Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

“ገዳማቶቻችን ይጠኑ! መዝገበ ምስጢር ናቸውና”

“ገዳማቶቻችን ይጠበቁ! መሠረተ ስልጣኔአችን ናቸውና”

በመምህር ሙሴ ኃይሉ (B.TH, MA IN PHILO)

የደብረ ምሕረት ጨለቖት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን
ታሪክ፣ ቅርስና መንፈሳዊ አገልግሎት

የጨለቖት ሥላሴን ታሪክ በተለያዩ ሙሁራን በተለያዩ መጻሕፍቶቻቸው በተለያየ ርእሰ ጉዳይ እየተነሱ የተቻላቸውን ያህል አትተዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ መምህር ያሬድ ፈንታ አንድ ናቸው፡፡ መምህር ያሬድ ፈንታ ቤተክርስቲያናችን በእንግሊዘኛ ቋንቋ ላሳተመችው “Ethiopian Church Treasures and Faith: 2009”የተሰኘ መጽሐፍ ስለ ጨለቖት ሥላሴ ያቀረቡት ግሩም የሆነ ጽሑፍ በውል ከተገነዘብኩት በኋላ ወደ አማርኛ ተመልሶ ሁሉንም ለአንባቢ ቢቀርብ የተሻለ መልካም ነው በሚል እሳቤ ሙሉ ጽሑፉን እነሆ እላለሁ፡፡ ከዚህ በመቀጠል ግን እኔም እንደ ታናሽነቴ መጠን ከገዳሙ ዘንድ ተገኝቼ የታዘብኳቸውን እውነታዎች ከሊቁ ከመምህር ያሬድ ፈንታ የጎደለ ታሪክ ለመጨመርና ለማስተካከል ሳይሆን ልናተኩርባቸው ስለሚገቡን ነገሮች ብቻ በስተመጨረሻ ትንሽ ማለቴ አይቀርም፡፡

 • የጨለቖት መልክዓ ምድር

“ጨለቖት” ትግራይ ክፍለ ሀገር በእንደርታ አውራጃ የሚገኝ ታሪካዊ ቦታ ነው፡፡ ይህ ቦታ ከመቀሌ በስተደቡብ ከሕንጣሎ ከተማ በስተሰሜን የሚገኝ ሲሆን እንደ ሰንሰለት በተያያዙ ተራራዎች የተከበበ ነው፡፡ የቦታው አቀማመጥ ወይና ደጋ ስለሆነ የአካባቢው አየር እንደየወቅቱ ይለዋወጣል፡፡ በክረምት ቀዝቃዛ ሲሆን በበጋ ወራት ደግሞ በጣም ይሞቃል፡፡

በሰሜንና በደቡብ ጨለቖትን እየከፈለ ከምስራቅ ወይም ምዕራብ የሚፈስ ወንዝ አለ፡፡ ወንዙ በክረምት ወራት ይሞላል፡፡ በበጋ ግን መጠኑ የቀነሰ ውሃ የሚወርድበት ሲሆን ከሁለት ቦታ እየተነፈሰ ለመስኖ ተግባር ትልቅ አገልግሎት ይሰጣል፡፡

የጨለቖት ነዋሪ ህዝብ ወንዙን ገድቦ የሚዘራቸው የእህል ዓይነቶች በቆሎ፣ ገብስ፣ ጤፍ፣ ስንዴ…የመሳሰሉት ሲሆን ከአትክልትና ፍራ ፍሬ ዓይነትም ጌሾ፣ ሽንኩርት በርበሬ ሎሚና ብርቱካን ወዘተ ተክሎ እያሳደገ ይጠቀማል፡፡

 • ሀገረ ማርያም

“ጨለቖት” መጀመሪያ “ሀገረ ማርያም” ይባል ነበር፡፡ ሀገረ ማርያም የተባለበት ምክንያትም በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ አፄ ዐምደ ጽዮን ከጨለቖት በላይ ወደ ምስራቅ ባለ በሁለት ዳገት የተከበበ ጉድጓድ ቦታ ቤተ ክርስቲያን ሰርተው ታቦተ ማርያምን አስገብተው ሲያበቁ በዙርያዋ ያለውን መሬት በመስቀልና በዕጣን አስከልለው ያም ማለት መሰቀልና ማዕጠንት ተይዞ የተሰጠው ርስት እየተዞረ ለታቦቲቱ አገልጋዮች ካህናት ማደሪያ ሰጥተው ሌሎች ባላባቶቹ ርስታችን ነው ብለው እንዳይካፈሉ በአዋጅና በውግዘት ይህች “ሀገረ ማርያም”ናት ብለው ስለሰየሟት “ሀገረ ማርያም”ተብላለች፡፡ ዳግመኛም ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ግማደ መስቀሉን ይዘው ሲመጡ ጨለቖት ውስጥ ስላደሩ መሰቀሉ ያረፈበት ቦታ እስካሁን ድረስ ቤተ መስቀል ይባላል፡፡

ከብዙ ዓመታት በኋላ በጎንደር ዘመነ መንግሥት በንጉሥ ሕዝቅያስ ዘመን በ1781ዓ.ም አቤቶ ወልደ ሥላሴ ክፍለ ኢየሱስ ደጃዝማች ተብለው አንደሚባለውም ከአለውሃ ምላሽ እስከ ቀይ ባህር ድረስ ትግረ ትግርኝን ጠቅልለው ሲገዙ ዋና ከተማቸው በእንደርታ አውራጃ መካከል ሕንጣሎን አድርገው ተቀምጠው ነበር፡፡ እርሳቸውም የሥላሴን ቤተ ክርስቲያን በዓል የሚያከብሩ መንፈሳዊ ሰው ነበሩ፡፡ በአቅራቢያቸው የሥላሴ ቤተክርስቲያን በዓል በክረምት ወራት ግባ ወንዝን ተሻግረው ተንቤን ሂደው ግንፈል እንዳ ሥላሴ ገዳም ገብተው ሐምሌ 7ቀን የሥላሴን በዓል ያከበሩ ነበር፡፡ እንደተለመደው በ1884ዓ.ም የሥላሴን በዓል ለማክበር ሐምሌ 6ቀን ተነስተው አሸከሮቻቸውን አስከትለው እየተጓዙ ግባ ወንዝ ደረሱ፡፡ ወንዙ ጐርፍ ሞልቶ ነበር እና እየጣሱ ሲሻገሩ የሚወዱትን አሽከራቸውን ጎርፍ ወስዶባቸው ተከታትለው ኢልባውን ስላጡት እያዘኑ ተመልሰው እገዳሙ ገብተው የሥላሴን ቤተ ክርስቲያን ተሳልመው እያዘኑ አደሩ፡፡ በነጋታ ሐምሌ 7ቀን በዓሉን አክብረው እንደፈጸሙ ከገዳሙ አበምኔት ከመምህር ገብረ ሥላሴ ጋር ተገናኝተው የገጠማቸውን አደጋ ነገሩዋቸው፡፡ መምህሩም እግዚአብሔር ያውቃልና ሬሳውን ፈልጋችሁ አምጡት አሉዋቸው ደጃዝማችም አሸከሮቻቸውን አስከትለው በግባ ወንዝ ለወንዝ ሲፈልጉ በሁለተኛው ቀን ሬሳውን ከወንዙ ዳር ተገልፎ አግኝተው በቃሬዛ አሸክመው አምጥተው ለመምህር ገብረሥላሴ አሳዩዋቸው፡፡ መምህሩም የበቁ የእግዚአብሔር ሰው ነበሩና ሬሳውን ዳስሰው በረደው እንጂ አልሞም እሳት አንድዱለትና ከዳሩ አስተኙት አሉዋቸው፡፡ የመጡትም እሳት አንድደው ከዳሩ አስተኙት፡፡ በዚህ ጊዜ አበምኔቱ ሰውን ሁሉ አውጥተው ብቻቸውን ቁመው“አምላኬ ጌታዬ ሆይ አልዓዛርን እንዳስነሳኸው ይህን ምውት አስነሳልኝ”እያሉ ሲፀልዩ ሟቹ ተንቀሳቀስ ተነስቶም ተቀመጠ፡፡ ያን ጊዜ አባ ገብረሥላሴ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ደጃዝማችን አስጠርተው የተነሳውን አሽከራቸውን ባሳዩዋቸው ጊዜ “መንክር ግብሩ ወዕፁብ ነገሩ”ድንቅ ነው ብለው እየተደነቁ ባዘኑት ፈንጋ ከአሽከሮቻቸው ጋር ሆነው እጅግ ተደሰቱ በማግስቱም ይህን ትንሳኤ ላደረገላቸው ለእግዚአብሔር ምስጋና መስዋዕት አቀረቡ፡፡

ከዚህ በኋላ መምህር ገብረሥላሴ ደጃዝማች ወልደ ሥላሴን ከእንግዲህ ወዲህ ባሉበት አገር የሥላሴን ቤተ ክርስቲያን አሠርተው ከዚያ ጸልዩ እንጂ ወደዚህ አይምጡ ብለው መከርዋቸው ደጃዝማችም ምክራቸውን ተቀብለው “እንግዲያውስ ቤተክርስቲያን የምሠራበትን ቅዱስ ቦታ እግዚአብሔር ቢገልጥልዎ አብረን እንሂድና ሱባኤ ገብተው ይጸልዩልኝ”ብለው ለመኑዋቸው መምህሩም ልመናቸውን ተቀብለው አብረዋቸው ወደ ሕንጣሎ ከተማቸው መጡ፡፡

ታላቅ ራእይ የተገለጸበት ሱባኤ

መምህር ገብረሥላሴ ማዶ ጭኽ በሚባል የቅዱሳን መጸለያ ቦታ ሱባኤ ገብተው ሲጸልዩ ከሰማይ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን እስከሚሠራበት ቦታ ቀስተ ደመና ተተክሎ ሦስት ጌቶች ቅዱሳን መላእክትን አስከትለው ሲወርዱና ቀስተ ደመናው በቆመበት ቦታ ሲያርፍ በራዕይ አዶ እርሳቸውም ከሱባኤያቸው ወጥተው ያዩትን አምላካዊ ራእይ ለደጃዝማች ወልደ ስላሴ ለብቻቸው ነገሩዋቸው፡፡ ደጃዝማችም በነገሩ እየተደሰቱ ከመምህር ጋር ሆነው ከሕንጣሎ ከተማ ወደ ሰሜን አቅጣጫ አፍጎል ወደ ሚባለው ቦታ መጥተው ከአደጋበት ጀምሮ እስከ ባሕርያቱ ድርስ በጥድና፣ በወይራ፣ በዋንዛም…የተሸፈነ ታላቅ ወንዝ አገኙ፡፡ መምህሩ እየመሩ በጫካው ውስጥ ለውስጥ አብረው ሲጓዙ ወለል ያለ መልክ ባዩ ጊዜ “ዝየ ይትሐነጽ ቤተ እግዚአብሔር”…ማለት የእግዚአብሔር ማመስገኛ ቤተ መቅደስ ከዚህ ይሠራል በዚህ መልክ መካከል ያለው ቆት የሚባለው ትልቅ ዛፍም በጠቅላላ ለቤተ ክርስቲያኑ መዝጊያና መስኮት ይበቃል ብለው ነገርዋቸው፡፡

ያን ጊዜ ቆት በሚባለው ትልቁ ዛፍ ስርም ሁለት አንበሶች ተኝተውበት ነበርና ደጃዝማች ወልደ ሥላሴ ደንግጠው ጦር ወርውረው ሁለቱን ገደሉዋቸው፡፡ በዱሩ ውስጥ ተሰውሮ ሲጸልይ የነበረው ባህታዊ ወጥቶ መላእክት ገደልህ እንጂ አናብስት አልገደልህም ንስሐ ግባ ብሎቸው ተሰወረ፡፡ እርሳቸውም መምህራን በወሰኑላቸው ቀኖና መሠረት ኃጢአታቸውን ለማስተሰረይ ንስሐ ገብተናል ከዚህ በኋላ በአዋጅ በተሰበሰበው ሕዝብ ጫካው ተመንጥሮ ቆት የሚባው ትልቁ ዛፍ ተቆረጠ፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ የሚሠራበት ቦታ ተስተካክሎ ተደለደለ፡፡

 • የግብረ ህንፃና የሥነ ኪነት ጠቢባን

ራስ ወልደ ሥላሴ ሙሴ ባያት ደብተራ ኦሪት አምሳል የሥላሴን ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት ስላሰቡ የግብረ ህንፃና የሥነ ኪነት ጠቢባን እንዲልኩላቸው ለወዳጃቸው ለእንግሊዝ ንጉስ ጊዮርጊስ ሣልሳዊ መጋቢት 21 ቀን 1784ዓ.ም በተጻፈ የወዳጅነት ደብዳቤ ጠየቁዋቸው መልእክቱም የተጻፈው በግዕዝ ቋንቋ ነው፡፡ ያውም እንዲህ ነው፡፡

 • ለእንግሊዝ ንጉሥ ሣልሳዊ ጊዮርጊስ 

ዛቲ መልእክት ትብጻህ ኅበ ፍቁርነ ሣልሳዊ ጊዮርጊስ ንጉሥ እንግሊዝ ደኅንኑ ሀሎከ ምስለ ሕዝብከ አነሂ ደኅን ሀሎኩ ምስለ ሕዝብየ ይትባረክ እግዚአብሔር፡፡ ናሁ እስእለከ ዓቢየ ነገረ በይነ ዘኅለይኩ ከመ እሕንጽ ቤተ እግዚአብሔር ፈኑ ሊተ ጠቢባነ እለ የአምሩ ግብረ ሕንጻ ወእለ ይኬንዎ አክሊላተ ዘወርቅ፣ ወመሳቅለ ዘወርቅ፣ ወጽዋዓተ ዘወርቅ፣ ወኩሎ ንዋያተ ቅድሳት፣ ወንያዋተ ማሕሌት፣ አርጋነ ወዕንዚራ ወመሰንቆ ወመዝሙረ ወከበሮ፣ ዘወርቅ፣ ወደየጽላተ ዘወርቅ ወኩሎ ዘይመሰሎ ወኩሎ ኪነተ ዘይከውን ለተዝካር ተጽሕፈ በትዕይንተ ሕንጣሎ አመ 20ወ1ለመጋቢት 1784ዓ.ም የሚል ደብዳቤ ለእንግሊዝ ንጉሥ ሣልሳዊ ጊዮርጊስ ላኩ፡፡

 • የመልእክቱ መልስ

የእንግሊዝ ንጉሥ ሣልሳዊ ጊዮርጊስም መልእክታቸውን ተቀብለው ከሰላምታ ጋር ግብረ ህንፃና ሥነ ኪነትን የሚያውቁ ሚስተር ሳውልትና ሚስተር ናትናኤል ፔርስ የሚባሉ ጠቢባን ላኩላቸው፡፡ ደጃዝማች ወልደ ሥላሴም እንግዶቹን በምስጋና ተቀብለው በክብር አስቀመጡዋቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ግብረ ሕንጻን የሚያውቁ ኢትዮጵያውያንና ሌሎችም ሠራተኞች ሰብስበው ቤተ ክርስቲያኑ የሚሠራበትን ቦታ ከጠቢባኑ ጋር ሆነው እንዲያዘጋጁ አዘዙዋቸው፡፡

 • የቤተ ክርስቲያኑ ሕንጻ መመሥረት

በዘመነ ማቴዎስ ሰኞ መስከረም 9ቀን 1785ዓ.ም በጠቢባኑ መሪነት ከሦስት ክፍል ተከፍሎና ተለክቶ መሠረቱ ተቆፈረ የመሠረቱ ጥልቀት አስር ሜትር ሆኖ በጥቁር ድንጋይ ከተነጠፈ በኋላ በላይ ላይ አሞሌ ጨው እንደ ብሎኬት ተደርድሮ በንጣፍነት ተሠራ፡፡ እንዲህ የተደረገበት ምክንያትም ቤተ ክርስቲያኑ የተሠራባቸው ዕንጨት ነክ የሆኑ እቃዎችና ዐምደ ወርቆች በምስጥ እንዳይበሉ ለመከላከል ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያኑ መቃንና መድረክ ጉበን መዝጊያ እንዲሁ በልዩ ልዩ ጌጥ የተሠሩ አእማድ የተዘጋጁት ከተቆረጠው ትልቁ የቆት ዛፍ ስለሆነ አናጢዎቹና ሠራተኞቹ ህዝቡም ሁሉ ዛፍን ጨለቆት እያሉ በትግርኛ ቋንቋ አደነቁት “ጨለቆት” ማለት በአማርኛ ቋንቋ መልካም ቆት ማለት ነው ከብዙ ቀን በኋላም ቃሉን መሠረት በማድረግ ያገሩ ስም ጨለቆት ተብሎ ተጠራ፡፡

 • የቤተ ክርስቲያኑ ውስጣዊና አፍአዊ ቅርጽ

የቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ ክብ ሆኖ በሦስት ክፍል የተከፈለ ነው፡፡ ውስጣዊ ክፍል ቤተ መቅደስ መካከለኛው ቅድስት ሦስተኛው ደግሞ ቅኔ ማኅሌት ይባላል፡፡ ቤተ መቅደሱ ጸሎተ ቅዳሴ የሚደርስበት ቅዱስ ቁርባንና መስዋእት የሚቀርብበት ነው፡፡ ከቀዳስያን በቀር ሌላ ሰው አይገባበትም፡፡ ሁለተኛው ክፍል ቅድስትም ቀሳውስትና ዲያቆናት ሰዓታትና ስብሐተ ፍቁር የሚያደርሱበት ምእመናንም የኅሊና ጸሎት የሚጸልዩበት ነው፡፡ ቅኔ ማህሌቱም ሊቃውንትና መዘምራን ያሬዳዊ ማኅሌት የሚያደርሱበት ምእመናንም የሚጸልዩበት ነው፡፡ በጉልላት ላይም ታላቅ መስቀል አለበት፡፡

ቤተ ክርስቲያኑ ሊሠራ ሲል ወልደ ስላሴ ታመው ስለነበር ፍጻሜውን ሳያዩ እንዳይሞቱ ከመስጋታቸው የተነሳ ሥራው በተጀመረበት ዓመት እንዲያልቅ ስለወሰኑ ወደ ላይ ያለው ከፍታ ከስፋቱ ጋር የተመዛዘነ አይደለም፡፡ ስለዚህ የተፈለገውን ያህል ወደ ላይ ሳይረዝም ባጭሩ ጣራው አልቆ ማክሰኞ ሐምሌ 4ቀን 1785ዓ.ም ታቦቱ ገባ፡፡ የቅዳሴ ቤቱ በዓልም በታላቅ ክብር ከተከበረ በኋላ የቤተ ክርስቲያኑ ስመ ማዕረግ “ደብረ ተድላ” ተብሎ ተሰየመ፡፡

 • የቤተ ክርስቲያኑ መተዳደሪያ

ራስ ወልደ ሥላሴ ለጨለቆት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ማደሪያ እንዲሆን የራሳቸው ርስትና ሌሎች ለም የሆኑ ሰባት አገሮችን በጉልትነት ሰጥተው “መኻሉ ገነት ዳሩ እሳት እንበለ ቀዳሲ ኢይባእ ነጋሲ”ብለው አካባቢውን በመስቀል በዕጣን አስከለሉት፡፡ ከክልሉ ውስጥና ከክልሉ ውጭ የሚኖር ሰው ድንገት ወንጀል ፈጽሞ ደብረ ተድላ ጨለቆት መጥቶ ሲማጸን ምሕረት ይደረግለታል ብለው አዋጅ ስላወጁ ከክልሉ ውጭ በጫካ ውስጥ እየተዛዋወረ ይኖር የነበረ ነፍስ ገዳይ ሽፍታ ወደ ደብረ ተድላ ቤተ ክርስቲያን መጥቶ ተማፀነ፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ራስ ወልደ ሥላሴ ምሕረት አድርገውለት ከባለ ደሞቹ ገንዘባቸውን ሰጥተው አስታርቀውታል፡፡ ከዚህ በኋላ የጨለቆት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የማዕረግ ስም “ደብረ ተድላ” መባሉ ቀርቶ “ደብረ ምህረት” ተብሎ ተሰይሟል፡፡

ከእለታት አንድ ቀን ራ ወልደ ሥላሴ ከሰራዊታቸው ጋር ሆነው ከቤተ ክርስቲያኑ ወደ ምስራቅ አቅጣጫ ወንዝ ወንዙ ሲሄዱ ትንሽ ዋሻ መሳይ ደልዳላ ቦታን አገኙ በዋሻው ውስጥም ቃለ እግዚአብሔር የሚገልጥ አስማት አስቀረፁበት ቀጥለውም አስማት ከተቀረፀበት ዋሻ ውስጥ ከሚወጣው ውሀ ካሃቱ ጠጥተው እግዚአብሔር ቃል ይገለፅላቸው ይሆናል ብለው በማሰብ ውሀውን በባዶ ወደ ቤተክርስቲያኑ ዐውደ ምህረት እንዲገባ አደረጉ፡፡

 • የቤተ መቅደሱ የግድግዳ ላይ ሥዕል

የቤተ ክርስቲያኑ ስዕል የተሳለው ሠዓሊ አለቃ ኃይሉ በተባሉ ባለሙያ ነው፡፡ የተሳለውም ከሌላው ቦታ በተለየ መልኩ የመቅደሱና የቅድስቱ የውጭ ግድግዳ በሙሉ ሲሆን በቅድስቱ የውጭ ግድግዳ ዙሪያ የተሳለው አቡቀለምሲስ ዮሐንስ ያየው ራእይ ሁሉ ነው፡፡ በተለይም ከመቅደሱ ፊት ለፊት የምስለ ፍቁር ወልዳ ሥዕል ዕፁብ ድንቅ በሆነ ህብረ ቀለም የተሳለ ሲሆን በተለያዩ ጊዜ በመሰሉና ረዘም ያለ ጊዜ በመውሰዱ የራስ ወልደ ሥላሴ ስም አንዳንድ ጊዜ ደጃዝማች አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ራስ እየተባለ ተጽፎአል፡፡ በግድግዳው ላይ ብቻ ሳይሆን በየበሮቹ ላይ ያሉት ስዕሎች ሁሉ ሳይቀሩ ለተመልካች እጅግ የሚያስደንቁ ሆኖ ይታያል፡፡ የቤተክርስቲያኑ ሥዕልና በመስከረም ወር 1786ዓ.ም ተጀምሮ በ7 ዓመት ተፈጽሟል ይባላል፡፡

 • የቤተ ክርስቲያኑ ንዋያተ ቅድሳት

 •  ከእንግሊዝ ንጉሥ ጊዮርጊስ ሣልሳዊ በስጦታ የተላኩት የሚከተሉት ናቸው፡፡
 • የወይን ዘለላ የተቀረፀበት ባለ መክደኛ ድምፅ
 • ትልቅ ቋሚ መስቀልና መዝሙረ ዳዊት
 • የቅዱስ ጊዮርጊስ ምስል ከነፈረሱ
 • መንበረ ታቦት ዘውድና አክሊል
 • ልዩ ልዩ የዜማ ስልት የሚያሰማ ባለምት አርጋኖን
 • ልብሰ መንግስትና ሌሎችም በወርቅ ያጌጡ ብዙ አልባሳት
 • ብዙ መሰቀሎችና ከዕርፈ መሰቀሎቻቸው ጋር

ከእነዚህም አልባሳቱ በወርቅ ያጌጡ እቃዎቹም ከወርቅ የተሠሩ ናቸው፡፡ ራስ ወልደ ሥላሴም እነዚህን ስጦታዎች ሁሉ በምስጋና ተቀብለው በፊርማቸው ተረክበዋቸዋል፡፡
ከውጭ በመጡ አቡስትሊ በተባሉ ግብፃዊ ጠቢብ የተሠሩ ንዋያተ ቅድሳትም የሚከተሉት ናቸው፡፡

 • ከወርቅና ክብር የተሠሩ ዘውዶች
 • መሰቀሎች፣ ፃህልና ጽዋዕ
 • ከበሮ፣ መቋሚያና ጸናጽል
 • ልዩ ልዩ ያጌጡ አልባሳትና መነሳንስ
 • የወይን ማጣሪያ ወንፊት
 • የወርቅ ዙፋንና ወንበር፣ የሐር ምንጣፎች

ጠቢባኑ እነዚህን ሁሉ ሠርተው ለራስ ወልደ ሥላሴ አስረክበዋቸዋል፡፡ እርሳቸውም አይተው እጅግ ደስ ስላላቸው በሚልዮን የሚቆጠር ወርቅ ሸልመዋቸዋል ይባላል፡፡

በቤተ ክርስቲያኑ ቤተ መጻሕፍትም ብዙ መጻሕፍት ይገኛሉ፡፡ በተለይም ከመጻሕፍቱ መካከል ሽፋኑ ወይም ገሉ በወርቅ የተለበሰ ወርቅ ወንጌልና የሦስት መቶ ዐስራ ስምንት ሊቃውንት ሥዕል ያለበት ሃይማኖተ አበው ይገኙበታል፡፡

የጨለቆት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አለቆች

አለቆች ማለት ቤተ ክርስቲያንን በኃላፊነት የሚያስተዳድሩ ሹማምንት ማለት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ከተሰራበት ከ1785ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በየዘመኑ የተሾሙ አለቆች ብዙዎች ናቸው፡፡ ከእነርሱም የመጀመሪያው አለቃ “መልአከ ተድላ ዘሚካኤል”ይባሉ ነበር፡፡ የተሾሙትም የቤተክርስቲያኑ የማዕረግ ስም “ደብረ ተድላ”ይባል በነበረበት ጊዜ ስለሆነ መልአከ ተድላ ተብለዋል፡፡ ከርሳቸው በኋላ የተሾሙት አለቆች ግን እስከ ዛሬ ድረስ የሚጠሩበት የማዕረግ ስም መልዐከ ምሕረት ነው፡፡

የደብሩ አለቆች ሆነው ከተሾሙት መካከልም አለቃ አስራት ዘውጉና አለቃ ደስታ የተባሉ ሊቃውንት በቤተ መንግስት የታወቁ ስለሆነ በዐፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግስት 1864-1881ከእስክንድርያና አራት ጳጳሳት ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል፡፡

በ1928ዓ.ም ጠላት ሀገራችን ኢትዮጵያን በወረሩ ጊዜም ጦርነቱ ጨለቆትን በሰሜንና በደቡብ ከበውት ነበርና የጨለቆት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ነባር ቅርስ ሁሉ እንዳይዘረፍ የሰጉ አለቃ ከርሱባሔል ወልደ ዮሐንስ ከሚያምኑዋቸው ከርእሰ ደብር አስራትና ርእሰ ደብር ገብረ ሥላሴ ተማክረው ስሙ ቸሩ በሚባል አገልጋያቸው ብቻ ትልቅ ጉድጓድ አሳምሰውና አስገንብተው አስለስነው ውድ የሆኑ ብዙ ቅርሶችንና ዋና ዋና መጻሕፍቱን በሙሉ በውስጡ ደብቀው አስቀምጠው ጥቃቅን አልባሳትንና ጥቂት መጻሕፍትን በዕቃ ቤቱ ውስጥ አስቀሩ፡፡

የቤተ ክርስቲያኑን ንዋየ ቅድሳትና ያለውን ቅርስ ሁሉ ለማየት ከጠላት የተላከው ባለ ሥልጣን በዕቃ ቤቱ ውስጥ የቀሩትን አልባሳትና መጻሕፍትን አይቶ ሌላውስ የት አለ ብሎ ቢጠይቃቸው ያለን ይህ ብቻ ነው ሌላ የለንም ብለው በድፍረትና በቆራጥነት ስለመለሱለት እርሳቸውንና ርእሰ ደብር ገብረ ስላሴን ናኩል ወስዶ አሰራቸው አለቃ ብርሱባሔል እስር ቤት እንዳሉ ሲሞቱ ርእሰ ደብር ገብረ ሥላሴ ግን ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ትንሽ ጊዜ እንደቆዩ ሞቱ እነዚህ ሊቃውንት የቤተ ክርስቲያኑ ቅርስ እንዳይጠፋ ብለው ሕይወታቸውን ለሞት አሳልፈው ስለሰጡ ታሪክ ሲያስታውሳቸው ይኖራል፡፡

ዳግመኛም ከጨለቆት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አለቆች አንዱ የሆኑ መልአከ ምህረት ያሬድ ግርማይ አባ መርሐ ክርስቶስ ተብለው ትግራይ ክፍለ ሀገር ሊቀ ጳጳስ ሆነው ባሁኑ ጊዜ ተሹመዋል፡፡ ይህ ሁሉ የማዕረግ ደረጃ በቤተክርስቲያኑ የተገኘው በተአምራትና በራእይ የተሰራ በመሆኑ ረድኤተ እግዚአብሔር ስላልተለየው ነው፡፡

እንዲሁም በዐፄ ተክለ ጊዮርጊስ ዘመነ መንግሥት ሊቀ ጳጳሳት የነበሩ ከጐንደር ተሰደው የመጡ አቡነ ቄርሎስ ራስ ወልደሥላሴ ክፍለ ኢየሱስ የአፄ ቴዎድሮስ ባለቤት ወ/ሮ ጥሩነሽ እነዚህ ከፍተኛ ማዕረግ ያላቸው ሰዎች ከቤተ ክርስቲያኑ ዐውደ ምሕረት ስለተቀበሩ ቦታው የታላላቅ ሰዎች መቃብር ለመሆን በቅቷል፡፡

በመጨረሻም ያረጀው የቤተ ክርስቲያኑ ሳር ክዳን ተነስቶ ባሁኑ ጊዜ ጣራው ቆርቆሮ ስለለበሰ በተሠራ በመቶ ሀምሳ ስድስት አመቱ ታድሷል፡፡ የእድሳቱ ሥራም ጥር 2ቀን 1947ዓ.ም በመፈፀሙ ጥር 7ቀን መኳንንትና መሳፍንት ሊቃውንትና ብዙ ህዝብም ባለበት የቅዳሴ ቤቱ በዓል ተከብሯል፡፡


መደምደሚያ

የጨለቆት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የተሠራው በተደረገው ተአምራትና በተገለጸው ራዕይ መሠረት ነው፡፡ በተደረገው ተአምራት መባሉ መምህር ገብረ ሥላሴ የሁለት ቀን ሬማ ጸልየው ካስነሱ በኋላ ደጃዝማች ወልደ ስላሴን ከእንግዲህ ወደዚህ አይምጡ በከተማዎ የሥላሴን ቤተ ክርስቲያን አሠርተው ከዚያ ይጸልዩ ብለው ስለመከርዋቸው ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ የሃገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ በቦታው ላይ ያሉትን በርካታ የታሪክ ቅርሶች የዘመነ መሳፍንት ታሪክና ቅርስ ዝክር እና በዚያ ዘመን ቤተ ክርስቲያን የነበራትን ሕይወት ማስታወሻ የሆኑ ሐብቶች መጠበቂያ የሚሆን ቤተ መዘክር የማሠራት እቅድ ያላቸው ሲሆን ይኸውም ከፍተኛ ድጋፍና ማበረታቻ የሚያስፈልገው ነው፡፡(ብፁዕ አባታችን ከመሞታች በፊት የተጻፈ ነው)

በተገለጸው ራእይ መባሉም መምህር ገብረ ሥላሴ የሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የሚሠራበት ቦታ እንዲገለጽላቸው ሱባኤ በገቡ ጊዜ በቀስተ ደመና ምልክት ቦታው ስለታያቸው ነው፡፡ በተአምራትና በራእይ እየተመሩ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው የሥላሴ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠራ ጥረት ያደረጉ ሁለቱ ሰዎች ራስ ወልደ ሥላሴና መምህር ገብረ ሥላሴ በዘርፍና ባለቤት ሙያ በስመ ሥላሴ መጠራታቸው ቤተ ክርስቲያኑን ለማሠራት መመረጣቸውን ስለሚያመለክት እጅግ ያስደንቃል፡፡ ስምን መልአክ ያወጣዋል እንዳሉ (ሉቃ.1፡31) ብለው መምህር ያሬድ የታሪክ ሐተታቸውን አጠቃልሎአል፡፡

መርጌታ ልሳነ ወርቅ ገብረ ጊዮርጊስም በበኩላቸው የጨለቖት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አለቆች ዝርዝር በተመለከተ “ጥንታዊ ሥርዓተ ማኅሌት ዘአቡነ ያሬድ ሊቅ”በተሰኘ መጽሐፋቸው በእንዲህ መልኩ ዘርዝረው አስቀምጠውታል፡፡

ቁጥር

የአለቃው ስም

ሞያው

1

መልአከ ተድላ ዘሚካኤል

ብሉይ፣  ሐዲስ፣  ሊቃውንት፣ ቅኔ፣ ዜማ

2

መልአከ ምሕረት ባሕርየ ሥላሴ

ሐዲስ፣ ሊቃውንት፣ ቅኔ፣ ዜማ

3

መልአከ ምሕረት አሥራት

ሐዲስ፣ ሊቃውንት፣ መጽሐፈ መነኮሳት፣ ቅኔ

4

አለቃ ደስታ

መዘምር

5

መልአከ ብርሃን አብርሃ

ሐዲስ፣ ዜማ

6

አለቃ መንክር

ብሉይ፣  ሐዲስ፣ ድጓ፣  ቅኔ፣ ሊቃውንት

7

መልአከ ምሕረት ሰይፈ

ሐዲስና ቅኔ

8

መልአከ ምሕረት ገብረማርያም

ዜማና ፍትሐ ነገሥት

9

መልአከ ምሕረት ገብረኪዳን

ዜማና ቅኔ

10

መልአከ ምሕረት ገብረ ሥላሴ

ዜማና ፍትሐ ነገሥት

11

መልአከ ምሕረት ሀብተ ሥላሴ

ቅኔና ዜማ፣ መጽሐፈ ሊቃውንት

12

መልአከ ምሕረት ገነት መንግሥቱ

ቄስ የንግግር ችሎታ ብቻ

13

አለቃ መኰንን ኢያቄም

ዜማና ቅኔ፣ ሐዲስ

14

መልአከ ምሕረት ወልደ ኪሮስ

መዘምር

15

መልአከ ምሕረት ያሬድ /ኋላ አባ መርሐ ክርስቶስ ሊቀ ጳጳስ/

ድጓ፣ ቅኔ፣ ብሉይ፣ ሐዲስ፣ ሊቃውንት

16

መልአከ ምሕረት ታደሰ

ድጓ፣ የ44 ጐንደር አባባል ሊቅ

እነዚህ በ1785ዓ.ም ቤተ ክርስቲያኑ ከተሠራ ጀምሮ እስከ 1984ዓ.ም በየዘመኑ የተሾሙ ናቸው በማለት በመጽሐፋቸው ዘርዝርው አስቀምጠዋል፡፡/መርጌታ ልሳነ ወርቅ ገ/ጊዮርጊሰ፡ጥንታዊ ሥርዓተ ማኅሌት ዘአቡነ ያሬድ ሊቅ ፡ 1989ዓ.ም ፡ ገጽ 302/

ጨለቖትን እንደጐበኘነው

ደብረ ምሕረት ጨለቖት ሥላሴ ይህን የመምህር ያሬድ የታሪክ ጽሑፍ አንብበን ከተለያዩ ሊቃውንት የሚነገረውን ታሪክ አድምጠን የዚህ ጽሑፍ አዘጋጆች በአካል ተገኝተን ከበረከቱ ለመሳተፍ ወደ ታሪካዊው ደብር አመራን፡፡

ወቅቱ የበጋ /የሐጋይ/ወራት ስለነበረ አብዛኛው አካባቢ የሚገኙ ዛፎች ቅጠላቸው ረግፎ ተራሮችም ልምላሜአቸው ደርቆ ወደ ወርሐ ክረምት በሰላም እንዲያደርሳቸው በመጸለይ ወደ ፈጣሪያቸው ወደ ላይ ፊታቸውን አንጋጥጠዋል፡፡ በሰንሰለታማ ተራሮች የታጠረች ጨለቖት ግን በዚህ ወቅት እንኳ ሳይቀር በልምላሜ አጊጣለች፡፡ የአከባቢው ሕዝብ እንደየአቅሙ በመስኖ ሥራ ላይ ተጠምዷል፡፡ በዚህም ወደ ገዳሙ ለሚመጡ እንግዶች አስቀድሞ የሚቀርበው ይኸው የመስኖ በረከት የሆነው ፍራፍሬ ነው፡፡ የጨለቖት ሕዝብ ፍጹም እንግዳ አክባሪ፣ ቤት ለእንግዳ ከቤት አርፈችሁ፣ እግራችሁ ውኃ ታጥባችሁ፣ የተገኘውን /ቤት ያፈራውን/ ተስተናግዳችሁ… እለፉ ማለት መለያቸው ወይም መልካምና ክርስቲያናዊ ልማዳቸው ነው ማለት ያንስ እንደሆነ እንጂ አይበዛም፡፡

ወደ ታሪካዊው ገዳማችን ለመሄድ የትራንስፖርት ነገር ብዙም አሳሳቢ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ገዳሙ ከመቐለ ከተማ የሚርቀው 16ኪ.ሜ.ነው፡፡ ስለሆነም ትራንስፖርት የሚባል ነገር የለም እንኳ ቢባል ርቀቱ ይህን ያህል አሳሳቢ ስላልሆነ በእግርም ደርሶ ጐብኝቶ መመለስ ይቻላልና ነው፡፡ የአከባቢው ህዝብም በብዛት የሚጠቀሙት ይኸው ነው፡፡ 

ጨለቖት ሥላሴ እንደደረስን የደብሩ ደጋግ አገልጋዮች አክብረው ተቀበሉንና ጠቅላላ ታሪኩን ቅርሶቹንና ያላቸውን ችግሮች በተመለከተ እጅግ መልካም በሆነ አንደበት ገለጻ አደረጉልን፡፡ የደብሩን ታሪክ በተመለከተ ሰፊ ገለጻ ያደረጉልን ከአባቶቻቸው ደብሩን በእልቅና አደራ ተረክበው አሁን በማገልገል ላይ ያሉ መልአከ ምሕረት ታደሰ ናቸው፡፡ መልአከ ምሕረት ታደሰ እውነትም በዓለመ መጻሕፍት የሚኖሩ ታላቅ ሊቅ ስለሆኑ በአጠቃላይ የመጻሕፍቱን ምስጢር ፈትተው የሚያውቁት አሁን በቦታው እሳቸው ብቻ እንደሆኑ አስቀድሞ ስለተነገረን በዚህ መሠረት ቀርበን ስናናግራቸው ከታሪኩ በላይ የአነጋገር ዜይቤአቸው፣ የአቀራረብ ስልታቸው… በጣም መስጦን ሁሉንም ታሪክ ጠይቀናቸው ሁሉንም መልስ ሰጥተውናል፡፡

የደብሩ አጠቃላይ ታሪክና የያዘው ቅርስ በተመለከተ መልአከ ምሕረትም የነገሩን ከመምህር ያሬድ ጽሑፍ ጋር ተመሳሳይ ስለሆነ ጽሑፉ ማንበብ ብቻ በቂ ይመስለኛል፡፡ግን በዚህ አጋጣሚ በታሪኩም ሆነ በቅርሶቹ አያያዝ ዙሪያ የታዘብኳቸዉን እነሆ ልበል፡፡

 • ቅርሶቹ የመኖራቸው ምሥጢር

ከላይ መምህር ያሬድ በጽሑፋቸው እንደገለጹትና መልአከ ምሕረት ታደሰም እንደተረኩልን በዚሁ ደብራችን የሚገኙ የታሪክ አሻራ የተላበሱ ቅርሶችን ተጠብቀው ከዘመናችን ለመድረስ ከምንም በላይ የሰው ሕይወት ያህል ክቡር ጸጋ የተከፈለላቸው፣ የሰው ደምን ያህል የፈሰሰላቸው…ወዘተ ናቸዉ፡፡ ይኸውም በ1928ዓ.ም ገደማ ወራሪ ኃይል ሀገራችን በገባ ጊዜ በጨለቖት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ከእንግሊዝ መንግሥት የተላኩ ውድ ስጦታዎችን ጨምሮ የተለያዩ ውድ የሆኑ ንዋያት ቅድሳት በዚህ ደብር በክብር ተጠብቀው መቀመጣቸውን ያውቅ ስለነበረ ሳይውል ሳያድር ወደ ደብሩ አመራ፡፡

ይህ እንደሚሆን አስቀድሞው ያወቁ ጠበብት ወላጆቻችን ግን(ስማቸው ከመምህር ያሬድ ጽሑፍ ዘንድ ተጠቅሷል)በምሥጢር ጉድጓድ ቆፍረው የተወሰኑ አልባሳትና ጥቂት መጻሕፍት ብቻ በማስቀረት ሌላውን ውድ የሆኑትን ቅርሶች በሙሉ በጥንቃቄ ወደ አዘጋጁት ጉድጓድ በመቅበር ከጠላት እይታ ሰውረዋል፡፡ ጠላት ዕቃ ቤቱን አይቶ ከመረመረ በኋላ እንደተሳለቁበት አውቆ የቀረው ቅርስ የት እንዳለ ቢጠይቃቸውም በቆራጥነትና በጀግንነት ከዚህ ውጭ ሌላ የለንም በማለታቸው እየተገረፉ ወደ እስር ቤት ተወስዷል፡፡ በእስር ቤት እንዳሉ አለቃ ብርሱባሔል ሞቷል፡፡ ልብ በሉ የታሰሩትም ሆነ የሞቱት ቅርሶቹ የት እንዳሉ አንናገርም በማለታቸው ብቻ ነው፡፡ ርእሰ ደብር ገብረ ሥለሴ ግን ጠላት ከጠፉ በኋላ ከናኩል ወደ ሀገራቸዉ ተመልሰው የቅርሶቹን ቦታ በአግባቡ አሳይተው ምሥጢሩንም በወቅቱ ለነበሩ ሊቃውንት ተርከው ትንሽ እንደቆዩ ሕይወታቸው አልፎአል፡፡


እነዚህ ሰማዕታት ቅርሶቹ መጥፋትና መዘረፍ የለባቸውም፤ የማንነታችን መግለጫዎች ስለሆኑ፤ የኋላ አባቶቻችን የጥበብ ምስክሮቻችን ስለሆኑ…በጥንቃቄ ተጠብቀው ለልጆቻችን መተላለፍ አለባቸው ብለዉ፤ የቅርሶቹ ደኅንነት ጠብቀው ሕይወታቸው ግን ለጠላት (ለእስርና ለሞት)አሳልፈው መስጠታቸዉ ታሪክ አብዝቶ፣ አስፍቶና አሟልቶ ሊዘክራቸዉ፣ ሊያስታውሳቸው፣ ሊያወድሳቸዉ…ይገባል እለለሁ፡፡ ምክንያቱም የእነዚህ ቅርሶች በዚህ ዘመን የመገኘታቸው ምሥጢር እነዚህ ሰማዕታት ስለሆኑ፡፡

ከእነዚህ ሰማዕታት ምን እንማራለን

 • ቅርስ ጠባቂነትን፡-

ቅርስ በዘርፉ ባለሙያዎች (professionals)ሲገለጽ ሰፊ ሐተታ እና ትርጉም ያለው ትልቅ ርእሰ ጉዳይ ነው፡፡ በአጭሩ ግን ቅርስ የአንድን ሕዝብ ታሪክ ማለት ማኀበራዊ፣ ፖለቲካዊና መንፈሳዊ የአኗኗር ዘይቤ ሳይጨምሩና ሳይቀንሱ የነበረውን እውነታ (ጥንታዊ ሥልጣኔ)ዘመን እየተሻገሩ ከትውልደ ትውልድ እየተላለፉ ለዓለም በአደባባይ ቆመው የሚያስረዱ ስው ሰራሽ ሕያዉ ምስክሮች (ማስረጃዎች)ናቸው፡፡ አሁን ለመኖርም ይሁን ወደፊት ለማቀድ የኋላ ታሪክ ማወቅ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ዓለም ያወደሰው እውነታ ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህ የኋላ ታሪኮች(ጥንታዊ ሥልጦኔአችን)የሚናገሩ ቅርሶቻችን ከማንም በፊትና ከማንም በላይ… ነቅተን መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ሰማዕታት ከዚህ በላይ ሕይወታቸውን እስከ መስጠት ደርሷልና ነው፡፡

በተለይ ግን ለወጣቱ ትውልድ የምለው አንድ ነገር አለ፡፡ የነበረንን የታሪክ እውነታ(ሥልጣኔ)መርምረን ወይም ጠንቅቀን አውቀን ወላጆቻችን በዛ ዘመን ይህን የመሰለ አስደናቂ ተግባር (ታሪክ)ሠርተው ማለፋቸውን ጠቅሰን በዚህ በተሻለው ዘመን ደግሞ ከዛ ከጥንቱ ዘመን የተሻለ ታሪክ ለመሥራት ማቀድ ብቻ ሳይሆን መንቀሳቀስ ወይም በተግባር መተርጐም ብልህነት ይመስለኛል፡፡ ይህ ደግሞ ሳይሆን ቢቀር (የተሻለ ታሪክ መሥራት ሳይቻል ቢቀር ማለቴ ነው) የነበረውን ታሪክ በአግባቡ አጥንቶ ምንነቱንና ጥቅሙን በሚገባ ተረድቶ ሳይበረዝና ሳይከለስ በጥንቃቄ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግም እውቀትና ችሎታ ነው፡፡

ከዚህ ውጭ መሆንስ ምን ይሉታል? …. ከዚህ ውጭ መሆን ማለት ምን ትሉኝ ይሆናል፡-

 • ……የነበረውን ነገር ታሪክ ጠንቅቆ አዉቆ አሁን የተሻለ ታሪክ መሥራት መቻልና ለመሥራት ማሰብስ ይቅር፤ ታሪኩን በአግባቡ አውቆ ጥበቃ ለማድረግና ድርሻውን ለመወጣት አለመፍቀድና አለመፈለግ…. ምን ይባላል?.....
 • ……ይህም ደግሞ ይቅር የታሪክና የቅርስ ጸር እስከሚያስመልስብህ ድረስ አገራዊ ታሪክና ሃይማኖታዊ ቅርስ ሲነሳ የተቃውሞና የተቃርኖ ሓሳብና ድርጊት መፈጸምስ ምን ይባላል?
 • .... ከዚህም በላይ… ይሄስ አይሁን ወይም አያድርግ…. እንደውም አልተባለም እያሉ የሆነ የተፈጸመ ታሪክ እስከ ማንኳሰስ መድረስስ ምን ያሰኛል?......
 • ከላይ የተገለጸውንም ይሁን፤ ይህን ሁሉ አለመፈጸም ትልቅ ኃጢአት ሆኖ እያለ የግል ጥቅምና ፍላጐት ከሀገርና ከወገን ጥቅምና ህልውና በላይ በመመልከት እንኳንስ ሊሠራውና ሊያሳድገው፣ ሊያውቀው እንኳ ያልቻለ የአባቶች የታሪክ ማኀደር የሆነውን ቅርስ እየዘረፉና እያበላሹ….ለባዕድ አሳልፎ መሸጥስ ምን ይባላል?.…ወሰን የሌለው ፍላጐት ሕይወትን ሽጦ ሕይወትን ለማግኘት መፈለግስ ምን ተብሎ ይተረጐማል?.….እነዚህ በዘመኑ የነበሩ ለቅርሶቻችን ሲሉ ሕይወትና ደም አሳልፈዉ የሰጡ ሰማዕታት ይህ የአደራ ደማቸው በእነዚህ የቅርስ ቀሳጢዎች (ዘራፊዎች)ላይ ምን ይፈርድ ይሆን?.……አያድርገውና እነርሱ አሁን ኖረው ቢሆንና ይህንን የከሐዲዎች ተግባር ቢያዩ ምን ይሉ ኖሯል?.….መልሱ በተረጋጋ መንፈስ ሆናችሁ በቅንነት ለምታነቡት ውድ አንባቢዎቼ ትቼዋለሁ፡፡ ፍርዱንም እውነተኛ ዳኛ ለሆነ ሕሊናችሁ ሰጥቼዋለሁ፡፡

ወደ መነሻችን እንመለስና ከእነዚህ ሰማዕታት ቅርሳችን በአግባቡ መጠበቅ የሕይወትና የደም አደራ አለብን፡፡ ቅርስንና መሰል እሴቶችን በተመለከተ በሌላ ርእስ እንገናኝ ይሆናል፡፡

የቅርሶቹ አቀማመጥ፡-

በደብረ ምሕረት ጨለቆት ሥለሴ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ ጥንታውያን ቅርሶች በአጠቃላይ በትንሽና ጠባብ ዕቃ ቤት ላይ ተከማችተው ይገኛሉ፡፡ የዕቃ ቤቱ ጥበትና የቅርሶቹ ብዛት ስላልተጣጣመ አንዱ በአንዱ ላይ ተደርቦም ጭምር ተቀምጦአል፡፡ ከእነዚህ ቅርሶች ውስጥ በብዛትና በጥንታዊንት የሚታወቁት የብራና መጻሕፍት ዋናዎቹ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በደብረ ምሕረት ጨለቆት ሥለሴ ቤተ ክርስቲያን ከአንድ መቶ ሃምሳ ስድስት በላይ ጥንታውያን የብራና መጻሕፍት በተለያዩ ጥንታዊ የጥበብ ሥልጣኔ የተዋቡ፣ በሃይማኖታዊ ሐረግ ያጌጡ…ከመሆናቸው በላይ ሦስት ዓይነት ደረጃ ወይም መጠን አላቸው፡፡ እነርሱም ትንሽ፣ ትልቅና በጣም ትልቅ የሆነ መጠን ያላቸው መጻሕፍት ናቸው፡፡ በጣም ትልቅ የሆኑ መጻሕፍት ከግዝፈታቸውና ከክብደታቸው የተነሳ በአራት ሰው እንኳ ለማንሳት በጣም ያስቸግራሉ፡፡

በደብረ ምሕረት ጨለቖት ሥላሴ ከሚገኙ ጥንታውያን መጻሕፍት መካከል በታላላቅ ሙሁራን ሳይቀር አድናቆትን ያተረፈና የተሟላ ይዘት እንዳለው የሚነገርለት መጽሐፍ “ሃይማኖተ አበው”ነው፡፡ በዚህ ደብር የሚገኝ “ሃይማኖ አበው”በብዛትም ሆነ በይዘት አሁን በመንበረ ፓትርያርክ እየታተመ ከሚገኘው ተመሳሳይ መጽሐፍ የበለጠ ይዘት እንዳለው ሙሁራን ይስማማሉ፡፡ ምስጢሩ በዚህ አዲሱ እትም ላይ የማይገኙ ምንባባት በጨለቖቱ ሃይማኖተ አበው ላይ ይገኛልና ነው፡፡

ሁለተኛም መጽሐፉ በውስጡ ብዛት ያላቸው የተለያዩ የደራስያኑ ሥዕልና ሁለት ትላልቅ ሥዕሎች ያካተተ መጽሐፍ ነው፡፡ ለምሳሌ “ይቤ ጐርጐርዮስ ዘእንዚናንዙ በእንተ ትሥጉተ አምላክ”ብሎ የሚጀምር ምንባብ ከሆነ አስቀድሞ የቅዱስ ጐርጐርዮስን ሥዕል ያስቀምጣል ማለት ነው፡፡ ሁለቱ ትላልቅ ሥዕሎችን በተመለከተ ደግሞ አንዱ መድኃኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ከፍ ባለ ተራራ ላይ ሆኖ ደቀ መዛሙርቱንና

ለተሰበሰበው ሕዝብ ወንጌለ መንግስትን ሲያስተምር የሚያሳይ ሲሆን ሁለተኛው ግን የጉባዔ ኒቂያ ሁኔታን በተመለከተ የሚገልጽ ታሪካዊ ሥዕል ነው፡፡ የዚህ መጽሐፍ ሥዕላዊዘት ይበልጥ ለአንባቢዎች  እንዲሆን

በፎቶ መልክ ቀርቧል፡፡ ከዚህ በመመልከት ጥበቡም ማወቅና ማድነቅ ይቻላል፡፡

እነዚህ ጥንታውያን ቅርሶች በሕብረት በጠባብ ዕቃ ቤት መቀመጣቸው ለብልሽት ስለሚዳርጋቸው መምህር ያሬድ ከላይ እንደጠቆሙት/የመምህር ያሬድ ጽሑፍ አቡነ መርሐ ክርስቶስ ከመሞታቸው አስቀድሞ የተዘጋጀ ስለነበረ ነው/በረከታቸው በእውነት ያለ ሐሰት ይደርብንና ብፁዕ አባታችን አቡነ መርሐ ክርስቶስ ሊቀ ጳጳስ በደብሩ ላይ ሁሉንም ቅርሶች በአግባቡ ይዞ ለጐብኝዎች ሙሉ እውቀትን ለቅርሶቹ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር አነስተኛ ሙዝየም ለማሠራት አቅደው እግዚአብሔር እንደፈቀደውና አቅማቸው ወይም ዓረፍተ ዘመን እስከገታቸው ድርስ በትጋትና በቅንነት ተንቀሳቅሰው የሙዝየሙ ግንባታ እንደተጀመረ ብፁዕ አባታችን አቡነ መርሐ ክርስቶስ በረከታቸው ይደርብንና ዓረፍተ ዘመን ገቷቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡

ሙዝየሙ በጥሩ ሁኔታ ተጀምሮ አሁንም በደብሩ ሰበካ ጉባኤንና በደጋግ የአካባቢው ተቆርቋሪዎች ግንባታው ከግማሽ ደርሶ ተመልክተነዋል፡፡ መልአከ ምሕረት ታደሰም ለዚህ ግንባታና መጀመር ፍጻሜውም ለማየት ብፁዕነታቸው የነበራቸው ፍላጎትና ምኞች ገልጸው ብፁዕነታቸው ከሞቱ በኋላ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ መቆሙን አስረድተውናል፡፡ መልአከ ምሕረት አያይዘውም ደጋግ ምዕመናንና ምዕመናት ብቻ ሳይሆን ይህ የሀገር ሀብት የወገን ኩራት የሆነ ቅርስ የሚቀመጥበት ባለአደራ ሙዝየም ስለሆነ ሀገር ወዳድ የሆነ ሁሉ፣ መንግስታዊ ድርጅቶች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች…ወዘተ የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉና ይህን ሙዝየም ከፍጻሜ እንድናደርስ ሁላችሁም በተቻላችሁ መጠን አግዙን በማለት አደራዊ ወአባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅም ለአንባቢዎች የሙዝየሙ ሥራ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ አይተው “እኛስ ምን እናድርግ” በማለት ሕሊናዊ ድርጊት እንዲቀሰቅስ በማለት በፎቶ አዘጋጅቶ አቅርቧል፡፡

ሙዝየሙ ቢያልቅ የሚሰጠው ጥቅም

 • ቅርሶቹ በተመቻቸ ሁኔታ ደኅንነታቸው ተጠብቆ አንዲቀመጡ ይረዳል፤
 • ጐብኝዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉንም ቅርሶች መመልከት ያስችላል፤
 • ለተመራማሪዎች ጊዜን ይቆጥባል፣ ያበረታታል፣ ይስባል… ወዘተ፤
 • የቅርሶቹ ዕድሜ የበለጠ ያራዝማል ከሰው ሰራሽ ጥቃቅን አደጋዎች ይጠብቃል፤
 • ለደብሩ ጥሩ የገቢ ምንጭ በመሆን ሊያገለግል ይችላል፤
 • ቅርሶቹ በአግባቡ ተጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ ይረዳል…

 … እነዚህንና ከዚህም በላይ የሆነ ጥቅም የሚያበረክተው ይኸው ሙዝየም አሁን ካለበት ደረጃ በማንሳት እስከ ፍጻሜ ድረስ በተቻለን መጠን እና በምንችለው ሁሉ እጅ ለእጅ ተያይዘን የመፈጸም ሃይማኖታዊ ብቻም ሳይሆን ሃገራዊ ግዴታም ጭምር እንዳብን ሳሳስብ በፍጹም ወንድማዊ ፍቅር ነው፡፡

በመሆኑም ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ከእኛ በላይ ለእኛ የሚቀርበንና ችግራችን የሚፈታልን ስለሌለ ይህ ጉዳይም በተዘዋዋሪ ዓለም በሙሉ ይመለተዋል እንኳ ቢባልም በቀጥታ ግን የሚመለከተን እኛን ነው፡፡
ስለሆነም ሙሁራን በእውቀታችን፣ ባለጸጎች በሃብታችን፣ ደካሞች በጸሎታችን…ይህን የብፁዕ አባታችን የአቡነ መርሐ ክርስቶስ ልጅ የሆነውን ሙዝየም በረከታቸውንም ጭምር እንዲያድርብን ከፍጻሜ ማድረስ የውሉደ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን የውሉደ ኢትዮጵያ የፍቅር ግዴታችን ነው ስል ከትልቅ አክብሮት ጋር ነው፡፡

በረከታቸው ይደርብንና የብፁዕ አባታችን አቡነ መርሐ ክርስቶስ ሊቀ ጳጳስ የተወለዱበት፣ የተማሩበትና ከእልቅና ጀምሮ እስከ ጵጵስና ድርስ በትጋት ያገለገሉት በዚሁ ደብራቸው ደብረ ምሕረት ጨለቖት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በመሆኑና የዘመን ፍጻሜአቸው በደረሰ ጊዜም መካነ መቃብራቸው በዚሁ ታላቅና ታሪካዊው ደብር ስለሆነ የብፁዕ አባታችን ሕይወት ታሪክ ከዚህ ቀጥዬ አቀርባለሁ፡፡

የብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ ሕይወት ታሪክ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ዜና ሕይወቱ ወዕረፍቱ ለብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ ሊቀ ጳጳስ

ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ መጋቢት 25ቀን 1921ዓ.ም በትግራይ ክልል በጨለቖት ሥላሴ ተወለዱ፡፡ አባታቸው ቄስ ግርማይ ገብረ ኢየሱስ እናታቸው ወ/ሮ ታደለች ተክለሃይማኖት ይባላሉ፡፡ ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ የመጀመሪያው የአብነት የትምህርት ደረጃ ከሆነው ከፊደል መቁጠርና ንባብ ጀምሮ ዳዊትና ምስጢረ ሥላሴ ከአባታቸው ከቄስ ግርማይ ገብረኢየሱስ ተማሩ፡፡ ድጓ፣ ምዕራፍና አቋቋም ደግሞ ተወልደው ባደጉበት በኋላም እስከ እልቅና ድረስ ባገለገሉበት ደብራቸው በደብረ ምሕረት ጨለቖት ሥላሴ ከመምህር ቀለመወርቅ ፍትዊ ዘልቋል፡፡

በቆቦ አውራጃ ዞብል ወረዳ በአንጐት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ከሊቀ ኅሩያን ወልደ ሰንበት ቅኔ ተቀኝቷል፡፡ በጥንቱ አጠራር ወደ ሸዋ ክፍለ ሀገር ሄደው በሰላሌ አውራጃ በመድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያነ ከመምህር ጥበቡ ገሜ የቅኔ ትምህርታቸውን በማስፋፋት ቅኔ እስከነ አገባቡ ድረስ በሚገባ ቀጽለው ካደላደሉ በኋላ በቅኔ መምህርነት ተመርቋል፡፡

ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ የቅኔ ሞያቸው እጅግ አድርገው ለማስፋፋት ወደ ጐጃም ክፍለ ሀገር በመሄድ በዋሸራ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከማዕበል ፈንቴ ዋሴ፣ በደብረ መዊእ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከመምህር ቃለ ማዕነቅ ተሰማ የቅኔ ጐዳና ተምረው በሚገባ አደላድሏል፡፡ የቅኔ ትምህርታቸው ጠንቅቀው ከተመረቁ በኋላ በጐጃም፣ በወይበላ ቅዱስ ሚካኤል፣ በደብረ ኢየሱስና ዲማ ጊዮርጊስ እየተዘዋወሩ ቅኔ አስተምሮአል፡፡

ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ በዜማና በቅዳሴ ብቻ ተወስነው መኖር ስላልፈለጉ ወደ ሞጣ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመሄድ ከመምህር ልየው የሐዲሳት መጻሕፍት ትርጉም ከተማሩ በኋላ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከአለቃ ኅሩይ ፈንታ በሞጣ የተማሩት የሐዲሳት መጻሕፍት ትርጉም አደላድሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት አንድምታ በአዲስ አበባ ከዶ/ር አለቃ አየለ ዓለሙና ከአለቃ ጥሩነህ ካሳ ጠንቅቀው፣ አራቅቀውና አመሳጥረው ተምሯል፡፡ የመጻሕፍተ ሊቃውንት /የሃይማኖተ አበው/ አንድምታ ትርጉምም በአዲስ አበባ ከኅሩይ ፈንታና ከሊቀ ሊቃውንት ሞገስ፤ በደሴ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ከመምህር ገብረ እግዚአብሔር በሚገባ አደላድለው ተምሯል፡፡ ቀጥለውም በዚህ ገዳም ከመምህር ገብረ እግዚአብሔር ለሦስተኛ ጊዜ አድርሰው ትምህርቱን ፈጽሟል፡፡

ሥልጣነ ክህነትና አገልግሎት በሚመለከት

ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ ዲቁና ከአቡነ ይስሐቅ ተቀብሏል፡፡ ምንኩስና በደብረ ሊባኖስ ገዳም ከመነኮሱ በኋላ ቅስናም ከብፁዕ አቡነ ይስሐቅ ተቀብሏል፡፡ ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶሰስ በአዲስ አበባ በታዕካ ነገሥት ባዓታ ለማርያም መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ከ1958–1982ዓ.ም ግእዝ ቋንቋንና የሥነ ምግባር ትምህርት እያስተማሩ በመምህርነት አገልግሏል፡፡ በክልል ትግራይ መቐለ በዓታ ለማርያም ሐዲሳት፣ ግእዝንና ቅኔን በማስተማር ወንጌልን አብዝተውና አምልተው በመስበክ አገልግሏል፡፡

ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ በ1971ዓ.ም ሕገ ቤተ ክርስቲያን በሚፈቅደው ቀኖና መሠረት የሞያ ብቃታቸውና መንፈሳዊ ሕይወታቸው ታይቶና ተመርምሮ ለጵጵስና ብቁ ሆነው ስለተገኙ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተመርጠው በሦስተኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አንብሮተ ዕድ ጵጵስና ተሹሟል፡፡ እሰከ 1973ዓ.ም የኤርትራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው አገልግሏል፡፡ ከዚህ በኋላ በቅዱስ ሲኖዶስ መልካም ፈቃድ በ1973ዓ.ም ወደ ድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ተዛውረው የድሬዳዋ ሊቀ ጳጳስ ሆነው እስከ 1977ዓ.ም በቅንነት፣ በትጋትና በብቃት ሀገረ ስብከቱን መርቷል፣ አገልግሏል፡፡

ከ1977–1980ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ መልካም ፈቃድ ከድሬዳዋ ወደ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ተዛውረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ጉባዔ ሰብሳቢ በመሆን አገልግሏል፡፡ ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ ከ1981 -1983ዓ.ም ተመልሰው የድሬደዋና የምዕራብ ሐረርጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመሆን የተቃና አገልግሎት አበርክቷል፡፡ ከ1983 -1985ዓ.ም ተቀይረው ወደ ትግራይ በመሄድ “ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዘኩላ አድያሚሃ”ሆነው በመመደብ ሠርቷል፡፡ ብፁዕነታቸው በ1985ዓ.ም እንደገና ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ተዛውረው የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ዲን ሆነው እሰከ 1989ዓ.ም መርቷል፣ አስተምሯል፡፡ በዚህም ብዙ ደቀመዛሙርትን አፍርቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የበላይ ኃላፊ በመሆን ቀና አገልግሎት አበርክቷል፡፡

ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ ከ1989–1990ዓ.ም የሃይማኖታዊ ፍልስፍናና ርቀት ማእከል የሆነውን የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዲን ሆነው ኮሌጁን በማስተዳደርና ለብዙ ደቀ መዛሙርት ትምህርት ሃይማኖትን በማስተማር አገልግሏል፡፡ ከ1990–1992ዓ.ም እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ትግራይ ክልል ተመልሰው“ሊቀ ጳጳስ ዘትግራይ”ሆነው አገልግሏል፡፡ ከ1992ዓ.ም ጀምሮ ከዚህ ዓለም በሞት እስከ ሚለዩ ድረስ የመቐለ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በመሆን በትጋት አገልግሏል፡፡

ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ ወንበር ዘርግተው፣ ጉባዔ አስፍተው ከማስተማርና ወንጌል ከመስበክ በተጨማሪ ትምህርተ ሃይማኖት የያዙ መጻሕፍት /ያልታተሙ/አዘጋጅተው ለነገረ መለኮት ተማሪዎቻቸው በማበርከት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በተደረጋላቸው ጥሪ መሠረት ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ወደ አዲስ አበባ መንበረ ፓትርያርክ መጥተው የመጡበትን ሐዋርያዊ ተልዕኮአቸውን በሚገባ ከፈጸሙ በኋላ ባደረባቸው ደንገተኛ ሕመም ምክንያት አጅግ አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ ጥር 28 ቀን 2002ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡

በረከታቸው ይደርብንና የብፁዕ አባታችን አቡነ መርሐ ክርስቶስ አስካሬን ከአዲስ አበባ ወደ ሀገረ ስብከታቸው/መቐለ/ተሸኝቶ በመንበረ ጵጵስናቸው ማህደረ ስብሐት ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተክርስቲያን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዝደንት መሪነት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ሙሉ ጸሎተ ፍትሐት ከተደገረላቸው በኋላ በብፁዕ ወቅዱስ አባታችን፣ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ በክቡር አቶ ፀጋዬ በርሀ የክልሉ ፕሬዝዳንትን ጨምሮ በመንግስት ባለሥልጣናት፣ በካህናትና በምዕመናን አንዲሁም በሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን ወጣቶች አስከሬናቸው ታጅቦ ወደ ተወለዱበት ደብር ደብረ ምሕረት ጨለቖት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተወስዶ ጥር 29 ቀን 2000 ዓ.ም ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡

ማንም እንደሚረዳው ብፁዕ አባታችን አቡነ መርሐ ክርስቶስ ሊቀ ጳጳስ በምጡቅ ትምህርተ ሃይማኖት እውቀታቸው፤ በአመስጥሮ መጻሕፍት ችሎታችው በአእምሮ ሥርዓተ ቤ/ክርስቲያን ታላቅ የቤተክርስቲያን ሊቅ ነበሩ፡፡ በማኅሌታዊነታቸውና በቅኔ አዋቂነታችው እጅግ የተደነቁ በሁሉም የቤተክርስቲያን ሙያ የሚጠየቁና ጥልቅ እውቀት የነበራቸው አራት ዓይና ታላቅ ሊቅ አባት ነበሩ፡፡

የብፁዕ አባታችን አቡነ መርሐ ክርስቶስ በረከታቸው ይደርብን
አሜን!!

የፎንት ልክ መቀየሪያ