Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

“ከሰንበት ትምህርት ቤት አገልጋዮች ምን ይጠበቃል?”

የጥናታዊ ጽሁፍ ዓላማ፡-

የሰንበት ትምህርት ቤት አገልጋዮች በቤተክርስቲያንም ሆነ በቤተሰብ ውስጥ ምሳሌነት ያለውን ሕይወት እየመሩ በማስተዋል ማገልገል እንዳለባቸው መጠቆም፡፡

1.    አገልግሎት ምንድነው?

“አገልግሎት” የሚለውን ቃል ሰዎች ለእግዚአብሔር ወይም ለሰው የሚሰሩት ሥራ ነው በማለት ልንተረጉመው እንችላለን፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ ያለው አገልግሎት ደግሞ ከዚህ ትርጉም በተጨማሪ “አምልኮት ነው” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ልጆች በአገልግሎታቸው ለአምላካቸው ክብርና ምስጋና ይሰጣሉ፣ ተገዢነታቸውን ያሳያሉ ብሎም ልጅነታቸውን ያረጋግጣሉ፡፡
ክርስቲያኖች በአምላካቸው ስም ተጠርተው እርሱን የሚያመልኩ ናቸውና የተጠሩት ለአገልግሎት ጭምር ነው ማለት እንችላለን፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱን መከተል ለማገልገል እንደሆነ “የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ” በማለት ተናግሯል /ዮሐ. 12.26/፡፡ አዎን በዘመነ ብሉይም እግዚአብሔር ፈርዖንን “እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ” ማለቱ በሕዝቡ ይገለገል ዘንድ እንደሚወድ ገልጿል /ዘጸ. 7.16/፡፡ ይህ ጥሪ በሐዲስ ኪዳን “የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌን ትቶላችሁ ስለእናንተ መከራን ተቀብሎአልና” ተብሎ ተገልጿል፡፡ /1ጴጥ.2.21/ እንዲህ ጌታ እንድንከተለው የተወልን ምሳሌ “የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሠጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” የሚል ነው /ማር.10.45/ ጌታችን ይህንን ቃል ብዙዎችን ከህመማቸው በመፈወስ፣ ድካማቸውን በማገዝ፣ እዳቸውን ቤዛ ሆኖ በመክፈልና እግራቸውን በማጠብ አሳይቷል፡፡ ስለዚህ የጌታችን ፈለግ ሊከተል የሚፈልግ አገልጋይ ቢኖር ያገለገለውን ጌታን ሊያገለግል፣ የሌሎችን እግር ለማጠብ ውሃና ማበሻ ጨርቅ ይዞ ሊያደገድግ ይገባዋል፡፡

የአገልግሎት አይነቶች

ቤተክርስቲያን ያሉትን የአገልግሎት አይነቶች በአራት ዋና ዋና ክፍሎች ልንከፍላቸው እንችላለን፡፡
1.    የልጅነት አገልግሎት፡- ይህ አገልግሎት ከአምላካችን በጥምቀት የተወለድን እኛ ልጆቹ የልጅነት ስሜት እየተሰማን ግዴታችንን በመወጣት የምናገለግለው አገልግሎት ነው፡፡ የልጅነት አገልግሎት ከቅጥረኝነት አገልግሎት እጅጉን ይለያልና ለአገልግሎታችን ተመጣጣኝ ክፍያ ሳንጠይቅ፣ ጉልበታችንንና ጊዜያችንን ሳንቆጥብ በፍቅር የምንገልጸው የአገልግሎት ዓይነት ነው፡፡ ጌታችን በልጅነቱ ለእናቱ ለድንግል ማርያምና ለአሳዳጊው ለዮሴፍ በመታዘዝ የልጅነት አገልግሎት አርአያ ሆኖናል /ሉቃ.2.51/ እንግዲህ የእግዚአብሔር ልጆች እንደሆንን የምናስብ አገልጋዮች ልጆች በመሆናችን የሰማያዊው ርስት ተካፋዮች የመሆን ተስፋ እንዳለን በማስተዋል አባታችን የሚያስተምረንን ሁሉ ከቅጣትም ጋር ቢሆን እየተማርን በፍቅር ልናገለግለው ይገባል /ሮሜ.8.17፣ ዕብ.12.7-11/
2.    የፍቅር አገልግሎት፡- ይህ አገልግሎት በልጅነት አገልግሎችን ላይ የምንጨምረው ከበጎ ፈቃድ የሚመነጭ አገልግሎት ነው፡፡ ፍቅራችን አገብሮን ለአገልግሎቱ የጉልበት፣ የአሳብና የገንዘብ ስጦታን  እናበረክታለን፡፡ “በበረከት የሚዘራ በሃብት ደግሞ ያጭዳል” የሚለውን ቃል በማሰብ የምናበረክተውን ማንኛውንም አይነት ስጦታ /አስተዋጽኦ/ በደስታ እንሰጣለን፡፡ በፈሪሳዊው በስምዖን ቤት ጌታን ከመውደድ የተነሳ አገልግሎቷን እግሩ ላይ የፈጸመችው ኃጢአተኛይቱ ሴት የፍቅር አገልጋይ ምሳሌ ናት፡፡ /ሉቃ.7.36-50/
3.    የባርነት አገልግሎት፡- ይህ አገልግሎት አይነት ከልጅነት አገልግሎት ጋር የሚቃረን ሳይሆን ለጌታ ያለንን ተገዢነት የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ አገልግሎት ከላይ ባየናቸው የአገልግሎት አይነቶቹ ካለመርካት የተነሳ የሚጨመር ነው፡፡ በብህትውና /በምንኩስና/ ራስን ለዓለም ገድሎና ለመንግሥተ ሰማያት ጃንደረባ አድርጎ ሰማያዊውን ክብር በማሰብ ብቻ ይገለጻል፡፡ ስሙን የባርነት ያልነው አገልጋዩ ያለውን ንብረት ሁሉ ለአገልግሎት ስለሚያውልና ራሱን እንኳን ለጌታው ስለሚሰጥ ነው፡፡ ሐዋርያው “የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች እንጂ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ አትሁኑ” በማለት ያስተላለፈው መልዕክት ይህን የአገልግሎት አይነት ያመለክታል፡፡
4.    የሹመት /የሥልጣን/ አገልግሎት፡- ቃሉ እንደሚያስረዳን ይህ አይነቱ አገልግሎት ሹመትን ወይም ስልጣንን በመቀበልና ኃላፊነትን በመወጣት የሚገለጽ ነው፡፡ የክህነት አገልግሎትና በቤተክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ባሉ ልዩ ልዩ ክፍሎች ሥራን በመምራትና በኃላፊነት የምናገለግለው አገልግሎት ለዚህ ምሳሌ ይሆናል፡፡ ይህ አገልግሎት የጠባቂነት (ዮሐ.21.5) የመጋቢነትና /1ቆሮ. 4.1/ የእረኝነት /ኤፌ. 4.11/ ነውና ሌሎች ወገኖች ለዚህ አገልግሎት ለተመረጡት ሊገዙ ይገባል፡፡ /ዮሐ.6.70/

የአገልግሎት ፍሬያት፡-

በቤተክርስቲያን ውስጥ ያለው አገልግሎታችን ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ማደግ ታላቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ስለሆነም በቤቱ ሰማያዊ አባታችንን በማገልገላችን፡-
1.    የልጅነት ስሜት ይሰማናል፡- ጌታ “በአባቴ ቤት እኖር ዘንድ እንዲገባኝ አታውቁምን” (ሉቃ. 2.49-51) እንዳለ ለቤቱ ደፋ ቀና ስንል ልጆቹ እናስባለን፡፡ አምላካችን  “ባሮች” ሳይሆን “ወዳጆች” በማለትም ጠርቶናልና፡፡ ለእርሱ ያለን ቀረቤታ በውስጥ ይሰማናል (ዮሐ. 15.15) “ሁላችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ” እንደተባለ ሕብረት ያለን፣ ቤታችን በሰማይ የሆነልን የርስቱ ወራሾች እንደሆንን ስለምንገነዘብ በአገልግሎታችን ደስ ይለናል፡፡ (ገላ.3.26) መከራና ፈተና ቢያጋጥመንም እንኳ ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ አውቀን ከቅድስናው እንድንካፈል በሚቀጣን ጌታ ደስ እየተሰኘን ተግሳጹን በፍቅር እንቀበላለን፡፡
2.    የመንፈስ ፍሬያትን ያበዛልና፡- አንድ አገልጋይ ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ሕይወት ከሌለው ከቶ ሊያገለግል አይችልምና አገልግሎቱ በሥነ ምግባራት የታነጸ እንዲሆንና ጌታን የመሰለ ሕይወት እንዲኖረው ግድ ይለዋል፡፡ በመሆኑም ለአገልግሎት አስፈላጊ የሆኑትን፡-

 • ፍቅርን (ገላ 5.13) “በፍቅር እርስ በእርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ”
 • ትህትናን (የሐዋ 20.19) “በትህትናና በእንባ እንደኖርኩ ታውቃላችሁ”
 • ፍርሃትን (መዝ.2.11) “በፍርሐት ለእግዚአብሔር ተገዙ”
 • ትዕቢትን ማራቅ (መዝ.100.7 ) “ትዕቢትን የሚያደርግ በቤቴ አይኖርም”
 • ቅድስናን (ዕብ.12.14) “ትቀደሱ ዘንድ ፈልጉ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና”
 • ምሳሌነትን (1ጢሞ.4.12) “በቃል፣ በኑሮ ምሳሌ ሁኑ” እና በአጠቃላይ የሕይወት ለውጥን ገንዘብ እናደርጋለን (ሮሜ.7.6)፡፡

3.    ሽልማት፡- ሐዋርያው “እግዚአብሔር ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉዋቸው ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ እግዚአብሔር አመጸኛ አይደለም” እንዳለ ጌታን በመከተል የተደረገ እውነተኛ አገልግሎት ለሰማያዊ ክብር ያበቃል (ዕብ.6.10) መገለጡን በመውደድ አገልግሎታልና ቅዱስ ጳውሎስ የጠበቀልን አይነት ሰማያዊ አክሊል ያስገኛል (2ጢሞ.4.8) እንዲሁም በአገልግሎት አምላካቸውን ደስ ያሰኙ አገልጋዮች “የሚያገለግለኝ ቢኖር አብ ያከብረዋል” የሚለው የጌታ ቃል ይፈጸምላቸዋል ሮሜ.14.18፣ ዮሐ.12.26
2.    እንዴት እናገልግል?
አገልጋዮች ጌታ በሚገለገልበት በቤቱ አገልግሎትን ከመጀመራቸው በፊት የሚያገለግሉት ጌታ ማን መሆኑን ሊያውቁት ይገባል (ቈላ.3.23-24)፡፡ ይህን ከተረዱና በወንጌል የታገዘ አገልግሎትን ለማገልገል ከተዘጋጁ ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚያስተምሩን በአገልግሎታቸው ምክንያት ራሳቸውን ሳያስታብዩ፡-

 • “የማንጠቅም ባሪያዎች ነን ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል” (ሉቃ.17.10)
 • “አገልግሎታችን ጌታ በሚሰጠን ኃይል ነው” (1ጴጥ.4.11)
 • “ሥራውን የሰራው ከእኛ ጋር ያለ የእግዚአብሔር ፀጋ ነው”(1ቆሮ.15.10) ሊሉ ይገባል፡፡

ከዚህ ጋር ለአገልግሎት ሲሰለፉ ነውረኛ ቃላትን ሳይመላለሱ ንግግራቸውን በጨው እንደተቀመመ በፀጋ እያደረጉ በፍቅር እየተነጋገሩና በአገልግሎት ሲደክሙ ለመልካም ሥራና ለፍቅር ይነቃቁ ዘንድ በቃሉ እየተያዩ በአጠቃላይ በቃልና በኑሮ ምሳሌ የሆነ ሕይወትን በመምራት ሊያገለግሉ ይገባል (ዕብ.10.24)፣ (ቈላ.4.6)፡፡ ለአገልግሎት በቤቱ እየተመላለሱ ከአማንያን አንዱን ብናሰናክል የባሰ ፍርድ እንደምንቀበል ተነግሮናልና በአገልግሎታችን ቀጥለው የተዘረዘሩትን ጥንቃቄዎች ልናደርግ ይገባል፡፡ (ማቴ.18.6) (ቈላ.4.17)/
1.    ሳይባክኑ ማገልገል፡- አገልጋዮች ብዙውን ጊዜ ሙሉ ሐሳባቸውን፣ ጉልበታቸውንና ትኩረታቸውን አገልግሎት ላይ ስለሚያውሉ የራሳቸውን ሕይወት ይዘነጋሉ፡፡ አገልግሎቱ ጸሎትና ንስሐ የሚሆናችው ይመስል በጸሎታቸው የተዘናጉና ንስሐ መግባትን የረሱ ይሆናሉ፡፡ ይህ ደግሞ በውስጥ ባዶነት እንዲሰማቸውና በአገልግሎቱ እንደሰለቹ ስለሚያደርግ በልዩ ስሜት የጀመሩት አገልግሎት ብዙም ሳይቆይ ይቆማል፡፡ ስለዚህ ሳንባክን የራሳችንን ሕይወት እየመረመርን በጥበብና በጥንቃቄ ማገልገል ይኖርብናል፡፡ (2ቆሮ.13.5)
2.    ቅድስናን መያዝ፡- አገልጋዮች ቅዱስ አግዚአብሔን የሚያገለግሉ ናቸውና ራሳቸውን ለአምላካቸው መቀደስ ይኖርባቸዋል (1ዜና.29.5)፡፡ እግዚአብሔርን ስናገለግለው እርሱ ይከብርበት ዘንድ የእኛን መቀደስ ይፈልጋልና አገልጋዮች ሕሊናን ከሚያዋርድ፣ ሰውነትን ከሚያረክስና አካልን ከሚያሳድፍ ኃጢአትን ተጠብቀውና የሥጋ ፍሬያትን አርቀው በንጽሕናና በቅድስና ማገልገል ይኖርባቸዋል፡፡ (ዘሌ.11.45 ፣ 19.2) ፣ (ዕብ.12.4) (መዝ.49.16)
3.    አገልግሎትን ማክበር፡- አገልጋዮች አገልግሎታቸው የሚያሰጣቸውን ሰማያዊ ክብር ከተረዱ በአገልግሎታቸው ቸልተኝነትንና መሰላቸትን ማራቅ ይኖርባቸዋል፡፡ በሥጋ ድካም ወይም በዓለማዊ ጉዳዮች ተጣቦ ለአገልግሎት ሊሰጡ የሚገባውን ቦታ መንፈግ ለአገልግሎታችን ያለንን ቅንአት ሊያጠፋብን ስለሚችል እኛ አገልጋዮች ከአገልግሎታችን በፊት ስለ እርሱ መፀለይ፣ የሚጠበቅብንን ሁሉ ማድረግና ለአገልግሎቱ መሳካት መወያየትን ማሰብ ያስፈልገናል፡፡ ለዚህ ነበር ሕዝቅያስ “አገልጋዮቹ ትሆኑ ዘንድ እግዚአብሔር መርጧችኋልና ችላ አትበሉ” ያለው (2ዜና.29.11) ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ አክሪጳ “በጌታ የተቀበልክውን አገልግሎት ትፈጽም ዘንድ ተጠንቀቅ” በማለት ያስጠነቀቀው (ቈላ.4.17) “የእግዚአብሔር ሥራ በቸልታ የሚያደርግ ርጉም ይሁን” /ኤር.18.10/
4.    ትህትናን ገንዘብ ማድረግ፡- አገልጋይ የጌታው ባሪያ ነውና ከእግዚአብሔር ጸጋ  የተነሳ ሞገስ ይበዛለት ዘንድ በአገልግሎቱ ቀዳሚ ስፍራ ቢሰጠውም ሌሎች ፊት በትህትና የሚያጎነብስ ሊሆን ይገባዋል፡፡ የአምላኩን ፈለግ የተከተለ አገልጋይ ሌላው ከእርሱ የተሻለ እንደሆነ ያስባል (ፊል.2.34)፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን እንደሚያዋርድ፣ ለትሁታን ግን ጸጋን እንደሚሰጥ ተረድተው የሁሉ ታዛዥ ይሆኑ ዘንድ ከእውነተኛ አገልጋዮች የሚጠበቅ ተቀዳሚ ተግባር ነው፡፡
5.    ፍቅርን መከታተል፡- ስለ ፍቅር ማገልገል እየገነቡ ማፍረስ ነውና መጽሐፍ ቅዱስ የላቀ ቦታ የሚሰጠው ፍቅር በአገልጋዮች ሕይወት ታላቅ ቦታ ሊኖረው ይገባል፡፡ አገልግሎት በፍቅር ከታጀበ ሕዝብ የሚድንበትና በረከት የሚወርስበት ቤተክርስቲያን የምትጠቀምበት ይሆናል፡፡ ስለዚህ በአገልግሎት መሃል መጋጨት ቢኖርም እንኳ እግዚአብሔር በክርስቶስ ይቅር እንዳለ ይቅር በመባባል ክፉን እናርቅ ዘንድ ፍቅርን መከታተል ይኖርብናል፡፡ (ሮሜ.10.10)፣ (ቈላ.3.14)፣ (ኤፌ.4.32)
6.    በእምነት መጽናት፡- አገልጋዮች የተሳካ አገልግሎት ሊያገለግሉ የሚችሉት እንደ ነህምያ “የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፡፡ እኛም ባሪያዎች ተነስተን እንሰራለን” የሚሉ የእምነት ሰዎች ሲሆኑ ነው /ነህ.1.20/፡፡ ገበሬ የዘሩን ፍሬ እንደሚጠብቅ አገልጋዮችም እግዚአብሔር በአገልግሎት የዘሩትን ዘር ለፍሬ እንደሚያበቃ የሚያምን እምነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከዘመኑ ኑፋቄ ርቀው በአካሄዳቸውና በአነጋገራቸው ኦርቶዶክሳዊነታቸውን ያስመሰክሩ ዘንድ ከአገልጋዮች በእጅጉ ይጠበቃል፡፡ በራሳቸው ምንም ማድረግ እንደማይችል ተነግሮዋቸዋልና፡፡ አገልጋዮች የራሳቸውን ፈቃድ ከማስቀደም ይልቅ ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም ይህንንና ያንን እናደርጋለን የሚለውን የእምነት ቋንቋ ሊናገሩ ይገባል፡፡ /ዮሐ.15.15፣ ያዕ.45.15/
4.    ታማኝነት፡- አገልጋዮች በአገልግሎታቸው ሊጠነቀቁለት ከሚገባ ቁም ነገር አንዱ ታማኝነት ነው፡፡ ጌታ ራሱ በጥቂቱ የታመነውን አገልጋይ በብዙ እንደሚሾመው ተናግሯል፡፡ ስለሆነም አገልጋዮች በተሰጣቸው መክሊት በማትረፍና ከጥቂት ኃጢአት በመጠበቅ፣ በመከራ በመታገስና፣ በመከራ በመጽናት ታማኝነታቸውን ማሳየት ይኖርባቸዋል፡፡ እውነተኛ አገልጋይ የቤርሳቤህ ውበት ሳይማርከው፣ የጲጥፋራ ሚስት ማባበል ሳይሸነግለው፣ የደሊላ ተንኮል ወጥመድ ሳይሆንበት፣ የይሁዳ ገንዘብ ሳያጓጓው፣ የተሰሎንቄ ከተማ ሳያስቀረው የጌታውን ተልዕኮ መወጣት አለበት፡፡ “ታምነህ ተሰማራ” እንደተባለም የሕይወት አክሊልን ይቀበል ዘንድ እስከ ሞት ድረስ ለአምላኩ ይታመን፡፡ /መዝ.36.6፣ ራዕ.2.10/
5.    አርአያነት፡- ሐዋርያው ጳውሎስ ልጁ ጢሞቴዎስን በእምነትና በንጽህና በፍቅርም ለሚያምኑት ሁሉ ምሳሌ ሁን እንዳለው አርአያነት ከአገልጋዮች በእጅጉ ይጠበቃል፡፡ (1ጢሞ. 4.12) እንግዲህ አገልጋዮች ራሳቸውን ምሳሌ አድርገው ያቀረቡና አገልግሎታቸው እንዳይደናቀፍ ከቶ ማሰናከያ ያልሰጡ መሆን ይኖርባቸዋል (2ቆሮ.6.3)፡፡ ይህንንም በፍቅርና በእምነት፣ በፆምና በጸሎት፣ በጽድቅና በበጎ ነገር ተቀዳሚውን ሥፍራ በመያዝ ማሳየት ያስፈልጋቸዋል፡፡
3.    አገልጋይ ምን ይምሰል፡-
ከላይ በአጠቃላይ አገልጋዮች እንዴት ማገልገል እንዳለባቸው ተመልክተናል፡፡ አሁን ደግሞ አንድ አገልጋይ በግል ሕይወቱ ፣ በቤተሰቡ ወይም በማኅበረሰቡ ዘንድ እንዴት መመላለስ እንደሚገባውና ሊይዛቸው ወይም ሊያስወግዳቸው የሚገቡ ነገሮች ምን እንደሆኑ ለማየት እንሞክራለን፡፡
በግል ሕይወቱ፡- አንድ አገልጋይ ጥሩ መንፈሳዊ ሕይወትን መምራት ከቻለ የሰማያዊውን ሕይወት በምድር ላይ የተለማመደ ብቻ ሳይሆን ራሱን በሥነ ምግባር ያነጸ ምርጥ ዜጋም ይሆናል፡፡ ስለሆነም በቤትና በትምህርት ቤትም ሆነ በሥራ ቦታ ለቀረቡት ሁሉ በማንነቱ ክርስቶስን ያሳያል፡፡ በአነጋገሩ፣ በአመለካከቱና በአካሄዱ አምላኩን ይሰብካል፡፡ እንዲህ አይነቱ አገልጋይ በኑሮው በማይመች አካሄድ ያልተጠመደ፣ ክፉ ባልንጀርነትን ያራቀና የዋዘኞችን መንገድ /መንበር/ የናቀ ነው፡፡
አምላኩን በሕይወቱ ያነገሰ በመሆኑ ባይናገርም ለሚያስተውሉት ሁሉ በዝምታ ስብከትን ይሰብካል፡፡ እውነተኛ አገልጋይ መንፈሳዊነቱ በቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን በየትም ቦታ ነው፡፡ /ምሳሌ፡- በዘመናዊ ትምህርትና በሥራ ቦታ/ በአምላኩ ቤት የተማረውን ሕይወት በሄደበት ቦታ ሁሉ ያንጸባርቃል፡፡ ክርስቶስ የሞተለትን ወንድም ላለማሰናከልም ስለሚጠነቀቅ በፍቅር በእምነትና በንጽህና ለሌሎች ምሳሌ ይሆናል እንጂ ማንንም አያሰናክልም /ሮሜ. 14.15 ፣ 1ጢሞ. 4.12/፡፡ ለራሱ ሕይወት መታነጽም ቃሉ ዘወትር የሚያነብና የወንጌልን ትምህርት ለማዳመጥ የታገሰ ነው፡፡
በአገልግሎት፡- አንድ እውነተኛ አገልጋይ ሥራውን ሁሉ በጸሎት እያስቀደመ ለአገልግሎቱ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋል፡፡ ስለሆነም ከሌሎች ጋር አብሮ ሲያገለግል፡-

 • ለራሱና ለመንጋው ይጨነቃል፡፡ የሐዋ.20.23
 • ልበ ሰፊ በመሆን ዕለት ዕለት ቅዱሳን መጻሕፍትን ይመረምራል፡፡ የሐዋ.17.11
 • የሚሰራውን ሁሉ በፍቅር ይሰራል፡፡ 1ቆሮ. 16.14
 • ለመስማት የፈጠነ ለመናገር ግን የዘገየ ይሆናል፡፡ ያዕ. 1.19
 • ከሌሎች አገልጋዮች ጋር በአንድ አሳብ ይስማማል፡፡ ፊል.2.2 ፣ ሮሜ 12.16
 • እኔ ዝቅ ልል ጌታ ሊልቅ ይገባል ይላል፡፡ ዮሐ. 3.30
 • የሚከብድበት የአብያተ ክረስቲያናት ነገር ይሆናል፡፡ 2ቆሮ.11.28
 • ከሌሎች ጋር ይተያያል፣ በቃሉ ይመካከራል፣ ዕብ. 10.24
 • ክፉ ነገር ሁሉ በበጎ ሕሊና ያሳልፋል፡፡ 1ጴጥ. 3.16

ከዚህ በተጨማሪም የሚከተሉን አላስፈላጊ ነገሮች ከአገልግሎ ያርቃል፤

ከራስ በሆነ ጥበብና ችሎታ ማገልገልን
የራስ ክብርን መፈልግን
የራስ ሕይወትና አገልግሎት ከሌሎች እንደሚሻል ማሰብን
አገልግሎት ሁሉም ለአንድ ጌታ መሆኑን አለመረዳትን (1ቆሮ. 12.5)
የማይጠቅሙ ልምዶችን /የማያንጽ ተራ ንግግር፣ ሀሜት፣ ብዙ ማውራት፣ አለመታዘዝ፣ ፌዝ………./
ለእግዚአብሔር ቃል ትኩረት አለመስጠትንና በመንፈሳዊ ሕይወት መድከምን ያስወግዳል፡፡

ማጠቃለያ፤

እንግዲህ እያንዳንዱ አገልጋይ በዚህ መልኩ ራሱን ካነፀና ለአገልግሎት ካዘጋጀ በአሁኑ ወቅት በአገልግሎት ውስጥ የሚታዩ ችግሮች ይወገዳሉ፡፡ ይህም የሚሆነው አገልጋዮች የሚያገለግሉት ጌታ ክርስቶስ መሆኑን አውቀው ራሳቸውን ባዶ በማድረግ አምላካቸው ሕይወታቸውን ይቆጣጠሩ ዘንድ ሲፈቅድ በአምላካቸው ደስ ሲሰኙና በነገር ሁሉ እርሱን ማመስገንን ሲያውቁ ብቻ ነው፡፡ አገልጋዮች ራሳቸውን በመናቅ በአገልግሎት መሃል የሚደርሱትን ነቀፋዎች በደስታ ከተቀበሉ፣ በነገር ሁሉ የባልንጀራቸውን ጥቅም ካስቀደሙና ሌላው ከእነርሱ እንደሚሻል ካሰቡ አገልግሎታቸው ፍሬያማ ይሆናል፡፡ ሁሉም አንድ ጌታን እንደሚያገለግሉ ተረድተው /1ቆሮ. 12.5/ እርስ በእርስ መረዳዳትና መደጋገፍ ከቻሉ፣ እግዚአብሔርን ለመምሰል ራሳቸውን በማስለመድ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን የሚመረምሩ ከሆነና አገልግሎታቸውን በማክበር በነገር ሁሉ መልካም ማድረግ /ፊል. 2.13/ ጌታን ካስቀደሙ በአገልግሎታቸው ደስተኞች ከመሆናቸውም በላይ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር የሚከብርበትና ነፍሳት የሚድኑበት መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ አምላካችን እርሱ እንደሚወደው እናገለግለው ዘንድ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡
“አቤቱ ሥራችንን  ሁሉ ሰርተህልናልና ሰላምን ትሰጠናለህ” /ኢሳ. 26.12/
“የሰላም አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን በእናንተ እያደረገ ፈቃዱን ታደርጉ ዘንድ በመልካም ሥራ ሁሉ ፍጹማን ያድርጋችሁ፣ ለእርሱ እስከ ዘለዓለም ድረስ ክብር ይሁን” /ዕብ. 13.21/


ምንጭ፡- ፍሬ ሃይማኖት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ መንፈሳዊ ጋዜጣ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የፎንት ልክ መቀየሪያ