Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

ከብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ

abun klimatosብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የከምባታና ሐዲያ ስልጤ ጉራጌ አኅጉረ ስብከትና በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ በመሆን እያገለገሉ የሚገኙ አባት ናቸው፡፡ ሁሉንም አኅጉረ ስብከታቸው ለማጠናከርና የተሰጣቸውን ሐዋርያዊ ተልዕኮ ለመወጣት እስከ ገጠሪቱ ቤተ ክርስቲያን ድረስ በእግርም ጭምር እየተንቀሳቀሱ የቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ አገልግሎት እንዲቃና እያደረጉ የሚገኙ አባት ናቸው፡፡ አኅጉረ ስብከቶቹ የተራራቁ ከመሆናቸው የተነሳ አንድም ቀን ዕረፍት ሳያደርጉ ሐዋርያዊ ጉዞ የሚያደርጉበት ጊዜ እጅግ በጣም ብዙ ነው፡፡
ይህንን ሐዋርያዊ አገልግሎታቸው ፈጽመው ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ ደግሞ የሕጻናትና ወጣቶች ሁለንተናዊ ዕድገትና አገልግሎት የሰመረ እንዲሆን ለማድረግ በመንበረ ፓትርያርክ ሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ በሚገኝ ጽ/ቤታቸው እየተገኙ በአገልግሎት የሚተጉ አባት ናቸው፡፡
ብፁዕ አባታችን ከሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን አንዱ ክፍል የሆነው የሰንበት ትምህርት ቤቶችን ወቅታዊ ሁኔታ በሚመለከት ማብራርያ እንዲሰጡን የዝግጅት ክፍላችን ሲጠይቃቸው ፈቃደኛ በመሆናቸው በሁሉ አንባቢዎቻችን ስም ከፍተኛ የሆነ ምስጋና እያቀረብን ብፁዕ አባታችን የሰጡት ማብራርያ እነሆ እንላለን፡፡

ጥያቄ በዝግጅት ክፍሉ ፡-

ቅዱስ ሲኖዶስ የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ በሊቀ ጳጳስ ደረጃ እንዲመራ የወሰነበት ምክንያት ቢገልፁልን?

መልስ በብፁዕ አባታችን፡-

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለሕፃናትና ለወጣቶች ትኩረት ይሰጣል፡፡ በሊቀ ጳጳስ ደረጃ እንዲመራ ማድረጉ ደግሞ የበለጠ ትኩረት መስጠቱ ያመለክታል፡፡ ምክንያቱ ሕፃናትና ወጣቶች ልዩ እንክብካቤ፣ ትምህርትና ክትትል የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ነው፡፡ ሁላችንም እንደምንገነዘበው ይህች ቅድስት፣ ሐዋርያዊት፣ ታሪካዊትና ጥንታዊት የሆነች እናት ቤተ ክርስቲያናችን በአግባቡ አባቶቻችን እንዳስረከቡን ክርስትናን እስከነሙሉ ክብሩ በጥንቃቄ በሕፃናትና በወጣቶች አእምሮ በጥንቃቄ አስቀምጦ /ዘርቶ/ ሠላሳ፣ ስልሳና መቶ እንዲያፈራ ካላደረግን ቀጣይ የቤተ ክርስቲያኗ አገልግሎት ከፍተኛ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ ይህ እንዳይሆን በማለት ነው ቅዱስ ሲኖዶስ መምሪያው በሊቀ ጳጳስ ደረጃ እየተመራ በሕፃናትና ወጣቶች ሁለንተናዊ ዕድገት አብዝቶ እንዲሠራ የወሰነው፡፡ በሊቀ ጳጳስ ደረጃ መመራቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ተደማጭነት ይኖረዋል፤ ችግሮች ሲኖሩ በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣ ሕፃናትና ወጣቶችን ማዕከል ያደረገ ጥያቄ ሲቀርብም አስቸኳይ መልስ እንዲያገኙ... በአጠቃላይ የሕፃናትና የወጣቶች ሁለንተናዊ አገልግሎት የበለጠ መልካምና የተቃና ለማድረግ ነው ቅዱስ ሲኖዶስ በሊቀ ጳጳስ ደረጃ እንዲመራ የወሰነው፡፡ ይህ በመሆኑም አሁን ቀደም ብሎ ከነበረው ይልቅ ይበልጥ እየተሰማ ይገኛል፡፡ ወጣቶች ሁለገብ መልካም አገልግሎት እንዲኖራቸው የሚያስችል መመሪያና አደረጃጀት ተዘጋጅቶ በቅዱስ ሲኖዶስ ጻድቋል፣ በጥናት ላይ የተመሠረተ ችግር ፈቺ የሆነ መሪ ዕቅድ እንዲኖርና በተግባር እንዲተረጎም በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡

ጥያቄ በዝግጅት ክፍሉ፡-

በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ስለጸደቀው አዲሱ አደራጃጀትና አወቃቀር፣ እንዲሁም ለሰንበት ት/ቤቶች አገልግሎት መስፋፋት የሚኖረው ፋይዳ ምን ይመስላል?

መልስ በብፁዕ አባታችን፡-

በመሠረቱ ሰንበት ት/ቤት ነባር ተቋም ነው፡፡ ይኸው ነባር ተቋም ከነበረውና ካለው አገልግሎት የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል የሚችለው በተናጠል ከሚሆን ይልቅ ከመንበረ ፓትርያርክ /ሀገር አቀፍ/ ጀምሮ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ነባር የቤተ ክርስቲያኗን መዋቅር በመከተል ሕብረትና አንድነት ቢመሠርቱ መሆኑን በመምሪያውና በሰ/ት/ቤቶች ዘንድ የጋራ መስማማት ላይ ተደረሰ፡፡ በመሆኑም ይኸው አደረጃጀት ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ ወረዳ ቤተ ክህነት ደረጃ አንድነት ለመመስረት የሚያስችል ጥናት በተለያየ ሙያና ልምድ ባላቸው የሰ/ት/ቤት ልጆች የሆኑ ምሁራን ከአንድ ዓመት በላይ ተጠንቶ ከተዘጋጀ በኋላ ለቋሚ ሲኖዶስ ቀርቦ ታርሞ ከተስተካከለ በኋላ ወደ ምልዓተ ጉባኤ ቀርቦ ጸድቋል፡፡ መምሪያው በሀገር አቀፍ ደረጃ ይኸው አደረጃጀት ተግባራዊ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ መሠረትም በሁሉም አኅጉረ ስብከቶች ዘንድ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ተመስርቶ አገልግሎቱ ተጀምሯል፡፡

አወቃቀሩንም በተመለከተ የቤተ ክርስቲያን ነባር መዋቅርን ተከትሎ የተደራጀ እንጂ አዲስ ወይም ከቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውጭ ሆኖ ራሱን ችሎ የተነጠለ መዋቅር አይደለም፡፡ ዓላማውም ይኸው በቤተ ክርስቲያኗ የቆየው የሰ/ት/ቤት ክፍል መዋቅር በበጎ አድራጎት የሚያገለግሉ የሰ/ት/ቤት ምሁራንን ጨምሮ የበለጠ በማጠናከር ለውጥ ሊያመጣ በሚያስችል መልኩ እንዲንቀሳቀስ፣ እንዲመራና እንዲያስተባብር ማድረግ እንጂ ከነባር መዋቅር መነጠል አይደለም፡፡ ስለዚህ የተነጠለ ራሱን የቻለ አዲስ መዋቅር የለንም፡፡ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት የምናደራጀው ያለው መዋቅር ተጠቅመን ነው፡፡ የወረዳ ቤተ ክህነት አቀፍ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ሰብሳቢውም ሆነ ተጠሪነቱ ለወረዳው ቤተ ክህነት ሰ/ት/ቤት ክፍል ነው፣ የሀገረ ስብከት ቤተ ክህነት አቀፍ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ሰብሳቢውም ሆነ ተጠሪነቱ ለሀገረ ስብከቱ ቤተ ክህነት ሰ/ት/ቤት ዋና ክፍል ነው፤ የሀገር አቀፍ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ሰብሳቢውም ሆነ ተጠሪነቱ ለሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ነው፡፡

ይኸው አደረጃጀት የሚሰጠው ጥቅም ሰ/ት/ቤቶች ያበረክቱት የነበረው የተናጠል አገልግሎት የሕብረት፣ የአንድነት ሆኖ ይበልጥ የሰመረና የተሻለ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ሰ/ት/ቤቶች ይህንን አንድነት ተጠቅመው ልምድ በመለዋወጥ፣ ችግሮችን በመፍታት፣ ማኅበራዊ የበጎ አድራጎት አገልግሎትን የበለጠ በማስፋፋት በሁሉም ሰ/ት/ቤቶች ዘንድ ተደራሽና ወጥ የሆነ ሥርዓተ አገልግሎት እንዲኖር በማድረግ በኩል ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ ፍሬውም ይኸው በመታየት ላይ ይገኛል፡፡ አጠቃልሎ ሲገለጽ ይኸው አደረጃጀት ሁሉም ሰ/ት/ቤቶች በኔትዎርክ ትስስር ፈጥረው ያላቸው ችግር ለመፍታት፣ ልምዳቸውን ለመለዋወጥ ስለቀጣይ አገልግሎታቸው ለመምከር... ወዘተ ከፍተኛ ጥቅም ይኖረዋል ብለን እናምናለን፡፡

ጥያቄ በዝግጅት ክፍሉ፡-

ከዚህ ጎን ለጎን አዲስ የውስጥ መመሪያ ተዘጋጅቶ ጸድቋል፡፡ የውስጥ መመሪያው አገልግሎት ምንድን ነው መሠረቱስ ምንድ ነው?

መልስ በብፁዕ አባታችን፡-

ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት አዲሱ አደረጃጀት ከላይ ከመንበረ ፓትርያርክ ጀምሮ እስከ ወረዳ ቤተ ክህነት ድረስ የሚዘረጋ ብዙኃን የሰ/ት/ቤት አመራሮችን ያቀፈ አደረጃጀት ነው፡፡ ስለሆነም ይህንን አደረጃጀት ለመምራት የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ ይህንን የውስጥ መመሪያ በባለሙያዎች ተጠንቶ ከተዘጋጀ በኋላ በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቋል፡፡ ይህንን የውስጥ መመሪያ አዲስ የተቀረጸ ሳይሆን በ1986 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ ለማደራጃ መምሪያ ከተሰጠው ዋና ደንብ የተቀዳ ወይም የተወሰደ ነው፡፡ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ደንብ ምዕራፍ ሦስት ቁጥር 17 ከሀ-ረ ተዘርዝሮ በቅዱስ ሲኖዶስ በተሰጠው ፈቃድ የሰ/ት/ቤቶችን ሁለገብ አገልግሎት ይበልጥ እንዲጠናከርና በሁሉም ዘንድ ተደራሽ አገልግሎት እንዲኖር ለማድረግ የሚያስችል ኃላፊነት አለው፡፡

ይኸው ኃላፊነት መሠረት በማድረግ አደረጃጀቱን ካጠና በኋላ አደረጃጀቱን በሕግ አግባብ ሊመራበት የሚያስችል ደግሞ የውስጥ መመሪያ አዘጋጅቶ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡ እዚህ ላይ አጽንኦት መስጠት የምፈልገው ነገር ቢኖር የውስጥ መመሪያው ከዋናው የማደራጃ መምሪያ ውስጠ ደንብ የተወለደ፣ ሕጋዊ አካሄድን የተከተለ እንጂ አሁን እንደ አዲስ የተረቀቀ መመሪያ አለመሆኑን ነው፡፡ የዚህ ውስጠ ደንብ ይዘት በየደረጃው የሚገኙ አደረጃጀቶች ኃላፊነታቸውንና ተግባራቸው ስፍሮ፣ ቆጥሮ፣ ለክቶ፣ መዝኖ ... የሚመራ ከቤተ ክርስቲያኒቷ ሕጎች ጋር ቅራኔ የሌለው ይልቁንም ከሕገ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ ከቃለ አዋዲው ጋራ በመስማማት የወጣቶች አገልግሎት የሰመረ እንዲሆን የሚያደርግ የተጠና መመሪያ ነው፡፡

ጥያቄ በዝግጅት ክፍሉ፡-

የማደራጃ መምሪያው መሪ ዕቅድና የሚያስገኘው ጠቀሜታ በሚመለከት ቢገልጹልን?

መልስ በብፁዕ አባታችን፡-

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ዘመኑን ዋጁ ብሎ እንደተናገረው ዘመኑን ተከትለን ዘመን በሚፈቅደው የአሠራር አካሄድ መከተል ብልህነት ይመስለኛል፡፡ ሁሉም እንደሚገነዘበው ያለዕቅድ የሚሠራ ሥራ ውጤታማ አይሆንም ማለት ባይቻልም ግን በዕቅድ እንደሚሠራ ግን ውጤታማ እንደማይሆን ግልጽ ነው፡፡ በዕቅድ የሚሠራ ሥራ በጊዜ፣ በቦታ፣ በሁኔታ... ወዘተ ተገድቦ፣ ተሰፍሮ፣ ተቆጥሮና ተመዝኖ የሚከናወን በመሆኑ ውጤቱም የዚያን ያህል አስደሳችና ዘመኑ የሚፈቅደውም ጭምር ነው፡፡ ይህ መምሪያም ደግሞ የወጣቶች መምሪያ እንደመሆኑ መጠን ወጣቶቹ በዘመናዊም ሆነ በመንፈሳዊ ትምህርት እጅግ የበሰሉ ምሁራን ናቸው፡፡ ታድያ ይኼ የተማረ፣ ሀገርንና ቤተ ክርስቲያንን ለመለወጥ የሚያስችል ዕውቀት ያካበተ ወጣት ዘመኑን በሚፈቅደው መልኩ የተለካና የተሰፈረ አገልግሎት ስታዘጋጅለት ከነበረው ይበልጥ በፍቅር ያገለግላል፣ አገልግሎቱንም ይለካል፣ ይገመግማል፡፡ ከዚህ በመነሳት የሰ/ት/ቤት ልጆች የሆኑ ምሁራን ባለሙያዎች ከአንድ ዓመት በላይ የፈጀ ጥናት በማድረግ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ በማውረድና በመሪ ዕቅዱ ላይ በመወያየት በጠቅላላ ጉባኤ አስተያየት ከተሰጠበት በኋላ በመምሪያው ጸድቆ ለሁሉም አኅጉረ ስብከት ተበትኖ ይኸው አንድ ብለን መተግበር ጀምረናል፡፡
የመሪ ዕቅድ ጠቀሜታ ብዙ ቢሆንም ከላይ እንደገለጽኩት አገልግሎታችንን እንድንሰፍር፣ እንድንለካ፣ ከየት ተነስተን የት ደረስን፣ ምን አሳካን ምን ቀረን በማለት የተሳኩ ሥራዎቻችንን አጠናክረን በመቀጠል ችግሮቻችንን ደግሞ ለይተን በማውጣት ለመፍታት የሚያስችል ዘመናዊ አካሄድ ነው፡፡ ስለሆነም መሪ ዕቅድ ሥራዎችን በመለካት የተነሳህለት ዓላማ ከግብ እንድታደርስ የሚያግዝ መልካም የሆነ የአሠራር ሂደት ነው፡፡

ጥያቄ በዝግጅት ክፍሉ፡-

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ዘንድ ወጥ የሆነ አገልግሎት እንዲኖር ለማድረግ መምሪያው ምን እየሠራ ነው?

መልስ በብፁዕ አባታችን፡-

በሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ዘንድ ተመሳሳይ የሆነ ሥርዓተ አገልግሎት እንዲኖር ማድረግ የመምሪያው አንዱ ተልዕኮና የመሪ ዕቅዱም አንድ አካል ነው፡፡ በመሆኑም ይህንን ለማሳካት የተለያዩ ጥረቶች እያደረግን እንገኛለን፡፡

በመምሪያ ደረጃ የሥርዓተ ትምህርትና የመዝሙር የአገልግሎት መጽሐፍ ቅድሚያ ሰጥተን በመንቀሳቀስ ላይ እንገኛለን፡፡ በማዕከል ደረጃ ወጥ የሆነ ሥርዓተ ትምህርትና ሥርዓተ መዝሙር ተዘጋጅቶ በሁሉም ሰ/ት/ቤቶች ዘንድ ተግባራዊ ለማድረግ በሊቃውንት ጉባኤ ተመርምሮና ተስተካክሎ ለሕትመት የተዘጋጀ አለ፡፡ በመሆኑም ይህንን ለሕትመት አብቅቶ ለማሰራጨት መምሪያው በጀት ስለሌለው የሰ/ትቤት አመራር ወጣቶችን ኮሚቴ አቋቁሞ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ ኮሚቴው ከተለያዩ በጎ አድራጊ ምዕመናንና ባለሃብቶች ገንዘብ በማሰባሰብ ሥርዓተ ትምህርቱም ሆነ መዝሙሩ ለሕትመት እንዲበቃ የሚያደርግ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚም ይህንን ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለሀገር የሚጠቅም ተልዕኮ የቤተ ክርስቲያናችን ልጆች ሁላችሁም እንደየአቅማችሁና እንደየችሎታችሁ የዚህ መልካም ሥራ አጋዥና ተባባሪ እንድትሆኑና መጽሐፉ ታትሞ ለሁሉም እንዲዳረስ እንድታደርጉ መንፈሳዊ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡

ጥያቄ በብፁዕ አባታችን፡-

ለወደፊትስ በሰ/ት/ቤቶች ዘንድ የሚታዩ ችግሮች በዘላቂነት እንዲፈቱ ለማድረግ ምን የታቀደ ነበር አለ?

መልስ በብፁዕ አባባታችን፡-

በዋናነት የሰ/ት/ቤቶችን ችግር በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው አሁን የተጀመረው አደረጃጀት የበለጠ በማጠናከርና በአግባቡ በመከታተል ነው ብለን እናምናለን፡፡ ምክንያቱም ይህን አደረጃጀት ሀገር አቀፍ ግንኙነትን በማዳበር መረጃን በመለዋወጥ ችግሮች በዘላቂነት እንዲፈቱ የሚያስችል ሁነኛ ዘይቤ ስለሆነ ነው፡፡ ወጣቶች ይህን አደረጃጀት ተጠቅመው በወረዳ፣ በሀገረ ስብከት ደረጃና በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ችግሮች ምንነት አጥንተው በመንስኤዎቻቸውና በመፍትሔዎቻቸው ዙርያ በጋራ መክረው በአንድነት ከተንቀሳቀሱ ዘላቂ የሆነ መፍትሔ፣ የተስተካከለ መልካም የሆነ አገልግሎት የማይሰፍንበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያ አቅጣጫችን አደረጃጀቱን እስከታች ድረስ ማለትም በሁሉም አኅጉረ ስብከትና ወረዳዎች ማደራጀትና ማጠናከር ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ የሚፈጠሩ አላስፈላጊ ጥቃቅን ችግሮች ለመፍታት ሀገር አቀፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ /የስልጠና/ መርሐ ግብሮችን አዘጋጅተን ተግባራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡

ጥያቄ በዝግጅት ክፍሉ፡-

በመጨረሻ ለማስተላለፍ የሚፈልጉት መልእክት ካለ?

መልስ በብፁዕ አባታችን፡-

የሰንበት ት/ቤቶች አገልግሎት የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ነው፡፡ መንፈሳዊ ወጣቶች ደከመን ሰለቸን ሳይሉ በፍጹም ፍቅር ቤተ ክርስቲያናቸውን ያገለግላሉ፡፡ ይኸው መልካም አገልግሎታቸውም የቤተ ክርስቲያኒቱ ሐዋርያዊ አገልግሎት ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡ ይህን የተናጠል አገልግሎት ደግሞ በአንድነት ብናስተሳስረው የቱን ያህል ሊደምቅና በሁሉም ዘንድ ተደራሽ ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ይቻላል፡፡ ስለዚህ ሁሉንም የሰ/ት/ቤት ወጣቶች የዚህ አደረጃጀት አካል በመሆን ቅዱስ ሲኖዶስ ባጸደቀላቸው መመሪያ መሠረት ሕጉንና ሥርዓቱን ተከትለው አገልግሎታቸውን የበለጠ እንዲያጠናክሩ አደራ እያልኩ በውጪው ክፍለ ዓለም የሚገኙ የሰ/ት/ቤት ወጣቶቻችንም አሐቲ ቤተ ክርስቲያን ስለሆነች በዚህ አደረጃጀት ውስጥ ገብተው ከማደራጃ መምሪያው ጋር ግንኙነት ፈጥረው በኢትዮጵያ ከሚገኙ ሰ/ት/ቤቶች ትስስር ፈጥረው አባቶቻችን በጊዜያቸው ታሪክ ሰርተው እንዳለፉ እኛም እግዚአብሔር በሰጠን ጊዜ ተጠቅመን ተከባብረን፣ ተደማምጠን፣ ተናብበን በፍቅርና በሰላም አንድ ሆነን ቤተ ክርሰቲያናችንን እንድናገለግል የአደራ መልእክቴን አስትላልፋለሁ፡፡

ምስጋና በዝግጅት ክፍሉ፡-

ብፁዕ አባታችን እግዚአብሔር ይስጥልን፤ የአገልግሎት ዘመንዎን ያቃናልዎ!

መልስ በብፁዕ አባታችን፡-

ልዑል እግዚአብሔር ይባርካችሁ ሥራችሁን የተቃና ያድርግላችሁ!


ወስብሐት ለእግዚአብሔ!

የፎንት ልክ መቀየሪያ