Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

መስቀል ብርሃን ለኩሉ ዓለም

መ/ር ንዋይ ካሣሁን

የሰ/ት/ቤቶች ማ/መምሪያ

የትምህርት ክፍል ኃላፊ (BTH,BSN)

ልዑል እግዚአብሔር ሰውንና መላእክትን የስሙ ቀዳሾች የክብሩ ወራሾች እንዲሆኑ ለዘለአለም ክብር ቢፈጥራቸውም ከመላእክት ወገን ዲያብሎስና ሠራዊቱ በክህደታቸውና በትዕቢታቸው ያልተሰጣቸውን ክብር በመሻታቸው ከክብራቸው ተዋርደው ወዳሲኦል ወረዱ፡፡ ለክብሩ የተፈጠረውም ሰው የምድር ንጉሥ መሆኑ አልበቃ ብሎት አምላክነትን ሲሻ በዕፅ ምክንያት ከክብሩ ተዋረደ፡፡ የመጀመርያዎቹ ሰዎች አዳምና ሔዋን እንደ አጋንንት በስሕተታቸውና በትዕቢታቸው ስላልጸኑ በደረሰባቸው ቅጣት ደንግጠው ንሥሐ ቢገቡ የምህረት ቃል ኪዳን ተስፋ አገኙ፡፡ ዘፍ. 3፡22

እግዚአብሔር ለአዳምና ለሔዋን የገባውን ቃል ኪዳን ለመፈጸም ድህነተ ዓለምን ለነቢያት እየገለጸ ትንቢት እያናገረ ሱባዔ እያስቆጠረ ምሳሌ እያስመሰለ ካስረዳ በኋላ ጊዜው ሲደርስ የተጠበቀው መድኅን በቤተልሔም ከድንግል ማርያም ተወለደ፡፡ገላ. 4፡4 ከዚህም ጀምሮ ዓመተ ፍዳ ዓመተ ኩነኔ አብቅቶ ዓመተ ምህረት ዘመነ ሰላም ተጀመረ፡፡ ጨለማው ተገፎ የጽድቅ ፀሐይ ወጣ በድንቁርና በቀቢስ ተስፋ የነበረው ሕዝብ ተስፋው ለመለመ የመዳኛው ቀን ቀረበ፡፡ የሕያው እግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ሰውን ለማዳን ሰው ሆኗልና መላእክትና እረኞች በአንድነት ዘመሩ፡፡ ሉቃ. 2፡15

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን ከድንግል ማህፀን የጀመረውን ቤዛነት ሁሉ እየፈጸመ በዚህ ምድር ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወራት ቆይቶ የድህነት ዓለም ጉልላት የሆነውን የመስቀል ሞት ለመቀበል የቀጠራት ዕለተ አርብ ስትደርስ አስራ ሦስቱን የመስቀል ላይ መከራ በፈቃዱ ተቀብሎ በመስቀል ላይ ተሰቀለ፡፡ በዕፅ ምክንያት የተዋረደው የሞተውና በስኦል እስርቤት የሚማቅቀው አዳም በዕፅ አማካኝነት ወደ ቀደመ ክብሩ እንዲመለስ የዘለዓለም ሕይወት እንዲጎናጸፍ ከሲኦል እስርቤት ነጻ ወጥቶ እረፍት ወዳለበት ገነት እንዲገባ ፈቃዱ የሆነ እግዚአብሔር መስቀልን የሕይወት እንጨት /ዕፀሕይወት/ አደረገው እሾህን በእሾህ እንዲሉ፡፡ በዘመነ ኦሪት መስቀል የወንጀለኛ መቅጫ /መግደያ/ በመሆኑ በሰው ዘንድ በመጥፎነቱና በአስፈሪነቱ ይታወቃል፡፡ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የሚሞት ሰው የተረገመ የተጠላ የአመጽ ሰው ከፍተኛ ወንጀል የሰራ በመሆኑ መስቀል የሞት የርግማን የጥል የውርደት ምልክት ሆኖ ለዘመናት ቆይቷል፡፡

በአዲስ ኪዳን ግን ንፁሐ ባህርይ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሰው ድኅነት ብሎ በመስቀል ተሰቅሎ በመለኮታዊ ደሙ ከቀደሰው በኋላ ግን መስቀል የሕይወት፣ የሰላም፣ የፍቅር፣ የክብር፣ የኃይልና የቅድስና፣ የበረከት እንዲሁም የነጻነት ምልክት ሆኗል፡፡ በዚህ ሳቢያ መስቀል በክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ ሰፊ ቦታ አለው፡፡ ለክርስቲያኖች መስቀል የነጻነታቸው አርማ በተጠቁ ጊዜ ጋሻቸው ባጠቁ ጊዜ የጦር መሳሪያቸው በታመሙ ጊዜ ምርኩዛቸው በጠቅላላው ሕይወታቸው ስለሆነ መስቀል ከክርስቲያኖች ክርስቲያን ከመስቀል አይለይም፡፡

የመስቀሉ በአይሁድ መቀበር

መስቀል የእግዚአብሔር ታላቅ ኃይሉ የተገለጸበት ዲያብሎስን ያዋረደበት ምእመናንን የታደገበት የሰላም ዙፋን ከመሆኑም በላይ በእለተ አርብ ቅዱስ ሥጋው የዋለበት፣ ካሣ የተከፈለበት፣ወርቀ ደሙ የፈሰሰበት ስለሆነ እናከብረዋለን፡፡ እንሳለመዋለን፣ እንመካበታለን፡፡ የጸጋ ስግደት እንሰግድለታለን፡፡ ጌታችን የተሰቀለበት መስቀል ሙት እያስነሳ ድውይ እየፈወሰ አጋንንት እያወጣ የተለያዩ ገቢረ ተአምራት ሲሰራ ሕዝቡ አይተው ክርስቲያን እንዳይሆኑ በመፍራት በ34ዓ.ም ከኢየሩሳሌም ወጣ ብሎ በሚገኝ ቦታ ቆፍረው ቀበሩት፡፡ ከዚያም የከተማውን ቆሻሻ ሁሉ ከዚያ መስቀሉ በተቀበረበት ቦታ ላይ እየደፉ ከዘመን ብዛት ቦታው በቆሻሻ ክምር የተነሣ ተራራ ሆነ፡፡

እስራኤልን ከሮም ቅኝ አገዛዝ ነጻ ለማውጣት ከ66-70ዓ.ም ባደረጉት እንቅስቃሴ ጥጦስ የተባለው የሮም ንጉሠ ነገሥት ዘምቶ ኢየሩሳሌምን በ70ዓ.ም ደመሰሳት፡፡ ትልቁን የአይሁድ ቤተመቅደስንም አቃጠለው፡፡ እስራኤላውያንም በመላው ዓለም ተበተኑ፡፡ ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ በተከታታይ በሮም የነገሡ ነገሥታት /ቄሳሮች/ በክርስቲያኖች ላይ የማያባራ መከራ አድርሰዋል፡፡ ክርስቲያኖች የተቀበረውን መስቀል አስፈልገው ለማውጣት ቀርቶ ሃይማኖታቸውን የማመን ነጻነት ስላልነበራቸው መስቀል ለ300 ዓመታት ያህል ተቀብሮ የጉድፍ መጣያ ሆኖ ቆየ፡፡

የመስቀሉ የመገኘት ታሪክ

የቤተክርስቲያን የመከራ ዘመን አልፎ የዕረፍትና የሰላም ዘመን ሲመጣ ለብዙ ዘመን ተቀብሮ በሰው ዘንድ እንደሞተ ሰው ከልብ የተረሳውን መስቀል ባለቤቱ መድኃኔዓለም አልረሳምና እሱ የፈቀዳት ዕለት ስትደርስ በዕሌኒ ንግሥት አማካኝነት ከተቀበረበት እንዲወጣ አደረገ፡፡ ለዚህ ታላቅ ክብር የተመረጠችው ንግስት ዕሌኒ ለ300 ዓመታት የተቀበረውን መስቀል በኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃድና ኃይል እንዴት እንዳወጣች ታሪኩን ጠቅለል አድርገን እናቀርባለን፡፡

ዕሌኒና ተርቢኖስ የሚባሉ ሁለት ደጋግ ክርስቲያኖች ተጋብተው ይኖሩ ነበር፡፡ ተርቢኖስና ዕሌኒ በኑሮአቸው ፍቅርና ሰላም የሰፈነበት በመሆኑ ለብዙ ሰዎች እንደ ምሳሌ ሆነው ይኖሩ ነበር፡፡ ተርቢኖስ ነጋዴ ነበር፡፡ ራቅ ወዳለ ሀገር በመርከብ እየሄደ በመነገድ ይተዳደር ነበር፡፡ ዕሌኒም ባለቤቷ ተርቢኖስ ለንግድ ወጥቶ እስኪመለስ ስለባሏ ከመጸለይና ከማሰብ በቀር ከግቢዋ አትወጣም ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ተርቢኖስ ለንግድ ሄዶ ብዙ ዓመታትን ቆይቶ ከጓደኞቹ ጋር ወደ ሀገሩ ሲመለስ ከነጋዴዎች አንዱ በእግዚአብሔር ፈቃድ ከሽፍታና ከማዕበል ከልዩ ልዩ አደጋ ተርፈን በሰላም ተመልሰን ግን ሚስቶቻችን ሌላ ሳይወዱ ሳይለምዱ እናገኛቸው ይሆን? ብሎ ጠየቀ፡፡ ተርቢኖስ ግን "እንኳን በሰላም አደረሰን እንጂ ሚስቴን በዚህ አልጠረጥራትም" ብሎ ሲመልስ ሌላው ጓደኛው "ያንተሚስት ከማን ትበልጣለችና ነው አሁን ሄጄ ከሚስትህ ጋር ለምዳኝ ወዳኝ ወድጃት ብመጣስ ምን ይቅጣህ?" አለው፡፡ ተርቢኖስም በሚስቱ እሌኒ ተማምኖና ይህንን ብታደርግ ይህን ያህል ዓመት የለፋሁበት ሀብት ከነትርፉ ውሰድ አንተም ብታደርግ እንዲሁ ሀብትህ ከነትርፉ ለእኔ ይሁን ተባብለው ተወራረዱ፡፡

ከዚያም መርከቡ ወደብ ከመድረሱ በፊት ነጋዴው ወደ ዕሌኒ ቤት ደረሰና በሩን አንኳኩቶ ሠራተኛይቱን ዕሌኒን ማነጋገር እፈልጋለሁና ንገሪልኝ ብሎ ጠየቃት፡፡ እሷም እያፈረች የተላከችውን ለዕሌኒ ነገረቻት ዕሌኒም ተቆጥታ ከመች ወዲህ ነው እንግዳ የማነጋግረው ብላ አሳፈረታቸው፡፡ ሠራተኛይቱም ለነጋዴው መልሱን ስትነግረው ነጋዴው እንደማይሆንለት ከተረዳ በኋላ ሌላ ተንኮል አቀደና ለሠራተኛይቱ ባልና ሚስቱ ብቻ የሚያውቁትን አንድ ነገር ብቻ ብትሰጪኝ ብዙ ገንዘብ ወርቅ እሰጥሻለሁ ብሎ ወርቅ ሰጣት፡፡

ሠራተኛይቱም ሁለቱ ብቻ የሚያውቁትን የእመቤቴ ሀብል አለ ያንን እመጣልሀለሁ መጀመርያ አንተ በከተማው ውስጥ እየዞርህ ነጋዴዎችን መጡ የብስ ረገጡ እያልክ አስወራ ከዚያም ተመልሰህ እንድትመጣ ብላ ሰደደችው፡፡ ነጋዴውም እንደተመከረው የነጋዴዎቹን መምጣት በከተማይቱ እንዳወራ የነጋዴዎቹ ቤተሰቦች ነጋዴዎችን ለመቀበል ዝግጅት ማድረግ ጀመሩ፡፡ የዕሌኒም ሰራተኛ እመቤቴ ነጋዴዎች መጡ ተብሎ ይወራልና፡፡ ባለቤትዎ በሰላም ስለመጡ ይዘገጃጁ ገላዎን ይታጠቡ ብላ መከረቻት፡፡ ዕሌኒም ገላዋን ስትታጠብ ያንገቷን ሐብል ቁጭ ካደረገችበት ቦታ ሠራተኛይቱ አንስታ ለነጋዴው በተቃጠሩበት ዕለት ሰጣች፡፡ ነጋዴውም ለሠራተኛይቱ የውለታዋን ብዙ ገንዘብ ሰጥቶአት ደስ እያለው ወደ ጓደኞቹ ሄደ፡፡ ለተርቢኖስ ሚስትህን ለምጃት ወድጃት መጣሁ አለው ተርቢኖስም ውሸት ነው ለዚህ ምን ምልክት አለህ ብሎ ጠየቀው፡፡ ተንኮለኛውም ነጋዴ ያንን ሐብል አውጥቶ ይህ ሐብል የሚስትህ አይደለምን ብሎ ሰጠው ተርቢኖስም ደነገጠ የሚናገረው አጣ፡፡ በውርርዱም ሀብቱን ሁሉ አስረከበና ባዶ እጁን ወደቤቱ እያዘነ እየተቆጨ ሔደ፡፡

ባለቤቷን በናፍቆትና በታማኝነት ስትጠብቅ የከረመችው ዕሌኒ በተርቢኖስ ያልተለመደ ሀዘንና ብስጭት ግራ ተጋብታ ወንድሜ ምን ሆነሀል? ለወትሮው እንኳን ይህን ያህል ዘመን ተለያይተን ቀርቶ ለጥቂት ቀናት ተለያይተን እንኳ ለጥቂት ቀናት ተለያይተን ስንገናኝ እንነፋፈቃለን፡፡ አሁን ግን ከመጣህበት ጊዜ ጀምሮ አዝነህ አይሀለሁ ብላ ጠየቀችው፡፡ ተርቢኖስም ብዙ የደከምኩበትና የለፋሁበት ሀብት ንብረቴ እንዳለ ማዕበል አጠፋብኝ እኔ ያላዘንኩ ማን ይዘን አላት፡፡ እሌኒም የተማረች ናትና እግዚአብሔር ሰጠ እግዚአብሔር ነሣ የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን እንዳለ ኢዮብን አስበው አንተ እንኳን በሰላም መጣህ እንጂ ሀብቱ ውሎ አድሮ ይመጣል፡፡ እያለች አጽናናችው፡፡ ተርቢኖስም እንግዲህ በተከበርኩበት ሀገር ተዋርጄ፣ በሰጠሁበት ሀገር ለምኜ ለመኖር አልችልምና ወደሌላ ወደማያውቁኝ ሀገር እሔዳለሁ አንቺ ግን ሁሉ ይወድሻል ያከብርሻል ከወደድሸው ጋር ኑሪ አላት፡፡ ዕሌኒም በደስታ ጊዜ አብሬህ እንደሆንኩ በችግርም ጊዜ ልለይህም የኔንና ያንተን አንድነት ችግር አይፈታውም ከአንተ ተለይቼ ወዴት እቀራለሁ ወደምትሄድበት አብሬህ እሄዳለሁ ብላ ተነሳች፡፡

ሁለቱም ቤታቸውን ጥለው ሲሄዱ በመንገድ ላይ ተርቢኖስ በልቡናው ይዞት የነበረውን ምሥጢር አወጣው "ዕሌኒ ስወድሽ የጠላሽኝ ሳምንሽ የከዳሽኝ ምን አድርጌሽ ነው?" ብሎ ጠየቃት፡፡ ዕሌኒም እኔ አንተን አልጠላሁም አልከዳሁምም ይህንን ሐሳብ እንዴት አሰብህ ብትለው ከኪሱ አውጥቶ ሐብሉ አሳያትና የሆነውን ሁሉ ነገራት፡፡ ዕሌኒም ያልጠበቀችውን ነገር ስለተፈጸመ አዝና የሆነውን እውነተኛ ታሪክ በሙሉ ነገረችው፡፡ ተርቢኖስ ግን አላመናትም፡፡ ከባህር ዳር በደረሱ ጊዜ በቁመቷ ልክ ሳጥን አሠርቶ ዕሌኒን በውስጡ አስገባትና ብታደርጊውም ባታደርጊውም እንደሥራሽ ሥራሽ ያውጣሽ ብሎ ወደ ባህሩ ወረወራት፡፡ ዕሌኒ ያለችበት ሳጥን በፈቃደ እግዚአብሔር እየተንሳፈፈ ከወደብ ደረሰ በዚያ ወደብ አካባቢ ምዕራብ ሮምን ያስተዳደር የነበረው ኮስታንዲዮስ /ቁንስጣ/ የተባለው ንጉሥ ነበርና ሳጥኑን አይቶ አውጥቶ እንዲከፍቱት ወታደሮችን አዘዘ፡፡ ሳጥኑን አውጥተውም ሲከፍቱት እጅግ የተዋበች ሴት ሆና አገኟት ንጉሡም ዕሌኒን ወስዶ ሚስቱ አደረጋት፡፡ ኮስታንዲዮስ /ቁንስጣ/ የመክስምያኖስ ቄሳር ሆኖ ምዕራብ ሮምን ያስተዳደር ነበር፡፡ ንግስት ዕሌኒም በ272ዓ.ም ታላቁ ቆስጠንጢኖስን ወለደችለት ቆስጠንጢኖስም ገና በወጣትነቱ የአባቱ እንደራሴ ሆኖ እንዳሠራ አባቱ ሞተ፡፡ የአባቱ ባለሟሎችና ህዝቡ ተስማምተው የ18 ዓመቱን ቆስጠንጢኖስን በአባቱ ቦታ ሐምሌ 25 ቀን 300ዓ.ም በሮም ምዕራብ ክፍል በገላትያ አነገሡት፡፡ በጦር ሜዳዎች ብዙ የጀግንነት ሥራዎች ስለሰራ በሠራዊቱ ዘንድ ይወደድ ነበር፡፡

ንግሥት ዕሌኒ ልጅዋን ቆስጠንጢኖስን ከልጅነቱ ጀምሮ ስለክርስትና ሃይማኖትና ስለክርስቲያኖች መከራ ታስተምረው ስለነበር በክርስቲያኖች ላይ የነበረው አመለካከት በሮም ከነገሡት ቄሣሮች ሁሉ የተሻለ ነበር፡፡ በተለይም በ312ዓ.ም ከጠላቱ ከመክስምያኖስ ጋር ለመዋጋት ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት ብሎ ለዘመቻ እንደተሰለፈ በራዕይ በሰማይ ላይ "በዚህ መስቀል /ምልክት/ ጠላትህን ድል ታደርጋለህ" የሚል መስቀልና ጽሑፍ ስላየ ለሠራዊቱ የመስቀል ምልክት በመሳሪያቸው እና በሰንደቅ ዓላማው ላይ እንዲያደርጉ አዘዘ፡፡ ወደያው ጦርነት ቢገጥም በቲቤር ወንዝ ድልድይ ላይ ጠላቱን ድል ነስቶ በጠቅላላው የሮም መንግስት ግዛቶች ሁሉ ገዥ ሆነ፡፡

ታላቁ ቆስጠንጢኖስ የሮም ንጉሠ ነገሥት ከሆነ በኋላ በ300 ዓመታት ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ ለክርስቲያኖች የነጻነት ዐዋጅ ዐወጀ፡፡ ክርስትናም ብሔራዊ ሃይማኖት ተባለች፡፡ ንግሥት እሌኒም በተፈጠረላት አመች ሁኔታ በመጠቀም የጌታችን መስቀል ከተቀበረበት ለማውጣት በ327ዓ.ም ወደ ኢየሩሳሌም ሔደች፡፡

ዕሌኒ ልጅዋ ቆስጠንጢኖስ ክርስቲያን ከሆነላት ወደ ኢየሩሳሌም ሔዳ መስቀሉን ለመፈለግ እንዲሁም በኢየሩሳሌም ያሉ ቅዱሳት መካናትንና አብያተ ክርስቲያናትን ከማነጽ ለእግዚአብሔር ተሳለች፡፡ ከዚህ በኋላ ቆስጠንጢኖስ አምኖ በ337ዓ.ም ተጠመቀ፡፡ ቅድስት ዕሌኒ ወደ ኢየሩሳሌም ሔደች ከእርሷም ጋር ብዙ ሠራዊት ነበር፡፡ እንደደረሰችም ስለ ከብረ መስቀል መረመረች ጠየቀች፡፡ ቦታውን የሚያስረዳት አላገኘችም፡፡ የአይሁድ ወገን እንቢ ቢሉም በኋላ ግን ባደረገችው ጥረት አረጋዊው ኪራኮስ የጎልጎታን ኮረብታ አመለከታት አስቆፍሪው ብሎ ነገራት ኪራኮስም ዘመኑ ከመርዘሙ ጋር ተያይዞ እውነተኛው ተራራ ይህ ነው ብሎ ማሳየት ባለመቻሉ ከሦስቱ ተራሮች አንዱ ነው ስላላት አይሁድ ተራሮቹን ይቆፍሩ ዘንድ አዘዘቻቸው፡፡ የጌታችን ቅዱስ መስቀል ከጌታ ሞት እያመነ በተቸገሩ ግዜ ማንም እንዳያገኘው የኢየሩሳሌም ነዋሪ ሁሉ የእቤቱን ቆሻሻ የከበረ መስቀል ባለበት ቦታ እንዲጥል አይሁድ አዝዘው ስለነበር ከሁለት መቶ ዓመት በላይ ጥራጊ ስለጣሉበት ታላቅ ተራራ ሆነ፡፡

ዕሌኒ ተራሮቹን ለማስቆፈር ከሦስቱ ተራሮች የቱ እንደሆነ ለመለየት ደመራ አስደምራ ብዙ እጣንም በመጨመርና በማቃጠል ምልክት አገኘች፡፡ እርሱም የእጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ በመውጣት በቀጥታ ተመልሶ መስቀሉ ባለበት ተራራ ላይ በማረፍና በመስገድ መስቀሉ ያለበትን ትክክለኛ ስፍራ አመለከታት፡፡ ቅዱስ ያሬድም "ሰገደ ጢስ" ጢሱ ሰገደ ብሎታል፡፡ ከዚያም መስከረም 16 ቀን ቁፋሮው እንዲጀመር አዘዘች፡፡ ሰባት ወር ያህል ከተቆፈረ በኋላ መጋቢት 10 ቀን ሦስት መስቀሎች በአንድነት ተገኙ፡፡ የክብር ባለቤት ጌታችን የተሰቀለበት የትኛው እንደሆነ ለማወቅ ተቸገሩ፡፡ አንድ የሞተ ሰው አምጥተው በሁለቱ መስቀሎች ላይ በተራ ቢያስቀምጡት አልተነሣም፡፡ ለመጨረሻ ግዜ በአንዱ መስቀል ላይ ቢያስቀምጡት ያን ጊዜ የሞተው ሰው ተነሣ፡፡ በዚህም የጌታን መስቀል ለይታው አገኘች፡፡ ዕሌኒም የጌታ መስቀል እንደሆነ አወቀ ሰገደችለት፡፡ ክርስቲያኖች ሁሉ ሰገዱለት፡፡ በየሀገሩ ያሉ ክርስትያኖች ሁሉ የመስቀሉን መገኘት በሰሙ ግዜ መብራት አብርተው ደስታቸውን በመግለጥ ለዓለም እንዲታወቅ አደረጉ፡፡ በዚህም ምክንያት ይህንን ታላቅ የድኅነት ምልክት የሆነው መስቀል የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ደመራ በመደመር በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ታከብረዋለች፡፡

ዳግማዊ ጐልጐታ ግሸን ደብረ ከርቤ

በወሎ ክፍለ ሀገር በአንባሰል አውራጃ ውስጥ ግሸን ማርያም የምትባል ደብር ትገኛለች፡፡ ይህች ደብር በሐይቅና በመቅደላ በደላንታ በየጁ መካከልና በበሽሎ ወንዝ አዋሳኝ በርዋ አንድ ዙርያውን በገድል የተከበበች አምባ ናት፡፡ በበርዋ ከተገባ በኋላ ግቢዋ፣ ከላይ ሜዳና መስቀለኛ ቦታ ነው፡፡ ወደዚህች ደብር ለመሔድ በረሃን አቋርጦ ተለያየን ወንዝና በሽሎን በመሻገር የተጠማዘዘ አስፈሪ ገደሉን ማለፍ ግድ ይላል፡፡

ግሸን የመጀመርያ ስሟ ደብረ እግዚአብሔር በመባል ይጠራ ነበር፡፡ ይህ ደብረ እግዚአብሔር የሚለው ስያሜም በጻድቁ ንጉሥ ላሊበላ እጅ ከቃጥኝ ድንጋይ ተፈልፍሎ የተሠራ ቤተመቅደስ በእግዚአብሔር አብ ስም ስለነበረ ደብረ እግዚአብሔር ተብሎ የተጠራ ነበር፡፡ ከዚያም በዓጼ ድግናዥን ዘመነ መንግሥት የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ሲመሰረት ሐይቅ ደብረ ነጐድጓድ ተብሎ ሲሰየም ግሸን የሐይቅ ግዛት ስለሆነች ደብረ እግዚአብሔር ተብላለች፡፡ ከዚያም በ14ኛው መቶ ከፍለ ዘመን ላይ በዓጼ ዘርአያዕቆብ ዘመነ መንግስት የክርስቲያን ግማደ መስቀሉ ግሸን ገብቶ ሲቀመጥ ከደብረ ነጐድጓድ ደብረ ከርቤ ተብላለች፡፡ የደብሩ አስተዳዳሪም መምህረ እስራኤል ዘደብረ ከርቤ ይባል ነበር፡፡ ከደብረ ከርቤ ግሸን ማርያም ተብላለች፡፡

መስቀሉ ወደ ግሸን አምባ የመውጣቱ ታሪክ

ንግሥት ዕሌኒ መስከረም 16 ቀን 320ዓ.ም በዕጣን ጢስ ምልክት ቁፋሮ አስጀምራ መጋቢት 10 ቀን አግኝታ በማውጣት ታላቅ ቤተመቅደስ ጎልጎታ ላይ ሠርታ በክብር አስቀመጠችው ይህ መስቀልም ከዚያ ዕለት ጀምሮ እንደ ፀሐይ እያበራ ድውይ እየፈወሰ አጋንንት እያባረረ ልዩ ልዩ ተአምራት እየሰራ ሙት እያነሳ ዕውር እያበራ ተአምራቱን ቀጠለ፡፡ ይህንንም ከኃያላን ነገሥታት መካከል የፋርስ ንጉሥ መስቀሉን ማርኮ ፋርስ ወስዶ አስቀመጠው፡፡ በዚህ ጊዜ የአየሩሳሌም ምዕመናን የድሉን ዜና ሰምተው ስለነበር የአንድ ቀን መንገድ ያህል ሄደው በመቀበል ካህናቱ በዝማሬና በቸብቸቦ ወንዱ በሆታ ሴቱ በእልልታ ሆ! እያሉና ችቦ አብርተው ተቀብለዋቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያኖችም ለመስቀል ችቦ እያበሩ በዓሉን በሆታ በእልልታ በስብሐተ እግዚአብሔር የሚያከብሩት ይህንን ታሪካዊ ትውፊት በመከተል ነው፡፡ ብዙ የቤተክርስቲያን አባቶች እንደሚሉት ንጉሡ ሕርቃል ይህንን ታላቅ ድል ለማግኘትና የጌታን ቅዱስ መስቀል ከአሕዛብ /ከፋርሶች/ እጅ ለማስመለስ የቻለው በዚያን ጊዜ አብያተ ክርስቲያንናት ሁሉ ለአንድ ሳምንት /አንድ ሱባዔ/ ባደረጉት ጾም ጸሎት ነው፡፡ ይህንንም ለማስታወስና ጌታን ለማመስገን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንና የግብጽ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ የዐቢይ ጾም /የጌታ ጾም/ ከመጀመሩ አስቀድሞ "ጾመ ሕርቃል" ብለው አንድ ሳምንት ይጾማሉ፡፡

የጌታ መስቀል ለብዙ ግዜያት ኢየሩሳሌም ከቆየ በኋላ ነገሥታት ይህን መስቀል እኔ ልውሰድ እኔ ልውሰድ በማለት ጠብ ፈጠሩ፡፡ በዚህ ጊዜ የአንጾኪያ፣ የኤፌሶን፣ የአርማንያ፣ የግሪክ፣ የእስክንድርያ፣ የመሳሰሉት የሃይማኖት መሪዎች ጠቡን አበረዱት ከዚያም አያይዘው በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የክርስቶስን መስቀል ከ4ት ከፍለው በዕጣ አድርገው በስምምነት ተካፍለው ከሌሎች ታሪካዊ ንዋያተ ቅዱሳት ጋር በየሀገራቸው ወስደው በክብር አስቀመጡት የቀኝ ክንፉ የደረሰው ለአፍሪቃ ስለነበር ከታሪካዊ ንዋየ ቅዱሳት ጋር በግብጽ የሚገኘው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ተረክቦ ወስዶ በክብር አስቀመጠው፡፡

ይህ ግማደ መስቀልም ለብዙ ዘመን በእስክንድርያ ሲኖሩ በግብጽ ያሉ እስላሞች እየበዙ ኃይላቸው እየጠነከረ ሔደ በእስክንድርያ የሚኖሩትን ክርስትያኖች ላይ ሥቃይ ያጸኑባቸው ጀመር፡፡ ክርስቲያኖቹም አንድ ሆነው መክረው ለኢትዮጵያዊው ዓጼ ዳዊት እንዲህ የሚል መልእክት ላኩ "ንጉሥ ሆይ! በዚህ በግብጽ ያሉ እስላሞች መከራ አጽንተውብናል ኃይልህን አንሥተህ አስታግስልን ብለው ጠየቁት ዳግማዊ ዓጼ ዳዊትም ለመንፈሳዊ ኃይማኖት ቀንተው የክርስቶስ ፍቅር አስገድዷቸው 20,000 ሠራዊት አስከትለው ወደ ግብጽ ዘመቱ በዚህ ጊዜ በግብጽ ያሉ ኃያላን ፈሩ ተሸበሩ ንጉሡ ዳግማዊ ዳዊትም እንዲህ የሚል መልዕክት ለእስላሞቹ ላከ በተፈጥሮ ወንድሞቻችሁ ከሆኑት ክርስቲያኖች ካልታረቃችሁ ሀገራችሁን መጥቼ አጠፋለሁ" የሚል ማስጠንቀቂያ ላከ፡፡ የንጉሡ መልዕክትም ለእስላሞቹ እንደደረሳቸው ፈርተው እንደ ጥንቱ በየሃይማታቸው ጸንተው በሰላም እንዲኖሩ ከክርስቲያን ወንድሞቻቸው ጋር ታረቁ፡፡ መታረቃቸውን ዓጼ ዳዊት ሰሙ በዚህም ጉዳይ ንጉሡ ደስ አላቸው፡፡ እግዚአብሔር አመሰገኑ በግብጽ የሚኖሩ ክርስቲያኖችም ከ12,000 ወቄት ወርቅ ጋር ደስታቸውን ለኢትዮጵያዊው ንጉሥ ለዳግማዊ ዳዊት በደብዳቤ አድርገው ላኩላቸው፡፡ ንጉሡም የደስታውን ደብዳቤ ተመልክተው ደስ አላቸው ወርቁን ግን መልሰው በመላክ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጻፉ፡፡ በግብጽ የምትኖሩ የክርስቶስ ተከታዮች ሆኖ እንኳን ደስ አላችሁ የላካችሁልኝ 12,000 ወቄት ወርቅ መልሼ ልኬላችኋለሁ፡፡ የእኔ ዓላማ ወርቅ ፍለጋ አይደለም የክርስቶስ ፍቅር አስገድዶኝ በተቻለኝ ችግራችሁን ሁሉ አስወገድኩላችሁ አሁንም የምለምናችሁ በሀገሬ ኢትዮጵያ ረሀብና ቸነፈር ድርቅ ስለወረደብኝ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀልና የቅዱሳን አጽም ከሌሎች ክቡራን ዕቃዎች ጋር እንድትልኩልኝ ነው የሚል ነበር፡፡

በእስክንድርያም ያሉ ምዕመናን ይህ መልዕክት እንደደረሳቸው ከሊቃነ ጳጳሳትና ከኤጲስ ቆጶሳቱ ጋር ውይይት በማድረግ ይህ ንጉሥ ታላቅ ክርስቲያን ነው፡፡ ስለዚህ ልቡን ደስ እንዲለው የፈለገውን የጌታችንን ግማደ መስቀል ከቅዱሳን አጽምና ንዋየ ቅዱሳት ጋር አሁን በመለሰው ወቄት ወርቅ የብርና የነሐስ የመዳብና የወርቅ ሣጥን አዘጋጅተን እንላክለት ብለው ተስማምተው በክብር በሥነ ሥርዓት በሠረገላና በግመል አስጭነው ስናር ድረስ አምጥተው ባስረከቧቸው ጊዜ በእጃቸው እያጨበጨቡ በእግራቸው እያሸበሸቡ በግንባራቸው እየሰገዱ በክብር በደስታተቀበሏቸው፡፡ መስከረም 16 በኢትዮጵያ ታላቅ ብርሃን ሌሊትና ቀን ሦስት ቀን ሙሉ ሲበራ ሰነበተ፡፡

ግማደ መስቀሉ ወደ መካከለኛው ኢትዮጵያ ሳይደርስ በድንገት ዓጼ ዳዊት ስናር ላይ አረፉ፡፡ ግማደ መስቀሉም የግድ በዚያው በስናር መቆየት አስፈለገው፡፡ ከዚህ በኋላ የሟቹ የዳግማዊ ዳዊት ልጅ ዓጼ ዘርዓ ያዕቆብ እንደነገሠ ወደ ስናር ሔደ ግማደ መስቀሉን ከሌሎቹ ንዋያተ ቅዱሳት ጋር አምጥተው በመናገሻ ከተማቸው በደብረ ብርሃን ላይ ቤተመቅደስ ሠርተው ለማስቀመጥ ሲደክሙ በሕልማቸው አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል ወዳጄ ዘርዐ ያዕቆብ ሆይ መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ ላይ አስቀምጥ የሚል ሕልም አየ፡፡ ንጉሡም መስቀለኛ ቦታ እየፈለጉ በኢትዮጵያ አውራጃዎች ሁሉ በመፈለግ ከብዙ ቦታ አስቀምጠውት ነበር፡፡ ለምሳሌ በሸዋ በደርሄ ማርያም፣ በማናገሻ ማርያም፣ በወጨጫ መስቀሉን አሳርፈውት ነበር፡፡ ነገር ግን የመጨረሻውን ቦታ ባለማግኘታቸው በራዕይ እየደጋገመ መስቀሌን በመስቀለኛ ሥፍራ አስቀምጥ እያለ ይነግራቸው ነበር፡፡ ዓጼ ዘርዓ ያዕቆብም ለሰባት ቀን ሱባዔ ገቡ፡፡ በዚያም የተገለጸላቸው መስቀለኛውን ቦታ የሚመራህ ዓምደብርሃን ይመጣል አላቸው፡፡ እርሳቸውም ከዚያ እንደወጡ መስቀለኛውን ቦታ የሚመራ የብርሃን ዓምድ ከፊታቸው መጥቶ ቆመ፡፡ በዚያ መሪነት ወደ ወሎ ክፍለ ሀገር አምባሰል አውራጃ ውስጥ ግሸን ከምትባል አምባ መርቶ አደረሳቸው፡፡ በእውነትም ይህች ግሸን የተባለችው አምባ ጥበበኛ ሰው እንደቀረጻት የተዋበች መስቀለኛ ቦታ ሆና ስላገኟት የልባቸው ስለደረሰ ደስ አላቸው፡፡ በዚያም አምባ ታላቅ ቤተመቅደስ ሰርተው መስቀሉንና ሌሎች ንዋየ ቅዱሳቱን በየመዓረጋቸው የክብር ቦታ መድበው አስቀመጡዋቸው፡፡ ዘመኑም በ14ኛው ክፍለ ዘመን ነው፡፡

ከእስክንድርያ ሀገር ከመስቀሉ ጋር በልዩ ልዩ ሣጥን ተቆልፈው የመጡትም ዝርዝር ስማቸው ጌታ በዕለተ ዓርብ ለብሶት የነበረው ቀይ ልብስ፣ ከሮም የመጣው ከለሜዳው፣ ሐሙት የጠጣበት ሰፍነግ /ጽዋ/፣ ዮሐንስ የሳለው ኩርዓተ ርዕሱ ስዕል እንዲሁም የተለያዩ የቅዱሳን አጽም፣ ከግብጽ ታላላቅ ገዳማት የተቆነጠረ አፈር፣ የዮርዳኖስ ውሃ ይገኛል፡፡

መስቀሉ በእኛ ሕይወት

 • በመስቀሉ ድነናል ኤፌሶን 1፡7፤1ኛ. ጴጥ. 1፡19
 • በመስቀሉ ክርስቶስ ወደ ራሱ አቅርቦናል፤ በሰማያት ወደ አባቱ አቅርቦናል ዮሐ. 12፡32 ፣ኤፌሶን 2፡13፣ መጽ.ኪዳን
 • በመስቀሉ ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀናል ሰላምን አግኝተናል ሮሜ. 5፡2፣ 1ቆሮ. 1፡31፣ ዕብ. 10፡10
 • በመስቀሉ ለዘለዓለም ፍጹማን ሆነናል ዕብ .10፡14
 • በመስቀሉ የዕዳ ደብዳቤያችን ተደምስሰዋል ቈላ. 2፡14
 • በመስቀሉ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለመግባት ሞገስ አግኝተናል፣ ዕብ.10፡19
 • በመስቀሉ ላይ በፈሰሰው ደም ከበደላችን ሁሉ ታጥበናል ራዕ. 12፡11
 • በመስቀሉ ቤዛነት እንመካለን ገላ. 6፡14

ዛሬ ያለው የመስቀል አከባበር በግሸን

ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ግሸን አምባ ከአዲስ አበባ 480 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ቅድስት ሥፍራ ናት፡፡ ጥንት በአባቶቻችን ዘመን ለጊሸን ማርያም ክብረ በዓል ጉዞ የሚጀመረው ከአንድ ወር በፊት ሲሆን መንገዱም አመቺ ባለመሆኑ አስቸጋሪ ነበር፡፡ በተለይም በአሁን ወቅት ከሀገር ውስጥም ይሁን ከሀገር ውጭ ያሉ ክርስቲያኖች ለመሳለምና ለመባረክ ዕቅድ ይዘው መምጣት ጀምረዋል፡፡ ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ምዕመናን ወደ ሥፍራው ይጓዛሉ፡፡ ጉዞውም በትራንስፖርት የታገዘ በመሆኑና እስከ ተራራው ጥግ መኪና ስለሚደርስ ጉዞው ብዙም አያስቸግርም፡፡ ብዙ ምዕመናንም እየዘመሩ፣ እየተማማሩ በማኅበር መጓዝ የተለመደ ነው፡፡ መግቢያ በሩ ጠባብና አንድ ብቻ በመሆኑ ለመተላለፍ ቢያስቸግርም በተለያዩ ማኅበራት የሚጓዙ ወጣቶች ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሚወጣና የሚወርደውን ምዕመን ሌትና ቀን በማስተባበር ይሰራሉ፡፡ በጊሸን አምባ በሁሉም ማዕዘን አብያተ ክርስቲያናት የታነፁ ሲሆን ከመስቀሉ ራስጌ የእመቤታችን፣ ከመስቀሉ ግርጌ የቅዱስ ሚካኤል ከቀኝ ክንፉ ላይ ቅዱስ ገብርኤል ከግራ ክንፉ ደግሞ ቅዱስ ዑራኤል ሲሆኑ መካከሉ ላይ መስቀሉ የተቀበረበት የእግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን ይገኛል፡፡ በተለይም መስከረም 21 ቅዳሴ ለማስቀደስ ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል የሚፈልጉ ምዕመናን ቁጥራቸው ብዙ ስለሆነ ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት በምዕመናን ይጨናነቃሉ፡፡ እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን ሴቶቹን ውጪ አውደ ምሕረቱ ላይ በመውጣት ካህናት ቅዱስ ቁርባን ያቆርቡዋቸዋል፡፡ ግሸን አምባ መካከል ላይ ከኢየሩሳሌም በመጣው የዮርዳኖስ ውሃ አምሳል መካከለኛ ኩሬ ይገኛል፡፡ በበዓሉ ላይ እንደጠበል ያገለግላል፡፡

ማጠቃለያ፡-

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እጅግ ብዙ የሆኑ ቅዱሳት መካናት ውስጥ አንዷ ግሸን ማርያም በመሆንዋ ምዕመናን ታሪካቸውን ከማወቅ ብሎም ተባርኮ ከመምጣት ባሻገር ለንግስ ሲሄዱ በአለባበስ ሥርዓት ቢጠብቁ በየቦታው ቆሻሻ ጥሎ ውቧን አምባ ከማበላሸት እንዲቆጠቡ የሄዱበትን ዓላማ ሳይረሱ እየጸለዩ፣ ውዳሴዋን ቅዳሴዋን እየሰሙ ጠበሉን ጠጥተው መስቀሉን ተሻሽተው ስጋ ወደሙን ተቀብለው በበረከት መመለስ አለባቸው በማለት ጽሑፌን አጠቃልላለሁ፡፡

ዋቢ መጻሕፍት፤

 • የእግዚአብሔር መንግስት ታሪክ በምድር ላይ፡፡ ቀ/ደ/ር ምክረ ሥላሴ ገ/አማኑኤል
 • የቤተክስቲያን ታሪክ፡፡ ፕ/ር ሉሌ መላኩ
 • ትንሣኤ መጽሔት
 • መጽሐፈ ስንክሳር

የፎንት ልክ መቀየሪያ