Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

ከሆሣዕና እስከ ትንሣኤ

የብዕር ቅኝት መምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ኃላፊ

በዛሬ ዝግጅታችን ትምህርተ ሃይማኖት የሚል ነው፡፡ ይህም ሆሣዕና ማለት ምን ማለት ነው? ዕለቱን በየዓመቱ እናከብረዋለን፤ ምን የተደረገበት ነው? የሰሙነ ሕማማት ምሥጢር ምንድን ነው? በጸሎተ ሐሙስ የተፈጸመው ሥርዓትስ፤ የዕለተ ዓርብ ታምራት፣ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት ስለሚባለው፤ ጌታ በመቃብር ስለቆየበት የሰዓት አቈጣጠር፣ እንዲሁም ጌታ "ወይቤ ተፈጸመ ኲሉ" ያለበት ምክንያት ምንድነው? ቅዳሜ ሥዑር የተባለበት ምክንያትስ ዋና ትርጉሙ ምን ይመስላል? ትንሣኤ ክርስቶስና ትንቢቱ፣ የሚሉና የመሳሰሉ ነጥቦችን ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከእኛ የሚጠበቀው የቤተ ክርስቲያንዋን ትምህርተ ሃይማኖት በጥንቃቄ ማቅረብ ሲሆን ከአንባቢው የሚጠበቀው ደግሞ ጽሑፉን በጥንቃቄ አንብቦ ማወቅና መረዳት ነው፡፡

ሆሣዕና

ሆሣዕና ማለት መድኃኒት ማለት ነው፡፡ "ሆሣዕና በአርያም" በሰማይ በምድር ያለ መድኃኒት፡፡ "አልቦ ካልዕ ስም ዘይትወሀብ ለዕጓለ እመሕያው ዘእንበለ ስሙ ለኢየሱስ ክርስቶስ" "መዳንም በሌላ በማንም የለም፣ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ከሰማይ በታች ሌላ የለምና" ብሎ ሉቃስ በግብረ ሐዋርያት ገልጦታል፡፡ የሐዋ. 4፡12 በሰማይ በምድር ሌላ ድኅነት የሚሰጥ የለም፡፡

የትንቢቱን ለመፈጸም "ነዋ ንጉሥኪ ይመጽእ ይጼዓን ዲበ እድዪግት ወዲበ ዕዋላ" "እነሆ ንጉስሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ትሑትም ሆኖ በአህያም በአህያዪቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል" ብሎ ዘካርያስ ወልደ ሐድ ከደቂቀ ነቢያት አንዱ ተናግሯል፡፡ /ዘካ.ምዕ.9፡9/ ማቴ. 21፡1-11

ነቢዩ ኢሳይያስ ደግሞ "በልዋ ለወለተ ጽዮን ነዋ ንጉሥኪ ይመጽእ ዘይጼዓን ዲበ እድግት ወዲበ ዕዋለ አድግ" "ለጽዮን ልጅ እነሆ ንጉስሽ በአህያዪቱና በውርንጫይቱ ላይ ተጭኖ ይመጣል በሏት" ኢሳ. 12፡6

ዘካርያስና ኢሳይያስ የተናገሩትን ትንቢት ለመፈጸም በአህያ ተቀምጦ መጣ፣፣ እናቲቱ ቀንበር ጭነት የለመደች ናት፡፡ የእስራኤል ምሳሌ፤ ሠረገላ ቀንበር መጫን የለመደች እንደሆነች፣ እስራኤልም ሕግ መጠበቅ የለመዱ ናቸውና፡፡

ዕዋል /ውርጫይቱ/ የአሕዛብ ምሳሌ መጫን ያልለመደች እንደሆነች አሕዛብም ሕግን መጠበቅ ያልለመዱ ናቸውና፡፡ አንድም እድግት እናቲቱ የኦሪት ምሳሌ፤

ዕዋል ግልገልዋ የወንጌል ምሳሌ ናቸው ስለዚህ ትንቢቱን ለመፈጸም በአህያ እና በግልገልዋ ተጭኖ መጣ፡፡

ከቤተ መቅደስ እስከቢታንያ 14 ምዕራፍ ነው በእድግት ሆኖ ከዚያ ወርዶ በዕዋል በግልገልዋ ሦስት ጊዜ ቤተ መቅደሱን ዙሮ ወደ ቤተ እግዚአብሔር ገብቷል፡፡ በበለጠ የማቴዎስ ወንጌል ምዕ. 21 አንድምታውን ተመልከት፡፡

"ወበልዋ ለወለተ ጽዮን" "ለጽዮን ልጅ ንገሯት" የተባለች ቤተ እስራኤል ናት፡፡ የባሕርይ አምላክ ክርስቶስ መጥቷልና የነገራችሁን ስሙ ማለት ነው፡፡

በዚሁ ዕለት ቅዱስ ያሬድ በሠራው መዝሙር "ወእንዘሰሙን በዓለ ፋሲካ ቀርቡ አርዳኢሁ ለአምላከ ጽድቅ ኀበ ደብረ ዘይት ሙራደ ዓቀብ ሀገረ እግዚአብሔር"

"በዚሁ በዓለ ፋሲካ ሰሞን በደብረ ዘይት በአቀበቱ መውረጃ አጠገብ በእግዚአብሔር ሀገር የእውነተኛ አምላክ ደቀ መዛሙርት ቀረቡ" ብሎ ተናግሯል፡፡ በሌላ በኲል ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ የገባበት ዕለት ተብሎ ነው የሚነገረው ይህ ሁሉ ትንቢትን ለመፈጸም የተነገረ ነው፡፡

የሆሣዕና ሥርዓት

የሆሣዕና ሥርዓት አከባበር ከመቼ ጀምሮ ነው ቢባል ከመጀመሪያው ጳጳስ ከአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ጀምሮ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ /ዕለት/ ሊቃውንቱ ማኅሌተ እግዚአብሔር ቆመው አድረው፣ ከቅዳሴ በፊት "ወበልዋ ለወለተ ጽዮን" "ለጽዮን ልጅ ንገሯት" እያሉ ቤተ መቅደሱን ወይም ቤተ ክርስቲያኑን በዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው በመዞር፣ ሥርዓተ ዑደቱን ይፈጽማሉ፡፡ ምስባክ ይሰበካል፤ ወንጌል የአራቱ ወንጌላውያን ለዕለቱ ተስማሚ የሆነ ከየምዕራፉ ይነበባል፡፡ ይህም ምሳሌ አለው፡፡ አብርሃም ይስሐቅን በወለደ ጊዜ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዞ አመሰግነዋልና ያንን ለመፈጸም ነው፡፡

ሰሌን እሳት አይበላውም ለብልቦ ይተወዋል፤ ክርስቲያኖችም ባሕርይህ አይመረመርም ሲሉ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው በየዓመቱ "ሆሣዕና በአርያም" እያሉ ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ፡፡

በዚህ ዕለት ለምን ልዩ ጸሎተ ፍትሐት ይፈጸማል?

በዚህ ዕለት ጸሎተ ፍትሐት የሚፈጸመው በሰሙነ ሕማማት በሚገኙ ዕለታት ለሙታን፣ ፍትሐት ስለማይደረግ ነው፡፡ ካሣ የተፈጸመው ጌታ ተሰቅሎ ነፍሳትን ከሲኦል ነጻ ካወጣ በኋላ ስለሆነ፤ ከዚያ በፊት ካሣ አልተፈጸመምና፡፡ ይኸውም በሰሙነ ሕማማት ለሙታን ፍትሐት እንዳይደረግ ካልዕ ሰላማ በግብረ ሕማም መጽሐፍ ስለአዘዘ፤ በዚህ ምክንያት የሆሣዕና ዕለት ጸሎተ ፍትሐት ይፈጸማል፤ እንጂ ሰኞ፣ ማክሰኞ፣ ለሞተ ሰው ጸሎተ ፍትሐት አይደረግለትም፡፡ በሆሣዕና ዕለት የሚደረገው ጸሎተ ፍትሐት ለዚህ ተብሎ ነው፡፡

አሁን ያለነው ድርጊቱ /ካሣ/ ከተፈጸመ የዛሬ 1970 ዓመት ነው፡፡ ይህ ዛሬ እንዴት እንደ አዲስ አድርጎ ሊፈጸም ይችላል? የሚል ካለ ያማ ጌታ የሠራውን ሥራ ሁሉ እስከ ዓለም ፍጻሜ ሥሩ ተብሎ የለ? ሥሩ ማለት እናንተ ስታልፉ /ስትሞቱ/ ልጆቻችሁ ይሰሩ ማለትኮ ነው፡፡

በሰሙነ ሕማማት ለምን መስቀል አንሳለምም?

ሰላምታንስ ለምን አንለዋወጥም?

በሰሙነ ሕማማት መስቀል የማንሳለምበት ዋና ምክንያት ገና ጌታ ተሰቅሎ ካሳ አልተፈጸመም፤ ነፍሳት ከሲኦል አልወጡም ነበር ለማለት ነው፡፡ ዓርብ በሠርክ ነው የወጡ ለማለት ያንን ለማስታወስ መስቀል አንሳለምም፡፡ ካሣ ከመፈጸሙ በፊት መስቀል የድኅነት /የመዳን/ ዓርማ /ምልክት/ አልነበረምና ያንን ለማስታወስ ነው፡፡

ሰላምም የማንባባልበት ምክንያት አይሁድ ጌታን ለመስቀል ሰኞና ማክሰኞ መከሩ፤ አልሆነላቸውም፡፡ ምክራቸው የተፈጸመው ረቡዕ ነው፡፡ ሉቃስ "ወአስተ ሐለፉ ነገረ" ብሎ ያነበዋል፡፡

ስለዚህ እያንሾካሾኩ "እንስቀለው" "እንግደለው" ብለው ይማከሩ ነበር፡፡ ያንን ለማስታወስ ሰላምታ አንለዋወጥም፤ መስቀልም አንሳለምም፡፡ ባጭሩ ሳምንቱ የክፋት ምክር የተመከረበት እንጂ ሰላም የታየበት ሳምንት ባለመኖሩ ነው፡፡

ዕለተ ረቡዕ

ከሆሣዕና በአራተኛው ቀን የሚገኘው ዕለት ረቡዕ የጌታ ምክረ ሞቱ የተፈጸመበት፣ የአስቆሮቱ ይሁዳ በ30 ብር ጌታን ለማስያዝ ከሊቃነ ካህናቱ ጋር የተሰማማበት ዕለት ነው፡፡ ማር. 14፡42 ፤ ማቴ. 26፡49 ፤ 27፡3 ፤ ሉቃ. 11፡47፡፡

ጸሎተ ኀሙስ

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በዚሁ ዕለት ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙንም ለሐዋርያት የሰጠበት ዕለት ነው፡፡ የአይሁድ ፋሲካ የነበረው ሐሙስ ነው፡፡ ከአይሁድ ጋራ በበዓል በጾም እንዳንገናኝ የኒቅያ ጉባኤ በድሜጥሮስ ቀመር፤ እንዲሁም የአውሻክር ሰዎች በአውሻህር፣ በባሕረ ሐሳብ በዚሁ ሁሉ ወስነውታል፡፡ "እመቦ ዘይጸውም ጾሞሙ ለአይሁድ ወያከብር በዓሎሙ ለአይሁድ ይሰደድ እምክርስቲያን"

"የአይሁድ ጾማቸውን የሚጾም፣ በዓላቸውንም የሚያከብር ካለ? ከክርስቲያንነት ይወገድ /ይባረር/ ብሏል ሰለስቱ ምዕት በሃይማኖተ አበው"

በዚሁ ዕለት በማቴዎስ ወንጌል ምዕ 26፡26 እንደተገለጸው ጌታ ክቡር ሥጋውንና ደሙን ለሐዋርያት ሰጥቷል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ቁርባን የሚለው በዕለቱ ተለውጧል ወይ? ወይስ አልተለወጡም?

በሌላ በኩል ጌታችን ለሐዋርያት የሰጣቸው "ሥጋዬ" ብሎ ሲሆን ይህ አማናዊ ነው ወይ? እንዴት ከመሰቀሉ በፊት "ሥጋዬ" ብሎ ሊሰጣቸው ቻለ? የሚሉ እንዳሉ ጥያቄ ሰምቼአለሁ፡፡

መልሱ ግልጽና አጭር ነው፡፡ ይኸውም አማናዊ ነው፡፡ ነገ በቀራንዮ የሚሰቀል "ዝውእቱ ሥጋየ ወዝውእቱ ደምየ" "ነገ በመስቀል የሚሰቀል ሥጋየ ይህ ነው፣ ነገ ኲናተ ሐራዊ የሚያፈሰው ደሜ ይህ ነው" ብሎ አክብሮ፣ ለውጦ ትኩስ ሥጋ፣ ትኩስ ደም አድርጎ ሰጣቸው፡፡ ስለፈሩ "ጥዒሞ አጥዓሞሙ" አይዟችሁ አትፍሩ ብሎ ቀምሶ ሰጣቸው፡፡

ጌታ ሳይቀበል አቀበሎአቸው ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ የሚቀድሰው ካህን አቀብየ ሳልቀበል ልውጣ ባለ ነበርና፣ ተቀብሎ ያቀብል ለማለት ለአብነት፣ የሠራው ሁሉ ለእኛ ነው፡፡

"እስመ አልቦ ነገር ዘይሰዓኖ" "ለእግዚአብሔርየሚሳነው የለም"፡፡ እግዚአብሔር ይህ ሥጋየ ነው ሲል ውሸት ነው አይባልም፡፡ የተናገረውን ሁሉ ማመን አለብን፣ ጥያቄው ሳይሰቀል ለምን ሥጋየ ነው አለ ነው፣ ነገር ግን ነገ የሚሰቀለው ሥጋዬ ይህ ነው ሲል ተለውጦ ሥጋ ወልደ እግዚአብሔር ሆነ ማለቱ እንደሆነ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ያ የዕለተ ሐሙስም ሆነ ዛሬ ካህናት የሚያቀርቡት መሥዋዕት አማናዊ ሥጋውና ደሙ ነው፡፡

ጠያቂዎቹ እንደምሳሌ አድርገው የሚያቀርቡት ጌታ ከመሰቀሉ በፊት ሥጋውና ደሙ ተበልቷል ወይስ አልተበላም እንዴት ጌታ ሳይሰቀል ሥጋው ተበላ የሚል ጥያቄ ነው፡፡

መልሱ፣ ነገ የሚሰቀለው ሥጋየ ይኸ ነው፣ ነገ የሚፈሰው ደሜ ይኸነው ሲል ቃሉ ለወጠው፤ ሥጋና ደሙ አደረገው፡፡ እኛ አምነን እንቀበላለን እንጂ አይደለም አይባልም፡፡ እግዚአብሔር የተናገረውን ሁሉ አምነን መቀበል አለብን፡፡ እሱ ይህ ሥጋየ ነው ይህ ደሜ ነው እያለ አይደለም የሚል ካለ ሐሰተኛ ይሆናል፡፡ "እስመ አልቦ ነገር ዘይሰአኖ ለእግዚአብሔር" እሩቅ ብእሲ ቢሆን ኖሮ አይሆንም ይባል ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን ያለው ሁሉ ይሆናል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም በዕለተ ሐሙስ ሐዋርያት የታጠቡት ኅፅበት ስለ ትሕትና ወይስ ስለ ጥምቀት የሚል ጥያቄ አለ፤ ይህም፡-

ሐዋርያት የታጠቡት ጥምቀት ነው፡፡ "እመ ኢሐጸብኩከ እገሪከ አልብከ ክፍል ምሳሌየ" "ካላጠብኩህ ከእኔ ጋር ዕድል የለህም" ሲል መልሶለታል፡፡ ዮሐ. 13፡7 ዕድል ፈንታ የለህም ማለት ልጅነት አታገኝም ማለት ነው፡፡

ጥምቀት እንዳንል ካሣ አልተፈጸመም የሚል ሐሳብ ካለ አስቀድሞ አጥቦ ወዲያው ሥጋና ደሙን ሰጣቸው፡፡ ዛሬ መጀመሪያ ሕፃኑን እናጠምቀዋለን፤ ኋላ ሜሮን ተቀብቶ ሥጋውና ደሙን ይቀበላል፡፡ ይኸ "ተሰዕሎተ ቢንያም" የሚባል ጥሩ አድርጐ ጽፎታል፡፡ ስለዚህ ሐዋርያት መቼ ተጠመቁ ቢባል በሕጽበተ እግር ጊዜ ነው፡፡ ይህም "አልብከ ክፍል" "ዕድል ፈንታ የለህም" ባለው ይታወቃል፡፡

ለጊዜው ሐዋርያት ዕግራቸው ብቻ እንደታጠቡ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ ግማሹ አካላቸው ታጥበውስ እንዴት ጥምቀት ሆኖ ሊቆጠር ቻለ ቢሉ? ያማ "ዘይውህጥ ርዕሶ" ብለው ሠለስቱ ምዕት የሕጻኑን ራስ በሚውጥ ባሕር ብቅ ጥልቅ ብቅ ጥልቅ አድርጉ ብለው በጥልቅ ባሕር፣ በማዕከላዊ ባሕር፣ በንዑስ ባሕር የተጠመቀ እንደ ሆነ ነው ብለው ጽፈው የለ፡፡ "ዘይውህጥ ርዕሶ" የሚጠመቀውን ሰው በፈሳሽ ወንዝ ብቅ ጥልቅ ብቅ ጥልቅ አድርገህ ታወጣዋለህ፡፡ ጴጥሮስ መላ አካላቴን እጠበኝ ባለበት ሰዓት ጌታ አይፈቀድልህም ያለው ይህ ለምንድነው ቢባል? እግሩን የታጠበ ሰው ሌላው ሊታጠብ አይፈልግም፡፡ አንዱ የሰውነት አካልህ ካጠብኩህ መላ ልጅነት ይሰጥሃል፡፡ ማለት ነውና በትልቁ ባሕር፣ በትንሹ ባሕር፣ በጳጳስ ቢጠመቁ አንድ ነው፡፡ "አሐቲ ጥምቀት" "አንዲት ጥምቀት" /ኤፌ. 4፡4/፡፡

አንዳንዴም ሐዋርያት የተጠመቁት በውሃ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ለዚያም እንደ ማስረጃ የሚጠቅሱት መጥምቁ ዮሐንስ በማቴዎስ ወንጌል የንስሐ ጥምቀት በሚያጠምቅበት ጊዜ "እኔ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳት ያጠምቃችኋል" ማቴ. 3፡11 ያለውን ይጠቅሳሉ፡፡

ለዚህ መልስ የሚሰጠን በግብረ ሐዋርያት ጴጥሮስ ሲናገር "ንስሐ ግቡ፣ ኃጢአታችሁም ይሠረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ የሚለው ነው፡፡ /የሐዋ. 2፡38/

ሐዋርያት ሲያጠምቁ ቋንቋ ይገለጽላቸው ነበር መንፈስ ቅዱስ ያድርባቸው ስለነበር ተጠቀሰ እንጂ የሐዋርያትን መጠመቅ አያስመለክትም፡፡ ከዚሁ ባልተለየ መልኩ አብሮ የሚታየው ኦሪት አለፈች፤ ወንጌል ተተካች የሚባለው መቼ ነው ቢሉ ከልደቱ እስከ ጥምቀቱ ከጥምቀቱ እስከ ዕለተ ሐሙስ ከዕለተ ሐሙስ እስከ ትንሣኤ ባለው ሰዓት ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ሲያስተምር እሷን ወደ ወንጌል እየሳበ ቆይቷል፡፡መስዋዕትዋን የሻረው በዕለተ ሐሙስ ነው፡፡ በግ ይሰዋ ነበር፤ ቀርቷል መስዋዕትዋን አሳለፈው፣ የበሉትን ምግብ ከሆዳቸው በግብር አምላካዊ አጥፍቶ አማናዊ ሥጋውን አማናዊ ደሙን ሰጣቸው፡፡ ሌላው በየስፍራው ሲያስተምር አሳልፎታል፡፡

ዐሠርቱ ቃላት ብቻ አላለፉም፡፡ ሌሎች ሥርዓቶች ግን አልፈዋል፡፡ የወንድምን ሚስት ማግባት ቀርቷል፡፡ የበግ፣ የላም፣ የዋኖስ የዕጉለር ግብ፣ መስዋዕትና ይህን የመሰለ ሁሉ ቀርቷል፡፡

አንዳንድ ሰዎች ኦሪት ለምን አለፈች ይባላል? "ጌታ በወንጌል ኢመጻእኩ እስዓሮሙ ለኦሪት ወለነቢያት አላ ከመእፈጽሞሙ" "ኦሪትንና ነቢያትን ሊሸራቸው አልመጣሁም፣ ልፈጽማቸው እንጂ" ብሎአልና አላለፈችም የሚሉ አሉ፡፡ "ኢመጻእኩ ከመእስዓሮሙ ለኦሪት ወለነቢያት" ማለት፤

ኦሪት፣ ነቢያት የተናገሩትን ላስቀር አልመጣሁም፣ ይወርዳል ይወለዳል፣ ብለው የተናገሩትን ሁሉ ልፈጽም ነው የመጣሁ፣ ማለት እንጂ ኦሪት አላለፈችም ለማለት አይደለም፡፡

"የውጣ" የተባለው ዐሠርቱ ቃላት ነው፡፡ ይኸውም እነሱ አልተሻሩም፡፡ኦሪት አለፈች የሚያሰኘው በግ፣ ላም መሠዋት፣ የወንድም ሚስት ማግባት፣ እጃቸው እስኪላጥ መታጠብ፣ ይህን የመሳሰለ ሁሉ አልፏል፡፡ ከአሥሩ ቃላት በቀር ሁሉም አልፏል፡፡ ዐሠርቱ ቃላት ግን በወንጌል እንኳንስ ነፍስ መግደል፤ ወንድሙን የሰደበ ይፈረድበታል፡፡ ሲል ፈጽሞ እያበለጠው ሄደ፣ "አትዘሙ" ያለውን "ኲሉ ዘርእያ ለብእሲት ወፈተዋ ዘመወ"

"ሴትን አይቶ የተመኛት አመነዘረ" ብሏል፡፡ እንኳንስ ከወንድ ሚስት መድረስ አይቶ የተመኘ በደለ፣ በማለት የኦሪትን ሥርዓት እየፈጸመው ሄደ፤

"አንሰ እብለክሙ፣ አንሰ እብለክሙ" እያለ የተናገረው ሁሉ አሳለፈው ፈጸመው ማለት ነው፡፡

በዓለ ፋሲካ

በብሉይ የነበረ በግ ምሳሌ በብሉይ ኪዳን በጉ ዓመት የሆነው፤ ቀንዱ ያልከረከረ፤ ጥፍሩ ያልዘረዘረ፤ ዓመት የሞላው ጠቦት አይታችሁ ከ10 እስከ 14 ቀን በመዓልቱ በሁለት እጅ ብርሃን፤ ከሌሊቱ በአንድ እጅ ጨለማ ሰውት፡፡ ስትሰውትም ሰባት፤ አሥር፣ አሥር ሁለት ሆናችሁ ሰውት ብሎአቸዋል፡፡

በጉ ቀንዱ ያልከረከረ፤ ጥፍሩ ያልዘረዘረ መሆኑ፤ ጌታም ምክንያተ ኃጢአት የለበትምና ነው፡፡ ደሙን ስትቀቡት "ወሶበ ርእየ መልአከ ሞት ደመ በግዕ ለበወ ሞተ እግዚእ ፈርሐ ወኢቀርበ" እንዲል "ይህ የክርስቶስ ምሳሌ ነው ሲለው ነው፣ አባር ቸነፈሩ ከእስራኤል ቤት እንዳይገባ ይሆናል"፡፡ ደመ በግዑን ያየ መልአከ ሞትም እስራኤልን እያለፋቸው መሄድ ጀመረ፡፡ የግብጻውያን በኩር፣ ይገድላል፡፡ ያ የክርስቶስ ምሳሌ በመሆኑ የደመ በግዑ የደም ምልክት ያለው ቤት ሞት አይገባውም፡፡ በደመ ክርስቶስ የተዋጀ፣ በደመ ክርስቶስ መዳኑን ያመነ ሰውም ሞተ ነፍስ አያገኘውም፡፡ ላቱ እስከ ምጽአት የሚነሱ መምህራን፣ ጸጉሩ የመንፈስ ቅዱስ፣ ስለሀብቱ ብዛት፣ ቀንዱ የሥልጣነ እግዚአብሔር፣ ዓይኖቹ የነቢያት ምሳሌ ናቸው"፡፡

በዚህ ዕለት በተለይ በምዕመናን የሚፈጸም ሌላ ድርጊት አለ፡፡ ይኸውም ዳቦ ይጋገራል፣ ንፍሮ ይነፈራል፣ ይኸ ልማደ ሀገር ቢሆንም የተቻለው ዓርብንና ቅዳሜን ያክፍል፣ ያልተቻለው ቅዳሜን ብቻ ያክፍል ብሏልና፡፡ ለአክፍሎት የሚስማማን ምግብ የሚጾም ሰው እንዳይደክም "ጉልባንን" አብዝቶ ይበላል፡፡

ጾሙን የጀመረው "ያዕቆብ እኁኁ ለእግዚእነ" የጌታ ወንድም ያዕቆብ ነው፡፡ ይኸውም የጌታ ትንሣኤን ሳላይ አልበላም በማለት ጀምሮታል፡፡ ጌታ ከተቀበረ በኋላ ሐዋርያት እህል እንብላ አሉ፡፡ "ያዕቆብ በሦስት ቀን እነሳለሁ" ብሏል አይሆንም ቢላቸው እንግዲያስ እኛም እንጹም ብለው ጹመዋል፡፡ እኛም ያንን ይዘን እንጾማለን፡፡

ዕለተ ዓርብ

ክርስቶስ የተሰቀለበት ዕለት ዕለተ ዓርብ ይባላል፡፡ ይህ ዕለት ክርስቶስ ከተሰቀለበት ጊዜ ጀምሮ እሰከ አሁን ድረስ በክርስቲያኖች ዘንድ በጾምና በስግደት በየዓመቱ ይከበራል፡፡ በመጀመሪያ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ የተሰቀለው ትንቢቱን ለመፈጸም ነው፡፡ ሙሴ "ስቅልተ ትሬእያ እስራኤል ለሕይወትከ ቅድመ አዕይንቲከ ወኢትትአመና"

"እስራኤል ሆይ ሕይወትህ /ክርስቶስ/ በዓይኖችህ ፊት በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ታየዋለህ፡፡ ግን አታምነውም፡፡" /ዘዳግ. 28/

ታላቁ ነቢይ ኢሳይያስም "መጽአ ከመ በግዕ ይጠባሕ ወከመ በግዕ ዘኢይነብብ በቅድመ ዘይቀርጾ ከማሁኢከሠተ አፍሁ በሕማሙ በቅድመ እለ ይረግዝዎ፤ ወበ ኃጢአተ ሕዝብየ በጽሐ እስከ ለሞት፣ ነሥአ ደዌነ ወጾረ ሕማመነ" አኮ በመልአክ ወአኮ በተንባል አላ ለሊሁ እግዚእ መጽአ ወአድኀነነ ተብሎ በሰፊው ተናግሯል፡፡ ጥቅሶቹ ብዙ ናቸው፡፡ ኢሳ. 53፡1-6

ነቢዩ ዳዊትም "አገቱኒ ከለባት ብዙኃን፣ ወአዙኒ ማኅበሮሙ ለእኩያን" ቀነውኒ እደውየ ወእገርየ ወኆ ለቁ ኵሎ አዕጽምትየ" "እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩኝ፡፡ አጥንቶቼ ሁሉ ተቈጠሩ፤ እነርሱም አዩኝ ተመለከቱኝም" እንዳለው፡፡ 6666 ጊዜ በገረፉት ጊዜ አጥንቱ ተቆጥሮዋል፣ ይኸ አስቀድሞ ቅዱስ ዳዊት የተናገረው ነው፡፡ 6666 ጊዜ ለመገረፉ ግብረ ሕማማት ይገልጻል፡፡ መዝ. 21/22 ቁጥር 17-18

ክርስቶስ ለምን ሞቱ በመስቀል ሆነ? ከመስቀል በሌላ ማዳን አይችልም ነበር ወይ? ቢባል በዘመኑ የነበረው የበደለኛ አገዳደል ሥርዓት እንደየሀገሩ ሁኔታ የተለያየ ነበር፡፡

ለምሳሌ የሮማውያን ሥርዓታቸው መስቀል ነው፡፡ የአይሁድ "ውግረተ ዕብን" ነበር፡፡ የባቢሎናውያን እሳት አንድዶ እዚያ መክተት ነው፡፡ ፋርስ ለአንበሳ መጣል ነው፡፡ ጌታም በሮማውያንም ሥርዓት ተሰቅሎ ሞተ፣ ለዚህም ራሱ ጌታ ሞቱ በመስቀል እንደሚሆን አስቀድሞ ተናግሯል፡፡ ዮሐ. 3፡14፡፡

ባይሰቀል፣ ጎኑ ባይወጋ ማይ ለሕጽበት፣ ደም ለጥምቀት ባልተገኘ ነበር፡፡ ብለው መምህራን ተርጉመዋል፡፡ አይ፣ በውግረትም ደሙን አይታጣም ብለው ትንቢትን ለመፈጸም ተሰቀለ ብሎ አስታርቀውታል እንጂ፡፡ የአይሁድ ሥርዓት በድንጋይ ወግሮ መግደል ነው፡፡ ጌታ የተሰቀለው በሮማውያን ሥርዓት ነው፡፡

"ኲሉ ሰቁል ዲበ ዕፀመስቀል ርጉም ውእቱ" "ሠርቶ ቀምቶ የተሰቀለ ሰው የተረገመ ነው" ትላለች ኦሪት፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም "ወፆረ መርግማ ለኦሪት" አለ፡፡

ርጉም ተብሎ የአዳምን መርገም ለማጥፋት በአዳም የተፈረደው ሁሉ ተቀብሎ አዳምን ከመርገመ ነፍስ አዳነው፡፡ "ወሠዓረ መርገመ እምኔነ" ከእኛ መርገመ ኃጢአትን ደመሰሰ፣ አጠፋ ያለው ስለዚህ ነው፡፡ ዛሬ ክርስቶስ ከተሰቀለ፤ ልጅነት ከተመለሰ ወዲህ ወደ ሲኦል መውረድ ቀርቷል፡፡ ይህም ዮሐንስ አፈወርቅ ገልጦታል፡፡ "እንከሰ ኢንወርድ ታሕተ አላ ፈድፋደ ንተልዎ ለዘፈጠረነ ወንበውእ ኀበ ቦአ ሐዋርያነ ህየ ንበውእ ኵልነ" ይላል፡፡ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ ጠፋልን የተባለው አምኖ፣ ተጠምቆ፣ ጥሩ ሥራ ከሠራ ወደታች መውረድ የለም ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት ነው፡፡

ቀድሞ በዘመነ ብሉይ መልካም ሥራ ቢሠሩም እነ አብርሃም ይስሐቅ፣ ያዕቆብ ሁሉ በሲኦል ነበሩ፡፡ የአዳምን መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ አጠፋ የሚለው ስለዚህ ነው፡፡

"ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ ወእድኅክ ውስተ መርህብከ ወእትቤዘወከ በሞትየ ወበመስቀልየ" ቀሌምንጦስ፤

"ወለትከ" የተባለችው ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡ ገድለ አዳም ገጽ 105፡125፡፡ መጽሐፈ ቀሌምንጦስ ገጽ 54፡8

ቀደም ብሎ እንደተገለጸው "ከመይሥዓር መርግማ ለኦሪት" በተባለው መሠረት አዳም ተርግሞ ነበር ወይ? ሲባል መልሱ አዎ ነው፡፡

ከገነት ሲኖር "ይችን ዕፅ የበላህ እንደሆነ ትመውት ሞተ" ሞትን ትሞታለህ በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ፣ በርደተ መቃብር ርደተ ሲኦል ያገኝሃል ነው ያለው፡፡ "ወአልበሶሙ አእዳለ ማዕስ" ያብርሃን የነበረው፣ እንደብርሌ፣ እንደ ብርጭቶ ንጹሕ የነበረው እሾኽ እማይወጋው፣ እንቅፋት የማይመታው፣ እማያደማው፣ ብርድ የሌለበት የነበር በኋላ መርገም ሲያድርብት እሾክ የሚወጋው፣ እንቅፋት የሚመታው፣ ብርድ የሚሰማው ልጅነት የሌለው ቁርበት አለበሰው፡፡

እሱ ባይረገም፣ ወደ ምድር ባይወርድ፣ በዘፍጥረት 1፡28 "ብዙ፣ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት ግዙአትም" ብሎ ነበረ አዳም ባያጠፋ ኑሮ ሰው እንዴት ሊበዛ ይችል ነበረ ቢሉ? ይኸማ መጀመሪያ አዳም በሥልጣነ እግዚአብሔር ተገኘ እንጂ ከሴት አልተገኘም፡፡ ሔዋንም ያለ ወንድ በሥልጣነ እግዚአብሔር ተገኘች እንጂ ሴትና ወንድ ተገናኝተው አልተፈጠሩም፡፡ ባይበድሉ በሥልጣነ እግዚአብሔር ወንድም በአዳም አምሳል፣ ሴቱም በሔዋን አምሳል በሥልጣነ እግዚአብሔር እየተባዛ፣ ዕፀ ሕይወትን እየበላ ሺህ ዘመን ሲሞላው መንግሥተ ሰማያትን ሊገባ ተፈጥሮ ነበር፡፡

እንግዲህ ለአዳም ዕፅዋትን ሰጠው፤ አንዱ የሚመገበው በመዓዛው ይጠግባል ሁለተኛው ሕግ ሊጠብቅለት ይችን ዕፅ አትብላ ብሎ፤ ሦስተኛው ሺህ ዘመን ኑሮ ያን ሲበላ ተሐድሶ መንግሥተ ሰማይ ሊገባ ፈጥሮት ነበር፡፡

ይኸንንም ሰሎሞን ገልጦታል "እግዚአብሔርሰ ኢገብረ ሞተ አላ ረሲአን ሰብእ አምጽእዎ በቃሎሙ ወዓርከ አምስልዎ" እግዚአብሔር ጥንቱን ሲፈጥረው ሞት እንዲሞት እንዲቀበር ወደሲኦል እንዲወርድ አልፈጠረውም፡፡ ሕጉን እንዲጠበቅ ሺህ ዘመን በሕይወት እየተቀመጠ ወደ መንግሥተ ሰማይ ሊገባ ተፈቅዶ ነበር፡፡ "ኢትብልዑ እምዕፅ" ይችን እንጨት አትብሉ ያለውን የዘነጉ አዳምና ሔዋን ሞትን፣ መቃብርን፣ ስበው ጎትተው አመጡት፡፡ "ወአርከአምስልዎ" ወዳጅ አስመሰሉት አለ ወዳጅ እንዳይለይ እንዳይለይ አደረጉት፡፡ ቀጥሎ ልጆቻቸውን፣ ይህንም ቅዱስ ጳውሎስ ገልጦታል፡፡ "ወሶበ ኵነኔ ኃጢአት ወጽአ እምላዕለ አሐዱ ብእሲ ተቀሰፈ ባቲ ኩሉ ፍጥረት" ሮሜ. 5፡12፡፡

ከአንዱ አዳም የተገኘች ኃጢአት ሁሉን /መላውን/ አደረሰች፣ ከአንድ ዛፍ በተቈረጠ ጨንገር ብዙ ሕፃናት እንደሚገረፋ ኃጢአትም ከአዳም ተገኝታ ሁሉን ያዘች፡፡ መባዛት በዘር በሩካቤ የሆነው ከመርገም በኋላ ነው፡፡ በገነት ሳሉ ወንድና ሴት መሆናቸው አይተዋወቁም፡፡ አዳም እኔ ብቻ ነኝ ሲል ረዳት እንድትሆነው ፈጠረለት እንጂ በዘር በሩካቤ ሊገናኙ አይደለም፡፡ ለምን ተባዙ አለ በሥልጣኑ ያበዛቸዋል፡፡

እግዚአብሔር ሁሉን አንድ አንድ ጊዜ ነው የተናገረው "ለታብቁል ምድር" አለ ይኸ መሬት ሁል ጊዜ ታበቅላለች፡፡

"ለያብርኁ ብርሃናት" አለ እነሆ ፀሐይና ጨረቃ፣ ከያለበት ሲያበሩ ይኖራሉ፡፡ "ለታውጽእ ባሕር ዘቦ መንፈሰ ሕይወት" ሲል አዞ፣ ጉማሬ አንድ ጊዜ ሲባዙ ይኖራሉ፡፡

ዕለተ ኅሪት

ዕለተ ኅሪት ተብላ በኢሳይያስ የተጠቀሰችው በዘመነ ብሉይ ዕለት ኅሪት ዕለተ ፄዋዌናት፣ ኅሪት አላት "ወሶበይበዝኅ አወጽአከ ለትፍስሕት" እንዲል፣ በሰባ ዘመን ትወጣለችሁ የሚለው ቃል ተስፋ ሰምተው ስለ ነበር ዕለተ ኅሪት አላት ዕለተ መድኃኒት፣ ዕለተ ሚጠት፣ ከፋርስ ከባቢሎን ሰባዘመን ኑረው የተመለሱበት ስለሆነች፡፡"

ዕለት ኅሪት በዘመነ ሐዲስ ዕለተ ጽንስ፣ ዕለተ መድኃኒት ዕለተ ልደት፣ዕለት ኅሪት ዕለተ ሥቅለት፣ ዕለተ መድኃኒት ትንሣኤ ዕለት ኅሪት ተስፋ ያለው ንስሐ የሚገባበት፣ ዕለተ መድኃኒት ዳግም ንስሐውን ጨርሶ ሲወጣ፣ ለበጎ ሁሉ የሚሆን እንጂ በጥቂት የሚወሰን አይደለም፡፡

ነፍሳት ከሲኦል የወጡ መቼ ነው?

ነፍሳት ከሲኦል የወጡ ዓርብ በሠርክ ነው፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስ "ሰበከሎሙ ግዕዛነ" "ነጻነት አወጃላቸው" ይላል፡፡ ጌታ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ "ሰላም ለኵልክሙ" "ሰላም ለእናንተ ይሁን" እንዴት ሰነበታችሁ? አስታረቋችሁ ሲላቸው ነው፡፡ አዳም የተቀጠረች የድኅነት ዕለት ዛሬ ናት ተንሥኡ ለጸሎት ሲል ነፍሳትም ምስለ መንፈስከ አሉ፡፡

ጌታም "እለውስተ ጽልመት ጻኡ ወእለ ውስተ ሲኦል ተከሠቱ ወርእዩ ብርሃነ" "በጽልመት ውስጥ ያላችሁ ውጡ፣ በሲኦል ያላችሁ ተገለጡ ብርሃንም አዩ" ብሎ እልፍ ፀሐይ ቢገባበት የማይለቅ የሲኦልንም ጨለማ ብርሃነ መለኮቱን ነዛበት ያኔ ጨለማው ለቀቀ የዚያን ጊዜ ወጐዩ ዓቀበተ ሥጋ መናፍስት /አጋንንት/ በዚህ ጊዜ ነፍሳትን የተቆራኙ አጋንንት ሸሹ፣ እለ ውስተ ሲኦል ጻኡ፤ ወእለ ውስተ ጽልመት ተከሠቱ ብሎ ባሕረ እሳትን ከፍሎ ወደ ገነት አገባቸው፡፡

በዚያ በሲኦል ሳሉም "ነፍሶሙ ለጻድቃን ውስተ ዕደ እግዚአብሔር" እንዲል "ያድነናል ብለው እንደነቢያት እንደአብርሃም፣ ያሉ አበው ዕደ እግዚአብሔር እንደ አጐበር እንደ ድንኳን ሆኖ ይጠብቃቸው ነበር እንጂ እንደ ኃጥአን ስቃይ መከራ አይጸናባቸውም ነበር፡፡"

ፊያታይ ዘየማን ደግም "አንተ ትቀድሞ ለአዳም በዊአ ውስተ ገነት" "አንተ አዳምን ቀድመህ ወደ ገነት ትገባለህ" ብሎት ነበርና እሱ ተቀድሞ ሲገባ፣ አዳም ከእነ ልጆቹ ስብሐት ለእግዚአብሔር ዘአውረሰነ መንግሥቶ ሰማያዊተ ሰማያዊት መንግሥቱን ላወረሰን ለአግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እያሉ ገብተዋል፡፡

በዕለተ ዓርብ ስንት ታምራት ታይቷል?

በዕለተ ዓርብ ጌታ በተሰቀለ ጊዜ የታዩት ታምራት ሰባት ናቸው፡፡ በሰማይ ፀሐይ ጨለማ ሆነ፣ ጨረቃ ደም ሆነች፣ ከዋክብት ረገፉ በምድር አዕባን ተፈተቱ፡፡ መቃብራት ተከፈቱ፡፡ አምስቱ ምእት ቢጽ ሙታን ተነሡ፤

የቤተ መቅደስ መጋረጃ ለሁለት ተከፈለ፡፡ "ወወጽአ ሕሩይ መልአክ እማዕከለ ኲሎሙ መላእክት እንዘ ይእኅዝ ሠይፎ ከመያጥፍኦሙ ለአላውያን፣ ወሶበ ከልአቶ ምሕረቱ ለአብ ወኂሩቱ ለወልድ ሜጠ ዝኩ መልአክ ሠይፎ ክሱተ ወዘበጦ ለመንጠላዕተ ቤተ መቅደስ ወሰጠጦ ወከፈሎ ለክልኤ፡፡"

መልአኩ ላጥፋቸው ቢለው ተውካጠፋኋቸውማ እኔ አጠፋቸዋለሁ አይደል? ብሎ አብ፣ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ከለከሉት፣ መልአኩ ተናድዶ ሰይፉን ሲወረውረው የቤተ መቅደሱን መጋረጃ ለሁለት ከፈለው ብሏል፡፡ ሃይማኖተ አበው ዘአትናቴዎስ፤

ለምን 450 ጊዜ እግዚኦ ይባላል?

በዚሁ ዕለት በአራት መዓዘን እየዞርን 450 ጊዜ ምሕላ እናደርጋለን፣ ምሕላ የምናደርገውም አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን የአዳም ልጆች በሲኦል ሆነው አቤቱ ይቅር በለን ብለው የለመኑትን ለማስታወስ ነው ከምሕላው በኋላ በወይራ እየተጠበጠቡ የንስሐ ስግደት እንደየ አቅሙ ይሰጣል፡፡ ከምን የተነሣ ነው ቢባል የክርስቶስን መከራ እንቀበላለን፡፡ በክርስቶስ ክርስቲያን ተብለናልና፡፡ የኛን መከራ ተቀብሎ እንዳዳነን እሱ የተቀበለውን መከራ እንቀበላለን፣ እንገረፋለን፣ አላውያን ነግሥታት፣ አላውያን መኳንንት፣ ሃይማኖታችሁን ካዱ ቢሉን ቢገርፉን እንገረፋለን በሰይፍ ቢመቱን፣ ቢሰቅሉን፣ መከራውን በጸጋ እንቀበላለን፡፡ ለማለት ነው፡፡ "ወዘኢጾረ መስቀለ ሞትየ ኢይጸመደኒ" እንዳለ ያለ ነው፡፡ እሱ የተቀበለው መከራ ተቀበሉ ተብሎ ታዟልና፡፡

በዕለተ ዓርብ ንሴበሖ ለእግዚአብሔር የሚባለው ለምንድነው?

በስቅለት፣ ዓርብ ማታ ከእግዚኦታ /ምሕላ/ በኋላ ንሴብሖ ይባላል፡፡ ምክንያቱም እስራኤል በምድረ ግብጽ 215 ዘመን በባርነት ቀንበር ሲገዙ ከነበሩ በኋላ በሙሴ መሪነት የኤርትራን ባሕር ስላሻገራቸው "ንሴብሖ ለእግዚአብሔር ስቡሐ ዘተሰብሐ" እያሉ አመስግነውታል፡፡ እኛ ደግሞ ከአጋንንት አገዛዝ ነጻ አውጥቶ ባሕረ እሳትን ከፍሎ ወደ ገነት ስለአገባን "ንሴብሖ" እያልን እናመሰግነዋለን፡፡

ንሴብሖ ለእግዚአብሔር ከተባለ በኋላ እግዚአብሔር ይፍታህ ይባላል፡፡ እግዚአብሔር ይፍታህ ይባላል፡፡ እግዚአብሔር ይፍታህ የሚባልበት ምክንያትም ካሣ ከተፈጸመ ወዲያ፣ ልጅነት የተመለሰ፣ ነጻነት የተገኘ ነፍሳት ከሲኦል የወጡ ስለሆነ ነው፡፡

ቅዳሜ ሥዑር

እስከ ምሴተ ሐሙስ ወይም እስከ ሐሙስ ማታ ጌታ የኦሪትን ሥራ ይሠራ ነበር፡፡ ከምሴተ ሐሙስ ጀምሮ መስዋዕተ ብሉይን፣ ሥርዓተ ብሉይ አሳልፎ ላም፣ በግ፣ ፍየል እንዳይሰዋ ከለከለ፡፡ መስዋዕቱን በስንዴና በወይን አድርጎ፡፡ ቀጥሎ ደግሞ አይሁድ ቅዳሜን ያከብሩ እሑድን ይሽሩ ነበር፡፡ ስለዚህ ቅዳሜን ብቻ ሳይሆን መላ የኦሪት በዓል ተሽሮ በዚያ ተተክቷል፡፡

ለምሳሌ፡- በበዓለ መጥቅዕ ቅዱስ ዮሐንስ መስከረም 1 ቀን ገባ

በሠርቀ ወርኅ ልደተ ክርስቶስ

በበዓለ መጸለት በዓለ ጥምቀት

በበዓለ ፍሥሕ ስቅለተ ክርስቶስ

በበዓለ ፋሲካ በዓለ ትንሣኤ

በበዓለ ሠዊት በዓለ ጰራቅሊጦስ

በጾመ አስቴር ጾመ ረቡዕ

በጾመ ዮዲት ጾመ ዓርብ

በጾመ ሙሴ ጾመ እግዚእነ

በቅዳሜ ዕለተ እሑድ ተክከቶበታል፡፡ስለዚህ ነው ተሻረ ያሰኘው፡፡

ስለዚህ ነው ተሻረ ያሰኘው፡፡ ቅዳሜ የምትቆጠረው ከዐሠርቱ ቃላት ነው፡፡ እንዴት ተሻረች ይባላል የሚል ካለ? "አክበር ሰንበቶ ስለ በማለቱ እሑድን ተካ እንጂ ከዓሠርቱ ቃላት አልጎደለም፡፡ አንድ ምሳሌ ጥቀስ አንድ ሰው አንድ ብር ተበድሮ ይሄዳል ተመልሶ የሰጠኝ እንደሆን ጎደለ ያሰኛል? ወይም ብሩ ጎደለ ይባላል አይባልም፡፡" እንደዚሁም በቅዳሜ ፈንታ እሑድን ተካባት እንጂ አላጎደላትም "ሠለስቱ ምእትም" "ወሠዓራ ለሰንበተ አይሁድ ወሠርዐ ህየንቴሃ ዕለተ እሑድ ቅድስት" ስለ ቅዳሚት ፈንታ እሑድን ሠራ መላው በዓል ተተክቶበታል ማለት ነውሰው ግን በልማድ እሺ አይልም፡፡ በሕንጻ መነኮሳት ዓመት እስከ ዓመት ጾም እንድትጾም አዘውባታል፡፡ "ወኢይደሉ ይጹሙ በዕለተ ቀዳሚት ሰንበት እስከ ዕርበተ ፀሐይ አው እስከ ስድስቱ አው እስከ ሰብዓቱ ሰዓት" በቀዳሚት ሰንበት እስከ ዕርበተ ፀሐይ ወይም እስከ ስድስት ወይም እስከ ሰባት ሰዓት በልቶ ቤተ እግዚአብሔር ሲያገለግል ይደር ተብሎ ተሠርቷል፡፡"

ሠለስቱ ምእትም በሃይማኖተ አበው "ኢይደልዎሙ ከመያጽርኡ ተገብሮ በዕለተ ቀዳሚት ሰንበት ከመአይሁድ፡፡"

ክርስቲያኖች በዕለተ ቀዳሚት እንደ አይሁድ ሥራ መፍታት አይገባቸውም፡፡ ጌታችንም ሲያስተምር ደቀ መዛሙርቱ እሸት ቀጥፈው ሲበሉ ፈሪሳውያን "ርኢ ዘይገብሩ አርዳኢከ ዘኢይከውን ገቢረ በዕለተ ሰንበት" ደቀመዛሙርቶችህ በዕለተ ቀዳሚት ሰንበት ሊደረግ የማይገባውን ሲያደርጉ አታይምን" ብለው ቢጠይቁት ጌታም ሲመልስ ለምን ነው እሸት አሽተው ቢበሉ የምትፈርድባቸው? "ሶበሰ ተአምሩ ምንት ውእቱ ዘይቤ ምፅዋተ አባደር እመሥዋዕት እምኢኰነንክምዎሙ ለእለ ኢይኤብሱ እስመ እግዚአ ውእቱ ለሰንበት ወልደ እጓለ እመሕያው" "ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም፡፡ያለው ምን እንደ ሆነ ብታውቁስ ኃጢአት የሌለባቸውን ሐዋያትን ባልኮነናችኃቸው ነበር" የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና ብሎአቸዋል፡፡ ማቴ. 12

ቀጥሎ ደግሞ እነሱ መንገድ አይሄዱም ጌታ ግን "ወበውእቱ መዋዕል ወፈረ ኢየሱስ በሰንበት ማዕከለ ገራውኅ" በዚያው ወራት ኢየሱስ በሰንበት ከእርሻ መካከል ሲያልፍ ደቀ መዛሙርቱ እየሄደ እሸት ይቀጥፉ ነበር፡፡ ማቴ. 2፡23

በዮሐንስ ወንጌል "አኮ ዘይሥዕር ሰንበተ ባሕቲቶ ዓዲ አባሁ ይሬስዮ ለእግዚአብሔር..." ሰንበትን ስለሻረ ብቻ አይደለም ነገር ግን ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ እግዚአብሔር አባቴ ነው ስለ አለ... ወኢያብኡ ጾረ ክቡደ ውስተ ኀዋኅዊሃ ለኢየሩሳሌም በነፍስክሙ /ኤርምያስ/ ያለውን ይዘው በሰንበት አይሸከሙም፡፡

ጌታ ግን ሰላሳ ስምንት ዘመን የታመመውን መጻጉዕን "ንሣዕ ዓራተከወሑር" "አልጋህን ተሸክመህ ሂድ" አለው፡፡ አልጋው የብረት ነው፡፡ አልጋውን ተሸክሞ ሄዷል፡፡

ጌታ ሠዓሬ ሰንበት የተባለበትን ዕለት አከብራለሁ ማለት ያው የአይሁድ ረዳት መሆን ነው፡፡ "ይከውንኬ ገቢረ ሠናይ በሰንበት" በቀዳሚት ሰንበት በጎ ሥራ መሥራት ይገባልን፡፡ "ሠናይ" እርሻ ብሎታል፡፡ ወአትሐተ መትከፎ ከመይትቀነያ "ይትጌበራ" ያለውን ሠናይት አላት፡፡ አንዳንድ ደግሞ ቅዳም ሥዑር የተባለው ዲያብሎስ የተሻረበት ነው በማለት የሚናገሩ አሉ፡፡ የዲያብሎስ መሻር ከዚህ ጋር የሚገናኝበት የለም፡፡ ዲያብሎስ የተሻረ ዓርብ ዕለት ነው፡፡ ወተርፈ ውሳጤ ነፋሳት ዘኢይክል ያንቀልቅል ወዲያና ወዲህ ማለት ዲያብሎስ አቅቶት ተሰቅሎ የዋለ ዓርብ ዕለት ነው እንጂ ቅዳሜ ዕለት አይደለም፡፡

ካህናት ቤተ ምዕመናን እየዞሩ ለምን ቄጤማ ያድላሉ?

ካህናት በቅዳሜ ሥዑር ነግህ /ጧት/ በየቤቱ እየዞሩ ቄጤማ /ግጫ/ የሚያድሉበት ምሳሌ አለው፡፡ ማየ አይኅ በወረደ ጊዜ መርከቢቱ እየተንሳፈፈች አራራት ላይ አረፈች፡፡ ኋላ ኖኅ ርግብን ላካት ግጫ ይዛ መጣች፡፡ የምሥራች ውሃው ደረቀ ስትል፡፡ ያ ቀደም ብሎ የተላከው ቁራ ከዚያው ቀረ የሰይጣን ምሳሌ፣ ርግብ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ፣ ግጫው፣ ውሃው ጐደለ ና ከመርከብ ውጣ ብላ ሰጠችው፡፡ እኛ ደግሞ የምሥራች መርገመ ኃጢአት ተሽሮ፣ ሞተ ነፍስ ጠፍቶ፣ ባሕረ እሳት ተከፍሎ፣ ነፍሳት ገነት ገቡ፣ ሰው ከፈጣሪው ጋር ታረቀ፣ ዲያብሎስ ተሻረ፣ "ገብረ ሰላመ በደመ መስቀሉ" እያልን ቄጤማ ይዘን የምሥራች እንናገራለን፡፡

ገብረ ሰላመ

ገብረ ሰላመ ማለት ሰባቱ መስተ ጻርራንን አስታረቀ ማለት ነው ሰባቱ መስተጻርራን የተባሉት ሰውና እግዚአብሔር፣

ሰውና መላእክት፣

ሕዝብና አሕዛብ፤

ነፍስና ሥጋ፣ እነዚህ ለ5500 ዘመናት ተለያይተው ይኖሩ ነበር፡፡ "ወነሠተ ዓረፍተ እንተ ጽልእ በሥጋሁ" አባቱን መሰተጻርራን አስታረቀ ሲል "ገብረ ሰላመ" ሰላምን አደረገ አለ፡፡ ሰውና እግዚአብሔር በአዳም ምክንያት ተጣልተው ስለነበር፡፡ ሰውና መላእክትም መላእክት ነፍሳትን ወደ ገነት አያገቡም ነበር ወደ ሲኦል እንጂ፤ ወደ ገነት የሚገባ አልነበረም፡፡ ዛሬ ግን የጻድቅ ነፍስ መላእክት በይባቤ ይዘዋት ወደ ገነት ሲገቡ በመዓዛ ገነትን ትለያለች፡፡

ሕዝብና አሕዛብ "ኢይባእሞአባዊ ወአሞናዊ" "ሞአባዊእና አሞናዊ አይግባ" ባለው መሠረት ከአብርሃም ልጆች በቀር ቤተ መቅደስ አያስገቡም ነበር፡፡ አሁን ግን "ዘአምነ ወዘተ ጠምቀ ይድኅን" የአመነና የተጠመቀ ይዳን ብሎ ለመላው ለአዳም ልጅ ድኅነቱን ሰጥቷል፡፡

ነፍስና ሥጋ ዲያብሎስ ነፍሳትን በሲኦል ተቆራኝቼ እኖራለሁ ሲል ከሲኦል አወጣበት፡፡ ሥጋም አበስብሼ አስቀራለሁ ብሎ ነበር፡፡ ጌታ አምስት መቶ ቢጽን አስነሳበት፡፡ "ተነሥአ እግዚእነ ከመይምሐረነ በተንሥኦ ሥጋቲነ" እንዲል የእኛን ትንሣኤ በእሱ ትንሣኤ አስረዳን፡፡

ትንሣኤ ክርስቶስ

ስለ ክርስቶስ መነሣት አስቀድሞ ትንቢት ተነግሯል፡፡ ይህም ዳዊት "ይትነሣዕ እግዚአብሔር ወይዘረው ጸሩ ወይጉየዩ ጸላዕቱ እምቅድመ ገፁ" እግዚአበሔር ያነሣ፣ ጠላቶቹም ይበተኑ፣ የሚጠሉትም ከፊቱ ይሽሹ፡፡ መዝ. 67፡1 "ወተንሥአ እግዚአብሔር ከመዘንቃህ እምንዋም ወከመ ኃያል ወኅዳገ ወይን ወቀተለ ፀሮ በድኅሬሁ" እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ የወይን ስካር እንደተወው እንደኃያል ሰው ጠላቶቹንም በኋላቸው መታ መዝ. 77፡65

በደቂቀ ነቢያት፡- በሠኑይ ዕለት ይቀስፈነ ወበሠሉስ መዋዕል ይሠርየነ ወየሐይወነ አመሣልስት ዕለት ይትነሣእ ወንቀውም ምስሌሁ፡፡ በኦሪት አንበሳ ዕጓለ አንበሳ ሰከብከ ዕርግ እምንዝኅትከ እየተባለ በብሉይ በሐዲስ በብዙ ዓይነት ተነግሯል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን በሞቱ ድል አድርጎ ተነሣ ማለት መግነዝ ፍቱልኝ፣ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል ዝም ብሎ ድንጋዩ እንደ ተገጠመ ተነሥቶ ሄደ፡፡ ከዚያ በማርቆስ ወንጌል እንደተጻፈው ሴቶች ወደ መቃብሩ ሂደው "መኑ ይከሥትለነ" "ድንጋዩን የሚገለብጥልን ማነው?" ሲሉ መላእክት አነሱላቸው፡፡ /ማር. 16፡1-8፤ ማቴ. 28፡1-8 ሉቃ. 24፡1-10 ዮሐ. 20፡1/

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቆሮንቶስ ክታቡ "ክርስቶስ ላንቃላፉት በኵር ሆኖ ተነሥቷል፡፡" ይላል ይህም ማለት መጀመሪያ ትንሣኤ ዘጉባኤ የተነሣ እሱ ነው፡፡ ሌላ ገና አፈር ሆኖ ለመነሣት ዕለተ ምጽአትን ይጠብቃል "ተነሥአ እግዚእነ ከመይምሐረነ በተንሥኦቱ እንከሰ ዳግመ ኢይመውት" ከእንግዲህ ወዲያ ሁለተኛ አይሞትም" እነ አልአዛር ቢነሱ ተመልሰው ሞተዋል፣ ትንሣኤ ዘጉባኤን ይጠብቃሉ፡፡

ጌታችንና እመቤታችን ግን ተመልሰው አይሞቱም እንዲህ ያለው ትንሣኤ ዘጉባኤ ይባላል፡፡"ቀደመ ተነሥኦ እምኲሉሙ ሙታን" ከሙታን አስቀድሞ ተነሣ የተባለው ስለዚህ ነው፡፡ እስከ አሁን ሁለቱ ብቻ ናቸው ትንሣኤ ዘጉባኤ የተነሡት፡፡ ከዚህ ጋር አብሮ ሊታይ የሚገባው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን እንደተነሣ ማርያም መግደላዊነት ቀርባ ልትነካው ባሰበች ጊዜ ገና ወደ አባቴ አላረኩምና አትንኪኝ ብሎ እንደነገራት በዮሐንስ ወንጌል ተጽፎ እናገኘዋለን፡፡ የዚህ ዋና ትርጉሙ ጌታችን ሴት እንዳትነካው /ንቆ/ ሳይሆን ማርያም መግደላዊት የሚያርግ መስሏት ስለነበር ገና 40 ቀን እቆያለሁ ለማለት ነው፡፡

ወንጌላዊው ዮሐንስ በሌላ ምዕራፍ "አኅዛ እገሪሁ ወሰገዳ ሎቱ" እግሮቹን ይዘው ሰገዱለት ይላል፡፡ አሁንም በዚሁ ምዕራፍ 20 ቁጥር 24 "ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ዲዲሞስ የሚባለው ቶማስ ኢየሱስ በመጣ ጊዜ ከእነርሱ ጋር አልነበረም ምልክት ከእጆቹ ካላየሁ ጣቴንም በችንካሩ ምልክት በጎኑ ካላገባሁ አላምንም" ማለቱን ያስረዳል፡፡ በእርግጥ ቶማስ ጌታ ከሙታን ተነሥቶ በዝግ ቤት ገብቶ ለቀደ መዛሙርቱ ሰላም ለእናንተ ይሁን ሲላቸው አልነበረም በዚህም ምክንያት ተጠራጥሮአል፡፡

ጌታ ደግሞ ለምን ተጠራጠርክ ካልዳሰስኩህ አላምንም ብለሃል፡፡ በልና የተወጋው ጎኔን እይ፤ የተቸነከረው እጄን ተመልከት፡፡ ብሎ እንዲዳስሰው ፈቀደለት፡፡ ቶማስም ሲዳስስ እሳተ መለኮት ቀኝ እጁን አቃጠለው፡፡

"እግዚእየ ወአምላኪየ" ፈጣርዬ አምላኬ አምላኪየ "መዳሰሱ ሲያይ" እግዚእየ ማቃጠሉን ሲያይ አምላኪየ አለ፡፡ ይኸንን "እግዚእየ ወአምላኪየ" ያለውን ወስዶ በሃይማኖተ አበው "አንተ ቀዳማዊ ወአንተ ዳኅራዊ" አንተ መጀመሪያ አንተም መጨረሻ ነህ ብሎ ተርጉሞታል፡፡

ይህች ገቦ መለኮት የዳሰሰች እጅ ሳትሞት ሕያዊት ሆኖ በሕንድ ሀገር ከታቦት ጋር ትኖራለች፡፡ ጥር 21 ቀን የአስተርእዮ ዕለት በዓሉ ይከበራል፡፡ ይህ ታሪክ የሚገኘው መጽሐፈ እንድልስ በሚባለው ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድም "ይትፌሣሕ ሰማይ ወትተሐሰይ ምድር ወይንፍሑ ቀርነ መሠረታተ ኅምዝ" ያለው ትሑታኑ ደቂቀ አዳም ልዑላኑ መላእክት ጌታ አስታረቃቸው ሁሉም ደስ አላቸው ማለቱ ነው ሰማያውያንና ምድራውያን በክርስቶስ አንድ ሆኖአልና፡፡ "ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሐጺባ በደመ ክርስቶስ" "ምድርም በክርስቶስ ደም ተቀድሳ የክርስቶስን ትንሣኤ ታከብራለች"፡፡

አንድም ያመኑ ምዕመናን ሁሉ በክርስቶስ ደም ነጻ ወጥተው በዓለ ትንሣኤን ያከብራሉ መጽሐፍ ለግዕዛን ሰጥቶ መናገሩ የተለመደ ነው፡፡

"ትባርኮ ምድር ለእግዚአብሔር" ምድር እግዚአብሔርን ታመሰግናለች ይህ ማለት ማኅበረ ምዕመናን እግዚአብሔር ያመሰግኑታል ማለት ነው፡፡ ክብር ምስጋና ይግባውና መድኃኔዓለም ክርስቶስ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር በመቆየት ሙስና መቃብርን አጥፍቶ፣ ሞትን ድል ነስቶ ተነሥቶልናል፡፡

ሠሉስ መዋዕለ ወሠሉሰ ለያልየ

የሚለው በሰዓት ሲቆጠር አይሞላም ይህ እንዴት ነው? ቢሉ? እንግዲህ ጌታ በምሴተ ኀሙስ ሦስት ሰዓት አሳልፎ ነው መከራ መቀበል የጀመረ፡፡ ሥጋወደሙ ለሐዋርያት የሰጣቸው በዕለተ ኃሙስ ነው፡፡

ስለዚህ "መዓልት ይስሕቦ ለሌሊት፣ ወሌሊት ይስሕቦ ለመዓልት" "ቀን ሌሊቱን ይስበዋል፣ ማለት መዓልተ ዓርብ ሌሊተ ኀሙስን፣ መዓልተ እሑድ ደግሞ ሌሊተ እሑድን ሲስበው፣ ቅዳሜ መዓልትና ሌሊት ሲቀመር ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት የተባለው ይኸ ነው፡፡"

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

መምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ኃላፊ

አዲስ አበባ

ኢትዮጵያ

የፎንት ልክ መቀየሪያ