Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ "በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዝክረ ቅዱስ ያሬድ" በሚል ጥር 5 ቀን 2005 ዓ.ም በተካሄደ ታሪካዊ ጉባኤ

 • ዜማ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

 • ዜማ ምንድን ነው?

በንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ

የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ


ዜማ ማለት ጣዕምና ለዛ ባለው ድምጽ ማቀንቀን፣ ማንቆርቆር ማለት ነው፤ የተጀመረውም በጥንተ ፍጥረት በመላእክት አንደበት ነው፤ መላእክት እንደተፈጠሩ በዜማ ፈጣሪያቸውን አመስግነዋል(ኢዮ.38፡6)፤ ከመጀመርያው ጀምሮ እግዚአብሔር ሰውንና መላእክትን መፍጠሩ ስሙን አመስግነው ክብሩን እንዲወርሱ ነውና በዜማ ማመስገን መደበኛ የሰማያውያን ሥራ መሆኑን በዚህ እንገነዘባለን፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ይህንን ረቂቅ ሀብት በባርህያቸው ውስጥ እንደ አንድ መሠረታዊ ፍላጎት አድርጎ ፈጥሮላቸዋል፡፡ ዜማን የመውደድ ተፈጥሮአዊ ዝንባሌ በመላእክትና በሰዎች ጎልቶ ይታይ እንጂ ከነሱም ሌላ ሕይወት ባላቸው ሌሎች ፍጡራንም የሚታይ ነው ለምሳሌ የወፎች ዜማ መጥቀስ ይቻላል፡፡

ከዚህ ተነሥተን የዜማን አመጣጥ ስናስተውል እግዚአብሔር አምላክ በዜማ መመስገን ፈቃዱ ስለሆነ ፍጡራን በተፈጥሮአቸው ዜማን እንዲወዱ አድርጎ እንደፈጠራቸው እንገነዘባለን፡፡
ጣዕሙና ይዘቱ ይለያይ እንጂ ሰዎች ከተፈጠሩበት ጊዜ ጀምሮ ከዜማ የተለዩበት ጊዜ የለም፤ ጥንትም ሆነ ዛሬ ሰዎች ዜማን ለተለያየ ነገር ሲጠቀሙበት ይታያል፡፡ ለምሳሌ ለአምላክ መመስገኛ፣ ለደስታ፣ ለሐዘን፣ ለልመና፣ ለቀረርቶና ለሽለላ እንዲሁም ለትዝታ መቀስቀሻ ወዘተ ይጠቀሙበታል፣ ዜማ ለነዚህ ሁሉ የጋራ መጠርያቸው ነው፡፡ ይሁንና ዜማዎች ሁሉ አንድ ዓይነት ባህርይ ያላቸው አይደሉም፣ በመሆኑም የተለያየ ስም አላቸው፡፡ ለምሳሌ የሃይማኖቱ ዜማ፣ ዝማሬ፣ መዝሙር፣ ማኅሌት፣ የደስታው ዘፈን፣ የሐዘኑ ልቅሶ ይባላሉ፤ እነዚህ ሁሉ በዜማ ስልታቸው፣ በሥነ ቃላቸውና በእንቅስቃሴአቸው የተለያዩ ናቸው፡፡

የሃይማኖት ዜማ የራሱ የሆነ የእንቅስቃሴ ስልት፣ የኃይለ ቃል ምጥቀት፣ የሥነ ቃልና የምሥጢር ቅንብር ስላለው ከሌሎቹ ሳይደባልቁ ራሱን አስችሎ ማስኬድ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ አለበለዚያ ግን ከራሱ ጠባይ ወጥቶ ከዘፈኑም ከቀርርቶውም ከተደባለቀ ሕዝቡ የሃይማኖትን ዜማ ከዘፈን ለመለየት ይቸገራል፤ ዜማው ከዘፈን ጋር ሲመሳሰል ክብርና ልዕልና ያጣል፣ ማንም ዘፋኝ እንደሚቀባጥረው ተራ ነገር መስሎ እንዲታይ ይሆናል፤ ተመስጦ አይሰጥም፣ ተወዳጅነትና ተቀባይነትም ያጣል፣ ስለሆነም የሃይማኖት መዝሙር ይህንን ሁሉ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በጥንቃቄ ሊዘጋጅና ሊዘመር የሚገባ ነው፡፡

እንግዲህ ስለዜማ አመጣጥና አጠቃቀም በአጭሩ ይህንን ካልን ዜማ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚለውን ከዚህ ቀጥሎ እናያለን፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዜማ

ዜማ ከሰዎች ባሕርይ ጋር በተፈጥሮ የተቈራኘ እንደሆነ ከላይ በተገለጸው መሠረት ኢትዮጵያውያን ከቅዱስ ያሬድ በፊት ዜማ አልነበራቸውም ማለት ባይቻልም እጅግ አስደናቂና በዓለም ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በግእዝ፣ በዕዝልና በዓራራይ የተቀነባበረ ዜማ የተከሠተው በ6ኛው ክፍለ ዘመን በታላቁ ሊቅ በቅዱስ ያሬድ አማካይነት ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ የተወለደው በ505 ዓ.ም ሚያዝያ 5 ቀን ሲሆን ወላጆቹም ከካህናተ አኲስም ወገን ነበሩ፤ ቅዱስ ያሬድ በሕፃንነቱ ወቅት ትምህርት አልገባ ብሎት ብዙ ጊዜ ተጕካልቶአል፤ ከጊዜ በኋላ ግን እግዚአብሔር በገለጸለት የአንድ ትል ጥረት ምልክትነት በመጽናናትና እግዚአብሔርን በመለመን መማሩን ስለቀጠለ ችግሩ ተወግዶለት በአጭር ጊዜ ብሉያትን፣ ሐዲሳትን ሊቃውንትንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ ተምሮ በማወቁ የአኲሱም ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህን ሆኖ ለብዙ ዓመታት አገለገለ፡፡

ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር "ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኅበ እግዚአብሔር" ማለትም "ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ታደርሳለች" (መዝ.87፡31) "ይገንዩ ቅድሜሁ ኢትዮጵያ" ማለትም የኢትዮጵያ ሰዎች በፊቱ ያመሰግናሉ (መዝ.71፡9) ሲል በቅዱስ ዳዊት አድሮ የተናገረውን የኢትዮጵያን ልዩ ዜማዊ ምስጋና ይፈጸም ዘንድ ቅዱስ ያሬድን ለዚህ ትንቢት መፈጸም መርጦአል፡፡ ለዚህ ታላቅ ዕድል የተመረጠው ቅዱስ ያሬድም በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደ ሰማይ ወጥቶ፤ የመላእክትን ዜማ አዳምጦ፣ ያዳመጠውን ጣዕመ ዜማ አጥንቶ ወደ አኲስም ጽዮን ማርያም ዓውደ ምሕረቱ በተመለሰ ጊዜ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በየትኛውም ክፍለ ዓለም የሌለ ሰማያዊ ዜማ አበርክቶላታል፡፡ ዜማው ለመጀመርያ ጊዜ የተሰማበት የአኲስም ጽዮን ዓውደ ምሕረትም "ሙራደ ቃል" የሚልና ከታሪኩ ጋር የተገናዘበ ስም ተሰጥቶታል ይህ ስያሜ ዜማው ከሰማይ የወረደ መሆኑን በግልጽ ያሳያል፡፡ ዓውደ ምሕረቱ እስከዛሬም ድረስ በዚህ ስም ሲጠራ ይገኛል፡፡ በአኲስም ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ዓውደ ምሕረት ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘመረውና የተዜመው ዜማም አርያም ይባላል፡፡ አርያም ማለት ከፍ ያለ ቦታ ማለት ነው፤ ከፍ ያለ ቦታ የተባለም ሰማይ ነውና ከሰማይ የተገኘ መሆኑን አሁንም በግልጽ ያሳያል፡፡ የዜማው ባለቤት ቅዱስ ያሬድም "ዋይ ዜማ ዘሰማዕኩ በሰማይ እመላእክት ቅዱሳን..." ሲል ተናግሮአል፤ ትርጓማውም ወይ ዜማ በሰማይ ሳለሁ ከቅዱሳን መላእክት የሰማሁት ማለት ነው፡፡ በሌላም ድርሰቱ ስለዜማው ሰማያዊነት ሲያስረዳ ሰማየ በአብ ወበወልድ አርያመ ወበመንፈስ ቅዱስ ኅበ ዐረጉ ሰማዕኩ እመላእክት ዝማሬ ብሏል የዚህም ትርጓሜ በአብ ወደ ሰማይ፣ በወልድም ወደ አርያም፣ በመንፈስ ቅዱስም በወጣሁ ጊዜ ከመላእክተ ዘንድ ዝማሬ ሰማሁ ማለት ነው፡፡

በዚህ ወቅት የነበሩ ቀደምት አባቶቻችን ይህንን ሰማያዊ ዜማ እግዚአብሔር በቅዱስ ያሬድ አማካይነት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንውስጥ ላለችውና ለምስጋናው ማደርያ ትሆን ዘንድ በሰጣቸው በሰማያዊቷ ጽዮም ማመስገኛ መጠበቂያና መከበርያ ሊሆን እንደሰጣቸው በራእይ ስለ ተገለጸላቸው እንደ እግዚአብሔር ቃል ተቀብለውታል፤ ተጠቅመውበታልም፤ ዛሬም ድረስ ለቤተ ክርስቲያኗ መጠንከርና መጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉ ነገሮች አንዱና ዋነኛው ይህ ሰማያዊ ዜማና ለአምልኮተ እግዚአብሔር እየተገለገልንበት ያለው ታቦተ እግዚአብሔር ናቸው፡፡

በእምነት ያልበረቱ፤ የእግዚአብሔርን ቃልና ኃይል ያልተገነዘቡ አንዳንድ ሰዎች የቅዱስ ያሬድ ወደ ሰማይ መነጠቅና የዜማው ሰማያዊነት ይጠራጠራሉ፤ ይሁንና ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ሰማይ ተነጥቆ ልዩ ራእይ እንዳየ በ2ቆሮ. 12፡2-5 ተጽፎአል፡፡ ከዚህ ቃለ መጽሐፍ ተነሥተን እውነቱን ስናስተውል የቅዱስ ጳውሎስ አምላክ የቅዱስ ያሬድም ነውና ጸጋውን ለመስጠት በፈቀደ ጊዜ ሊያደርገው የሚችል እንጂ የማይችል እንዳልሆነ መገንዘቡ የሚከብድ አይደለም፡፡

የቅዱስ ያሬድ ዜማ ይዘትና ባሕርይ

የቅዱስ ያሬድ ዜማ በይዘቱ ድጓ፣ ምዕራፍ፣ ዝማሬ፣ መዋሥእትና ቅዳሴ የተባሉትን ክፍሎች ያካተተ ነው፤ ከነዚህም ውስጥ ቅዳሴ ድርሰቱ የሌሎች አበው ሆኖ ዜማው የእርሱ ነው ሌሎቹ ግን ድርሰታቸውም ሆነ ዜማቸው የራሱ ናቸው፤ ቅዱስ ያሬድ በዜማ ብቻ ሳይሆን በድርሰት፣ በሥነ ቋንቋ፣ በቅኔና በትርጓሜም የተዋጣለት ስመጥር ሊቅ ነው፡፡ በድርሰቱ ውስጥ የብሉያት፣ የሐዲሳት፣ የሊቃውንት፣ የመነኮሳት፣ በኪዳን መጻሕፍት፣ የሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንና የገድለ ቅዱሳን መጻሕፍት ተጠቅሰዋል፤ ከዚህም በተጨማሪ ምስጋናን፤ ጸሎትን፣ ምክርን፣ ታሪክን፣ ትምህርተ መለኮትንና የሥነ ምግባር ትምህርትን ይዞ ይገኛል፡፡

የቅዱስ ያሬድ ዜማ በባህርዩ ሲታይ አንዱ ክፍል ከሌላው ክፍል የተለየ ነው፤ ይህም ማለት የዜማው ቃና ከሦስቱ ድምጾች ማለትም ከግእዝ፣ ከዕዝልና ከዓራራይ ሳይወጣ በመርዘምና በማጠር አንዱ ክፍል ከሌላው ክፍል ይለያል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ድጓ ከዝማሬ፣ ዝማሬ ከመዋሥእት፣ መዋሥእት ከቅዳሴ በአንዱ የዜማ ምልክት ሳይቀር ይለያያሉ፣ ይህም በቅዱስ ያሬድ አማካኝነት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተሰጣት ጸጋ ምን ያህል ታላቅና ዓይነተ ብዙ እንደሆነ ያሳያል፡፡

የቅዱስ ያሬድ ድርሰት ክብደቱ የሚመዘነው በጣዕመ ዜማ ብቻ ሳይሆን በኃይለ ቃሉም ጭምር ነው፤ ለምሳሌ የኋላ ሊቃውንት ጥቂት የሆኑ አንዳንድ ድርሰቶች አዋልድ ተብለው በድጓው ውስጥ እንዲካተቱ አድርገዋል፤ ይሁንና አንድ ተመራማሪ የቅዱስ ያሬድንና የኋላ ሊቃውንትን ድረሰትና ዜማ ለይልን ቢባል ያለምንም ችግር ለይቶ መናገር ይችላል፤ ለምን ቢባል የቅዱስ ያሬድ ድርሰት ከሆነ ከዜማው ወይም ከኃይለ ቃሉ ክብደት አይጠፋምና ነው፤ በዚህና በመሳሰለው ሁሉ የሌሎች ሊቃውንት ድርሰት ከቅዱስ ያሬድ ጋር ሲመዛዘን የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት ይታይበታል፤ ሌላው የዜማው ባህርይ እንዲሁ ልቅ ሳይሆን የራሱ የሆነ መታወቂያ ቤት ያለው ነው፤ እያንዳንዱ የዜማ ክፍል የተለየ ስም፤ የተለየ ቤት፣ ወይም ኮድ፣ የተለየ ሃሌታና የተለየ አገልግሎት ያለው፣ በኃይለ ቃል፣ በምልአተ ንባብ፣ በዜማ ክብደትና በአመል የተለየ ባህርይ ያለው በመሆኑ ተመሳሳይ የሌለው ልዩ ዜማ ሆኖ ይገኛል፡፡

የዜማው መስፋፋት

በቅዱስ ያሬድ ዘመን የነበረው አጼ ገብረ መሰቀል ዜማው በመላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አገልግሎት ላይ እንዲውል ከቤተ ክህነቱ ባለሥልጣናት ጋር በመሆን አዋጅ አስነገረ፤ ተሰዓቱ ቅዱሳንም በወቅቱ አክሱም ውስጥ ቤተ ቀጢን በተባለው ቦታ ነበሩና ዜማው ቤተ ክርስቲያን እንድትገለገልበት በማስተማራቸው የአኲስም ካህናተ ደብተራ በሙሉ ወደ ሙራደ ቃል የቅዱስ ያሬድ ትምህርት ቤት ገብተው ተምረውታል ከቅዱስ ያሬድ እውቅ ተማሪዎች መካከል የሚከተሉት አራት ነበሩ፣ እነርሱም፤

ሀ/ መንከራ            

ለ/ ሳዊራ

ሐ/ ብስድራ    

መ/ እስክንድራ የተባሉት ናቸው

ከቅዱስ ያሬድ ምናኔና መሠወር በኋላ እስክንድራ በአክሱም፤ ሳዊራ ዓድዋ አካባቢ በሚገኘው የአባ ገሪማ ገዳም ልዩ ስሙ መደራ፣ መንክራ በደብረ ዳሞ፣ ብስድራ በሐማሴንና በሸዋ ጎሀ ጽዮን ውስጥ ሆነው በማስተማራቸው ዜማው በመላ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአጭር ጊዜ ተስፋፋ፤ ነገሥታቱም ለካህናተ ደብተራ ተገቢ የሆነ እንክብካቤ ስላደረጉላቸው ዜማው በአስተማማኝ ሁኔታ እስከ ዘመናችን ሊደርስ ችሎአል፡፡

ዜማው ለቤተ ክርስቲያናችን የሰጠው ጥቅም

የቅዱስ ያሬድ ዜማ ለቤተ ክርስቲያናችን የሰጠው ጥቅም ከፍተኛ ነው፤ ለምሳሌ ያህል የቤተ ክርስቲያናችን ሃይማኖት፣ ቀኖና፣ ባህልና ሥርዓት ሁሉ ከመለወጥ፣ ከመፋለስና ከመበረዝ የጠበቀ፣ ያጸናና በየጊዜው ለተነሡ መናፍቃን ሁሉ በሩን ክርችም አድርጎ የዘጋ ይህ የቅዱስ ያሬድ ዜማና ድርሰት ነው፡፡ በዓለማችን መጻሕፍት በየጊዜው ሲተረጐሙ ብዙ የምሥጢር፣ የንባብና የሐሳብ መፋለስ አጋጥሞአቸዋል፤ ይህ የሐሳብ መፋለስ ለተለያዩ ሃይማኖት መፈጠር ምክንያት መሆኑ አልቀረም፤ የቅዱስ ያሬድ የዜማ ድርሰት ግን በኖታ ወይም በምልክት፣ በቤት ወይም በኮድ የታሠረ በመሆኑ፤ ከዓመት እስከ ዓመት በትምህርትና በአገልግሎት ስለሚሰጥ፣ ለመፋለስ ያለው አጋጣሚ ዝግ ሆኗል፣ ስለሆነም ቤተ ክርስቲያናችን ከዛሬ ወደኋላ አንድ ሺህ አምስት መቶ ዓመታት አካባቢ ምን ዓይነት ሃይማኖትና ሥርዓት ነበራት ብሎ ለሚጠይቅ ሰው የቅዱስ ያሬድ ድርሰት እንደመስታወት ቁልጭ አድርጎ ማሳየት ይችላል፤ ከቅዱስ ያሬድ በኋል ብዙ መቶ ዓመታት ቈይተው የተነሡ የሃይማኖት ተቋማት እና የሚያስተምሩት ትምህርት ምን ያህል ከእውነት እንደራቁና በሐዋርያት ትምህርት ሳይሆን በራሳቸው ፍላጎት የፈጠሩት ሃይማኖት ለመሆኑ በቁ ግንዛቤ ይሰጣል፡፡

የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያናችንን ወደ እምነቷ ለመለወጥ ያደረገችው ሙከራ ሳይሳካላት ሲቀር ያደረገችው ዘዴ እዚህ ላይ መጥቀሱ ለቅዱስ ያሬድ ዜማ ጥንካሬ ማስረጃ ሊሆን ይችላል፣ የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለብዙ ዘመናት ቤተ ክርስቲያናችንን ወደ ጉያዋ ማስገባት ያቃታት ምስጢር ለማወቅ መልእክተኞችዋን ሰብስባ ምሥጢሩ ምን እንደሆነ እንዲያጠኑ ሕዝቡን መስለው የሚሰልሉ ሰዎችን በመላክ ሰፊ ጥናት አደረገች፣ በጥናቱ መሠረት የተገኘው ውጤት የቤተ ክርስቲያኗ ኃይል ድጓ የተባለው መጽሐፍና የድጓ አዋቂዎች የሆኑ ካህናተ ደብተራ እንደሆኑ አረጋገጠች፤ እነዚህ ሊቃውንት በቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይወሰኑ በቤተ መንግሥቱም አንጋሾች፣ ፈራጆችና ጸሐፊዎች መሆናቸውን በአጠቃላይ የቤተ መንግሥት የሥልጣን ቁልፍ በእጃቸው እንደሆነ፣ በዕውቀት ረገድም እጅግ የመጠቀ የምሥጢረ መጻሕፍት ትርጓሜና የቅኔ ፍልስፍና እንዳላቸውና ሁሉንም ደግሞ በቃላቸው እንደዝናም የሚያወርዱት መሆናቸውን አረጋገጠች፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለማዳከም በቅድሚያ ካህናተ ደብተራ የሚዳከሙበት ድጓ የሚጠፋበት መርሐ ግብር በማውጣት በአጼ ሱስንዮስ ዘመነ መንግሥት በሰፊው ተንቀሳቅሳበታለች፤ በዚህ ዘመን ድጓ አበቃ ጠፋ የተባለበት ጊዜ ነበር፤ ነገር ግን እነ እጨጌ በትረ ጊዮርጊስን ተስፋ ቈርጠው ተመልሰዋል፡፡ በዚህም

"ወረከብናሁ ለበትር ዘያደክማ ለሮሜ
ቅሩፀ በንባብ ወጽሩበ በትርጓሜ"..... ተብሎ ቅኔ ተበርክቶላቸዋል፡፡ የቤተልሔሙ ካህነ ደብተራ መሪጌታ ልሳነ ዕፍረትም ድጓውን በጥንቃቄ ሸሽጎ በማቈየቱ እንደገና ኃያሉ የቤተ ክርስቲያን መሣሪያ ድጓ እንደነበረው ሃይማኖትን የመጠበቅ ተግባሩ ሊቀጥል ችሎአል፤ ይህ ሁሉ ድጓ ለቤተ ክርስቲያን ያለውን ጥበቃ ምን ያህል እንደሆነ በግልጽ ያሳያል፡፡

በሌላም በኩል የቅዱስ ያሬድ ዜማ ባለው ተወዳጅነትና መንፈሳዊ ተመስጦ የቤተ ክርስቲያናችን ደቀ መዛሙርት እናት አባታቸውን፣ እኅት ወንድማቸውንና የተወለዱበትን አገር ጥለው፣ ረጅም ጉዞ ተጉዘው፣ ረሀብ፣ እርዛት፣ የአገርና የቤተሰብ ፍቅር ሳይበግራቸው ለዐሥርት ዓመታት እንዲማሩና ደከመን ሰለቸን ሳይሉ 24 ሰዓት በሙሉ ያለማቋረጥ በተመስጦ እንዲያመሰግኑ አድርጎአቸዋል፤ በዚህም ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ታደርሳለች፣ የኢትዮጵያ ሰዎች በፊቱ ሆነው ያመሰግናሉ፤ የተባለውን አምላካዊ ቃል በትክክል በቤተ ክርስቲያናችን በቅዱስ ያሬድ ልጆች አማካኝነት መፈጸሙን እንመለከታለን፡፡ ምእመናኑም ምሑሩ ካህነ ደብተራ እንዲያስተምራቸው፣ በጣዕመ ዜማው እንዲያገለግላቸው በማሰብ፣ ካላቸው ሀብት ከፍለው እየሰጡ እንዲገለገሉበት ሆኗል፤ ለካህናተ ደብተራ ካላቸው ፍቅር የተነሣም የአገራችን ደብተራ እየው ቅኔው ሲያመራ እያሉ ፍቅራቸውንና አክብሮታቸውን በመግለጽ አቀንቅነውላቸዋል እስካሁንም ድረስ በጎንደር ይባልላቸዋል፡፡ ይህ ሁሉ ድጓው በቤተ ክርስቲያኗ ያሠረጸው መንፈስ ቅዱሳዊ ተመስጦ ጥልቅ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ የቅዱስ ያሬድ ዜማ ካለው አገልግሎት አኳያ ስንመለከተው የቤተ ክርስቲያን ልሳን ነው ማለት ይቻላል፤ ምክንያቱም ያለ ቅዱስ ያሬድ ዜማ ቤተ ክርስቲያኗ የምታስተላልፈው ጸጋ መንፈስ ቅዱስ የለምና ነው፤ ለምሳሌ የምንጠመቀው፤ የምንቈርበው፣ የምንቀድሰው፣ ሥርዓተ ተክሊልን የምንፈጽመውና ጸሎተ ፍትሐትን የምናካሄደው በቅዱስ ያሬድ ዜማ ነው፡፡

ዜማው በሥነ ጽሑፍ፣ በሥነ ቋንቋ፣ በመንፈሳዊ ባህል፣ በቅድስና ሕይወት፣ በመልካም ሥነ ምግባርና በመሳሰሉት ሁሉ ለአገሪቱም ሆነ ለቤተ ክርስቲያኗ ከፍተኛ ጥቅም ሰጥቶአል፡፡

ዜማ በአሁኑ ጊዜ የሚገኝበት ሁኔታ

የቅዱስ ያሬድ ዜማ ከጥንቱ የመማርና ማስተማር ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር በአሁኑ ጊዜ የድክመት አቅጣጫን ተከትሎ እየሄደ ነው፡፡ በጥንት ጊዜ መምህራኑ የሚገኙት በየገዳማቱና በታላላቅ አድባራት፣ እንዲሁም በገጠሬው ሕዝብ መካከል ነበር፤ እንደዚሁም የመምህሩም ሆነ የተማሪው ኑሮ የተመሠረተው በገጠሩ ሕዝበ ክርስቲያን ላይ ነበር በመሆኑም የመምህሩም ሆነ የደቀ መዝሙሩ ልብ በዓለማዊ ሐሳብ ሳይከፋፈል በተረጋጋ ሁኔታ እየተማረና የቅድስና ሕይወቱም እንደጠበቀ ወደ የትውልድ ሀገሩ በመመለስ ያገለግል ነበረ፣ በዚህም ሁኔታ የትምህርቱ ጥራትና ስርጭት በገጠርና በከተማ ሚዛናዊ ነበረ፣ በአሁኑ ጊዜ ግን ለጋሱ የገጠር ሕዝበ ክርስቲያን የኑሮው ሁኔታ እያሽቆለቆለ፣ የዘመኑ አስተሳሰብም እየተቀየረ በመምጣቱ ሕዝቡ ለመምህራኑም ሆነ ለደቀ መዛሙርቱ የነበረው አመለካከት በመጠኑም ቢሆን መለወጡ አልቀረም፤ ስለሆነም መምህሩም ሆነ ተማሪው በአንድነት ወደ ከተማ መጉረፍ ተያይዘውታል፡፡ ከተማ ከገባ ዘንድ ደግሞ የተሻለ ሥጋዊ ኑሮ ስለሚመለከት መንፈሳዊነቱን ገሸሽ እያደረገ የከተማ ኑሮን ለመለማመድ ዘመናዊ ትምህርትን ስለሚከታተል የደከመበትን የዜማ ትምህርት ወደ አገሩ ተመልሶ ማስተማርና ማገልገል ይቅርና ጭራሽ ያጠፋዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ጠቅለል ብሎ ሲታይ የቀድሞ ዘመን ተምሮ አገርን ማገልገልና ማስተማር ነበረ፤ የአሁኑ ግን መምህርና ተማሪ ባይጠፋም ተምሮ ወደ ከተማ ብቻ በመሄድ ሳያስተምሩ መቅረት ሆኗል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ሁኔታ ከአሁኑ ጀምሮ ታስቦበት በመላ ኢትዮጵያ፣ በገጠሩም ሆነ በከተማ፣ ሚዛናዊ የሆነ የትምህርት ስርጭት የሚገኝበት፣ የመምህራንና የተማሪዎች እንክብካቤ የሚረጋገጥበት፣ ሥርዓት ትምህርቱም ቀልጣፋና ጥራት ያለው፣ በስብከተ ወንጌል ሥልጠናም ጭምር የታገዘና የቅድስና ሕይወት የተላበሰ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያስችል ሁኔታ ካልተፈጠረ፣ ውጤቱ አስጊ ሆኖ ይታያል፡፡ ከዚህም ጋር ዜማው በጣም ተወዳጅ ሆኖ ሳለ በአንዳንድ የቴክኒክ ጉድለቶች ምክንያት የሚታየው መዝረክረክ ተስተካክሎ እጅግ ማራኪና ተወዳጅ የሚሆንበት ሁኔታም ሊመቻች ይገባል፡፡

ወጣቱ ትውልድ በቅዱስ ያሬድ ዜማ ላይ ያለው አመለካከት

ወጣቱ ትውልድ በቅዱስ ያሬድ ዜማ ላይ ያለው አመለካከት እንደ አባቶቹ አክብሮት፣ ፍቅርና ተመስጦ ያለበት ለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ይሁንና ከእምነትና ከአመለካከት ችግር ሳይሆን ከዜማው ክብደትና በቀላሉ ሊያጠኑት የሚችሉበት ሁኔታ ካለመፍጠሩ የተነሣ አንዳንድ ጉድለቶች ይታያሉ፣ ለምሳሌ ቤተ ክርስቲያኗ የብዙ ምሥጢር ግምጃ ቤት፣ የእውቀት ምንጭ፣ የቅኔና የፈሊጣዊ አነጋገር ባለቤት ስትሆን በአሁኑ ጊዜ በወጣቶች መዝሙር የሚተላለፉ የሥነ ግጥም ቃላት በእጅጉ ቀላልና ተራ ንግግር የሚመስሉ ሆነው ይታያሉ፡፡ በዜማ ይዘታቸውም ከጥቂቶች በቀር ያሬዳዊ ለዛ ያልተላበሱ ከመሆናቸውም በላይ እዚህ ግቡ የሚባሉ አይደሉም፣ ለቤተ ክርስቲያናችን ዕውቀት የሚመጣጠኑም አይደሉም፤ መዝሙሮች በአብዛኛው ከበሮ፣ መሰንቆና በገና ከመምታት፣ ዋሽንት ከመንፋት፣ ከማጨብጨብና እልል ከማለት በቀር ሌላ ብዙም አይታይባቸውም፤ ነገር ግን ጌታ በማቴ.23፡23 ዘንተኒ ግበሩ ወዝክተኒ ኢትሕድጉ ማለትም ይህንንም ሥሩ ያንንም አትተው እንዳለው በተጠቀሱት መሣርያዎች በመታጀብ ጥሩ ጥሩ የሆኑ የንስሐ መዝሙራትም ሊዘጋጁ ይገባል፤ የሲና ሐመልማል፣ የሰው ልጅ ሁል ጊዜ እና ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን የመሳሰሉ ያሬዳዊ ዜማን የተላበሱ መዝሙራት መዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ያለው የመዝሙር ችግር ምንድን ነው ብለን ብንጠይቅ ዋና ዋናዎቹ ሦስት ነገሮች ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ እነርሱም፤

ሀ/ የግል ጥቅም ላይ በማተኮር ብቻ ተሠማርቶ ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ መንቀሳቀስ
ለ/ የልምድ ልውውጥና የሙያ ሥልጠና የሚሰጥበት ተቋም አለመኖር
ሐ/ በኃላፊነት ያለን ሰዎችም ችግሩን ተመልክተን መፍትሔ አለመስጠት የሚሉት ናቸው፡፡ ይህ ችግር እንዳለ ከቀጠለ የባሰ ድክመት ማስከተሉ አይቀርም፤ ነገር ግን ያ ከመሆኑ በፊት መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል፡፡

መፍትሔ

መፍትሔው በመጀመሪያ ከአደራጁ ክፍል መመንጨቱ የግድ ነው የሚሆነው፤ አደራጁ ክፍል ችግሩን ለመፍታት ወጣቱን ትውልድ በአንድነት አደራጅቶ የመዝሙር ማሰልጠኛ ማዕከል፤ የድርሰት፣ የዜማና የሥነ ጽሑፍ ክፍሎችን አደራጅቶ ቢከፍት ማእከላዊ የሆነ አሠራር የሚኖርበትን ሁኔታ ቢያመቻች፣ የቤተ ክርስቲያኗ ልሳን የሚሆኑና ላላት ዕውቀት የሚመጥኑ መዝሙሮች ብቻ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ ይቻል ዘንድ የሳንሱር ሕግና ደምብ አጽድቆ ሥራ ላይ ቢያውልና አፈጻጸሙንም ቢቈጣጠር፣ ወጣቱም ቤተ ክርስቲያኗ ለምትሰጠው አመራር አጋዥና ተገዥ ቢሆን ተጨባጭ የሆነ ውጤት መምጣቱ አይቀርም መፍትሔውም ይኸው ነው፡፡
ስለሆነም ሁላችንም ድክመቶቻችንን አርመን በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት በቊጭትና በበጎ ተነሳሽነት ለያሬዳዊ ዜማ መጠበቅና ለወጣቱ ትውልድ መዝሙር ጥራት ከልብ መሥራት ይኖርብናል ለዚህም የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን አሜን፡፡

የጽሑፉ ምንጮች

1. መጽሐፍ ቅዱስ

2. ክብረ ነገሥት ዘአኲስም ጽዮን

3. ድርሳነ ጽዮን ዘአኲስም ጽዮን

4. ገድለ ቅዱስ ያሬድ

5. ጥንታዊ ሥርዓተ ማኅሌት ዘአቡነ ያሬድ ሊቅ ከመሪጌታ ልሳነ ወርቅ ገብረጊዮርጊስ

6. መጽሐፈ ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ

7. ዝማሬ መዋሥእት ዘቅዱስ ያሬድ

ከንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ
ጥር 5 ቀን 2005

የፎንት ልክ መቀየሪያ