Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

"የመንፈሳዊ ትምህርት ቤቶችና የገዳማት የወደፊት ዕጣ"

ከንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ
የመንፈሳዊ ዘርፍ ጉዳዮች ም/ሥራ አስኪያጅ
ከየካቲት 21 እሰከ 22 ቀን 2006 ዓ.ም በመ/ፓ/ጠ/ጽ/ቤት
ለተዘጋጀው የምክክር ስበሰባ የተዘጋጀ

መግቢያ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የኢትዮጵያን ሕዝብ በሃይማኖትና በፈሪሃ እግዚአብሔር ከማነጽ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ታሪክ ባህልና ሥነ ጥበብ በመሳሰሉት ጠቃሚ ነገሮች መተኪያ የማይገኝለት ጉልህና ደማቅ ሥራ እንደሠራች ይታወቃል፤

ቤተ ክርስቲያናችን በረጅሙ ታሪካዊ ጉዞዋ በኅበረተ ሰቡ መካከል መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ሥነ ጥበባዊ ተግባራትን በማሥረጽ እንደዚሁም የተቀደሰ ባህል በመፍጠር ሕዝቡ ጥሩ የሆነ ሰብእና እንዲኖረው አድርጋለች፤

ቤተ ክርስቲያናችን በሀገሪቱ ላይ ከውጭ ኃይሎች የሚሰነዘርባትን ማንኛውንም ጥቃት በመመከት፣ የሀገሪቱ ሉዓላዊነት፣ ነጻነትና አንድነት እንዲከበር ሕዝቡንና መንግሥታቱን በማስተማርና በመምከር፣ አስፈላጊ በሆነ ጊዜም በግንባር ተገኝታ መሥዋዕትነትን በመክፈል የሚጠበቅባትን ሁሉ አድርጋለች፤

በሀገሪቱ ላይ በአሁኑ ጊዜ የሚታወቁ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ እሴቶች ሁሉ ዋና ምንጫቸው የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ገዳማትና በውስጣቸው የሚገኙ መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች ውጤቶች ናቸው፤

ስለሆነም ዛሬ የሦስት ሺሕ ዓመታት ታሪክና ቅርስ ያላት ሀገር እንድትኖረን፣ በሃይማኖትና በመልካም ሥነ ምግባር የተገነባ ማኅበረ ሰብ እንዲኖረን፣ ያስቻሉን ገዳማትና የመንፈሳዊ ት/ቤቶች መሆናቸው አይካድም

ዛሬም ቢሆን የኢትዮጵያ ሃይማኖት፣ ታሪክና ማንነት ተጠብቀው የሚገኙት በገዳማት ውስጥ ነው፤ ይህ ታላቅ ሀብት እንዳለ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ገዳማቱ ያላቸው ሚና ከሁሉም የላቀ ነውና እነርሱን በተመለከተ በዚህ ጽሑፍ ለውይይት የሚሆን መንደርደሪያ ሐሳብ ቀርቦአል፤

1. ትርጓሜ

ገዳም ማለት ምን ማለት ነው?

ገዳም ማለት ዱር፣ ጫካ፣ በረሀ፣ ምድረ በዳ፣ ከሀገር ከመንደር የራቀና የተከለከለ፣ ልዩ የመነኮሳት ሰፈር፣ በደለኛ ሸሽቶ የሚጠጋበት ደውሎ የሚማጠንበት ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ያለበት ስፍራ ማለት ነው፡፡

የገዳም አመሠራረት

ገዳማዊ ሕይወት ከዘመነ ብሉይ ጀምሮ የነበረ እንደሆነ የሚከተሉትን አበው በመጥቀስ መረዳት እንችላለን፡፡

1. መልከ ጼዴቅ
እንደ ቅዱስ መጽሐፍ አገላለጽ ገዳማዊ ሕይወትን ለመጀመሪያ ጊዜ የመሠረተ የልዑል እግዚአብሔር ካህን የነበረው መልከ ጼዴቅ ነው፤ አባት እናት፣ ወንድም እኅት፣ ሚስት ልጅ እንደነበሩት ያልተጠቀሰለት መልከ ጼዴቅ፣ የመናንያንና የባህታውያን ገዳማዊ ሕይወት መሥራች ነው፤ መልከ ጼዴቅ ጠጉሩና ጥፍሩ ተላጭቶና ተቆርጦ የማያውቅ፣ በገዳመ ሳሌም ወይም እንደ ቅዱስ ጎርጎርዮስ አባባል በደብረ ታቦር እግዚአብሔርን በማገልገል ብቻ መላ ዘመኑን ያሳለፈ ነው (ዘፍ.14÷18-20)

2. ነቢዩ ኤልያስ
በ7ኛው ዓመተ ዓለም ከልደተ ክርስቶስ በፊት የእሥራኤል ስመጥር ነቢይ የነበረው ኤልያስ፣ በድንግልናዊ ሕይወት፣ በንጽሕና እና በቅድስና ያጌጠ፣ መላ ዘመኑ እግዚአብሔርን በማገልገል ያሳለፈ፣ አምልኮተ ጣዖት ከተጠናወታቸው ነገሥታተ እሥራኤልና ከነቢያተ ሐሰት ጋር ስለ እግዚአብሔር አምልኮ ሲጋፈጥ የነበረ፣ ብዙ አስደናቂ ተአምራትን ያደረገ፣ ገዳማዊ ሕይወትን በገዳመ ቀርሜሎስ የፈጸመ ሁለተኛው የዘመነ ብሉይ ገዳማዊ ነቢይ ነው፤(ነገ.ቀዳ 17÷1-24፤ 18÷1-36፤ 19÷1-21)

3. ቅዱስ ዮሐንስ
በዘመነ ብሉይና በዘመነ ሐዲስ መካከል የነበረው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ፣ እንደ ኤልያስ በንጽሕና እና በቅድስና ያጌጠ፣ በድንግልና ሕይወት የኖረ፣ ወገቡ በጠፍር የታጠቀ፣ ምግቡ የበረሃ ማርና አንበጣ ብቻ የነበረ፣ ልብሱም ከግመል ጠጉር የተሠራ ሆኖ በገዳመ ዮርዳኖስ በብሕትውና ይኖር የነበረ የገዳማዊ ሕይወት ተጠቃሽ ገዳማዊ ነው፤(ማቴ.3÷1-10)

4. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ

ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ገዳማዊ ሕይወትን ለገዳማውያን ባርኮ ለመስጠት፣ በገዳመ ቆሮንቶስ ከምግብና ከመጠጥ ተለይቶ ዓርባ ቀንና ዓርባ ሌሊት በመጾም ሰይጣንን ድል በማድረጉ፣ ገዳማዊ ሕይወት ዲያብሎስ የሚሸነፍበት የመንፈሳዊ ጦር ሜዳ መሆኑን በተግባር ከመግለጽ ጋር ገዳማዊ ሕይወትን ባርኮ ሰጥቶአል፤(ማቴ. 4÷1-11 )

5. ቅዱስ እንጦንስ

በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሣው ታላቁ አባት ቅዱስ እንጦንስ፣ በክርስትናው ዓለም ለተስፋፋው ገዳማዊ ሕይወት የመጀመሪያው ተጠቃሽ አባት ነው፤ ቅዱስ እንጦንስ የቀደምት ገዳማውያንን፣ የጌታችን አብነትና ትምህርትን፣ የቅዱስ ጳውሎስና የቅዱስ ዮሐንስ ድንግልናዊ ሕይወትን በመከተል እንደዚሁም ምናኔ ለስብከተ ወንጌልና ለእግዚአብሔር አገልግሎት ያለው ምቹነት በሚገባ በመረዳት ምንኩስናን፣ ብሕትውናን፣ ምናኔን፣ ድንግልናዊ ሕይወትና ገዳማዊ ሥርዓተ ማኅበርን በገዳመ አስቄጥስ መሥርቶአል፤

ከእርሱ በኋላም ተከታዮቹ አበው እነ አቡነ መቃርስ፣ አነ አባ ጳውሊ፣ እነ አባ ቴዎድሮስ፣ እነ አባ ጳኩሚስ ገዳማዊ ሕይወትን በግብፅ አገር በከፍተኛ ደረጃ አስፋፍተዋል፤

ከዚህ በኋላ ገዳማዊ ሕይወት ለሃይማኖትና ለቀኖና ቤተ ክርስቲያን መጠበቅ፣ ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት፣ ምሁራንን ለማፍራት እጅግ ጠቃሚ መሆኑ ስለታመነበት ገዳማዊ ሥርዓተ ማኅበር በዓለም አቀፍ በከፍተኛ ደረጃ ተስፋፋ፤

ገዳማት በኢትዮጵያ

ሥርዓተ ገዳም ወደ ኢትዮጵያ የገባው በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ ወደ ኢትዮጵያ በመጡ በተስዓቱ ቅዱሳን አማካኝነት ነው፤

ተስዓቱ ቅዱሳን በአክሱም ከተማ የነበራቸው ቆይታ የሀገሪቱን ቋንቋ በሚገባ ለማወቅ፣ እንደዚሁም ከነገሥታቱና ከሕዝቡ ለመተዋወቅና ተቀባይነትን ለማግኘት ምቹ ዕድል ፈጥሮላቸዋል፤

ተስዓቱ ቅዱሳን በኢትዮጰያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ፣ በሊቃውንቱ፣ በነገሥታቱና በሕዝቡ ዘንድ ከፍ ያለ ተቀባይነትና ታዋቂነትን ካገኙ በኋላ፣ ትምህርተ ሃይማኖትንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ለማስፋፋት፣ ምሁራንን ለማፍራት፣ ሥርዓተ ምንኩስናን ለማደራጀት የሚያስችሉ ገዳማትን ለመሥራት ከአክሱም ወጣ ብለው በሚገኙ ስፍራዎች ገዳማትን መሠረቱ፤

ተስዓቱ ቅዱሳን ሁሉም በመረጡአቸው ቦታዎች የየራሳቸው ገዳም መሥርተው ገዳማዊ ሕይወትን ያስፋፉ ቢሆኑም በአቡነ አረጋዊ አማካኝነት የተመሠረተው የደብረ ዳሞ ገዳም ለገዳማዊ ሕይወት ካለው ምቹነት የተነሣ ከሌሎቹ ገዳማት በበለጠ የተስፋፋና የተደራጀ ነበር፣ ገዳሙ ለመንፈሳዊ አገልግሎት፣ ለጸሎትና ለጽማዌ እጅግ በጣም የተመቸ በመሆኑ ነገሥታቱ ሳይቀሩ ‹‹አክሱምኒ ቤተ መንግሥትነ ወዳሞሂ ቤተ ጸሎትነ›› በማለት ወደ ገዳሙ እየሄዱ ይጸልዩ ነበረ፤

ከዚህ ዘመን ጀምሮ ሥርዓተ ገዳም በኢትዮጵያ እየተስፋፋ ሄደ፤ ገዳማቱ በዋናነት የምናኔና የትምህርት ማእከል ሆነው ያገለግሉ ስለነበረ የሊቃውንት መፈጠሪያ፣ የሥነ ጥበብ ማስፋፊያ፣ የቅድስና ሕይወት ማጽኛ፣ የትምህርተ ሃይማኖትና የሥርዓ ቤተ ክርስቲያን መጠበቂያ ነበሩ፣

ገዳማት ባሉበት አካባቢ ሁሉ የሃይማኖት ችግርና የሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መፋለስ አያጋጥምም ነበር፣ ለዚህ ተጠቃሽ ሊሆኑ ከሚችሉ ቀደምት ገዳማት እነ ደብረ ዳሞ፣ዋልድባ፣ ዙር አባ አቡነ አረጋዊ፣ ሐይቅ እስጢፋኖስ፣ደብረ ሊባኖስ፣ ዝቋላ አቦ፣ የጣና ሐይቅ ገዳማት ተጠቃሽ ናቸው፤

የገዳማት መሠረታዊ ዓላማ

ገዳማት ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግባራቸውን ለማከናወን የሚከተሉት ዓላማዎች አሉአቸው፤ ይኸውም፡-

ሀ. ከዓለም ርቆ፣ ንጽሕን ጠብቆ፣ ጨርቄን ማቄን፣አባቴን እናቴን፣ ሚስቴን ልጄን፣ ሀብቴን ርስቴን፣ ወንድሜን እህቴን ሳይሉ፣ ሁሉንም እርግፍ አድርጎ በመተውና በመናቅ፣ እግዚአብሔርን በአንድ ልብ ማገልገል
ለ. በየገዳማቱ መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶችን በማቋቋም ትምህርተ ሃይማኖትንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ማስተማር፣ ማስፋፋትና መጠበቅ
ሐ. ጾምን፣ ትሕርምትን፣ ንጽሕናን፣ ቅድስናንና ምናኔን በመጠበቅ በየጊዜው ለጸሎት መትጋት
መ. ማኅበራዊ ኑሮን በመከተል ችግረኞችን መርዳትና ያለውን ሁሉ በኅብረትና በአንድነት መጠቀም
ሠ. ጥበበ እድን በማስፋፋት ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውሉ ንዋየ ቅድሳትን ማምረትና ለአብያተ ክርስቲያናት ማከፋፈል
ረ. በቡድንና በተናጠል በመዝመትና ሐዋርያዊ ተልእኮን በማካሄድ ያላመኑትን ማሳመን ያልተጠመቁትን ማጥመቅ
ሰ. ተግባረ እድን በማጠናከር በእርሻ ሥራ፣ በንብ ርባታ፣ በልዩ ልዩ የአትክልትና የፍራፍሬ ምርትና በእንስሳት ርባታ ተሠማርቶ ራስን መርዳት
ሸ. በማንኛውም ረገድ በመንፈሳዊ ሕይወትም ሆነ በሥጋዊ ጥበብ ለሕዝቡ መልካም የሥነ ምግባር አርአያና ምሳሌ ሆኖ መገኘት የገዳማት መሠረታዊና ዋና ዋና ዓላማዎች ናቸው፡፡

ገዳማት ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና ለኢትዮጵያ ያበረከቱት አስተዋጽኦ

ገዳማት ከተቋቋሙለት ዓላማ የተነሣ የሚያከናውኑአቸው ሥራዎች መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተብለው በሦት ሊከፈሉ ይችላሉ፤

1. በመንፈሳዊ ሕይወት ረገድ የገዳማት አስተዋጽኦ፡-

ሀ. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት፣ በውስጣቸው በሚገኙ መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች አማካኝነት ትምህርተ ሃይማኖትና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ጠብቀው፣ መልካም ሥነ ምግባርና አኩሪ ባህልን አስጠብቀው ለትውልደ ትውልድ አስረክበዋል፤
ለ. ገዳማት በነበሩአቸው መንፈሳዊ ት/ቤቶች ውስጥከነገሥታቱ ልጆች ጀምሮ የሕዝቡን ልጆች በፈሪሃ እግዚአብሔር፣ በሥነ ምግባርና በዕውቀት ኰትኩተው በማሳዳግ፣ በማስተማርና በማሠልጠን፣ የሀገር መሪዎችና የሃይማኖት መሪዎችን ሲያስገኙ ኖረዋል፤
ሐ. አብያተ ክርስቲያናት አገልጋይ ካህናትን በማጣት እንዳይዘጉና ሕዝበ ክርስቲያኑ መንፈሳዊ አገልግሎትን አጥቶ ከሃይማኖቱ እንዳይናወጥ በመንፈሳዊ ት/ቤቶች ውስጥ ሊቃውንትን፣ መምህራንን፣ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን በማስተማርና በማሰልጠን የትምህርት ማእከላት ሆነው ኖረዋል፤
መ. ገዳማቱ ራሳቸው ብራና ፍቀው፣ ቀለም በጥብጠው፣ ብዕር ቀርፀው፣ ልዩ ልዩ ቅዱሳት መጻሕፍትን በመጻፍ፣ አብያተ ክርስቲያናት በመጻሕፍት እጥረት መንፈሳዊ አገልግሎትን እንዳያጡና ትምህርተ ሃይማኖት እንዳይቋረጥ አድርገዋል፡
ሠ. የብሕትውና፣ የንጽሕና፣ የቅድስና እና የምናኔ ሥርዓት ጠብቀው፣ በጸሎትና በትሕርምት ጸንተው፣ እግዚአብሔርን በቀንና በሌሊት በማመስገን፣ ሕዝብና ሀገር ከጠላት ጥቃት፣ ከዓባርና ከቸነፈር እንዲድን በጸሎታቸው ሲጠብቁ ኖረዋል፤
ረ. ሕዝበ ክርስቲያኑ በሃይማኖትና በምግባር እንዲታነጽ በየአካባቢው እየተዘዋወሩ በመስበክና በማስተማር፣ በእምነቱ የጸና እንዲሆን አድርገዋል፡፡

2. ገዳማት በማኅበራዊ ጉዳይ ረገድ ያበረከቱት አስተዋጽኦ

ከገዳማት ዓላማ አንዱ ማኅበራዊ ሥርዓተ ማኅበርን በመከተል፣ በገዳሙ ውስጥ ያሉት አበው ሁሉ በመካከላቸው ልዩነት ሳይኖር በኅብረት እየሠሩ ማምረት፣ ያለውን ሀብት በአንድነት መጠቀም፣ መምህራን፣ ዓቅመ ደካሞችና፣ አካል ጉዳተኞች፣ የመሳሰሉት ሁሉ በማኅበሩ ታቅፈው እንዲረዱ ማድረግ ነው፤

በዚህም መሠረት ገዳማት የእርሻ ሥራን፣ የአትክልትና የፍራፍሬ ምርትን፣ የእንስሳትና የንብ ርባታን፣ የመጠለያና የቤተ ክርስቲያን ግንባታን በኅብረት ስለሚሠሩና ስለሚጠቀሙ ሌላውን ከመርዳት በቀር በቀድሞው ጊዜ መነኮሳቱ ምግብና ልብስ አጥተው የሚቸገሩበት ሁኔታ አልነበረም፤

ከዚህም በተጨማሪ እያንዳንዱ ገዳማዊ መነኮስ በገዳሙ ውስጥ ካሉ፤ መንፈሳዊ ት/ቤቶች ከአንድ እስከ ሦስት ተማሪ እንደ ዓቅሙ በመርዳት፣ ተማሪዎቹም ለመነኮሳቱ እንጨት በመስበርና ውሀ በመቅዳት በመላላክ፣ የመረዳዳትና የመማማር ሥራ በገዳማት ውስጥ የተለመደ ባህል ነበረ በመሆኑም ማኅበራዊ ኑሮ ከማንኛውም በተሻለ በገዳማት የተጠናከረ ነበረ፡፡

3. ገዳማት ኢኮኖሚን በማሳደግ ረገድ የነበራቸው ሚና፡-

 • ገዳማት ከሚታወቁበት አንዱ በኢኮኖሚ ጠንካራ ዓቅም የነበራቸው መሆኑ ነው በመሆኑም ተግባረ እድና ሥነ ጥበብ በማስፋፋት፤ ሰፋፊ የእርሻ መሬትን በማረስና ለገዳማቱ በቂ ምርትን በማምረት፣
 • የእንስሳትና የንብ ርባታን በማካሄድ
 • የአትክልትና የፍራፍሬ ተክሎችን በመትከልና በማምረት
 • ብራና ፍቀው፣ ብዕር ቀርፀው፣ ቀለም በጥብጠው ቅዱሳት መጻሕፍትን በመጻፍና በመደጎስ፣
 • የሥዕልና የቅርጻ ቅርጽ ሥራዎችን በመሥራት የገዳማቱን የኢኮኖሚ ዓቅም እንዲያድግና መናንያን ያለችግር ገዳማዊ ሕይወታቸውን ጠብቀው ለዘመናት እንዲዘልቁ አድርገዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ያሉን ገዳማትም እንደቀድሞው ዘመን ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ባይኖሩአቸውም የሽመና ሥራ በመሥራት፣ በኪራይ ገቢ ሊያስገኙ የሚችሉ የሕንፃ ግንባታዎችን በከተሞች በመገንባት፣ የተለያዩ የተግባረ እድ ውጤቶች ማለትም እንደ መኪና ስፌት፣ መቋሚያና መስቀል መሥራት የመሳሰሉትን ሥራዎች እየሠሩ ራሳቸውን መደጎም የሞከሩ ገዳማት አልፎ አልፎ ቢሆንም አሉ፤ እንደዚህ የመሳሰሉ የልማት ሥራዎች በዘመናችን ቢስፋፉ አዋጪነታቸው ተስፋ ሰጪ ስለሆነ ሊጠናከሩ ይገባቸዋል፡፡

ገዳማት በአሁኑ ጊዜ ያሉበት ሁኔታ

ከ1967 ዓ.ም ወዲህ ባሉት ዘመናት ገዳማተ ኢትዮጵያን ያየን እንደሆነ በአጠቃላይ የመዳከም ባህርይ ይታይባቸዋል፤ ለገዳማት መዳከም በዋናነት ከሚጠቀሱት ምክንያቶች የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፤ ይኸውም፡-

ሀ. የገዳማት መተዳደሪያ ሆኖ ለዘመናት የኖረው የገዳማት መሬት በመሬት ላራሹ አዋጅ ሲወሰድ ገዳማውያኑ መተዳደሪያ ማጣታቸው፤
ለ. ገዳማውያን ለኑሮ ድጎማ ይጠቀሙባቸው የነበሩ የብራና ጽሕፈትና ድጒሰት ሥነ ጥበባት በዘመናዊ የሕትመት ሥራ ከመተካታቸውም በተጨማሪ የብራና መጽሐፍ ውድ ከመሆኑ የተነሣ በገበያ ያለው ተፈላጊነት ዝቅ እያለ መምጣቱና በዚህ ምክንያት ገዳማውያኑ ከዚህ ጥበብ ያገኙት የነበረው ገቢ መቆሙ፤
ሐ. ከሃያ ሦስት ዓመታት በፊት ለዐሥራ ሰባት ዓመታት በሀገሪቱ የተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት በገዳማውያኑ ላይ መፈናቀልና ፍልሰትን ማስከተሉ፣
መ. ቤተ ክርስቲያን በሰበካ ጉባኤ አስተዋጽኦ መተዳደር ስትጀምር በርከት ያለ ገንዘብ የሚገኘው በትላልቅ ከተሞች ሆኖ በመገኘቱና ይህ በከተማ የተገኘው ገንዘብ ወደ ገዳማውያኑ መድረስ የሚችልበትን ሥርዓት ባለመፈጠሩ ገዳማውያኑ ኑሮን ለማሸነፍ ገዳማቸውን እየለቀቁ ወደ ከተሞች መጉረፋቸው፣
ሠ. ከሥርዓተ ገዳም አንዱ አጽንዖ በዓት መሆኑ ይታወቃል፤ በመሆኑም ምንም እንኳ ችግሮች መኖራቸው የታወቀ ቢሆንም ችግሩን ተቋቁሞ በገዳም ጸንቶ መኖር አማራጭ የሌለው አድርጎ በመውሰድ ፈንታ ከሥርዓተ ገዳም መላላት የተነሣ ከላይም ከታችም ቁጥጥር እየጠፋ ስለሄደ ገዳማውያን መነኮሳት በየከተማው እንደፈለጉ እየዞሩ መኖርና የሥነ ምግባር ዝቅጠት በስፋት መከሠቱ፣
ረ. ከሥርዓተ ገዳም መላላት የተነሣ ለምናኔ ሳይሆን በገዳማዊነት ስም እየለመኑ ከፍተኛ ጥቅምን ለማግበስበስ አልመው የሚመነኩሱ የከተማ ጮሌዎችን መለየትና፣መቆጣጠር ባለመቻሉ ብዙ አስመሳይ መነኮሳት በስመ ገዳም በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ገንዘብ እየሰበሰቡ ለግል ጥቅም ማዋላቸው፣
ሰ. አንዳንድ አስመሳይ መነኮሳት በማጭበርበር በሚሰበስቡት ገንዘብ በከተማ ሆነው የተለያዩ ወንጀሎችን ሲፈጽሙ እየተደረሰባቸው በሕግ ቁጥጥር ሥር ሲውሉና ወህኒ ቤቶች በእስረኞች መነኮሳት ተጥለቅልቀው ሲታዩ ምእመናን በሃይማኖታቸው ክፉኛ እየተሸማቀቁ አንዳንዶቹም በብስጭት ወደ ሌላ ሃይማኖት እየገቡ መገኘታቸው፣
ሸ. በሁሉም አቅጣጫ ቤተ ክርስቲያኒቱን እንደመልሕቅ ቀጥ አድርገው ይዘው የነበሩ ገዳማት ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች እየተፈቱ ሲመጡ ‹‹ዳሩ ሲፈታ መሐሉ ይፈታ›› እንዲሉ በውስጣቸው የነበሩ የመንፈሳዊ ት/ቤቶችም አብረው ስለተፈቱ የሁለቱም ቀጣይ ዕድል ጥያቄ ውስጥ መግባቱ፤
ቀ. በሀገራችን በተፈጠረው የዘመናዊ ትምህርት መስፋፋት ምክንያት የትውልዱ አስተሳሰብ በፍጥነት እየተለወጠ መምጣቱ፣ ይህም በገዳማዊ ሕይወት ላይና በገዳምም ሆነ በገጠር በሚገኙ መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩ፣
በ. በዘመናችን እየተከናወነ ያለው የምንኩስና አሰጣጥ ብቃትን፣ ዕውቀትንና ገዳማዊነትን ተኮር ያላደረገና ይልቁንም በተቃራኒው ለሥልጣን ማግኛ፣ ለሀብት ማከማቻና ለሌሎች ዓለማዊ ጥቅማጥቅሞች ተብሎ የሚፈጸም ሆኖ መገኘቱ፣
ተ. ገዳማውያኑ በገዳማቸው ውስጥ በራሳቸው ጥረት ልዩ ልዩ የገቢ ምንጮችን በመፍጠር ራሳቸውን በራሳቸው መርዳትና ሃይማኖታዊ ግዳጃቸውን በአግባቡ መወጣት የሚያስችል በራስ የመተማመን መንፈስ በማጎልበት ፈንታ፣ በየከተማው እየዞሩ ገዳሙ ሊፈታ ነው ፣ወይም ሊዘጋ ነው እባካችሁ እርዱን በሚል የሰው እጅ ርዳታ ጠባቂነትና የጥገኝነት አስተሳሰብን መከተላቸው፣
ቸ. ከመነኮሳት ተግባር አንዱና ዋነኛው ሚሽንን ወይም ሐዋርያዊ ተልእኮን በዘመቻ መልክና በተደራጀ ሁኔታ በማካሄድ ያላመኑትን ማሳመን፣ ያልተጠመቁትን ማጥመቅ፣ የአገልጋይ እጥረት ያለባቸውን አብያተ ክርስቲያናት ማገልገል መሆኑ ግልጽ ነው፤

ይሁንና ቀደም ሲል በዘመነ አክሱም፣ ኋላም በአቡነ ተክለሃይማኖትና በተከታዮቻቸው መነኮሳት በስፋት ይካሄድ የነበረው ሐዋርያዊ ተልእኮ በአሁኑ ጊዜ ጭራሽ መረሳቱ፣ የመሳሰሉት በዘመናችን የገዳማት ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው፡፡

ገዳማትን ለመታደግ ምን ማድረግ አለብን

ገዳማት በዓለም አቀፍ ደረጃ ማለትም በኦሪየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት፣ በምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትና በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ከፍተኛውን የሃይማኖትና የማኅበራዊ ሥራ እንደሠሩ በታሪክ ይታወቃል፤

በሀገራችን በኢትዮጵያም በሃይማኖትም ሆነ በማኅበራዊ ተግባር ገዳማት የመጀመሪያውን ደረጃ ይዘው እንደሚገኙ እሙን ነው፤ በመሆኑም ለሃይማኖት ህልውና መቀጠል፣ ለማኅበራዊና ሥነ ጥበባዊ ዕውቀት መበልፀግ፣ ለትምህርተ ሃይማኖትና ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መጠበቅ፣ ገዳማት መተኪያ የሌለውን ሚና ይጫወታሉ፤

ከዚህ አኳያ ገዳማትን አቋቁሞ አጠናክሮና ጠብቆ መቀጠሉ ለጥያቄ የሚቀርብ መሆን የለበትም፤ በዚህ መሠረተ ሐሳብ ቤተ ክርስቲያናችን የማይናወጥና ጠንካራ አቋም መያዝ ይገባታል፣ ከአቋም ቀጥሎ ልዩ ልዩ የአፈጻጸም ስልቶችን መቀየስና መተግበር ይጠበቅባታል፣ ለዚህም የሚከተሉትን ሐሳቦች እንደመነሻ ሐሳብ ማየት እንችላለን፡-

1. ገዳም ማለት ምንማለት ነው? የሚለውን ዴፍኒሽን ወይም መሠረታዊ ትርጉም በትክክል ማስቀመጥ ለአጠቃላይ ገዳማዊ ተግባርና አደረጃጀት መሠረታዊ ሐሳብ ስለሚሰጥ ዴፍኒሽኑ በሊቃውንት በትክክል ቢገለጽና ቢቀመጥ፣
2. ገዳማዊ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ተብራርቶ የገዳማውያን መነኮሳትን ማንነት ሊገልጽ በሚችል መልኩ መሠረታዊ ትርጉሙ ቢገለጽና ቢቀመጥ፤
3. የገዳምና የገዳማውያን መሠረታዊ ዓላማና ተግባር ግልጽና ግልጽ በሆነ ሁኔታ ቢቀመጥ፣
4. እንደዚሁም የገዳምና የገዳማውያን ተልእኮ ራእይና ግብ በግልጽ ተለይቶ ቢቀመጥ፣
5. ገዳማውያንን ሊያቋቁም ሊያጠናክርና ሊጠብቅ የሚችል የገዳማት ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ቢጸድቅ፣
6. ገዳማትን በሙሉ አንድ አድርጎ ሊመራና ሊያስተዳድር የሚችል ወጥ የሆነ የገዳማት መተዳደሪያ ደንብ ተዘጋጅቶ ቢጸድቅ፣
7. ለገዳማት የሚዘጋጀው ፖሊሲም ሆነ መተዳደሪያ ደንብ የገዳማትን ደረጃ ለይቶ የሚያስቀምጥና የገዳማት መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግባራትን የሚያካትት፣ ሆኖ ቢዘጋጅ፣
ገዳማት የዕውቀት፣ የትምህርት፣ የተግባረ እድና የሥነ ጥበብ ማእከላት መሆናቸውን፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ የገዳማውያን ተቀዳሚ ተግባር መንፈሳዊ ት/ቤቶችን ማቋቋም፣ ሚሽንን ወይም ሐዋርያዊ ተልእኮን ማስፋፋትና ማጠናከር መሆኑ በፖሊሲውና በመተዳደሪያ ደንቡ ቢገለጽና ቢቀመጥ፣
8. በሀገር አቀፍ ደረጃ በእያንዳንዱ ወረዳ ለገዳማዊ ሕይወትና ለከፍተኛ መንፈሳዊ ት/ቤቶች በማእከልነት የሚያገለግል የተጠናከረና የተደራጀ ገዳም እንዲኖር መርሐ ግብር ቢነደፍ
9. ከፖሊሲውና ከመተዳደሪያ ደንቡ መውጣትና መጽደቅ ቀጥሎ ገዳማት የመሪ እቅድና የትግበራ አፈጻጸም በዝርዝር ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ቢገባ፣
10. ገዳማውያኑ በፖሊሲውና በመተዳደሪያ ደንቡ፣ በመሪ እቅዱና በትግበራው አፈጻጸም ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የተለያዩ የፓናል ውይይቶችና ሴሚናሮችን በማዘጋጀት ንቃተ ኅሊናቸው ከፍ እንዲል ቢደረግ ለሥራው አፈጻጸም ምቹና ፈጣን የሆነ ግብረ መልስ ሊያስገኝልን ይችላል፤ በዚህ አኳኋን ወደ አጠቃላይ ሥራ መግባት ከተቻለ የሥራውን አፈጻጸም በመከታተል ፣ በመቆጣጠር፣ በመገምገምና በማስተካከል ገዳማት እንደገና ሕይወት እንዲዘሩ ማድረግ ይቻላል፡፡

ማጠቃለያ

በመንፈሳዊም ሆነ በሥጋዊ ደረጃ ለማኅበረ ሰቡ ይጠቅማሉ ተብለው የሚቋቋሙ ተቅዋማት ጉልበትና ጥንካሬ ኖሮአቸው ጉልህ የሆነ ፍሬ ሊያፈሩና ግባቸውን ሊመቱ የሚችሉት ግልጽ የሆነ ፖሊሲ፣ መተዳደሪያ ደንብ፣ መሪ ዕቅድና የአተገባበር ስልት ሲኖራቸው እንደሆነ ጥርጥር የለውም፣

የተጠቀሱ መርሆዎችን የመከተልና የመጠቀም ዕድሉ ካለ የተቅዋሙ አቅጣጫ ምን ላይ ነው ያለው? የሚለውን ለይቶ ለማወቅና በጊዜው የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ ቀላል ይሆናል፤ እነዚህ ከሌሉ ግን ማስተካከል ቀርቶ ችግሩ ስለመኖሩ እንኳ ማወቅ የሚቻልበት ዕድል የለም፤ እውነተኛውን መረጃ በትክክል ማግኘት ካልተቻለ ደግሞ ያለው እንደጠፋ፣ የጠፋው እንዳለ ሊታይ ይችላል፤

ሌላው ደምብና ሕግን ተከትሎ መሥራት ለአንድ ተቅዋም ዘላቂ ህልውና እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ሕግ ልጓም ነው፤ ልጓም የሌለው ፈረስ ወይም በቅሎ የተቀመጠበትን ሰው ወዳልፈለገው ቦታ ወስዶ እንደሚጥል ሁሉ ሕግና ደምብ፣ ራእይና ግብ፣ ተልእኮና ዓላማ የሌለው ተቅዋምም ሥርዓት የለሽና ልቅ ስለሆነ በመጨረሻ ጥፋትና ውድቀትን ያስከትላል

ስለሆነም ገዳማቶቻችንና መንፈሳዊ ት/ቤቶቻችን አሁን ባለው ሁኔታ ተጉዘው ጭራሽ ከመጥፋታቸው በፊት የፈረስ ልጓም እናበጅላቸው፤ መልሶ የማቋቋም መርሐ ግብርም እናውጣላቸው ይህን ካላደረግን ግን ገዳማቶቻችንና መንፈሳዊ ት/ቤቶቻችን ከሞት አፋፍ ላይ መሆናቸውን ልብ ልንል ይገባል፡፡

ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን አሜን!
ከንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የመንፈሳዊ ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ
የካቲት 21 ቀን 2006 ዓ.ም
አዲስ አበባ

የፎንት ልክ መቀየሪያ