Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

ክብረ ቅዱሳን

በርዕሰ ደብር መሐሪ ኃይሉ

ክብረ ቅዱሳን በምንልበት ጊዜ በውስጡ ከዚህ ቀጥለው ያሉ ጉዳዮችን ለማየት እንገደዳለን፡፡ እነሱም፡- ክብረ ቅዱሳን ማለት ምን ማለት ነው?

 • ቅዱስ የሚለው /ስም/ ቅጽል የሚሰጣቸውስ ምንና ምን ለሰሩ ነው፤

 • የቅዱሳን ምልጃ እንዴት ነው የሚታየው /በቅዱስ መጽሐፍ አንጻር/፡፡

 • የቅዱሳን ምልጃ በብሉይ ኪዳንና በሐዲስ ኪዳን

 • የቅዱሳን ምልጃ

ሀ/ በአፀደ ሕይወት ሥጋ
ለ/ በአፀደ ነፍስ

ቅዱሳን የሚያማልዱት ፍጡራን ሁነው ሳለ እንዴት የፍጡራን ባሕርይና ጩኸት አውቀው እንዴትስ ሰምተው ሊያማልዱን ይችላሉ? የሚሉትና ሌሎችም በቅዱሳን ክብርና ምልጃ ዙሪያ የሚነገሩ ጉዳዮችን በቅዱስ መጽሐፍ መሠረትነት በመጠኑ ለማየት እንሞክራለን፡፡

ወደ ዋናው ሐተታ ከመግባታችን በፊት ክብርና ቅዱስ የሚለውን ሐረግ አብረን እንይ /እንመልከት/

መጀመሪያ ክብር ምንድነው?

ክብር ቃሉ ጌትነትንና ከፍተኛነትን ዋጋንና ጥቅምንም አጠቃልሎ መወደድን ያሳያል፣ ዋና ትርጉሙ ለፈጣሪ የሚሰጥ ሲሆን ለፍጡራንም ይሰጣል፡፡ ሰብእሰ እንዘ ክቡር ውእቱ ኢያእመረ /መዝ. 48፡20/ ጠቅላላ የእግዚአብሔር ፍጥረት ሁሉ ክብር አለው ሉቃስ. 2፡9፣ 1ቆሮ. 11፡7፣ 15፡41፡፡ 1ጴጥ. 2፡47 ለሰዎች እንደ ማዕረጋቸው ማክበር እንደሚገባ ሮሜ. 13፡7 ክብር የሚለው የቃል ሐረግ ይህን ሲመስል፤

ቅዱስ የሚለውን ደግሞ እንየው

ቅዱስ የሚለው ቃል የዕብራይስጥ ቃል ሲሆን የቃሉ ትርጉም፤ "የተለየ ንጹሕ ልዩ" ማለት ነው፡፡ በግዕዝም ቃሉ ከነ ትርጉሙ ሳይለወጥ ይህንኑ ይዞ ይገኛል፡፡
1ኛ. ሰው ወይም ማንኛውም ነገር ለእግዚአብሔር አገልግሎት ሲለይ ቅዱስ ይባላል፡፡ ዘጸ.28፡41፤ ዘጸ. 3፡5፣ ኢዮ. 6፡9፣ ዘሌ. 19፡2 ዘካ. 14፡20-21፣ 1ጴጥ. 1፡15፣ 1ቆሮ. 1፡2፡30፡፡ ሰው ከመንፈስ ቅዱስ በሚወለድበት ጊዜ የቅድስና ሥራ ይጀምራል፡፡ 1ቆሮ. 15፡5፣ 1ተሰ. 4፡7፣ 5፡23-24፡፡

"ክብርና ቅዱስ"ና ትርጉማቸው ከዚህ በላይ እንደ ተገለጸው ሲሆን ሁለቱ ተገናኝተው ሲናበቡ ክብረ ቅዱሳን ይባላል፡፡ በመሠረቱ ክብረ ቅዱሳን ራሱ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ነው፡፡ ለዚሁም ማስረጃ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ከተናገራቸው ቃላት በከፊል እንደዚህ ይቀርባል "ተሰብከ መድኅን ክብረ ቅዱሳን ቤዛ ብዙኃን አክሊሎሙ ለሰማዕት ሰያሜሆሙ ለካህናት መድኃኒቶሙ ለነገሥት ክብሮሙ ለመላእክት ሞገሶሙ ለሐዋርያት"፡፡ ይኸውም የቅዱሳን ክብራቸው የሰማዕታት አክሊላቸው የካህናት ሿሚያቸው የነገሥታት መድኃኒታቸው የመላእክት ክብራቸው የሐዋርያት ሞገሳቸው የሚሆን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ተሰበከ ተነገረ ተገለጠ ታወጀ... ማለት ነው /ድጓ የስብከት ክብረ ቅዱሳን ከሚለው ክፍል ይገኛል፡፡

ክብረ ቅዱሳን ራሱ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ከሆነ እንዴት ለሰው ተሰጠ?

መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ራሱ ክብር ሲሆን ሰውንም በራሱ ክብር አክብሮ ክቡር አድርጎታል፡፡ በመሠረቱ ከነውር ከኃጢአት በባሕርዩ ንጹህ የሆነ ከፈጣሪ በቀር ሌላ የለም፡፡

ነገር ግን "ኲኑ ቅዱሳነ እስመ አነሂ ቅዱስ አነ" እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ ብሎአልና ሰው በእግዚአብሔር ቅድስና ይቀደሳል ዘሌ. 19፡2፡ 1ጴጥ. 1፡15-17፡፡

በፊት አገልጋዮቹ መላእክትን የቀደሰ ማለት ያከበረና ከፍ ከፍ ያደረገ እርሱ ነው፡፡ በኋላም ዓለሙን ሁሉ የቀደሰው ደሙን በፈቃዱ በመስቀል ላይ በማፍሰስ ተከታዮቹን ሁሉ ቀደሳቸው አከበራቸው፤

ስለዚህ 1ኛ ቅዱሳን ሰዎች /ጾታን ሳይለይ/ ሁሉ ለቅዱስ ለእግዚአብሔር ሲሉ ሕይወታቸውን በሞት ስለ አሳለፉ በደማቸው ታጥበው ቅድስናን ገንዘብ ስለአደረጉ የቅድስናና የብፅዕና መዓረግ ተሰጥቷቸው እናገኘዋለን፡፡

እንዲሁም ስለሰው ልጅ ሕይወት ስለ ዓለም ሰላም ጽድቅ የሠሩ የተናገሩ ሁሉ ጾታ ዕድሜ ሳይለይ ቅዱሳን ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን የቅድስናና የብጽዕና መዓረግ ሰጥታ ቅዱሳን ብላ ሰይማቸው ትገኛለች፡፡

በዚህም መሠረት ሐዋርያትና የእነርሱ ተከታዮች ሁሉ ወንድ፣ ሴት፣ ሕፃን ሽማግሌ ሳይባል በጠቅላላ ቅዱሳን እንላቸዋለን፡፡

2ኛ. ቅዱስ የሚያሰኛቸው አንቀጽ ምንድ ነው? ቅዱሳንስ የሚባሉት መለያቸው ምንድነው? ምንስ የሰሩ ናቸው? የሚለውን ጥያቄ ሁል ጊዜ እየተመላለሰ የሚቀርብ ጥያቄ ነው፡፡ ተገልጦም ሊታወቅ ያስፈልጋል፡፡ ይሁን እንጂ ቅዱሳን የሚባሉት፡፡

ሀ/ ዓለምን በመላዋ ዙሪያ ያስተማሩና ስለክርስቶስ የመሰከሩ እንደ ሐዋርያት ያሉት ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ የቀደሳቸውና ቅዱሳንም ያላቸው ናቸው፡፡

ለ/ ስለ ክርስቶስ በዓላውያን ነገሥታት ፊት ቀርበው ሳይፈሩ ሳያፍሩ የመሰከሩ ሰማዕታት ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ ይኸንም የመሰለውን ምስክርነት ራሱ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ሲያስተምር "አንሰ እንበይነዝ መጻዕኩ ወእንበይነዝ ተወለድኩ ከመ እኲን ሰማዕተ በጽድቅ" ብሎ በተናገረው መሪ ቃል ነው፡፡

ሐ/ አብዛኛቸው ዕድሜ ልካቸው በምናኔ በብቸኝነት በጸሎት በምልጃና በትምህርት ያሳለፉ ከክፉ ነገር የራቁ ጣዕመ ዓለምን የናቁ ጻድቃን ሁሉ ቅዱሳን ይባላሉ፡፡ የቅድስናም መዓረግ ተሰጥቷቸው እናገኛቸዋለን፡፡ ቅዱሳን አንድ ጊዜ በእግዚአብሔር ጸጋ ተመርጠውና ከብረው ቅዱሳን ከሆኑ በኋላ አይሻሩም ጸጋውም አይወሰድባቸውም፡፡

እነዚህ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት ሁሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በዕድሜ በወገን በጾታ ሳትለይ ማለት ትንሽ ትልቅ ሴት ወንድ ኢትዮጵያዊ የውጭ ዜጋ ሳትል ለሁሉም የቅድስና የብፅዕና መዓረግ እየሰጠች የሕይወት ታሪካቸው እየጻፈች እንደስንክሳር /ገድለ ቅዱሳን/ በመሰለው መጽሐፍ የሕይወት ታሪካቸው በክብረ መዝገብ እየመዘገበች ከትውልድ ወደ ትውልድ እያስተላለፈች ስለኖረች ቅዱሳን ሁሉ በዚህ ስም ሲጠሩ በዚህም መሠረት ሲከብሩና ሲከበሩ ኑረዋል አሁንም ይገኛሉ፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ለዚሁ ታላቅ ምሥጢር እንዲህ ብሏል "ለኲሎሙ ቅዱሳኒሁ በሰናያቲሁ ወሀቦሙ ከመይኲኑ ቅድሳነ እንተ ይዕቲ ቅዱሳቱ እንተ ኢትትነሰት ወኢትማሰን" ለቅዱሳኑም ሁሉ በቸርነቱ ቅዱሳን ይሆኑ ዘንድ ሰጣቸው ይህችውም የማትፈርስና የማትጠፋ ቅድስት ናት /ቅዳሴ ዘዮሐንስ አፈወርቅ ቁጥር 36/ ሲል አስተምሮአል፡፡

3ኛ. ክብረ ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ የሚለው ቅጽል ለሌሎች ቅዱሳን ሲሰጥ ለድንግል ግን ቅድስተ ቅዱሳን የሚል ቅጽል ነው የተሰጣት ለምን ቢባል ፈጣሬ ፍጥረታት ቅዳሴ ቅዱሳን የሆነው ቅዱስ እግዚአብሔር ስለመረጣትና ከሁሉ በላይ ስለአከበራት የምሕረት መዝገቡ ስለሆነችና የእግዚአብሔር ወልድ በሥጋ እናት ለመሆን ስለበቃች ንጽሕት ሆናም ስለተገኘች ነው፡፡ ከላይ እንደ አየነውም ልዩ ንጹህ ቅዱስ በሚለው ላይ ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም የአዳም ዘር ብትሆንም ከዓለም /ከአንስተ ዓለም/ ልዩ የሚያደርጋት ወልድን ከድንግልና ጋር አስተካክላ አስተባብራ በመገኘትዋ ነው፤ አንስተ ዓለም ከወለዱ ድንግል አይባሉም በድንግልና እያሉም አይወልዱም ንጽሕተ ንፁሐን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ግን የድንግልና ሕይወትና የእናትነትን ባህርይ አስተባብራ በመገኘት ካለዘርዓ ብእሲ በድንግልና ወልዳ በድንግልና ጸንታ በመኖር ድንግል ወእም መባልዋ ከተፈጥሮ ሕግ በላይ የሆነ አስደናቂና አምለካዊ ምሥጢር በወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ስለተፈጸመ ነው፡፡

መልአኩም ወደእርሷ ተልኮ "ደስ ይበልሽ ጸጋ የተሞላሽ ሆይ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነውና ያላት" ሉቃ. 1፡28 ድንግል ማርያም ፍጹም አምላክ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በድንግልና በመውለድዋ ልዩ ክብርና ቅድስና ስለተሰጣት ነው፡፡

ክብርዋም ከቅዱሳን ሁሉ በላይ ነው፡፡ የቅድስት ድንግል ማርያም ቅድስና በውስጥ በአፍአ በነፍስ በሥጋ ነው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር አብ ለልጁ ማደርያ አድርጎ /ማኅደረ መለኮት/ ስለመረጣት ልዩ ያደርጋታል፡፡

ቅድስት ድንግል ማርያም አምላክን ለመውለድ ያበቃት ንጽሕናዋ ቅድስናዋ ነው፡፡ "ወሶበ ርእየ ንጽሕናኪ ለሊሁ እግዚአብሔር አብ ፈነወ ኅቤኪ መልአኮ ብርሃናዌ ዘሰሙ ገብርኤል" እንዳለው አባ ሕርያቆስ፡፡

ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ክብር ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ አንቀጸ ብርሃን በተባለው ድርሰቱ "ቅድስት ወብፅዕት ስብሕት ወቡርክት ክብርት ወልዕልት አንቀጸ ብርሃን መዓረገ ሕይወት ወማኅደረ መለኮት ቅድስተ ቅዱሳን" በማለት የሚገባትን ክብር በመስጠት ነው አድናቆቱን የገለጸው፡፡

ቅዱስ አባ ሕርያቆስም "ወረከብኩ በውስቴታ ዘይብል ዘንተ ቅዳሴ ዘይቄድስ ካህን አኮ ማርያምሃ ዘድቄድስ አላ ውእቱ ይትቄደስ ወኲሎሙ እለ ሰምዕዋ ይትቄደስ እስመ እግዚእ ትነሰ ማርያም ቅድስት ይእቲ ወትረ በሰማይ ወበምድር" በማለት ክብረ ቅድስናዋን ገልጾ ተናግሯል፡፡

የቅዱሳን ምልጃ

በመሠረቱ ምልጃ ምንድነው?

ምልጃ ማለት በንባቡ ማስታረቅ ይመስላል፡፡ ነገር ግን ማስታረቅ ማለት በሁለት ጸበኞች መካከል ገብቶ አንተም ተው አንተም ተው ብሎ ማስማማት ሲሆን አማላጅነት ግን ከዚህ ለየት ይላል፡፡ ምክንያቱም ምልጃ አንዱ ሌላውን ሰው ያስቀየመ በደለኛ ጥፋቱን በመገንዘቡ ከአስቀየመው ሰው በኩል የነበረውና ሊኖረው የሚችለው ጥቅም ስለሚቀርበት እንዲሁም እንዲሁም ከአስቀየመው ሰው ጋር በሰላም ካልኖረ ችግር ሊደርስበት ስለሚችል አስታርቁን ብሎ አማላጅ ይልካል፡፡ የተወሰኑ ሰዎች ግን አማላጅ በመላክ ፈንታ ራሱ ሂዶ ይቅርታ ለምን አይጠይቅም የሚሉ አሉ፡፡ ነገር ግን እንኳን በፈጣሬ ፍጥረታት በእግዚአብሔርና በበደሉ ሰዎች መካከል ይቅርና በሰው እና በሰው መካከል በአለው መፈራራት አንኳ ያስቀየመ ሰው ራሱ ቀርቦ ተቀያሚውን ሰው ይቅርታ ለምን አይጠይቅም ቢባል ያስቀየመውን ሰው ከማክበሩ የተነሳ በቀጥታ መሄዱን እንደ ድፍረት በመቈጠሩ፣ ወይም ያን ሰው በጣም በማስቀየሙ፣ እንዴት አድርጌ ዓይኑን ለማየት እችላለሁ ብሎ በመፍራት ወይም ደግሞ ያ አማላጅ ከሚላክበት ሰው በደረጃው ከፍ ያለ ከመሆኑ የተነሳ በቀላሉ ሊያገኘው የማይችል በመሆኑ ነው፡፡

በዚህም መሠረት የእግዚአብሔር ወዳጆች ቅዱሳን የእግዚአብሔርን መቅሰፍት ለማስወገድ በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል በመሆን ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት ልመና፣ ሰው /አማኝ/ ከፍተኛ ኃጢአት በመሥራቱ በቀጥታ ወደ እግዚአብሔር ሄዶ ይቅርታ መለመን እግዚአብሔርን እንደመድፈር ስለሚቆጥረው ነው፡፡ ይህም ድርጊት እግዚአብሔርን በጣም የማክበር ትሕትና እንጂ የአምላክን ክብር ለፍጡር አሳልፎ መስጠት አይደለም፡፡

የዘመኑ የሃይማኖት ተከራካሪዎች ስለአማላጅነት ምን ይላሉ?

በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ሌላ ሦስተኛ ሰው ሊባ አይችልም እግዚአብሔርም እንደ ሰው አማላጅነት አይቀበልም ወይም ፍርዱን በአማላጅነት በምንም ዓይነት አይለውጥም፡፡ ስለዚህ በአማላጅነት ማመን ስሕተት ነው ይላሉ፡፡

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ግን ስለቅዱሳን አማላጅነት ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት በማድረግ የሚከተለውን አቋም ወይም መሠረተ እምነት አላት፡፡ ለዚህም የቤተ ክርስቲያናችን ቀኖናዊያን መጻሕፍት ይቆዩና መሠረቱ ቅዱስ መጽሐፍ ስለሆነ ቅዱስ መጽሐፍ ስለ ቅዱሳን ምልጃ ምን ይላል? ነው የምትለው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን፡፡

ቅዱስ መጽሐፍማ የእግዚአብሔርን ሕግ የሚያከብሩና በእውነተኛውም እምነት የጸኑ ሰዎች የማማለድ መብት /ሥልጣን/ እንደተሰጣቸው ያረጋግጣል፡፡ ይኸውም፤

1ኛ. የቅዱሳን ምልጃ በሕይወተ ሥጋ፣
2ኛ. የቅዱሳን ምልጃ በአፀደ ነፍስ የሚል ሲሆን በመጀመሪያ የቅዱሳን ምልጃ በሕይወተ ሥጋ እንመለከታለን፡፡

"ኰናኒ በጽድቅ ፈታሒ በርትዕ" እግዚአብሔር የቅዱሳኑን ጸሎት የሚቀበል መሆኑን በመግለጥ ሰዎችን ወደ አማላጆች እንዴት አድርጎ እንዲላክ የሚከተሉት ማስረጃዎች አንመለከታለን፡፡

"አሁን ግን ሴቲቱን ለባልዋ መልሰህ ስጥ እርሱ ነቢይ ስለሆነ እንዳትሞት ይጸልይልሃል እርስዋን መልሰህ ባትሰጥ ግን እንዳትሞት እወቅ አንተ ብቻ ሳይሆን ሕዝብህም በሙሉ ታልቃላችሁ" ዘፍ. 20፡7፡፡

በመጽሐፈ "ኢዮብም የኢዮብ ወዳጆች አሁን ሰባት ወይፈኖችና ሰባት አውራ በጐችን ይዛችሁ ወደኢዮብ ሂዱ እዚያም ስለራሳችሁ ኃጢአት የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርቡ፡፡ ባርያዬ ኢዮብ ይጸልይላችኋል፡፡ እኔም የእርሱን ጸሎት ስለምቀበል በበደላችሁ መጠን አልቀጣችሁም" ኢዮብ. 42፡8፡፡

አማላጃችን አንድ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ እንጂ የፍጡር አማላጅነት አስፈላጊ ጠቃሚም አይደለም የሚሉት ወገኖች ይህን የእግዚአብሔር ምስክርነት ምን ትርጉም ይሰጡት ይሆን? እኔ የኢዮብን ጸሎትና ምልጃ ስለምቀበል ሂዱ እርሱ ይጸልይላችኋልና ይቅርታ አደርግላችኋለሁ አለ አንጂ ሌላ ሰው አያስፈልግምና ራሳችሁ ጸልዩ አላለም እንዲሁም አቤሜሌክን አብርሃም ነቢይ ስለሆነ እንዳትሞት ይጸልይልሃል ነው ያው፣ እኛም እኮ ቅዱሳንን ወደ እግዚአብሔር እንዲማልዱልን እንለምናቸዋለን አንጂ የእግዚአብሔር ክብር ሰጥተን አናመልካቸውም፡፡ በእርግጥ ቅዱሳን ክቡራን ስለሆኑ እናከብራቸዋለን፤ አክብሮት ደግሞ አምልኮት አይደለም እኔ ወደ እግዚአብሔር ፊት ለመቅረብ ብቃት ስለሌለኝ የቅዱሳን አማላጅነት ያስፈልገኛል በማለት በትህትና መቅረብ እግዚአብሔርን ማክበር እንጂ የእግዚአብሔርን ክብርና አምልኮት ለፍጡራን አሳልፎ መስጠት አይደለም፡፡

 

ቅዱሳን ፍጡራን ሲሆኑ እንዴት የኛን ጩኸትና ፍላጎት አውቀው ሊረዱን ይችላሉ?

የቅዱሳን ክብርና ዕውቀት፣ ዕውቀት ሰጭ ከሆነ ከእግዚአብሔር በተሰጣቸው ጸጋ ሁሉን ያውቃሉ፡፡ ለምሳሌ ኤልሳዕ ነቢይ በዚህ ዓለም በነበረ ጊዜ ደቀ መዝሙሩ ግያዝ በምሥጢር /በስውር/ ከሶሪያዊው ንዕማን ስጦታ መቀበሉን ማንም ሳይነግረው እንዴት እንዳወቀ በሁለተኛው መጽሐፈ ነገሥት. 5፡25-27 መመልከት ይቻላል፡፡

ሌላም ከሶርያ ንጉሥ ባለሟሎች አንዱ ለንጉሡ ስለ ኤልሳዕ እንዲህ ሲል ነገር ሠራ "ጌታ ሆይ እንዲህ አይደለም ነገር ግን በእልፍኝህ ውስጥ ሆነህ የምትናገረውን በእሥራኤል ዘንድ ያለ ነቢይ ኤልሳዕ ለእስራኤል ንጉስ ይነግረዋል" በማለት ኤልሳዕ በቦታም አንድ አካባቢ ሳይሆኑ በጸጋ መንፈስ ቅዱስ ያውቅ እንደ ነበረ ተጽፎአል 2ኛነገ. 6፡12 በረሀብ ጊዜም የእስራኤል ንጉሥ ሊያስገድለው መልእክተኛ መላኩን ኤልሳዕ አወቀ 2ኛነገ. 6፡12፡፡

በዚህም ዓይነት ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ የሐናንያንና የሰጲራን ምሥጢራዊ ተንኮል የነገረው ሳይኖር አውቆ በሞት ቀጣቸው የሐዋ. 5፡3-9፡፡

ቅዱሳን ከዚህ ዓለም ከተለዩ በኋላ ፈጣሪ ይመስል የዚህን ዓለም ሁኔታና የኛን ፍላጎት እንዴት ሊያውቁ ይችላሉ? የዚህ ዓይነት ጥያቄ ባልታደሉ ሰዎች ሲቀርብ ይሰማል፡፡ በመሠረቱ የቅዱሳን ከሥጋ መለየት በበለጠ የሚያውቁ እንጂ የማያውቁ አያደርጋቸውም፡፡ በነፍሳቸው ሕያዋን እንጂ ሟቾች አይደሉምና ነው፡፡ ለዚህም ነው ጌታ ከሰዱቃውያን ጋር ስለሙታን ይነጋገር በነበረበት ጊዜ እግዚአብሔር የአብርሃም የይስሐቅ አምላክ ነው ሲባል እነዚህ የቀድሞ አባቶች በነፍስ ሕያዋን ስለሆኑ ነው እንጂ እርሱ የሙታን አምላክ ስለሆነ አይደለም ያለው ማስረጃችን ነው ማቴ. 22፡31-32 በተጨማሪም መላእክትም ሆኑ ቅዱሳን በዚህ ዓለም ስለአለው ሁናቴ የሚያውቁ መሆናቸውን ከቅዱሳት መጻሕፍት ማረጋገጥ ይችላል፡፡

ጸጋውና ምሕረቱ ከቅዱሳኑ ጋር እንደሆነና የተመረጡትንም እንደሚያከብራቸው ይህን ሰዎቹ አይተው አልተረዱትም በአእምሮአቸውም አላኖሩትም፡፡ ስለዚህ የሞተው ጻድቁ ሰው ባልሞቱት ኃጢአተኞች ላይ ይፈርዳል ጥበብ. 4፡15-16፡፡
"እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ ሙሴና ሳሙኤል በፊቴ ቢቆሙ እንኳ ልቤ ወደዚህ ሕዝብ አይመለስምና ከፊቴ አስወግዳቸው ይሂዱ" ኤርም. 15፡1-4፡፡

ይህ አባባል የሚያመለክተው ከኤርምያስ ዘመን በፊት ከሞቱት ብዙ ዓመታት ያሳለፉ ሙሴና ሳሙኤል ስለ እስራኤል ዘሥጋ እግዚአብሔርን ይማጸኑና ይማልዱ የነበሩ መሆናቸውን ነው የሚያሳየው፡፡

በመጽሐፈ ዜና መዋዕል ላይም የይሁዳ ንጉስ ኢዮራም ብዙ ኃጢአት በመሥራቱ ከዓመታት በፊት በእሳት ሰረገላ ወደ ሰማይ ተወስዶ የነበረው ነቢዩ ኤልያስ የተግሳጽና የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ላከለት ይላል 2ኛዜና መዋዕ. 21፡12-16፡፡

በትንቢተ ዘካርያስም ላይ የእግዚአብሔር መልአክ ስለኢየሩሳሌም ከተማ ይቅርታ ለምኖ እግዚአብሔር ልመናውን የተቀበለው መሆኑ ተገልጾአል፤ ዘካር. 1፡12-16፡፡

መላእክቶቻቸው ዘወትር በሰማይ ያለውን የአባቴን ፊት ስለሚያዩ ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ ማቴ. 18፡10 "ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ ምክንያት በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል" ሉቃ. 15፡10፡፡

የሚያስደንቀው ደግሞ በሉቃስ ወንጌል ላይ "አብርሃምና ባለጸጋው ነዌ ሲነጋገሩ አብርሃም በሰጠው መልስ ባለጸጋው በዚህ ዓለም ሳለ በተድላና በደስታ ሲኖር አልአዛር ግን በችግር እንደኖረ የነገረው ሳይኖር ሁኔታውን በዝርዝር ገልጦለታል" ታዲያ አብርሃም ስለእነ አልአዛር የዚህ ዓለም ኑሮ እንዴት ሊያውቅ ቻለ?

እንዲሁም ባለጸጋው በዓለም ስለአሉት ወንደሞቹ አስቦ አብርሃምን በለመነው ጊዜ ሙሴና ነቢያት አሉላቸው ብሎታል ሙሴና ነቢያት የተነሱት አብርሃም ከሞተ ከብዙ ዘመን በኋላ ሲሆን መጻሕፍት በዓለም ላይ መኖራቸውን አብርሃም እንዴት ሊያውቅ ቻለ?

ስለዚህ ዕውቀት ሲያብራራ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ብሎአል "አሁን በመስታወት እንደምናየው ዓይነት በድንግዝግዝ እናያለን በዚያን ጊዜ ግን እግዚአብሔርን ፊት ለፊት እናያለን" 1ቆሮ. 13፡12፡፡

እስከዚህ ድረስ የቅዱሳን ዕውቀት በሕይወተ ሥጋና በአፀደ ነፍስ የፍጡራንን ምንነት ማንም ሳይነግራቸው እንዴት ማወቅ እንደሚችሉ ከሞላ ጎደል ለማየት ሞክረናል፡፡

ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ የቅዱሳን ምልጃ በብሉይ ኪዳንና በሐዲስ ኪዳን በአጭር በአጭሩ ለማየት እንሞክራለን፡፡ በመጀመርያ በብሉይ ኪዳን ቀደም ሲል የአብርሃምና የኢዮብ ምልጃ ምን እንደሚመስል አይተናል፡፡ አሁን ደግሞ ከሙሴ ጀምሮ እናያለን፡፡

1ኛ. የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ባለመስማቱ እግዚአብሔር ግብፅን በዕንቁራሪት /ጓጉንቸር/ አስወረራት፣ መላዋ የግብፅ አገር በእንቁራሪት ተሸፈነች፣ ፈርዖንም ይህን አስደንጋጭ መቅሰፍት አይቶ ሙሴና አሮንን ጠርቶ /ጓጉንቸሮቹ/ ከእኔና ከሕዝቤም እንዲርቁ ወደ እግዚአብሔር ጸልዩልኝ አላቸው፡፡ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ /አማለደ/ እግዚአብሔርም በሙሴ ምልጃ ጓጉንቸሮቹን በሙሉ ገደለ፣ ዘጸ. 8፡8-15፡፡

2ኛ. ተናካሽ የዝንብ መገንጋ ዘጸ. 8፡25-31፡፡

3ኛ. እስራኤላውያን ጣዖትን በማምለክ ከባድ ኃጢአት በፈጸሙ ጊዜ እግዚአብሔር ሙሴን ጠርቶ ይህን ሕዝብ አጠፋለሁ /እደመስሳለሁ/ አንተም በታላቅ ሕዝበ ላይ እሾምሃለሁ ባለው ጊዜ ሙሴ ወደ ፈጣሪው ወደ እግዚአብሔር አጥብቆ ጸለየ /አማለደ/ በዚህ ጊዜ መሐሪ እግዚአብሔር በሙሴ ምልጃ ሊያደርገው ካሰበው መቅሰፍት በራሱ መሐሪነት ተመልሶ መቅሰፍቱን አስቀረ ሕዝቡንም በሙሉ ጸሎት ምልጃ ይቅር አለ ዘጸ. 32፡11-14፡፡

4ኛ. ሙሴ ኢትዮጵያዊትዋን ሴት ልጅ በማግባቱ ወንድሞቹ አሮንና ማርያም ሙሴን በመቃወም አሙት በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር የነገሩ ቆስቋሽና ጀማሪ የነበረችውን ማርያምን በለምጽ በሽታ መታት /በረዶ መሰለች/ ነገር ግን ሙሴ ሰባት ቀን ወደ እግዚአብሔር ጸለየላት /ማለደላት/ እግዚአብሔርም በሙሴ ጸሎት /ምልጃ/ ፈወሳት ዘኁል. 12፡1-7፡፡

የነቢየ እግዚአብሔር አማላጅነት

ስሙ በውል ያልተጠቀሰ ብእሴ እግዚአብሔር በሚል ስያሜ ብቻ የተጠቀሰው በመሰውያ ላይ ዕጣን እያጠነ በነበረው የኢዮርብዓም ላይና በመሰውያው ላይ ትንቢት በመናገሩ ንጉሱ ኢዮርብዓም ተው ያዙት ብሎ እጁን ዘረጋ በዚህ ጊዜ በትንቢቱ መሠረት በደቂቃ ውስጥ የተዘረጋች የንጉሡ እጅ እንደብረት ደርቃ እንደተዘረጋች ቀረች ሊያጥፋት ቢሞክርም አልቻለም፡፡

ከአቅሙ በላይ ሲሆንበት ኦብእሴ እግዚአብሔር ጸሊሊተ ኅበ እግዚአብሔር በማለት ንጉሡ ወደ እግዚአብሔር ሰው አማልደኝ ብሎ በመለመኑ የእግዚአብሔር ሰውም ወደ መሐሪ እግዚአብሔር በመለመኑ የደረቀችው ንጉሡ እጅ ወደእርሱ ተመለሰች ማለት /ታጠፈች/ እንደ ነበረችውም ሆናለች ይላል. 1ኛነገ. 13፡1-7፡፡

የነቢየ የኤልያስ ምልጃ

ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስ በምልጃው /በጸሎቱ/ ብዙ አስደናዊ ተአምራቶች ፈጽሞአል፡፡ ከእነርሱም መካከል፡፡

1ኛ. ሕገ እግዚአብሔርን የተው ወገኖችን ለመቅጣትና ለማሳፈር የሰማይ ዝናብ እንዳይዘንብ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ የሰማይ ዝናብም በኤልያስ ቃል ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ሳይዘንብ ቀጥ አለ፡፡ ከእነዚህ ዓመታት በኋላ ግን ነቢዩ ኤልያስ ዝናብ እንዲዘንብ ወደ ፈጣሪው /ምልጃ/ ጸሎት አቀረበ፡፡ ዝናብም በሚገባ ዘነበ 1ኛነገ. 17፡1-7 እንደገና 1ኛነገ. 18፡30-46 በጸሎቱ መሥዋዕቱን ከሰማይ እሳት ወርዶ በላለት፡፡

2ኛ. ለሞተው ሕፃን ልጅ ስለእናቱ ሲል ኤልያስ ወደ እግዚአብሔር ጸልዮ /ምልጃ/ አቅርቦ የልጁም ነፍስ ተመልሳ ልጁም ከሞት ተነሳ 1ኛነገ. 17፡17-24፡፡
የነቢዩ ኤልሳዕ አማላጀነት

ገቢሬ ተአምር ኤልሳዕም በጸሎቱ /በምልጃው/ ብዙ ተአምራቶች አድርጎአል፡፡ ከተአምራቶቹም መካከል አንደኛው የሞተውን ልጅ ጸልዮ ማስነሳቱ ነው 2ኛነገ. 4፡18-37 ራሱ ታሞ የሞተው ልጅ ነው ያስነሳው፡፡

የዳዊት አማላጅነት

"ምንተ ገብሩ እሉ አባግዕ እንዘኖላዊሆሙ አነ ዘአበስኩ" "ጠማማም ሥራ እኔ አድርጌአለሁ፡፡ እነዚህ በጐች ግን ምን አደረጉ እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ እንድትሆን" በማለት ከአንጀቱ በአቀረበው ጸሎት /ምልጃ/ መቅሰፍቱ በፈጣሪ ቸርነት ተገታ 2ሳሙ. 24፡15-25፡፡

የነቢዩ ኤርምያስ ምልጃ

በአሥር ቀን ጸሎት /ምልጃ/ በእስራኤላውያን ታስቦ የነበረውን መቅሰፍት አንደተገታ ተገልጾአል ኤርምያስ. 42፡1-17፡፡ እስካሁን ድረስ ከሞላ ጎደል ያየነው የቅዱሳን ምልጃ በዘመነ ብሉይ ነው፡፡

ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ የቅዱሳን ጻድቃን ምልጃ በዘመነ ሐዲስ እናያለን፡-

ይህ የአማላጅነት አገልግሎት ሳይቋረጥ በዘመነ ሐዲስም ማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ዘመንና በዘመነ ሐዋርያትም ይፈጸም እንደነበረ ከዚህ ቀጥለን እንመለከታለን፡፡ በወንጌል እንደ ተጻፈው "ልጄ ታሞ ለሞት ተቃርቦአልና ፈውስልኝ" በማለት ስለታመሙ ሰዎች ወጥተው በአቀረቡት ምልጃ እንኳን ሲታመሙ ሲሞቱ ሳይቀር ከሞት እያስነሳ በጥያቄአቸው መሠረት ይፈቅድላቸው እንደነበር ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል ማቴ. 9፡18-20፡፡

በዚህ ዓይነት ጌታችንን እየለመኑ ልጆቻቸውን ያዳኑ ብዙ ናቸው ማቴ. 15፡21፣ ማቴ. 17፡14፣ ማር. 5፡22-44፣ ሉቃ. 7፡1-10፡፡

ስለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንዳንድ ጊዜ በሽተኞች በቀጥታ ሲለምኑት ይፈውሳቸው እንደነበረ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከዚህ በላይ እንዳየነው ስለበሽተኞቹ ሌሎች ሰዎች በማለዱላቸው ጊዜ ይፈውሳቸው ነበር፡፡ በዚህ መሠረት አማላጅነት ማለት አንዱ ስለሌላው መጸለይና መለመን፣ ማማለድ ማለት ነው፡፡

አማላጅነት በዘመነ ሐዋርያት

ሐዋርያት በተሰጣቸው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ መሠረት በሐዲስ አማንያንና በበሽተኞች ላየ እጃቸውን አያኖሩ መንፈስ ቅዱስን ሲያሰጡና ሕመምተኞች ሲፈውሱ ያየ ሲሞን ይህን ታላቅ የመንፈስ ቅዱስ ሥልጣን እንዲሰጠው ገንዘብ ይዞ ወደሐዋርያት ቀረበና እንዲህ አላቸው እጄን በምጭንበት ሁሉ መንፈስ ቅዱስን ይቀበል ዘንድ ለእኔ ደግሞ ይህን ሥልጣን ሰጡኝ አለ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ይህንን ሰምቶ ሲሞንን አጥብቆ ገሰጸው ንስሐም እንዲገባ መከረው፡፡ ሲሞን የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ /ጸጋ/ በገንዘብ መግዛት /መለወጥ/ ታላቅ ስሕተት መሆኑን ከተገነዘበ በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስን ካላችሁት ማለትም ከተናገራችሁት አንዳች እንዳይደርስብኝ እናንተው ወደ ጌታ ለምኑልኝ አማልዱኝ አላቸው ዮሐዋ. 8፡14-25፡፡

ከዚህ ላይ ከሲሞን አባባል የምንረዳው ዓቢይ ቁም ነገር አለ ይኸውም አንዳች ክፉ ነገር እንዳይደርስብኝ እናንተ ወደ እግዚአብሔር አማልዱልኝ /ለምኑልኝ/ ማለቱ በዚያን ጊዜ ሐዋርያት ስለበደሉ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ይጸልዩና ምልጃንም ያቀርቡ እንደነበረ ይረጋገጣል፡፡

የቅዱሳን ታላቅ ዕውቀትና ምልጃ በአጸደ ነፍስ

ቅዱሳን በአካለ ሥጋ ሆነው ማንም ሳይነግራቸው እጅግ ምሥጢራዊ የሆኑ ነገሮችን ካወቁ የዚህን ዓለም ውጣ ውረድና ፈተና አልፈው በአካለ ነፍስ ሲሆኑማ ምን ያህል የጠለቀ እውቀት ይኖራቸው? ቅዱስ ጳውሎስ ዛሬስ በመስታወት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን "ዛሬስ በዐውቀት ከፍዬ አውቃለሁ በዚያን ጊዜ ግን እኔ ደግሞ እንደታወቅሁ አውቃለሁን" በማለት የቅዱሳን ዕውቀት በአጸደ ነፍስ ታላቅ እንደሆነ ተናግሯል 1ቆሮ. 13፡12፣ 1ሳሙ. 28፡8-21፣ ሉቃ. 9፡30-32፡፡

ቅዱሳን በአካለ ነፍስ ሆነው በምድር የሚሰራውን ነገር ማወቅ እስከ ቻሉ ድረስ የኛን ልመና ሰምተው መግለጽ አይሳናቸውም፡፡

በአካለ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን "ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድምን ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትቀበልምን?" በማለት በአካለ ነፍስ እንደሚከሱ ራዕይ. 6፡9-11፡፡ በአጸደ ነፍስ ስለሚያውቁ ለቀረቡት ጥያቄዎች በዚ መልስ ነው፡፡ ቅዱሳን በአካለ ነፍስ ተበቀልልን ብለው ከለመኑ ለበጎ ነገር አማልዱን ስንላቸውማ ምን ያህል አብዝተው ይለምኑልን?

እንኳን ቅዱሳን /ጻድቃን/ ይቅርና በበደልና በኃጢአት ይኖር የነበረው ባለጸጋ /ነዌ/ በአካለ ነፍስ ሆኖ የወንድሞቹን በንስሐ አለመመለስ አውቆ አልአዛርን ስደድላቸውና ያስትምራቸው ሲል አብርሃምን ለምኖላቸዋል ሉቃ. 16፡20-31፡፡

ጌታ ሐዋርያትን "አንትሙ ውእቱ ብርሃኑ ለዓለም" ያላቸው ብርሃንነታቸው በዚህ በኃላፊው ዓለም ብቻ ተወስኖ እንዲቀር አይደለም፣ አማላጅነታቸውም በሕይወተ ሥጋ ሳሉ ነው እንጂ ከሞቱስ በኋላ ማማለድ የለባቸውም እንዳይባልማ የሰው ልጅ በግርማ መንግሥት በክበብ ትስብዕት መጥቶ በጌትነቱ በተገኘ ጊዜ እናንተም በ12 መንበሮች ተቀምጣችሁ በ12ቱ ነገደ እስራኤል ላይ ትፈርዳላችሁ ብሎአቸዋል ማቴ. 19፡28 ማማለድና መፍረድስ የቱ ይቀላል?

ጠቢቡ ሰለሞንም ቅዱሳን ጻድቃን ከሞቱ በኋላ በኃጥአኑ ላይ እንደሚፈርድባቸው ለደጋጉ እንዲፈርድላቸው ሲያስረዳ "ወብእሲሰ ጻድቅ መዊቶ ይኬንን ረሲዓነ እንዘሀለሙ ሕያዋኒ ሆሙ" ጻድቅ ሰው ግን ከሞተ በኋላ በሕየወት ሳሉ እግዚአብሔርን የዘነጉ ሰዎችን ይገዛል /ይቀጣል/ ይላል፡፡ ጥበብ. 2፡20፣ አማርኛው ግን 4፡16 ላይ ነው፡፡

በዚሁም መሠረት መሞት ማለት-

1ኛ የነፍስና የሥጋ መለያየት ሲሆን 2ኛ መሞት ማለት ደግሞ በአካለ ነፍስ ወደ መንፈሳዊ /ረቂቅ ዓለም መሄድ/ ወደ እግዚአብሔር መድረስ /መመለስ/ ማለት ነው፡፡ በሞት ጊዜ ነፍስ ወደ እግዚአብሔር እንደምትሄድና ሟቹ ሰው በነፍሱ እግዚአብሔርን ማየት እንደሚችል መጽሐፍ ቅዱስ በሰፊው ያስረዳል፡፡

ጻድቁ ኢዮብ በነፍሱ ወደ እግዚአብሔር እንደሚሄድ ሲያስረዳ "ይህ ቁርበቴ ከጠፋ በኋላ በዚያን ጊዜ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንዳይ አውቃለሁ፡፡ እኔ ራሴ አየዋለሁ፡፡ አይኖቼም ይመለከቱታል" ሲል ተናግሯል ኢዮብ. 19፡26፡፡

እንዲሁም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መሞት ማለት በነፍስ ወደጌታ መሄድና ከጌታ ጋር በክብር መኖር ማለት መሆኑን ሲገልጽ "ለእኔ ሕይወት በክርስቶስ አምኖ መሞት ጥቅም ነውና ነገር ግን በሥጋ መኖር ለኔ ለሥራ ፍሬ ቢሆንም ምን እንደምመርጥ አላውቅም በእነዚህም በሁለቱ እጨነቃለሁ፡፡ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፡፡ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ይህ ነውና" በማለት አስረድቷል ፊልጵ. 1፡24-24፡፡

ነገር ግን በቅዱሳን ክብር የማያምኑ መናፍቃን ከዚህ በላይ የቀረበውን ማስረጃ ላለመቀበል ብዙ ማደናገሪያ ለመደርደር ይሞክራሉ፡፡ ይህም የሚያሳየው "አውቆ የተደበቀን ቢጠሩት አይሰማም" እንደሚባው እነሱ አውቀውና ወደው የቅዱሳንን አማላጅነት ስለካዱ ምንም ዓይነት ማስረጃ አይመልሳቸውመ ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ግን "መኑ ውእቱ ዘይትዋቀሶሙ ለሕሩያነ እግዚአብሔር" የእግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳንን አልበቃችሁምና አታማልዱም በማለት የሚከራከራቸው የሚወቅሳቸው ማን ነው? እርሱ ያከበራቸውንስ የሚያዋርድ ማን ነው? በማለት አስተምሮአል ሮሜ. 8፡30-31፡፡

ቅዱሳንም በሃይማኖትና በምግባር የጸኑ ስለሆነ የሚሳናቸው ነገር የለም፡፡ ተራራ ማፍለስ፣ ሙት ማስነሳት፣ ሕሙማንን መፈወስ እንደቻሉ ካወቅን፣ ማማለድ እንደማይሳናቸውም እናምናለን፡፡

እንግዲህ ክብረ ቅዱሳን እንዲሁ በአጭር ጊዜ ተነግሮ በአጭር ጽሑፍ ተጽፎ የሚያልቅ አይደለም፡፡ በአጭሩ ያልቃል ብሎ መገመት ወይም ማሰብ፣ አባይን በጭልፋ እንደሚባለው ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የቅዱሳን ምልጃ በብሉይ ኪዳንና በሐዲስ ኪዳን፣ የቅዱሳን ምልጃ በአጸደ ሥጋና በአጸደ ነፍስ የቅዱሳን ረቂቅ እውቀት በሚል ርዕስ በአጭሩ ለመግለጽ ሞከርኩ እንጂ የእግዚአብሔርን ሕግጋት /ትእዛዝ/ የፈጸሙና በጾምና በጸሎት ተወስነው የኖሩ በነፍስና በሥጋ ከፈጣሪያቸው ክብር የተሰጣቸው ብዙ ናቸው፡፡ ጸጋቸውና ክብራቸውም ተነግሮ አያልቅምና ለጊዜው ከዚህ ይቆየን፡፡

ክብረ ቅዱሳን መድኃኔ ዓለም በረድኤት አይለየን
አሜን!!!

የፎንት ልክ መቀየሪያ