Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

የሰ/ት/ቤት ወጣቶች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለቅዱስ ሲኖዶስ ሐሳባቸውን አቀረቡ

የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በአጠቃላይ ወቅታዊ የቤተክርስቲያን ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሐሳባቸውንና የአገልግሎታቸውን አቅጣጫ የሚያሳይ ሐሳብ በቃልና በጽሑፍ ለቅዱስ ሲኖዶስ አቀረቡ፡፡ ወጣቶቹ መግለጫውን በአካል ተገኝተው ለብፁዕ አቡነ ናትናኤል ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ካቀረቡ በኋላ ይህንን ጽሑፍ ለቅዱስ ሲኖዶስ ለማቅረብ የተገደዱት በሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ስም የማይመለከታቸው አካላት የወጣቶቹ ሐሳብና አቋም ያልሆነውን አካሄድ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በመግለጻቸው እውነተኛ የወጣቶቹ ወቅታዊ ሐሳብ በአካል ለቅዱስ ሲኖዶስ ቀርበን ለማስረዳት ነው በማለት ገልጸውላቸዋል፡፡ የወጣቶቹ ጽሑፍ የተቀበሉት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ በወቅታዊ የቤተክርስቲያናችሁ ሁኔታ የልጅነት ድርሻችሁን ለመወጣት እንዲህ ዓይነት ሐሳብ ለቅዱስ ሲኖዶስ ማቅረባችሁ የሚያስመሰግን ነው በማለት ጽሑፉንም ለቅዱስ ሲኖዶስ እንደሚቀርብ ገልጸውላቸዋል፡፡የተከበራችሁ አንባቢዎች ከዚህ ቀጥሎ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ለቅዱስ ሲኖዶስ ያቀረቡትን ጽሑፍ እነሆ እንላለን፡፡

በወቅታዊ የቤተክርስቲያን ጉዳዮች ላይ የሰ/ት/ቤት ወጣቶች ሐሳብ

ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን

ቅዱስ ሲኖዶስ የቀረበ

ከአዲስ አበባ አድባራት እና ገዳማት ሰ/ት/ቤቶች

ጥቅምት ፳፻ወ፭ ዓ.ም.

አዲስ አባባ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

‹‹ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ሐሳብ ነው፡፡››፩ቆሮ ፲፩፥፳፰

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፡-

ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊት እና ታሪካዊት የሆነች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለአለፉት በርካታ ምዕተ ዓመታት ሕዝቦቿን በፍቅር፣ በሰላም እና በአንድነት አስተባብራ በመንፈሳዊ ሕይወት በመምራት፣ ሀገራችንንም በጸሎት እና በቡራኬ በመጠበቅ እንዲሁምየታሪክ እና የቅርስ ባለቤት በማድረግ ታላቅ ሥራ ሠርታለች፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ረጅም መንፈሳዊና ማህበራዊ የአገልግሎት ጉዞ ከውስጥም ከውጭም በሚያጋጥሟት ፈተናዎች ብዙ እንግልት ቢደርስባትም የገሃነም ደጆች እንኳን እንደማያናውጿት የተነገረላትና በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተመሠረተች አማናዊት ቤተክርስቲያን በመሆኗ በጽናት ከዛሬ ደርሳለች፡፡

ዛሬ አምስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የእግዚአብሔር ጥሪ ደርሷቸው ባላሰብነው እና በልጠበቅነው ሁኔታ ተለይተውናል፡፡ አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር ነፍሳቸውን በምህረት ተቀብሎ ከቅዱሳን ኅብረት ይደምርልን ዘንድ የዘወትር ጸሎታችን ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም የብፁዕ ወቅዱስ አባታችንን ዕረፍት ተከትሎ ቅድስት ቤተክርስቲያን በቀጣይነት የምታከናውነው መንፈሳዊ አገልግሎት የተሳካ እንዲሆን የአወጀውን ምህላ እና ጸሎት በታላቅ መንፈሳዊ ደስታ በመቀበል እና በመሳተፍ እንዲሁም በየሰንበት ት/ቤቶቻችን ልዩ የጸሎት መርሐግብር በመዘርጋት ስለሀገራችን እና ስለቤተክርስቲያናችን እግዚአብሔር አምላክ መልካሙን ሁሉ ያደርግልን ዘንድ በመማጸን አሳልፈናል፡፡

ብፁዓን አባቶቻች ሆይ ፡-

እንደምታውቁት እኛ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ከታዛዥነት ጋር የቤተክርስቲያናችን መንፈሳዊ እድገት እንዲፋጠን፣ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ በሥራ ላይ እንዲውል እና ለብፁዓን አባቶች የሚያስፈልገውን ድጋፍ ሁሉ በማድረግ ቅድሚያ ተሰላፊዎች የሆንን የቤተክርስቲያን ኃይላት ነን፡፡ ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ ደግሞ በቅርበት ከእናንተ ከብፁዓን አባቶቻችን ጋር በመመካከር ለቤተክርስቲያን አገልግሎት ይበጃሉ ያልናቸውን ሐሳቦች እና በቤተክርስቲያን ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችንም ስናቀርብ እናንተም ጉዳዮቹን በአርቆ አስተዋይነታችሁ እየተመለከታችሁ እና እየተወያያችሁ የምትሰጡት ውሳኔ በቤተክርስቲያን አገልግሎት ላይ እምርታ እያሳየ መጥቷል፡፡

በዚህ የምህላ እና የጸሎት አዋጅም እግዚአብሔር በክቡር ደሙ የዋጃት ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ያሉባት ችግሮች ተቀርፈው የተሳካ መንፈሳዊ አገልግሎት እንድትሰጥ ያላችሁን ጽኑ ፍላጎት ተገንዝበናል፡፡ እኛ የመንፈስ ልጆቻችሁ በቀጣዩ የሚኖረው ሁለንተናዊ የቤተክርስቲያን አገልግሎት ምን መምሰል እንዳለበት በማሰብ እና ለብፁዓን አባቶቻችን ታዛዥ በመሆን ድጋፍ ልናደርግ በምንችልባቸው ሁኔታ ላይ ረዘም ያለ ጊዜ ወስደን በየደረጃው ውይይት እና ምክክር አድርገናል፡፡

ከዚህም በመነሳት ዘመኑን በመዋጀት እንዲሁም ወቅታዊና መሠረታዊ ችግሮችን በማጤን ብፁዓን አባቶቻችን ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩባቸው ይገባል የምንለውን ሐሳብ በትህትና እና በአክብሮት ስናቀርብ ብፁዓን አባቶቻችን ሐሳባችንን ተረድታችሁ፣ መርምራችሁ እና ተመካክራችሁ ወጣቱን እና ምዕመኑን የሚያስደስት፣ የቤተክርስቲያንን ልዕልና የሚያስከብርና የእግዚአብሔር ፈቃድ የሚገለጽበት ውሳኔ እንደምትሰጡበት ጽኑ እምነታችን ነው፡፡

1 ዕርቀ ሰላምን በተመለከተ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በየዘመናቱ ከገጠሟት ችግሮች መካከል ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ የተከሰተውና ቤተክርስቲያኗን በአስተዳደርም ቢሆን ለሁለት የከፈለው "የሁለቱ ሲኖዶሶች" ጉዳይ አንዱና ዋነኛው ነው ብንል አንሳሳትም፡፡ ጥቂቶች ይህን ጉዳይ አቅልለው ቢያዩትም መለያየትን ለሚጸየፈው ለእግዚአብሔር አሳዛኝ እና ለእውነተኛ የቤተክርስቲያን ልጆች አሳሳቢ ሆኖ ቆይቷል፡፡ እርስ በርሷ የምትለያይ መንግሥት አትጸናም እንደተባለ መለያየት ውስጣዊ ጥንካሬን በማዳከም ለተለያዩ ለከፉ ችግሮች ቢያጋልጥ እንጂ ለምንም አይጠቅምም፡፡ ለዚህ የቤተ ክርስቲያን መለያየት ሁላችንም የእየራሳችን አሉታዊ ሚና ያለን ቢሆንም የአባቶቻችን የሊቃነ ጳጳሳት ድርሻ ግን ከፍተኛ ነው፡፡ ሌሎችም የራሳቸውን አጀንዳ ከማስፈጸም አኳያ መለያየቱን ሲጠቀሙበት ቆይቷል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት በሁሉቱ ወገኖች መካከል ዕርቅ ወርዶ ሰላምና አንድነት ይሰፍን ዘንድ የተለያዩ ሙከራዎች ሲያደረጉ የነበሩም አሉ፡፡ እንዳለመታደል ሁኖ በተለያዩ ግለሰባዊ እና ቴክኒካዊ ምክንያቶች የተነሳ የተፈለገው ዕርቅና አንድነት ግን ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ለዕርቀ ሰላሙ አለመሳካት እንደ አንድ ዋነኛ ምክንያት ሆኖ ይነገር ከነበሩ ምክንያቶች ውስጥ ሁለት ፓትርያርኮች የመኖሩ ጉዳይ እና ከእርሱ ጋር ተያይዞ በሚቀርቡ የመፍትሔ ሐሳቦች ላይ መስማማት አለመቻል እንደነበረ በተለያየ ጊዜ በዕርቀ ሰላሙ ላይ የተዘገቡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ዛሬ አምስተኛው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ፓትርያርክ ብ/ወቅ/አ/ጳውሎስ የእግዚአብሔር ጥሪ ደርሷችው ባላሰብነው እና ባልጠበቅነው ሁኔታ ተለይተውናል፤ ነፈሳቸውን አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር በክብር ተቀብሎ ከቅዱሳን ኅብረት ይደምርልን ዘንድ የዘወትር ጸሎታችን ነው፡፡ የብፁዕ ወቅዱስ ዕረፍት ለቀረነውም ጥሪያችን መቼ እና እንዴት እንደሚሆን እንደማይታወቅ በመጽሐፍት የተነገረውን የሚያስረግጥልን ከመሆኑ ባሻገር ለዕርቀ ሰላሙ ምንም ዓይነት አመክንዮ በማምጣት ልናጓትተው እንደማይገባ ያስገነዝበናል፡፡ ያለምን ቅድመ ሁኔታ እና ምክንያት ወደ አንድነት ልንመጣ ያሳስበናል፡፡

ይህንን በተመለከተ ብዙዎች አባቶች እያሳዩ ያሉት በጎ ፈቃደኝነት እና እንቅስቃሴ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ይህ ጊዜ ለቤተክርስቲያን የሚፈለገውን ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ብለን ብዙዎቻችን እደምንጠብቅ ሁሉ በፓትርያርክ መተካት ዙሪያ የራሳቸውን ጥቅም እና ፍላጎት ለማሳካት ይችሉ ዘንድ ይህን ታላቅ አጀንዳ ወደጎን በመተው፣ግርግር በመፍጠር፣ አባቶችን በማስጨነቅና በማዋከብ ጸረ-ሰላምና ጸረ-አንድነት ሥራቸውን አጥብቀው በማስረጽ ላይ የሚገኙ ወገኖች እንዳሉ እንረዳለን፡፡እናም የነዚህ አሉታዊ እቅስቃሴዎች ውጤት በተጣደፈ፣ በውል ባልተጠና እና በቂ ዝግጅት ባልተደረገበት ሁኔታ ተተኪ ፓትርያርክ መምረጥ ከሆነ ደግሞ ቤተክርስቲያኗን ካሳለፍነው ዘመን የባሰ የሚያሳዝን እና የተወሳሰበ ችግር ውስጥ እንደሚከትታት እሙን ነው፡፡ ከዚህ ስጋት በመነጨ በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ የብዙሀን መገናኛዎች፣ መካነ ድሮች (ዌብ ሳይቶች) ፣ እና የቡድን ውይይቶች እንዲሁም በሌሎችም መንገዶች አብዛኞቹ የቤተክርስቲያን አባላት ሐሳባቸውን እና የሚመኙትን በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡

ይህንን ስጋት እኛም የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ወጣቶች እንጋራዋለን፡፡ የቤተ ክርስቲያን ጉዳት ለኛም ሕመማችን ነው፡፡ በአባቶች መለያየት የተነሳ ብዙ ነገር አጥተናል እናቶቻችንና አባቶቻችን ምእመናን ተለያይተዋል፤እኛም ከእህትና ወንድሞቻችን የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ጋር ተለያይተናል፡፡ ሌሎችን ማዳን ስንችል ከወገኖቻችን መካከል ብዙዎችን አጥተናል፡፡ አባቶቻችን እርስ በርስ ሲወጋገዙ እና የቤተ ክርስቲያን የውስጥ ጉዳይ እንደተራነገር አደባባይ ላይ ሲወጣ አይተን አንገታችንን ደፍተናል፡፡ የዕርቅና የሰላም ቤት የሆነችው ቤተክርስቲያናችን የመለያየት እና የመከፋፈል ቤት ስትሆን ተስፋችን ጨልሞብናል፡፡

ስለዚህም ዛሬ ድምጻችንን እናሰማለን፡፡ የቤተክርስቲያን አባቶች እኛን ወጣት ልጆቻቸውን እንዲሰሙን እንማጸናለን፡፡ በዕርቀ ሰላሙ ዙሪያ ድምጻችን ግልጽ ነው፡፡ ይህም በሁለቱም በኩል ያሉ አባቶች በታላቅ መንፈሳዊ ውሳኔ ጉዳዩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ይስጡት የሚል ነው፡፡ ይህንንም ለማድረግ ከአሁኑ የተሻለ ጊዜ ካለመኖሩ አንጻር እስከ አሁን እየተደረጉ ላሉት እንቅስቃሴዎች ክብር እና ድጋፍ በመስጠት፤ የሰላምና የፍቅር አምላክ የሆነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃዱ ይሆን ዘንድ በመማጸን፤ የመለያየቱ ክስተት ሲፈጸም ያዩ እና የነበሩ ጥቂት ብፁዓን አበው በእግዚአብሔር ጥሪ ሳይለዩን የቤተክርስቲያኒቷን አንድነት እንደገና በጽኑ መሠረት ላይ በማቆም ትውልዱን ዕርቅ እና ሰላም እንዴት እንደሚከናወን በተግባር ልታሳዩት ይገባል እንላለን ፡፡

በእርግጥ ሰላም ከአንድ ወገን ብቻ የሚፈጸም ባለመሆኑ ሒደቱ ውስብስብ እና አስቸጋሪ መሆኑን ብንረዳም ለቤተክርስቲያኒቱ መረጋጋት እና ለምዕመናኑ መጽናናት ሲባል እስከመጨረሻው ጥረት እንዲደረግ እንጠይቃለን፡፡ ሁኔታው ከሚጠበቀው ውጪ ቢሆን፣ ከሚያስፈልገው በላይ ረጅም ጊዜ የሚጠይቅ ከሆነ እና ለሌላ ውሳኔ የሚያስገድድ ሁኔታ ከተፈጠረ ግን ውሳኔው በምዕመናኑ ዘንድ ሁሉ ተዓማኒነት እና ተቀባይነት ይኖረው ዘንድ ጥረቱን ሁሉ የሚያሳይ የመረጃ ግልጽነት ሊፈጠር ይገባልም እንላለን፡፡ ዕርቀ ሰላሙን በማስታከክም ለዓመታት የቤተክርስቲያንን እምነት፣ ቀኖና፣ ትውፊት እና ሥርዓት ሲያጎድፉ የነበሩ በንስሐ እና በቀኖና ስህተታቸውን ሳያርሙ ከእነ ስህተታቸው ወደ ቤተክርስቲያን እንዳይቀላቀሉም ብርቱ ጥንቃቄ እንዲደረግ እንጠይቃለን፡፡

2 አስተዳደራዊና መዋቅራዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዘመናት የሚሻገር ምድራዊያንን ሰማያውያን የሚያደርግ ስፉህ፣ምጡቅ እና ልዕልና ያለው መንፈሳዊ ዓላማ አላት፡፡ ይህንዓላማዋን ለማሳካት በተለያየ መልኩ የምታከናውናቸው አምልኮታዊ ተግባራት በአግባቡ ይፈጸሙ ዘንድ ጠንካራ እና ዘመኑን የዋጀ አስተዳደራዊና መዋቅራዊ ሥርዓት ሊኖራት ግድ ነው፡፡ ዛሬም በጥንቱ እና ልማዳዊ በሆነ የአሠራር እና የሰው ኃይል አያያዝ የትም መድረስ አትችልም፡፡ እርግጥ ነው ከጥቂት አሥርት ዓመታት ወዲህ የአስተዳደራዊ እና መዋቅራዊ ዘመናዊነትን መሠረት ለመጣል ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ በዚህም መሠረት ቤተክርስቲያን ከላይ እስከ ታች ድረስ የተዘረጋ እና ሁሉን አሳታፊ ሊያደርግ የሚችል መዋቅር አላት፡፡የአስተዳደሯ ቁንጮ የሆነ ሕግ አውጪ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ ሲሆን ሕግ አውጭው አካል በየጊዜው የተለያዩ ሕጎች፣ ደንቦች እና መመሪያዎችን ያወጣል፡፡ በነዚህ ሕጎች፣መመሪያዎች እና ደንቦች መሠረት የሚሠሩ የተለያዩ መዋቅራዊ አካላት በየደረጃው ይገኛሉ፡፡

የሰው ልጅ በተሟላ የጤና ሁኔታ ሥራውን በትክክል ይሠራ ዘንድ አጥንትና ጅማት እንደ አጽም፣ሥጋ እንደ አንቀሳቃሽ አካል፣ ነርቭ እንደ እዝ ሰንሰለት፣ደም የአካል ክፍሎችን ለመመገብ፣ለማበልጸግ፣ለማናበብና ለማገናኘት ወ.ዘ.ተ ያለምንም ጥያቄ ያስፈልጉታል፡፡ ከእነዚህ አንዱ ቢጎድል እንኳ በተገቢው ሁኔታ መንቀሳቀስ እና ሥራ መሥራት አይችልም፡፡ በተመሳሳይም አንድ ድርጅት እንደ አጽም መዋቀር፤እንደ ሥጋ የተደራጀ የሰው ኃይል፤እንደ ነርቭ ከላይኛው አካል ጀምሮ የሚወርድ የእዝ ሰንሰለት፤እንደ ደም በየደረጃው ያሉ አካላት እርስ በርሳቸው የሚያደርጉት መናበብ፣ መግባባት እና መከባበር የግድ ያስፈልጉታል፡፡ ከነዚህ የአንዱ መጓደል ከላይ እንደገለጽነው ሁሉ ለተሟላ አሠራር አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ይፈጥራል፡፡ ቤተክህነትም ከዚህ እውነታ አትወጣም፡፡ የእግዚአብሔር በጎፈቃድ ሁሌም የሚያስፈልግ ቢሆንም ይህ በጎ ፈቃድ በወደደው መጠን ይገለጽ ዘንድ የእነዚህ የተለያዩ ክፍሎች አስፈላጊነት አያጠያይቅም፡፡ ቤተ ክህነት መዋቅርን በተመለከተ ብዙ ባትታማም ሌሎችን በተመለከተ ግን ገና ብዙ መሥራት እዳለባት ይታመናል፡፡ በየደረጃው በተገቢ ሁኔታ የሰለጠነ፣የሚሠራውን የሚያውቅ፣የቤተ ክርስቲያን ፍቅር ያለው፣ ዓላማውን የተረዳ፣ በዘረኝነት እና በምዝበራ የማይታማ ወ.ዘ.ተ የሰው ኃይል ያስፈልጋታል፡፡ ይህን የሰው ኃይል ሁልጊዜ ያለ መሸራረፍ በሚሠራ የእዝ ሰንሰለት ማሰማራትና ማሠራት የግድ ይላል፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት ሁሉም አካላት ውጤታማ ይሆኑ ዘንድ መናበብ መግባባት እና መከባበር ይኖርባቸዋል ፡፡

እድገታችን በውስጧ ከመሆኑ አንጻር እኛ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች እንደ ቤታችን በምናያት ቤተክርስቲያናች ውስጥ የሆነውን እና እየሆነ ያለውን በሙሉ እንገነዘባለን፡፡በተለያዩ ምሁራን እደሚተቸው የመመሪያዎች እና ደንቦች እርስ በእርስ አለመጣጣም፣ የወጡትን ደንቦች እና መመሪያዎች አተገባበር አለመፈተሸ፣ ኃላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት፣የተለያዩ የአስተዳደር በደሎች፣ ከተዝረከረከ የፋይናንስ አስተዳደር የተነሳ ከፍተኛ የሆነ ሙስና፣ የቋሚ ሠራተኛውን አግባብነት ያለው ፍላጎት እና ጥቅም አለማስጠበቅ እና የመሳሰሉት ችግሮች በብዛት ይታያሉ፡፡

የተከበራችሁ አባቶቻችን የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ሐዋርያው ‹‹ሰፊ የአገልግሎት በር ተከፍቶልኛል›› እንዳለው መጭው ጊዜ ከላይ የተዘረዘሩ ችግሮችን በሙሉ ቀስ በቀስ ለማስወገድ ቁርጠኛ አቋም የሚወሰድበት እንደሆነ እኛ ታናናሽ ልጆቻችሁ ይሰማናል፡፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ እኛ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ልንታዘዘው የሚገባን ማንኛውንም ሥራ በታዛዥነት ለመቀበል፣ የተለያዩ ሙያዊ ድጋፍ ለመስጠት እና በጥናቶች ላይ ተሳተፊ ለመሆን ዝግጁ መሆናችን ከወዲሁ እናረጋግጣለን፡፡

3 የምዕመናን እና የአባቶችን ግኑኝነት የማሻሻል አስፈላጊነት

የብሉይ ኪዳን እምነት እና ትውፊት ይዛ ወደ ክርስትና በተሸጋገረችው ቤተክስቲያናችን ምዕመናን ለቤተክርስቲያን ብሎም ለካህናት አባቶች ያላቸው ከበሬታ እና ፍቅር ለነገሥታቱ ካላቸው ፍርሃት በላይ ሆኖ የቆይ ነው፡፡ ይህም የሆነው ካህናት አበው ከክርስቶስ የተሰጣቸው መንጋውን የመጠበቅ እና የማስማራት ተልዕኮ ከምንም በላይ አሰቀድመው ይተገብሩት ስለነበረ ነው፡፡ የቅድስት ቤተክርስቲያን ተቀዳሚ ተግባርም ይኸው የሰው ልጅን ማዳን እና የዘላላም ሕይወት ተካፋይ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ለዚህ ዓላማ ብዙ ልንደክምበት እና ልንለፋበትም ይገባል፡፡ ስለዚህ የቤተክርስቲያን አባቶች ለመንጋቸውና ለመንፈሳዊ ልጆቻቸው ድኅነት አጥብቅው እንዲሠሩ ይጠበቃል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ ... ለመንጋው ተጠንቀቁ....›› ያለው ለዚህ ነው፡፡ መንጋው ከእረኛው ተለይቶ መባዘን የለበትም፤ምዕመኑ የቤተክርስቲያን አባቶቹን ድምፅ፣ ሐሳብ፣ ፈቃድ ሳይቀር የሚረዳ፣ የሚቀበል፣ የሚፈጽም ሊሆን ይገባል፡፡ እረኛውም ቢሆን ከመንጋው አንድም ነፍስ እንዳይጠፋበትና እንዳይሰናከልበት እንደ ዓይኑ ብሌን ሊጠነቀቅለት ይገባል፡፡

ሁልጊዜ እንደሚገለጸው ቤተክርስቲያን የሕዝበ ምዕመናኑ ናት፡፡ ምዕመኑ ከቤተክርስቲያን ጋር በቅርብ የተቆራኘ እና የማይነጣጠል አካል ነው፡፡ ቤክርስቲያንን የሚያንጹ፣ አሥራት በኩራት የሚያወጡ፣ የአገልጋይ ካህናትን ደሞዝ የሚከፍሉ፣ በቤተክርስቲያን የሚገኙ ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን የሚሠሩ ምዕመናን ናቸው፡፡ የምዕመናን የእኔነት ስሜት ሊጠበቅ ይገባዋል፡፡ ምዕመናን ከቤተክርቲያን ተለይተው ወደ ሌሎች ቤተእምነቶች ከተሰደዱ ለቤተክርስቲያን ትልቅ ውድቀት ነው፡፡ ስለዚህ ለምዕመናን ትኩረት የሰጠ አገልግሎት ያስፈልጋል፡፡

የተወደዳችሁ አባቶች የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ተከታዮች ዛሬም ቢሆን ለእናንተ ለብፁአን አበው የተለየ ክብር እና ፍቅር አላቸው፡፡ እናንተን በዓዩ ሰዓት ክርስቶስን እንዳገኙት ነው የሚሰማቸው፤ እናንተ እንደራሴው እንደሆናችሁ ያምናሉ፤ እርሱ በሐዋርያቱ በኩል ይሠራ እንደነበረው ከእናንተም ጋር እንደሚሠራ ይረዳሉ፡፡ ስለዚህ ያከብሯችኀል፣ ድምጻችሁን ይሰማሉ፣ ከጫማችሁ ስር ተደፍተው ይሳለሟችዃል፡፡ የእናንተን ክብር ለማዋረድ የሚሞክረውን የመታገስ አቅም የላቸውም፡፡ ነገር ግን በጊዜ ሒደት በልዩ ልዩ ምክንያቶች ይህ ግንኙነት እየተሸረሸረ መጥቷል፡፡ ይህም መልካሙን የአባቶች እና የምዕመናን ግንኙነት በመበጣጠስ ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት ሌት ተቀን ለሚጥሩ አጽራረ ቤተክርስቲያን ሰፊ በር ይከፍታል፡፡ ስለዚህም ብፁዓን አባቶቻችን ለችግሩ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ጠንክራችሁ እንደምትሠሩ በመተማመን ምዕመኑ አባቶቻችን እንድታደርጉለት የሚጠብቃችውን አንዳንድ ሐሳቦች ከዚህ እንደሚከተለው እንጠቁማለን፡፡

 • ምዕመናን ለቤተክርስቲያኒቷ አስፈላጊ አካለት እንደመሆናቸው በቤተክርስቲያን ጉዳዮች በተለይም ወሳኝ እና ቁልፍ በሆኑ ጉዳዮች ውሳኔ ሲሰጥ የውሳኔው ቀጥተኛ ተሳታፊ የሚሆኑበት እና የራሳቸውን አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበት መድረክ እንዲዘጋጅላቸው እና በቤተክርስቲያን ለሚከናወኑ ማንኛቸውም ክንውኖች ግልጽ እና ቀጥተኛ የሆነ መረጃ ያገኙ ዘንድ ይሻሉ፤

 • ቤተክርስቲያን ዛሬም ሆነ ወደፊት በአጽራረ ቤተክርስቲያንም ሆነ በአንዳንድ የመንግሥት ሹመኞች እና ባለሥልጣናት የሀገሪቷ ሕግ በማይፈቅድላቸው መንገድ ክብሯ ሲነካ እና ሲደፈር አፋጣኝ ምላሽ እና ማስተካከያ እንዲሰጥ፤

 • ቤተክርስቲያን የተለያዩ ፈተናዎች ሲገጥሟት የምህላ፣ የጾም እና የጸሎት አዋጅ በማወጅ ምዕመኑም በባለቤትነት እንዲሳተፍ እንዲደረግ፤

 • በዶግማ እና በቀኖና ቤተክርስቲያን ይህንንም በመሳሰሉ ጉዳዮች ከውስጥም ይሁን ከውጭ ጠላቶች በምዕመኑ ውስጥ ውዥንብር ሲፈጠር አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ባለው የመገናኛ ዘዴ ሁሉ ለምዕመኑ እንዲዳረስ ማድረግ፤

 • ገዳማቱ ሲመዘበሩ፣ መናኒያኑ ከበዓታቸው ወጥተው ለእስር ለእንግልት ሲዳረጉ አስፈላጊው ውሳኔዎች በወቅቱ እንዲወሰኑ እና ምዕመኑን በማስተባበር አስፈላጊው ምላሽ እንዲሰጥ ማድረግ፤

 • በቀኖና ቤተክርስቲያን ያልተገባቸው ወንድ እና ሴት ምዕመናን የቤተክህነቱን ሆነ የአጥቢያ ቤተክርስቲያንን ኃላፊነት ሲቆጣጠሩት እና የቤተክርስቲያንን መንፈሳዊ አገልግሎት የሚያውክ ተግባር ሲፈጽሙ በዝምታ እንዳይታለፍ እና አስቸኳይ እርምት እንዲሰጥ፤

 • ዘረኝነት፣ ምዝበራ፣ ጉቦ፣ ብኩንነት እና የአስተዳደር በደል ከቤተክርስቲያን እንዲወገዱ ፤

 • አጽራረ ቤተክርስቲያን በተለይም የተሃድሶ መናፍቃን ምእመናንን ከአባቶች ለማለያየት ለሚሰነዝፘቸው የሐሰት ትረካዎች በቂ እና አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው እና ከቤተክርስቲያን መድረክ እንዲገለሉ፤

 • በኪነጥበብ ስም አንዳንድ በዘርፉ የሚገኙ ወገኖች የቤተክርስቲያንን የአምልኮ ሥርዓት ባላገናዘበ መልኩ የምዕመናንንም ሆነ የቤተክርስቲያንን መብት ሲጥሱ እና ክብሯን ሲነኩ ከዕውቀት ማነስ ለሚሠሩት በማስተማር፣ በዓለማ ለሚያደርገት ግን አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ ምላሽ እንዲሰጣቸው፤

ብፁዓን አባቶቻችን

ዛሬ ጊዜው ከላይ የተጠቀሱትን እና ሌሎችም ምክንያቶች በማስወግድ የአባቶችን እና የምዕመናንን ትስስር የምናጠናክርበት ጊዜ እንደሆነ ይታሰባል፡፡ ምዕመኑ ዛሬም በሙሉ ልቡ ከእናንተ ጋር ለመሆን ዝግጁ ነው፤ ዛሬም ምዕመኑን ና ስትሉት ሊመጣ፣ ሂድ ስትሉት ሊሄድ፣ ዝመት ስትሉት ሊዘምት፣ አምጣ ስትሉት ሊያመጣ፣ እንካ ስትሉት ሊቀበል፣ ...... ይህን ሁሉ በሙሉ ልቡ ሊያደርግ ዝግጁ ነው፡፡ ነገር ግን ዘወትር በመንፈሳዊ ግርማና ሞገስ ከፍ ብላችሁ በታላቅ ክብር ሊያያችሁ ይወዳል፡፡ በዘር ከመከፋፈል፣ በቡድን ከመጣላት፣ ለሥጋ ከማድላት፣ ከስልጣን ፍላጎት፣ ከፖለቲካ ጥገኝነት፣ ...... ይህን ከመሳሰሉት ፈተናዎች ነጻ ሆናችሁ መንፈሳዊነታችሁ ተከብሮ ሊያይ ይናፍቃል፡፡

ስለዚህ የቤተክርስቲያን አባቶች እና የምዕመናን ትስስር ተጠናክሮ ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ ብፁዓን አባቶቻችን ዛሬ የዓለም እና የፖለቲካ ጉዳዮች ከተለያዩ ኢክርስቲያናዊ ጉዳዮች ጋር በተሳሰሩበት ወቅት የምትወስኑት ወሳኔ፣ የምትሠሯቸው እና የምትናገሯቸው ሁሉ ለምዕመኑ ትኩረት የሰጡ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ለምሳሌ ያክል ከቅዱስ ፓትርያርኩ ዕረፍት በኋላ በአቃቢ መንበር አመራረጥ፣ ቋሚ ሲኖዶስ የሚያግዙ ሊቃነ ጳጳሳት በመሰየም፣ ስለመጭው የቤተክርስቲያን ሁኔታ ጸሎተ ምህላ እንዲደረግ የወሰናችሁትን በማየት ብዙዎች ምዕመናን መንፈሳቸው ተነቃቅቷል፣ ልቦናቸው ተነሳስቷል፣ የቀደመው የአባቶቻችን ዘመን ሊመለስ ነው በማለት ተስፋም እያደረጉ ነው፡፡ ይህ በየቤታችን ከእናት ከአባቶቻቻን፣ ከጎረቤቶቻቻን እና በየአጥቢያዎቻችን ካሉ ምዕመናን እና ምዕመናት የምንሰማው እና የምረዳው እውነታ ነው፡፡ ስለዚህ የምዕመኑን ተስፋ ታጎለብቱት ዘንድ በልጅነት መንፈስ ከአደራ ጋር እንማጸናችኋለን፡፡ ውሳኔያችሁ የቤተክርስቲያኒቷን ክብር እና የምዕመኑን ተስፋ የጠበቀ እንዲሆን እንማጸናችኋለን፡፡

4 ከውጫዊ አካላት ተጽዕኖ ነጻ መሆን

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ማህበረሰቡን በአንድነት፣ በአንድ ዓላማ፣ በአንድ ሃይማኖት አስተባብራ በመምራት ሰፊ ተሞክሮ ያላት ቤተክርስቲያን ነች፡፡ ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ማንነታችን፣ ባህላችን፣ አነጋገራችን፣ ሰላምታችን፣ አለባበሳችን... በጥቅሉ አኗኗራችን ከቤተክርስቲያኒቷ የተወሰደ ወይም የተሳሰረ ነው፡፡ ይህም ሀገሪቷን ከየትኛውም ዓይነት ወረራ እና ቅኝ ግዛት ጠብቆ አቆይቷል፡፡ በሀገር ውስጥም ቢሆን ቤተምዕምን ከቤተመንግሥት ጋር አስተባብራ በመምራት፣ የቤተመንግሥትን አካሄድ በማስተካከል፣ በቤተመንግሥት እና በቤተ ምዕመናን መካከል ግጭት ሲፈጠር በመሸምገል እና በመዳኘት ከፍተኛ አገልግሎት ስትሰጥ ቆይታለች፡፡

ይህ የቤተክርስቲያን አስተዋጽኦ ኢትዮጵያን በአመለካከት፣ በሀብት እና በፖለቲካ ቅኝ ግዛት ለማድረግ ለሚሹ አካላት ከፍተኛ እንቅፋት እንደሆነባቸው በተለያዩ ጽሑፎቻቸው ሲገልጹት የኖሩት ዐብይ ጉዳይ ነው፡፡ በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ ቤተክርስቲያኒቷን ለማዳከም፣ ከምዕመኑ ጋር ያላትን ትስስር ለማቋረጥ፣ በቤተመንግስትም ሆነ በቤተ ምዕመን ያላትን ተሰሚነት ለማዋረድ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ አሁንም ወቅቱ ያመጣቸውን የለውጥ አጋጣሚዎች በመጠቀም በቤተክርስቲያኒቷ የውሳኔ አሰጣጥ ላይ የራሳቸውን ፈቃድ ለማስረጽ እና የቤተክርስቲያኒቷን ልዕልና ለማዋረድ የተለያዩ ጥረቶች እያደረጉ እንደሆነ የተለያዩ ማሳያዎች እና ማስረጃዎች አሉ፡፡ስለዚህ ብፁዓን አባቶቻችን በሚቻላችሁ ሁሉ ውሳኔያችሁ ከማንኛውም ውጫዊ አካል ነጻ እንዲሆን እና በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ብቻ የሚመራ እንዲሆን አደራ እንላለን፡፡

ብፁዓን አባቶቻችን

እኛ የመንፈስ ልጆቻችሁ የቤተክርስቲያን ወቅታዊ ችግሮቸ ናቸው ብለን ያሰብናቸውን ሐሳቦች ቅዱስ ሲኖዶስ አጽንኦት ሰጥቶ ሊወያይባቸው፣ ሊመካከርባቸው እና መፍትሔ ሊሰጥባቸው ይገባል ብለን ስናቀርብ እግዚአብሔርን በመፍራት፣ አባቶቻችንን በማክበር እና ለርትዕት ሃይማኖታችን በመቆርቆር፣ በትህትና እና በታላቅ የቅንነት መንፈስ በመነሳት ነው፡፡ ምንም እንኳ ገና በወጣትነት እና በጀማሪ ጎልማሳነት እድሜ የምንገኝ ታናናሽ ልጆቻችሁ ብንሆንም የነገዋን ቤተ ክርስቲያን ከናንተ ተረክበን በክብር ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ በመዘጋጀት የሕይወት ውሃዋን እየጠጣን፣ ምግቧን እየተመገብን በውስጧ የምንኖር በመሆናችን ደኅንነቷ፣ሰላሟ እና እድገቷ ያሳስበናልና የቤተክርስቲያንን ችግሮች እያየን እና እየሰማን ዝም ማለት አንችልም፤ ችግሮቹንም ለአባቶቻችን ብቻ መተው ወይም ቸል ማለት አንችልም፡፡ ስለዚህ አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔርን አጋዥ አድርገን ከአባቶቻችን ጋር በመመካከር የሚቻለንን ሁሉ እያደረግን ቤተክርስቲያንን ለማገልገል ዝግጁ ነን፡፡

ስለዚህ አባቶቻችን የቤተክርስቲያን ችግሮች ተፈትትው፣ኢኮኖሚያዊ አቅሟ ተጠናክሮ፣ ሰላሟ ተጠብቆ እና እድገቷ ተፋጥኖ ወደ ቀደመ ልዕልናዋ ለመመለስ እንድትችል በምታደርጉት ጥረት ሁሉ በታዛዥነትና አባታዊ ቡራኬአችሁን በመቀበል እስከመጨረሻው ድረስ ከጎናችሁ በመሆን የእግዚአብሔርን አገልግሎት በተገቢው መንገድ ለመፈጸም ቁርጠኝነታችንን ልንገልጽላችሁ እንወዳለን፡፡

የአባቶቻችን ጸሎት እና ቡራኬ አይለየን

አሜን!

የፎንት ልክ መቀየሪያ