፣ ዐረገች... እያሉ ሕዝባችንና ሀገራችን ከማወካቸው በፊት እነርሱን ፈጽመን ምክንያት ለማሳጣት ከጉያቸው ነጥቀን፣ በእሳት አቃጥለን እናጥፋት" በማለት በሙሉ ተስማሙ፡፡

ይህንን ሰይጣናዊ ተልዕኮ ከግብ ለማድረስ ይቻል ዘንድም ከእነርሱ ሆዱ የሞላ፣ ደረቱ የቀላ ሰው "ታውፋንያ"ን መረጡ፡፡ ታውፋንያ በጉልበቱ ይመካ የነበረ ሰው ስለነበረ ጉልበተኛ እንደሆንክ እናምናለንና ይህንን ፍላጎታችንን አሟላልን ብለው ሲጠይቁት በደስታ ተቀበለ፡፡ ታውፋንያ ይህንን ተልዕኮ ለመፈጸም የሚያስችለውን ሰይፍ አንስቶ አይሁዳውያንን መርቶ አባቶቻችን ሐዋርያት ለመቅበር ተሸክመዋት በመሄድ ላይ ሳሉ ከመንገድ አቆሙአቸው፡፡ ከዚህ በኋላ በጉልበቱ የሚመካ ታውፋንያ የእመቤታችንን አስከሬን ከአጐበሩ ወደ መሬት ጥሎ ለማቃጠል ሁለቱ እጆቹ ዘርግቶ ገና የአልጋ መያዣውን ሲነካ መልአከ ሰማይ ድንገት ተገልጾ በሰይፈ ነበልባል እጁን ቀጣው (ቆረጠው)፡፡ በኃይሉ ይመካ የነበረው ታውፋንያ በጉልበቱ ወድቆ ተንበርክኮ፣ በግንባሩ ተደፍቶ ማልቀስና ማዘን ጀመረ፡፡ በመሆኑም እመቤቴ ማሪኝ ብሎ ስለ ጸለየ በአማላጅነቷ መልአኩ መልሶ በሰይፉ ቢነካው እንደነበረ በመሆን ድኗል፡፡ በምቀኝነት ተነሳስተው የመጡ አይሁዳውያን ይህንን ሰማያዊ ድንቅ ተአምር ባዩ ጊዜ ደንግጠው ወደ ኋላ በመሸሽ ተመለሱ፡፡

መድኃኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስም ወዲያው መጥቶ ከዮሐንስ ፍቁሩ ጋር በደመና ነጥቆ ወሰዳቸውና በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር አኖራት፡፡ ፍቁረ እግዚእ ቅዱስ ዮሐንስም ሲመለስ ወንድሞቹ ቅዱሳን ሐዋርያት የድንቅ ነገሩ ምስጢር አጥብቀው ጠየቁትና ያየውንና የሰማውን ሁሉ ነገራቸው፡፡ አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያትም ዮሐንስ ያየውን ምስጢር እኛ ሳናየው፣ የተቀበለውን በረከት እኛ ሳናገኝ ቀርተናል፡፡ ስለሆነም ሱባኤ ገብተን ፈጣሪያችንን እንለምን በማለት ከአየኅጉረ ስብከታቸው መጥተው በመሰባሰብ ሱባኤ ጀመሩ፡፡ አንድ ሱባኤ ሰባት ቀን ነው፡፡ ሁለት ሱባኤ እንደጨረሱ ጌታ ከዕፀ ሕይወት ሥር አምጥቶ ስጣቸውና በ14ኛ የሱባኤ ቀናቸው ደስ ብሏቸው በጌቴሰማኒ ቀበሯት፡፡ በሦስተኛ ቀን /በ16ኛው ቀን/ የልጇ ትንሣኤ በሚመስል ትንሣኤ በልጇ አስነሽነት በቅዱሳን መላእክት ሰማያዊ ምስጋና ታጅባ ወደ ሰማይ ዐረገች፡፡ ቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያት ግን ይህንን ምስጢር አላዩም ነበረ፡፡

ሱባኤው ከተፈጸመ በሦስተኛው ቀን ነሐሴ 16 ቀን በመላእክት ምስጋና በታላቅ መንፈሳዊ ክብር ወደ ሰማይ ስታርግ ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ለሆነ ለቶማስ በመንገድ ላይ ተገለጸችለት፡፡ ቶማስ በሱባኤ ጊዜ በሀገረ ስብከቱ በማስተማር ላይ ከቆየ በኋላ ደመና ነጥቆ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለስ በእንዲህ ዓይነት ግርማ መላእክት ድንግል ማርያምን ተነሥታ እያረገች ሲያይ እጅግ አድርጎ አዘነ፡፡ "ቀድሞ ከጌታዬ ትንሣኤ ከወንድሞቼ ተለይቼ ሳላይ ቀረሁ አሁንም የእመቤቴ ዕርገት ሳላይ እንዲሁ ሆኜ ቀረሁ" ብሎ የወላዲተ አምላክ በረከት በመመኘት አዘነ፡፡

ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያምም ለቶማስ "አይዞህ አትዘን ወንድሞችህ ሐዋርያት አንተ ያያኸውን ትንሣኤዬንና ዕርገቴን ፈጽመው አላዩም፡፡ ስለዚህ አሁን አንተ ሂድና ማርያም ከሙታን ተነስታለች ወደ ሰማይም ዐርጋለች ብለህ ንገራቸው" በማለት ምልክት ይሆነው ዘንድ የገነዙበትን ሰበን /መጎናፀፊያ/ ሰጥታው ሄደች፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስም ወላዲተ አምላክ እንደ አዘዘችው ወደ ሐዋርያት ሄዶ "የእመቤታችን ነገር እንዴት ሆነ" በማለት ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም ሱባኤ ገብተን ፈጣሪያችን ለምነን ስናበቃ ጌታችን አምጥቶልን በጌቴሰማኒ ቀበርናት ብለው ሁሉንም ነገር አስረዱት፡፡ ቶማስ መልሶ "ድንግል ማርያም የሞተችው በጥር የተቀበረችው ደግሞ በነሐሴ (ሞት በጥር ነሐሴ መቃብር) እንዴት ይሆናል?" ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም መቃብሯን ለማሳየት ወደ መቃብሯ ወስዶ ሲቆፍር መቃብር ባዶ ሆኖ አገኘው፡፡ በዚህም አባቶቻችን ሐዋርያት እጅግ አብዝተው ሲጨነቁ ባየ ጊዜ በመካከላቸው ቆሞ እንዲህ አለ፡- "ወንድሞቼ እኔ አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ ድንግል ማርያም ከመቃብር ተነሥታ በቅዱሳን መላእክት ምስጋና እየተመሰገነች ወደ ሰማይ ዓርጋለች፡፡ ለዚህም ምልክት ወይም ምስክር ይሆነኝ ዘንድ ይህንን ሰጥታኛለች" ብሎ የሰጠችውን ሰበን ለሁሉም ሰጣቸው፡፡ እነርሱም ሰበኑን ወስደው በመካፈል ለበረከት ይሆናቸው ዘንድ መስቀላቸው ላይ አስረውታል፡፡ አሁን አባቶቻችን ካህናት በመስቀላቸው ላይ የሚያንጠለጥሉት ከዚህ ታሪካዊ ትውፊት በመነሳት ነው፡፡

ይህ በተፈጸመ በዓመቱ አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት ከመካከላችን ቶማስ ትንሣኤዋንና ዕርገትዋን አይቶ ከበረከተ ትንሣኤውንና ዕርገትዋ ተሳታፊ ሲሆን እኛ ቀረብን በማለት አሁንም እንደገና በዓመቱ ነሐሴ አንድ ቀን ጀምረው ሁለት ሱባኤ ከፈጸሙ በኋላ በሦስተኛው ቀን ነሐሴ 16 ቀን ለሁሉንም ትንሣኤዋንና ዕርገትዋን ተገለጸላቸው፡፡ በዚህም ምክንያት "የተመሰገነ የሆነ ምስጉን አምላክ እናመሰግነዋለን" ብለው እጅግ አብዝተው ፈጣሪያቸውን አመሰገኑ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊትና ታሪካዊት እንደመሆንዋ መጠን ይህን ሐዋርያዊ ትውፊት በአግባቡ ጠብቃ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓቱንም ጠንቅቃ በየዓመቱ ፍልሰታ ለማርያም ምክንያት በማድረግ ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምሮ እስከ ነሐሴ 16 ቀን ህፃን ሽማግሌ በአንድነት በጾም በጸሎት፣ በቅዳሴ፣ በማኅሌት፣ በሰዓታት፣ በታላቅ መንፈሳዊ አገልግሎት ድምቀት ይከበራል፡፡

በመሆኑም ቅዱስ ያሬድ "ፈለሰት እምዘይበሊ ኅበ ኢይበሊ፡- ከሚያልፈው ዓለም ወደ ማያልፈው ዓለም ተሻገረች፣ ሄደች፣ ዐረገች" በማለት እንደተረጎመልን ጾሙ "ጾመ ፍልሰታ" በዓሉ "በዓለ ፍልሰታ" በማለት ጥንታዊት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የእመቤታችን በዓለ ትንሣኤ፣ በዓለ ዕርገት በየዓመቱ ታስታውሳለች፣ ታስተምራለች፣ ለምዕመናኗም ከበረከቱ እንዲሳተፉ ትመክራለች፡፡

ዓመታትን በአውራኅ፣ አውራኅን በሰሙናት፣ ሰሙናት በዕለታት፣ ዕለታትን በሰዓታት ቆጥሮና ቀምሮ ዓመቱን በሰላም አስፈጽሞ ለዚህ ዓመታዊ የእመቤታችን በረከት የምንሳተፍበትን ጾመ ፍልሰታ በሰላም በጤና ያደረሰን አምላክ ክብር ምስጋና ይግባው አሜን፡፡

የፎንት ልክ መቀየሪያ