Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

ዐቢይ ጾምና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮ

ክፍል አንድ

በመምህር ሙሴ ኃይሉ

በተለያዩ መጻሕፍት እንደተጻፈውና በተለያዩ የቤተክርስቲያናችን መምህራን ሊቃውንት በየዓውደ ምሕረቱ ዘወትር እንደሚተነተነው ጾም ማለት በታወቀ፣ በተወሰነ፣ በተቀመረ... ጊዜ ከመብል ከመጠጥ መከልከል፣ መቆጠብ፣ መወሰን... ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን "ጾም" ከክርስቲያናዊ ምግባርና ትሩፋት የሚመደብ ኣስተምህሮ ነው፡፡ ጾም የመሠረተውም ሆነ የታዘዘው ከፈጣሬ ሰማያት ወምድር ከእግዚአብሔር ነው፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ምዕመን ጾምን በመከተል ለሠራዔ ጾም (ጾም ለሠራለት) አምላክ እየተገዛ፣ እያመለከ፣ እያከበረ፣ እየታዘዘ... በበጎ ሕሊና ተሞልቶ ፈቃደ ሥጋውን (ትዕቢት፣ ስስት፣ ዝሙት፣ ቅንዓት...) ለፈቃደ ነፍሱ (የዋህነት፣ በጎነት፣ ርህሩህነት...) በማስገዛት በፈጣሪ መመሪያ፣ ትእዛዝ እና ፈቃድ መኖር ማለት ነው፡፡

ጾም መጋቤ ዓለማት እግዚአብሔር ከብዝሐ ፍቅሩ የተነሳ ምልዓተ ፍቅሩን ለማጋራት ፈልጎ የፈጠረው አዳም የመታዘዙ ምስጢር አድርጎ ከሰጠው ጸጋ የመነጨ የመንፈሳዊ ሕይወት ምርኩዝ ነው፡፡ ይኸውም በመንፈሳውያን ጸጋዎች አንቆጥቁጦ ለፈጠረው አዳም ሁሉም ነገር አሟልቶ ከሰጠው በኋላ የፈጣሪን አዛዥነት፣ የፍጡርን ታዛዥነት የሚገልጽ ሕግ መኖር ስለነበረበት "ከዚህ ከገነት ፍሬ ሁሉ ብላ ነገር ግን ክፉውንና ደጉን ከምታሳውቅ ከዚህች ዕፀ በለስ እንዳትበላ ከበላህ ግን ሞትን ትሞታለህ ብሎ መስጠቱ መሠረተ ጾም እግዚአብሔር መሆኑ ይገልጽልናል፡፡

በዚህ በጥንተ ፍጥረት ጊዜ የተጀመረው ይኸው አምላካዊ ፈቃድ መንፈሳዊ የምግባር የትሩፋት እሴት ስለሆነ ይኸው ትእዛዝ ከተነገረ ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ዘመን እየተሻገረ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ ምክንያቱም የሃይማኖት መገለጫ ስለሆነ፡፡

ጾም ፈቃደ ነፍስን በፈቃደ ሥጋ ለማሰልጠን የአጋንንት ኃይል ለመቋቋም የሚያስችል የክርስቲያኖች ጋሻ.. በመሆኑ በሃይማኖት ለሚመሩ ምዕመናን እጅግ አስፈላጊና ከምንም በላይ የሕይወታቸው መርህ መሆን እንደሚገባ ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ እንዲህ በማለት ያስተምራል፡-

 • "አሁንም ወንድሞቻችን በዚህ በሥጋችን ሳለን ፈቃደ ሥጋችንን ልንሠራ አይገባም፣ ፈቃደ ሥጋቸውን የሚሠሩ ሰዎች በወዲያኛው ዓለም ምዉታን ናቸውና፡፡ የሥጋችሁን ፈቃድ በነፍሳችሁን ፈቃድ ድል ካልነሳችሁት ለዘለዓለም ሕያዋን ትሆናላችሁ፡፡ የነፍሳቸውን ፈቃድ የሚሠሩ ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና" ሮሜ 8፡12-14

ጾም አበው ቅዱሳን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በጊዜ ቀምረው፣ በበታ ወስነው፣ በሁኔታ ገድበው... ባስቀመጡልን ወቅት ከእህልና ከውሃ በመከልከል ሰውነትን በማድከም ብቻ ሳይሆን ሌሎች ለስሕተት ከሚዳርጉ ነገሮችና ቦታዎች ተቆጥቦ በጸሎት መትጋትም እጅጉን አስፈለጊ ነው፡፡ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትም ይህንን እውነታ በተመለከተ እንዲህ ይላል፡፡

 • "እኔ ግን እዘንልን ለምንልን ባሉኝ ጊዜ ማቅ ምንጣፍ ለብሼ አዘንኩላቸው፤ ሰውነቴን በጾም አደከምኩዋት፤ ልመናዬም እኔም ወደመጥቀም ተመለሰችልኝ" መዝ. 34/35 .13

ጾም ከሥነ ምግባራት ሕግ አንዱ በመሆኑ እንኳንስ ያልተፈቀደውን ቢሆን የተፈቀደውም የማይጠቅም ከሆነ ፈጽሞ በመተው ለእግዚአብሔር ያለንን ፍጹም ፍቅር የምናስመሰክርበት ምስጢር ነው፡፡

ጾም ከመብልና ከመጠጥ ጋር የተያያዘም በመሆኑ፤ መብል ጊዜያዊ ስለሆነ ማለትም በዚህ ዓለም እስካለን ብቻ የምንገለገልበት እንጂ ዘለዓለማዊ ስላይደለ ለጊዜያዊ መብልና መጠጥ ምክንያት ከሃይማኖት ሥነ ምግባር እንዳንወጣ ቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያት ሲመክሩ "መብል በእግዚአብሔር ዘንድ ግዳጅ አይፈጽምልንም ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም ብንበላም አይረባንም አይጠቅመንም ብንተወውም አይጎዳንም /1ኛቆሮ.8.8.../" በማለት ሲመክሩን ቅዱስ ጳውሎስም የመብልና የሆድ ጊዜያዊነት አስመልክቶ እንዲህ በማለት አስተምሯል፡፡

 •  "ሁሉ ነገር ተፈቅዶልኛል፤ ሁሉ ግን አይጠቅመኝም፡፡ ሁሉ ተፈቅዶልኛል በእኔ ላይ ግን አንድ ነገር እንኳ አይሰለጥንብኝም፡፡ መብል ለሆድ ነው ሆድም ለመብል ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ሁለቱንም ያሳልፋቸዋል" 1ኛቆሮ 6.12-13፡፡

 •  "ለሚጠፋ ምግብ አትስሩ ይልቅስ የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ የዘላለም ሕይወት ስለሚሆን ምግብ ስሩ" ዮሐ. 67 እንዲል፡፡

በተወሰነ ከላይ ለመጠቆም እንደሞከርኩት ጾም ከመጀመሪያው ሰው ጀምሮ በዘመነ አበው፣ በዘመነ ኦሪት፣ በዘመነ ነቢያትና በዘመነ ሐዋርያት... ሁሉ የነበረ ከመሆኑም በላይ የተለመደ የሃይማኖት መርሕም ነው፡፡ ለምሳሌ ክቡደ መዝራዕት ሊቀ ነቢያት ሙሴ በእግዚአብሔር ጣት ዓሰርቱ ቃላተ ኦሪት የተጻፈባቸውን ሁለቱ ጽላቶች ለመቀበል የበቃውና ከሲና ተራራ የቃል ኪዳን መገለጫ ጽላቶች ይዞ ወደ ሕዝቡ ሲወርድ ፊቱ በብርሃን ከመሞላቱ የተነሳ ማየት ስላልቻሉ "ሙሴ ሙሴ ተገልበብ ለነ" ሙሴ ፊትህን ሸፍንልን ብርሃን የተሳለበት ፊትህን ማየት አይቻለንምና ያሉት 40 ቀንና 40 ሌሊት በመጾሙና እግዚአብሔርም በሰማያዊ በረከት በመጐብኘቱ ምክንያት ነው፡፡ (ዘፀ. 31.18 ፤ 34.29)

 •  ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስም የዚህን ዓለም ሞት ሳይቀምስ ወደ ብሔረ ሕያዋን በእሳት ሠረገላ ለማረግ የበቃው 40 ቀን ከጾመና ከጸለየ በኋላ ነው፡፡ (1ኛ ነገ. 19 .7-18)

 • ዳንኤልም ሃያ አንድ ቀን ጾሞ ከጸለየ በኋላ የፈጣሪው የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጾለታል፡፡ (ዳን. 10.2-13)፡፡ እያሱም ከሙሴ ጋር እኩል በእግረ ደብር ሆኖ ጾሞአል (ዘጸ. 24. 13-13)

መልአከ ብርሃናት አድማሱ ጀምበሬ "ኰክሐ ሃይማኖት" በተሰኘ መጽሐፋቸው ባስቀመጡት ኦርቶዶክሳዊ መልስ ስለጾም ባጭሩ ሲያስቀምጡ፡-

"... ጾምሰ ተከልኦተ ብእሲ እመብልዕ በጊዜ ዕውቅ በውስተ ሕግ እንዘ ይትአዘዝ ለዘሐገጎ ለሥርየተ አበሳ ወብዝኀ ዕሤት ፈቂዶ ኪያሁ ከመ ያድክም ኃይለ ፍትወት ወትትአዘዝ ለነፍስ ነባቢት፡፡ ጾም ማለት ሰው ሕጉን ለሠራለት ለክርስቶስ እየታዘዘ ኃጢአቱን ለማስተሥረይ ብዙ ዋጋ ለማግኘት ሽቶ የፍትወት ኃይል ደካማ ሥጋ ለነባቢት ነፍስ ትገዛላት ዘንድ በታወቁ ጊዜያቶች ከመብል መካከል ነው ብሎ ከመብል መከልከል፤ ያውም በታወቀ ጊዜ መሆኑን ለይቶ ጽፎአል፡፡ (ፍት.ነገ አንቀጸ ጾም ተመልከት)
..... ቅዱስ ያሬድ አንደኛ የሐዋርያውን ቃል ጠቅሶ አከለክሙ መዋዕለ ዘሐለፈ ዘተቀነይክሙ ለግእዘ ሥጋክሙ እምይእዜሰ ጹሙ ወጸልዩ ለእግዚአብሔር ተቀነዩ ብሏል፡፡ /1ኛ ጴጥ.4 .1-4/
ሁለተኛ ወዝንቱ ዘመድ ኢይወጽእ ዘእንበለ በጾም ወበጸሎት ያለውንም ጠቅሶ ጾም ትፌውስ ቁስለ ነፍስ ወታጾምም ኩሎ ፍትወታተ ዘሥጋ ትሜሕሮሙ ለወራዙት ጽሙና ብሎ ጾም ፈቃደ ሥጋን ከመተው ጋራ መሆኑን ካስረዳ በኋላ ቀድሱ ጾመ ቀድሱ ጾመ እስመ ሙሴኒ በሲና ጾመ፤ ጾመ እግዚእነ ጾመ በእንቲአነ አርዓያሁ ከመ የሀበነ ብሎ ሙሴ 40 ቀን ከምግብ ተከልክሎ መጾሙን አስረድቶናል፡፡ ጾም ከምግብ መከልከል አይደለም ማለትን ተው፡፡ ከዚህ የበለጠ ስለጾም መረዳት ብትፈልግ የሕግ መጽሐፍ ተመልከት፡፡ (ዘፀ.2428 ፤ ማቴ.4፡2 ፤ ማር.1፡13 ፤ ሉቃ.4.2)" በማለት አመስጥረውታል፡፡ (መልአከ ብርሃናት አድማሱ ጀምበሬ፡ ኰክሐ ሃይማኖት፡1949 ዓ.ም ገጽ ከ241 - 242
ጾም፡- በቅዱሳን አበው፣ በቅዱሳን ነቢያትና በቅዱሳን ሐዋርያት እምነት የተመሠረቱ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ከነቢያትና ከሐዋርያት ሲያያዝ የመጣ የጾም ሕግና ሥርዓት አላቸው፡፡ የጊዜው ቀመር፣ የአጿጿሙ ትውፊትና፣ የቦታው ሁኔታ ከሚለያቸው በቀር ሁሉም የጾም ሕግና ሥርዓት እንዲሁም ጥልቅ የሆነ አስተምህሮና ግንዛቤ አላቸው፡፡
ከእነዚህ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት (እህት አብያተ ክርስቲያናት) አንዷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በመሆንዋ እንደ ጥንታዊነቷና ሐዋያዊነቷ መጠን ከሐዋርያት የተቀበለችውን አስተምህሮ በጥንቃቄ አክብራ በመያዝ ሳትጨምርና ሳትቀንስ በሥርዓቱ እየተገለገለችበት ትገኛለች፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሕግ የታወቁ ሰባት አጽዋማት አሏት፡፡ እነርሱም፡-

1. ዐቢይ ጾም 5. ጾመ ረቡዕ ወዓርብ /ጾመ ድኅነት/
2. ጾመ ሐዋርያት 6. ጾመ ገሃድ እና
3. ጾመ ነቢያት 7. ጾመ ነነዌ ናቸው፡፡
4. ጾመ ፍልሰታ

ቅዱስ አባ ሕርያቆስ ዘሀገረ ብሕንሳ ቅዳሴ ማርያም በደረሰበት አንቀጹ "ንግባዕኬ ኅበ ጥንተ ነገር......." ብሎ ወደ ተነሳበት ምስጢር እንደተመለሰ ሁሉ እኛም ወደ መነሻ ርእሳችን እንመለስና ስለ ዐቢይ ጾም፤ ቀላይ ከሆነው ከሊቃውንት አስተምህሮ እንዲሁም ጥልቅና ምጡቅ ከሆነው ከቤተክርስቲያናችን ትውፊት ውስጥ በጭልፋም ሳይሆን እንደ ታናሽነቴ መጠን በትንሽ ማንኪያ በሚመስል ሁናቴ እነሆ ልበል፤

ዐቢይ ጾም፡-

የጌታ ጾም "ዐቢይ" የተባለበት ምክንያት፡-
1. ከሌሎች አጽዋማት የጊዜ ብልጫ ወይም ረጅም ጊዜ /አምሳ አምስት ቀን/ ስለሆነ ነው፡፡
2. ዐቢይ መባሉ አስቀድሞ ዓበይት ነቢያት የጾሙት በሐዲስ ዘመን ደግሞ መድኃኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ኦሪትንና ሕግን ለመጠበቅና ለመፈጸም እንዲሁም ለእኛ አርአያና ምሳሌ ሊሆን /ጾሞ ጹሙ ለማለት/ የጾመው ጾም ስለሆነ ዐቢይ ተብሏል፡፡
3. ጌታ በዚህ መዋዕለ ጾሙን ከፈጸመ በኋላ ከሰይጣን የቀረቡለትን ሦስቱን አርዕስተ ኃጣውእ ድል ያደረገበት በመሆኑም ዐቢይ ተብሏል፡፡


ከዚህ በተጨማሪም ዐቢይ ጾም፡-

1ኛ. የጌታ ጾም /ጾመ እግዚእ/፣ የኢየሱስ ጾም /ጾመ ኢየሱስ/ ተብሎም ይጠራል፡፡
2ኛ. ዐቢይ ጾም "ሁዳዴ ወይም ጾመ ሁዳዴ" ተብሎም ይጠራል፡፡
ሁዳዴ፡- የተባለበት ምክንያት ባጭሩ መልአከ ሰላም ዳኛቸው ካሳሁን "ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባራት" በተሰኘ መጽሐፋቸው ሲያስቀምጡ፡-
ዐቢይ ጾም.... በሕዝባዊ አገላለጥ ሁዳዴ ይባላል፡፡ ቀደም ባለው ሥርዓተ ማኅበር የመሬት ይዞታና አጠቃቀም ሥሪት በመንግስት ይዞታ የነበሩ ሰፋፊ መሬቶች "ሁዳዴ" በመባል ይታወቃሉ፡፡ የግብርናው ተግባር የሚከናወነው በአከባቢው ነዋሪ ሕዝብ ኅብረትና ጉልበት ስለሆነ የብዙኃን እንቅስቃሴ ያለበት መሆኑን ለመግለጽ "ሁዳዴ" ተብሎአል፡፡ ዐቢይ ጾምም ክርስቶስ ለተከታዮቹ ምዕመናን በምሳሌነት የጾመው የአዋጅ ጾም ስለሆነ፣ ልጅ አዋቂ፣ ሴት ወንድ ሳይለይ ክርስቲያኖች ሁሉ ይጾሙታል፡፡ የአዋጅ የማኅበር ጾም በመሆኑ "ሁዳዴ" የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ከሌሎች የጾም ወራት ሠፋ ያለ ጊዜና ብልጫም አለው፡፡ (መልአከ ሰላም ዳኛቸው ካሳሁን፡ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባራት፡ 1997ዓ.ም፡ ገጽ 121)

ይቆየን

ስብሐት ለእግዚአብሔር ኪያነ ዘፈጠረ ከመ ናምልኮ፣
/እንድናመልከው እኛን ለፈጠረ ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን/

የፎንት ልክ መቀየሪያ