Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ? ሉቃ. 10፡25

ከንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ

ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ተገልጦ ወንጌል መንግሥተ ሰማያትን እየተዘዋወረ በሚያስተምርበት ጊዜ ከተለያዩ የሕግ አዋቂዎች የተለያዩ ጥያቄዎች ይቀርቡለት እንደነበር በቅዱስ ወንጌል ተጽፎ የምናገኘው እውነት ነው፡፡ ከነዚህም መካከል በሉቃስ. 10፡25 ተመዝግቦ የሚገኘው ስሙ ሳይጠቀስ አንድ ሕግ አዋቂ ተብሎ የተጠቀሰው ይገኝበታል፡፡

በመሠረቱ ስለሥራ በምናወሳበት ወቅት ከሥራ ጋር ተዛምዶ ያላቸው አንዳንድ ነገሮች መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ እንደምንረዳው ሥራ የደስታ ምንጭ ነው፡፡ እግዚአብሔር ፍጥረታትን አሳምሮ በፈጠረ ጊዜ ደስተኛ እንደነበረ በስፋት ተገልጾአል፡፡ ዘፍ. 1፡12፣ ምሳ. 8፡27-31፣ መዝ. 103፡31፡፡ በዚህም መሠረት እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ሲፈጥረው በአርአያውና በአምሳሉ ነውና እርሱ በሥራው እንደሚደሰት ሁሉ ሰዎችም በሥራ ደስተኞች እንዲሆኑ አስቦ ባርያቸው ለሥራ የሚነሣሣ፣ ሥራን የሚናፍቅ አድርጎ ከመፍጠሩም በላይ በሥራ ደስተኛ ሆኖ እንዲኖር ብሎ "ሰውን ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በገነት አኖረው" ዘፍ. 2፡15፡፡

ከዚህ ከጥንተ ተፈጥሮ ተነሥተን ዛሬ እኛ እስከ አለንበት ዘመን ድረስ የተከናወኑ መልካም ነገሮች ሁሉ የሥራ ውጤቶች ናቸው፡፡ ታፍሮና ተከብሮ ለመኖር የራስን የቤተሰብ ኑሮ በሚገባ የተሟላ ለማድረግ የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ በአጠቃላይ በዓለመ ሥጋ ይሁን በዓለመ ነፍስ ያለሥጋት በተመቻቸና አስተማማኝ የሆነ ሕይወት ለመኖር መሠረታዊ መፍትሔው ሥራ ነው፡፡

ስለሆነም ይህንን ዕድል ለማግኘት ሰው ሁሉ አጥብቆ መፈለግና ማወቅ ያለበት የዘላለም ሕይወት የሚገኝበትን ሥራ መሥራት ነው፡፡ በበጎ ሥራ በመጽናት ምስጋናና ክብርን የማይጠፋንም ሕይወት ለሚፈልጉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል ተብሎ ተጽፎአልና ሮሜ. 2፡7፡፡

እንግዲህ ሥራ በዓለመ ሥጋ ይሁን በዓለመ ነፍስ ያለው ጥቅም ምን ያህል እንደሆነ ካየን በኋላ በተለይም በመንፈሳዊ ረገድ መፈጸም ያለበት መልካም ሥነ ምግባር እንዴት ነው የሚለውን መመልከቱ ይበጃል፡፡

ከርእሱ በተጠቀሰው አንድ የሕግ አዋቂ ሰው የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ፈልጎ ደም ሆኖ ያለሥራ እንደማይገኝ በውል ስለተረዳ በተሳሳተ መንገድ ሂዶ ለዘላለም ሕይወት የማይበቃ ሥራ እየተከተለ ከንቱ ልፋት እንዳያጋጥመው በመስጋት መሥራት ብቻ ሳይሆን ለዘላለም ሕይወት የሚያበቃ የማያጠራጥር እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ለመሥራት ፈልጎ ለእውነተኛው መምህር ጥያቄ አቀረበ፡፡ ይህም ምንም እንኳ እርሱ ለዘላለም ሕይወት የሚያበቃ ምን እንደሆነ በውል ያወቀ ሰው እንደነበረ ለጌታችን ከሰጠው መልስ አንጻር ያወቀውን ነገር መጠየቅ ብዙ አስፈላጊ ባይመስልም መልካም የሚሠሩ እየመሰላቸው በተሳሳተ መንገድ ለሚሄዱ ሁሉ ትምህርት ሰጭነቱ ግን የማይታለፍ ነው ምክንያቱ በዚህ ምክንያት የከሠሩ ብዙ አሉና፡፡

ለምሳሌ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ብንወስድ በዚህ መሥመር ተጉዞ ያልሆነ አቅጣጫ ሂዶ እንደነበረ እናስተውላለን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ወንጌልን መቃወም ሐዋርያትን ማስገደል፣ ክርስቲያንን ማሳሰርና ማሳደድ እግዚአብሔርን እጅግ በጣም ደስ የሚያሰኝ ለእግዚአብሔር ሕግ ተቈርቋሪና ተከራካሪ እንደሆነና ይህም መልካም ሥራ እንደሆነ ይቈጥር ነበር፡፡ የሐሥራ. 22፡3-5፣7፣60፡፡

ነገር ግን ጳውሎስ እንዳሰበው መልካም ሥራ ሳይሆን ለዘላለም ኲነኔ የሚዳርግ መጥፎ ሥራ ነበር፡፡ እግዚአብሔርን ደስ እያሰኘ ሳይሆን ከዋለበት አላሳድር፣ ካደረበት አላውል እያለ ፈቃዱን እየተቃወመ ነበረ፡፡ የባህርይ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስን እያሳደደ በተጸራሪ ቆሞ ገደል አፋፍ ደርሶ ነበር፡፡

እንደዚሁም አይሁዳውያን እስከ ዛሬ ድረስ ከሕይወት ማዕድ ርቀው በጨለማ መንገድ የሚጓዙት ክርስቶስንና ተከታዮቹን ማሳደድ መልካም ሥራ እየመሰላቸው ለእግዚአብሔር ሕግ የቀኑ እየመሰላቸው ነው፡፡ ሮሜ. 10፡2፡፡ 7-10፡፡ ግን አልነበረም አስተዋዩ መምህራቸው ገማልያል እንደነገራቸው ከእግዚአብሔር ጋር ሲጣሉ እስከ ዛሬ ድረስ ይገኛሉ የሐ ሥራ. 5፡34-39፡፡

ስለዚህ መልካም እየሠራሁ ነኝ እያሉ ክፉን ሥራ በመሥራት ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት በሕይወት ፈንታ ዘላለማዊ ፍርድን መሸከምም አለና የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ የሚያስችል ትክክለኛ ሥራ አውቆ ለመተግበር ሕግ አዋቂው ያቀረበው ጥያቄ መከተል እጅግ ይጠቅማል፡፡

ይህ ሰው ላቀረበው ጥያቄ መልሱ የተሰጠው በጥያቄ መልክ ሲሆን ጠያቂው በሰጠው መልስ ጥያቄው ተደምድሞአል፡፡ እርሱም ከኦሪት የተጻፈው ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህም፣ በፍጹም ኃይልህም፣ በፍጹም አሳብህም፣ ውደድ፣ ባልንጀራህንም እንደራስህ ውደድ የሚለው ነው፡፡ ዘዳ. 6፡5፣ ዘሌ. 19፡18፡፡

ሕግ አዋቂው ሰው ይህንን መልስ ከሰጠ በኋላ የዘላለም ሕይወትን ለመውረስ የሚያስችል ከዚህ የበለጠ ሌላ ነገር በምንም ዓይነት የሌለ በመሆኑ የተሰጠው መልስ ይህንን አድርጎ በሕይወትም ትኖራለህ የሚል ቀጥተኛና አጭር መልስ ነው፡፡ ዛሬም የዘላለም ሕይወትን ለመውረስ ምን እናድርግ ብለው ለሚጠይቁ ሰዎች መልሱ ይኸው ነው፡፡ "ለሺ ፍልጥ ማሠሪያው ልጥ" እንደሚባለው ሁሉ በመጻሕፍት ሁሉ የተነገረው በዚህ አጭር አገላለጽ ተጣምሮና ተካቶ ይገኛልና ነው፡፡ አንድ ሰው እግዚአብሔርን በፍጹም ከወደደ በቃሉ ይኖራል እንጂ ቃሉን አያፍርስም ከእሱ በቀር ሌላ አያመልክም፣ ሌላውን ሁሉ ተስፋ አያደርግም ይወደዋልና አይገድልም፣ አይሰርቅም፣ አይዋሽም፣ አያመነዝርም፣ ስሙን በከንቱ አይጠራም፣ ክፉ የሆነውን ሁሉ አይመኝም በአጠቃላይ በቃሉ ይኖራል እንጂ ቃሉን አይተላለፍም፡፡

ዮሴፍን የጴጥፋራ ሚስት ለመጥፎ ሥራ በጋበዘችው ጊዜ ድርጊቱን ቢፈጽመው ማንም ሰው የሚያየው አልነበረም ግን ዮሴፍ ያ የሚወደው አምላክ ከፊቱ ቆሞ እያየው እንደሆነና ይህንን ነገር ቢያደርገው ፍቅረ እግዚአብሔርን እንደሚያፈርስበት፣ በማስተዋል በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ይህንን ትልቅ ክፉ ኃጢኣት እሠራለሁ በማለት ፍቅረ እግዚአብሔርንና ፍቅረ ቢጽን የጠበቀው ዘፍ. 39፡9፡፡

ይህ የዮሴፍ መልካም ሥራ ነበር፡፡ ብዙ ታላላቅ ሥራዎች እንዲያከናውን ያስቻለው ለብዙ ጥበበኞች ነን ባዮች ያልተቻለው ትርጓሜ ሕልም ከሚወደውና በመልካም ሥራ ከተከተለው አምላክ ተገልጾለት፡፡ በነበረው መልካም ሥራ በመላዋ ምድረ ግብጽ ተከብሮና ታፍሮ እንዲኖር ከመቻሉም በላይ በከነአንና በግብፅ ለሰባት ዓመታት በዘለቀ የረኃብ ዘመን ለብዙ ሰዎች ሕይወት መትረፍ ምክንያት ድኅነት ሆነ፤ ምክንያቱም ሰው በመልካም ሥነ ምግባር ፈጣሪውን ከመሰለ ፈጣሪውም ከእርሱ ጋር ይሆናል እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ የሚያቅተው ነገር የለምና ዘፍ. 39፡21፣ ሮሜ. 8፡31፡፡

ሌላው ከፍቅረ እግዚአብሔር ጋር አብሮ ሲሄድ የምናየው ፍቅረ ቢጽ ነው ወይም ዘር፣ ጐሳ ዘመድ፣ ባዕድ ሳይለዩ ከአርአያ እግዚአብሔር የተፈጠረውን ሰው ሁሉ መውደድ ነው፡፡ ለሰዎች ሁሉ የምናደርገው ፍቅር መመዘኛውና መሥፈርቱ እንደራስህ አድርገህ ውደድ የሚል ነው፡፡ ትክክለኛ አገላለጽ ነው አሁንም ቢሆን አንድ ክፉ ነገር በሰዎች ሲደርስ በምናይበት ጊዜ በቀላሉ እንገምት ይሆናል ግን ይህ በወንድሜ የደረሰው በኔ ላይ ቢደርስ ምን እንደምሆን ስገነዘብና ምን ዓይነት ዕርዳታ እንዲደረግልኝ እንደምፈልግ መልሱ በግል ማየቱ ቀላል ነው፡፡ በእንደዚህ መልኩ ተገንዝበን እኛ በታመምን ጊዜ ብዙ ሰዎች እንዲጠይቁን የሕክምና፣ የገንዘብ ዕርዳታ እንዲያደርጉልን የምንፈልግ ከሆነ ያም ወንድማችን እንደዚሁ የሚፈልግ መሆኑን ተገንዝበን ከልብ እንድንወደው ያስፈልጋል "ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው" ተብሎአልና ማቴ. 7፡12፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅረ ቢጽ ወይም የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ የሚያስችል ሰውን እንደራስህ አድርጎ መውደድ ማለት ምን እንደሆነ በዝርዝር ምሳሌ ለጠያቂው የሕግ አዋቂ ሰው ሲያስረዳ፣ አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ሲወርድ ወንበዴዎች አግኝተው ገፈፉት ደበደቡት፣ እስከሞትም ድረስ አቈስለው በሞት አፋፍ ላይ ጥለውት ሄዱ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ አንድ ካህን አይቶት እንዳላየው ዘወር ብሎ አልፎ ሄዶ እንዲሁም አንድ ሌዋዊ መጥቶ እንደካህኑ አይቶት እንዳላየ ዘወር ብሎ ሄዶ በኋላ ግን አንድ ሳምራዊ መጥቶ ባየው ጊዜ አዘነለት፣ አስፈላጊውን ሁሉ አደረገለት፣ በቊስሉ ላይ ዘይትና ወይን አደረገለት፣ በአህያውም አስቀምጦ ወደ እንግዶች ማደሪያ ወሰደው፣ የሚድንበትም መንገድ አፈላለገ፣ ሁለት ብርም አውጥቶ በዚህ አድንልኝ ከዚህ ሌላ የምትከስረው ሁሉ ስመለስ እከፍልሃለሁ ብሎ መንገዱ ሄደ፣ ብሎ ከነገረው በኋላ ከሦስቱ ሰዎች ለተደበደበው መልካም የሠራለት የትኛው ይመስልሃል ብሎ ሕግ አዋቂውን ሲጠይቀው ምሕረት ያደረገለት ነዋ ብሎ መለሰ፡፡ በዚህ ጊዜ ጌታችን ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግ ብሎ ለባልንጀራው ማድረግ የሚገባውን ነገር አስረድቶ የዘላለም ሕይወትን ለመውረስ የሚያስችለውን ነግሮታል ሉቃ. 10፡29-37፡፡

እንግዲህ ከዚህ ምሳሌ የምንረዳው ትልቁ ቁም ነገር ሕይወት የምትገኘው ወንድምን እንደራስህ በመውደድ በመከራው ቀን መከራውን መከራ አድርጎ ተቀብሎ በመረዳዳት መሆኑን ነው፡፡

ሰው ፍቅረ እግዚአብሔርን ፍቅረ ቢጽን አንድ አድርጎ ከያዘ ሕግንና ነቢያትን በሙሉ ፈጸመ ማለትም የሕግና የነቢያት የመጻሕፍት ሁሉ ትእዛዝ ፈጸመ በማለት ጌታችን ራሱ በማያሻማ መልኩ ገልጾታልና፡፡

ስለሆነም ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ይህንን በዕውቀት ተገንዝቦ ለመተግበር የሚያስቸግር አይደለምና ዘወትር ሊፈጽመው ይገባል ማቴ. 22፡40፡፡

በዚህ ዓይነት ሁኔታ መልካም ሥራን እየሠራ እርሱ በርሱ እየተረዳዳ ማኅበራዊ ኑሮን አመቻችቶ ፈጣሪውን አመስግኖ በደስታ ሲኖር በእግዚአብሔር የተፈጠረው የሰው ልጅ፣ ይህንን ከአምላኩ በተፈጥሮና በመጻሕፍት ትእዛዝ የተነገረውን የሕይወት ሥራ ጥሎ ራሱ ባወጣውና ሁሌም ሥጋት ነው፣ ጭንቀት ነው፣ ረኃብ ነው፣ ጦርነት ነው፣ በሽታ ነው፣ ስደት ነው ሌላም ሌላም ችግሮች ዓለማችንን በመክበብ ናቸው ለምን ቢባል መልሱ አንድና አንድ ነው መልካም ሥራ ምግባር ስለጠፋ፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር ስለተረሳ፣ ሰዎች እንደ ዮሴፍ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር እንዴት እንሠራለን አይቶ ይፈርድብናል ማለትን ትተው ከነአካቴው ህልውናውና ተቈጣጣሪነቱን ስለካዱ ብቻ ነው፡፡ ታዲያ ከዚህ ከጠማማ ትውልድ መካከል ለእግዚአብሔር ወግኖ ከቃሉ ጋር በመሆን በበጎ ሥራው ምሳሌ እየሆነ የእግዚአብሔርን ስም እያስከበረና እያስመሰገነ ዓለምን ከገጠማት ድቅድቅ የሥነ ምግባር ጨለማ የሚያላቅቃት ማን ነው፡፡

እግዚአብሔር ይህንን ኃላፊነት ለክርስቲያኑ ሕዝብ ሰጥቷል እንዲህ ሲል እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ ... መልካም ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁ እንዲያከብሩት ብርሃናችሁ በሰው ሁሉ ፊት ይብራ ማቴ. 5፡14-16፡፡ ክርስቲያኖች በየትኛውም ዘመን በየትኛውም ቦታ ይኑሩ ለዓለም ብርሃን ሆኖ ጨለማውን ማብራት አልጫውን ማጣፈጥ፣ ከእግዚአብሔር የተጣለባቸው ኃላፊነት ነው፡፡ በቃላቸውም በሥራቸውም፣ የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደሆነ ሊያስተምሩ አርአያ ምሳሌ ሊሆኑ በቤታቸውም፣ በጎረቤታቸውም፣ በትዳራቸውም፣ በሥራቸውም፣ በማኅበራዊ ኑሯቸውም ሁሉ መልካምን እየሠሩ ታማኝነታቸውን በማስመሰከር ዓለምን ሊለውጡ ይገባል፡፡

ዓለም ዛሬ በምጥ ጣር ተይዛ የምትጨነቀው የሰላም ባለቤት የሆነውን ፈጣሪዋን አልከተል ብላ ነው እንጂ ብትከተልማ ኖሮ እኔ የሚረባህን ነገር፣ የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ፣ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ፣ ትእዛዜን ስማ፣ ከሰማህ ሰላምህ እንደወንዝ፣ ጽድቅህም እንደባህር ሞገድ ይሆናል፡፡ ብሎ ቃል ገብቶ ነበር ኢሳ. 48፡17-19 ለዓለም ብርሃን የመሆን ኃላፊነት የተሰጠው ክርስቲያን ይህንን የተሰጠው ኃላፊነት በአግባቡ ሳይፈጽም ቀርቶ ቢገኝ ግን ከሌላው ሕዝብ የበለጠ ፍርድ በእግዚአብሔር ፊት እንደሚያስከትልበት ቅዱስ መጽሐፍ ያረጋግጣል፡፡ ለምን የአዋቂ አጥፊ ነውና የጌታን ፈቃድ አውቆ እንደፈቃዱ ያላደረገ እጅግ ይገረፋል፡፡ ብዙ የተሰጠው ብዙ ይፈለግበታል ሉቃ. 12፡47-49፡፡

ስለዚህ ክርስቲያን ሁሉ ራሱንና የሚያዩትን፣ የሚሰሙትን፣ አድኖ የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ያለው መንገድ ፍቅረ እግዚአብሔርንና ፍቅረ ቢጽን አጥብቆ በመያዝ በሥራ ያልተመሰከረ ሃይማኖት በቁሙ የሞተ መሆኑን ተገንዝቦ ለብዙዎችም ተጠያቂና ኃላፊም ጭምር እንደሆነ በመረዳት አንዳንዶቹን ከእሳት እየነጠቀ፣ ከክፉ ሥነ ምግባር እያላቀቀ፣ ከመናፍቃን አንድነት እያራቀ፣ በሥነ ምግባር እየመጠቀ፣ በሃይማኖት እየተራቀቀ፣ ፍጹም የሆነ የነፍስና የሥጋ ደስታ የሚቀዳጅበትን ሥራ ዘወትር መሥራት ይገባል፡፡ በዚህ የዘላለም ሕይወት ይወርሳልና፡፡

ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለሁላችን ይሁን አሜን፡፡
"ወስብሐት ለእግዚአብሔር"
ከንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ

የፎንት ልክ መቀየሪያ