Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መምህራን ወንጌልን እንዴት ማስተማር አለባቸው?

በመምህር ሙሴ ኃይሉ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት
የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ምክትል የመምሪያ ኃላፊ

መድኃኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ለቀደ መዛሙርቱ ከሰጣቸው ዓበይት የሐዋርያዊነት ተልዕኮ ትልቁ ወይም ቀዳሚ የሆነው ምስጢር ወንጌለ መንግስትን በዓለም ዙርያ እንዲያስተምሩ የሚያዝ ተልዕኮ ነው፡፡

 • "እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው" ማቴ. 28፡19-20 እንዲል፡፡

ይህንን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትእዛዝ ለመፈጸም አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት (የቤተ ክርስቲያን መምህራን) በመንፈሳዊ ጥበብ እጅግ የተካኑ ከመሆናቸው የተነሣ የተለያዩ መንፈሳዊና ማኅበራዊ እሴቶችን ምክንያት በማድረግ በረቀቀ ስልት ተጠቅመው ወንጌልን በሚገባ አስተምረው አልፈዋል፡
በመሆኑም ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ፡- "የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አሰቡ፤ የኑሮአቸውም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምስሉአቸው" /ዕብ. 13፡7/ በማለት እንዳስተማረን አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት እንዳስተማሩን ከጌታችን የተሰጣቸውን አምላካዊ ወንጌልን የማስተማር ተልዕኮ በሚገባ ፈጽመው እንዳለፉ ሁሉ እኛም አባቶቻችንን መስለን የእነርሱ ትውፊታዊ ወንጌልን የማስተማር ጸጋ ወይ ስልት ተከትለን የማስተማር ግዴታም ጭምር አለብን፡፡

 • "በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፤ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ነው" ኤፌ.2፡20 እንዲል፡፡

ከላይ እንደተገለጸው እነዚህ እውነተኞች የቤተ ክርስቲያን መምህራነ ወንጌል ለዓለም ሁሉ ለማዳረስ የተጠቀሙበት የትርጉምማስተማር ስልት እጅግ በጣም ብዙ ቢሆንም በዚህ ጽሑፍ ግን ጠቅለል በማድረግ በሦስት ዋና ዋና ክፍል በመክፈል እንመለከታለን፡፡

1. ምስጢረ መጻሕፍትን አራቅቀው በመተርጎም /ተምረው በማስተማር/

እንኳንስ ረቂቅ የሆነ መንፈሳዊ ትምህርት ሥጋዊ ትምህርትም ቢሆን ለማስተማር ቅድመ ሁኔታው ከሊቃውንት መምህራን ዘንድ ተገኝቶ መማር እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ምክንያቱም ሳይማሩ ማስተማር አንድም ፈጽሞ የማይቻል ነው፤ በድፍረትና በክፉ ልቡና በመነሳሳት ደግሞ ይሁን ቢባል መንገዱን እንደማያውቅ መንገደኛ መነሻና መድረሻውን፤ ወሰኑንና ድንበሩን ስለማያውቅ በማያውቀው ትምህርት ወደማያውቀው ስሕተት ያመራል፡፡ በመሆኑም በአግባቡ ስለሚያስተምሩት /ስለሚናገሩት/ ትምህርት ሳይማሩ ማስተማር በእግዚአብሔር ዘንድ ያልተፈቀደና የሚያስወቅስ የፈሪሳውያን ሕይወት ነው፡፡

 

 • "ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፡- መጻሕፍትንና የእግዚአብሔር ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ አላቸው" ማቴ. 22፡29

 • "መጻሕፍትንና የእግዚአብሔር ኃይል አታውቁምና ስለዚህ የምትስቱ አይደላችሁምን? ማር. 12፡24 እንዲል

 

መንፈሳዊ ትምህርት ከፍጡራን አእምሮ እጅግ በጣም የረቀቀ የሰማያዊውን ሕይወት የሚያትት ምስጢር ስለሆነ ያለ አስተማሪ መጻሕፍትንና ምስጢራዊ ትርጉማቸውን ጠንቅቆ ማወቅ እጅግ ከባድ ነው፡፡ ስለሆነም ያለ አስተማሪ የተጻፉ መጻሕፍትን በማንበብ ለመተርጎም መሞከርም ትልቅ ስሕተትና የተከለከለም ነው፡፡ ምክንያቱም ያለትርጉም ንባብ ብቻ መከተል ስሕተት ውስጥ ይጥላል ነውና ነው፡፡

 • "ፊደል ይገድላልና መንፈስ /ትርጉም/ ግን ሕይወትን ይሰጣል" 2ኛቆሮ.3፡6 እንዲል፡፡

ከዚህ እውነታ በመነሳት የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ለማስተማር መጀመርያ ስለ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ምስጢር /ትርጉም/ በሚገባ ከሊቃውንት ዘንድ ተገኝቶ ከትምህርት ቤት ገብቶ መማርና ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
እነዚህ ምሳሌዎቻችን የሆኑ ቀደምት የቤተ ክርስቲያን መምህራን የመረጡትም ለማስተማር ከመሰማራታቸው አስቀድመው የክርስትናን ትምህርት በሚገባ ይማሩና ምስጢሩንም ይጠነቀቁ ነበር፡፡ ለምሳሌ፤

1. 1. ጌታችን ለደቀ መዛሙርቱ እንዲያስተምሩ ያሰማራቸው መጀመሪያ አስተምሮ ነው፡፡

መድኃኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በባሕረ ዮርዳኖስ ተጠምቆ ዓርባ ቀንና ሌሊት ከጾመ በኋላ የመጀመሪያ ሥራ ያደረገው ደቀ መዛሙርትን መምረጥ ነበረ፡፡ ምክንያቱም የጌታችን አምላካዊ የድኅነት የምሥራች /ወንጌል/ ወደ ዓለም ሁሉ የሚያደርሱ እነርሱ ናቸውና ነው፡፡ ሉቃ.6፡13፤ ማቴ.8፡22፤ ማር.2፡14፤ ሉቃ.5፡27፤ ዮሐ.1፡44፡፡
እነዚህን የጠራቸው ደቀ መዛሙርቱ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዋለበት እየዋሉ ካደረበት እያደሩ ሁሉንም ትምህርተ ክርስትና ካስተማራቸው፤ ምስጢረ ክርስትናም ካሳያቸው በኋላ ብቁ መሆናቸውን አረጋግጦ ለዓለም ያዩትን ድንቅ አምላካዊ ተአምራትን እንዲመሰክሩ፣ የተማሩትን የወንጌል ትምህርት እንዲያስተምሩ ታላቅ ተልዕኮ ሰጣቸው፡፡

 • "በጨለማ የምነግራችሁን በብርሃን ተናገሩ፤ በጀሮም የምትሰሙትን በሰገነት ላይ ስበኩ" ማቴ. 10፡27

 • "ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ" ማር. 16፡15 እንዲል፡፡

አማናዊ መምህረ ወንጌል ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያት መምህራን ቤተ ክርስቲያን አድርጎ ወደ ዓለም ሲልካቸው ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ሊፈጽሙበት የሚያስችላቸውን የክህነት ስልጣንም ሰጥቶና አክብሮ ነው፡፡

 • "አብ እንደላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው፡፡ ይህም ብሎ እፍ አለባቸውና መንፈስ ቅዱስ ተቀበሉ፡፡ ኃጢአታቸው ይቅር ያልኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል" ዮሐ.20፡21-23፡፡

 • "የመንግስተ ሰማያትንም መክፈቻ እሰጥሃለሁ፣ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፡፡ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል" ማቴ. 16፡19 እንዲል፡፡

ይህ የሚያስገነዝበን የቤተ ክርስቲያን መምህራን የተመሰለውን ተርጉመው፣ ያልተመሰለውን መስለው በምስጢር የሚያራቅቁ የወንጌል መምህራን የክህነት ስልጣንም ገንዘብ ያደረጉ እንደሆኑ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ጥንታዊትና ሐዋርያዊት እንደመሆንዋ መጠን ይህንን ትውፊት በሚገባ በመጠበቅ የወንጌል መምህራን ሥልጣነ ክህነትንም ገንዘብ ያደረጉ እንዲሆኑ በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡

1.2. ሐዋርያትም አርድእቶቻቸው እንዲያስተምሩ የላኳቸው መጀመሪያ አስተምረው ነው፡፡

አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት "ኑና ተከተሉኝ" ብሎ የጠራቸው በኋላም "ሑሩ ወመሐሩ" ብሎ ወደ ዓለም መምህራነ ወንጌል አድርጎ የላካቸው አምላካቸውን አብነት አድርገው አርድእቶቻቸው አስቀድመው ቅዱሳን መጻሕፍትን ካስተማሩና ምስጢሩንም በሚገባ ካስረዱአቸው በኋላ በመጨረሻም ሥልጣነ ክህነትን በመስጠት ሀገረ ስብከት በመለየት እንዲያገለግሉ ይፈቅዱላቸው እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ለመንፈስ ቅዱስ ልጁ ለጢሞቴዎስ መጀመሪያ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ቅዱሳት መጻሕፍትን በሚገባ ካስጠናው በኋላ ስልጣነ ክህነት ሰጥቶ እንዲያስተምር መፍቀዱ ለዚህ ማስረጃ ነው፡፡

 • "አንተ ግን በተማርክበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፤ ከማን እንደተማርኸው ታውቃለህና፡፡ ከሕፃንነትህ ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳት መጻሕፍትን አውቀሃል" 2ኛጢሞ.3፡14-15 እንዲል፡፡

1.3. ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም ወንጌልን ያስተማሩት መጀመሪያ የቅዱሳት መጻሕፍትን ምስጢር በሚገባ ከጠነቀቁ በኋላ ነው፡፡

ሐዋርያትን መስለውና አኽለው የተነሱ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትም ይህንኑ የሐዋርያት ትውፊት በመጠበቅ ወንጌል ያለ አስተማሪ ማወቅ እንደማይቻል በመገንዘብ የሥነ መለኮት ትምህርት ቤት እንዲቋቋሙ አድርገዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችም በዚህ ትምህርት ቤት ገብተው የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጉም እንዲማሩና እንዲራቀቁ ከማድረጋቸውም በላይ ለትምህርተ ክርስትና ዕድገትም ዓይነተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ለዚህ መልካም ምሳሌ የሚሆኑን ከጥንታውያን የሥነ መለኮት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የእስክንድርያና የአንጾኪያ ትምህርት ቤቶች በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በመሆኑም ከሐዋርያት ቀጥለው የተነሱ ሊቃውንትም አስቀድመው በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ገብተው የቅዱሳት መጻሕፍትን ምስጢር በሚገባ ጠንቅቀው የተማሩና የተመራመሩ ስለነበሩ ቤተ ክርስቲያናቸውን መርተው ሕዝባቸውን በሚገባ አስተምረው እንዲሁም በየጊዜው ይነሱ የነበሩት የመናፍቃን ትምህርት መጻሕፍትን ጠቅሰው በመርታት መናፍቃኑም መክረውና ዘክረው በማረምና በማስተካከል፣ እምቢ ካሉም እውነቱን ከሐሰት፣ እምነቱን ከክሕደት አስረድተው በጉባኤ እንዲወገዙ አድርገው ከጌታችንና ከሐዋርያት ተዋረዱን ጠብቆ የመጣውን ንጹሕ ትምህርት ሳይበረዝና ሳይከለስ ለትውልድ እንዲተላለፍ በማድረግ በቤተ ክርሰቲያን ታሪክ ውስጥ ወርቃማ ትሩፋት የፈጸሙት ከማስተማራቸው አስቀድመው ትምህርተ ክርስትናውን በመማራቸው ነው፡፡
ለምሳሌ አርዮስን የረታው ቅዱስ አትናቴዎስ፣ ንስጥሮስን የረታው ቅዱስ ቄርሎስ፣ ከጣዕመ ስብከቱ የተነሳ "አፈ ወርቅ" የተባለው ቅዱስ ዮሐንስ ከተጠቃሾቹ የቤተ ክርስቲያን መምህራን ወገን ናቸው፡፡
ከዚህ እውነታ የምንረዳው በታሪክ መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ሳይማር በድፍረትና በትዕቢት ላስተምር ብሎ ያስተማረ አለመኖሩን ነው፡፡ ተምሮ ማስተማር ቀኖናዊ ከመሆኑም በተጨማሪ በሠላሳ ፣ በስልሳና በመቶ ትርፋማ የሚያደርግ የስብከት ዘዴ ነው፡፡
በዚህ በዘመናችንም ለማስተማር መማር የሚያስቀድሙ እውነተኞቹ የቤተክርስቲያን መምህራን እንደሚጠቀሱ ሁሉ ሳይማሩ በድፍረት ለማስተማር የሚቆሙ እንዳሉም ማወቅና መገንዘብ ብልህነት ነው፡፡
እኛም በተለይ በወንጌል አገልግሎት የተሰማራን ወንጌላውያን ሁላችን ከዚህ ህያው የክርስትና የታሪክ ተዋረድ ጥልቅ ግንዛቤ በመውሰድ ዘመን ከወለደው ምስጢር አልባ ከንቱ ልፍለፋና ክርክር ርቀን እንደ ቀደሙ አባቶቻችን ትምህርተ ቤተ ክርስቲያናችንን በሚገባ ተምረን፣ የተማርነውን ትምህርት ላልተማሩ ወገኖቻችን በማስተማር ክርስቲያናዊ የፍቅር ግዴታችን (አገልግሎታችን) መወጣት ይኖርብናል፡

 • "በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ አስተምሩና ገሥጹ በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊ ቅኔ በጸጋው በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ" ቈላ. 3፡16 እንዲል፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር ኪያነ ዘፈጠረ ከመ ናምልኮ፣ /ልናመልከው እኛን ለፈጠረ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን/

ይቀጥላል .......

የፎንት ልክ መቀየሪያ