Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

ክፍል አንድ

በሊቀ ካህናት ብርሃኑ ገ/አማኑኤል

ሀ. እምነት የሚለው መሠረታዊ ቃሉ ግዕዝ ሲሆን ትርጓሜውም ማመን፣ ወይም መታመን ማለት ነው፡፡ ማመን ስለ እግዚአብሔር የሰሙትንና የተረዱትን፣ እንዲሁም የተቀበሉትን ትምህርት እውነት ነው ብሎ በልብ መቀበል ነው፡፡

መታመን ደግሞ ያመኑትን ወይም የተቀበሉትን እምነት በሰው ፊት ሳይፈሩና ሳያፍሩ መመስከር ነው፡፡ መረጃውም "በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፣ በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማይ ባለው አባቴ ፊት እከደዋለሁ" የሚለው ነው፡፡ ማቴ. 10፥32፡፡

ከዚህም ጋር ብርሃነ አሕዛብ፣ የተመረጠ የሃይማኖት መሣሪያ የተሰኘው ቅዱስ ጳውሎስም" ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን ለይቶ እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህ" ሲል አስተምሯል፡፡ ሮሜ. 10፣9 በመሆኑም ስለሃይማኖት የተማሩትን በልብ ማመን፣ ያመኑትን በሰው ፊት መመስከር ተጠቃሎ ሃይማኖት ይባላል፡፡ ከዚህም ጋር ቤተ ክርስቲያን የተሰጣትን የሃይማኖት አደራ በጥብቅ መንክባከብ ያለባት ዘመን ከመቼውም ይልቅ አሁን ነው፡፡

ሃይማኖት ዓለም አቀፍ ክስተት ስለሆነ ሰብአዊ ፍጡር ሁሉ የሃይማኖት ቁራኛ ነው፡፡ ሃይማኖት የሰውን የውስጥ መንፈሳዊ ሕልውና የሚዳስስና የሚቈጣጠር፣ ስሜትን የሚቀሰቅስና ሕይወትን የሚመራ ታላቅ ኃይል ነው፡፡ሃይማኖት ለሰው ልጆት ከተሰጡት ታላላቅ በረከቶች መሀል አንዱና ዋናው ነው፡፡

ሃይማኖት ራሱ ምንድን ነው

ሃይማኖት ሰው በአእምሮው ጥቂት መመራመርንና ማስተዋልን እንደጀመረ የተገኘ ጥንታዊና መሠረታዊ ክቡር ኃይል ነው፡፡

የመጀመሪያውን ሰው መለስ ብለን ስንመለከተው በሰውነቱም ሆነ በሃይማኖቱ ረገድ የነበረበት ደረጃ ዝቅ ያለ እንደነበር እናያለን፡፡ ይህም ማለት በሀሳቡና በሥራው፣ በአምልኮውም ዓይነት እንደዛሬው ሁሉ የተራቀቀ አልነበረም፡፡ እንደአሁኑ የተዋቡ ቤቶች፣ ሞቃት ልብሶች በመሬት የሚሽከረከርበት፣ በባሕር ላይ የሚንሳፈፍበት፣ በአየር ላይ የሚበርበት በጠቅላላም ኑሮውን ምቹ የሚያደርጉለት ነገሮች ሁሉ አልነበሩትም፡፡ ይሁን እንጂ በተፈጥሮው በተሰጠው አምላካዊ ፀጋ መሠረት ለኑሮው አስፈላጊ የሆኑትን መሠረታዊ ፍላጎቶች ሁሉ ከአለመኖር ወደ መኖር፣ የማምጣት ወይም የማስገኘት ኃላፊነት ነበረበት፡፡ ምክንያቱም ለሌሎች ፍጥረታት ያልተሰጠ አእምሮ፣ ወይም ማስተዋል በእግዚአብሔር የተሰጠው ለሰው ብቻ ስለሆነ ነው፡፡

በዘመናችን ከላይ ለተወሳው ጥያቄ መልስ ለማግኘት ብዙዎች የዓለምን ሃይማኖቶች እና በሰብአዊ ሕይወት ውስጥ ሃይማኖት እንዴት እንደሚከሰት አበክረው ይመረምራሉ፣ ያጠናሉም፡፡ በሃይማኖት መካከል ንጽጽራዊ ጥናት በማድረግ የሃይማኖትን ትክክለኛ ገጽታና በተለያዩ የዓለም ሕዝቦች ዕለታዊ ኑሮ ውስጥ ሳይቀር እንዴት እንደሚከሰት በማየት አጠቃላይ የሆነ ትርጉም ለመስጠት ሞክረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ምርምራቸው ብዙውን ጊዜ ከሃይማኖት ውጪ እንዳደረጋቸው ይታያል፡፡ ዳሩ ግን የሃይማኖትን ትክክለኛ ሁኔታ በትክክል እንድንረዳ የሚያደርገንና ቀጥተኛ አመለካከትን የሚያስጨብጠን ስነ ፍጥረትና ቅዱስ መጽሐፍ ብቻ ነው፡፡

ማስረጃውም፡- "ወዘኢያስተርኢ እግዚአብሔር እምፍጥረተ ዓለም ይትዐወቅ በፍጥረቱ" ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ታይቶ የማይታወቅ እግዚአብሔር የፈጠረውን ፍጥረት በማሰብና በመመርመር ይታወቃል፡፡ የሚለውና "ትስሕቱ በኢያእምሮ መጻሕፍት ወኢ ኃይለ እግዚአብሔር" ቅዱሳት መጻሕፍትን የእግዚአብሔርንም ኃይል ባለማወቃችሁ ትስታላችሁ፡፡ የሚለው ይሆናል ሮሜ. 1፡20፣ ማቴ.22-29 ከዚህ መሠረተ ሀሳብ በመነሳት ተፈጥሮ ራሱ በጉልህ ፊደሎች የተጻፈ ለሰው ልጅ የእግዚአብሔርን መኖር የሚያሳይ ታላቅ መጽሐፍ ነው በማለት ሊቃውንት ማብራሪያ ይሰጣሉ፡፡ "ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፣ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል" የሚለውም ተጨማሪ ማስረጃ ነው፡፡ መዝ. 18-1፡፡

ለ/ የሃይማኖት መነሻ
በቅድመ ታሪክ ሰው እውነተኛውን ነገር ለማግኘት ማለትም እግዚአብሔር ማን እንደሆነና ከዓለሙ ጋር ያለው ግንኙነት ምን እንደሆነ፣ ለመረዳት ብዙ ጥረት አድርጎአል፡፡ ስለሆነም በዚህች ዓለም ፈጣሪን ለመረዳትና የማመን የቻለ አእምሮ ያለው ሰው የተባለው ፍጡር ብቻ ሆኖ ተገኝቶአል፡፡ ሌሎቹ ፍጥረታት ግን የእግዚአብሔርን ጥበብ /ሥራ/ በሰውነታቸው ላይ ከማሳየት በስተቀር ጥበቡ ከምን ላይ እንደሆነና የፈጣሪ መኖርም በፍጥረት በኩል ግልጽ ሆኖ መታየቱን አይገነዘቡም፡፡ ስለሆነም ልዑል እግዚአብሔር በነቢያትና በሐዋርያት አንደበት በማናገሩ እና በመናገሩ ራሱን ገልጾአል፡፡ እንዲህ በማለት ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ሁሉን በፈጠረበት በልጁ በኋለኛው ዘመን ለእኛ ተናገርን ዕብ. 1፡1-2፡፡

ሐ/ ሃይማኖት ማለት ምን ማለት ነው
ትምህርተ ሃይማኖት ብለን ስንናገር ትምህርተ እግዚአብሔር ወይም ስለ እግዚአብሔር ሕልውና /መኖር/ የሚታየውንና የማይታየውን ረቂቁንና ግዙፉን የሚዳሰሰውንና የማይዳሰሰውን የፈጠረና ያስገኘ ኃያል አምላክ መኖሩን የምናጠናበትና የምንመረምርበት ክፍል ትምህርተ ሃይማኖት ይባላል፡፡

በመሆኑም "አመንኩ በዘነበብኩ" መዝ. 115፡1 ተብሎ በአፈ ዳዊት የተሰጠውን ወይም የተነገረውን ቃለ ስምዕ መሠረት በማድረግ እያንዳንዱ አማኝ ሁል ጊዜ የሚናገረውና የሚመሰክረው ምስክርነት ትምህርተ ሃይማኖት ይባላል፡፡

አንድ አማኒ ምኑን እንደሚያምን እንዴትም እንደሚያምን መጀመሪያ ደህና አድርጎ እምነቱን መረዳት ማወቅም አለበት ያን ያመነውንና የተረዳውን ደግሞ ሳያፍርና ሳይፈራ ለሌላው መናገር መመስከርም አለበት ይኸም የአማንያን ሁሉ ተግባርና ግዴታ ነው፡፡

የክርስትና እምነት ሁል ጊዜ ምስክርነትን የሚጠይቅ እምነት ነው፡፡ ስለዚህ ነው ቤተ ክርስቲያን በቁጥር የበዙ ሰማዕታትን የምታከብር እነዚህ ሰማዕታት በእውነት ስለ እውነትም የሚያምኑትን ሲመሰክሩ የመሰከሩትንም ሲያምኑ በመገኘታቸው የእውነት ጠላት በሆኑ ሰዎች ሕይወታቸውን በሞት ያሳለፉ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ስማቸው ከመቃብር በላይ ነው፣ ነፍሳቸው ደግሞ በገነት በደስታ ሆኖ በየዓመቱ መታሰቢያቸው ሲከብር ይኖራል፡፡

ሰማዕት ወይም ሰማዕታት ማለትም ምስክሮች ማለት ነው፡፡ ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያኑ በእውነት ሲናገሩ ሲመሰክሩ የሚያምኑትን ሲናገሩ የተናገሩትን እያመኑና በዚያውም እያጸኑ በመገኘታቸው ይኸው ቀዋሚ ምስክርነታቸው ለቤተ ክርስቲያን ሕይወትን ሰጥተው ይኖራል፡፡ ዛሬም እንደእነዚህ ሰማዕታት የሚያምኑትን የሚናገሩ የሚናገሩትንም የሚያምኑ ካህናትም ምእመናንም ለቤተ ክርስቲያን በጣም ያስፈልጓታል፡፡ ግን እንዲህ ያለ ምስክርነት ከመስጠት አስቀድሞ የሚያምኑትን መማር ማወቅ ከዚያ በኋላ ምስክርነትን መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡

"ርትዕት ይእቲ ሃይማኖቶሙ ለቅዱሳን አበዊነ" የአባቶቻችን ሃይማኖት የቀናች ናት፣ እንደተባለው እምነታችን የቀና ደግሞም የጸና ነው፡፡ ይህም እምነታችን በልብ ወለድነት የተወሰነ ሳይሆን በክርስቶስ የተመሠረተ የተገለጠ፣ ሃይማኖታቸው በቀና አባቶች የተደገፈና የተመሰከረለት ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ኦርቶዶክሳዊት፣ ጥንታዊት ሐዋርያዊትም የሆነችውን ያህል እምነታችን ትምህርታችን ሥርዓታችንም ሁሉ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የነበረ በልዩ ልዩ ዐረፍተ ዘመን ለውጥ ያላገኘው ሊጨመርበትም ሊቀነስበትም የማይቻል የማይገባም ሁኖ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ሃይማኖት ነው፡፡

ይህ የጸናው የቀናውም እምነታችን በወንዱም በሴቱም በትልቁም በትንሹም በካህኑም በጨዋ ልጁም በግድ መታወቅ፣ መነገር፣ መገለጥም ግድ አለበት፡፡ ከዚያ በፊት ግን እያንዳንዱ በየራሱ ምን እንደሚያምን ምን እንደሚቀበል ማወቅና መረዳትም አለበት፡፡
የሚያምኑትን ማወቅ መናገር መመስከርም የሚናገሩትንም የሚመሰክሩትንም መናገር ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ (መዝ. 115፥1) እምነቱን ለይቶ የማያውቅና የማይመሰከር በሥራም የማይገልጥ አማኝ ነው ሊባል ከቶ አይገባም በወንጌል ምሳሌው እንደተነገረበት ወርቁን እንደቀበረ ሰነፍ አገልጋይ ይሆናል እርሱንም ይመስላል፡፡ ሰነፉን አገልጋይ ባለቤቱ በተቆጣጠረው ጊዜ መልስ አጥቶ ባለቤቱ እንደተቆጣው እንደቀጣውም ቅዱስ ወንጌል ይነግረናል ማቴ. 25 ፥ 24 – 30፡፡

ስለዚህ ሁላችንም ስለ እምነታችንና ስለ ትምህርታችን በልዩ ልዩ አጋጣሚ መናገር መመስከር ማስተማር ለተተኪውም ትውልድ በሚገባ ማስተላላፍ ግዴታ መሆኑን ማመንና ማወቅ አለብን ስለክርስቲያናዊ እምነትና ትምህርት የወል መግለጫ ነው ተብሎ የተወሰነ፣ ኦርቶዶክሳውያን አባቶቻችን ያስተላለፉልን የኒቅያና የቁስጥንጥንያ ተአምኖ ሃይማኖት (ጸሎተ ሃይማኖት የተባለው አለን፡፡

ይህም ተአምኖ በ2 ዐበይት የመጀመሪያዎቹ ጉባኤዎች የተወሰነ ሲሆን እያንዳንዱ ምእመን ራሱን እንዲጠብቅበት፣ አስፈላጊም በሆነበት ቦታ ሁሉ ለሌላው እንዲመሰክርበት በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት በኦርቶዶክሳውያን አባቶቻችን የተወሰነ ነው፡፡

የመጀመሪው ዐቢይ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ በቢታኒያ ከተማ በኒቅያ በ325 ዓ.ም በተደረገው ጊዜ የተሳተፉት ሊቃውንት ብዙዎች ነበሩ ከነዚያም ውስጥ የተለያዩና የታወቁ ኦርቶዶክሳውያን ሆነው የተገኙት 318 ብቻ ናቸው እነርሱም ዘመን የማይሽረውን የሃይማኖት ውሳኔ" ነአምን በአሐዱ አምላክ" ብለው" ዳግመ ይመጽዕ በስብሐት ይኰንን ሕያዋነ ወሙታነ ወአልቦ ማኅለቅት ለመንግሥቱ" እስከሚለው ድረስ 7 አንቀጾች ያሉበትን የሃይማኖት ትምህርት ወስነዋል፡፡ ለዚህም ጉባኤ መንስኤ የሆነው የአርዮስ ኑፋቄ በመከሰቱ ስለሆነ እርሱን ለይቶ ሃይማኖትን አቅንቶ ሥነ ሥርዓትን ሠርቶ ለመወሰን የተደረገ ጉባኤ ነው፡፡
በመሆኑም 318 አበው ሊቃውንት ጉባኤውን በሚገባ አካሄደው ስለወልድ የባሕርይ አምላክነት አረጋግጠው አርዮስን አውግዘው ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ለይተው ተአምኖ ሃይማኖት (ጸሎተ ሃይማኖት) በአንቀጽ ወስነው ለቤተ ክርስቲያን ዘለዓለማዊ መመሪያ እንዲሆን አድርገዋል፡፡

በጉባኤ ቁስጥንጥንያ ማለትም በ318 ዓ.ም በ2ኛው ዐቢይ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ በቁጥስንጥንያ ጉባኤ ከተማ በተደረገ ጊዜ ከብዙ ሊቃውንት መካከል 150 ኦርቶዶክሳውያን አባቶች እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው እውነተኛውን የሃይማኖት መግለጫ አምስት አንቀጾች ያሉበት አድርገው "ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ" ከሚለው ጀምረው እስከ መጨረሻው ያለውን ተአምኖ ሃይማኖት ወስነው አስተላልፈዋል፡፡ ለሁለተኛው ጉባኤም መንስኤ የሆነው መቅዶንዮስ የተባለው መናፍቅ ነበር፡፡ እርሱም መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ያንሳል (ሕጹጽ) ነው፡፡ ብሎ ስለተነሣና ስላስተማረ የኑፋቄ ትምህርቱን ለማጥፋትና እርሱንም ከቤተ ክርስቲያን አንድነት አውግዘው ለመለየት የተደረገ ጉባኤ ሲሆን ከላይ ቁጥራቸውን የገለጽነው አባቶች ተሰብስበው በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ጉባኤውን አካሂደው መቅዶንዮስን አውግዘው ሃይማኖትን መልሰው ተአምኖ ሃይማኖትን (ጸሎተ ሃይማኖትን) ወስነው አሰተላልፈዋል፡፡

በሁለቱ ዐረፍተ ዘመናት በተለያዩ አባቶች የተወሰነው የሃይማኖት ውሳኔ በአንድ መንፈስ ተቃኝተው እንደወሰኑት ሁኖ በጸሎተ ቅዳሴ፣ በግል ጸሎት የሚውል ስለሆነ ጸሎተ ሃይማኖት ለሃይማኖትም መግለጫና መመስከሪያ ሲሆን ተአምኖ ሃይማኖትም እየሆነ አንድ ሥረ-ወጥ ውሳኔ ሆኖ በአንዲቱ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ሲነበብና ሲተረጎም ይኖራል፡፡ ይኸው ተአምኖ ሃይማኖት ለትምህርትና ለምስክርነት በቂ ስለሆነ ማንኛውም ምሑር ስለዶክትሪን (ዶግማ) ሰፋ አደርጎ እጽፋለሁ ቢል ከዚህ ውጭ ሊሄድ ከቶ አይችልም፡፡ እንዲሁም በመጠኑ ቢጽፍም ከዚህ ውስጥ የሚቀንሰው የሚተወውም የለም ምክንያቱም መጀመሪያውኑ በመንፈስ ቅዱስ መሪነትና አጋዥነት የተዘጋጀ ስለሆነና ያለምንም ለውጥ ለመኖር የሚችል ስለሆነ ነው፡፡

እንደ አጋጣሚ ሆኖ በምሥጢረ ክህነት ጊዜ በተለይም በሢመተ ጵጵስና ጊዜ ተአምኖ ሃይማኖት ሲሰጥ ይህንን እና ይህን የመሠለ የሃይማኖት መግለጫ መስጠት ግዴታ ነው፡፡ በአጠቃላይ በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት የጸሎት ሁሉ መሣሪያና ማጠቃለያም ጸሎተ ሃይማኖት እንዲሆን ተወስኗል፡፡ ይኸ የእምነት መግለጫ እንደ ጸሎት እየሆነ በልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሁሉ ይግባ እንጂ ተፈላጊነቱ የእምነት ምሥክርነት የእምነት መግለጫ ሁኖ እንዲሰጥ ምዕመናን እምነቱን ከቀን ወደ ቀን ቀስ በቀስ እንዲማሩት እንዲያውቁት እንዲያጠኑት ቀጥሎም እንዲመሰክሩት ያስፈልጋል፡፡

ጠቅለል ባለ መልኩ ትምህርተ ሃይማኖት ብለን ስንናገር ትምህርተ እግዚአብሔር ወይም ስለ እግዚአብሔር ሕልውና (መኖር) የሚታየውንና የማይታየውን፣ ረቂቁንና ግዙፈን የሚዳሰሰውን የፈጠረና ያስገኘ ኃያል አምላክ መኖሩን የምናጠናበትና የምንመረምርበት ክፍለ ትምህርት ማለት ነው፡፡

መ. እግዚአብሔር ማለት ምን ማለት ነው
እግዚአብሔር ተብሎ የተተረጎመው በዕብራይስጡ ቋንቋ "ኤል" ማለት ወይም በብዙ ቁጥር ኤሎሂም የሚለው ቃል ማለት ኃያል ማለት ሲሆን ኤልሻዳይ ማለት ደግሞ ሁሉን ቻይ ማለት ነው፡፡ በግእዝ ቋንቋችን እግዚአብሔር ማለት ግን የአገር ወይም የዓለም ጌታ ሁሉን አስገኝ ማለት ነው፡፡

እግዚአብሔር የሚለውን ቃል ትርጉም ለመወሰን የዓለም ሕዝብ በየቋንቋው ይለያይ እንጂ ፍጥረታትን ሁሉ የፈጠረና የየዕለት እንቅስቃሴውን የሚመራና የሚያስተናብር አንድ የማይታይ የማይዳሰስ ኃይል መኖሩን ያምናል፡፡ በሌላ አገላለፅ እግዚአብሔር የሚለው ስም የባሕርይ ስም ነው፡፡ ትርጉሙም ዓለምን ፈጥሮ የሚገዛ ማለት ነው፡፡ የማይታይና የማይመረመር ሁሉን ማድረግ የሚችል፣ ሁሉንም የፈጠረ፣ መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው ዘለዓለማዊ አምላክ መኖሩና ራሱን ለሰው ልጆች እንደገለጠ በቅዱሳት መጻሕፍት ተረጋግጦአል፡፡ ዘፀ3፣ 5፥6

ይሁን እንጂ ማንኛውም ሃይማኖት አንዱ ከሌላው ተለይቶ የሚታወቅበት መመሪያና ሥርዓት አለው፡፡የክርስትና ሃይማኖትም ምንም እንኳ እንደ ሌሎቹ ሃይማኖቶች ሰው ሠራሽ ባይሆንም በቅዱሳት መጻሕፍት መነሻና መረጃነት የራሱ የሆነ ትምህርተ ሃይማኖት አለው፡፡ ይኸንንም ፈረንጆች ዶግማ ይሉታል፡፡ ዶግማ ቃሉ የጽርዕ /የግሪክ/ ይሁን እንጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሁሉም የሚጠቀሙበት ቃል ነው ፍችውም እምነት ማለት ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን የክርስትና ሃይማኖት በብሉይ ኪዳን በሐዲስ ኪዳን ብቻ ሳይሆን ከአበው ሐዋርያርያት ከአበው ሊቃውንት በአፍ በመጣፍ ሲነገር የመጣውን ሁሉ ትቀበላለች ይኸም ትውፊት ይባላል፡፡ በቅብብል የመጣ፣ የወረደ፣ የተወረሰ ማለት ነው፡፡ ዮሐ. 20 ፥ 30 21 ፥ 25
ትምህርተ ሃይማኖት አንደኛው ክፍል መጽሐፍ ቅዱስ ሲሆን በፍርድ በብያኔ ወይም እንደ ጊዜው ሁኔታ የማይሻሻልና የማይለወጥም ነው፡፡ ሁለተኛው ክፍል ደግሞ ቀኖና ይባላል፡፡ ቀኖና (ካኖን) ቃሉ ጽርዕ (ግሪክ) ነው፡፡ ቀጥተኛ ፍችውም መቃ ማለት ነው የጥንት ሰዎች ልብስም ሆነ መሬት የሚለኩት በመቃ እየከነዱ ነበረ የቤተ ክርስቲያን መጋቢዎች አበውም የሠሩትን ሥርዓትና ሕግ ቀኖና ብለውታል፡፡

ይህ ማለት ምዕመኑ የዲያቆኑን ዲያቆኑ የቄሱን ቄሱ የኤጲስ ቆጶሱን (ጳጳሱን) የሥራ ድርሻ በማዕረግም ሆነ በሌላው ሁሉ መሻማት እንዳይኖር ሁሉም ድርሻውን እንዲያውቅ ከዚህም ጋር የአፅዋማት የበዓላት ልካቸውና መጠናቸው የመጽሐፍት ቁጥራቸውና ቅደም ተከተል አቀማመጣቸው ሁሉ በቀኖና ነው የሚታወቀው፡፡

ቀኖና ከትምህርተ ሃይማኖት (ዶግማ) ጋር አንድ ነው፡፡ ነገር ግን በአንድ ነገር ብቻ ይለያል በትምህርተ ሃይኖት ውስጥ ምንም የሚሻሻሉ ወይም የሚለወጥ ነገር የለም በቀኖና ውስጥ ግን እንደጊዜው ሁኔታ የሚሻሻሉ አንቀጾች ሊሻሻሉ ስለሚይችሉ ነው፡፡ ለምሳሌ የጾም ሰዓት የቅዳሴ ሰዓት በጠቅላላው በችግር ወቅት የሚደረጉ ለውጦችን ይመለከታል፡፡ ስለዚህ ትምህርተ ሃይማኖትና ቀኖናን ለይቶ ማወቅና መረዳት ያስፈልጋል፡፡

እነዚህ ሁለት ዐበይት ነገሮች በትክክል ተለይተው ካልታወቁ ቤተ ክርስቲያንን እምነት አልባ ሥርዓት ዓልባ ያደርጋታል፡፡ አንዳንድ ሃይማኖት አልባ ሰዎች "ሃይማኖት ሰው ሠራሽ ቅዠት፣ ወይም ከፍርሐት የመነጨ ምትሀት ነው ይላሉ፡፡ በእነሱ አስተሳሰብና አባባል ሃይማኖትን የፈጠሩት ወይም የፈለሰፉት ሰዎች ናቸው፡፡ ስለዚህም አባባላቸው ዋናው ምክንያት የቀድሞ የዋሃን ሰዎች እሳቱ ዛፉን፣ ቅጠላ ቅጠሉን ደረቁንም እርጥቡንም ሲያቃጥል ሲያዩ በእሳት ያመልኩ ነበር፡፡ ነፋስ ደግሞ ባሕርን ሲያናውጽ ሲያዩ በነፋስ ያመልኩ ነበር፡፡ ማዕበል መርከብን ሲገለብጥ ሲያዩ በውሃ ያመልኩ ነበር፡፡ ስለዚህ የሃይማኖት ምንጩ ፍርሃት ወይም ሰቀቀን ነው ይላሉ፡፡

በክርስትና ሃይማኖት ግን እንደዚህ አይደለም ሃይማኖት በሰዎች የተፈጠረ፣ ወይም የተፈለሰፈ አይደለም ከፍርሃትና ከድንጋጤም የመጣ አይደለም፡፡ ሃይማኖት ከመጀመሪያው የሰውና የእግዚአብሕር ግንኙነት ነው፡፡ ማለትም እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር ስሙን ጠርቶ ስሙን አምኖ እንዲያመሰግነው፣ ክብሩንም እንዲያወርሰው ነው፡፡

ሰው የታዘዘውን ሲያፈርስ እምነት አጉዳይ ሆነ ሃይማኖቱ ጠፋው በዚህ ጊዜ ከፈጣሪው ተደበቀ፡፡ ፈጣሪውም እንደገና የጥሪ ድምፁን አሰማው ወዴት ነህ አለው ዘፍ. 1 ፥ 1-26
እንግዲህ በቤተ ክርስቲያን አማካይነት በትምህርተ ሃይማኖት መነጽርነት የምናየው፣

ሀ. መጀመሪያ በመፍጠር ዘፍ. 1 ፥ 1-26
ለ. ትእዛዝን (ሕግን) በመስጠት
ሐ. ሦስተኛውም ከጠፋበት በመፈለግ እግዚአብሔር ለሰው ያሰማው ድምፅ ወደ ሰው ያደረገው ጉዞ ነው፡፡
በዚህም ምክንያት ሃይማኖት ፍኖተ እግዚአብሔር ይባላል፡፡

በተለይም የክርስትና ሃይማኖት የአምላክ መገኘት ስለሆነ የአምላክን ወደ ሰው መምጣት፣ የጠፋውን መፈለግ ስለሆነ የመጀመሪያውን ሰው ለመፈለግ የተደረገው አምላካዊ ጉዞ የተፈጸመበት እና የታተመበት ስለሆነ ሃይማኖት ፍኖተ እግዚአብሔር ነው ቢባል ትክክለኛ ትርጉም ይሆናል፡፡

የፎንት ልክ መቀየሪያ