Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

ራዕይ ባይኖር ህዝብ መረን ይሆናል፡፡

ምሳ. 29፡18

መምህር ንዋይ ካሳሁን

የማ/መ/ትምህርት ክፍል ኃላፊ (BTH,BSCN)

የቸርነት ባለቤት እግዚአብሔር ይህንን ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ እንደ ጥንቱ ተፈጥሮ ጠብቆ አሁንም ያኖረዋል፡፡ ታዲያ በውስጡ ያሉ ፍጥረታት በተለይ የሰው ልጆች ይህንን የአምላክ ተጥባቦት ሲያደንቁ ይኖራሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር ይህ ዓለም የራሱ አስገኝ፣ መጋቢ፣ እንዳለውም በመጽሐፉ ከተጻፈ ጥቅስ ይልቅ አፈጣጠሩ ራሱ በትልቁ ይመሰክራል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ"የማይታየው ባህርይ እርሱ የዘለዓለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከአለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና" ሮሜ. 20፡21 በማለት ስለ እርሱ ኃይልና አምላክነት የፍጥረቱን ምስክርነት ይገልጣል፡፡

የሰውን ልጅ አፈጣጠር ወይም ለምን ተፈጠረ ለሚለው ሥነ መለኮታዊ ጥያቄ መልስ በተሳሳተው ሳጥናኤል ምትክ ቁጥር ለመሙላት አዳም ተፈጠረ ሌሎች ደግሞ እግዚአብሔር በራሱ ብቸኛ በመሆኑ ጉድለቱን ለመሙላት፣ ለራሱ ለእግዚአብሔር ክብር መገለጫ አለምን ፈጠረ፤ ሌላም የሚሉ አሉ፡፡ ይህንን አስተምህሮ በተመለከተ ጻድቁ ኢዮብ "በውኑ ሰው እግዚአብሔርን ይጠቅመዋል? ጠቢብ እንኳ ቢሆን ምን ይጠቅመዋል? ጻድቅ መሆንስ ሁሉን የሚችለውን አምላክ ደስ ያሰኘዋልን?" በማለት ሲጠይቅ የሰው ልጅ መፈጠር ለእግዚአብሔር ህልውና አስፈላጊና ወሳኝ አለመሆኑን ነው ኢዮ. 22፡2፡፡

እንደዚህ ከሆነ በተለይ ሰው ደግሞ የእግዚአብሔር ባህርይ የሆነውን ፍቅሩን ሊያካፍለው የተፈጠረ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ የነገረ መለኮት ምሁራንን አስተምህሮ ይደግፋል፡፡ "ጌታችንና አምላካችን ሆይ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል" በማለት ሀያ አራቱ የሰማይ ካህናት አመሰግነውታል፡፡ እንደ ስነ ፍጥረት አስተምህሮ ከሆነ ከሀያ ሁለት ፍጥረታት ውስጥ በእግዚእብሔር መንግስት ውስጥ ልዩ ስፍራና ክብር እንደ ሰው የተሰጠው የለም ይህንንም ለማስረዳት ሌሎች ፍጥረት በሀልዮ /በሀሳብ/፣ በነቢብ /በቃል/፣ ሲፈጠር የሰው ልጅ ግን በእግዚአብሔር እጅ ቅርጽ ወጥቶለት ተበጀ ተፈጠረ ከዚህም በላይ የሕይወትን አስትንፋስ እፍ እንዳለበት መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል ኦ.ዘፍ. 2፡6፡፡

በእግዚአብሔር እጅ መሰራት ወይም መበጀትን ለሰው የተሰጠውን ልዩ ክብር እንዲሁም እግዚአብሔር በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ ያኖረው ዘለአለማዊ ዓላማ ያሳያል፡፡ ኢ.ሳ 49፡16 እኛ እንደ ሌሎቹ ፍጥረታት መጨረሻችን ከመሬት ተፈጥረን ወደ መሬት ተመልሰን በመሞትና በመበስበስ የምንቀር እንደ እንስሳቱ አይደለንም ጠቢቡ ሰሎሞንም "የሰው ልጆች ነፍስ ወደ ላይ እንደምትወጣ የእንስሳም ነፍስ ወደታች ወደ ምድር እንደምትወርድ የሚያውቅ ማን ነው" በማለት የመጨረሻውን እጣ ፈንታ ገልጧል፡፡ መክ. 3፡21

ለዛሬው በጥቂት ለማየት የምንሞክረው የሰው ልጅ ከትልቅ ራዕይ ጋር የተፈጠረ መሆኑን ነው፡፡ ለዚህም ነው መጽሐፍ ቅዱስ ከመነሻው እስከ መድረሻው ስለ ሰው ልጅ በጥልቀት የሚናገረው ምሪት ይሆነው ዘንድ ቃለ እግዚአብሔርም የተሰጠው ብቸኛ ፍጡር ነው፡፡ እንስሳት ከእንስሀስሆ /መንቀሳቀስ/ በቀር ህያዋን አይደሉም የሰው ልጅ ግን ከእንስሳትና ከተክሎች በተለየ መልኩ ኃይለ ዘርዕ (vegitative life) አንሳህስሆ (Social life) ኃይለ ንባብ (rational life) ወይም አስተውሎት ኖሮት የተፈጠረው፡፡ እንስሳት ድምፅ ቢያሰሙ ከሰው ወገን የሚይዘው የሚቋጥረው የለም አይተረጎምም (animal language is signal) የሰው ድምፅ ግን ይተረጎማል፣ ይታሰባል፣ የቋጠረው ትርጉም ወይም ጭብጥ አለው (man's language is cancept) የሚለው የአርስቶትል ፍልስፍናም ያየው ይህንን እውነታ ነው፡፡ ታድያ እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ ያለው ራዕይ አውቀን ተረድተን ሕይወታችንን በተስፋ እንኖራለን፡፡ በዕድሜያችን ለኑሮ የምንከፍለውን ዋጋ ያህል ውስጣችን ለተቀመጠው ራዕይ ወይም አላማ ከፍለንም ሆነ አስበን አናውቅም፡፡

ራዕይ ምንድን ነው?

ይህ ቃል ብዙ ግዜ ከዓላማ ጋር በተለዋዋጭነት የምንጠቀምበት ቃል ሲሆን አንድ የሆነ ቋሚ ሁሉንም የሚያስማማ ትርጉም ባይሰጠውም በጥቅሉ ግን የሕይወት ዓላማን የምናሳካበት ቁልፍ ሲሆን ለምንና እንዴት እንደተፈጠርን፤ ለምን እንደምንኖር፣ በሕይወታችን ምን ማድረግና መስራት እንዳለብን በመጨረሻም ግባችን ምን ልንሰራ እንደተፈጠርን ወደ መጨረሻው የሕይወት ግብ የሚያስጉዘን እግዚአብሔር በኛ ውስጥ ያኖረው ዘለዓለማዊ ዕቅድ ነው፡፡

የዕለት ኑሮአችንን ለማሟላት በሰባቱ አለማት ተበታትነን ቀንም ሆነ ሌሊት ደፋ ቀና እንዳልን እንኖራለን፡፡ ሁሌም ወደ ልባችን ባሰብን ቁጥር መልስ የሌላቸው ብዙ ጥያቄዎች ውስጣችን ተከማችተው እናገኛለን፡፡ ለምንድን ነው የምንኖረው? ለምንስ ተፈጠርን? የመኖሬ ጥቅም ምንድነው? እውነተኛ ፍላጎቴስ ምንድን ነው ብለን የጠየቅንባቸው ግዜያት ጥቂት አይደሉም፡፡ ግን መልሱን በአግባብ የመለስን ስንቶቻችን እንሆን? ለማንኛውም ይህንን ጥያቄ መመለስ ለመንፈሳዊ ሕይወት ትርጉም መስጠት ስለሆነ እንደ ቀላል መታለፍ የሌለበት የዘለዓለማዊነት ጥያቄ ነው፡፡ አልያ ግን ጠቢቡ ሰሎሞን እንደተናገረው "ራዕይ ከሌለ ህዝብ መረን ይወጣል" ምሳ. 29፡18 ይላል፡፡ መንፈሳዊ ሕይወት ያለ ራዕይ ትርጉም የለውም መኖራችንን ትርጉም ያጣል፡፡ዛሬም የኖርነው እግዚአብሔር መኖራችንን ስለወደደ ብቻ ነው፡፡ ያለትርጉም መኖር ደግሞ ምንኛ ሚስኪንነት ነው፡፡

ለምን እንኖራለን?

በአባትና እናታችን ፈቃድ ወደዚህ ዓለም መጥተን ዓለም ሚዛኗን በደፋችበት ወገን እየዋዥቅን የአርባ ቀን እድል ያደረገንን፣ በባለጠግነት ይሁን በድህነት፣ በጥቁርነት አልያ በነጭነት፣ ምሁርነት አልያ በመሀይምነት ተፈርዶብን የምንኖር አይደለም፡፡ ህፃናት እንደሚዝናኑባቸው አስቂኝ አሻንጉሊቶች ሌላው የሚኖር እኛ የምኗኗኑር ሆነንም አልተፈጠርንም ሁላችንም የማይጠፋ የራሳችን የሆነ ራዕይ ያለን እግዚአብሔር ወደ ምድር ስንመጣ የምናከናውነውን ዓላማ እኛ ውስጥ አስቀምጦ ፈጥሮናል፡፡ ይህንን ዓላማና ራዕይ ጠንቅቆ ካለማወቅ የተነሣ ሕይወት በህልም ዳውላ እንደመሸከም አሰልቺ ሆኖብናል፡፡ በህልም ትልቅ ሸክም ተሸክመን ከብዶን ሲያልበን ሲደክመን ከሸክሙ የተነሣ ጉልበታችን ዝሎ የምናይበት ግዜ አለ፡፡ የሚገርመው ነገር ያ ሁሉ ድካም ያዛለን፣ ያላበን፣ ምንም ሸክም በሌለበት ሁኔታ ነው፡፡ አንድ ቀን አባትና እናት ለዘመን መለወጫ ለልጃቸው ልብስና መጫወቻ ሊገዙ ወደ አንድ ሱቅ ይገባሉ፡፡ ወላጆች ሱቁን እየተዘዋወሩ ሲመለከቱና የሚገዙትን ሲመርጡ ልጁ ግን በጣም ያስደስተውን የፈረሰ አሻንጉሊት ላይ ተቀምጦ እየተናጠ ይጫወታል መነሣት አልፈለገም ወላጆቹ የሚፈለገውን ሁሉ ገዝተው ሲመለሱ ልጁ ከመናጡ የተነሳ ደክሟል አልቦታል፡፡በመንፈሳዊ ሕይወታችንም ይሁን በስጋዊ ኑሮአችን ውስጣችን ያለውን ራዕይ ባለማወቅ የተነሣ አሸንጉሊት በሆነ ግዜያዊ የምኞት ፈረስ በመናጥ ጊዜ እናሣልፋለን፡፡ አንድ ክንድ እንኳ ፈቀቅ አያደርገንም አንድ ቀን የሕይወት ለውጥ ሳይኖረን ደክሞን ውለን ደክሞን እናድራለን፡፡ እግዚአብሔር ግን በሚናጥ ፈረስ ላይ እንድንቀመጥ አይፈልግም ተጉዘን የምንደርስበት ሌላ ኑሮ አለን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ "ልሔድ ከክርስቶስ ጋር ልኖር እናፍቃለሁ" ፊሊ.1፡23 በማለት አሁን ፊት ለፊት ያለውን ግዜያዊውን የሚናጥ ፈረስ ሳይሆን የወደፊቱን ዘለዓለማዊነትና መንፈሳዊ ግብ በውስጡ ያለውን ራዕይ ያየ ሐዋርያ ነው፡፡

የምንኖረው በልቶ ጠጥቶ ለመኖር ጥሩ ስራ ይዞ ዳጎስ ያለ ደሞዝ አግኝቶ ደስተኛ ለመሆን ጥሩ ትዳር መስርቶ ቤት ቀልሶ ደስ ለመሰኘት አይደለም፡፡ እነዚህ ሁሉ የሚያስፈልጉን ቢሆንም በራሳቸው ግን የሕይወት ግብ አይደሉም፡፡ ደስታ የኑሮ እርካታ ነው፡፡በአፈጣጠራችን በማህበራዊ ኑሮአችን በስራችን ውጤት ወዘተ ስኬታማነት የምናገኘው የህሊና እርካታ ደስታ ነው፡፡ ምኞታችን እውን ሲሆን ተስፋ ያደረግነው ሲሟላልን እቅዳችን ሲሰምርና የደከምንበት ነገር ውጤታማ ሲሆንልን የምናገኘው የመጨረሻው ነገር ደስታ ነው፡፡ እግዚአብሔር ደስ ብሎን እንድንኖር ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን ደስታችን በስጋዊ ድሎት የተነሣ ከሆነ ግዜያዊ ሲሆን መንፈሳዊ ግብ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለሆነም ሁላችንም ለምን እንደምንኖር መጠየቅ አለብን፡፡

የምንሰራው ሥራ ስላለን እንኖራለን

እግዚአብሔርን ስናውቀው በስራው ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚጀምረው በሰላምታ ቃል አይደለም "እግዚአብሔር በመጀመርያ ሰማይንና ምድርን ፈጠረ" በሚለው የሥራ ቃል ነው፡፡ እኛንም የፈጠረን በምድር ላይ ከምንፈጽመው ስራ ጋር ነው፡፡ ሙሴ የሕይወት ታሪኩ በኦሪት ዘጸአት ላይ በሰፊው ተመዝብቦ እናገኛለን፡፡ የተለየ ፍጡር አይደለም አልያ ከተለየ ዘር የተወለደ አይደለም እንደሌሎቹ ዕብራዊ ነው፡፡ ከድሀ ቤተሰብ የተወለደ ሲሆን እንደተወለደም የሕይወትን ፈታኝ ጉዞ የጀመረው ከእናት ጡት ተለይቶ በአባይ ወንዝ ላይ በመጣል ነው፡፡ ከዚያም ወደ ንጉስ ቤት ገብቶ በቅምጥል ቢያድግም ከነገስታት ቤተሰብ በተለየ ግን የሕይወት ራዕዩን በጥልቀት ያየ ታላቅ መንፈሳዊ ሰው ነበር፡፡ ለምን እንደሚኖር አስቦ ምን ሊሰራ እንደተፈጠረ አስተዋለ አገኘም፡፡ መጽሐፍ "ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንደሆነ አስቧልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ ብድራቱን ትኩር ብሎ ተመልክቷልና" ዕብ. 11፡24 በማለት ምን መስራትና ማድረግ እንዳለበት ለይቶ ነበር፡፡ በዚህም ግዜያዊውን ከዘለዓለማዊው፣ ከጊዜያዊው ደስታ ይልቅ አምላካዊውን ደስታ ከኃጢአት ይልቅ መንፈሳዊ ተጋድሎን በትኩረት ተመልክቶ በዚህም ዘመናትን ተሻግሮ ዛሬ ሁላችንም የምንደነቅበትን የአመራር ጥበብ (management) አስተምህሮ አለፈ ትልቅ ትውልድን መርቶ ነጻ አወጣ የሙሴ ራዕይ ባይኖር የእስራኤልን ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል መተንበይ አያቅተንም፡፡

ሙሴ ሌላም ራዕይ ነበረው፡፡ እግዚአብሔርን በቃል ከማናገር ባሻገር ፊት ለፊት መተያየት ፈለገ፡፡ ይህ የሙሴን ሩቅ አሳቢነት መንፈሳዊ ጥማቱን ሲያመላክት ለግዜው እግዚአብሔርን ባያይም መንፈሳዊ ምኞቱ ግን ሳይገደብ ከሞት በኋላ ያሰበውንና የጠየቀውን ሁሉ ተመልክቶ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየ፡፡ ራዕይ ሳይፈጸም ባለራዕይ፣ አይሞትም የሚባለው ይህ ነው ዘጻ.33፡17 ፤ ማቴ. 17፡1፡፡ ሙሴ ሕይወቱን ሥራ ሰርቶ ያለፈ በመሆኑ የሚያስተምረን ትልቁ ቁም ነገር ያለ ዓላማ የተፈጠርን አለመሆናችን እንድናስተውል ነው፡፡

የሕይወት ታሪኳ ብዙ ያልተባለላትን የማይወደድ የሚባል ተግባር የነበራት የአንዲት ሴትን ታሪክ ብንመለከት ደግሞ አስገራሚውን የሰው ልጅ የኑሮ ትርጉም ማየት እንችላለን ስሟ፣ ረአብ ይባላል፡፡ ጋለሞታ አልያ የዝሙት ተዳዳሪ እንደሆነች መጽሐፈ ኢያሱ ይነግረናል፡፡ እንደ ሌሎቹ ታላላቅ ሰዎች ሕይወትን ትርጉም የሰጠች አትመስልም ነገር ግን የተፈጠረችበትን ዓላማ በማሳካቱ መጽሐፍ ቅዱስ ከታላላቅ መንፈሳዊ እናቶች ተርታ አስገብቶ በገድለኛነት ጠቅሷታል፡፡ ዕድሜዋ ምን ያህል እንደሆነም አናውቅም ነገር ግን እግዚአብሔር ለድል የላካቸውን የኢያሱን ሰላዩች ከጠላት ደብቃ ለድል አበቃቻቸው፡፡ እስራኤል በእግዚአብሔር ኃይል ከነዓንን እንደሚይዙ አመነች፡፡ በሕይወቷ ይህንን ሥራ ሰራች ምናልባትም በዚህ ምድር ላይ የኖረችበት ዓላማ እነዚህን ስላዮች መደበቅና ለድል ማብቃት ቢሆንስ? እግዚአብሔር ያለ ዓላማ የሚያኖረው ሰው እንደሌለ በረአብ ዘማ ሕይወት ልንማር ይገባል፡፡ ዕብ. 11፡31 ፤ ያዕ. 2፡25 ይህ ሥራዋ አስመሰገናት ታሪኳ ከታላቁ መጽሐፍ ተመዘገበ፡፡ በየትኛው የኑሮ ሁኔታ የትምህርት ደረጃ እንገኝ እግዚአብሔር በውስጣችን ራዕይ አስቀምጧል፡፡

ዕድሜያችን ሲገፋ በጡረታ የምንገለል ሳይሆን ዘመን ተሻጋሪ ራዕይ አለን፡፡ ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚያደርስ የተስፋ ኑሮ አለን በስጋዊ ኑሮአችን የሞት ዋዜማ ስንደርስ እንደ መምህራችን ኢየሱስ ክርስቶስ "ተፈጸመ" ማለት አለብን፡፡ ጌታችን ለምን በዚህ ምድር እንደሚኖር ሲነግረን "እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ..." በማለት የመጣበትን፣ የተወለደበትን ግብ አስተማረን የምንመሰክረውና የምኖርለት ዓለም አለን ውስጣችንን እንየው፡፡ ዮሐ. 18፡37፡፡

ውስጣችን ምን አለ?

ይህንን ጥያቄ ለማይጠቅም ነገር አላነሣሁም፡፡ራሣችን እንደማንጠቅም ስንቆጥር የተወለድንበትን ቤተሰብ መቀበል አቅቶን ጊዜያችን ስንኮንን መታየት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ በድሀ ሀገርና ከድሀ ቤተሰብ መወለዳችን አልያ በክፉ ግዜ መወለዳችንን እያነሣን መማረራችን ግልጽ ከመሆኑም ባሻገር ዕድለ ጠማማ ነኝ፣ አቤት አውሮፓ ተወልጄ ቢሆን ተአምር እሰራ ነበር፡፡ ቤተሰቦቼ የተማሩ ቢሆኑ ኖሮ... እያልን የምንብከነከን ቤት ይቁጠረን፡፡ እግዚአብሔር በአስፈላጊው ጊዜ፣ ከአስፈላጊው ቤተሰብ፣ በተመቸ ቦታ እንድንወለድ እንዳደረገ ልንገነዘብ ያስፈልጋል፡፡ መክ.3፡1-8 አሁን የሆንነውን ነገር ብቻ እንቀበል፡፡ እኛ ባሰብንበት ሳይሆን እርሱ ያደረገን ነገር ብልጫ አለው፡፡ መኝታ ላይ እኛ አደላድለን ካስቀመጥነው ህጻን ይልቅ እግዚአብሔር በማህፀን ዘቅዝቆ ያስቀመጠው ጽንስ ምቹ ስፍራ አለው ጽንሱ በማህፀን ውስጥ መዘቅዘቁ ምቾቱን አይነሣውም፡፡ ዋናው ነገር ያለንበት ሁኔታ ሳይሆን ውስጣችን መመልከት ትልቁን ስፍራ ይይዛል፡፡

የታይላንድ ዋና ከተማ ባንኮክ ከብዙ ዓመታት በፊት ለከተማዋ እድገት መንግስት የከተማዋን ቀለበት መንገድ ለመስራት ፕላን ሲያወጣ በአጋጣሚ መንገዱ በአንድ ጥንታዊ የቡድሃ ገዳም ላይ ያልፋል፡፡ ስለሆነም ገዳሙን ወደ ሌላ ቦታ ለመውሰድ ወስነው ሌላ ቦታ ከሰሩ በኋላ የቡድሃን ሀውልት ማንሳቱ ግድ ነበርና በትልቅ ክሬን /ማሽን/ ለመንሳት ሲሞክሩ ሀወልቱ መሰነጣጠቅ ጀመረ ሁሉም ደነገጡ ፈሩ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ግን ሁሉም አይናቸውን ማመን አቃታቸው ከሀውልቱ ውስጥ ንጹህ ወርቅ አዩ ሐውልቱ በዘመናት ብዛት ወርቁ በአፈር ተሸፍኖ እንጂ በጭቃ የተሰራ አልነበረም፡፡ ዛሬ ለብዙ ቱሪስቶች የጉብኝት ቦታ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ይህንን ምሳሌ መጥቀስ ያስፈለገው ሁላችንም ብንሆን ያየነው የአሁን ማንነታችንን ብቻ ነው፡፡ አፈራችንን እስቲ እናርግፍ በእርግጥም ውስጣችን ወርቅ የሆነ መንፈሳዊ ዓላማ አለ፡፡ በዘረኝነት፣ በክፋት፣ በወሬኝነት አፍነነዋል፡፡ በንስሐ እናራግፈው ውስጣችን ወርቅ አለ የተለየ ራዕይ ማንም የማይሰራው አንተ ብቻ የምትፈጽመው ዕቅድ አለህ ለዚህ ተፈጥረሀልና፡፡ እኛ ልዩ፣ድንቅ ስራዎቹ ነን፡፡

የሰውን ልጅ ኑሮ ቀልጣፋና ተስማሚ እንዲሆን አለምን በበጎ ጎን የቀየሩ ሰዎች ሁሉንም ብንመለከት ባለ ራዕይ ሰዎች ናቸው፡፡ ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርነው ያለ ራዕይ የተፈጠረ ማንም እንደሌለ በሰፊው እይተናል፡፡ እነዚህ የለውጥ ሰዎች የሚለዩት ግን ወደውስጣቸው ማየታቸው ነው፡፡ የፊዚክስ ምሁር የነበረው አንስታይን በልጅነቱ ትምህርት የሚገባው የተጨበጨበለት ተማሪ አልነበረም፡፡ እንደውም በስንፍናው ከትምህርት ቤት ወላጅ አምጣ በመባል ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ጉንዳን የገብስ ፍሬ ተሸክሞ ወደ ጉድጓድ ሲጎትት አየ አስተዋለ፡፡ ይህ ትንሽ ፍጥረት ይህንን ከእርሱ የሚበልጥ ጥሬ ለምን ይጎትታል ብሎ ጠየቀ ዓላማ ስላለው ነው አለ ወደ ራሱ ተመለከተ የኔስ የመኖሬ ራዕይ ምንድን ነው አለ፡፡ ዓለምን ያስደነቀ ግኝት የንጽጽር ህግ (Low of relativity) አገኘ፡፡

ቶማስ ኤድሰን ሙሉ ጊዜው የሚያሳልፈው በሩን ዘግቶ በሙከራ ላይ ይጠመድ ነበር፡፡ ሰዎች ምትክ የማያበጁለትን የአለምን ዋነኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ሰራ፡፡ ይህ ድንገት ወይም አጋጣሚ አይደለም ውስጡ እግዚአብሔር ያስቀመጠውን ራዕይ የማየት ብቃት ነው፡፡ ኤሌክሳንደር ግራሐም ቤል ድምፅን ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል ተለውጦ በሽቦ ሊተላለፍ የሚችልበትን መንገድ አሰበ ሰዎች እንደ እብድ ቆጠሩት ዛሬም ቢሆን ሁላችንም ስልክ እንጠቀማለን ግን ማን እንደሰራው አስበን አናውቅም፡፡ እርሱ ግን ባለራዕይ ሰው ነበር፡፡ በሐገራችንም ለመጀመርያ ጊዜ አጼ ሚኒሊክ ስልክ ተሰርቶ ሐረር ደወሉ ሀገረ ገዢውን አናገሩት ማመን አቅቷቸው ጓሮዬ ሆነህ ነው የምታናግረኝ ብለው ወጥተው አዩ ይባላል፡፡ ብዙዎች ካህናቱም ንጉሡ ከሠይጣን ጋር ተነጋገሩ ብለዋቸው ነበር፡፡ ከሁሉ የሚደንቀው የዚህ ጥበብ ስራ ባለቤት ደግሞ መስማት የተሳነውና ስልክን አንድም ቀን ያለተጠቀመበት መሆኑ ነው፡፡ እኛ ክርስቲያኖች በህይወት አብነት የሚሆኑን ብዙ ቅዱሳን እና ቅዱሳት አንስት አሉን ሁሉም ቢሆን የህይወት ራዕይ ኖሮአቸው እስከ ፍጻሜ የፀኑ ናቸው፡፡ዕብ 12፡1 ከነዚህ መካከል አንዷን ቅድስት እናት ታሪክ በአጭሩ ለርዕሳችን እንዲመች አድርገን እንጥቀስ ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ እንደ ሌሎች እናቶች በቅድስና፣ በተጋድሎ የታወቀች እናት ናት፡፡ ነገር ግን ከሌሎቹ ቅዱሳን ብሎም ከመላዕክት ወገን እንኳ ያልተሰማን ጥረት አድርጋለች ይህውም ሰይጣንን ለማስታረቅ፡፡ ሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን ጠብ ምንጩ ሰይጣን በመሆኑ ሁሌ ሰዎችን ከማማለድ ሰይጣንን ባስታርቅ ችግሩ ይፈታል ብላ አሰበች፡፡ ውድ ክርስቲያኖች ይህን ጥያቄ ከመላዕክት ወገን የጠየቀ ማን ነው? በውስጧ ያለውን አይቻልም የሚባለውን ጥያቄ ማንሳቷ ምንኛ ብርቱ መሆኗን ያሳያል፡፡ ሰይጣን መታረቅ አልፈለገም እንጂ፣ እንደ እርሷ ጥረት ተሳክቶ ታርቆ ቢሆን አስቡት፡፡ መንፈሳዊ ራዕይ በጥልቀትና በትልቁ እንድናይ ያደርጋል፡፡

ስንፍና ተጭኖን አልችልም አይሆንም ከማለት በትጋት መክሊታችንን ለይተን መጣር ተገቢ ነው ራዕይ ካለን ወደ ተግባር ለመግባት ያነሣሣል አልያ ግን እንደ ተወለድን መሞት ፍፃሜያችን ይሆናል፡፡

የባለ ራዕይ ሰው መገለጫ

ብዙ ሰዎች ሕይወታቸው እግዚአብሔር እንድትሆን ከፈጠራት በተቃራኒው ይኖራሉ ምክንያቱ ደግሞ የተፈጠሩበትን ዓላማ አለማወቃቸው ነው፡፡ ሥራ እንኳ ሲሰሩ አንዴ የያዟትን ሥራ በተለየ መልኩ መሞከር በተሻሻለ መልኩ መስራት የተሻለ ለመቀየር ፍርሃት ያድርባቸዋል፡፡ ስለዚህም ሕይወት ከውኃ ማንበጫረቅ የተለየ አይሆንም፡፡ ለነዚህ ዓይነት ሰዎች ደግሞ ሕይወት አሰልቺ ትሆንባቸዋለች፡፡ እኛስ ነገሮችን በተለየ መልኩ የማየት ልምዱ አለን ወይ ? እስከ ዛሬ ማስቀደስ ብቻ ከሆነ የተሻለ አድርገን ቆራብያን መሆን፣ የተነበበውን ወንጌል መሳለም አልፈን ገላልጠን የምናነብ መሆን የህይወትን ትርጉምም ይቀይራል፡፡ ታላቅ ራዕይ ያላቸውን ሰዎችም ነገሮችን በተለይም ለሕይወት ያላቸው አተያይ ለየት ያለ በመሆኑ በሚከተለው ነገሮች የተገለጡ ናቸው፡፡

ስነ ምግባራዊ ኑሮ ይኖራሉ

ስነ ምግባር ከአንደበት አልያ ከቃል ይልቅ አብዝታ ትናገራለች ይባላል፡፡ ማናችንም ብንሆን ውስጣችን ባለው ዕውቀት መጠን ላንታወቅ እንችላለ፡፡ ትልቁም ዋጋ የሚሰጠን በተማርነው መጠን አልያ በሀብታችን ልክም አይደለም፡፡ ነገር ግን ስነ ምግባር ሁሉንም ሲያስተምር ተወዳዳሪ የለውም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም "ብርሃናችሁ በሰዎች ፊት ይብራ" በማለት በጎ ምግባርን የባለራዕይ ሰው መገለጫ አድርጎ ጠቅሷል፡፡ መታወቅም ያለብን በተግባራችን እንጂ በምናወራው የምንታወቅ መሆን የለብንም፡፡ በተለይ በአሁኑ ዘመን በተግባር የማይታወቅ ወሬያቸው አልያ ንግግራቸው ብቻ ቀድሞ ያሳወቃቸው ለውድቀታቸው በር ሲጠርጉም ማየት የተለመደ ነው፡፡ በመልክ የማናቃቸው በዘመናችንም ያልኖሩ ነገር ግን በኛ ዘመን እንደኖሩ ያህል እስኪሰማን ድረስ የምንወዳቸው የምናከብራቸው ባለራዕይ ሰዎች አሉ ሀገር በመውደዳቸው፤ ሐይማኖት በማስከበራቸው፣ ለወንጌል በመቆማቸው፣ በቅድስናቸው የምናውቃቸው ጥቂት አይደሉም፡፡ የዚህ ምስጢር ደግሞ ስነ ምግባራዊ ኑሮአቸው ነው፡፡ የሐዋርያትን አጠቃላይ ሕይወት በአጭሩ የሚነግረን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሐዋርያት ሥራ ነው፡፡ ግብ ስለነበራቸው ሕይወታቸው በግልጽ ራዕይ የተዋበ በመሆኑ በትውልድ መካከል ለውጥ አምጥተዋል፡፡ አይነኬ የሚመስሉ መንግስታትን አነቃንቀዋል፤ ዓለምን ለውጠዋል በነገስታቱ ዘንድም ዓለምን ያወኩ ናቸው ተብለዋል፡፡ እኛ ማንን ለወጥን፣ ምን እየሰራን ነው ብለን ስንጠይቅ መልሳችን ምን ይሆን? ደግሞ መጣ፣ መጣች የምንባል ወይስ መምጣታችን መሰባሰባችን፣ መዘመራችን፣ መናገራችን የሚናፈቅ እንሆን? ሐዋርያት ተፈርዶባቸው ሲገደሉ እንኳ ክፉ ተግባር እንደሌላቸው እየታወቀ በሐሰት ምስክር ነበር መከራ የሚጸናባቸው፡፡

የራሳቸውን ዓላማ ብቻ ይሰራሉ

ለሁሉም ነገር አልተፈጠርንም የተለየንበት የራሳችን ዓላማ ልዩ ሥራ አለን፡፡ ማንም ሰው ቢሆን ሁሉንም ሥራ ሊሰራ እንዳልተፈጠረ ሁሉ ምንም የማይሰራም ሆኖ አለመፈጠሩን ያውቃል፡፡ ብዙዎቻችን የራሣችን ሥራ እንዳለን ባለማወቃችን የተነሣ ምን መሆን እንዳለብን እንኳ መለየት አቅቶናል፡፡ ያሸነፈና ወርቅ የተሸለመ ሯጭ ስናይ ሯጭ መሆን፣ ጥሩ የተወነ አርቲስት ሰናይ አርቲስት፣ መሆን ጥሩ ሰባኪ፣ ስናይ ሰባኪ መነኩሴ ስናይ መነኩሴ፣ መሆን የሚያምረን ቀላለ አይደለንም፡፡ ይህ ሁሉ የሚመነጨው የሰዎችን ስራ ከራሳችን ሥራ ጋር ቀላቅለን መስራት መፈለጋችንና የራሳችንን ራዕይ አለማወቅ ነው፡፡ እኛ ግን ሁሉንም መሆን አንችልም የራሳችን ብቻ ስለሆንን፡፡ የተፈጠርንበትን ዓላማ ለይተን መስራት ያስፈልጋል፡፡ ቅዱስ ያሬድ የተለየበትን የራሱን ዓላማ ለይቶ በዜማው ተመስጦ ታሪክ ሰራ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀገር ማስተዳደር ዕድል ተሰጥቶት ነበር፡፡ የራሱ ዓላማ ግን ለወንጌል መኖር ስለነበር የራሱን ዓላማ አከናወነ በተለይ እኛ ክርስቲያኖች ሁሉ አማረሽ ሳንሆን በሕይወት ወስኖ የራሳችንን ዓላማ ብቻ ለማከናወን ልንጥር ይገባል፡፡ ልዩ ሆነን የተፈጠርንበት ዓላማ አለንና፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ይቆየን.....

የፎንት ልክ መቀየሪያ