Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

"ውዳሴ ከንቱ የዘመናችን በሽታ"

በመምህር ሙሴ ኃይሉ (B.TH, MA In plilo)

 • "ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ አትሁኑ" ኤፌ.6፡6

 • "ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉት" ቈላ.3፡22

ውዳሴ፡- ወደሰ ከሚል ግስ ተገኝቶ ማወደስ፣ መወደስ፣ አወዳደስ፣ ውደሳ፣ ምስጋና... የሚል ትርጉም ያስገኛል፡፡ ውዳሴ ማርያም፣ ውዳሴ አምላክ... ሲል የማርያም ምስጋና፣ የአምላክ ምስጋና የሚል እንደሚያስገኝ፡፡

ማመስገን፣ መመሰጋገን በመሠረቱ ከጥንቱ ከጥዋቱ የተመለከትን እንደሆነ በተሠራ ሥራ፣ በተከወነ ምግባር ትሩፋት፣ በተኖረ መንፈሳዊ ሕይወት... ሲሆን ተገቢና መልካም ነው፡፡ ይህንን "ውዳሴ" ማለት ምስጋና የሚገባ ስለሆነ ሰጪውም ሆነ ተቀባዩ ከሚያስመሰግናቸው ውጪ አንድም ነገር የሚያስነቅፋቸው ሁኔታ የለም፡፡ በእርግጥ ከታሪከ ቅዱሳንም (ከሕይወተ ቅዱሳን) በሰፊው እንደምንማረው ለእነዚህ ቅዱሳን አበው ወእመው ከቅድስና መዓርግ ማለት ቅዱስ፣ ቅድስት ብሎ ከመሠየም አንስቶ ቅድስናቸው ተከትሎ የሚሰጡት የቅድስና ውዳሴ ተቀባዮቹ ወይም የተደረሰላቸው ቅዱሳን ፈልገውት ወይም ስጡን፣ አመስግኑን፣ መልክዕ ጻፉልን፣ ገድል ደጉሱልን ብለው ሳይሆን ቤተ ክርስቲያን ያላትንና ከአዶናይ እግዚአብሔር የተቀበለችውን ሰማያዊ ስልጣን ተጠቅማ ይገባቸዋል፣ ይስማማቸዋል፣ ይፈቀድላቸዋል በማለት የምትፈጽመው የፍቅርና የአክብሮት ውዳሴ ነው፡፡

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ይህንን መንፈሳዊ ቀኖና ተከትሎ ነው ሲሠራበት የኖረው፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ ግን አንድ ቅዱስ ይህን አድርጉልኝ ሲል ተሰምቶም፣ ተነቦም አይታወቅም፡፡ ቅዱሳን በሕይወተ ሥጋ እያሉ ለሚኖሩትን ሕይወት የሚስማማ የክብር ስም በደቀ መዛሙርቶቻቸው እንኳ ሳይቀር ሲነገራቸው በአትሕቶ ርእስ እያስተባበሉ፤ ያራቀቁትን የዕውቀት መጠን ሲነገራቸው እንዳልተማሩ በመሆን ዘመናቸውን ሙሉ ካሳለፉ በኋላ ለትውልድ መካሪና አስተማሪ ይሆን ዘንድ የሕይወታቸውን ቅድስና፣ የዕውቀታቸውን ምጥቀትና ጥልቀት በሚያውቁ አርድእቶቻቸው የተጻፈ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንጂ እነርሱ ስለራሳቸው የጻፉትም ያሉት ውዳሴ ርእስ የለም፡፡ ይህንን ውዳሴ ወይም ምስጋና የሚገባ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ከጥቅም ውጪ ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ጉዳት የሌለበት ውዳሴ ስለሆነ በፈጣሪ ለተመሰገኑ ቅዱሳን ማመስገን ታሪክና መጻሕፍት እንደሚያስረዱን ትውፊታዊ እውነት ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ውዳሴ የሚያወድስም ቢሆን ባወደሰበት አወዳደስ ይወደሳል ማለት ነው፡፡ ውዳሴ ዘለክብር ነውና፡፡

"ከንቱ" የሚለው ቃል ትርጉም የማያስፈልገው በቁሙ ትርጉም የሆነ ቢሆንም የማይጠቅም፣ የማያስፈልግ፣ ረብ የለሽ፣ እርባና ቢስ... ተብሎ ሊተነተን ይችላል፡፡ ታድያ ይህንን "ከንቱ" የሚል ቃል ከላይ ከተመለከትነው "ውዳሴ" ጋር አብሮ ሲነበብ ሙሉ በሙሉ የዚህን መልካም ትርጉምና እሴት ቀይሮ የማይጠቅም ምስጋና፣ ረብ የለሽ ምስጋና... የሚል ትርጉም እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ ስለዚህ "ከንቱ ውዳሴ" ማለት እርባናየለሽ ምስጋና፣ ውሸት የሆነ ምስጋና፣ የማይጠቅም ምስጋና... ማለት ነው፡፡

 • ከንቱ ውዳሴ የሚገለጽባቸው መንገዶች፡-

ውዳሴ ከንቱ ከምናስበውና ከምናምነው በላይ እጅግ በጣም በረቀቀ ሁኔታ እየተገለጸ ሰዎችን በክፉ የጦር ፍላጻ ወግቶ የሚጥል መድኃኒት የለሽ በሽታነው፡፡ ውዳሴ ከንቱ በመጀመርያ ተወዶ በመጨረሻ የሚጠላ፣ በመጀመርያ ጣፍጦ በመጨረሻ የሚመርር፣ በመጀመርያ ትልቅ አድርጎ በመጨረሻ ትንሽ የሚያደርግ "ውኃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው" እንደሚባለው ዓይነት የመገለጫ ዘይቤ የሚከተል የረቀቀ የሰዎች ጠላት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ምንም ያልተማረ ሲሆን "ሊቀ ሊቃውንት" ብሎ መሰየሙ፤ የጠብና የነገር አባት ሲሆን "መልአከ ሰላም" ብሎ መጥራቱ፤ መጻሕፍተ ብሉያትም ይሁኑ መጻሕፍተ ሐዲሳት በዋሉበት ሳይውል ባደሩበት ሳያድር ማለትም በአግባቡ ሳይቀጽል መጋቤ ሐዲስ፣ መጋቤ ብሉይ እያሉ ማወደሱ... ተቀባዩን በመጀመርያ እያስደሰተ እውነት አለመሆኑን (አንድም በሞት አንድም በትምህርት) ሲያውቁ ደግሞ እያሳዘነ ሰዎች ያልሆኑትንና ያልደረሱትን ሕይወት ገንዘብ እንዳደረጉ እያስመሰለ ሳይሆኑ ከሁሉም እንዲቀሩ፣ በማይጠቅም ምስጋና እንዲታጠሩ የሚያደርግ የተሳለ ኲናት (ጦር) ነው፡፡ መምሰል የመሆን ተቃራኒ ከመሆኑም በላይ ለክርስትና ሕይወት ጠንቅም በመሆኑ አምላካችን "ቅዱሳን ሁኑ" ብሎ አስተምሮናልና (ዘሌ.11:44)፡፡ "ውዳሴ ከንቱ" ከንቱነቱ እንዳይታወቅበት ለሁሉም ሰው ማለትም ሊተጥም ይሁን ለሚቀበል በሚወደው ዘይቤ ብቻ እየተገለጸ የሚያስመስል የሐሰት አገልጋይ ነው፡፡

 • ውዳሴ ከንቱ መገኛው ወይም ምንጩ ከየት ነው?

"ውዳሴ ከንቱ" እንደ ስሙ ከንቱ በመሆኑ ከእግዚአብሔር የተገኘ ጸጋ ሳይሆን ከውዳሴ ከንቱ ፈላጊዎች ፍጡራን ተገኝቶ ለእነርሱ እንደየፍላጎታቸው እያገለገለ ዘመናትን አስቆጥሮአል፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ያስገኘው "ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና" (ዮሐ.8፡14) በማለት ጌታችን እንዳስተማረን ከራሱ ለራሱ በራሱ አፍልቆ ለመጀመርያ ጊዜ ከንቱ ውዳሴን ተግባራዊ ያደረገ የኃጢአትና የሞት መገኛ (የክፋት ሁሉ መገኛ) የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው፡፡ ነገደ መላእክት ካለመኖር መጥተው ምስጢረ ግኝታቸው ስለረቀቃቸው "መኑ ፈጠረነ ወእምኃበ አይቴ መጻእነ፡- የፈጠረን ማን ነው የመጣነውስ ከየት ነው ብለው እርስበርስ በተነጋገሩ ጊዜ ሳጥናኤል አለቃ ስለነበረ ከፍ ብሎ ቢመለከት ከእርሱ ሰባት እጥፍ የረቀቀ ፈጣሪው ማየት ባለመቻሉ፤ ዝቅ ብሎ ቢመለከት እርሱ የሚመራቸው ነገደ መላእክት ሆነው ሲያይ "ካለመኖር በማምጣት የፈጠርኳችሁ እኔ ነኝ" ብሎ የትዕቢት ሐጢአትን ካስገኘበት ቅጽበት ጀምሮ አብሮ የተገኘ የዚሁ የድፍረት ኃጢአት አካል ነው፡፡

በመሆኑም እግዚአብሔር አምላክ ለአዳም ሁሉንም ሰማያውያንም ይሁኑ ምድራውያን ጸጋዎች አብዝቶ ካከበረው በኋላ የፈጣሪን አዛዥነት የፍጡርን (የአዳምን) ታዛዠነት የሚገለጽበት ሕግ መኖርና መስጠት ግድ ስለነበረበት "ከዕፀ በለስ እንዳትበላ ከበላህ ግን የሞት ሞት ትሞታለህ" ብሎ የመጀመርያ የሆነው ሕግ ልቡናዊ ሰጠው፡፡

አዳም አፈጣጠሩ ሳጥናኤል በትዕቢት ምክንያት ከነገደ መላእክት ተባርሮ ወደ እንጦርጦስ ከተወረወረ በኋላ በፊት መቶ ነገድ የነበሩትን አንድ ነገድ ስለጎደለባቸው "ፈጠረ ሰብአ ህየንቴከ፡- በአንተ ፈንታ ሰውን ፈጠረ" እንዲል አዳም እጅግ መልካም ሆኖ የተፈጠረው በእርሱ ቦታ ስለነበረ እኔ ያጣኋትን ገነት እንዴት አዳም ያገኛታል በማለት በክፉ ልቡና ተነሳስቶ አዳምን ለማሳሳት እባብን መስሎ አንድም በእባብ ላይ አድሮ "የሰማይና የምድር ንጉሥ የሆንክ አዳም ሆይ..." በማለት ነገሩን ሲጀምር ቃለ ውዳሴው ከንቱ መሆኑን አውቆ "ምድርንስ ጌታዬ ሰጥቶኛል በሁሉም ፍጥረታትንም ሾሞኛል የሰማዩን ግን አልሰጠኝም አይቻለኝም..."ብሎ ገና ሲመልስለት ሊያሳስተው እንደማይችል አውቆ ወደ ሔዋን እናታችን ቀረብ ብሎ "የሰማይና የምድር ንግሥት ሔዋን ሆይ..." ብሎ ቢጠራት ይኸው ከንቱ ውዳሴ በደስታ ስለተቀበለችው በዚህች ቀዳዳ አበጅቶ እስከ መጨረሻ ድረስ እጅ አስዘርግቶ በድፍረት ቅጠል እስከመበጠስ አስደርሶ ለሞተ ሥጋ ለሞተ ነፍስ ቅጣት የዳረገ ከጥንተ ጠላታችን የተገኘ ጥንተ ጠላት ነው፡፡

የከንቱ ውዳሴ ፍጻሜ ወይም ውጤት ሁልጊዜም ቢሆን ሞትና ውድቀት መሆኑን የመጀመርያ አስተማሪያችን ይኸው ክስተት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ እስከ አሁንም ቢሆን የከንቱ ውዳሴ ውጤት ሞት እንጂ ሕይወት ሆኖ አያውቅም፤ ሊሆንም አይችልም፡፡ ውዳሴ ከንቱ ሰዎች ለዘመናት የገነገቡትን ሃይማኖታዊ የሥነ ምግባር ግንብ በጥቂት ቀናት (በሰዓታትም ጭምር) የሚያፈርስ የክርስቲያናዊ ሕይወት ጠንቅ ነው፡፡ ውዳሴ ከንቱ ለዚህ ዓለም የሚመች ምድራዊ ፍላጎት እንጂ ፍጹም ለመንፈሳዊው ዓለም ምንም የማይበጅ ፀረ ክርስትና ነው፡፡ ምክንያቱም በከንቱ ውዳሴ የሚሠራ ማንኛውም ሥራ ለሰዎች ወይም ለታይታ የሚፈጸም በመሆኑ አገልግሎቱም የአገልግሎት ውጤቱም እዚሁ ምድር ላይ ከሰዎች የሚገኝ የሚታጣ ነገር ስለሆነ ጌታች መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚህ ሕይወት ተጠበቁ በማለት አስተምሮናል፡፡

 • "ለሰዎች ትታዩ ዘንድ ምጽዋታችሁን በፊታቸው እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ፤ ያለዚያ በሰማይ ባለው አባታችሁ ዘንድ ዋጋ የላችሁም። እንግዲህ ምጽዋት ስታደርግ፥ ግብዞች በሰው ዘንድ ሊከበሩ በምኩራብ በመንገድም እንደሚያደርጉ በፊትህ መለከት አታስነፋ፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። አንተ ግን ምጽዋት ስታደርግ ምጽዋትህ በስውር እንዲሆን ቀኝህ የምትሠራውን ግራህ አትወቅ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል። ስትጸልዩም እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በመንገድ ማዕዘን ቆመው መጸለይን ይወዳሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል" ማቴ.6፡1-5 እንዲል፡፡

አይሁዳውያን፣ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ውዳሴ ከንቱ ልማዳቸው ብቻ ሳይሆን የዘወትር ምግባቸውም እንደነበረ በመጻሕፍተ ሐዲሳት ጌታችን የገሰጻቸው ትምህርቶችን መመልከቱ በቂ ነው፡፡ መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስም ከእነርሱ ወገን የተላኩ መልእክተኞች መጡና በክፉ ልቡና ተነሳስተው ለማሳሳትና ለማስወንጀል በማሰብ "መምህር ሆይ፥ እውነተኛ እንደ ሆንህ በእውነትም የእግዚአብሔርን መንገድ እንድታስተምር እናውቃለን፥ ለማንምም አታደላም፥ የሰውን ፊት አትመለከትምና፤ እንግዲህ ምን ይመስልሃል? ንገረን ለቄሣር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም? አሉት። ኢየሱስም ክፋታቸውን አውቆ። እናንተ ግብዞች፥ ስለ ምን ትፈትኑኛላችሁ? (ማቴ.22፡16-18)" ብሎ በመመለስ ከከንቱ ውዳሴ የራቀ መሆኑን አስተምሮ እነርሱም እንዲማሩ መክሮ ፈተናቸውም በአግባቡ መልሶ ወደ ተላኩበት ክፍል ሄደው እንዲያስረዱ በሰላም አሰናብቶአቸዋል፡፡

አንድ ወጣትም እንዲሁ መጥቶ የከንቱ ውዳሴ ጣዕም አቅርቦ በሰጠው አሰጣጥ እንዲቀበል ንግግሩ ሲጀምር ምን እንደፈለገ አስቀድሞ የሚያውቅ "ማእምረ ኩሉ" ሁሉን አዋቂ አምላክ ስለሆነ ተናግሮ ሳይጨርስ የሚናገረውም ሆነ ለመቀበል የፈለገው ሳያገኝ፣ የጠየቀውም በሕይወቱ ሳይመልስ ፊቱን ጠቁሮ ወደ ቤቱ ተመልሶአል፡፡

 • "እርሱም በመንገድ ሲወጣ አንድ ሰው ወደ እርሱ ሮጦ ተንበረከከለትና። ቸር መምህር ሆይ፥ የዘላለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ? ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም፦ ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም" (ማር.10፤17-18) በማለት መልሶለታል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ አምላካዊ ስብከቱ የከንቱ ውዳሴ ከንቱነትና ሁላችንም ከዚሁ የተሳሳተ አመለካከት እንድንቆጠብና ፈጽመን እንድንጸየፈው ለማስተማር ፈልጎ ያስተማረው ትምህርት ነው እንጂ እርሱስ ክብር ይግባውና ቸርነት የባሕርዩ የሆነ አምላክ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ የመጣውን ወጣት ግን በአምላክነቱ አምኖ በትምህርቱና በተአምራቱ ተማምኖ ስላልነበረ የልቡናውን ፍላጎት አውቆ ይህንን መልሶለታል፡፡ "ምን ላድርግ" ብሎ ለጠየቀው ጥያቄ ትእዛዛቱ በፍጹም ኃይሉ፣ በፍጹም ነፍሱ፣ በፍጹም ልቡ እንዲያከብር ሲነገረው በትዕቢት "ከሕጻንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ" ማለቱ የአመጣጡ ዓላማ ከንቱ ውዳሴ ሰጥቶ ከንቱ ውዳሴ ተቀብሎ ለመሄድ ስለነበረ "እንግዲያውስ ያለህን ሁሉ ለድሆች ስጥና ተከተለኝ" የሚል ሐዋርያዊ ጥያቄ ሲቀርብለት ፊቱ ጠቁሮ፣ በልቡናው አርሮ መመለሱ መፍቀሬ ውዳሴ ከንቱ መሆኑን ይስገነዝበናልና፡፡ (ማር.10፡22)

ውዳሴ ከንቱ የማይጠቅም፤ በፈተና የሚጥልና ለትዕቢት የሚጋብዝ ረብ የለሽ ምስጋና በመሆኑ አባቶቻችን አምላካቸውን አብነት አድርገው እየራቁት፣ እየሸሹት ሙሉ ዘመናቸውን በሕይወት ኖረዋል፣ በመጻሕፍቶቻቸውም ጽፈዋል፡፡ ምክንያቱም ከመጀመርያ ከሳጥናኤል ጀምሮ በዚህ የከንቱነት ፍላጎት ምንኛ እንደተጎዱ ጠንቅቀው የሚያውቁ ማእምራነ መጻሕፍት ናቸውና፡፡

ለምሳሌ፡-
 • አዳም በከንቱ ውዳሴ "አምላክ ትሆናለህ" ሲባል ያልተሰጠውንና ያልተፈቀደለትን ክብር ፈልጎ የሞት ሞት ሞተ፡፡ ዘፍ.3፡1
 • ናቡከደነጾር ከከንቱ ውዳሴም በላይ ራሱ አምላክ ሆኖ ለምን አልተመለኩም በማለቱና የፈጣሪን ልዕልና ዘንግቶ በትዕቢት ራሱን ስላሳበጠ አምላክነቱን አውቆና አምኖ እዲያመልክ ከሰው ተለይቶ በምድረ በዳ ውስጥ ሣር እስከመጋጥ ደርሶአል፡፡ ዳን.4:33
 • ሄሮድስም እንዲሁ በትዕቢትና በብዝሐ ውዳሴ ከንቱ መስሎት የሚኖረውን ሕይወት የእውነት የሆነና የሚሆን መስሎት ለሕዝቡ በተናገራቸው ጊዜ "ይህ የእግዚአብሔር ድምጽ ነው የሰውም አይደለም" ብለው በጮኹ ጊዜ በድፍረት ዝም ብሎ አምኖ በመቀበሉ ፈልቶ ተልቶ ኳ ኮርኳ ብሎ ደርቆ እስከ መሞት ደርሶአል፡፡ ሐዋ.12፡21-23

ይህ በእንዲህ እንዳለ ውዳሴ ከንቱ እንዲጠፋ ትክክለኛዎቹ (እውነተናዎቹ) የተማሩ መምህራን ቢያስተምሩም በተለይ በዚህ ዘመን ተፈላጊነቱ በጣም ጨመረ መሰለኝ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየገነነ መጥቶአል፡፡ የሚገርመው ግን ይህን ጉድ በስፋት የሚታየው በአገልጋዮች በኩል መሆኑ ነው፡፡ በቤተ መንግስት እየጠፋ በቤተ ክርስቲያን አከባቢ ደግሞ እየተስፋፋ በመሄድ ላይ ስለሚገኝ ስለዚሁ ውዳሴ ከንቱ በስፋት በሕብረተሰቡ (ከአገልጋዮቻችን) በይፋ እንዲወገዝ መወያየት፣ መመካከርና ግንዛቤአችን ማዳበር እንዳለ ሆኖ የእነዚህ ከንቱ ውዳሴ ፈላጊ አገልጋዮች አከፋፈልና ለሚዳርገው የሥነ ምግባር ብልሽቶች በተመለከተ የጸሐፊው ስምና አድራሻ የማይገልጽ ግን ከዚህ ርእስ ጋር አብሮ የሚሄድ ጽሑፍ በቤተ መጻሕፍት ውስጥ ስለአገኘሁና ጥሩ ሆኖም ስለአገኘሁት እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ፡፡

 • "በመቀጠል ውዳሴ ከንቱን በተለያየ መልኩ የሚፈልጉ ስድስት [ዓይነት ሰዎችን ፀባይ] እንመልከት፡፡

 1. የመጀመሪያዉ ሰው [ፀባይ] ሲያገለግል ያዩትንና ያዳመጡትን እንዲያመሰግኑት አይገፋፋቸውም፤ ባመሰገኑት ጊዜ ግን በውስጡ በጣም ይደሰታል፡፡ ነገር ግን በውጫዊ ገጽታው ደስታውን ስለማይገልጽና ክብሩን የሚንቅ ስለሚመስል መደሰቱን ማንም አያውቅበትም፡፡
 2. ከዚህ ለየት ያለ ሰው ደግሞ ሰዎች ሲያመሰግኑት በልቡ ደስ የሚሰኘውና የበለጠ እንዲያመሰግኑት የሚገፋፋቸው ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ [ፀባይ ያለው] ሰው ዘወትር በንግግሩ መሃል እርሱ የሚመሰገንበት አንዳንድ ቃላትንና ሐረጋትን ይጠቀማል፡፡ ምንም ግኑኝነት ሳይኖረው የማንኛውም ወሬ ርእስ ርእሱ ወደ ሚመሰገንበት የወሬ ርእስ ይቀይረዋል፡፡ አመስጋኞቹንም ስለ እርሱ አንዲያወሩ ያበረታታቸዋል፡፡ ለምሳሌ "ጥሩ ሰብኬአለሁ? ወይም ጥሩ ዘምሬአለሁ?" ብሎ ባይናገርም እንደሚያደንቁት እያወቀ እያወቀ "ስብከቱ (መዝሙሩ) እንዴት ነበር?" በማለት ይጠይቃል፡፡ የጥያቄው ሽፋንም ድክመቴን ለማረም የሚል ነው፡፡ ግን ይህ ሰው የሚጠይቀው በዕውቀት የሚበልጡትንና ከነቀፋ ጋር ድክመቱን ሊነግሩት የሚችሉትን ሰዎች ሳይሆን በእውቀት ከእርሱ የሚያንሱትንና ያደንቁኛል (ያመሰግኙኛል) ብሎ የሚገምታቸውን ሰዎች ነው፡፡
 3. ከሁለቱም የሚብሰው ደግሞ የሚመሰገንበትን መልካም ሥራ ጠብቆ ብዙ ሰዎች በተሰበሰቡበት ሰዓት ለታይታ የሚሠራ ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው ሆን ብሎ የዘወትር ተግባሩ ያልሆነውን ሥራ በማስመሰል የሚሠራው ሰዎች ያመሰግኑት ዘንድ ብቻ ስለሆነና ከንቱ ምስጋናን ስለወደደ ከአምላኩ የሚገኘው አንዳች በረከት የለም፡፡
 4. ከላይ ከተሰቀሱት ከሦስቱ የባሰው ሰው ደግሞ ውዳሴ ከንቱ ስለሚወድና ሌሎች ባመሰገኑት ምስጋና ስለማይረካ ስለመልካም ሥራው እየተናገረ ራሱን በራሱ የሚያሰግነው ነው፡፡ ይህ ሰው ማንንም ሳያፍር በድፍረት ስለ በጎ ምግባሩ ስለሚናገር በትዕቢት፣ በትምክህተኝነት፣ በኩራትና በከንቱነት ኃጢአት ይወድቃ፡፡ ከዚህ አልፎም ባልሠራው ሥራ ራሱን ወደሚያመሰግንበት የከፋ ደረጃ ላይ ይደርሳል፡፡
 5. እስከ አሁን ድረስ ከጠቀስናቸው ከአራት ሰዎች በጣም የከፋው ደግሞ ምስጋናን የሚናፍቅና ሆን ብሎ የሚጠብቅ ሰው ነው፡፡ ያመሰግነኛል ብሎ ከሚያስበው ሰው እንደጠበቀው ሳይመሰገን ከቀረ ያንን ሰው እንደ ጠላቱ ያየዋል፣ ክብሩን እንደቀነሰበትና ከደረጃውም እንዳሳነሰው ይቆጥረዋል፡፡ የውዳሴ ከንቱ ጥማቱን በሚያረካ መልኩ ስላላመሰገነውም ከዚህ ሰው ጋር ሊጣላም ይችላል፡፡ እንግዲህ ይህ ሰው አመስጋኙን እንደሚፈልገው ስላላመሰገነው ብቻ የሚጠላው ከሆነ የሚነቅፈውንና የሚያርመውን ደግሞ ምን ያደርገው ይሆን? ያለምንም ጥርጥር እንዲህ ዓይነቱ ሰው ከታላላቆቹ፣ ከአባቶቹ፣ ከመምህራንና ከካህናት የሚሰነዘረውን ተግሳጽና ነቀፋ በተአምር አይቀበልም፡፡ ለእርሱ ጥቅምና እድገት ብለው ቢገስጹት እንኳ ተግሳጻቸውን እንደ ክፉ ቁጣ፣ የቅንዓትና የምቀኝነት ውጤት አደርጎ ይወስደዋል፡፡
 6. የመጨረሻውና እጅግ በጣም የከፋ ባሕርይ[ፀባይ] ያለው ሰው ደግሞ ለውዳሴ ከንቱ ካለው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ ብቻውን መመስገን የሚሻውና ስለእርሱ ክብር ብቻ እንዲነገር የሚወደው ነው፡፡ ምስጋናንንና ክብርን ለራሱ ብቻ ስለሚሻ ሌላ ሰው ሲመሰገን መስማት አይፈልግም፡፡ ቢሰማ እንኳን አመስጋኙን ይጠላዋል፣ ለተመሰገነውም ሰው ምቀኛ ይሆናል፡፡ ከእርሱ ውጪ ሌላውን ስላመሰገነም አመስጋኙን እንደ ጠላቱ እና ጓደኝነቱ እንደተቋረጠ ሰው አደርጎ ይመለከተዋል፡፡ ከዚህ በፊት እርሱን ያመሰግነው የነበረውን አሁን ግን ሌላ ሰውን ሲያመሰግን የሰማውን ጓደኛውን ባሏን ጥላ እንደሄደች ሚስት ይመለከተዋል፡፡ የተመሰገነውንም ሰው ስም ማጥፋት ይጀምራል፣ ብቸኛ ተመስጋኝ እርሱ ብቻ መሆን እንዳለበት ስለሚያስብም በሐሰት ይከሰዋል፡፡

ከላይ ከተመለከትናቸው የስድስቱ ሰዎች ባሕርያት [ፀባዮች] አንጻር ውዳሴ ከንቱ ቀጥለው ለተዘረዘሩት የሥነ ምግባር ብልሽቶች ይዳርጋል፡፡

ሀ. ምስጋናን ለራሱ የሚፈልግ ሰው ግብዝ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ስለዚህ በሰዎች ፊት የተትረፈረፈ ሥነ ምግባር ያለው ሰው መስሎ መታየትን ይሻል፡፡ ለምሳሌ በማይጾምበት ወቅት ጿሚ መስሎ ይታያል፡፡ በልቡ ጥላቻ ሞልቶ ሳለ ይቅርባይ ለመምሰል ይሞክራል፡፡ በሌሎች ላይ ሴራን እያሴረም እንደሚያፈቅራቸው ይናገራል፡፡ በአጠቃላይ ግብዝነት በሕይወቱ ነግሷል፡፡

ለ. እንደዚህ ዓይነቱ ሰው ቁጡ እና ትዕግስት አልባ ነው፡፡ ከሚነቅፈውና በአሳቡ ከማይስማማው ሰው ጋር ይጣላል፡፡ ከእርሱ በቀር ሌላዉን ሰው ሲያመሰግን የሰማውንም ሰው ይጠላዋል፡፡ ለዚህ ሰው "ክብር" ማለት "የሚመለክ ጣዖት" ማለት ነው፡፡ ዘወትር "ክብሬ... ሥልጣኔ..." ሲል ይሰማል፡፡

ሐ. ለታይታና ለከንቱ ምስጋና የሚኖር ሰው በምቀኝነትና በጥላቻ የተሞላ ነው፡፡ ከእርሱ የበለጠ ሥልጣንና ክብር ባገኘው በማንኛውም ዓይነት ሰው ላይ ቀና ልቡና የለውም፡፡ በምቀኝነትና በቅንዓት ይገረፋል፣ እነዚህም ባሕርያት [ፀባዮች] ለክፉ ስሕተቶች ይዳርጉታል፡፡

መ. ውዳሴ ከንቱን መሻቱ ባልተረጋጋና ቋሚ ባልሆነ ሁኔታ እንዲኖር ያደርገዋል፡፡ ሁልጊዜ የሚመርጠው ምስጋናን የሚያስገኝለትን ቦታ ነው፡፡ አንድ ቦታ ላይ ሲመሰገን ኖሮ ምስጋናን ከጠገበ በኋላ ወደ ማይታወቅበት ቦታ ሄዶ ዝናው ታውቆለት በውዳሴ (በምስናገና) መኖር ይፈልጋል፡፡

ሠ. ምስጋናን ለራሱ የሚያደርግ ሰው ሐሰተኛ ነው፡፡ ጥፋቱን በመሸፈን ክብሩን ለማስጠበቅ ሲል ይዋሻል፣ ያታልላል፡፡ እርሱ ጥፋት አልባ እንዲሆን የራሱን ጥፋት በሌሎች ላይ ያደርጋል፡፡ የራሱ ያልሆነውን ሥራ የራሱ እንደሆነ አድርጎ በመናገሩ ራሱን በሐሰት ያገናል፡፡ እንዲሁም በሰዎች ፊት የሁሉ የበላይ ይሀን ዘንድ ሌሎችን እያቋሸሰ ከበታች በማድረግ ስለ ችሎታውና ስለክብሩ ብቻ ያወራል ..." ይላል በቤተመጻሕፍት ያገኘሁት ጽሑፍ፡፡

ከንቱ ውዳሴ ሥጋዊ ሥርዓት፣ የአሕዛብ ተልዕኮና ልማድ በመሆኑ ከዚህ የከንቱነት መገለጫ ርቀን ከመስጠትም ሆነ ከመቀበል እንድንቆጠብ መድኃኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ እና ተከታዮቹ አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት በመዋዕለ ስብቶቻቸው በአጽንኦት ኮንነው አስተምረውናል፡፡

 • "እኔ እላችኋለሁ ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል" ማቴ.12፡36
 • "የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ተብሎ እንደተጻፈ በእውነት ትንቢት ተናገረ" ማር. 7፡7
 • "እንግዲህ አሕዛብ ደግሞ በአእምሮአቸው ከንቱነት እንዲመላለሱ ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትመላለሱ እላለሁ በጌታም ሆኜ እመሰክራለሁ" ኤፌ.4፡17
 • "ከዚህ የተነሣ በማይታዘዙት ልጆች ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ ይመጣልና ማንም በከንቱ ንግግር አያታልላችሁ" ኤፌ.5፡6
 • "ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር" ፊሊጲስዩስ 2፡3
 • "ከእነዚህም አንዳንዶች ስተው፥ የሚሉትን ወይም ስለ እነርሱ አስረግጠው የሚናገሩትን ሳያስተውሉ፥ የሕግ አስተማሪዎች ሊሆኑ እየወደዱ፥ ወደ ከንቱ ንግግር ፈቀቅ ብለዋል" 1ኛጢሞ.1፡6-7
 • "ጢሞቴዎስ ሆይ፥ በውሸት እውቀት ከተባለ ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍና መከራከር እየራቅህ፥ የተሰጠህን አደራ ጠብቅ" 1ኛ ጢሞ.6፡20
 • "ከንቱና ከመጠን ይልቅ ታላቅ የሆነውን ቃል ይናገራሉና፥ በስሕተትም ከሚኖሩት አሁን የሚያመልጡትን በሥጋ ሴሰኛ ምኞት ያታልላሉ። 1ኛ ጴጥ. 2፡18...... እንዲል፡፡

"ከንቱ ውዳሴ" በተለይ በአገልጋዮቻችን በኩል በስፋት የሚታየው "መጥወኒ እመጥወከ" በሆነ ዘይቤ ሆኖ በማይገባው፣ ባልዋለበትና በማይመለከተው ስም ከመጠራት ስለሚጀምር እስኪ እንደመነሻ በቤተ ክርስቲያናችን የክብር ስም አሠጣጥ ዘይቤውንና ሥርዓቱ እንዲሁም ሂደቱ በተመለከተ ጥቂቱን እንመልከትና በስፋት ግን በያለንበት ሁላችንም ስለዚህ ጉዳይ ጉዳያችን አድርገን እንወያይበት፣ እንመካከርበት፡፡

የቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ስሞች፡

ጥንታዊት ቤተክርስቲያናችን ሐዋርያዊት እንደመሆንዋ መጠን ከመድኅነ ዓለም ጀምሮ እስካለንበት ድረስ ከዚያም በኋላ ቢሆን የምትፈጽመውን የአምልኮ ሥርዓት በአጠቃላይ በሕግና በቀኖና የታጠረ፣ በሕገ ትሩፋት (በፍቅር) የተቀመረ ስለሆነ ዘመን እየተሻገረ በመጣ ቁጥር አዲስ እየሆነ በሁሉም ምዕመናን ዘንድ የበለጠ እየተወደደና እየተናፈቀ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡

ይህንን ሐዋርያዊ አገልግሎት የተሳካ እንዲሆንም አገልጋዮቿ ከላይ ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጀምሮ እስከ ዓጻዌ ሆኅት (የቤተ ክርስቲያን በር የሚዘጋ) ድረስ ሐዋርያዊ ተዋረዱን ጠብቃ በቅብዓትና በአንሮተ ዕድ (በመቀባትና እጅ በመጫን) እንደየመዓርጋቸው በመሾም ሊኖራቸው ወይም ሊማሩት ከሚገባቸው የሥነ መለኮት ትምህርት ባልተናነሰ ሁኔታ የሥነ ምግባር አክሊል በሕይወታቸው እንዲቀጸሉ በማድረግ ከላይ እስከታች ድረስ ምልዓተ ክህነታቸውንና ክበበ አእምሮአቸውን መሠረት በማድረግ የዲቁና፣ የቅስና (የምንኩስና) እና የጵጵስና ማዕርገ ክህነት በመስጠት ለምዕመናን ምሳሌ ሆነው እንዲያገለግሉ በሕግ በሥርዓት እንዲሁም በቀኖና ተደንግጎ ይገኛል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎንም የጥንታዊት ቤተ ክርስቲያናችን ትምህርተ መለኮት እጅግ የጠለቀና የመጠቀ ከመሆኑም በላይ የዚህች ቅድስት ቤተክርስቲያን አገልጋዮች የነበሩ ደጋግ አባቶቻችንም እጅግ የረቀቁና የተራቀቁ ጠቢባን ስለነበሩ ቤተ ክርስቲያናችን በትርጓሜ መጻሕፍት፣ በዜማ፣ በቅኔ... በኩል ለሥርዓተ አምልኮ ማለትም ለልመናና ለምስጋና የሚጠቅም የዕውቀት ትሩፋት ባለቤት አድርገዋት አልፈዋል፡፡ በዚህ ምስጢራዊ አገልግሎት ተጠቃሽ ወርቃማ ታሪክ ባለቤት የሆነው ደግሞ ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ ስለ ቅዱስ ያሬድ አጠቃላይ ሕይወት ታሪኩና የዕውቀት ጸጋውና ትሩፋቱ በሌላ ጊዜ የምናትተው ጥልቅ ምስጢር ሆኖ ቤተ ክርስቲያናችን ግን በስፋት ለሥርዓተ አምልኮ የምትገለገልበት የጸሎት ሥርዓት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ያቀናበረው ቅዱስ ያሬድ እንደመሆኑ መጠን ቅዱስ ያሬድን አብነት አድርገው የዚሁ መንፈሳዊ የቤተ ክርስቲያን ሙያ ባለቤት የሚሆኑ ሊቃውንት እንደየሙያቸውና እንደየ ዝንባሌአቸው በሊቃውንት ታይቶ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እየተጠኑ የክብር ስም ይሰጣቸዋል፡፡ ይህ የክብር ስም የሚሰጠው በሊቃነ ጳጳሳት ሲሆን ያሬዳዊ ሙያና ሥነ መለከታዊ ዕውቀት ማዕከል ያደረገ የቤተ ክርስቲያን ጸጋ ነው፡፡

ለምሳሌ፡

 • የድጓ መምህር
 • የአቋቋም መምህር
 • የቅኔ መምህር
 • የቅዳሴ መምህር... ሆኖ ከጉባዔ ቤት ተመርቀው ጉባዔ ሰርተው፣ ወንበር ዘርግተው፣ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው... ለሚያስተምሩ መምህራን ሊቀ ማእምራን፣ የኔታ፣ መጋቤ ስብሐት፣ መጋቤ ጥበብ፣ መጋቤ አእላፍ... ወዘተ ተብለው ይሰየማሉ፣ ይጠራሉ፡፡

መጻሕፍትን በተመለከተ

 • የሐዲስ ኪዳን፣
 • የብሉይ ኪዳን፣
 • የአራቱ ጉባኤያት.... መምህራን ሆነው እንደላይኞቹ መምህራን በቅተው አራት ዓይና መምህራን ሆነው ሲገኙ አሁንም እንደየመዓርጋቸው መጋቤ ሐዲስ፣ በጋቤ ብሉይ፣ ሊቀ ሊቃውንት፣ ሊቀ ጉባኤ... ወዘተ ተብለው ይሰየማሉ፣ ይጠራሉ፡፡

የተለያየ ታሪካዊ እሴት ያላቸው ጥንታውያን ገዳማቶቻችን የሚያስተዳድሩ የገዳማት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም የአድባራት አስተዳዳሪዎች ከፓትርያርክ ጀምሮ እንደየመአርጋቸውና እንደየደረጃቸው የክብር ስም በመስጠት አገልጋዮቿ አክብራ እንዲከበሩ ታደርጋለች፡፡ በዚህ የክብር ስምም እንዲጠሩ ታደርጋለች፡፡

ወደ ጥንት ነገራችን እንመለስና አሁን በተለይ በአዲስ አበባ አከባቢ የሚታየው ይኸው የቤተ ክርስቲያናችን የስም አሰጣጥ ሥርዓት መነሻውና መድረሻው የማይታወቅ፣ ሰጪውም ሆነ ተቀባዩ የማይታወቅ እየሆነና ይኸው ትውፊታዊና ብቸኛ የቤተ ክርስቲያናችን እሴት የሆነ የክብር ስም የአሰጣጡ ሥርዓት እየተለወጠ ከመምጣቱ በተጨማሪም ያልሆኑትንና የማይሆኑትን እየሰጡ እየተቀበሉ የከንቱ ውዳሴ ማጫወቻ ሜዳ ሆኖ የከንቱ ውዳሴ መስጫም መቀበያም መንገድ እየሆነ በመምጣቱ ሃይማኖታዊም ሆነ ማኅበራዊ ቀውስ ከማምጣቱ በፊት ሁላችንም የቤተ ክርስቲያን ልጆች እጅግ ልናስብበት ይገባል እላለሁ፡፡

የከንቱ ውዳሴ ማጫወቻ ሜዳ ያልኩበት ምክንያት አንድ ሰው ያልሆነውን እያሉ እያቆላምጡ የሚገባውም የማይገባው ሥራ ለመሥራትም ሆነ ለማሠራት ተብሎ የማይስማማ ስም በመስጠት ሲያሞግሱ ውሎ ማደሩ አንድ ብሎ ይጀምርና በዚህ ስም የተለያዩ ስሕተቶች እስከመፈጸም መድረስ ያካትታል፡፡

የጥንቶቹ መምህራን መጋቤ ሐዲስ፣ መጋቤ ብሉይ፣ ለቀ ሊቃውንት፣ የኔታ... የሚባሉት በቤተ ክርስቲያን የዕውቀት ጥበብ ቢያንስ በአንዱ ሙያ በሚገባ ዘልቀው፣ ቀጽለውና አድርሰው ሲያበቁ ነው፡፡ ሥርዓቱም በቤተ ክርስቲያን የሚከወን በመሆኑ የሚገባ ነው፡፡

የአሁኖቹ በየመንደሩ የሚሰጡ ስሞች ግን ትውፊታዊ እሴቱን ጠብቀው በቤተክርስቲያን በኩል የማይሰየሙ ከመሆናቸውን በላይ የቤተ ክርስቲያን የዕውቀት ጥበብን ማዕከል ያላደረጉና ከሚሰየመው ሰው መንፈሳዊም ሆነ ማኅበራዊ (አካላዊ) ሁኔታ የማይስማሙ ሆነው ይታያሉ፡፡ አሰያየማቸውም አግባብነት የላቸውም፡፡

ለምሳሌ፡-

 • ከጽርፈተ አበው (አባቶችን ከመሳደብ) ውጪ ምንም እዚህ ግባ የሚባል ዕውቀት የሌለው ሰው (እንኳንስ ዘልቆ፤ ሰምቶ እንኳ ያልጠነቀቀውን) "መጋቤ ሐዲስ፣ መጋቤ ብሉይ፣ መምህር..." ተብሎ ይጠራል፡፡
 • የሆነ ያልሆነ ወሬ በማመላለስ ሰላም የሚያውከው ሰው "መልአከ ሰላም" ተብሎ የሚጠራበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም፡፡
 • ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የማያውቅ፤ ሥርዓተ አበውን ሲያናጋ የሚውል "መጋቤ ሥርዓት" ተብሎ የሚጠራበት አጋጣሚም አይጠፋም፡፡
 • አቅመ ደካማውን "መልአከ ኃይል"
 • ግብሩም መልኩም ጥቁር የሆነውን "መልአከ ፀሐይ"
 • በጨለማ የሚንቀሳቀሰውን "መልአከ ብርሃን"... ወዘተ እያሉ መጥራት እየተዘወተረ መጥቷል፡፡

ይኼ በቤተ ክርስቲያን የሚሰጥ ሳይሆን በግለሰቦች ምክንያት አንዳንዱም ምንጩ ሳይታወቅ የሚሰየም በቀልድ መልክ እየተዘወተረ ስለመጣ እንዳይለመድና የተፈቀደም እንዳይመስለን ለማለት ጥቂቱን አቀረብኩ እንጂ ሁላችንም የምናውቀው ብዙ ነው፡፡ የተዘወተረ ነገር መለመዱ አይቀርም፤ የተለመደ ነገር ሄዶ ሄዶ የተፈቀደ መምሰሉ አይቀርምና ነው፡፡

እጅግ በጣም የሚገርመው ነገር ግን ዘመኑን በመዋጀት ቤተ ክርስቲያንን ሁለገብ አገልግሎት በማበርከት ብቻ ሳይወሰን ከሚመጣባት ማንኛውም ጥቃት በንቃትም እየተከላከለ በፍጹም ነፍሱና ኃይሉ በማገልገል ላይ የሚገኘው ወጣትም ሁሉንም ባይወክልም አንዳንድ ግን በዚህ መልክ መንቀሳቀስ መጀመራቸው የወጣቶችን ክብር የሚነካ በመሆኑ በስፋት መርሐ ግብር ዘርግተን መወያየትና የመፍትሔ ሐሳብ ማቅረብ ለነገ የማይባል የቤት ሥራችን በሆኑ መገንዘብ ይኖርብናል፡፡

በተለያየ መልኩ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ልማታዊ ጉዳዮችን በጥናት ተመርኩዞ እያበረከተው ያለው አገልግሎት ያለ ምንም ክፍያ በነጻ የፍቅር አገልግሎት ከመሆኑም በላይ በቅጥር ከሚያገለግሉት አገልጋዮች ቢበዛ እንጂ በፍጹም እንደማያንስ በእውነት ዓይን የተመለከተ ሰው የሚመሰክረው ሐቅ ነው፡፡ ታድያ ወጣቱ አገልግሎቱ የሠመረ እንዲሆንና እውነት የሰፈነበት አገልግሎት እንዲሆን ይህንኑ የወጣቱን ሞራልና ሕሊና የማይፈቅደውን "የከንቱ ውዳሴ አገልግሎት" እንኳንስ አካሉ አይደለም ፍንጩ ይታይበታል የሚለው ሁሉ በመድፈን ይበቃል ልንለው ያስፈልጋል፡፡

በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በዚሁ መንገድ የሚጓዙ አንዳንድ ወጣቶች ወንድሞቻችንም መንገዳቸው አለመሆኑን በአግባቡ አስረድተን ልንመልሳቸውና ልንመክራቸው ይገባል፤ የፍቅር ግዴታችንም በመሆኑ፡፡

ውዳሴ ከንቱ የእውነተኛ ክርስቲያናዊ ሕይወት ጠንቅ የእውነተኞቹ አገልጋዮች ረቂቅ ጠላት መሆኑን ተገንዝበን ለራሳችን ይህንን ሕይወት ተጸይፈን ለሌሎች ወንድሞቻንና እኅቶቻችንም መክረንና ገስጸን ዓለም ሳይፈጠር ለወዳጆቹ ወደ አዘጋጃት ገነት መንግስተ ሰማያት ለመውረስ የበቃን የተዘጋጀን ያደርገን ዘንድ አምላካችን እግዚአብሔር ይፍቀድልን ይርዳን በማለት ጽሑፌን ስቋጭ ሌሎች ሙሁራን የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንትና ወጣቶች በዚህ ዘርፍ የተሸለ ጽሑፍ እንድታስነብቡንና ልምዳችሁ እንድታካፍሉን በእግዚአብሔር ስም ጥሬን አስተላልፋለሁ ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር

ይትአኮት ወይሰባሕ ስሙ ለእግዚአብሔር አምለክነ

ወትረ በኩሉ ጊዜ ወበኩሉ ሰዓት

አሜን!

ጥቅምት 2004 ዓ.ም

አዲስ አበባ

የፎንት ልክ መቀየሪያ