Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

ወጣቱና ክርስቲያናዊ ባህል በኢትዮጵያ

ከመልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን
የሊቃውንት ጉባኤ አባል

ቤተ ክርስቲያን ማለት በትርጓሜ ቤት ዘይቤ የምእመናን ስብስብ ማለት ሲሆን ምእመናን አምልኮተ እግዚአብሔርን ለመፈጸም የሚሰበሰቡበት ቤተ ጸሎትም ቤተ ክርስቲያን ይባላል፡፡ የምእመናን ስብስብ በእድሜ፣ በጾታ፣ በማዕረግ የተለያየ የኅብረተሰብ ክፍል የሚገኝበት መድበለ ማኅበር ሲሆን ይህም መድበለ ማኅበር፤

 • ካህናት ወመኃይምናን /ካህናትና መኃይምናን/
 • ዕድ ወአንስት /ወንዶችና ሴቶች/
 • አዕሩግ ወደቂቅ /ሽማግሌዎችና ልጆች/
 • ዐቢይ ወንዑስ /ትልቅና ትንሽ የመዓረግ/

በሚል ክፍል ይከፈላል፡፡

ከዚህ መድበለ ማኅበር ዝርዝር ውስጥ "ደቂቅ" ወይም "ልጆች" የሚለው ክፍል ከሕፃናት ጀምሮ ወጣቱን ትውልድ ይመለከታል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም እንደ ቤተ ክርስቲያንነቷ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ተሟልቶ የሚገኝባት ተቋም ስለሆነች እንኳን ወጣቶችን ሕፃናትን ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ማለት ከምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ተሳትፎ አታገልም፤ ወጣት ሽማግሌ ሳትል ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል እንደ አንድ ቤተሰብ ትንከባከባለች፡፡

1. የወጣቶች አስተዳደግና አያያዝ በቤተ ክርስቲያን፤

"ጠቦቶቼን ጠብቅ" ዮሐ. 21፡16

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ብርሃንና የዓለም ጨው ሁነው የሰውን ልጅ እንዲያገለግሉ ካዘጋጃቸው ደቀ መዛሙርት መካከል ለአንዱ ለቅዱስ ጴጥሮስ ከተናገረው የአደራ ቃል አንዱ "ጠቦቶቼን ጠብቅ" የሚል ነው፡፡ ጠቦቶቼ የሌባ ሰለባ እንዳይሆኑ ሌት ተቀን ነቅቶና ተግቶ ይጠብቃል፡፡ ሕፃናትና ወጣቶችም ከሕፃንነታቸውና ከወጣትነታቸው አንጻር ለማይፈለግ ምኞትና ተግባር የወደፊት ሕይወትን ሊጎዳ ለሚችል ሕገ ወጥነት፣ በጀብደኝነት ለሚመጣ ድቀት ወዘተ የተጋለጡ እንዳይሆኑ በመንፈሳዊ ምግብና ቤተ ክርስቲያን ለልጆችና ወጣቶች የምታደርገው ጥንቃቄ ከሌላው የላቀ መሆን ይኖርበታል፡፡

ቤተ ክርስቲያን የመንጋ ጥበቃ ተግባሯን ፍጹም ለማድረግ ጠንካሮች፣ ፈቃደኞች፣ ፍትወት ያላቸነፋቸውና በኅሊናቸው የነጹ፣ እርምጃቸው የተቃነ ማለት "የወይፈን በሬ" የሆኑ ወጣቶች ያስፈልጓታል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ወጣቱን ትውልድ የመሳብና ወደ ራስዋ የማቅረብ ግዴታ አለባት፡፡ ስለሆነም የየዘመኑን ወጣት እርምጃ ለማስተካከል ብትችል ምን ጊዜም የወደፊት ሕይወቷ ብሩህ ሊሆን ይችላል፡፡

ከዚህ ግዴታ በመነሣት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለወጣቱ የምታደርገው ጥበቃና አያያዝ ገና ፍጹምነት የሚቀረው ቢሆንም በወጣት የተሞላች ቤተ ክርስቲያን መሆንዋ ግን አይካድም፡፡ ይህም የሆነው እንዲያው ሳይሆን ለሕፃናትና ለወጣቶች የሚከተለውን የእናትነት ተግባር ስለምትፈጽም ነው፡፡

1. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወጣቶች ከአርባና ከሰማንያ ቀን ጀምሮ በጥምቀት የቤተ ክርስቲያንን ምሥጢር እንዲሳተፉና ሙሉ አባልም እንዲሆኑ ታደርጋለች፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሕፃናት ጥምቀትን ከሚቀበሉ አብያተ ክርስቲያናት አንዱዋ በመሆንዋ ወጣቶች የቤተ ክርስቲያንን እንክብካቤ የሚያገኙት ገና ከሕጻንነት ጀምሮ ነው፡፡

2. ለሕሣናትና ወጣቶች ሲታተሙ ቤተ ክርስቲያን ፈውስ ለማግኘት የሚችሉበትን እንክብካቤ ታደርጋለች፣ ይኸውም ቅዱስ ቁርባንን እንዲቀበሉ ማድረግ ነው፡፡

3. እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በየአጥቢያው ቤተ ክርስቲያን በተቋቋሙ ትምህርት ቤቶች ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ የሚሰጠውን ትምህርት እንዲከታተሉ በማድረግ ለቁም ነገር ተበቃለች፡፡

4. ይህም የትምህርት ዕድል ማግኘት ላልቻሉ ወጣቶች በአሁኑ ጊዜ በየአብያተ ክርሰቲያናቱ በተቋቋሙ የሰንበት ትምህርት ቤቶች የሃይማኖትና የግብረ ገብ ትምህርት ትሰጣለች፡፡ የቀሩትም ከወላጆቻቸውና እንዲሁም ከቤተሰቦቻቸው መምህረ ንስሐ የሃይማኖት ትምህርት በማግኘት ጥሩ ምእመን ለመሆን እየቻሉ ናቸው፡፡ ሆኖም ወላጆች ለልጆቻቸው ብቁ የሃይማኖት መምህራን ለመሆን ይችሉ ዘንድ ምእመናን በቂ ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ ከቤተ ክርስቲያን የሚጠበቅ ኃላፊነታቸው ለወላጆች ብቻ ሳይሆን ለቤተሰብ ሁሉ ስለሆነ ለወላጆች የሚያደርጉትን የመንጋ ጥበቃ ተግባር ለልጆችም የማድረግ ግዴታ አለባቸው፡፡

ከዚህ ባህልና ሥርዓት መረዳት የሚቻለው በቤተ ክርስቲያንና በወጣቶች መካከል ያለው ግንኙነት በወላጆችና ልጆች መካከል ከአለው ግንኙነት የተለየ አለመሆኑን ነው፡፡ወላጆች የልጆቻቸውን መፍቀደ ሥጋ ለማሟላት የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት እንደሚያደርጉ ሁሉ ቤተ ክርስቲያንም የወጣቶችን መፍቀደ ነፍስ ለማሟላት የሚጠበቅባትን የእናትነት ተግባር ለመፈጸም መብቃት ይኖርባታል፡፡

ይህም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ "ጠቦቶቼን ጠብቅ" ሲል ለቅዱስ ጴጥሮስ የተናገረውንና እንዲሁም ከዚህ በታች የተገለጸውን የቅዱስ ያሬድ ቃል መፈጸም ነው፡፡

"ዘአፍቀራ ለቤተ ክርስቲያን ኢይጻሙ፤ ወተሐቅፎ ከመ እሙ፣ ወተዐብዮ እምነ ቢጹ፣ ወትሴስዮ እክለ ጥበብ ወአእምሮ፣ ወታስትዮ ወይነ ትፍሥሕት ዘበአእምሮ፤ ወታስተቄጽሎ አክሊለ ትፍሥሕት ወሐሤት" /ጾመ ደጓ/፡፡
ትርጉም

"ቤተ ክርስቲያንን የወደዳት መንፈሰ ደካማ አይሆንም፡፡ እንደ እናት ታቅፈዋለች፤ ከጓደኛውም የላቀ ታደርገዋለች፤ የዕውቀትና ጥበብ ምግብን ትመግበዋለች፣ በዕውቀት የሚገኝ የደስታ ወይንንም ታጠጣዋለች፣ የደስታ አክሊልንም ታቀዳጀዋለች፡፡"

ይህ ያሬዳዊ ቃል ቤተ ክርስቲያን ለወጣቶች በዕርግጥ የዕውቀትና ጥበብ ተቋም መሆንዋን በትክክል የሚያረጋግጥ ነው፡፡

ቅዱስ መጽሐፍ "ኢየሱስም ደግሞ በጥበብና በቁመት፤ በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ ነበር" ይላል፡፡ ሉቃ. 2፡52 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብሉየ መዋዕል አምላክ "ብሉየ መዋዕል አምላክ" ሲሆን ለእኛ ሲል ከቅድስት ድንግል ተወልዶ ሕፃንም፣ ወጣትም ሁኖ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት በጥበብና በሞገስ ያደገው እኮ ለወጣቶች አርአያ ለመሆን ነው፡፡ በመሆኑም ወጣቶች እሱን አብነት አድረገው በእግዚአብሔርና በሰው ፊት በጥበብና በሞገስ ያድጉ ዘንድ ቤተ ክርስቲያን እናትም፣ ሞግዚትም፤ የዕውቀትና ጥበብ ተቋምም ልትሆናቸው ያስፈልጋል፡፡

ቅዱስ ያሬድ እንደተናገረው ወጣቶች ከዕውቀት እንዳይራቡና እንዳይጠሙ ቤተ ክርስቲያን ይህን የእናትነትና የሞግዚትነት ኃላፊነቷን ልትወጣ የምትችለውም ለሥጋዊና መንፈሳዊ ሕይወት ግንባር እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነውን መንፈሳዊና ሥጋዊ ዕውቀትና ጥበብ በማያቋርጥ ትምህርት እየመገቡ በማሳደግ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን እስከ አሁን ተጠብቃ የኖረችውም ይህን ባህል ጠብቃ በመኖሯ ነው፡፡

የወጣቶች የሥራ ድርሻ በቤተ ክርሰቲያን

 • በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ወጣቶች ዕድሜያቸውና የዕውቀት ደረጃቸው ሲፈቅድ በዲቁና፣ በቅስና፣ በድብትርና /መዘምርነት/ በመምህርነት ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል የበቁ ይሆናሉ፡፡
 • ከዚህም ጋር የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት የሚጠይቀውን የጉልበት ተልዕኮ ይፈጽማሉ፤
 • ለግብረ ክህነት ያልበቁ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በየክብረ በዓላቱ በቤተ ክርስቲያን በመገኘት በመንፈሳዊ ዝማሬና እንዲሁም በባህላዊ ዜማና ግጥም አምልኮታቸውን ከመፈጸም ጋር ክብረ በዓሉን አድምቀውት ይውላሉ፡፡ እንዲያውም እንደ ጥምቀት ባሉ በዓላት ወላጆች ከብትና ቤት እየጠበቁ ልጆች ወደ ቤተ ክርስቲያን እየሄዱ በዓል እንዲያከብሩ ማድረግ በቤተ ክርስቲያናችን ኅብረተሰብ የተለመደ ባህል ሁኖ ኑሯል፡፡

ከዚህ በላይ የተደረገው ጠቅላላ ትንተና ወጣቶች በቤተ ክርስቲያን ያላቸው አስተዳደግና አያያዝ ምን እንደሚመስል ባጭሩ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ ባህልና ሥርዓት የነበረ ብቻ ሳይሆን አሁንም ያለ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አያያዝና አስተዳደግ ወጣቱን ትውልድ ለማቅረብና ታማኝ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተረካቢ ለማድረግ በሚያስችል ትምህርትና ዕውቀት፣ ባህልና ሥርዓት ለማነጽ የሚያስችል ስለሆነ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለወጣቱ ትውልድ መልካም አስተዳደግና አያያዝ የምታደርገው ጥረት የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ወጣቱ ትውልድ ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመቅረብ ያለው ፍላጎት ለምንግዜውም የላቀ ነው፡፡ ሆኖም ቤተ ክርስቲያን ወጣቱን ለማቅረብና የቀረበውንም ለመቀበል ያላት ዝግጅት የሚፈለገውን ያህል ብቁ አይደለም፡፡ በመሠረቱ ከቤተ ክርስቲያን አካል አንዱ ክፍል ወጣቱ ስለሆነ ያለወጣቱ ህልውና ቤተ ክርስቲያን የተሟላ አካል አይኖራትም ማለት ያላት ጾታ ምእመናን ወይም ያላት መድበለ ማኅበር የተሟላ አይሆንም፡፡ ስለዚህ ሰውን ማጥመድ አሣ ከማጥመድ ያላነሰ ትጋትና ጥረትን የሚጠይቅ ስለሆነ /ማቴ. 19/ ቤተ ክርስቲያን ወጣቱን ለማቅረብ ጥሩ አጥማጅ መሆን ይኖርበታል፡፡

ወጣቱና የአለባበስ ባሀል በቤተ ክርስቲያን

በሀገራችን በየብሔረሰቡ የተለያየ የአለባበስ ባህል አለ፡፡ ሆኖም ያን ሁሉ መዘርዘር የዚህ ዝግጅት አላማ አይደለም፤ ከተነሣበት ርእስ አንጻር መናገር የሚቻለው ቤተ ክርሰቲያን ለወጣቱ ትውልድ እያወረሰችው ያለውን ባህል ምንነት ነው፡፡ በኦርቶዶክሳዊት ኢትዮጵያ ሁለት ዓይነት የአለባበስ ባህል ይታያል፡፡ ባህሉ መነፈሳዊና ሥጋዊ ጠባይ ያለው ሲሆን በዓይነቱ ከሌላው የክርስትና ዓለም የተለየ ነው፡፡

የክህነት አለባበስ

በካህናት የአለባበስ ባህል ረጅም እጅ ጠባብና ሰፊ ሱሪ መልበስ፣ ሻሽ መጠምጠምና ከተቻለም ካባ መደረብ የተለመደ ሲሆን አንድ ሰው ካህን መሆን አለመሆኑን ሕዝቡ በአለባበሱ ሊያውቀው ይችላል፡፡ በተለይ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ግን ካህኑ የግብርና ሥራ በሚሠራበት ጊዜ የምእመን አለባበስ ይለብሳል፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ግን ከሌሎች ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ባህል የተወረሰ የአለባበስ ባህል ሥር ሰድዶ ይታያል፤ ይኸውም ጥቁር ቀሚስና ፈረጅያ የመልበስ ባህል ነው፡፡

የምእመን አለባበስ፤

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ምእመናን የራሳቸው የሆነ የአለባበስ ባህል አላቸው፡፡ ይህንም ባህል መንፈሳዊ ሥጋዊ በሚል ሁለት ክፍል ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ አንድ ምእመን ወደ ቤተ ክርስቲያን በሚገባበት ጊዜ ልብሱን አመሳቅሎ ይለብሳል፡፡ ይህ ዓይነቱ አለባበስም ትእምርተ መስቀል ዓይነት አለባበስ ይባላል፡፡ የመስቀል ምልክት ያለው ይህ ዓይነቱ አለባበስ ምንጊዜም በቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎች የሚፈጸም መንፈሳዊ ባህል ሲሆን ከቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ውጭ ግን የአለባበሱ ዓይነት ይቀየራል፤ ያም ዓይነት አለባበስ ሥጋዊ ሊል ይችላል፡፡ ይህ ከዚህ በላይ የተገለጸው የአለባበስ ባህልና ሥርዓት በዘመኑ ክርስቲያን ወጣቶች ዘንድም በትውፊትነት ሲፈጸም ይታያል፡፡ ባህል የማንነት መታወቂያ ስለሆነ በየዘመኑ በሚነሳው ወጣት ምን ጊዜም መጠበቅና መከበር ይኖርበታል፤ እንዲሻሻል ሲያስፈልግም መሠረቱም ሳይለቅ የራስን ባህል በራስ ማሻሻል ይቻላል፡፡ በሌላ የውጭ ባህል ግልበጣ የራስን ባህል መቀየር ግን ማንነትም መቀየር እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡

የወጣትነት ሕይወት በቤተ ክርስቲያን ትምህርት ቤት

በቤተ ክርስቲያን ት/ቤት ወጣቶች ያላቸው ጓደኝነትና የፍቅር መተሳሰብ ምሳሌነት ያለው ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ትምህርት ቤት የሚገናኙት ከየትኛውም አቅጣጫ የተሰባሰቡና እርስ በእርሳቸው የማይተዋወቁ ወጣቶች ናቸው፡፡ ኑሮአቸው የተመሠረተውም በእግዚአብሔር ስምና በእመቤታችን እንዲሁም በሌሎች ቅዱሳን ስም በሚለገሥ የበሰለና ጥሬ እህል ገቢ ላይ ነው፡፡ የሚመገቡትም በቡድን በቡድን ሁነው በኅብረት ነው፡፡ ዓይነ ስውሮችና ዓቅመ ደካሞች በደኅነኞች ጓደኞቻቸው ስለሚረዱ የምግብና መጠለያ ችግር አይኖርባቸውም፡፡ አንድ ተማሪ ሲታመም ተላላፊ በሽታ ቢሆንም እንኳ ጓደኛው ጥሎ አይሸሽም፣ እስከ መጨረሻው ያስታምማል፡፡

የዜማ ትምህርትን በሚመለከት ተማሪው ሌሊት በቃል፣ ቀን በዓይን መጻሕፍት ከመምህሩ አጠገብ ቁጭ ብሎ እያዜመ ይማራል፣ ትምህርቱ የሚሰጠው በተራ ስለሆነ የተወሰኑ ተማሪዎች በመምህሩ ዙሪያ ሁነው የየራሳቸውን ትምህርት ሲማሩ የቀሩት ደቀ መዛሙርት በያሉበት ጎጆ ሁነው በትምህርት ከነሱ በታች የሆኑትን ተማሪዎች በተዋረድ ያስተምራሉ፡፡ የቅኔና የትርጓሜ መጻሕፍት ትምህርት ሂደትም እንዲሁ የራሱ ባህል ስለአለው በየትምህርት ቤቱ ባህሉን ተከትሎ ይሰጣል፡፡ አስተማሪው ተማሪዎቹን የሚያስተምረው እንደ ሠራዒ መጋቢት ሁኖ ስለሆነ የትምህርት ቤቱን ሥነ ሥረዓት /ዲሲፕሊን/ ይቆጣጠራል፤ ዳኝነትም ያያል፤

ተማሪዎቹ መምህራቸውን ስለሚያከብሩ መምህራቸውን የሚጠሩት የኔታ /የኔ ጌታ/ በማለት ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ት/ቤት ተማሪዎች እንግዲህ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ያለውን የትምህርት ዓይነት በመከታተል ለመንፈሳዊ ማኅበራዊ አገልግሎት የሚበቁት በዚህ ዓይነት ሕይወት በማለፍ ስለሆነ የቤተ ክርስቲያን ነባር ትምህርት ቤቶች ህልውና ለቤተ ክርስቲያን ህልውና ምንጊዜም አስፈላጊ ነው፡፡ የተማሪዎቹ ኑሮና የትምህርቱ አሰጣጥ ባህልና ሥርዓት ግን ከበድ ያለ ስለሆነ የጊዜውን ወጣት በማያርቅ ሁኔታ መሻሻል ይኖርበታል፡፡

ኦርቶዶክስ ሃይማኖትና ወጣቶች፤

ቅዱስ መጽሐፍ በጉብዝናህ /በሕፃንነትህ/ ወራት እግዚአብሔርን አስብ ይላል መክ. 12፡1 ከልጅነትና ከወጣትነት ጊዜ ጀምሮ እግዚአብሔርን ለማሰብ ሃይማኖተኛ መሆንን ይጠበቃል፡፡ ሃይማኖተኛ ለመሆንም የሃይማኖት ትምህርት ያስፈልጋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ቀኖና አባቶች ልጆቻቸውን አስቀድመው የሢራክና የሰሎሞን መጻሕፍትን፣ የዳዊትን መዝሙር እንዲያስተምሩ ያዝዛል /ዲዲስቅልያ/፡፡ እነዚህ መጻሕፍት ከሌላው ተለይተው የተጠቀሱት ወጣቱ ትውልድ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት በጥበብና በሞገስ ቢያድግ የሕይወት ጉዞው እስከ መጨረሻው የተቃና ሊሆን እንደሚችል የሚሰጡት ምዕዳን ጥልቀት ያለው በመሆኑ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት ትምህርት የምታስተምርባቸው ሁለት ዓይነት ት/ቤቶች አሏት፡፡ ከእነዚህም አንዱ አስቀድሞ የተገለጸው ነባር ትምህርት ቤት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ዘመናዊው የሰንበት ትምህረት ቤት ነው፡፡ በነባሩ የቤተ ክርስቲያነ ት/ቤት የሚሰጠው ትምህርት እስከ አሁን ድረስ የሚያተኩረው በቀለሙ ትምህርት ላይ ስለሆነ ለወደፊቱ በእነዚህ ት/ቤቶች ከቀለሙ ትምህርት ጎን ለጎን የሃይማኖት ትምህርትም መስጠት ይኖርበታል፡፡ ይህም ሁኖ ወጣቶቹ በነባሩ ት/ቤት የሚማሩት የቀለም ትምህርት መንፈሳዊ በመሆኑ ትምህርቱ በተማሪዎቹ ሕይወት ላይ መንፈሳዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ አልቀረም፡፡ ይኸውም ለተማሪዎቹ የሚሰጠው የቀለም ትምህርት የሃይማኖት ትምህርት ስለአለው ነው፡፡ በሰንበት ትምህርት ቤት የሚሰጠው ትምህርት ግን በቀጥታ የሚሰጥ የሃይማኖት ትምህርትና ስብከት ስለሆነ ይኸው ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡

የኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ሃይማኖትን መከተል በኢትዮጵያ እንደ ባህልም ነው፡፡ ሃይማኖቱ እንደባህል ላይ የቻለውም በሕዝቡ ዘንድ እጅግ በጣም የሠረጸ በመሆኑ ነው፡፡ በሀገሪቱ ከሚታየውም ሕዝባዊ ባህል አብዛኛው ሃይማኖታዊ ነው፡፡ ወጣቱ ትውልድ ሃይማኖተኛ ሁኖ የኖረው በቀጥታ በሚያገኘው የሃይማኖት ትምህርት ብቻ ሳይሆን ከባህሉም በመማር ነው፡፡ ያለውና የነበረው ክርስቲያናዊ ባህል ወጣቱን ወደ እምነት የሚመራ ገንቢ ስለሆነ ወደፊትም ለዘለዓለም ይኑር፡፡

ወጣቶችና ግብረ ገብነት፤

ወጣቶች ሆይ ብርቱዎች ስለሆናችሁ፣ የእግዚአብሔርም ቃል በእናንተ ስለሚኖር፤ ክፉውንም ስለአቸነፋችሁ እጽፍላችኋለሁ፡፡ 1ዮሐ. 2፡14፡፡
ይህ ቃል ወንጌላዊው ዮሐንስ በዘመኑ ለነበሩ ብርቱዎች ወጣቶች የጻፈው የማበረታቻ ቃል ነው፡፡ ወጣቶች ብርቱዎች ተብለው በሐዋርያው አንደበት ሊወሰዱ የቻሉት ከዚያው ከወንጌላዊው ቃል መረዳት እንደሚቻለው የእግዚአብሔር ቃል በእነሱ ስለሚኖርና በዚያም ክፉውን ሁሉ ለማቸነፍ በመቻላቸው ነው፡፡

የወጣትነት ዘመን የእሳትነት ዘመን ስለሆነ የእግዚአብሔር ቃል በእነሱ ከሌለ ወጣቶች የማይፈተኑበት ክፉ ነገር የለም፡፡ ትዕቢት፣ ጀብደኝነት፣ ስሜታዊነት በክፉ መልኩ የሰውን ልጅ የሚፈታተነው በወጣትነት ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ፈተና የወደቁ ወጣቶች ለወላጆቻቸው አይታዘዙም፤ ሽማግሌ አያከብሩም፤ ለወላጆች መታዘዝና ሽማግሌ ማክበር ውርደት መስሎ ይታያቸዋል፤ ስሜታዊነት ስለሚያጠቃቸው ውጤቱ አደገኛ የሆነውን ድርጊት ሳይቀር ለመፈጸም ይደፍራሉ፤ ፋሪሃ እግዚአብሔር የላቸውም እከብር ባይ ልቡና ያጠቃቸዋል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ገንዘብ ያባክናሉ ወዘተ፡፡ በዚህ ምክንያት በእንዲህ ዓይነቱ ወጣቶች ሰውነት ግብረ ገብነት ቦታ ያጣል፡፡
የእግዚአብሔር ቃል በእነሱ የሚኖር ከሆነ ግን ጥበብ፤ ማስተዋል፣ ትሕትና፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር፣ ፍቅረ ቢጽ ወዘተ ስለሚኖራቸው ከላይ የተጠቀሰውን ሁሉ ክፉ ነገር ለማቸነፍ ዓቅም ያገኛሉ፡፡ ፍትወተ ሥጋን ሐውዘ ዓለምን ድል መንሳት ይችላሉ፡፡

ዘመን በተለወጠ ቁጥር ባህልም ቀስ በቀስ ስለሚለወጥ በአባቶቻችን ጊዜ የነበረው ግብረ ገብነት አሁን ሙሉ በሙሉ በተግባር ላይ አይታይም፤ ለምሳሌ ሽማግሌን የማክበር፣ የመታዘዝ፣ ድንግልናን እስከ ጋብቻ የመጠበቅ ባህል ወዘተ በአሁኑ ዘመን ወጣት ሕይወት የቀድሞውን ያህል ቦታ የለውም፣ ሁኖም የኢትዮጵያ ወጣቶች ግብረ ገብነት ከምዕራቡ ክፍለ ዓለም ወጣቶች ጋር ሲነጻጸር እጅግ በጣም በተሻለ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ከላይ የተዘረዘረው ግብረ ገብነት በምዕራቡ ክፍለ ዓለም ወጣቶች ዘንድ የተረሳ ባህል ሁኗል፡፡ ያስረሳውም የዘመኑ ሥልጣኔና ዲሞክራሲ ነው፡፡ ሌላው ምክንያት ደግሞ የወጣቱ ትውልድ ከሃይማኖት እየራቀ መሄድ ነው፡፡
የሣይንስና ቴክኖሎጂ ሥልጣኔ በምሥራቁ ክፍለ ዓለምም ከምዕራቡ በአላነሰ ሁኔታ እያደገ በመሄድ ላይ ነው፡፡ ሁኖም ሥልጣኔያቸው ባህላቸውን አላስለወጣቸውም፡፡ ስለሆነም በእነዚያ ሀገሮች የወጣቱ ትውልድ ግብረ ገብነት ከአለፈው የቀጠለ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ግብረ ገብነትም እንዲሁ ከአለፈው የቀጠለ ቢሆን ለሀገር ዕድገት የሚበጅ እንጂ የሚጎዳ አይሆንም፡፡ ሃይማኖትና ግብረ ገብነት ያለው ትውልድ የእግዚአብሔር ቃል በእሱ ስለሚኖር ምን ጊዜም ክፉውን ሁሉ ለማቸነፍ የሚችል ብርቱ ይሆናል፡፡ ሃይማኖትና ግብረ ገብነትም የኢትዮጵያ ባህል ጸንቶ የሚኖርበት መሠረት ስለሆነ ይህ መሠረት ሳይናወጥ ምንጊዜም ጸንቶ መኖር ይገባዋል፡፡

ጋብቻና ወጣቶች

እያንዳንዱ ወንድ ለራሱ ሚስት ይኑረው፣ እንያንዳንዷ ሴትም ለራስዋ ባል ይኑራት 1ቆሮ. 7፡2
የእግዚአብሔርን ቃል መሠረት በማድረግ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እያንዳንዱ ወንድ ሚስት እንዲኖረው፣ እያንዳንዷም ሴትም ባል እንዲኖራት ይመክራል፡፡ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ባልና ሚስት ለመሆን ሕጋዊ ጋብቻን መመሥረት ይኖርባቸዋል፡፡

የጋብቻ አስፈላጊነት

 • ጋብቻ አስፈላጊ የሆነው ፈቃደ ሥጋን ለመፈጸም 1ቆሮ. 7፡2-7 ፍ.ነ.አንቀጽ 24
 • ልጅ ለመውለድ ዘፍ. 1፡28
 • እርስ በርስ ለመረዳዳት ወዘተ... ዘፍ. 1፡2-25 ነው

የጋብቻ ምሥጢር

ጋብቻ ሁለቱን ባልና ሚስት አንድ ሥጋ ወይም አንድ አካል የሚያደርግ ምሥጢር ነው፡፡ ዘፍ. 24፣ ማቴ. 19፡5 ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በባልና ሚስት መካከል ያለውን የአንድነት ምሥጢር በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን መካከል ከአለው አንድነት ምሥጢር ጋር በማነጻጸር ተናግሯል ኤፌ. 5፡32 በዚህ ምክንያት ጋብቻ ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን እንደ አንዱ ሁኖ ይፈጸማል፡፡

የጋብቻ አፈጻጸም፤

ጋብቻ በቤተ ክርስቲያን ጸሎተ ተክሊል የሚፈጸም ምሥጢር ነው፡፡ ጋብቻ ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ያለ ምሥጢረ ተክሊል ጸሎት መፈጸም እንደማይገባው ፍትሐ ነገሥት ይደነግጋል አንቀጽ 24 ቁጥር 883፡፡ የቤተ ክርስቲያን ቀኖና ይህን ቢልም ቤተ ክርስቲያን በመንደር ሽማግሌና በማዘጋጃ ቤት ለሚፈጸመውም ጋብቻ ዕውቅና መስጠቷ አልቀረም፤ ይኸውም ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ጋብቻቸውን ለፈጸሙት ወገኖችም እኩል አገልግሎት ስለምትሰጥ ነው፡፡
ጋብቻ በሁለቱ ተጋቢዎች ፈቃድ መፈጸም እንደ አለበትና በእነሱ ፈቃድ ላይም የወላጆች ፈቃድ እንዲጨመርበት አሁንም ፍትሐ ነገሥት ያዝዛል አንቀጽ 24 ቁጥር 866፡፡ የፈቃድ ጋብቻ በዘመነ ብሉይም ሲፈጸም የኖረ ባህል እንደነበር ከርብቃ ጋብቻ መረዳት ይቻላል፡፡ ርብቃ ይስሐቅን ያገባችው በራስዋም በቤተሰቧም ፈቃድ ነበር ዘፍ. 24፡50-60 በሀገራችን ሴቶች ልጆችን ያለፈቃዳቸው ማጋባት የተለመደ ባህል ሆኖ መቆየቱ አይካድም፡፡ ሁኖም ይህን ባህል ቤተ ክርስቲያን አትቀበለውም፡፡

የጋብቻ ዕድሜ

የፍትሐ ነገሥት ለጋብቻ የተፈቀደው ዕድሜ ለወንድ ከሐያ፣ ለሴት ልጅ ከአሥራ አምስት ዓመት ዕድሜ በላይ ነው አንቀጽ 24፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ ሕገ መንግሥት የተፈቀደው የጋብቻ ዕድሜም ለሴት ከአሥራ ስምንት በላይ ሲሆን ለወንድ ከሐያ አንድ በላይ ነው፡፡ ይህ ሕግ የወጣው የሴቶች ልጆች ደኅንነትን ለመጠበቅ ሲባል ስለሆነ ቤተ ክርስቲያንም ትደግፈዋለች፡፡ በጸሎተ ተክሊል የሚፈጸመውን ጋብቻ በሚመለከት ለተጋቢዎቹ የጸሎተ ተክሊል ሥርዓት የሚፈጸመው በድንግልና ተወስነው ለኖሩ ተጋቢዎች ብቻ ሲሆን ከሁለቱ አንዱ ድንግልና የሌለው ወይም የሌላት ከሆነ ተክሊል የሚፈጸመው ድንግልናውን ጠብቆ ለቆየው ብቻ ነው፡፡

የጋብቻ ኑሮ ሥርዓት

ባልና ሚስት አንድ ሥጋ ስለሆኑ ባል እናት አባቱን ትቶ ሚስቱን መከተል እንደአለበት ማቴ. 19፡5 ሚስቱን እንደራሱ መውደድ እንደሚገባው ኤፌ.5፡15፣ ፈቃዷን እንዲፈጽም 1ቆሮ. 7፡3 ወዘተ... የእግዚአብሔር ቃል ያዝዛል፡፡ ሚስትም እንዲሁ ባሏን የምትወድ፣ ለባሏ የምትገዛ፣ ልጆቿን የምትወድ፣ ቤተሰቧን የምታስተዳድር፣ ራስን የምትገዛ ወዘተ... እንድትሆን የቅዱስ መጽሐፍ ቀኖና ይበይናል፣ ቲቶ. 2፡4-6፤ 1ጴጥ.3፡1-6፣ 1ጢሞ.5፡14፤

ቅዱስ መጽሐፍ እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን ሰው አይለይ ማቴ. 19፡6 ስለሚል የጋብቻ ቃል ኪዳን ዘለዓለማዊ ማለት እስከ ሞት ድረስ የጸና መሆን ይኖርበታል፡፡ ሆኖም በተወሰኑ ምክንያቶች ፍች ሊፈቀድ ይችላል ማቴ. 5፡31፤

ባህላዊ ጋብቻ በሀገራችን

በሀገራችን በአሁኑ ጊዜ ሁለት ዓይነት የጋብቻ ባህል አለ፡፡ ይኸውም አንደኛው በቈየው ባህል መሠረት ሁለቱ ሳይተዋወቁ በሁለቱ ወላጆች ስምምነት የሚፈጸም ጋብቻ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በተለይ በአሁኑ ጊዜ በሁለቱ ተጋቢዎች ፈቃድና በቤተሰብ ስምምነት የሚፈጸም ጋብቻ ነው፡፡ በሁለቱ ተጋቢዎች ስምምነት የሚፈጸመው ጋብቻ በቤተ ክርስቲያን ቀኖናም የተወሰነ ስለሆነ የቤተ ክርስቲያን ድጋፍ አለው፡፡

ማጠቃለያ

ባህል ማለት በኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ዘይቤ ሕግ ሥርዓት ወግ ልማድ ማለት ነው፡፡

በተለይም የክርስትና ባህል መንፈሳዊ ስለሆነ ክርስቲያናዊ ባህል ማለት መንፈሳዊ ሕግና ሥርዓት ማለት ነው፡፡ አብዛኛው ሥጋዊው ባህልም በተለይ በሀገራችን ሃይማኖትንና ሃይማኖተኛነትን የሚያንጸባርቅ ስለሆነ መነፈሳዊነት አለው፡፡ የባህል ምንነት እንዲህ ከሆነም ክርስቲያናዊ ባህል ምንጊዜም ሊከበር የሚገባው ሕግና ሥርዓት መሆን ይኖርበታል፡፡ ሆኖም ባህል ሃይማኖትን የሚያጠናክር እንጂ የሚያዳክም መሆን አይኖርበትም፡፡ ከዚህም ጋር ወጣቱ ትውልድ ቤተ ክርስቲያን የምትቃወመው ጎጂ ባህል ወራሽ እንዳይሆን ማስተማር የመምህራን ግዴታ ይሆናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን
የሊቃውንት ጉባኤ አባል

የፎንት ልክ መቀየሪያ