Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

ገዳማትና ገዳማውያን

መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል ፈለቀ

የቅርስ ጥበቃና ምዝገባ የቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ ኃላፊ

ሀገራችን ኢትዮጵያ በማንኛውም የሰው ልጅ የሥልጣኔ ታሪክ በእምነትም ሆነ በሥነ ጥበብ በየትኛዉ ዘመን በዐለም ላይ ገነው ከወጡ ታሪኮች ጋር አብራ የምትጠራ ጥንታዊት ሀገር ናት፡፡ የተጻፈ ሕግና የተደራጀ የእምነት ተቋም ባልነበረበት ዘመን በሕግ ልቡና ከዚያም በሕገ ኦሪት አንድ አምላክን በይፋ ስታመልክ የነበረች ለመሆንዋም ብዙ ምስክሮች አሉ፡፡ በሐዲስ ኪዳንም የክርስቶስን መንግሥት የምስራች /ወንጌል/ ከኢየሩሳሌም ቀጥሎ በመስማት ቀዳሚ ሀገር ኢትዮጵያ ናት፡፡ በሐዲስ ኪዳን ከተፈጸሙት አበይት ክንዋኔዎች በሐዋርያት የኑሮ ዘይቤ ላይ የተመሠረተው ሥርዓተ ብሕትውና አርዓያ የወጠነው ሥርዓተ ምንኵስና አንዱ ነው፡፡ በአፍሪካ በረሃ ውስጥ በአባ እንጦንስ የተጀመረው ሥርዐተ ብሕትውና ሐዋርያዊ ትውፊቱን ሳይለቅ የመንፈሳዊ ቅድስና ትውልድ ሐረጉ ሳይበጠስ ፀንቶ የቆየው በኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡

የምንኩስና አመጣጥ በሀገራችን የመጀመሪያው መነኵስ ጳጳስ ከሆኑት ከአባ ፍሬምናጦስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ጋር ሊገናኝ ቢችልም የገዳማት ታሪክም ከርዕሰ አድባራት ወገዳማት ቅድስት አክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን የሚጀምር ቢሆንም ምንኵስና በጣም የተስፋፋውና ገዳማትም በሰፊው የተቋቋሙት ከ፱ቱ ቅዱሳን በኋላ ነው፡፡ በዚሁ መሠረትነትም ከዚያ በኋላ የተነሱት ኢትዮጵያዊያን ሊቃውንት ገዳማዊ ሕይወት በሕዝቡ ውስጥ ሰርጾ እንዲገባና ለሀገር በረከት አንዲሆን አድርገዋል፡፡ በዘመነ አክሱም ከ5ኛዉ ክፍል ዘመን ማብቂያና ከ6ኛዉ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ጀምሮ ገዳማት ጥንታዊ ሥልጣኔ አንዳይጠፋ የሐዋርያት መሠረት ላይ የቆመችው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ክርስትና እንዳትዳክም፤ የክርስትና ጥልቅ መንፈሳዊ ሕይወት መመሪያ በሕዝቡ ማኅበራዊና ቤተሰባዊ ሕይወት ውስጥ መሪ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ መነኰሳት አበው ራሳቸውን ለክርስቶስ ትምህርት ወንጌል አስገዝተው ሕዝቡን በቃልና በምግባር አርዓያ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በአሳለፉአቸዋው ዘመንም የአራዊትን ድምጽ ታግሰው፣ የሌሊት ብርድ ቁርን የቀን ጸሐይ ሐሩርን ተቋቁመው፣ ዋሻ በራሳቸው እጅ ምሰው፣ ጤዛ ለብሰው፣ ዳዋ ተንተርሰው፣ የባዕድ ወራሪን፣ መክተው ገዳማታቸውን የትምህርት፣ የሥነ ጥበብ፣ የበጎ ምግባር ኮሌጆች በማድረግ አኩሪ ታሪክን ሠርተዋል፡፡ ብራና ፍቀውና ረመው፣ ቀለም በጥብጠውና አቅልመው፣ ብርዕ ቀርጸው መጽሐፍ ደጉሰው ታሪክንና ዕውቀትን፣ ትርጉምንና ድርሳንን በጽሑፍ በሥዕል በዜማ አቆይተዋል፣ ሰው በተፈጥሮው ተጋብቶ ትዳር መሥርቶ ወንድም እህት ልጅ አፍርቶ ከሚኖረው ኑሮ ተለይተው በዘር፣ በቋንቋ፣ በመንደር፣ በቀለም፣ ሳይወሰኑ፣ ለዓለማዊ ሥልጣን ሳይጓጉ ሳይተዋወቁ ተዋደው ከአንድ እናት ሳይወለዱ ወንድማማች እህትአማች እህትና ወንድም ሆነው አባትና ልጅ ተባብለው ጠንካራ ማኀበራዊ የአንድነት ሥርዓትን በየገዳማቸው መሥርተዋል፡፡ በዚህ ሥራ ፍሬም ሀገራችን ኢትዮጵያም የዓለምን ቀደምት ሥልጣኔ የምትወዳደርባቸውን ሀብቶች በማፍራት በየዘመኑ የሚመጣው ትውልድ ሁሉ አንገቱን ሳይደፋ ቀጥ ብሎ የሚሔድበትን ታሪክ አቆይተዋል፡፡ በማኅበራዊ ኑሮም ገዳማት ባሉበት ቦታ ሁሉ ልጆች ተምረው፣ የተጣሉ ታርቀው፣ ዘር ያጡ ዘር አግኘተው በአባቶች በረከት ከብረው እንዲኖሩ አድርገዋል፡፡

ጥንታውያኑ ገዳማት ከፍተኛ የትምህርትና የምርምር ተቋማት ስለነበሩ የውጩ ዓለም ዕውቀት እንዳይቀርብን የክርስትና መጽሐፍትን ጨምሮ ወደ ግእዝ ቋንቋቸው በጥንቃቄ በመተርጎም ሀገራቸው የክርስቶስን ትምህርት በራሷ ቋንቋ እንድትሰማ አድርገዋል፡፡ በዚህም መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ ከተተረጐመባቸው ስምንት ቋንቋዎች የኢትዮጵያ ቋንቋ አንዱ ሊሆን በቅቷል፡፡ ሀገር በቀሉ የሥነ ሕንፃ፣ ሥነ ሥዕል፣ ሥነ ጽሕፈት፣ ሥነ ዜማ በመከተል አቢያተ ክርስቲያናትን፣ ድንቅ ሥዕላትን የዜማና የሥርዐት መጽሐፍትን በማዘጋጃ ጽኑ መሠረትን ጥለዋል፡፡ ከእነዚህ ሥራዎቹ ለአብነት ለመጥቀስ የቅዱስ ያሬድ የዜማ ሥራ፣ የአባ ጊዮርጊስ ድርሰቶች፣ የአባ ጽጌ ማኅሌት፣ የአባ ሳሙኤል ጸሎት ሁሉ የአበው ገዳማውያን ውጤት ነው፡፡

ከትምህርት ቤቶቹም ለመጥቀስ ከመጀመሪያው የምንኵስና ትምህርት ቤት ከአቡነ አረጋዊ ጀምሮ ብዙ ትምህርት ቤቶች ያደጉ ሲሆን፡፡ በዚህ ቦታ ከተሰዓቱ ቅዱሳን አንዱ የሆኑት አቡነ አረጋዊ ጥንታዊውን የክርስትና ሥርዓተ ገዳም፣ ከሥርዓተ ምንኵስና ጋር አብረው በማስተማራቸው ቦታው ለረጅም ዘመን የገዳማውያን አበው ከፍተኛው የምንኵስና ማዕረግ አስኬማ የሚሰጥብት መሆን በቅቷል፡፡

ከአቡነ አረጋዊ በተጨማሪ የአቡነ ጰንጠሌዎን ገዳምም በንጉሡ በአጼ ካሌብ ከተማ በአክሱም ስለነበር ጻድቁ አባታችን የንጉሡ መንፈሳዊ አባት ለመሆን በቅተው ነበር፡፡ በጻድቁ ጸሎትና ምክርም ንጉሡ በየመን ናግራን መከራ ይደርስባቸው የነበሩ ክርስቲያኖችን ነጻ አውጥቷል፡፡ ንጉሡ ከድል በኋላ ሀገሩን አረጋግቶ የመጨረሻ ሕይወቱን በቅድስና ለመኖር በመፈለጉ መንግሥቱን ለልጁ ለአጼ ገብረ መስቀል አስረክቦ በአቡነ ጰንጠሌዎን ገዳም በመግባት በምንኵስና ለመኖር በቅቷል፡፡ ይኽም የሚያሳየው ገዳማዊ ሕይወት በሀገራችን ምን ያሕል የተከበረ እንደሆነ ነው፡፡

ገዳማት የዕውቀት ምንጭም ናቸው፣ ሀገራችን የራስዋ የሆነ ሥነ ጽሑፍ፣ እንዲኖራት፣ ከክርስትና እምነት ጋር የክርስትናን ቅዱሳት መጻሕፍት በራሳችን ቋንቋ እንድናነብ ያደረጉትም በገዳማት የነበሩ ቅዱሳን ሊቃውንት አባቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ቋንቋ ግእዝ መጽሐፍ ቅዱስ ከተተረጎመባቸው ጥንታውያን ቋንቋዎች አንዱ ሊሆን በቅቷል፡፡ ለዚህም ምስክሩ በቅርቡ በመላው ዓለም ዜናው የተሰማው በአቡነ ገሪማ በግእዝ ቋንቋ የተጻፈው ወንጌል ነው፡፡ ይኽ ወንጌል የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎችን ጨምሮ በተደረገው ምርምር በአክሱም ዘመን ከአምስተኛው እስከ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን የተጻፈ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በዚህም የሀገራንን የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ቅድምና ከማረገጡ ባሻገር ገዳማትና ገዳማውያን አባቶች ያበረከቱትን አስተዎጽኦ ለማስረዳት ችሏል፡፡

ለአብነት ያኽል የተወሰኑ ጉዳዮችን አነሳን እንጅ አሁነም በጥልቀት እያጠናን ስለ የመጀመሪያዎ የእግዚአብሔር ኬዳን ምስክር የሆነችው ጽላተ ሙሴ ተጠብቃ ከምትኖርባት ከርዕሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ጀምረን፣ ስለ ጥንታዊው የየሐ ሕንጻ፣ ስለ ምእራፈ ቅዱሳን የባሕታውያን መናሐሪያ ዋልድባ፣ ስለ ገረኣልታ ዋሻዎች፣ በሐዲስ ኪዳን ቅዱስ ሥጋው ቆርሶ ክቡር ደሙን አፍሶ ሰውን ያዳነበት መስቀሉ የተቀመጠባት ስለ ደብረ ከርቤ ግሸን ማርያም፣ ስለ ቅዱስ ላሊበላ ውቅር ገዳማትና ስለ ጥንታዊው ዩኒቨርስቲ ደብረ ሐይቅ፣ የጣና ሐይቅ ከዋክብት ስለሚባሉት የጣና ገዳማት፣ ከብዙ ጥፋት ተርፈው አሁንም ጥንታዊነታቸውን ስለሚመሰክሩት ስለ ብርብር ማርያም፣ ስለ ምድረ ከብድ፣ ስለ ዝቋላ፣ ስለ ደብረ ሊባኖስ፣ በሰሜን በደቡብ በምዕራብ በምስራቅ ስላሉት ገዳማት ሁሉ ብንናገር ምን ያኽል ጊዜ ይበቃናል፡፡

ስለ ገዳማት ታሪክ ይኽን ያህል ካልን የገዳማውያን መነኰሳት ሥርዓት፣ የመካነ ምኔታቸው ወይም የገዳምን ምንነት፣ በመጠኑ እንዳስ፡፡ ምንኩስና ማለት ብቸኝነት፣ ምነናም፡- ኃላፊ ጠፊ የሆነውን ዓለም መናቅ ማለት ነው፡፡ የዚህን ዓይነት ሕይወት ከብሉይ ኪዳን ነቢይት እንደ ኤልያስ፣ ዳንኤል፣ የመሳሰሉት ኑረውታል፡፡ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስም በዚሁ ሕይወት የሚመራ ጻድቅ ነበር፡፡ በክርስትና የብሕትውናን ወይም የምነናን ሕይወት ባርኮ የመሠረተው ጌታችን ሲሆን ሐዋርያት ተከትለውታል፡፡

አባቶች መነኰሳትን ሰማያውያን ሰዎች ምድራዉያን መላእክት ተብለው እንዲጠሩ ያደረጋቸው ምክንያት ብዙ ቢሆንም ከቤተ አይሁድ ክፍል አንድ ቡድን የነበሩት ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ጌታችንን ሰዎች ከትንሣኤ ሙታን በኋላ በመንግሥተ ሰማያት ስለሚኖራቸው የጋብቻ ሕይወት ሲጠይቁት "እነርሱ ግን ከትንሣኤ በኋላ አያገቡም አይጋቡም እንደ እግዚአብሔር መላእክት ይሆናሉ እንጂ" (ማቴ፤ 12፡ 19") ብሎ መለሰላቸው ስለዚህ መነኰሳት የዚህን ዓለም ኃላፊ ምኞት ንቀው ከጋብቻ ተከልክለው ለመንግሥተ ሰማያት ሲሉ ራቸውን ጃንደረባ አድርገው አንደ መላእክት የሚኖሩ ስለሆነ ምድራያን መላእክት ተባሉ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በአኗኗቸው ከዚህ ዓለም ግብርና ሥራ አምሮት ርቀው ለጸሎትና ለምስጋና ተግተው የሚኖሩ እንደ ሰው በምድር፤ የበጎ ምግባር ትእዛዝን ፈጽመው ትሩፋትን ወይም ከምግባር ብዙ ትርፍ የሚያስገኘን መልካም ሥራ በመሥራት እግዚአብሔርን ለማስደሰት የሚተጉ ስለሆነ እንደ መላእክት ሀብት ንብረት ሳይኖራችው ሌሊት ከቀን እግዚአብሔርን ብቻ እያሰቡ የሚኖሩ በመሆናቸውም ምድራውያን መላእክት ተብለዋል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ መከኰሳትን ሰማያውያን የሚያሰኛቸው የሚከተሉት ሕይወት የፍጹምነት፣ የጥበብ፣ ሥጋንና የሥጋን ሕይወት በመንፈሳዊ ሕይወት የዓለምን ባሕር አሸንፈው ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት ያሻገሩ፣ ከዚህ ዓለም ሠርግና ለማድ ርቀው ከፊታቸው ሊመጣ ያለውን ሥጋዊ ሞት ቀድመው በመሞት ዘለዓለማዊ ሕይወትን በዚሁ ዓለም የወጠኑ በሕይወታቸው አግዚአብሔርን ያመሰገኑ ክብሩን የገለጹ የሰማያዊ መንግሥት ሠርገኞች ማለት ናቸው፡፡ ሌላም ብዙ ማለት ይቻላል መነኰሳት የሐዋርያት ምሳሌ፣ በመንኖተ ዓለም፡ ከዓለም ፍጥረት በመለየት ፈቃድ ሥጋን በመተው እስከ ሰውነታቸው ድረስ ሥራውን ሁሉ በመናቅ ስለ ትእዛዙ ስለ ፍቅሩ ፈቃዱን ለመፈጸም ያዘዛቸውን ትእዛዝ ስለሚያደርጉ እርሱንም ብቻ ከአባቶች ከልጆች ከሚስት ከገንዘብ ይልቅ ፈጽሞ ስለሚወዱ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሚፈጽ እንደ መላእክት ተመሰሉ፡፡ ምንኵስናም የብፅዕና መንገድ ነው፡ ዛሬ በፈቃዳቸው ከሚሰሯት ድካም ዕረፍት ስለማድረግ ከኋለኛውም ዓለም ፍርድ ፈጽሞ ስለመዳን ተዘጋጁ ስለሆነ ብፁዓን ናቸው፡፡ በትክክል መነኰሳት የምንላቸው በዚህ ምድር ምንም ቁሳዊ ሀብትን ሳያካብቱ፣ የገንዘብና የንብረት መዝገብ ሳይኖራቸው፣ ቤት ንብረት ርስት ጉልት ሳይዙ፣ መዝገባቸው፣ ርስታቸው፣ ጉልታቸው፣ መንግሥተ ሰማያት የሆነች፣ በገዳማዊ አንድነት ተወስነው፣ በመሐላ ቃልኪዳን ከሚኖሩባት መኖሪያቸው፣ በፍቅር ከታሠሩባት ማኅበራቸው (ማኅበረ መነኰሳት) የታመኑ ናቸው፡፡ የክርስቶስ መግነዝ ምሳሌ ከሆነችው ከተገነዙባት መግነዝ፣ የክርስቶስ የሾህ አክሊል ምሳሌ ከሆነችው ከደፏት የክብር ቆብ፣ የወንጌል ምሳሌ ከሆነችው ከታጠቋት የንጽሕና ቅናት፣ የለበሷትን የማዕረግ ቀሚስ አክብረው፣ ሳይሸሹ የዓለም ጌጥ ሳይረታቸው፣ ማዓቸው መዐዛ ዕጣን፣ መዓዛ ምግባር፣ ጌጣቸው ትሩፋትና ሃይማኖት፣ አክሊላቸው የጽድቅ አክሊል የሆነ ጌታችንን መድኀኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን መስለው ክርስቶስን መምሰልን አስተምረው የክብር ባለቤቶች የሆኑትን ነው፡፡ ከዚህ የበለጠ ክርስቶስን መምሰል የለምና የአበው መነኰሳት መኖር ለእኛ ክርስቶስን የመምሰል መንገድ ብርሃን ማግኘት ነው፡፡

በምንኵስና ዋና ዋናዎቹ ትዕዞች አንዱ መንኖ ጥሪት ነው፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ አለ፡፡ "ፍጹም ትሆን ዘንድ ትወዳለህ" ያለህን ሁሉ ሂደት ሸጠህ ለነዳያንም መጽውተህ ና ተከተለኝ የዘለዓለም ሕይወትን (ማቴ. 09፡!1-!2) ከኔ ይልቅ አባቱንና እናቱን የወደደ ለእኔ ሊሆን አይገባም ከእኔ ይልቅ ወንድ ልጁንና ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባም የሞቱን መስቀል ተሸክሞ ያተከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባም፡፡" (ማቴ 0፡"6-"8)፡፡ ከማኅበር ተለይቶ ንብረት ማካበት ወይም መደበቅ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ለሐናንያ እንዳለው መንፈስ ቅዱስን ማታለል ነው፡፡ የመነኰሳት ማኅበርና ቤተ ሰብእ የመንፈስ ቅዱስ ማኅበር ነውና፣ ሐዋርያው ቤቱን በአግባቡ ሊመራ ያልቻለ ቤተ ክርስቲያንን ሊመራ አይችልም እንዳለ ዛሬም አባቶች በገዳም ከትንሹ ረድነት አገልግሎት ጀምረው እስከ አበ ምኔትነት ድረስ ቤተ ሰባቸው ሆነች ማኅበረ መነኰሳትን ከመሩ ቤተ ክርስቲያንን የምእመናን አንድነት በአግባቡ ይመራሉ፡፡1ኛ ጢሞ 3፡5፡፡ ገዳማውያን በገዳም ንብረታቸው በአንድ ነው፣ ጸሎታቸው በአንድ ነው፣ ማዕዳቸው በአንድ ነው፣ ለአንዱ የሆነው የሁሉም ነው፡፡

በገዳም ብዙ አባቶች ቢኖሩም ሥራ ክፍፍልና፣ በፍቅር ሥርዓት፣ የአንድነት ተግባሮች አሉ፣ ከታላላቆቹ መምህራንና ሊቃውንት ጀምሮ፣ የጉልበት ሥራ፣ የምክር ሥራ፣ የአስተዳደር ሥራ፣ የስብከተ ወንጌል ሥራ፣ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ፣ የጤናና የልዩ ልዩ ሥራ ዘርፎች ሁሉ በአግባቡ ተከፋፍለው የሚከናወኑበት ተቋም ገዳም ነው፡፡ ገዳማት ከበጉ አበባ መዓዛን ቀስመው ማር የሚሠሩ ንቦች ማር ለመሥራት እንዳላቸው ትጋት ለመንፈሳዊ ፍሬ የሚተጉ መነኰሳት የሚኖሩባቸው የመንፈሳዊ ማር ቀፎዎች፣ እንደ መላእክት ከምስጋና የማያርፉ አበው የሚኖሩባቸው ሰማዮች ናቸው፡፡

በዘሁኑ ጊዜ የሀገራችን የገዳማትና ገዳማውያን ሕልውና ከዘመን ዘመን ተሻግሮ ባሕር አቋርጦ በቦታ ሰፍቶ የሚገኘበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያውያን ባሉበት ቦታ ሁሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አለች፡፡ ከምዕራባዊው የሰሜን አሜሪካ ጥግ የባሕር ዳርቻ እስከ ኒውዚላንድ ድረስ በሁሉም አህጉሮች የካሪቢያንን ደሴቶች ጨምሮ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትገኛለች፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰሜን አሜሪካ ሦስት አህጉረ ስብከት ሲኖራት እጅግ በርካት አብያተ ክርስቲያናት ተመሥርተዋል፣ በደቡብ አሜሪካ በካሪቢያን አንድ ሀገረ ስብከት ሲኖራት በጃማይካ፣ በትሪኒዳድ ቶቤጎ እና አካባቢው ሁሉ አብያተ ክርስቲያናት አሏት፣ በአውሮፓ ከሁለት በላይ አህጉረ ስብከት ሲኖሯት በአህዛኛዎቹ የምዕራብና ምስራቅ አውሮፓ ሀገሮች ሰፍታ ትገኛለች፣ በእስያ እና በመካከለኛው ምስራቅም እንዲሁ በቤሩት፣ በዱባይ፣ በዮርዳኖስ፣ በኢየሩሳሌም ሰፊ ይዞታ አላት፣ ከኢትዮጵያ ውጭ ባለው የአፍሪካ አህጉርም በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ፡፡ በገዳም ደረጃ ግን እስከ ዛሬ የምንሰማውና የምናውቀው የኢየሩሳሌም ገዳማትን ብቻ ነበር፡፡

የኢየሩሳሌም ገዳማት የመሬት ይዞታ ታሪክም ከንግሥት ሳባ ጊዜ ጀምሮ የሚታወቅ ሲሆን በክርስትና በገዳማው ሕልውናው እጅግ ጥንታዊ ነው፡፡ ለምሳሌ የምዕራባውያን ታሪክ ጸሐፊና መነኵሴ የነበረው ግሪካዊው ጀሮም በአምስተኛው ክፍለ ዘመን በላቲን በጻፈው ጽሑፍ በየቀኑ ኢትዮጵያውያን መነኰሳት በኢየሩሳሌም ይታዩ እንደነበር ተናግሯል፡፡ ስለዚህ የኢየሩሳሌም ታሪክ እጅግ ጥንታዊ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ይኽንኑ ታሪክ ለመጠበቅም ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ለኢየሩሳሌም ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በቅዱስነታቸው ዘመነ ፕትርክና ተጨማሪ የማጠናከሪያ ሥራዎች ተጨማሪ ግንባታዎችና እድሳቶች ተከናውነዋል፡፡

አሁን ደግሞ ሌላ ልዩ የሆነ ታሪክ በደቡብ አፍሪካ ተከናውኗል፡፡ ከኢየሩሳሌም ቀጥሎ የመጀመሪያው ታላቅ ገዳምና ከሀገራችን ውጭ የመጀመሪያው የቤተ ክርስቲያን የካህናት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ተመሥርቷል፡፡ በእግዚአብሔር ፈቃድ፣ በቅዱሳኑ ቃልኪዳን፣ በብፁዕ ወቅዱስ አባታችን አባታዊ አመራርና ፈቃድ በኢትዮጵያውን ቅን ጥረት የተመሠረተውን የብሎምፎንቴን መንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ አንድነት ገዳም የቅዱስ ያሬድ ካህናት ማሰልጠኛ ሁኔታ እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ይቀጥላል

ዳንኤል ሰይፈሚካኤል ፈለቀ (መ/ር)

የቅርስ ጥበቃና ምዝገባ የቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ ኃላፊ

አዲስ አበባ ፡ 2004

የፎንት ልክ መቀየሪያ