Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

ቀን 25/09/04ዓ.ም

ቃለ ጉባኤ

ግንቦት 25 ቀን 2004ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ የተካሄደ

ግንቦት 26 ቀን 2004ዓ.ም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብሰባ አዳራሽ የተካሄደ

የስብሰባው አጀንዳ

1. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ አዘጋጅነት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ የሰንበት ትምህርት ቤት ቀን በሚል ከግንቦት 25-26 ቀን 2004ዓ.ም ድረስ በተዘጋጀው መርሐ ግብር ላይ በሚቀርቡ ጥናታዊ ጽሑፎች እና በማደራጃ መምሪያ መሪ ዕቅድ ረቂቅ ላይ ተወያይቶ የጋራ አቋም መያዝ፤

2. የጠቅላላ ጉባኤ አስተባባሪ ኮሚቴን ማዋቀር በተመለከተ ይሆናል፤

 • ብፁዕ ወቅዱስ ዶ/ር አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት የጉባኤው ሰብሳቢ፤

 • ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የኢሉባቦርና የጋምቤላ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤

 • ብፁዕ አቡነ ገሪማ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የውጭ ግንኙነት መምሪያ የበላይ ኃላፊና የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊና የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤

 • ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት

 • የተከበሩ ተስፋዬ ውብሸት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ም/ሥራ አስኪያጅ

 • የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያውና የድርጅት ኃላፊዎች፣ የ48 አኅጉረ ስብከት የሰንበት ት/ቤት የክፍል ኃላፊዎችና በአዲስ አበባ 160 የገዳማትና አድባራት የሰንበት ት/ቤት የሥራ አመራር ተወካዮች በተገኙበት መርሐ ግብሩ በቅደም ተከተሉ መሠረት ተጀምሯል፡፡

ጸሎት፡- በቅዱስ ፓትርያርኩ መሪነት ከተከናወነ በኋላ የመግቢያ መዝሙር በማዕከላውያን ዘማሪያን ያሬዳዊ ዜማ የቀረበ ሲሆን፣ ዜማውም እመእቶነ እሳት ዘይነድድ አንገፈነ ፣ብርሃናተ ዘይትአፀፍ ተንስአ ለነ፣ /ከሚነድ ከእቶን እሳት አወጣን፣ ብርሃንን የተጎነናፀፈው ተነሳልን/ በማለት ዘማሪያኑ ያቀረቡት ምስጋና ለጉባኤው መግቢያ እጅግ የተዋጣ ዝማሬ ለመሆኑ ጉባኤው በሰዓቱ ካቀረበው የደስታና የምስጋና መግለጫ ለመረዳት ችለናል፡፡ ከዚህ በመቀጠል የእንኳን በደህና መጣችሁ መልዕክትን ጨምሮ የተላየዩ ጠቃሚ መልዕክቶች ከሚመለከታቸው አካላት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

1. የአቢይ ኮሚቴው መልዕክት በዲ/ን በላይ ገ/ሕይወት የቀረበ ሲሆን

ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ አንስቶ ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ የሰጠውን ትዕዛዝ በጎችን ፣ጠበቶችንና ግልገሎችን የመጠበቅና የማሰማራት አደራ ተቀብላ በተለያየ የዕድሜ ደረጃ ያሉ ልጆቿን በዕቅፍ ሰብስባ ማኖሯ ይታወቃል፡፡

የሰንበት ት/ቤት በተናጠል በአንድ አጥቢያ ከአዳራሽ ከማይወጣ አገልግሎት ይልቅ በጋራ እየተመካከሩና እየተደጋገፉ ለመሥራት የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው መቀጠል ይገባቸዋል፡፡ የቤተ ክርሰቲያኒቱን መዋቅም ጠብቀው ከወረዳ እስከ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በተዘረጉ መዋቅሮች አገልግሎታቸውን ማጠናከርም ይጠበቅባቸዋል፡፡

በዚህም መሠረት በየደረጃው የሚዋቀሩ የሰንበት ት/ቤት አንድነት ጉባኤያት የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ወጥ በሆነ መልኩ ከማዳረሱ ባሻገር የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያን ሥራ በማቀላጠፍና የሥራ ጫናውንም በማቅለል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሎ ይታመናል፡፡

ስለዚህም የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ በየደረጃው የሰንበት ት/ቤት ክፍሎች፣ የሰንበት ት/ቤት የአንድነት ጉባኤያትን ለማዋቀርና ለማደራጀት የጀመረውን ሥራ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መልኩ አጠናክሮ መቀጠል እንዲችል ሁላችንም ከጐኑ መቆማችንን እንገልጻለን፡፡ በመጨረሻም ለዚህ ጉባኤ መሳካት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት፣ የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት ሰንበት ት/ቤቶች እንዲሁም ይህን ጉባኤ ለማሳካት የተባበሩትን ሁሉ ላደረጉት የላቀ አስተዋጽኦ ያለንን ክብርና ምሥጋና ለመግለጽ እንወዳለን በማለት መልዕክታቸውን አጠቃለዋል፡፡

2. የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መ/መልዕክት በመ/ር እንቈባሕርይ ተከስተ የማደራጃ መምሪያ ዋና ኃላፊ አቅርበዋል፡፡ በብርኃን ብንመላለስ እያንዳንዳችን

ኅብረት አለን 1ዮሐ.1፡7

 • የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ በሁለተኛው ፓትርያርክ በሰማእቱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ተተክሎ፤ በብፁዕ ወቅዱስ ዶ/ር አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት ተኮትኩቶ እና የመንፈስ ቅዱስ ውሃ ጠጥቶ ያደገ በልዑል እግዚአብሔር ቸርነት አድጎ ለበረከት የበቃ መንፈሳዊ ፍሬ ነው፡፡
 • የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ በአሁኑ ጊዜ በሀገር ውስጥና በውጭ ዓለም ከ20,000,000 በላይ አባላት ያሉት ሲሆን ወጣቶች ባሉበት ሌት ተቀን ስለቤተክርስቲያናቸው እና ስለቅድስት ሀገራቸው የሚያገለግሉና መልካም ዜጋን በመቅረጽ ላይ የሚገኙትን ወጣቶች ያቀፈ መምሪያ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ማደራጃ መምሪያው ብዙ መልካም ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል፡፡
 • የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ከአዲሱ ትውልድ ጋር ባለው ልዩ ቀረቤታ በመነሳት የወጣቱ ትውልድ ችግር ምን እንደሆነ በመለየት፣ ትላንት፣ ዛሬ እና ነገ በምን ያህል ፍጥነትና ግልጽነት መጓዝ እንዳለበት በማለምና በማቀድ ዘመኑን መቅደም አለበለዚያም መከተል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በዚህ መሠረት የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የ5 ዓመት ሀገር አቀፍ መሪ ዕቅድ ላይ ለመወያየት ከመላ ሀገሪቱ ከ600 በላይ የሰንበት ት/ቤት ኃላፊዎች የዚሁ ጉባኤ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ በመሆኑም ይህ ጉባኤ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን ጉባኤው የ5 ዓመት መሪ ዕቅዱን መርምሮና አዳብሮ እንደሚያጸድቅም ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ ይህ ታሪካዊ ጉዞ እንቅስቃሴያችንን በበለጠ ለማጠናከርና ለማስኬድ ይቻል ዘንድ ያለንበትን ሁኔታ መገምገምና በውይይትም ሐሳብ ለሐሳብ መለዋወጥ በይበልጥ ለወደፊቱ እጅ ለእጅ ተያይዘን ለምናደርገው እድገት መንገድ ጠራጊና የጎበጠውን አሠራር የሚያስተካክል፣ የተበተኑትን የክርስቶስ መንጋዎች የሚሰበሰብ፣ የቆሰሉትን የሚፈውስ፣ ያዘኑትን የሚያጽናና፣ በመሆኑ ከሁላችን ጠቃሚና ዘላቂ የሚሆን ቁም ነገር ይጠበቃል በማለት የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልዕክታቸውን አቅርበዋል፡፡

3. ትምህርተ ወንጌል፡- በብፁዕ ዶ/ር አቡነ ገሪማ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት የውጭ ግንኙነት የበላይ ኃላፊና የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንደሚከተለው ቀርቧል፤

 • ወቅቱን መነሻ በማድረግ በዓለ ሃምሳ /በዓለ ጰራቅሊጦስ/ በሚል ርዕስ ተዘጋጅተው አስተምረዋል፤
 • በአለ ሃምሳ ከጌታ ዘጠኙ አበይት በዓላት መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህ ቀን የሚከበረው ከበዓለ ፋሲካ 50ኛው ቀን ሲሆን የሚከበርበትም ታላቁ ዕለት የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን በመባል ይታወቃል፡፡
 • ይህ ቀን በሐዋ.ሥራ.2፡1 እንደተገለፀው የቅድስት ቤተ ክርስቲያን የኃይሏና የህይወቷ ቀን መሆኑን በስፋት በመግለፅ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም በዘዳ.16፡9 እና ዘፀ.34፡22 ላይ ያለውን አምላካዊ ቃል በመጥቀስ የሃይማኖታችን መሰረት የሆነውንም ጸሎተ ሃይማኖትን በመተንተን በስፋት በጥናታዊ ጽሑፍ መልክ የተዘጋጀውን ትምህርት ለጉባኤው አስተላልፈዋል፡፡

4. የቅ/ፓትርያርክ መልዕክትና ቃለ ምዕዳን በብፁዕ ወቅዱስ ዶ/ር አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት ሰንበት ት/ቤት ከተቋቋመበት ረጅም ዘመን አንጻር ስንመለከተው ይህ የዛሬው የሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች ቀን በጣም የዘገየ ሲሆን ነገር ግን ከትናንት ብንዘገይም ከነገ ቀድመናል ዛሬን ሥራ እንሥራበት በሚለው መርህ ከተነሳን የዛሬው ጉባኤም ወቅቱንና ጊዜውን የሚዋጅ ለነገዋ ቤተ ክርስቲያን ተረካቢ ወጣቶችን /ትውልድን/ ከማፍራት አንጻር ጥቅሙ እጅግ የጎላ እንደሆነ ሰፊ ማብራርያ ከሰጡ በኋላ ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አልፈን በሀገር አቀፍ ደረጃ ህብረታችንና አንድነታችንን ብናጠናክር የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል አሳስበው እንደዚህ መሰባሰባችን በአመት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በየጊዜው ተገናኝተን መነጋገር ብንችል እጅግ የተሻለ እንደሚሆን አሳስበዋል፡፡ አያይዘውም አባታዊ ቡራኬያቸውን በመስጠት ለጉባኤው ያላቸውን አድናቆትና አክብሮት በመግለጽ ሀገር አቀፍ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ሰንበት ት/ቤቶች ጠቅላላ ጉባኤ መከፈቱን በይፋ አብስረዋል፡፡

5. ጥናታዊ ጽሑፍ የወጣቱ አስተዋጽኦ በቤተ ክርስቲያን

ወጣቱና ቤተ ክርሰቲያን በሚል ርዕስ በዲ/ን ዶ/ር ያየህ ነጋሽ ቀርቧል፡፡ የጥናቱ መነሻ ያደረጉትም፡-

 • የወጣቱ ፈተና፣
 • መፍትሔዎች፣
 • የወጣቱን አስተዋጽኦ በቤተ ክርስቲስቲያን ውስጥ መጠቆም፣
 • ለተመራማሪዎች የመነሻ ሀሳብ መጠቆም የሚሉት ይገኙበታል፡፡

በመግቢያው ወጣትነት፣ ከህጻንነት ወደ አዋቂነት በዘመነ ወጣትነት ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች የተሻለ የአዋቂነት ህይወት እና የመሳሰሉትን ያካተተ ነው፡፡ በኢትዮጵያም ሆነ በቤተ ክርስቲያን የወጣቱ ቁጥር /ከ7-35/ ዕድሜ በ1999ዓ.ም ቆጠራ መሠረት 35,000,000 እንደሆነ ተቀምጧል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ወደ 20 ሚሊዮን የሚቆጠሩት የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ አማኞች መሆናቸው መረጃው ያስረዳል፡፡

 • የወጣቱ የአኗኗር ሁኔታ፣

  • ወጣቱ በተገቢው ከተያዘ ሀገርንና ቤተ ክርስቲያንን እንደሚጠቅም፣ አስረድተው ለምሳሌ ከሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጢሞቲዎስ እነ አቤልን ይስሐቅን .. የተለያዩ ወጣቶችን ከቅዱሳን መጽሐፍት መልካም የሰሩትን ሕይወት ጉባኤው እንዲያስታውስ አድርገዋል፡፡
 • ወጣቶች በኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን

  • በቤተ ክርስቲያን የወጣቶች ተሳትፎ የታወቀና የተከበረ መሆኑ ይታወቃል፡፡
  • ወጣቶች በቤተ ክርስቲያን፣ በገጠር በከተማ በእድሜና በተለያዩ የአገልግሎትና የክህነት አገልግሎት ድርሻቸውን እንደሚወጡ ጥናቱ ያስረዳል፡፡
 • በወጣቶች አገልግሎት ዙሪያ ያሉ ተግዳሮቶች

የአብነት ተማሪዎችን መዝግቦ ያለማወቅ እና ያለመያዝ በዚህ ምክንያት ለተሀድሶና ለመናፍቃን አላማ መሆን፣ በሰንበት ትምህርት ቤት የእድሜ ገደብ የተነሳ ትምህርቱ በእድሜና በጾታ ተለይቶ ያለመዘጋጀቱ፣ የተለያዩ ወጣቶች በማኅበራት በመደራጀታቸው ምክንያት ለቤተ ክርስቲያን ፈተና መሆናቸውን ፣ በስሜታዊነት ወደ ግጭት መድረስ፣ በግልም ሆነ በማኅበር የቤተ ክርስቲያንን ስርዓት ያልጠበቁ መዝሙሮች በገፍ መሰራጨታቸው ከችግሮቹ መካከል የሚገኙ ናቸው፡፡

 • ወጣትነትና ፈተናዎቹ

በዚህ ሥር ከእድሜ ጋር የተያያዙ ችግሮች እነኚህ ከላይ የተጠቀሱት በአግባቡ ካልተያዙ ለህብረተሰቡም ሆነ ለሀገር ችግር እንደሚፈጥሩ ተወስቷል ይኽውም፤

 • የኢኮኖሚ ችግር ለምሳሌ ስራ አጥነት ተስፋ መቁረጥ
 • ሉአላዊነት (Globalization) ተጽዕኖ ማሳደር፣ ለምሳሌ ባህልን የማስቀረትና የመሳሳት ግብረ ሰዶማዊነት ሃይማኖታዊ ተጽዕኖ ማሳረፍ፤
 • ዘረኝነት ጉሰኝነት ዘውጌነት ሃይማኖት በጎሳም በቋንቋም መለያየት የወጣቱ ችግር መሆኑን ጥናቱ አስረድቶአል፡፡
 • ከስነ ተዋልዶ ጋር የተያያዙ ችግሮች ለኤች አይቪ መጋለጥ፣ ሌላው ችግር ሲሆን በቤተ ክርስቲያን መኖር ግን ከላይ የተዘረዘሩትን ችግሮች የሚቀረፍ መሆኑ በጥናቱ ላይ ተጠቁሟል፡፡
 • ፈተናዎችን መቋቋሚያ መንገዶች

 • ባለድርሻ አካላት መንግስት በዘርፉ ከፍተኛ ስለ መስራት ይጠበቅበታል፤
 • ቤተ ክርስቲያን ወጣቶች በትምህር ቤት በከፍተኛ ትጋት ማስተማር አለባት፤
 • የሃይማኖት ትምህርት ለከፍተኛ ተቋማት መስጠት
 • ነገረ ሃይማኖትንና ግብረ ገብነትን በተጠና መልኩ መስጠት የቤተ ክርስቲያን ዋናው ሥራዋ መሆኑንም ጥናቱ አስረድቷል፡፡ በመጨረሻም ማጠቃለያ ተሰጥቶ አብቅቶአል፡፡

6. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ትላንት፣ ዛሬና ነገ በሚል ርዕሰ በመ/ር በፈቃዱ ደሳለኝ እንደሚከተለው በስፋት ተገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በጉዞዋ ሁሉ ወጣቱን ከጎልማሳውና ከአረጋውያን ጋር በማጣመር መልካም የሆነ መንፈሳዊና ሀገራዊ ልማት ስታካሂድ ኖራለች፡፡ በተለይም ደግሞ በትምህርት ዘርፍ ወጣቱን ከህጻንነቱ ጀምሮ በማስተማር ለሰው ልጅ በሚያስፈልጉት የአእምሮና የመንፈስ እድገት የተሟላ እንዲሆኑ ስትሠራ ቆይታለች፡፡ ወደፊትም ትሠራለች ዛሬ ባለው የቤተ ክርስቲያንዋ መዋቅር ወጣቱን አስባስቦ አደራጅቶ የማስተማርና በአእምሮም ሆነ በመንፈስ የጎለበተ ሆኖ እንዲያድግ በትምህርት የማሳደግ ኃላፊነት የተጣለው በሰንበት ት/ቤቶች ላይ ነው ሲሉ የጥናቱ አቅራቢ አብራርተዋል፡፡ አያይዘውም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የቅዳሜና እሁድ ት/ቤት በኢትዮጵያ ማቋቋም የጀመረችው ከ1939ዓ.ም ጀምሮ ለመሆኑ የመዛግብት መረጃ እንዳለውም ተገልጾአል፡፡

ሰንበት ት/ቤት ከ1970-1982ዓ.ም

በኢትዮጵያ የሰንበት ት/ቤት ታሪክ ላይ ታላቅ ድርሻ ያለው ክፍለ ጊዜ ነው፡፡ የሰንበት ት/ቤት ሕልውና በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ ተቀባይነት አግኝቶ ሰንበት ት/ቤት የሚል ስያሜ ይዞ ሕጋዊ ሆኖ እንዲቀጥል እና በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ሰንበት ት/ቤት አንዲቋቋም፣ የተቋቋሙትም እንዲጠነክሩ በ1970ዓ.ም ተሻሽሎ በተዘጋጀው ቃለ ዐዋዲ ጸድቆአል፡፡

ሰንበት ት/ቤት ከ1983ዓ.ም በኋላ

ቀደም ሲል በወጣቶች ላይ የነበረው የመንግስት ተጽዕኖ በመነሳቱ የፕሮቴስታንት መናፍቃን በወጣቱ ላይ ያደረጉት ወረራ የፈጠረው ቁጭት እና ሌሎች በጎ አጋጣሚዎች ተጨምረው ወጣቱ ፊቱን ወደ ቤተ ክርሰቲያን እና በወጣቱ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እምርታ የታየበት ጊዜ መሆኑንም በጥናታዊ ጽሑፋቸው ጠቅሰዋል፡፡

ሰንበት ት/ቤት በጊዜው ያጋጠመውን ችግር በመቋቋምና በመጠናከር በመንፈሳዊና በብሔራዊ በዓላት፣ በንግሥ በዓላት በታላቅ ድምቀት እንዲከበሩ፣ ሥርዓት በማስያዝ እና የዝማሬ አገልግሎት በማበርከት የእግዚአብሔር መንፈስ ቀዱስ ጥሪ እየደረሳቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚጎርፉትን ወጣቶች መሠረታዊ የክርስትና እምነት ትምህርት መርሐ ግብር ዘርግቶ በማስተማር በኮርስ በማሰልጠን ስብከተ ወንጌልን በማጠናከር ያሬዳዊ ዜማ ለምዕመናን በማቅረብ፣ በማስተናገድና በማስተባበር በበዓላት ነዳያንን በመመገብና በማልበስ ያከናወኑት ታላላቅ ሥራዎች መካከል በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በጥናቱ አቅራቢ ከተላለፉት ዘርፈ ብዙ ማሳያዎች መካከል ቤተ ክርስቲያናችን ለሰንበት ት/ቤት የሚከተሉትን ሁኔታዎች ልታመቻች እንደሚገባትም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡

ይኸውም፡-

1. ሀገር አቅፍ የአንድነት ጉባኤ

2. የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት

3. የሰንበት ት/ቤት አስፈላጊነትን በሚገባ ማስተማር

4. ቋሚ የሆነ የበጀት ምደባን ማከናወን

5. ልዩ ልዩ የሙያ አገልግሎቶችን ለወጣቱ መክፈት

6. ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ

7. የጥናትና የምርምር ማዕከል ማቋቋም ወዘተ... ናቸው፡፡

ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ት/ቤት በኩል ለወጣቶች ልትሠራው የሚገባውን ለማመላከት የቀረበ መሆኑን በመግለጽ የነገዎቹ ጳጳሳት ዛሬ ወጣቶች ናቸው የነገዎቹ ካህናት ዛሬ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች ናቸው፣ የነገዎቹ የሰበካ ጉባኤ መሪዎች ዛሬ የሚንቀሳቀሱት ወጣቶች ናቸው ለዚህም ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ወጣቶች በማፍራት ላይ አተኩራ ልትንቀሳቀስ ይገባታል በማለት ጥናታዊ ጽሑፋቸውን በሚገባ በማብራራትና በማስረዳት አብቅቶአል፡፡

7. የሰንበት ት/ቤቶች ሀገር አቀፋዊ አንድነት ጉባኤ የመሪ እቅድ ረቂቅ በሦስት መምህራን

1. በዲ/ን በላይ ገ/ሕይወት

2. በወጣት ዳንኤል አበባው

3. በመ/ር ፋንታሁን ዋቄ አማካኝነት ለጉባኤው ቀርቧል

ክፍል አንድ

የሚደራጀው ሀገር አቀፍ ጠቅላላ ጉባኤ መሪ ያለው ሆኖ በአካባቢው ተመሳሳይና ተደጋጋፊ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተልዕኮና ዓላማ በውጤታማነት የሚያሳካ የእቅድና የክንውን መርሐ ግብሮች ለመፈጸም የሚያስችል መሪ አቅድ ማስፈለጉን በመጠቆም በክፍል አንድ መሪ አቅድ ለምን ያስፈልጋል እንዲሁም ዳራ እና የመምሪያው ተቋማዊ ይዘት፣ የሰንበት ት/ቤት የተዋረድ አደረጃጀት ዝርዝርም ተብራርቶአል፡፡

በክፍል ሁለት

 • የመምሪያው ራዕይ፣ የመምርያው ተልዕኮ፣ የአገልግሎት አካላት እሴቶችም፣ በጥናት አቅራቢዎቹ የተጠቀሱት ናቸው፡፡

ክፍል ሦስት

 • የነባራዊ ሁኔታ ቅኝት እያጋጠሙና ሊያጋጥሙ የሚችሉ እንቅፋቶች የሰንበት ት/ቤቶቻችን ተቋማዊ ይዘትና የአገልግሎት ሁኔታ የሚመለከት ግምገማ በተመለከተም በጥናቱ ውስጥ ተካቶ ቀርቧል፡፡

በክፍል አራት

 • የመሪ እቅድ የተናጠልና የወል ፍጻሜ ዓላማዎችና ግቦች ሰንበት ት/ቤትንና የሰንበት ት/ቤት አባላትን በብዛትና በጥራት ማደራጀት ላይ ሊሰራ ስለሚገባው ሥራ በስፋት ተገልጾአል፡፡
 • ከዚህም ጋር በማያያዝ የሰንበት ት/ቤት የአስተዳደር ወጥነትና የፋይናንስ ሥርዓት ዝርጋታ የትምህርትና ሥልጠና መርሐ ግብር፣ በየደረጃው የሚሰጥ የትምህርት ደረጃንም በተመለከተ በስፋት ለጉባኤው በጥናታዊ ጽሑፍ በአቅራቢዎቹ በሚገባ ተብራርቶአል፡፡

በክፍል አምስት

 • የመሪ አቅድ ተግባር ሂደቶች አፈጻጸም ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ አንስቶ እስከ ገጠሪቷ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ያለውን ሰንሰለት ቅድም ተከተል ተዋረድን የሚያስረዳ ክፍል ሲሆን፤ መጨረሻም ክትትልና ግምገማ በተመለከተ ሥራን መገምገምና ለአርምት መዘጋጀትን የወጡ መመሪያዎችና ውሳኔዎች ፍሰት /ከላይ ወደታች/ እንዲሁም በየደረጃቸው የሚመጡ አስተያየቶችንና ልዩ ልዩ ግብአቶችን ማስተናገድ በሚል ማብራሪያ በመደገፍ የቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ ለጉባኤው እጅግ በርካታ ግንዛቤዎችን በመስጠት አብቅቶ ጉባኤው በተያዘው ፕሮግራም መሠረት ወደ ውይይት ገብቶ ሰፊ የልምድ ልውውጥ ማግኘት ተችሎአል፡፡

ማጠቃለያ፤

በዕለቱ በቀረቡት 2 ጥናታዊ ጽሑፎች ማለትም ወጣቱና ቤተ ክርስቲያን እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ትናንት ዛሬና ነገ በሚሉ ርዕሶች የቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፎች ወቅታዊና ለወደፊቱ ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለሰንበት ት/ቤት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘታቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ከተሰብሳቢ ቀርበው በቂ መልስ ከተሰጣቸው በኋላ፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የሰንበት ት/ቤቶች ሀገር አቀፍ አንድነት ጉባኤ ላይ የቀረበውን መሪ እቅድ አንዳንድ ማሻሻያዎች በማድረግ ሙሉ ለሙሉ ይህ ጉባኤ ተቀብሎአል፡፡ በመጨረሻም ጉባኤው ከዚህ በመነሳት የሚከተሉትን የአቋም መግለጫዎች አውጥቶአል፡፡

የአቋም መግለጫ

1. የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ በሚያስፈልገው አቅም ሁሉ ለመርዳትና ለማገዝ እኛ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች አመራና አባላት ቃል እንገባለን፤

2. የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት በየደረጃው እንዲቋቋምና ሀገር አቀፍ ጉባኤውም እንዲቀጥል በጋራ እንሰራለን፤

3. በሀገር አቀፍ ደረጃ ተቀርጾ የሚቀርበውን ሥርዓተ ትምህርት ተግባራዊ እናደርጋለን፤

4. የሰንበት ት/ቤቶችን አስፈላጊነት ለባለድርሻ አካላትና ለሚመለከታቸው ሁሉ ለማስረዳትና ለማስተማር ቃል እንገባለን፤

5. ሰንበት ት/ቤቶች በገንዘብና በቁሳቁስ ያለባቸውን ችግር ለመቅረፍ እንዲችሉ ያላሰለሰ ጥረት እናደርጋለን፤

6. ባለን እና በተሰጠን ሙያ ቤተ ክርስቲያናችንን ለማገልገል ቃል እንገባለን፤

7. የጥናትና የምርምር ክፍል ለማቋቋምና የሚያስፈልገውን ማተሪያል ለሟሟላት የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናደርጋለን፤

8. በማደራጃ መምሪያው የተዘጋጀውን የመሪ ዕቅድ ረቂቅ አስመልክቶ አስፈላጊውን ግብዓት በማካተት የመጨረሻ ደረጃ ላይ እንዲደርስ አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ ጠንክረን ለመሥራት ቃል እንገባለን፤

9. በየደረጃው የሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያናችን አመራር አካላት ለማደራጃ መምሪያው አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን፤

10. ሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች ጉባኤ በየዓመቱ እንዲቀጥል ያለመታከት እንሰራለን፡፡ ከላይ ከ1-10 ተራ ቁጥር የተዘረዘሩትን የአቋም መግለጫ ተግባራዊ ለማድረግ የቤተ ክርስቲያን አምላክ እንዲረዳን የዘወትር ጸሎታችን ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ግንቦት 26 ቀን 2004ዓ.ም

አዲስ አበባ

ኢትዮጵያ

ግንቦት 25 ቀን 2004ዓ.ም

የፎንት ልክ መቀየሪያ