Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የግብጽ ኦርቶዶክ ቤተ ክርስቲያን ግንኙነት

በአባ ኃ/ማርያም መለሰ /ዶ.ር/
በኢ.ኦ.ተ.ቤ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ
ጽ/ቤት ም/ጠ/ሥ/አስኪያጅ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከውጭው ዓለም ጋር ጥንታዊና የቆየ ግንኙነት አላት ጥንታዊው ግንኙነት በአሁኑ ጊዜ ካለፈው በበለጠ እያደገና እየተስፋፋ በመሄድ ላይ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በአፍሪካ አኅጉር የሚገኙ ጥንታውያን አኃት አብያተ ክርስቲያናት ናቸው የሁለቱ ግንኙነት ሃይማኖታዊና ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ትሥሥሩ በክርስትናው በኲል ከ2ሺህ ዓመታት በላይ ሲሆን በተፈጥሮ ደግሞ ግዮን /አባይ/ መፍሰስ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡

በተለይም በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቅዱስ ፍሬምናጦስ /አባ ሰላማ/ ማዕረገ ጵጵስናን እስክንድርያ ውስጥ ከቅዱስ አትናቴዎስ ተቀብሎ ከተመለሰ በኋላ ክርስትና በይፋ የመንግሥት ሃይማኖት በመሆን በሀገራችን በስፋት ተሰበከ ሆኖም በሐዋርያት ሥራ 8÷26-40 እንደ ተመለከተው ቀደም ሲል በ34 ዓ.ም በኦሪት እምነት መሠረት ለስግደት ኢየሩሳሌም ደርሶ ሲመለስ ጋዛ አካባቢ በፊልጶስ አስተማሪነት አምኖና ተጠምቆ ወደ ሀገሩ የተመለሰው የንግሥት ሕንዳኬ ጃንደረባ /በጅሮንድ/ የክርስትናን ዜና በቤተ መንግሥትና በአካባቢው ያሰማና ያስፋፋ መሆኑ አይዘነጋም፡፡

እንደሚታወቀው የክርስትናው ዓለም በባህል በቋንቋ በአህጉር በተለያዩ ሕዝበ ክርስቲያን አንድነት ላይ የተመሠረቱ አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙበት ሰፊ ዓለም ነው፡፡ በዚህ ሰፊ ዓለም ላይ ተራርቀው በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የእርስ በርስ ትውውቅና ትብብር ሊኖር የሚችለው ዓለም አቀፍ ግንኙነት ማድረግ ሲቻል ነው፡፡ የውጭ ግንኙነት የሚባለውም ይህ ዓይነቱ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ግንኙነት የሃይማኖትና የተፈጥሮ /በኣባይ/ ነው በነዚህና በመሰሳሉት ትስስር ምክንያት ከግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር ያለን ግንኙነትም ረጅም ዘመንን ያስቆጠረ ነው፡፡

በ4ኛው መ.ክ.ዘ. ከእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ጋር የተደረገ የውጭ ግንኙነትና የኢትዮጵያ መንበረ ጵጵስና መመሥረት፣

የክርስትና እምነት ወደ ኢትዮጵያ የገባው በ34 ዓ.ም ቢሆንም ቤተ ከርስቲያኒቱ በመንበረ ጵጵስና ደረጃ ተደራጅታ ተልዕኮዋን ለማከናወን የበቃችው ግን በኋላ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው የቤተ ክርስቲያኒቱ የመጀመሪያው ጳጳስ ሆኖ የተሾመውም ጢሮሳዊው ፍሬምናጦስ ሲሆን ጊዜው በ325 ዓ.ም በኒቅያ ከተማ በተደረገው ዓለም አቀፍ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ አርዮስ ተወግዞ ከቤተ ክርስቲያን ከተለየ ከ328 ዓ.ም ቅዱስ አትናቴዎስ የእስክንድርያ ፓትርያርክ ሆኖ በተሾመበት ወቅት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ነገሥታት አብርሃ ወአጽብሐ የእግዚአብሔርን ህልውና በማመን ሕዝበ ኢትዮጵያን በመንፈሳዊ ጥበብ እየመሩ ለ15 ዓመታት ኢትዮጵያን ከአስተዳደሩ በኋላ በመንፈስ ቅዱስ አነሣሽነት ጳጳስ እንዲያመጣላቸው በዚያን ጊዜ በአፍሪካ የክርስትና ማዕከል ወደ ሆነችው ወደ እስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ግብጽ ፍሬምናጦስን ላኩት፡፡ ፍሬምናጦስም በጊዜው በእስክንድርያ በቅዱስ ማርቆስ መንበር ተቀምጠው ለነበሩት ፓትርያርክ አትናቴዎስ በኢትዮጵያ ግዛት ክርስትናን ለማስፋፋት ስለተደረገው ጥረት ሁሉ ካብራራ በኋላ ለኢትዮጵያ ምእመናን ጳጳስ እንደሚያስፈልግ በአክሱም የኢትዮጵያ ነገሥታት ከሆኑት ከኢዛናና ሳይዛና የተላከ መሆኑን ገለጸላቸው ፓትርያርኩም ሕዝቡን ቋንቋውንና ባህሉን የሚያውቅ ከፍሬምናጦስ የተሻለና የበለጠ እንደሌለ በመገንዘባቸው መጀመሪያ ዲቁናና ቅስናን ቀጥሎም ማዕረገ ጵጵስናን ሹመውና ሙሉ ሥልጣን ሰጥተው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ እንዲመጣ ላኩት፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ ፍሬምናጦስ ከኢትዮጵያ ያመጣውን መልእክት ተቀብሎ ጉዳዩን ለማየት ጉባኤ አደረገ መልእክቱም በቅዱስ አትናቴዎስ ሊቀ መንበርነት በጉባኤ ታይቶ የሀገሩን ቋንቋና የሕዝቡን ባህል የሚያውቅ ከፍሬምናጦስ በቀር ሌላ ሰው ስለሌለ የኢትዮጵያ ጳጳስ ሆኖ እንዲሾም በጉባኤ ተወሰነ በውሳኔውም መሠረት ቅዱስ አትናቴዎስ ፍሬምናጦስን ‹‹ኤጲስ ቆጶስ ዘአክሱም ወዘኩላ ኢትዮጵያ›› ብሎ በአንብሮተ ዕድ ሹሞ ላከው ፍሬምናጦስም በ330 ዓ.ም የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ ሆኖ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ፡፡

ከእስክንድርያ እንደተመለሰም ነገሥታቱን ኢዛናንና ሳይዛናን አስተምሮ አጠመቃቸው አብርሃ አጽብሓ ብሎ በክርስትና ስም ጠራቸው ከዚያም መንበረ ጵጵስናውን አክሱም አድርጎ ሐዋርያዊ ተልዕኮውን በማስፋፋት የክህነትንና የቁርባንን ሥርዓት መፈጸም ጀመረ በኢትዮጵያ ወንጌልን ለማስፋፋት የሚረዱትን ቀሳውስትና ዲያቆናት ሾመ ቅድሳት መጻሕፍትን ከሱርስት ከእብራይስጥና ከጽርዕ /ግሪክ/ ወደ ግእዝ ቋንቋ መለሰ በዚህ ምክንያት ክርስትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃይማኖት ሆነ እሱም በሚፈጽመው ሐዋርያዊ ተግባር #ከሳቴ ብርሃን $ ተብሎ ተሰየመ ፍሬምናጦስ በእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ በቅዱስ አትናቴዎስ ከተሾመበት ጊዜ ጀምሮ ከእስክንድርያ ጋር ያለው ግንኙነት ቀጣይነት ያለው ሰለሆነ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስከ ጊዜያችን ድረስ ለአንድ ሺህ ስድስት መቶ ዓመት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ ከግብጽ ስታመጣ ኑራለች፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ ከገብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር የሚደረገው የውጭ ግንኙነት አሁንም አልተቋረጠም ያን ጊዜ የተደረገው ይህ የውጭ ግንኙነት የክርስትና እምነትን ሙሉ በሙሉ መቀበሏን ያረጋገጠችበት ስለሆነ ታላቅ ግምትና አክብሮት የሚሰጠው የውጭ ግንኙነት ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው መካከል ጳጳሳትን ለመሾም
የተደረገ የውጭ ግንኙነት፣

አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ ሆኖ ከተሾመበት ከ330 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1921 ዓ.ም ድረስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምትመራው አስቀድሞ እንደተገለጠው ከእስክንድርያ መንበረ ማርቆስ እየተሾመ በሚላክ ግብጻዊ ጳጳስ ነበር፣ ሆኖም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምኞቷና ጥረቷ ከራስዋ አበው ሊቃውንት መካከል ተመርጦ በሚሾም ጳጳስ መመራት ስለነበር ይህ ምኞትና ጥረት እያደገ ሂዶ በ11ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ የነገሠው ቅዱስ ሐርቤ ኢትዮጵያውያን ጳጳሳትን ለማሾም ለመጀመሪያ ጊዜ ለእስክንድርያው ፓትርያርክ ገብርኤል በደብዳቤ ጥያቄ አቀረበ፡፡ ሆኖም ጥያቄው ተቀባይነትን በአለማግኘቱ በየጊዜው ከተነሡ አንዳንድ ነገሥታት ተመሳሳይ ጥያቄ መቅረቡ ባይቀርም እስከ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ድረስ ጉዳዩን ከፍጻሜ ለማድረስ አልተቻለም ነበር፡፡ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመነ /በ1921/ ዓ.ም ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በዚያን ጊዜ የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ባለሙሉ ሥልጣን አልጋ ወራሽ የነበሩ ሲሆን ለእስክንድርያው ፓትርያርክ ተመሳሳይ ጥያቄ ስለአቀረቡ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ በዚሁ በተጠቀሰው ዓ.ም አራት ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት ካይሮ ላይ በእስክንድርያው ፓትርያርክ ዮሐንስ 19ኛ ተቀብተው ተሾሙ እነዚህ ጳጳሳት፣

1. ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ
2. ብፁዕ አቡነ አብርሃም
3. ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ
4. ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ነበሩ፣

በ1921 ዓ.ም ፓትርያርኩ ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት ስለመጡ ዕጨጌ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ሳዊሮስ ብለው ጵጵስና ስለሾሙዋቸው የኢትዮጵያውያኑ ጳጳሳት ቁጥር አምስት ሆነ በዚህም ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው ሊቃውንት መካከል ጳጳስ እንዳይሾሙ የሚያግደው የግብጻውያን ሰው ሠራሽ ቀኖና ሊፈርስ ችሏል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያውያን በእውቀትና በብቃት ሕዝባቸውን መምራት እንደሚችሉ ማረጋገጥ ችለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥረትና ምኞት በዚህ ብቻ አላበቃም ከእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን የበላይነት ነፃ ወጥታ በልጆቿ በራሷ ሊቃነ ጳጳሳትና ፓትርያርክ ለመመራት እስክትችል ድረስ ጥረቷን ስለቀጠለች በ1943 ዓ.ም ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዮሳብ ግብፃዊ እጅ የኢትዮጵያ ሊቃነ ጳጳሳት በ1951 ዓ.ም ደግሞ በብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ እጅ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ሆነው ተሾሙ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና በግብጽ ቤተ ክርስቲያን መካከል የነበረው የመሪነትና የተመሪነት ግንኙነት ስለአከተመ በአሁኑ ጊዜ ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት የሚያደርጉት በእኩልነትና በእኀትነት ደረጃ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን በራስዋ ጳጳሳት፣ ሊቃነ ጳጳሳትና ፓትርያርክ መመራት ከጀመረች ወዲህ የውጭ ግንኙነቷ እየሰፋና እያደገ ስለመጣ በዚያው መጠን የበለጠ ዓለም አቀፍ ዕውቅናን እያገኘች ትገኛለች፡፡

በ1968 ዓ.ም በወቅቱ በነበረው ለውጥ ምክንያት ቀዝቅዞ የነበረው ግንኙነትና በመካከል የነበሩት አለመግባባትና ቅሬታዎች ተወግደው የግብፅና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የዓለም የሃይማኖቶች የሰላም እና የክብር ፕሬዝዳንት እንደገና ተጠናክሮ በሁለቱም በኩል ውይይትና የልምድ ልውውጥ በማድረግ የቆየውን ግንኙነት ሊያጠናክሩት ችለዋል፡፡

የ2007 ዓ.ም የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የግብጽ ጉብኝት፣

ቀደም ሲል የተመሠረተው ግንኙነት ሳይዘነጋ በቅረቡ ከጥር 1 ቀን እስከ ጥር 7 ቀን 2007 ዓ.ም ለ6 ቀናት ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊና ይፋዊ ጉብኝት አድረገው ተመልሰዋል፡፡ የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎድሮስ፣ የግብጽ ገዳማትና አድባራት ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ በግብጽ የኢትዮጵያ አምባሳደር መሐመድ ድሪር የሰንበት ት/ቤት መዘምራን አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ እንዲሁም የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት አብደል ፍታሕ አልሲሲ በተጨማሪም ከግብጽ የእስልምና ሃይማኖት መሪ የታላቁ አልአዝሐር መስጊድ ኢማም ከሸክ መሐመድ አልጠይም ጋር ተገናኝተው በኢትዮጵያ ሰላለው የሃይማኖቶች ተከባብሮ መኖር በጋራ ጉዳዮቻቸው ደግሞ አብረው እንደሚሠሩ የሀገራችንን ልምድ አንስተው ገለጻ ማድረጋቸውንና በግብጽም ተመሳሳይ ዓይነት አሠራር መኖሩን ያስረዳቸው መሆኑን፤ ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን በጉብኝቱ ወቅት ለግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና ለመላው ህዝብ ካስተለለፉት መልእክት መካከል፣

ሀ. የግብጽና የኢትዮጵያ ግንኙነት እንደ እንግዳ ደራሽ ዛሬ የተጀመረ ክስተት ሳይሆን በማህበራዊና ሃይማኖተዊ መስተጋብር የተሰላሰለ መሠረት ያለው እሴት ነው፡፡ ይኸውም በሃይማኖት ለሁለት ሺህ ዘመናት ያህል አንድ ዓይነት እምነት ተቀብለን አንድ ዓይነት ሥርዓትና ቀኖና አክብረን የኖርን መሆናችንን ታሪክ የሚመሰክረው ሐቅ ነው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከእስክንድርያ አባቶች ሊቃነ ጳጳሳት እየተላኩ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያገለገሉ እንደነበረና ሁለታችንም የአንድ አባት የቅዱስ ማርቆስ ልጆች መሆናችን የጠንካራ መንፈሳዊ ግንኙነታችን ምስክሮች ናቸው፡፡

ለ. በማኀበራዊ ጉዳይ የተመለከተን እንደሆነ ደግሞ ሁላችንም ከአንድ ዓባይ የሚመነጭ ውሃ የምንጠጣ ሕዝቦች ነን፡፡ የምንለያይበት ምንም ነገር የለንም ሁላችንም አንድ ሕዝቦች ነን ዓባይ የእግዚአብሔር ጸጋ ሆኖ ለፍጡራን ሁሉ የተሰጠ በረከት ነው፡፡ በዚህ የአምላክ በረከት ደግሞ ፍጡራን ሁሉ በእኩልነት የመጠቀም መብት አላቸው እንኳንስ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠርን እኛ እንሰሳትንና እፅዋት እንኳን ከዚህ የፈጣሪ ጸጋ የመጠቀም መብት አላቸው ስለሆነም ይህ የአምላካችን በረከት የሆነው የማያቋርጥ የጋራ ሀብታችንን በፍትሐዊነትና በእኩልነት መጠቀም ግዴታችንም ጭምር መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል ብለዋል
በአጠቃላይ ቀደም ሲል የነበረው ግንኙነት በአሁኑ ጊዜ ዘመኑን በዋጀ በእኩልነት ላይ በተመሠረተ ተጠናክሮ ቢቀጥልና የልምድ ልውውጥ ቢደረግ ይኸውም በትምህርት በገዳማዊ ሕይወት፣በወጣቶች አያያዝ ስለመንፈሳዊ ግንኙነት መጠናከር ስለዓለም ሰላምና የሰው ልጆች ደህንነት እንዲሁም በማህበረሰብ ችግሮች ላይ በጋራ ስለመሥራት በሰፊው ትኩረት ቢሰጠው ቤተ ክርስቲያናችን በአሁኑ ጊዜ ህልውናዋን ይበልጥ ለማጠናከርና የውጭ ግንኙነቷንና ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት በምታደርገው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ሐዋርያዊ ተልዕኮዋን ለመወጣት ያስችላታል፡፡ ይህች ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ወቅቱ የሚጠይቀውን መንፈሳዊና ማኀበራዊ አገልግሎት በሚገባ መወጣት የምትችለው የቤተ ክርስቲያን አበውን ቁጥር በማላቅና አህጉረ ስብከትን በማስፋፋት፣ መንፈሳዊና ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን በመክፈትና የነበሩትን በማጠናከር በቤተ ክርስቲያን ትምህርት የተሟላና ከፍተኛ ዕውቀት ያላቸው መምህራንን በዘመናዊ የስብከትና የአስተዳደር ዘዴ እንዲሰለጥኑ በማድረግ ነው፡፡ ከአኀት አብያተ ክርስቲያናት ጋር የልምድ ልውውጥ ማድረግ ደግሞ እጅግ ጠቃሚ ሲሆን ልዑካን በየጊዜው እየተላኩ የዕውቀት ልውውጥ ቢደረግ ግንኙነታችንን የበለጠ ያጠናክረዋል ትውልዱንም ለመምራት የሚያስችል ክህሎት ይገኛል፡፡ ለዚህም እግዚአብሔረ ይርዳን፡፡

አባ ኃ/ማርያም መለሰ /ዶ.ር/
በኢ.ኦ.ተ.ቤ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ
ጽ/ቤት ም/ጠ/ሥ/አስኪያጅ

የፎንት ልክ መቀየሪያ