Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!

"መነ ይብልዎ ሰብእ ለወልደ ዕጓለ እመሕያው፣ ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?" (ማቴ. 16፥13)

በሀገራችን በኢትዮጵያና በተለያዩ ክፍላተ ዓለም ሆናችሁ ይህን የቅዱስ ወንጌል ቃል በመስማት ላይ የምትገኙ ውሉደ እግዚአብሔር ሁሉ፣ እግዚአብሔር አምላካችን በረከቱን፣ ጸጋውንና መልካም ስጦታውን ሁሉ እንዲያበዛላችሁ እየጸለይን፣ እንኳን ለበዓለ ደብረ ታቦር በሰላም አደረሳችሁ እንላለን ፡፡

የደብረ ታቦር በዓል ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ ባህርዩንና ምሥጢረ መንግሥቱን የገለፀበት ቀን በመሆኑ፣ በክርስትናው ዓለም ዓቢይ ስፍራ የሚሰጠው ታላቅ በዓል ነው ፡፡

የታቦር ተራራ ቀደም ሲል ከክርስቶስ ልደት በፊት ዲቦራ የተባለች ነቢይት በዚህ ተራራ ላይ ቆማ ወደ እግዚአብሔር በመጸለይና የጦር አመራርን በመስጠት፣ ሕዝበ እሥራኤልን ለመውጋትና ለመውረር በእብሪት ተነሣሥቶ የመጣውን ሲሣራን፣ በባርቅ አዝማችነት ድል ያደረገችበት የድል ተራራ እንደሆነ በቅዱስ መጽሐፍ ተጽፎአል፤ (መሳ. 4፡4-24)፡፡

ይህ ድል በዘመነ ሥጋዌ የሚነሡትን የኑፋቄ ትምህርቶች ሁሉ በደብረ ታቦር በሚገለፀው መለኮታዊ ትምህርት ድል የሚደረጉ መሆናቸውን የሚያመለክት ነበር ፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊትም "ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል፤ ስምህንም ያመሰግናሉ፤ ክንድህ ከኃይል ጋር በዚያ ይገለጻል" በማለት እግዚአብሔር ወልድ በዚህ ተራራ ላይ ኃይለ መለኮቱን ሲገልጽ፣ ተራራው በብርሃነ መለኮቱ ደምቆ የደስታ ተራራ እንደሚሆን ከክርስቶስ ልደት በፊት በአንድ ሺሕ ዓመት ገደማ በትንቢት ተናግሮለታል፤ (መዝ. 88፡12)፡፡

የክርስትና ሃይማኖት ከጥንተ ፍጥረት ጀምሮ በልዩ ልዩ ኅብረ ትንቢት፣ በልዩ ልዩ ኅብረ አምሳል፣ በልዩ ልዩ ኅብረ ቃል እንደ ሰንሰለት ተያይዞ የመጣውን ተስፋ-ድኅነት መሠረት አድርጎ የቀጠለ ሃይማኖት እንጂ፣ በሆነ ፈላስፋ ወይም የፈጠራ ክሥተት የመጣ አይደለምና፣ እንደ ሌላው ትምህርተ ክርስትና ሁሉ፣ የታቦር ተራራ መለኮታዊ ክሥተትም በድንገት የተገለፀ ሳይሆን፣ ከክርስቶስ ልደት በፊት ለአንድ ሺሕ ዓመታት ያህል እየተነገረ የመጣና በተስፋ ሲጠበቅ የነበረ ድንቅ የእግዚአብሔር መለኮታዊ ክሥተት እንደሆነ ከቅዱስ መጽሐፍ ትምህርት እንገነዘባለን ፡፡

የትንቢትና የምሳሌ ሁሉ መዳረሻ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና፣ መድኃኒታችን በሥጋ በዚህ ዓለም ተገልጾ ወንጌለ መንግሥተ ሰማያትን ሲያስተምር፣ በተነገረው ትንቢት መሠረት መለኮታዊ ባህርዩንና ድል አድራጊው ምሥጢረ መንግሥቱን በደብረ ታቦር ላይ ገለፀ፤ የነገሩንም አፈጻጸም ቅዱስ መጽሐፍ እንደ ሚከተለው ያስተምረናል፡-
ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሕዝቡ መካከል ተገኝቶ ከሚያስተምረው ጥልቅ ትምህርትና ከሚሠራው ድንቅ ተአምር የተነሣ ሕዝቡ ስለማንነቱ ብዙ ያወራና ይናገር ነበር ፡፡

ጌታችንም በሕዝቡ ዘንድ ያለውን የተለያየ አባባል ተቀባይነት አግኝቶ ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ እንዳይሄድ ለማረም በፈለገ ጊዜ "ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?" በማለት ደቀ መዛሙርቱን ጠየቀ ፡፡

ደቀ መዛሙርቱም ሕዝቡ የሚለውን በመጥቀስ አንዳንዶቹ ኤልያስ ነው ይሉሃል፤ አንዳንዶቹም ኤርምያስ ነው ይሉሃል፣ አንዳንዶቹ ደግሞ መጥምቁ ዮሐንስ ነው ይሉሃል፣ ሌሎቹ ደግሞ ከቀደምት ነቢያት አንዱ ሳይሆን አይቀርም ይሉሃል ብለው መለሱ ፡፡

ጌታችንም እናንተሳ ማን ትሉኛላችሁ? አላቸው፤ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ "አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ" ብሎ መለሰ ፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ ትክክለኛውንና እውነተኛውን መልስ ስለመለሰ፣ ጌታችን "የዮና ልጅ ስምዖን ጴጥሮስ ሆይ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ፣ ሥጋዊና ደማዊ አእምሮ ይህንን አልገለጸልህምና ብፁዕ ነህ" ብሎ መልሱን ከምስጋና ጋር ተቀብሎአል፤ (ማቴ. 16፡13-19)፡፡
ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ጌታችን ነቢይ ወይም ከነቢያት አንዱ ሳይሆን "የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ" መሆኑን ለደቀ መዛሙርቱ አረጋገጠላቸው፡፡


ከዚህ ቀደምም ጌታችን የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ቅዱስ ገብርኤል ቅድስት ድንግል ማርያምን ባበሠረ ጊዜ "ካንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል፤ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ" ሲል ስሙንና ማንነቱን በግልጽ አሳውቆ ነበር፤ (ሉቃ. 1፡30-35) ፡፡
እግዚአብሔር አብም ጌታችን በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ "የምወደው ልጄ ይህ ነው" በማለት ገልጾ ነበር፤ (ማቴ. 3፡17)፡፡

በጣም የሚገርመው ደግሞ አጋንንት ሳይቀሩ "አንተ ማን እንደሆንህ አውቀናል፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ፤ አንተ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ" እያሉና እየሰገዱ በተደጋጋሚ መመስከራቸው ነው፤ (ሉቃ. 4፡31-41) ፡፡

ይሁን እንጂ ጌታችን የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ እንደሆነ በፈጣሪም ሆነ በፍጡራን ዘንድ ብዙ ጊዜ ቢነገርም ሰዎች ይህን መገንዘብና ማወቅ አቅቶአቸው ወዲያና ወዲህ ሲባዝኑ በመገኘታቸው፣ ጌታችን በስማቸው እየተጠቀሰ ያሉትን ነቢያት በተገኙበት፣ በታቦር ተራራ ላይ ማንነቱንና የመንግሥቱን ምንነት ለመግለጽ ብሎ፣ ቅዱስ ጴጥሮስ በቂሳርያ ምስክርነቱን በሰጠ በስድስተኛው ቀን፣ ሦስቱ ደቀ መዛሙርቱን ይዞ ወደ ታቦር ተራራ ወጣ ፡፡

በዚያም ፊቱ ተለውጦ እንደ ፀሐይ ብርሃን ሆነ፤ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ሆነ፤ ሙሴና ኤልያስም ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩ፤ ብሩህ ደመናም መጥቶ ጋረዳቸው፤ ከደመናውም "የምወደው ልጄ ይህ ነውና እርሱን ስሙት" የሚል ድምፅ መጣ፤ ሦስቱ ሐዋርያት ማለትም ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ቅዱስ ዮሐንስና ቅዱስ ያዕቆብም ከግርማ መለኮቱ የተነሣ ፈርተው በምድር ላይ ወደቁ፤ በመጨረሻም ጌታችን ዳሰሳቸውና እንዲነሡ አደረጋቸው፤ (ማቴ. 17፡1-8) ፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
እንግዲህ ይህ ሁሉ የሆነው ዓለም በጌታችን ማንነትና በሚያወርሳት መንግሥቱ ምንነት መንታ መንገድ ላይ ቆማ በጥርጥርና በክሕደት እንዳትጎዳ እውነተኛው ትምህርትና እምነት የትኛው እንደሆነ ለይታ እንድታውቅ ለማድረግ ነው ፡፡

ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ካበሠረበት ቀን ጀምሮ እስከ በዓለ ደብረ ታቦር ድረስ ስለጌታችን ማንነት የተነገሩ ሁሉ ፣ጌታችን "የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ መሆኑን የሚያስረግጡ ናቸው፤ ይህም ማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር የተወለደ እግዚአብሔር መሆኑን አረጋግጠዋል ማለት ነው ፡፡

ምክንያቱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ መባሉ ሰዎች ከእግዚአብሔር በባህርይ ሳይወለዱ፣ በጸጋ ወይም በስጦታ የእግዚአብሔር ልጅ የመሆን መብት ተሰጥቶአቸው ውሉደ እግዚአብሔር እንደሚባሉት ዓይነት ሳይሆን፣ የእግዚአብሔር ብቸኛ የባሕርይ ልጅ ነው ለማለት ነው ፡፡

በሌላ አባባል በባህርያዊ ልደት ክዋኔ ከሰው የተወለደ ሰው፣ ከእንስሳም የተወለደ እንስሳ እንጂ ሌላ ሊሆን እንደማይችል ሁሉ፣ ከእግዚአብሔር በባህርይ የተወለደም እግዚአብሔር ከመሆን በቀር ሌላ ሊሆን አይችልምና ጌታችን የእግዚአብሔር የባህርይ ልጅ በመሆኑ እግዚአብሔር ነው ማለት ነው ፡፡

ፍጡራን በሙሉ በባህርይም፣ በመልክም ራሳቸውን የሚመስል ልጅ እንደሚያስገኙና ባህርያዊ ውርስንም በዘር እንደሚያስተላልፉ ሁሉ፣ ጌታችንም የእግዚአብሔር የባህርይ ልጅ ስለሆነ በባህርዩም፣ በመልኩም እንደአባቱ ነው፤ እንደዚሁም ለአባቱ ያለው ሁሉ ገንዘቡ በመሆኑ እንደ አባቱ እግዚአብሔር ነው፤

በዚህ የባህርይ ልጅነት ዓይነት ከእግዚአብሔር የተወለደ ሌላ ልጅ የለምና ቅዱስ መጽሐፍ ጌታችንን "አንድያ የእግዚአብሔር ልጅ ወይም ወልድ ዋሕድ" ይለዋል ፡፡ ይህ አገላለፅ የጌታችን ወልደ እግዚአብሔርነት በጸጋ ወይም በችሮታ ከእግዚአብሔር ከተወለድነው ከክርስቲያኖች ልጅነት ጋር በእጅጉ የተለየ መሆኑን ያስረዳል፣ (ዮሐ. 1፡ 12-18፣ ዮሐ. 3፡16) ፡፡

ጌታችንም ይህንን ሲያመለክት ነው "እኔና አብ አንድ ነን፤ እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ፤ ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ የእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው፤ የአንተም የእኔ ነው" ያለው (ዮሐ. 10፡30፣ 14፡11፤ 16፡15፤ 17፡10) ፡፡
ወንጌላዊው ዮሐንስም "በመጀመሪያው ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ፤ ... ያ ቃል ሥጋ ሆነ" በማለት የጌታችንን እግዚአብሔርነት በማያሻማ መልኩ በግልጽ ጽፎልናል፤ (ዮሐ. 1፡1-14) ፡፡

ከዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን ዓቢይ ነገር ጌታችን የእግዚአብሔር አብ ልጅ ቢሆንም፣ በአባቱና በእርሱ መካከል መቀዳደምና መበላለጥ የሌለ መሆኑን ነው፤ ምክንያቱም ባህርየ እግዚአብሔር አንድ ከመሆኑም ሌላ በሦስቱ አካላት መካከል የባህርይና የህልውና ልዩነት የለምና ነው፡፡

ቃል የሚለው የጌታችን ስምም ይህንን በሚገባ ይገልፀዋል፤ ምክንያቱም፡- የቃል ህላዌ ከልብና ከእስትንፋስ እንደማይቀድም ወይም እንደማይዘገይ ሁሉ ወልደ እግዚአብሔር ክርስቶስም በህላዌው ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ የማይቀድም ወይም የማይዘገይ መሆኑን በግልፅ ያስረዳልና ነው ፡፡

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ከጥንት ዘመን ጀምሮ ማለትም ከዘመነ ብሉይ አንሥቶ በግልጽና በማያሻማ መልኩ የተገለፀ ቢሆንም፣ ጥንትም ሆነ ዛሬ ሰዎች በዚህ ጉዳይ ላይ የተለያዩ አባባሎችን በመፍጠር መለያየታቸው አልቀረም ፡፡

ሆኖም ከሰዎች ደካማ ዕውቀትና አናሳ ግንዛቤ የተነሣ ችግሩ መከሠቱ ባይቀርም፣ ቅዱሳት መጻሕፍት ግን ጌታችን "የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ" እንደሆነ በማያሻማ መልኩ ነግረውናል፤

እግዚአብሔር አብም በፈለገ ዮርዳኖስና በደብረ ታቦር ይህንን አረጋግጦልናል፤ ቅዱስ ገብርኤልም በናዝሬት ከተማ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ባበሠረ ጊዜ፣ ቅዱስ ጴጥሮስም በቂሳርያ እግዚአብሔር ገልጾለት በመሰከረ ጊዜ፣ አጋንንትም በቅፍርናሆም ጌታችንን ባዩ ጊዜ፣ እርሱ ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን መስክረዋል ፡፡
የእግዚአብሔር ልጅ ማለትም እግዚአብሔር ማለት እንደሆነ ተቃዋሚዎቹ አይሁድ ሳይቀሩወቁትና የተረዱት ሐቅ ነበረ፡፡

አይሁድ ይህን ግንዛቤ ሊይዙ የቻሉት፣ የሰው ልጅ ሰው ከመሆን በቀር ሌላ እንስሳ ሊሆን እንደማይችል ሁሉ፣ የእግዚአብሔር ልጅም እግዚአብሔር ከመሆን በቀር ሌላ ሊሆን እንደማይችል በመገንዘባቸው ነው፤ አይሁድ ቁም ነገሩን አምነው ባይቀበሉትም አባባሉን ግን ምን ማለት እንደሆነ በትክክል ተገንዝበውታል ፡፡

ነገሩም እንዲህ ተገልጾአል፡- "ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ አይሁድ ሊገድሉት ፈለጉ" ይላል ቅዱስ መጽሐፍ፤ ይህ የአይሁድ ቁጣ፣ እግዚአብሔር አባቴ ነው ማለቱ፣ እግዚአብሔር ነኝ ማለቱ ነው፤ ከሚል የተነሣ እንደሆነ ጥቅሱ ያመለክታል፤ (ዮሐ. 5፡18) ፡፡

ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎች የነቢያትን ስም እየጠቀሱ ስለማንነቱ ይናገሩት የነበረውን አባባል ፍጹም ስሕተት መሆኑን ለማሳየት፣ በቅዱስ ጴጥሮስ የተነገረውን ምስክርነት፣ እንደገና በዓበይተ ነቢያት በሙሴና በኤልያስ፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ በባህርይ አባቱ በእግዚአብሔር አብ፣ የእግዚአብሔር የባህርይ ልጅ መሆኑን በታቦር ተራራ ላይ አረጋገጠ፤ ይህም ከሆነ ዓለም ስለጌታችን ማንነት መቀበል ያለባት እውነት ይህና ይህ ብቻ ነው፤ ከዚህ ውጭ የሆነ ሁሉ ስሕተትም፣ ቅዠትም፣ ውሸትም ከመሆን በቀር ምንም ዓይነት እውነትነት የለውም ፡፡

እኛም ከዚህ ተነሥተን ስለጌታችን ማንነት አምነን ስንመሰክር፡-

"በአንድ የእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን፤ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፣ ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ፣ የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ፣ በባህርዩ ከአብ ጋር አንድ የሆነ፤ ሁሉ በእርሱ የሆነ፣ ያለእርሱ ግን ምንም ምን የሆነ የሌለ" እያልን እናምናለን፤ እንመሰክራለንም ፡፡

ከዚህም ጋር "ጌታችን ሰውም፣ አምላክም ነውና በወልደ እግዚአብሔርነቱ እግዚአብሔር እንደሆነ ሁሉ፣ በክርስቶስነቱ ደግሞ የእግዚአብሔር ልጅም የሰው ልጅም መሆኑን አንዘነጋም፤ ስለሆነም ወልደ እግዚአብሔርና ወልደ ማርያም የሆነው ክርስቶስ ከሁለት አካላት አንድ አካል፣ ከሁለት ባህርያት አንድ ባህርይ ሆኖ በተዋሐደ ህላዌ በታቦር ተራራ ላይ ቆሞ ሳለ፣ አብ "ይህ የምወደው ልጄ ነው፤ እርሱ የሚላችሁን ስሙ" በማለቱ፣ ጌታችን በተዋሕዶ "የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ" መሆኑን አውቀናል፤ አምነናልም፤ ከዚህ አኳያ ስለክርስቶስ ማንነት የሚጠይቀን ካለ መልሳችንም፤ እምነታችንም ምሥጢረ ተዋሕዶ የተገለፀበት ይኸው የደብረ ታቦር ትምህርት ብቻ ነው ፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናን ወምእመናት፡-

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታቦር ተራራ ላይ የገለፀው የእግዚአብሔር የባህርይ ልጅነቱን ብቻ ሳይሆን ምሥጢረ መንግሥቱንም ጭምር ነው ፡፡

ነቢያትም፣ ጌታችንም፣ ሐዋርያትም፣ ብዙ የተናገሩላት፣ የእግዚአብሔር ልጆች የሆንን ምእመናንም በተስፋ የምንጠባበቃት የእግዚአብሔር መንግሥት፣ በመጨረሻ ጊዜ ተገልጻ ሁሉንም በቁጥጥሯ ሥር እንደምታደርግ ይታወቃል፤ (ራዕ. 21፡1-4) ፡፡

ስለሆነም የዚህ መንግሥት ገዥ ማን ነው? በዚህ መንግሥት ውስጥ የሚኖሩስ እነማን ናቸው? ይህ መንግሥት ሲገለጥ የሚሆነው ክሥተትስ ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ የደብረ ታቦር ክሥተት በሚገባ ገልጾታል ፡፡

የታቦር ተራራ ውብና አስደሳች ከመሆኑም ሌላ በጣም ከፍ ያለ ተራራ ነው፤ ቅዱስ ያሬድ የዚህን ተራራ ውበት ሲገልጽ "ሰላም ለከ ኦ ደብረ ታቦር ዘከለሎ ብርሃን ይሤኒ ላህዩ እምኩሉ አድባር፤ ከተራሮች ሁሉ ይልቅ ውበትህ ያማረ፣ ብርሃነ መለኮት የጋረደህ ደብረ ታቦር ሆይ ሰላምታ ላንተ ይገባል" ብሎአል ፡፡

በመሆኑም ይህ ውብ፣ ብርሃናዊና ከፍ ያለ ተራራ የመንግሥተ ሰማያት አምሳያ ነው፤ ወልደ እግዚአብሔር ክርስቶስ በግርማ መለኮት፣ በክበበ ትስብእት በዚህ ተራራ እንደተገለጸ ሁሉ፣ በመጨረሻ ጊዜ በምትገለጸዋ የእግዚአብሔር መንግሥትም ጌታችን በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት ተገልጾ ብርሃንዋና መሪዋ፣ ገዢዋም ሆኖ በመካከልዋ እንደሚኖር ምሥጢሩ ያሳያል ፡፡

በታቦር ተራራ ላይ ከዘመነ ብሉይ ነቢያት፣ ሙሴና ኤልያስ፣ ከዘመነ ሐዲስ ሐዋርያት፣ ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ቅዱስ ዮሐንስና ቅዱስ ያዕቆብ፣ ከሕያዋን ኤልያስና ዮሐንስ፣ ከሙታን ሙሴና ጴጥሮስ፣ ከደናግል ኤልያስና ዮሐንስ፣ ከሕጋውያን ሙሴና ጴጥሮስ፣ ተገኝተዋል፤ ይህም ከክርስቶስ በፊትና በኋላ የተነሡ ቅዱሳን፣ ሙታንና ሕያዋን፣ ደናግልና ሕጋውያን በአንድነትና በእኩልነት በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ በፍጹም ደስታ እንደሚኖሩ ምሥጢሩ ያመለክታል፤ (1ቆሮ 15፡52፣ 1ተሰ. 4፤15፡17) ፡፡

በመሆኑም ስለእግዚአብሔር መንግሥት ምንነት የሚጠይቀን ካለ የእግዚአብሔር መንግሥት ከሁሉም በላይ ከፍ ያለችና ውብ የሆነች፣ ዕፁብ ድንቅ በሆነ መለኮታዊ ብርሃን አሸብርቃ የምትኖር፤ ክርስቶስ በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት በቅዱሳኑ ላይ ነግሦባት የሚኖር፣ በዘመነ ብሉይም ሆነ በዘመነ ሐዲስ የተነሡ ቅዱሳን ሁሉ የሚገኙባት፣ ሙታንም ሆኑ ሕያዋን፣ ሕጋውያንም ሆኑ ደናግል፣ በአንድነትና በእኩልነት ከብረውና ደስ ተሰኝተው የሚኖሩባት፣ ዘላለማዊት መንግሥት እንደሆነች ከደብረ ታቦር በተማርነው ትምህርት መሠረት እንመልስለታለን፤ በዚህም አምነን እንኖራለን፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤

የእግዚአብሔር መንግሥት ለወደፊቱ በግልጽ የምትመጣበት ጊዜ እንዳለ ብናውቅም፣ ዛሬም ቢሆን በዓለሙ ሁሉ በገዥነት አለች፤ ይልቁኑም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዛሬም የእግዚአብሔርን ሕዝብ በመምራት ትገኛለች፤ የእግዚአብሔር ሕዝብ በዋናነት የሚተዳደረውና የሚመራው በእግዚአብሔር ሕገ መንግሥት ነው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብም የእግዚአብሔር ሕዝብ ስለመሆኑ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፤ ከሆነ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያና እግዚአብሔር የተለያዩበት ጊዜ ፈጽሞ የለም፤ ዛሬ ለዓለም ሕዝብ ምሥጢር ሆኖ የሚገኘው የሕዝባችን አንድነትና ነጻነት የእግዚአብሔር ሕዝብ ከመሆናችን የተገኘ እንጂ ሌላ እንዳይደለ አንዘንጋ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ከደብረ ታቦር አስተምህሮ የተወረሰ ነው፤ ደብረ ታቦር የብሉዩንና የሐዲሱን፤ ሕጋዊውንና ድንግሉን፣ ፈጣሪንና ፍጡራንን፣ ሕያዉንና ምውቱን በአንድነት በእግዚአብሔር መንግሥት ክልል ውስጥ ያገናኘ የእግዚአብሔር መንግሥት አምሳያ ነው፤ ኢትዮጵያ ሀገራችን ይህንን ትምህርት ተቀብላና እንደ ደብረ ታቦር የእግዚአብሔር መንግሥት ተምሳሌት ሆና፣ የተለያየ ቋንቋና ባህል ያላቸውን ልጆቿን ሁሉ በፍቅር፣ በአንድነት፣ በክብር፣ በስምምነትና በወንድማማችነት አስማምታና አቅፋ ለዝንተ ዓለም የነበረች ቅድስት ሀገር ናት፤ ይህ ለማንም ሆነ ለማን ያልተሰጠ ልዩ ጸጋና በረከት ለኢትዮጵያውያን በምልአት የተሰጠ በመሆኑ ልናከብረውና ልንጠብቀው ይገባል፤ በዚህም እጅግ ደስ ሊለንና ለዚህ የመረጠንን እግዚአብሔርን ዘወትር ልናመሰግን ይገባል፡፡

ዛሬም እንደትናንቱ በወንድማማችነት፣ በፍቅር፣ በስምምነት፣ በእኩልነት በመዋደድ፣ በመከባበር፣ በመተማመን የተመሠረተ አንድነትን፣ ነጻነትንና ሃይማኖትን ጠብቆ መኖር ለኢትዮጵያውን ከማንኛውም በላይ የሆነ ክብርና ጸጋ ነው፤ የቀደሙት ኢትዮጵያውን አበው ለዝንተ ዓለም የገነቡት ይህ ጠንካራና ጽኑ ግንብ በተራ ምክንያት እንዳይፈርስ በሚገባ መጠበቅ አለብን ፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነትና የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖት ለድርድር የሚቀርቡ አይደሉም፤ ባሉበት ብቻ ተጠብቀው መኖር አለባቸው፤ ሕዝቡም ይህንን መጠበቅ አለበት፤ የደብረ ታቦር አስተምህሮ ይኸው ነውና ፡፡
"ጸጋ ዘአብ ሂሩት ዘወልድ ሱታፌ ዘመንፈስ ቅዱስ የሀሉ ምስሌየ ወምስለ ኵልክሙ" ‹የአብ ጸጋ፣ የወልድ ቸርነት፣ የመንፈስ ቅዱስ አንድነት፤ ይህን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቴሌቪዥን ትምህርተ ወንጌል ከምትከታተሉ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ካላችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ሁለ ጋር ለዘለዓለም ጸንቶ ይኑር ፡፡

 

እግዚአብሔር ይባርካችሁ ይቀድሳችሁ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤
አሜን!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ነሐሴ 13 ቀን 2008 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

የፎንት ልክ መቀየሪያ