Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

ቅዱሳት መጻሕፍት ምን ይላሉ?

በሊቀ ማዕምራን ብርሃነ መስቀል አጠና

ቅዱስ ማለት ንጹሓ ጽኑዕ ክቡር ልዩ ማለት ነው በዚህ መሠረት ቅዱሳት መጻሕፍት ስንል ንጹሐት መጻሕፍት ክቡራት መጻሕፍት የጸኑ መጻሕፍት የተለዩ መጻሕፍት ማለታችን ነው፡፡ ይኸውም በዘፈቀደ የተሰጠ ስያሜ ሳይሆን በየአንዳንዱ ስያሜ በቂ የሆነ ምክንያት ስለአለው ነው፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍት መባላቸው ቅድስና የባሕርዩ የሆነ የቅድስና ባለቤትና ምንጭ የሆነ ለዘለዓለም በቅዱሳን መላእክት ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እየተባለ የሚመሰገን ቅዱስ እግዚአብሔርን ስለሚሰብኩ የእግዚአብሔርን ቅድስና ስለሚናገሩ ቅዱሳት መጻሕፍት ይባላሉ ኢሳ. 6፡1፡፡

ንጹሐት መጻሕፍት መባላቸው "እስመ ንጹሐት ጠባይዓቱ ሁ ለእግዚአብሔር" አማርኛ "የእግዚአብሔር ባሕርዩ ከነውር የነጻ ነው" ዮሐ. ድርሳን 13 እንዲል እግዚአብሔር ንጹሐ ባሕርይ እንደሆነ እግዚአበሔር ንጽሕናን እንደሚወድ ንጽሕና የእግዚአብሔር ገንዘብ እንደሆነ አበክረው ስለሚናገሩ መጻሕፍት ንጹሐት ሊባሉ ችለዋል በተጨማሪ ርኩሳት መጻሕፍተ ጥንቈላ መጻሕፍተ ሐሰት አሉና ከእነዚያ ለመለየትም ይሏል፡፡

ክቡራን መጻሕፍት መባላቸው "እግዚአብሔር ይሁብ ክብረ ወሞገሰ" አማርኛ "እግዚአብሔር ክብርን ሞገስን ይሰጣል" መዝ. 83፡11 እንዳለ ከከበሩ ሁሉ የከበረ ክብር የባሕርዩ የሆነ ራሱ ክቡር ሁኖ ሌላውን የሚያከብር እግዚአብሔር ስለአጻፋቸውና የእግዚአብሔርን ክብር ስለሚናገሩ ክቡራት መጻሕፍት ተብለዋል፡፡ ከዚህ ሌላ የተናቁና ወዲያው ተቀዳድደው የሚወድቁ ተራ የሆኑ መጻሕፍት /ደብዳቤዎች/ አሉና ከእነዚህ ለመለየት ክቡራን ተብለዋል፡፡

የጸኑ መጻሕፍት መባላቸው እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ አልለወጥም ሚል. 8፡6 እንዳለ ያጻፋቸው ለዘለዓለሙ በአምላክነቱ ጸንቶ የሚኖር ኅልፈተ ውላጤ የሌለበት ወይም የማያልፍ የማይለወጥ አልፋና ዖሜጋ ያለና የሚኖር እግዚአብሔር ነውና ጽኑዓን መጻሕፍት ተባሉ፡፡

የተለዩ መጻሕፍተ መባላቸው እኔ እናንተ አማልክት ናችሁ አልሁ መዝ. 81፡6 ዮሐ. 10፡34 እንዲል ካህናት በሀብት አማልክት ቢባሉም የእነዚህ ሁሉ አምላክነት መባል ጊዜያዊና ኃላፊ ከመሆኑም በላይ በኋላ ያገኙት ነው እግዚአብሔር አምላክ ግን አምላክነቱ የባሕርዩ ከመሆኑም በላይ አምላክነቱ የማያልፍ የማይቀነስ ዘለዓለማዊ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ልዩ አምላክ ስላጻፋቸውና የዚህ ልዩ አምላክ ታላቅነትና እውነታ በሚገባ ስለሚናገሩ የተለዩ መጻሕፍት ይባላሉ፡፡በተጨማሪ ስመ እግዚአብሔር ያልተጻፈባቸው ረድኤተ እግዚአብሔር የተለያቸው አስመሳዮች መጽሕፍት አሉና ከእነዚያ ለመለየት የተለዩ መጽሐፍት ይባላሉ እንደዚሁም ቅዱሳት መጻሕፍት እስትንፋስ እግዚአብሔር ይባላሉ ምክንያቱም የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል እንዳሉ 2ጢሞ. 3፡15፣ የእግዚአብሔር እስትንፋስ በሆነ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት በመንፈስ ቅዱስ ምሥጢር ገላጭነት በመንፈስ ቅዱስ ተራዳኢነት ስለተጻፉ ነው ሮሜ. 13፡4፣ 2ጴጥ. 29፡20፡፡

ከዚህ ሌላ ቅዱሳት መጻሕፍት መጻሕፍት አምላካውያት "ዘአዙዝ ተወክፎቶ ኅበ ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ዘኁልቆሙ ሰማኒያ ወአሐዱ ረሰጣ ሰብዓ ወአሐዱ ረሰጠብ ኀምሳ ወስድስቱ መጻሕፍት እንተ ተወክፍዎ ምእመናን እንተ ተወከፍዎን ውስተ ቤተ ክርስቲያን" አማርኛ ቁጥራቸው ሰማኒያ አንድ የሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ቤተ ክርስቲያን የተቀበለቻቸውና አምላክ አዝዞ ያጻፋቸው ለስጣ ሰባ አንድ ረሰጠብ አምሳ ስድስት እነዚያ ምእመናን በቤተ ክርስቲያን የተቀበሏቸው ናቸው ፍት.መን አንቀጽ ሁለት፡፡

እነዚህ ሁሉ ቅዱሳት መጻሕፍት ሀልዎተ እግዚአብሔርን ይሰብካሉ በመጀመሪያ እግዚአብሔር አምላክ ሁሉን ቻይ ኰናኒ በጽድቅ ፈታሒ በርትዕ ማለት ፈጥሮ የሚገዛ ሕጉንና ትእዛዙን በተላለፈ ደግሞ ፍርዱን ሳያዛባና ሳያዳላ በትክክል የሚፈርድ መሆኑን ራሱ እግዚአብሔር ገልጾአል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ አዳምን በአርአያውና በምሳሌው ፈጥሮ ገነትንም በመልካም ነገር ሁሉ የተሞላችና እጅግ የተዋበች አድርጎ ካዘጋጀ በኋላ ለአባታችን ለአዳም በማስረከብ "እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያሳውቅ ዛፍ አትብላ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ" ዘፍ. 2፡8-17፡፡ በማለት ሀልዎቱን ከመግለጹም በላይ ሕጉንና ሥርዓቱን ጠብቆ እንዲኖር በተዘዋዋሪ መልእክት ወይም በስማ በለው ሳይሆን ራሱ ባለቤቱ በቃል አስጠንቅቆት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አባታችን አዳም የተሰጠውን አምላካዊ ትእዛዝ ወደ ጎን በመተው ስቶ የሚያስት የእባቡን /በእባቡ ያደረው የሰይጣን/ ምክር ሰምቶ ዕፀ በለሱን በላ የፈጣሪውን ሕግ ተላለፈ፡፡

እውነት ፈራጅ የሆነ እግዚአብሔርም በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስን በርደተ መቃብር ርደተ ገሃነምን ማለት በሥጋው እንዲሞት በነፍሱም ፍዳ እንዲያገኘው በሥጋው ወደ መቃብር እንደሚወርድ በነፍሱም ወደ ሲኦል እንዲወርድ ፈረደበት ዘፍ. 3፡1-19፡፡

ስለዚህ ነው እግዚአብሔርሰ "ኢገብረ ሞተ አላ ረሲዓን ጸውዕዎ ወአርከ አምስልዎ" አማርኛ እግዚአብሔርስ ሞትን አልፈጠረም እግዚአብሔርን የዘነጉ ሰዎች ግን በቃል ጠሩት ባልንጀራም አደረጉት በዚሁም ጠፉ ጥበ. 1፣13፡16፡፡

እግዚአብሔር ለሁሉ እንደሥራው ዋጋ የሚሰጥ ነው

እግዚአብሔር አምላክ አዳምና ሔዋን ቢበድሉ እንደፈረደባቸው ሁሉ በአንጻሩ ወይፈድዮ ለኲሉ በከመ ምግባሩ አማርኛ ለሁሉም እንደሥራው ዋጋውን ይሰጠዋል መዝ. 61፡12 ሮሜ. 2፡6 እንዲል በጎ ሥራ ሠርቶ ለተገኘ ሁሉ ሊለካና ሊመጠን የማይቻል እጅግ ከፍ ያለ ዋጋ ይሰጣል፡፡

ለአብነት ሄኖክን እንውሰድ ቅዱስ ጳውሎስ ስለሄኖክ ሲናገር "ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ እግዚአብሔር ስለወሰደው አልተገኘም ሳይወለድ እግዚአብሔርን ደስ እንደ አሰኘ ተመስክሮለታል ያለ እምነትም እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም" ዕብ. 11፣5-6 ከዚህ ልብ ልንለው የሚገባ ሄኖክ ዋጋ ያገኘው በእምነት ብቻ እንዳልሆነ ነው ከእርሱ በፊት የነበሩ አቤልና ቃየልም በእምነት አንድ ሁነው ሳለ በሥራ እንደተለያዩ "እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ ወደ ቃየልና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም" ዘፍ. 4፡4-5 ይላል እንዲሁም ሄኖክም ይህን እጅግ ከፍተኛ የሆነ ጸጋና ክብር ሊያገኝ የቻለው በመልካም ሥራውም ጭምር እንደሆነ "ከዚህ በኋላ ከአምላክ መላእክት ጋር ስድስት የኢዮቤላት ዘመኖችን ኖረ በምድርም ያለውን ሁሉ በሰማይም ያውን የፀሐይን ሥልጣን አሳዩት፡፡ ሁሉንም ጻፈ ከሰው ልጆች መካከል ተነሥቶ ሄደ ለጌትነት፣ ለክብር፣ ወደ ኤዶም ገነት ወሰድነው በዚያም የዘለዓለም ቅጣትና ቁርጥ ፍርድን የአዳምን ልጆች ኃጢአት ሁሉ እርሱ በዚያ ይጽፋል" ኩፋ. 5.28-30፡፡

ይህ ከዚህ በላይ የተጻፈው የሚያስረዳን አዳም ዕፀ በለስን በልቶ በምግብ ምክንያት ሞትን ቢያመጣ ሄኖክ ደግሞ በኢዮቤልያት የሚቈጠሩ ዘመናትን ከመላእክት ጋር እንደ መላእክት ከምግብ ተከልክሎ በመኖሩ ከሞት ተሰውሮ ከእርሱ በኋላ የተነሱ እነ ኤልያስ እነ ዕዝራ ወደገቡበት ወደ ብሔረ ሕያዋን በሕይወተ ሥጋ ሊያርግ ችሎአል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው በሃይማኖት ጸንቶ ከፍ ያለ የሥራ ፍሬ ሊያስመዘግብ በመቻሉ ነው፡፡

ኖኅና ሥራው ከሄኖክ ቀጥሎ ሀልዎተ እግዚአብሔርን በብዙ መልኩ አውቆ ያሳወቀ ኖኅና ሥራው ነው ኖኅ ሰዎች ሁሉ ኃጢአትን አብዝተው በመሥራት እግዚአብሔርን ፈጽመው ባሳዘኑበት ወቅት በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን ያገኘ ዘፍ.6፡8፡፡ "ከዚህ ትውልድ በፊቴ ጻድቅ ሁነህ አይቸሃለው ብሎ ዘፍ. 7፡1፡፡ ፈጣሪው እስኪመሰክርለት ድረስ በጽድቅ ሥራው በእግዚአብሔር ዘንድ ከፍ ያለ ባለሟልነትን ያገኘ ፍጹም የሆነ ደግ ሰው"፡፡ "እግዚአብሔር አምላክም ኖኅን አለው አንተ ቤተ ሰዎችህን ይዘህ ወደ መርከብ ግባ" ዘፍ. 7፡1 ብሎ ባዘዘው ጊዜ ኖኅም መመሪያውን ተቀብሎ በታዘዘው መሠረት መርከብ ሠርቶ ካለው ፍጥረት ሁሉ ለዘር ሁለት ሁለት ይዞ በመግባትና ከንፍር ውኃ አድኖና ይዞ በመውጣት አዲስ ሕይወት ለመኖር አዲስ ትእዛዝ ተቀበለ፡፡ ከእግዚአብሔር የተሰጠው ትእዛዝም ከዚህ ቀጥሎ ያለው ነው፡፡ እግዚአብሔርም ለኖኅ እንዲህ ብሎ ነገረው አንተ ሚሰትህንና ልጆችህን የልጆችህንም ሚስቶች ይዘህ ከመርከብ ውጣ ከአንተ ጋር ያሉት አራዊትን ሁሉ ሥጋ ያላቸውን ሁሉ ወፎችንና እንስሶችን ሁሉ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ከአንተ ጋር እውጣቸው በምድር ላይ ብዙ ተባዙ ምድርንም ምሉአትን ዘፍ. 8፡15-17፡፡ የሚል ነው፡፡

በዚህ ሁሉ ሂደት ኖኅ ሀለዎተ እግዚአብሔርን በጐላ መልኩ አውቆ ከማሳወቁም በላይ ከጥፋት ውኃ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ ኖኅ ያቀረውን መሥዋዕት ተቀብሎ ምድርን ዳግመኛ በንፍር ውኃ ላለማጥፋት በመወሰንና ደጋግሞ ብዙ ቃል ኪዳን በመስጠት የኖኅን ባለሟልነት አረጋግጦአል ዘፍ. 8፡20፣ 9፡17 ከቃል ኪዳኖቹ መካከል የተወሰኑትን እንመልከት፡፡

"እኔ እነሆ ቃል ኪዳኔን ከእናንተና ከእናንተ በኋላ ከሚመጣው ከዘራችሁ ጋር አቆማለሁ ከእናንተ ጋር ላሉትም ሕያው ነፍስ ላለው ሁሉ "እግዚአብሔርም አለ በእኔና በእናንተ መካከል ከእናንተም ጋር ባለው በሕያው ነፍሰ ሁሉ መካከል ለዘለዓለም የማደርገው የቃል ኪዳን ምልክት ይኸ ነው፡፡ ቀስቴን በደመና አደርጋለሁ የቃል ኪዳንም ምልክት በእኔና በምድር መካከል ይሆናል በምድር ላይ ደመናን በጋረድሁ ጊዜ ቀስቲቱ በደመናው ትታያለች ቃል ኪዳንን አስባለሁ፡፡ ቀስቲቱም በደመና ትሆናለች በእኔና በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ባለው በሕያው ነፍስ ሁሉ መካከል ያለውን የዘለዓለም ቃል ኪዳን ለማሰብ አያታለሁ፡፡ የቆሙሁት የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው ዘፍ. 9፡1-17 በማለት ምልክቱ ቀስተ ደመና የሆነ ይህን እጅግ የጸና ቃል ኪዳን ሲሰጠው ሀልዎቱን መግቦቱን በማያሻማ ሁኔታ አረጋግጦለታል፡፡

ከባለሟሎች የበለጠ ባለሟል

ምድራውያን ነገሥታት መኳንንት ከባለሟሎቻቸው ሁሉ የበለጠ ባለሟል ይኖራቸዋል፡፡ እግዚአብሔር አምላክም ከቅዱሳን ባለሟሎቹ መካከል አልቆ የሚጠራቸው ከፍ ያለ ክብር የሚሰጣቸው አሉ ለምሳሌ ስለ ነቢየ ኦሪት ሙሴ ስለ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ ራሱ እግዚአብሔር የሰጠው ምስክርነት መጥቀሱ በቂ ማስረጃ ይመስለኛል ዘኁ. 12፡1-16፣ ማቴ. 11፡11፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ሙሴን ለመጀመሪያ ጊዜ በደብረ ሲና ላይ በቊጥቋጦ ውስጥ ሁኖ አነጋገረው ዘፀ. 3፡4 ደግሞም እኔ የአባቶችህ አምላክ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆም አምላክ ነኝ አለው ዘፀ. 3፡6 ቀጥሎም አሁንም እነሆ የእስራኤል ልጆች ጩኸት ወደ እኔ ደረሰ ግብጻውያንም የሚያደርጉባቸውን ግፍ ደግሞ አየሁ አሁንም ና ወደ ግብጽ ንጉሥ ወደፈርዖን እልክሃለሁ ሕዝቤን የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ምድር ታወጣቸዋለህ ዘፀ. 3፡9-10፡፡ ሙሴ ማን ላከህ ባሉኝ ጊዜ ምን እላቸዋለሁ ቢለው እግዚአብሔርም ያለና የሚኖር ወደ እናንተ ላከኝ ትላቸዋለህ አለው ዳግመኛም እግዚአብሔር ሙሴን አለው ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ትላቸዋለህ የአባቶቻችሁ አምላክ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ እግዚአብሔር ወደ እናንተ ላከኝ ይህ የዘለዓለም ስሜ ነው እስከ ልጅ ልጅ ድረስም መታሰቢያዬ ይህ ነው ዘፀ. 3፡13-15፡

እግዚአብሔር አምላክ ሀልዎቱ ማለትም የነበረ ያለ የሚኖር ዘለዓለማዊ አምላክነቱን ከመግለጹም ባሻገር ይህ የዘለዓለም ስሜ ነው በማለት ስሙን ገልጾ የተናገረው ለዚህ ታላቅ ነቢይ ነው፡፡ እንደዚሁም ከእግዚአብሔር እንደተላከ ወገኖቹ እስራኤልንም ሆነ የግብጽ ንጉሥ ፈርዖንን የሚያሳምንበትንና ልዩ ልዩ ተአምራትን በትሩን ሲጥላት እባብ ሲያነሣ በትር እንድትሆን አድርጎ ከምድያም ወደ ግብጽ ላከው ዘፀ. 4፡1-7፡፡

ከዚህ ሁሉ በጣም የሚገርመው ደግሞ እኔ ለፈርዖን አምላክ አድርጌሃለሁ ዘፀ. 6፡1 የሚለው ነው እግዚአብሔር አምላክ ለብዙ ባለሟሎች አስገራሚ የሆኑ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አድርጎላቸዋል፡፡ ነገር ግን በዘመነ ብሉይ ሆነ በዘመነ ሐዲስ አምላክ አድጌሃለሁ የተባለ አንድም የለም፡፡

ስለሆነም በዚህ በተሰጠው ሙሉ ሥልጣን ወገኖቹ ሕዝበ እስራኤል ያሉባት ምድረ ጌሴሞን ሳይነካ ከፈርዖን ቤተ መንግሥት አንሥቶ በመላዋ ግብጽ ዘጠኝ መቅሠፍት ዐሥረኛ ሞተ በኲር አምጥቶ ፍዳቸው ሲያሳያቸው ዘፀ. 7፡1-25፣ 8፡1-32፣ 9፡1-35፣ 10፡1-29፣ 11፡1-10፣ 12፡1-32 ፈርዖን እኔ እግዚአብሔር እንዳለ ዐውቄአለሁ፡፡ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት በእናንተም ላይ በድያለሁ፡፡ አሁን እንግዲህ እንደገና በዚህ ጊዜ ብቻ ኃጢአቴን ይቅር በሉኝ ይህንም ሞት ብቻ ከኔ ያነሣልኝ ዘንድ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ጸልዩልኝ እያለ ከመለማመጥ በስተቀር በሙሴና በአሮን ላይ አንዳች የበቀል ሥራ ሊፈጽም አልቻለም፡፡

እንደዚሁም ዘጠኝ መቅሠፍታት በሚወርዱበት ወቅት ሀልዎተ እግዚአብሔርን ያወቀ ፈርዖን ብቻ አይደለም፡፡ ንስሐ ገብተው ባይጠቀሙበትም ግብጻውያን በሙሉ ሀልዎተ እግዚአብሔርን በሚገባ ተረድቶዋል፡፡ ስለሆነም የፈርዖን ሹሞች ሕዝበ እግዚአብሔር እስራኤልን እንዲለቅ ፈርዖንን አጥብቀው ይወተውቱ ነበር ዘፀ. 10፡7-8፡፡

የመጨረሻይቱ ሰዓት

ግብጻውያንና እስራኤል በሚለያዩባት ሕዝበ እስራኤል ዘግናኝ መከራ ሲቀበሉባት የነበረች ምድረ ግብጽን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተሰናብተው በሚወጡባት በመጨረሻይቱ ሰዓት ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን በሌሊት ጠርቶ እናንተ የእስራኤል ልጆች ተነሡ ከሕዝቤ ውጡ ሂዱም እንዳላችሁም እግዚአብሔርን አምልኩት በጎቻችሁንም ላሞቻችሁንም ውሰዱ ሂዱም እኔንም ባርኩኝ አላቸው የእግዚአብሔር ሀልዎቱን ከሀሊነቱን ኃያልነቱን የተረዱ ግብጻውያንም ፈጥነው ከምድሩ ይወጡ ዘንድ እስራኤልን ያስቸኩልዋቸው ነበር ሁላችንም እንሞታለን ብለዋልና ዘፀ. 12፡31-33፡፡ ስለሆነም እስራኤል በዚያች ሰዓት ለዘመናት የኖሩባትን ግብጽን ለቅቀው ወጡ፡፡

ከዚህ በኋላ ፈርዖንና ግብጻውያን እስራኤልን በመልቀቃቸው ስለቈጫቸው ለመመለስ እስከ ኤርትራ ባሕር ድረስ ቢከተሏቸውም ኃያሉ አምላክ እግዚአብሔር ባሕሩን ከፍሎ እስራኤልን በማሻገር ግብጻውያንን ለእስራኤል በተከፈለው ባሕር እንሻገራለን ብለው ሲገቡ አንድም ሳይቀር ሁሉም በኤርትራ ባሕር ሰጥመው እንዲቀሩ በማድረግ በግብጽ አገር የጀመረውን ድንቅ ሥራ በኤርትራ ባሕር ደመደመው ዘጸ. 14፡1-31፡፡

በዚህ ጊዜ ሕዝበ እስራኤል እነርሱን ከግብጻውያን እጅ ፈጽሞ ነጻ በማውጣቱ ኤርትራን ያህል ባሕር ከፍሎ በማሻገሩ ግብጻውያንን አንድም ሳይቀር በኤርትራ ባሕር እንዲሰጥሙ በማድረጉ የእግዚአብሔርን ሀልዎትና ከሀሊነት በበለጠ ዐውቀውና ተረድተው እግዚአብሔርን ፈሩ በእግዚአብሔርም አመኑ በእኛ ላይ ማን ገዥና ፈራጅ አደረገህ ብለውለት የነበረ አዳኝና መልአክተኛ አድርጎ እንደላከው በሚገባ ተረድተው ባለሟሉ ሙሴን አከበሩ ዘፀ. 14፡1-20፣ ዘጸ. 21፡14 ዮሐ. ሥ. 6፡35-36፡፡

የእስራኤል ጉዞ በሲና በረሀ

ሕዝበ እስራኤል በእግዚአብሔር ፈቃድ በሙሴ መሪነት በቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት ከግብጽ ከወጡ በኋላ ክፉና መልካም እየተፈራረቀባቸው የበረሀውን ጉዞ ተያይዙት ለመጀመሪያ ጊዜ የገጠማቸው ፈተና የውኃ ጥም ነው፡፡ ሦስት ቀን ሙሉ ውኃ በሌለበት በረሀ ሲጓዙ ሰንብተው በሦስተኛው ቀን ውኃ ቢያገኙም ውኃው መራራ ስለሆነ ሊጠጡ ባለመቻላቸው እጅግ ተቸገሩና በሙሴ ላይ አንጐራጐሩበት፡፡

በዚህ ምክንያት ሙሴ ወደ እግዚአብሔር ስለጮኸ እግዚአብሔር የሙሴን ጩኸት /ምልጃ/ ተቀብሎ /ሰምቶ/ መራራውን ውኃ የሚያጣፍጥበትን እንጨት በማሳየቱ መራራው ጣፋጭ ሁኖላቸው ስለጠጡ ያጋጠማቸው ችግር በሙሴ አማላጅነት በእግዚአብሔር ቸርነት ሙሉ በሙሉ ስለተወገደላቸውና አሥራ ሁለት የውኃ ምንጮች ካሉበት ቦታ ስለደረሱ ለጊዜው እፎይታን አግኝተዋል ዘፀ. 15፡22-27፡፡

ከዚህ ቀደም እንደታየው እስራኤል በግብጽ አገር ሳሉ በግብጻውያን ላይ ከመጣው መቅሠፍት ሁሉ ያዳናቸው አስቀድሞ በመጠበቅ ነው ባሕሩንም ሲሻገሩ አስቀድሞ ባሕሩን ከፍሎና መንገዱን አስተካክሎ ነው ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ግን የአግዚአብሔርን ቃል ቢሰሙ መልካም ሥራ እየሠሩ ሕጉና ሥርዓቱን ከጠበቁ ከገጠማቸው ከሚገጥማቸው ልዩ ልዩ መከራ ሁሉ ለማዳን ሙሉ ሥልጣን ያለውና ሀልዎቱንና ከሀሊነቱን አምነው በለመኑት ጊዜ ሁሉ ቸል ሳይል ፈጥኖ የሚያድናቸው መሆኑን በግልጽ አስረድቶአቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሕዝበ እስራኤል ድንቅ ሥራውን ሁሉ ፈጥነው በመዘንጋት በበደል ላይ በደልን እየጨመሩ እግዚአብሔርን ብዙ ጊዜ አሳዘኑት ሙሴንም ባለማቋረጥ አወኩት አበሳጩት አስመረሩት፡፡

ነገር ግን "ሙሴሰ የዋህ ውእቱ እምኲሎሙ ደቂቅ እስራኤል አማርኛ ሙሴም በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ የዋህ ነበረ" ዘኊ. 12፡3 ተብሎ እንደተመሰከረለት በየጊዜው ወገኖቹ የሚያመጡበትን ፈተና ሁሉ እየታገሠ በየዋህነትና በቅንነት ማገልገሉን ገፋበት እንጂ ወደ ኋላ አላለም፡፡ "ወአዕረገ ሙሴ ቃለ ሕዝብ ኀበ እግዚአብሔር" አማርኛ ሙሴም የሕዝቡን ቃል ወደ እግዚአብሔር አደረሰ" ዘፀ. 19፡8 እንዲል እነርሱ እየበደሉት እርሱ በየጊዜው ወደ እግዚአብሔር ይማልድላቸዋል የፈለጉትን ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ያሰጣቸዋል፡፡

ሕዝቡ ግን ዕረፍት ሲያገኙ እግዚአብሔርን ያማሉ ሙሴን ያሳዝናሉ ችግር ሲመጣባቸው ከሙሴ ዘንድ ሂደው ከኛ ስሕተት ኃጢአት ከእግዚአብሔር ቸርነት አይታጣምና ጸልይልን አማልደን ይሉታል፡፡ እርሱም እንደተለመደው ይጸልይላቸዋል ይማልድላቸዋል እንዲያውም አሁንም ይህን ኃጢኣታቸውን ይቅር ትላቸው እንደሆነ ይቅር በላቸው ያለዚያ ግን ከጻፍከው መጽሐፍ ደምስሰኝ ዘጸ. 32፡31 ብሎ ስለ እነርሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ የነበረውን ባለሟልነት እስኪያጣ በቈራጥነት ማለደ፡፡

እግዚአብሔርም ቸርና ርኅሩኅ አምላክ ከመሆኑም በላይ የወዳጆቹን ምልጃ ቸል አይልምና "እግዚአብሔርም በሕዝቡ ሊያደርገው ስላሰበው ክፋት ይቅር አለ ዘፀ. 32፡14 እንዲል በደላቸውን ይቅር ከማለቱም ባሻገር ሕዝቡ የሚሹትንና ሙሴ የጠየቀውን ሁሉ ያለ መከልከል መና ከደመና እያወረደ ውኃ ከደንጊያ እያፈለቀ ሥጋ አማረን ሲሉ ሥጋ እያዘነመ ሲመግባቸው ኑሮአል፡፡

በዚህ መሠረት የሰው ልጅ በሙሉ በተለይ የሕዝብ መሪ የሆነ ሁሉ እንደሙሴ ኅዳጌ በቀል ከራሱ ጥቅም ይልቅ የሕዝቡን ጥቅም የሚያስቀድም መሆን አለበት ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ በተቃራኒ መንገድ ሁሉ ራስ ወዳድ የገንዘብ ተገዥ ስግብግብ በመሆን ሕይወቱን በሙሉ ለሥጋዊ ጥቅም ብቻ አሳልፎ የሰጠ ሁኖ ይታያል ስለዚህ ኃያሉ እግዚአብሔር ይህንን ታሪክ ለውጦ ሁሉም ግዴታውን እንዲወጣ ያደርግ ዘንድ ልባዊ ጸሎት ያስፈልጋል፡፡

የሙሴን ታላቅነት በእግዚአብሔር አፍ እንደመሰከረ

ከሙሴ መጻሕፍት ተቀንጭቦ በተጻፈው በዚህ አጭር ጽሑፍ በተመዘገበው ከማነኛው የእግዚአብሔር ባለሟል ሁሉ የሙሴ ባለሟልነት እጅ ጐልቶ ይታያል፡፡ እግዚአብሔር ወልድ ሰው ሁኖ በተገለጠ ጊዜ በተለያየ መልኩ ይከተለው ከነበረ ከአምስት ገበያ ሰው መካከል መቶ ሃያ ቤተሰብን /አሥራ ሁለቱ ሐዋርያትን ሰባ ሁለት አርድእትን ሰላሳ ስድስት ቅዱሳት አንስትን/ መርጦ በዋለበት እየዋሉ ባደረበት እያደሩ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር በቤተሰብነት ከአነጋገሩት ሰዎች አስቀድሞ ከአበው ከነቢያት ከካህናት ሁሉ በላይ ሙሴ የእግዚአብሔር ባለሟል እንደነበረና ከእግዚአብሔር ጋር ብዙ ጊዜ እንደተነጋገረ ነው በዚህ መሠረት አምስት መቶ ሰባ ጊዜ እንደ አነጋገረው ይተረካል፡፡

ከዚህ ጋር ሊገለጽ የሚገባው ወንድሙ አሮንና እኅቱ ማርያም ኢትዮጵያዊቱን ሴት አግብቶ በእኛ ላይ እንዴት ይሰለጥንብናል ብለው ሙሴን ስለአሙት እግዚብሔር ጽድቅን ይወድዳልና ጻድቃኑም አይጥላቸውምና ለዘለዓለሙ ይጠብቃቸዋል ለንጹሐንም ይበቀላለቻል፡፡መዝ. 36፡28፡ እንዳለው እግዚአብሔር ባለሟሎቹን ማንም በሐሰት እንዲግደረደራቸው አይፈቅድምና፡፡

"እግዚአብሔር ወዲያው ሙሴንና አሮንን ማርያምንም ሦስታችሁ ወደ ምስክሩ ድንኳኑን ብሎ ተናገረ በመጡ ጊዜም ቃሌን ስሙ በመካከላችሁ ለእግዚአብሔር ነቢይ የሆነ ቢኖር በራእይ እገለጥለታለሁ፡፡ ወይም በሕልም እናገረዋለሁ፡፡ አገልጋዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው እኔ አፍ ለአፍ እናግረዋለሁ፡፡ በስውርም አይደለም የእግዚአብሔርን ክብር ያያል፡፡

አገልጋዬ ሙሴን ማማትን ለምን አልፈራችሁም አለ የአግዚአብሔር ቁጣ በእነርሱ ላይ ወረደ እርሱም ሄደ" ዘኁ. 12፡1-16 በዚህ መልኩ አሮንና ማርያም በእግዚአብሔር አፍ ከመገሠጻቸው በላይ ማርያም እስከ ሰባት ቀን በለምጽ ስትገረፍ ሕዝቡም በአሮንና በማርያም ጥፋት የሰባት ቀን ጒዞአቸው ተጓጒሎ ከባድ ጒዳት ደርሶባቸዋል፡፡

ይህም የአንድ የሁለት ሰው በደል ብዙኃኑን አልፎ ተርፎም አገርን የሚጐዳ በአንጻሩ ደግሞ የአንድ የሁለት ሰው ደግነት ወገንና አገርን እንደሚጠቅም ትልቅ ማሳያ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ የእግዚአብሔር ባለሟሎች በሆኑ በቅዱሳኑ ላይ የድፍረት ቃል በሚናገሩና ቅዱሳኑን በሚሳደቡ ላይ የነፍስ ቅጣትና ፍርድ እንደማይቀርላቸው በዚህ መገንዘብ ይቻላል፡፡

ይህ ከዚህ በላይ የተጻፈው በጥቅሉ ሲታይ በአንደኛ ደረጃ ከማነኛው ጸሐፊ ሁሉ በላይ ሙሴ ሀልዎተ እግዚአብሔርን በሰፊው የገለጸ መሆኑን በሁለተኛ ደረጃ ከእግዚአብሔር ባለሟሎች ሁሉ ሙሴ የበለጠ የአግዚአብሔር ባለሟልና እጅግ የቀረበ ወዳጅ እንደሆነ በግልጥ የሚያስረዳ ነው፡፡

እግዚአብሔር ለፍጥረቱ በፍጥረቱ እንደተገለጸ

እግዚአብሔርን ስለማወቅ ቅዱሳት መጻሕፍት ምን ይላሉ ከዚህ በላይ እንደታየው የተወሰኑ የአግዚአብሔር ባለሟሎች ለአብነት እነኖኅ እነ አብርሃም ለልጆቻቸው፣ ነቢያትና ካህናት ለሕዝበ እስራኤል ሀልዎተ እግዚአብሔርን ዐውቀው አሳውቀዋል፡፡ እንደዚሁም በሠለስቱ ደቂቅና በዳንኤል ምክንያት ናቡ ከደነፆርና ሰዎቹ በዮናስ ምክንያት የነነዌ ሰዎች ሀልዎተ እግዚአብሔርን ዐውቀዋል ዳን. 2፡47፣ 3፡24-30፣ ዮና. 3፡5-10፡፡

ከዚህ ውጭ የነበረው የዓለም ሕዝብ በሙሉ ግን ቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን ዙረው በማስተማር ሀልዎተ እግዚአብሔርን እስከ አሳወቁት ድረስ የእግዚአብሔርን ሀልዎት ባለማወቅ በአምልኮ ጣዖት በገቢረ ኃጢአት ተተብትቦ ነበር የኖረው፡፡
ቅዱሳት መጻሕፍት ግን እግዚአብሔርን ሁሉ ሊያውቀው የሚችልበት መንገድ እንዳለ በግልጽ ያስረዳሉ ለምሳሌ ከቅዱሳት መጻሕፍት አንዱ መዝሙረ ዳዊት "ሰማያት ይነግራል ሰብሐተ እግዚአብሔር ወግብረ አደዊሁ ያየድን ሰማያት አማርኛ ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ የእጁንም ሥራ ሰማዮች ያወራሉ መዝ. 18፡1፡፡

ሰማያት የእግዚአብሔርን ምስጋና ይናገራሉ ማለቱ ሰማያት የሚናገሩ ሁነው አይደለም ግዑዛን ፍጥረታት ናቸው፡፡ ነገር ግን በአንደኛ ደረጃ በሰማያት የሚኖሩ ሊቃነ መላእክት ሠራዊተ መላእክት የእግዚአብሔርን ምስጋና ይናገራሉ ሲል ነው፡፡ ሁለተኛ ሰማያትን የፈጠርህ ተመስገን ተብሎ የሚመሰገንባቸው ስለሆነ ነው ሦስተኛ ሰው ጠፈርንና በጠፈር የሚኖሩ ፀሐይ ጨረቃ ከዋክብትን እይቶ እነዚህን አስደናቂ የሆኑ ፍጥረታትን የፈጠረ ኃያል አምላክ አለ ብሎ ሀልዎተ እግዚአብሔርን የሚያምንባቸውና የሚረዳባቸው ስለሆነ ልበ አምላክ ዳዊት እግዚአብሔር እንደገለጸለት ይህን ጥልቅ ምሥጢር ተናገረ፡፡ ቅዱሰ ጳውሎስም "ወዘኢያስተርኢ እግዚአብሔር እምፍጥረተ ዓለም ይትዐወቀ በፍጥረቱ በኀልዮ ወበአእምሮ ወከመዝ ይትአመር ኃይሉ ወመለኮቱ ዘለዓለም" አማርኛ የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ እርሱም የዘለዓለም ኃይሉና ጌትነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ የፈጠረውን ፍጥረት በማሰብና በመመርመር ይታወቃል ሮሜ. 1፡20 በማለት ፍጥረታት ሁሉ የእግዚአብሔርን ሀልዎት የሚያስረዱ መሆናቸውን በግልጽ ተናግሮአል፡፡

እግዚአብሔር በፍጥረቱ ለፍጥረቱ ይታወቃል ሲባል የሰው ልጅ እግዚአብሔር የፈጠራቸውን አስደናቂ ፍጥረታት የሚታዩ ግዙፋኑን በዐይን አይቶ የማይታዩ ረቂቃኑን አስቦና ተመራምሮ እግዚአብሔርን ያውቅባቸዋል ማለት ነው፡፡
ከእነዚህ የእግዚአብሔር ሀልዎት ከሚታወቅባቸው አስደናቂ ፍጥረታት ጥቂቶችን ለአብነት እንመልከት ልበ አምላክ ዳዊት ከብዙ ውኆች ድምፅ የተነሣ የባሕር እንቅስቃሴዋ ድንቅ ነው ድንቅስ በልዕልና ያለ እግዚአብሔር ነው ምስክርህ እጅግ የታመነ ነው አቤቱ እስከ ረጅም ዘመን ድረስ ለቤትህ ምስጋና ይገባዋል መዝ. 92፡4-5፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍት ሐይቆችንም ውቅያኖስንም ባሕር እያሉ ይጠሩአቸዋል፡፡ ስለሆነም ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ከዚህ ባሕር ብሎ የጠራው ውቅያኖስን ነው የባሕር ንውጽውጽታዋ /እንቅስቃሴዋ/ ድንቅ ነው ማለት እጅግ ሰፊና ጥልቅ ሁና ከመፈጠርዋ ጋር በነፋስ ኃይል ወደላይ ወደታች ወደፊት ወደኋላ ወደቀኝ ወደ ግራ ስትነዋወጽ የምታሳየው አግራሞት ድንቅ ነው ካለ በኋላ ድንቅስ በልዕልናው ያለ እግዚአብሔር ነው በማለት መደነቅ የሚገባው ይህችን አስደናቂ የሆነችውን ፍጥረት የፈጠረ ከድቆች ሁሉ የበለጠ ድንቅ በፍጥረቱ ለፍጥረቱ የሚታወቅ እግዚአብሔር ነው በማለት እውነተኛ ምስክርነቱን ተናግሮአል፡፡

እንደዚሁም እግዚአብሔር መንፈስ ነውና የሚሰግዱለትም በመንፈስና በውነት ይሰግዱለት ይገባል ዮሐ. 4፡24 ይላል፡፡ ስለዚህ የማይታይ የማይዳሰስ ከሆነ እንዴት ይታወቃል በምንስ ልናውቀው እንችላለን የሚሉ ብዙ አላዋቂዎች አሉ ይሁን እንጂ ልበ አምላክ ዳዊት ለዚህም መልስ የሚሆን በሰማይና በምድር በባሕርና በጥልቆችም ሁሉ እግዚአብሔር ሁሉን አደረገ ከምድር ዳር ደመናት ያወጣል ለዝናም ጊዜም መብረቅን አደረገ ነፋሳትንም ከመዛግብቱ ያወጣል መዝ. 134፡6-7 ይላል፡፡

ለሥልጣኑ ለጌትነቱና ለግዛቱ ወሰን የሌለው ሁሉን ያለ ገደብ የፈጠረ ሁሉን ቻይ አምላክ ዓለማትንና በውስጣቸው ያለውን ሁሉ በፈጠረ ጊዜ ከመካከላቸው በእጅ የማይዳሰሱ /የማይጨበጡ/ በዐይን የማይታዩ ብዙ ረቂቃን ፍጥረታት ይገኛሉ እነርሱም መላእክት፣ ነፍሳት ነፋሳት፣ መባርቅት ናቸው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ መላእክት በሃይማኖት በቅዱሳት መጻሕፍት ነው እንጂ በሰው ሰውኛ መኖራቸው የሚታወቅበት ወይም የሚረጋገጥበት ሁኔታ የለም፡፡

የቀሩት ግን ባይታዩና ባይዳሰሱም የየአንዳንዳቸው ህልውና የሚረጋገጥበት መንገድ አላቸው፡፡ ይኸውም ነፍስ ሥጋን በማንቀሳቀስ የሥጋ ሕይወት ሁና በመኖርዋ ሀልውናዋ ይታወቃል፡፡ ነፋስ ባሕር በመንሠጹ ዛፉን በማናወጹ ወይም በማወዛወዙ ፊታችንን ሲገርፉን የለበስነው ልብሳችን ሲገፈን ገለባውን ከፍሬ ሲለይ ነፋስ መኖሩ በግልጥ ይታወቃል፡፡ መብረቅ በብልጭታውና በድምፁ መኖሩ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ረቂቃን ፍጥረታት ኃያላን ናቸው የቅዱሳን መላእክት ኃያልነት "ወመጽአ መልአክ እግዚአብሔር ሌሊተ ወቀተለ እምትዕይንተ አሦር ዐሠርተ ወሰመንተ እልፈ ወኀምስተ ምእተ" አማርኛ በዚያች ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ መጣ ከአሦር ውያንም ሰፈር መቶ ሰማኒያ አምስት ሺህ ገድለ 2ነገ. 19፡35 ኢሳ.37፡36 "ወነሥአ አሐዱ መልአክ ኃያል ወጽኑዕ አብነ ዐቢየ ከመ ማኅረጽ ወወገረ ውስተ ባሕር ወይቤ ከመዝ ትትነደፍ ባቢሎ ሀገር ዐባይ ወኢትትረከብ እንከ" አማርኛ አንድ ኃያልና ብርቱ መልአክ እንደወፍጮ ያለ ታላቅ ድንጋይ አንሥቶ ወደ ባሕር ወረወረው እንዲህም አለ ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን እንዲህ ተነሥታ ትገለበጣለች እንግዲህም አትገኝም ራእ. 18፡21 በማለት የመላእክትን መኖርንና ኃያልነት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኛ ምስክርነት ለሚቀበሉ ሁሉ ይህ በሚገባ ያስረዳል፡፡

ስለ ነፋስ ኃያልነት ንጉሥ ዳዊት በነፋስ ኃያል ትቀጠቅጠን "ለአሕማረ ተርሴስ" አማርኛ በኃይለኛ ነፋስ የትርሴስ መርከቦች ትቀጠቅጣቸዋለህ መዝ. 47፡7 በማለት እንደተናገረው ከትንንሽ ጀልባዎች አንሥቶ እስከ ግዙፍ መርከብ ድረስ እየገለበጠ ስፍር ቁጥር የሌለው ሕይወትንና ንብረትን ሲያወድም ለመኖሩ በብዙ ቅዱሳት መጻሕፍት ተመዝግቦ ይገኛል ዮናስ. 1፡4-16 ማቴ. 8፡23-27 ማር. 4፡35-41 የሐ.ሥ. 27፡1-44፡፡

በዘመናችንም በሰዓት ይህን ያህል ኪሎ ሜትር እየተጓዘ ይህን ያህል ሕይወት አጠፉ ይህን ያህል ንብረት አወደመ ሲባል ከመስማታችንም በላይ ይሆናል ተብሎ የማይገመት በዐይን ያየ ካልሆነ በስተቀር ለማመን የሚያዳግት ዕድሜ ጠገብ የሆኑ ትልልቅ ዛፎችን እየገነደሰ ሲጥል ስማይ ጠቀስ ፎቆችን እየገለጠና እየፈረካከሰ ሲጥል ዘመን ባመጣው በቴሌቪዥን በየጊዜው የምናስተውለው ጉዳይ ነው፡፡

የመብረቅም ኃያልነት እንደሚታወቀው ደረቁን ከርጥቡ አንድ አድርጎ ያቃጥላል ብዙ ሕይወት ብዙ ንብረት ያጠፋል በድምፁም ምድሩ ሁሉ ይንቀጠቀጣል ፍጥረቱ ሁሉ ይደነግጣል የሚገባበትን ያጣል፡፡

የእነዚህ ሁሉ ተፈጥሮ ማለት እንደዚሁ ረቂቃንና ኃያላን ሁነው መፈጠራቸው አስተዋይ ልቡና ያለው የሰው ልጅ እነዚህን አይቶ ከእነዚህ በስተጀርባ እነዚህን ሁሉ የፈጠረ ከረቂቃን ሁሉ የበለጠ ረቂቅ ከኃያላን ሁሉ የበለጠ ኃያል እግዚአብሔር ያለ መሆኑን በውል ይገነዘባል፡፡

ለማጠቃለል፤

የእግዚአብሔርን ሀልዎት ለማወቅ ሕጉንና ሥርዓቱን ለመጠበቅ በዚህ ዓለም እግዚአብሔር የሚወደውን ሥራ ሠርቶ በወዲያኛው ዓለም መንግሥተ ሰማያትን ወርሶ ለመኖር ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ ግድ ይላል፡፡ ሌላ አማራጭ የማይገኝለት ወሳኝ መፍትሔውም ይህና ይህ ብቻ ነው፡፡

ጥበበኛው ሲራክ የመጽሐፉን ነገር ሁሉ ፈጥነህ ስማ የጥበብም ምሳሌ አይዘንጋህ ብልህ /የተማረ/ ሰው ብታይ ፈጥነህ ወደእርሱ ሂድ እግርህም በደጃፉ መድረክ ይመላለስ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ዐስብ መጻሕፍቱንም ሁል ጊዜ አንብብ ሲራ. 6፡35-36 ያለውም ስለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስም ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ ተጠቃሚ እንዲሆን ደቀመዝሙሩ ጢሞቴዎስን መጻሕፍትን አዘውትሮ እንዲያነብ አጥብቆ አዞታል 1ጢሞ. 4፡13-15፡፡

ነገር ግን ትውልዱ በአሁኑ ጊዜ ከእግዚአብሔር ይልቅ በቴሌቪዥን ውስጥ የሚታዩትን መዝናኛ ተብዮዎቹ የሰይጣን አላማ ማስፈጸሚያ የሆኑትን አብልጦ ስለወደደ ሀልዎተ እግዚአብሔርን አምልኮቱንና መግቦቱን ከሀሊነቱ ወዘተ ሁሉ የሚናገሩ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ በመመልከትና በማድመጥ ፈንታ የሰይጣን ወጥመድ የሆኑትን ጐጅ ፊልሞችን ድራማዎችን ዘፈኑና ዳንኪራውን እንደዚሁም ከተሰጡት ተአምራት የተነሣ በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ያስታል፡፡ የአውሬውን ምስል ያደርጉ ዘንድ የአውሬው ምስል ይናገር ዘንድ በአውሬው ነፍስ ያሳድበት ዘንድ ራእ. 13፡13-15 ያለው እንዲፈጸም ተንቀሳቃሽ ሥዕሎችን /አሻንጉልቶችን/ መመልከትና ማዳመጥን ነው ቋሚ ሥራ አድርጎ የተያያዘው ይህ ለሥጋዊ ሕይወት አስፈላጊ ነው ነገር ግን ሥጋ የሚወደውን ነፍስ አትወድም ገላ. 5፡15-21 እንዳለው በነፍሱ እየሞተ እንደሆነ ሁሉ ሊገነዘበው ይገባል፡፡

ስለሆነም ሁሉም ቆም ብሎ ሊያስብና ርቆ ከሄደበት ከሰይጣን ጎዳና ተመልሶ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ ሀልዎተ እግዚአብሔርን አውቆና ተረድቶ በዚች በቅፅበት በምታልፈዋ ዓለም የማያልፈውን ዘለዓለማዊ የእግዚአብሔር ፈቃድ ፈጽሞ ዘለዓለማዊ መንግሥቱን ወርሶ ለመኖር ንስሓ መግባቱ እጅግ እጅግ የተሻለ ነው ሥጋ እንደፈለገ መዝናናቱ አያዋጣም በተዘፈነበት ቤት ሳይለቀስበት አይቀርም እንደተባለው ዛሬ በተሳቀበት አፍ ነገ ማልቀሱ አይቀሬ ነውና ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ በነፍሱ ከተጐዳ ምን ይረባዋል ተብሎ ተጽፎአልና ማቴ. ፡፡

ቸርነት የባሕርዩ የሆነ እግዚአብሔር አምላክ ሁላችንንም መንግሥቱን ለመውረስ የተገባን እንድንሆን ይርዳን አሜን፡፡

 

የፎንት ልክ መቀየሪያ