Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ገብረ ሰላመ በደመ መስቀሉ

በብፁዕ አቡነ ገሪማ

ጌታችን መደኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማዕከለ ምድር ቀራንዮ ጎልጎታ፤ ኢየሩሳሌም ተሰቅሎ ባፈሰሰው ደሙ ሰላምን አደረገ ይላል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ (ኤፌ.2፡14-15 ፤ ቈላ. 1፡20)

ይህ በየዓመቱ በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት የምናከብረው የምሥራች በዐል፣ ዓመተ ፍጻው፣ ዓመተ ኩነኔው አክትሞ የሰው ዘር ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከኃጢአት ወደ ስርየት፣ ከሲኦል ወደ ገነት የተመለሰበትና የተሻገረበት ዕለት መሆኑን ለማዘከር ነው፡፡ ይህንም የሰው ሕይወት የታደሰበትን ሰላማዊና መንፈሳዊ በዐል የምናስበው በየዓመቱ ከምናስበው ከምናከብረው ከዕለተ ስቅለተ ዓርብ ማታ ጀምሮ ነው፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ከሰርከ ሆሣዕና እሰከ ዕለተ ትንሣኤ ያለው ሰሙነ ሕማማት አዳም የፈጣሪውን ትእዛዝ በተመላለፉ በሲኦል ተጥሎ ወድቆና ተረግጦ የኖረበትን አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን፣ ዓመተ ፍዳ፣ ዓመተ ኵነኔ የሆነበትን፤ በዚሁ መሠረት ከጧቱ ከመነሻው እግዚአብሔር አምላካችን በገባው ቃል ኪዳን፤ ስለሰው ልጆች ድኅነት ብሎ የተቀበለውን ጸዋትወ መከራ ዕሥራቱን፤ ግርፋቱን፤ እንግልቱን፤ ስቅለቱንና ሞቱን የምናስብበት ጊዜ ነው፡፡

ይህ ሳምንት ከሆሣዕና እሑድ ዋዜማ ጀምሮ እሰከ በዐለ ትንሣኤ ድረስ ያለው ሳምንት በየዓመቱ ግብረ ሕማማቱ የሚከርበት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

መለስ ብለን የሥነ ፍጥረትን ታሪክ ስንመለከት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው የፈጣሪና የፍጡር ግንኙነት የተቋረጠው የሰው ልጅ የፈጣሪውን ትእዛዝ ከተላለፈበት ጊዜ አንሥቶ መሆኑን እንረዳለን፡፡

አዳም በሥላሴ አርአያና አምሳል ተፈጥሮ ጸጋ እግዚአብሔርን ተጐናጽፎ ነፃ የኅሊና ፈቃድ ያለው ሰው ሁኖ ገነትን ያህል ቦታ ይዞ ሥዩመ እግዚአብሔር፣ ነቢየ እግዚአብሔር ካህነ እግዚአብሔር ሆኖ በገነት ይኖር ነበር፡፡

"እግዚአብሔር ያደረገውን ሁሉ አየ፤ እነሆም እጅግ መልካም ሆነ" /ዘፍ. 1፡31/ ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንደምንረዳው እግዚአብሔር አምላካችን በስድስቱ ቀናት የፈጠረው ሁሉ መልካም ሲሆን በተለይም በሥላሴ አርአያና አምሳል ለተፈጠረው ሰው የሕይወት እስትንፋሱን ሰጥቶ በገነት በሕያውነት እንዲኖር ያስቀመጠው ክቡር ፍጡር ነበር፡፡ "ሰብእሰ እንዘ ክቡር ውእቱ ኢያእመረ ወኮነ ከመ እንስሳ ዘአልቦ ልብ ወተመሰሎሙ"ሰው የከበረ ክቡር ሆኖ ሳለ አላወቀም፤ ማሰብ እንደማይችሉት አእምሮ እንደሌላቸው እንደ እንስሳት ሆነ ይላል ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት፡፡ /መዝ. 48፡12/

እግዚአብሔር የሰውን ልጅ የስሙ ቀዳሽ፤ የክብሩ ወራሽ አድርጎ ቢፈጥረውና የጸጋ ገዥ ቢያደርገው የፈጣሪ እንጂ የፍጡር ባህርይ ያልሆነ አምላክነትን በመፈለጉ የገዥና የተገዥ፤ የፈጣሪና የፍጡር ምልክት የሆነውን ትእዛዘ እግዚአብሔርን በመጣሱ በዚሁ ምክንያት ሞተ ሥጋ፣ ሞተ ነፍስ ተፈረደበት፡፡ ከክብሩ ተዋርዶ ከገነት እንዲወጣ ተደረገ፡፡ ተመልሶ ወደ ገነት ገብቶ ተጨማሪ ኃጢአትን እንዳይሠራም ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውን መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍ ሜሎስን በኤደን ገነት ምሥራቅ አስቀመጠ ይላል የእግዚአብሔር ቃል፡፡ /ዘፍ. 3፡22-24/

አዳም ሳይቸገር፣ ሳይቸግረው በጠላት ከንቱ ስብከት እንደ እግዚአብሔር ለመሆን ክፉውንና ደጉንም ፈጥኖ ለማወቅ ቸኩሎ ትእዛዘ እግዚአብሔርን በማፍረሱ ወደቀ፤ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ፡፡ በሰው ሕይወት ላይ አሳፋሪ፣ አስፈሪና አስነዋሪ ታሪክ ፈጸመ፡፡ አዳም "እግዚአብሔር አታድርግ" ያለውን የአምላኩን ትእዛዝ በማፍረሱ የሞት ሞት ተፈረደበት፡፡

ነቢዩ ሕዝቅኤል "እነሆ ነፍሳት ሁሉ የእኔ ናቸው፡፡ የአባት ነፍስ የእኔ እንደሆነች ደግሞ የልጅ ነፍስ የእኔ ናት ኃጢአትን የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች" /ሕዝ. 18፡4/ በማለት የዚህን ማስጠንቀቂያ ኃይለኛነትና ጥብቅነት ያሳያል፡፡

ይሁንና ቀዳማዊ አዳም በስሕተቱ ተጸጽቶ በማዘኑ፣ በማልቀሱና ንስሐ በመግባቱ ቸርነቱ ወሰን የሌለው አምላክ ንስሐውን ተቀብሎ የተስፋ ቃለ ሰጠው፡፡ የተሰጠውም የተስፋ ቃል "አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ ሥጋዬን ቆርሼ፣ ደሜን አፍስሼ አድንኃለሁ" የሚል ነበር፡፡

ይህ የተስፋ ቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ፤ ትንቢት ሲነገር ሱባኤ ሲቆጠር ኖሮ አምስት ሺህ አምስት መቶ የተስፋው ዘመን ሲፈጸም የተናገረውን የማይረሳ፣ የሰጠውን ተስፋ የማይነሣ እግዚአብሔር "ክርስቶስኑ መጽአ በዕድሜሁ ይሙት በእንተ ኃጢአትነ እንዘ ኃጥአን ንሕነ" /ሮሜ. 5፡6/ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ጊዜው ሲደርስ በጊዜው ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሰው ልጅ ኃጢአት ሊሞት መጣ፤ ሰው ሆነ፤ በሥጋም ተወለደ በተወለደ በ30 ዘመኑ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠመቀ፤ ዕለቱን ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ ዓርባ መዓልት፤ ዓርባ ሌሊት ጾመ፤ ተራበ በሰይጣን ተፈተነ፤ ፈታኙ ሰይጣንም ድል ተመታ፡፡ ሦስት ዓመታት ከሦስት ወራት በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም እስራኤል ማለት በገሊላ፤ በሰማርያና በይሁዳ አውራጃዎች እየተዘዋወረ ወንጌለ መንግሥተ ሰማያትን አስተማረ፡፡ ትምህርቱ እየሰፋ ሲሔድ የተነገረውን ትንቢት ለመፈጸም ለሕማም፤ ለሞት፣ በክብር ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ በሥጋ ተሰቀለ፣ በሥጋ ሞተ፣ ተቀበረ፣ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ በመነሣት ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ ሞተ ኃጢአት፣ ሞተ ነፍስ ድል የሆነው ድል የተመታው፣ መጋቢት 27 ቀን 34ዓ.ም ሰርከ ዕለተ ዓርብ ሲሆን ሞተ ሥጋም የተሸነፈው መጋቢት 29 ቀን 34ዓ.ም በክርስቶስ ትንሣኤ ዕለተ እሑድ ነው፡፡

ክርስቶስ ከተሰቀለበት መስቀል አናት "ኢየሱስ ናዝራዊ ንጉሠ አይሁድ" የሚል የክስ ጽሑፍ በዕብራይስጥ በፅርዕና በሮማይስጥ ተጽፎ ተለጥፎ ነበር፡፡ /ማቴ. 27፡37/ የእነዚህ የሦስቱ ወገን ቋንቋዎች የሥልጣኔና የጥበብ ኃይል በአንድነት ቢተባበሩም የክርስቶስን ኃይል ሊቋቋሙት አለመቻላቸው በግልፅ ታይቷል፡፡

ጌታችን መድኃኒታን ኢየሱስ ክርስቶስ የሞት መደምሰሻ፣ የሰይጣን ድል መነሻ፣ የድኅነት ጋሻ ያደረገው መስቀል በክርስትና ሕይወት የላቀ ክብርና ቦታ ያለው ሆነ:: የዓለሙን ሁሉ ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚእብሔር በግ ስለእኛ መከራን ተቀብሎ፤ ከኃጢአት ቀንበር ነጻ አወጣን፤ ከሰይጣንም እጅ በክብር ደሙ፣ መድኃኒት በሚሆን መስቀሉ አዳነን፡፡

መስቀል ኃይላችን ነው፤ መስቀል ጽናችን ነው፤ መስቀል ቤዛችን ነው፤ መስቀል የነፍሳችን መድኃኒት ነው፤ መስቀል መከታችን ነው፤ መስቀል ፍቅራችን ነው፤ መስቀል ሰላማችን ነው፤ መስቀል አርማችንና ጉልበታችን ነው፣ መስቀል ሕይወታችን ነው፤ መስቀል የነፃነታችን፤ የድላችን ምልክት ነው፤ "በዝ ትእምርተ መስቀል ትመውእ ጸረከ" የሚል በሦስተኛው መቶ ዓመት በጸፍጸፈ ሰማይ የተፈጸመ ተአምራታዊ ድርጊት ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማዕከለ ምድር ቀራንዮ በመሰቀል ላይ ተሰቅሎ ደሙን አፍስሶ፤ ሥጋውን ቆርሶ የሰውን ሕይወት ወደቀደመ ቦታው ከመለሰ ወዲህ መስቀል ቅዱስና ክቡር የሚለውን ስያሜ አግኝቶ የክብርና የበረከት፤ የሕይወትና የመዳን ምልክት ሆኖ ይገኛል፡፡

በዚሁ መሠረት በዐለ መስቀሉን በየዓመቱ በዚህ ሁኔታ በማክበር ላይ የምንገኘው በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለንን የጸና እምነት ለመግለጥና ድርጊቱን ለመዘከር ነው፡፡

ስለዚህ በመስቀሉ የተገኘውን ሕይወት ሰላም፤ ነፃነትና ክብር ጠብቆ በፍቅር አንድነት መኖር ነው፡፡

ቅድስት ድንግል ማርያምን ከገሊላ አውራጃ ከናዝሬት ከተማ ወደ ይሁዳ አውራጃ ወደ ዳዊት ከተማ ቤተልሔም ምድረ ኤፍራታ የወሰዳት የሮማዊው የአውጋስጦስ ቄሣር የሕዝብ ቆጠራ ትእዛዝ ሲሆን (ሉቃ. 2፡1-3) እንደ ይሁዳ አስተሳሰብ የክርስቶስ ስቅላት የተካተተውም ሮማዊው እንደራሴ ጲላጦስ "እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ እናንተ ተጠንቀቁ" በማለት በሕዝቡ ፊት እጁን በውሀ ታጥቦ በሰጠው ኢሕጋዊ ትእዛዝና ፍርድ ነበር፡፡ (ማቴ. 27፡24)

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከገማልኤል የተማረ የሕግ ሰው እንደመሆኑ ወገኖቹ አይሁድ በኢየሩሳሌምና በቂሣረያ-ሰማርያ አድበስብሰው ሊገሉት በወሰኑ ጊዜ የሮሜ ዜግነት ያለው በመሆኑ በሮማዊ ዜግነቱ ተመክቶ ያለአግባብ የተፈረደበትን በይግባኝ እንዲያይለት ወደ ሮሜው ቄሣር ይግባኝ ብሎ በእሥረኛነት ወደ ሮሜ ከተማ ደርሶ ለሁለት ዓመታት ያህል በሮሜ በማስተማር ቆይቶ ቄሣር ኔሮን ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ሁለቱም በሮም አደባባይ እንዲገደሉ አድርጓል፡፡ (የሐዋ. 25፡11-13)

ከዚህ አንጻር የሮማውያን ሕግ አዋቂነትና አስከባሪነት ደካማ፤ የግሪኮችም ፍልስፍና ፍሬ ቢስ፤ የአይሁድ ሃይማኖታዊ ሥርዓትም ከሁሉም የተራቆተ መሆኑን እንመለመከታለን፡፡

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ሦስቱ ኃይላትም አቋማቸውን አጠናክረው በኃይላቸው ተመክተው ለጊዜው ድል የሚያደርጉ መስለው ቢነሡም ከጊዜ በኋላ ፈርሰውና ወድመው ሲቀሩ ክርስቶስ ግን በሚወዱትና በሚያፈቅሩት ተከታዮቹ ልብ ለዘለዓለም የማይፈርስ ወንጌለ መንግሥተ ሰማያትን ለመመሥረት ችሏል፡፡

ይህም ወንጌለ መንግሥተ ሰማያት እስከ ዓለም ፍጻሜ ሲሰበክ ይኖራል፡፡ "ሰማይ ወምድር የኅልፍ፤ ወቃልየሰ ኢየኅልፍ" ሰማይና ምድር ያለፋል፤ ቃሌ ግን አያልፍም (ማቴ. 24፡35) ይላል የእግዚአብሔር ቃል፡፡

እስመ ነገረ መስቀሉሰ ዕበድ ውእቱ በኀበ ኅጉላን

ወበኅቤነሰ ለእለ ድኅነ ኃየለ እግዚአብሔር ውእቱ

የመስቀሉ ቃል፤ የመስቀሉ ነገር ለሚጠፉት ሞኝነት፤ ለእኛ ለምንድነው ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና ይላል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ (1ቆሮ. 1፡18) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመስቀሉ ነገር የእግዚአብሔር ኃይልና ጥበብ እንደሆነ ያስተምረናል፡፡

የመስቀሉ ነገር ሞኝነትና ኃይል በሆነላቸው ሰዎች መካከል እንደመለኪያ ያለ ነገር ይሆናል ማለት ነው፡፡ ለአይሁድ የመርገም፣ ለአማልክት አምላኪዎች የሞኝነት ለክርስቶስ ወገኖች የእግዚአብሔር ኃይል የሆነውን የመስቅሉን ትርጉም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ያስተማረው በሁለተኛው ሐዋርያዊ ጉዞ በፊልጵስዮስ፣ በመቄዶንያ፣ በተሰሎንቄ፣ በአቴና አድርጎ ወደ ቆሮንቶስ ደርሶ በዚያ ቆይታው ጊዜ ነበር፡፡

ኃይለ እግዚአብሔር የሆነው የመስቀሉ ታሪክ የተመሠረተው መጋቢት 27 ቀን 34ዓ.ም በማዕከለ ምድር ቀራንዮ ጎልጎታ ነው፤ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባም ጥምቀተ ክርስትናውን በወንጌላዊ ፊልጶስ የተጠመቀው ከኢየሩሳሌም በስተደቡብ ወደ ጋዛ በሚወስደው መንገድ በ34 ዓ.ም ነው፡፡

እግዚአብሔርሰ ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም፤ ወገብረ መድኃኒተ በማዕከለ ምድር......"እግዚአብሔር ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፤ በምድር መካከልም መድኃኒትን አደረገ" ይላል ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት /መዝ. 73፡12/

ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ማዕከለ ምድር ያለው ቀራንዮ ጎልጎታን ነው፤ ምክንያቱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ቦታ በተተከለው መስቀል በሥጋ ተሰቅሎ በሥጋ ሞቶ ዓለምን ያዳነ፤ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለቱ፤ የመቃብሩና የትንሣኤው ቦታ ቀራንዮ ጎልጎታ ማዕከለ ምድር በመሆኑ ነው፡፡

ይህም ጌታችን መደኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጋቢት 27 ቀን 34ዓ.ም በዕለተ ዓርብ በዕፀ መስቀል የተሰቀለበት፤ በሥጋ የሞተበትና የተቀበረበት በይቀጥላልም ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር ውሎና አድሮ መጋቢት 29 ቀን 34ዓ.ም በዕለተ እሑድ የተነሣበት ነው፡፡

ቀራንዮ ጎልጎታና የቀሩትም ቅዱሳት መካናት የሆኑት ሁሉ እስከ ታላቁ ቄስጠንጢኖስ መነሣት ድረስ ማለት እስከ ዐራተኛው መቶ ዓመት ድረስ እንዴት እንደነበሩ መናገሩ ይከብዳል፤ ጊዜንም ይጠበቃል፡፡

የክርስቶስ ቅዱስ መስቀል መጋቢት 27 ቀን 34ዓ.ም በዕለተ ዓርብ ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ድል የተነሣበት ሆነ፡፡ እንኳን አማናዊው የክርስቶስ መስቀለ ይቅርና የእርሱ ምሳሌ የሆነው፤ ሙሴ ከእግዚአብሔር መመሪያን ተቀብሎ በምድረ በዳ የሰቀለው ዛሬ እንደንዋየ ቅድሳት የተቈጠረው በፓትርያርኮች፤ በሊቃነ ኤጲስ ቆጶሳት ወኤጲስ ቆጶሳት የሚያዘው አርዌ ብርት እንኳ ሳይቀር ብዙ ተአምራትን ሠርቷል፡፡ በዚያ በዓርባ ዘመናቱ የእስራኤላውያን የበረሀ ጉዞ በቆላተሐራሴቦን እባብ የነደፈው እስራኤላዊ ሁሉ በአላማ ላይ የተሰቀለውን የናሱን እባብ በእምነት በተመለከተ ጊዜ ሕይወቱን አግኝቷል፡፡ ከደዌው ተፈውሷል፣ ከኅዘኑ ተጽናንቷል፡፡ /ዘኁቁ. 21፡6-9/ ይህን ያህል ተአምር የሠራው ያ የመስቀለ ክርስቶስ ምሳሌ የነበረው ነው፡፡ ይሁንና ከላይ ከተጠቀሰው ዕለትና ዓመተ ምህረት ወዲህ መስቀል የተፈተነ መድኃኒት በመሆኑ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በመስቀል ይመካል፤ መስቀልን ይሸከማል፤ በአንገቱም ያደርገዋል፡፡ ካህን የሆነው ሁሉም በእጁ ይይዘዋል፡፡ መስቀል ለመጀመሪያ ጊዜ በሰው አንገት መንጠልጠል የቻለው ታዳጊነቱ ከታወቀ ወዲህ ነው፡፡ እየቆየ የታዳጊነቱ ኃይል ሳይሻር ጌጥነትም ስለአለው ትንሹም ትልቁም፤ ወንዱም ሴቱም ያጌጥበት ጀመር፡፡ ሁሉም የመስቀልን ክብር፣ ኃይል ሲናገር መስቀል ኃይላችን ነው፤ መስቀል ግርማችን ነው፤ መስቀል ጽናችን ነው፤ መስቀል ታዳጊያችን ነው፡፡ እኛ በመስቀሉ ኃይል አምነናል፤ ያመነውም ሁሉ እንድናለን እያሉ ተአምራቱን ይናገራሉ፤ ክብሩንም ይገልጣሉ፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት፣ እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከመድኃኒችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ ይላል /ገላት. 6፡14/

ይህ ከዚህ በላይ የሰማነው ትምህርት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በስህተት ትምህርት ለተወናበዱት የገላትያ ሰዎች ትክክለኛውን የክርስትና እምነትና ሕይወት ለማሳወቅ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

እኛም ስለነገረ መስቀሉ መናገር ያለብን በሐዋርያው ብቅዱስ ጳውሎስ ዘይቤ መሆን አለበት፡፡

ከዚህ በላይ እንደተገለፀው መስቀል በክርስትና ሕይወት ከፍተኛ ክበርና ቦታ ስላለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በራሷ ኪነ ጥበብ በተዘጋጀው መስቀል ምእመናንን ስታገለግልበት፣ ስትገለገልበት ትገኛለች፡፡

ዛሬ የምናከብረው በዐለ መስቀሉ ዓለም ሁሉ ክብር ያገኘበትና ከግብርናተ ዲያብሎስ ነፃ የወጣበት ስለሆነ ይህን የመንፈስ ነፃነት በዐል ስናከብር የሚሰማን ደስታ ከፍተኛ ነው፡፡

እስከ አሁን ከተነገረውም ታሪክ ጋር በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖናዊ ሥርዓት መሠረት ይህ የገብረ ሰላመ በዐል የሚታወቅበት ዋናው ምልክት በካህናት ተባርኮ፤ ካህናትን ምእመናን በራሳቸው የሚያስሩት፤ በእጃቸው የሚይዙት ለምለም ቄጤማ ነው፡፡ የቄጤማው ታሪክ ለአዳም 10ኛ፣ ለሴት 9ኛ ሐረገ ትውልድ ከሆነው ከጻድቁ ኖኅ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በዚያ ዘመን ምድር በእግዚአብሔር ፊት ተበላሽታ ታየች፤ ሥጋን የለበሰም ሁሉ በምድር መንገዱን፤ ሕይወቱን አበላሽቶ ታይቶ ነበርና፤ ስለዚህም በዚህ ጻድቅ ሰው ዘመን ኃጢአትን አብዝተው የሠሩ ሰዎችን ለመቅጣት እግዚአብሔር አምላክ ምድርን በጥፋት ውሀ ማጥለቅለቁ ይታወቃል /ዘፍ. 6-8/፡፡ ይህ የጥፋት ውሀ ባለመቋረጥ ዓርባ መዓልትና ዓርባ ሌሊት ሙሉ ከወረደ በኋላ በመጨረሻ ጊዜ ኖኅ የውሀውን መጉደልና አለመጉደል ዓይታ እንድትመጣ በመርከብ ከእርሱ ጋር ከነበሩት በራሪዎች መካከል ርግብን ቢልካት ሔዳ የውሀውን መጉደል ዓይታ ወደ እርሱ በተመለሰች ጊዜ በአፍዋ ለምለም የወይራ ቀምበጥ ይዛ በመምጣቷ፤ የውሀውን መጉደል አብሥራው ነበር /ዘፍ. 8፡11/፡፡

ከዚህ አንፃር ቤተ ክርስቲያናችን ገብረ ሰላመ በመሰቀሉ ትንሣኤሁ አግሐደ፡- እነሆ ጌታችን መደኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ሰላምን አደረገ፤ መሠረተ፣ ትንሣኤውንም በግልፅ አሳየ፤ በሲኦል ያሉ እስረኞች ተፈቱ፣ ገነት ተከፈተች፣ ዲያብሎስ ታሰረ፤ በዚህም ላይ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን መልቶ ይፈስ የነበረው ባሕረ ኃጢአት ፈጽሞ ደረቀ፤ ነጠፈ እያለች የኖኅ ርግብ አምሳል በመሆን ለምለም ቄጤማዋን ይዛ ለሰው ልጅ የተሰጠውን ጸጋ በመግለጽ ፓትርያርኩ፤ በሊቃነ ኤጲስ ቆጶሳቱ፤ በኤጲስ ቆጶሳቱና በካህናቱ እየተባረከ ለምእመናን የምሥራች መልእክቷን የምታስተላልፍበት ዋናው ምክንያት እንዲህ ያለው ታላቅ ድርጊት የተፈጸመበትን ታሪክ ይዛ ነው፡፡

እስከዚህ ድረስ እንደተገለፀው የገብረ ሰላመ በዐል የሰው ልጆች አባት ቀዳማዊ አዳም በዳግማዊ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ፍርድ ወደ ዘለዓላማዊ ሕይወት የተመለሰበት፤

 • ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከፅንሰቱ እስከ ልደቱ፤ ከልደቱ እስከ ጥምቀቱ፤ ከጥምቀቱ እሰከ ቀራንዮ ጎልጎታ ስቅለቱ፤ በሥጋ ሞቶ መነሣቱ፤ በይቀጥላልም እስከ እርገቱ ድረስ ለሰው ልጅ ያደረገውን ቸርነት የምናዘክርበት፣

 • ከእግዚአብሔር አምላካችን ለሰው ልጅ የተሰጠው ጸጋ፤ የተረጋገጠበት፤

 • በዓለም ሁሉ ሰላም የሰፈነበትና ፍጡር ከፈጣሪው ፍጹም ሕይወትን ያገኘበት ዕለት ነው ብለናል፤

ከዚህም ጋር ቤተ ክርስቲያን ለወገኖቿ ሁሉ ታላቅ የምስራች የምታበስርበት ዕለት መሆኑንም ተገንዝበናል፡፡

ስለዚህ ከመስቀለ ክርስቶስ በቀር ሌላ ሰላምን ሰጭ የለምና ይህ የሰላማችን፤ የደስታችንና የድል በዓላችን የሆነውነ በዝማሬና በውዳሴ ልናከብረው የሚገባ በመሆኑ "ገብረ ሰላመ በደመ መስቀሉ" በማለት ይኸውና በየዓመቱ በዚህ ሁኔታ በታላቅ ስነ ሥርዓት እናከብረዋለን፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ለሀገራችን፤ ለዓለሙ ሁሉ ሰላሙን ይስጥልን፡፡

ስለአዳመጣችሁኝ አመሰግናለሁ

እግዚአብሔር አምላካችን ይባርከን ይቀድሰን፡፡

 

የፎንት ልክ መቀየሪያ