Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

የኢትዮትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥነ ምግባርን በማስፋፋትና ሙስናን በመከላከል

የኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርሲቲያን ሐዋርያዊት፣ ጥንታዊት፣ ታሪካዊትና ብሔራዊት መሆንዋ ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ይኸውም እንዲህ የሚያሰኛት ቤተ ክርስቲያንዋ የምትገለገለው በየቀኑ አዲስ በፈጠራ ቃል ሳይሆን በመንፈሳዊ ትምህርት በሚሰጠው ቀዋሚ ትምህርት ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያናችን ጥንታዊ ትምህርት ቤት በማናቸውም ጊዜ ኢትዮጵያዊ መልኩንና ጠባዩን ሳይለውጥ መስመሩንም ሳይለቅና የሕዝቡን አንድነት ሳያላላ በረዥሙ የታሪክ ጐዳና እየተጓዘ እስከ ዘመናችን የደረሰና የሚቀጥል ነው፡፡ ቀዋሚው መንፈሳዊ ትምህርት ቤትም ማለት በሥነ ጽሕፈት፣ በዜማ፣ በሥነ ጥበብ፣ በሥነ ቅኔ ውብና ድንቅ የሆኑ ሥራዎችን ማበርከቷ አይካድም፡፡በህብረተሰቡም ማህበራዊና መንፈሳዊ ኑሮ ጽኑ መሠረት አኑራለች፡፡ ኢትዮጵያን ነጸነታቸውን ጠብቀው በአንድነት እንዲኖሩ የሚያስችል ሃይማኖታዊ ትምህርት፣ ፍቅረ፣ ሀገር ስትሰጥበት ኖሮአል አሁንም እየተሰጠችበት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብዕር ቀርጻ፣ ብራና ዳምጣ፣ የእምነት መጻሕፍትን በራስዋ ቋንቋ በግእዝ ጽፋ መንፈሳዊ መገልገያ ከማደረግዋም ሌላ ቤተ ክርስቲያንዋ ዋና ለሀገሪቱን የቅርስ ባለቤት በማድረግ በውስጥም በውጭም እየተጎበኘች ትገኛለች፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በዓለም ከምትታወቅባቸው አንዱ ለሀገራችን ያበረከተችው የራሷ የሆነ የዘመን አቆጣጠር ሥርዓት ያለትና ይህም ከሌላው ዓለም ለየት የሚያደርጋት በመሆኑ ትልቅ ሥፍራ ሊሰጠው ይገባል፡፡ በዚህ የዘመን አቆጣጠር ሂደት መሠረትም ቤተ ክርስቲያናችን ባሳለፈችው የብሉይና የሐዲስ ዘመን ዓመታት ዓለምን ያስደመመ ታሪክ ያላት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን እንዲሁም ለዓለም ሕዝብ ያበረከተችውን በየዓመቱ የሚከበሩ በሌላው ዓለም የሌሉ በሀገራችን ብቻ (የሚከበሩ) ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት የሚታይባቸው ሃይማኖታዊ አገልግሎቶች በሰፊው ገልጣ የምታቀርብበት ያለ ነው፡፡

እንዲሁም ፈለገ ሕይወት በሚል ስም ቋሚ ትምህርት ቤት በመከፈት ለትምህርት ሚኒስቴር አርአያና ምሳሌ በመሆን የእውቀት ምንጭና የሥልጣኔ መሠረት ( ፋና ወጊ)ከመሆንዋም በላይ በአፀደ ቤተ ክርስቲያንና በዛፍ ሥር ከፊደል ቆጠራ እስከ ዳዊት ደገማ እና ቅዳሴ ድረስ በማስተማር ለኢትዮትያ ሕዝብ ባለውታ ናት፡፡

ከዚህም አልፋ ተርፋ 22 አንቀጽ መንፈሳዊ 29 አንቀጽ ሥጋዊ ፍርድ መስጫ ሕግም በመጽሐፍ መልክ አዘጋጅታ ፍትሐ ነገሥት ብላ ሰይማ ለኢትዮጵያ አገራችን ያበረከተች ከመሆንዋም በላይ ፍትሐ ብሔር እስከ ሚዘጋጅ ድረስ ሀገሪቱን መርታበታለች፡፡

በመሠረቱም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥነ ምግባርን ለማስፋፋት እና ሙስናን ለመከላከል የምታደርገው አስተምህሮም ሕግ አምላካዊን (ዓሥርቱ ቃላትን) መሠረት በማደረግ ነው፡፡

ምክንያቱም በመጀመሪያ እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ልጅ ከመሬት አንሥቶ ሲፈጥረው ብልህና ዐዋቂ የሚጎዳውንና የሚጠቅመውን ለይቶና አስተውሎ የሚሠራ አድርጎ ነው፡፡ በተጨማሪም ከሰማይ በታች ከምድርም በላይ ያሉትንም ፍጥረታት ሁሉ ለእርሱ አገልጋዮች እንዲሆኑ ፈቅዶለት ነበር፡፡ (ዘፍ 1፡28 - 30)

ነገር ግን ከዚያች ከሚንኖርባቸው ምድረ ገነት መካከል መብላት ይቅርና እንዳይነካት በጥብቅ የተከለከለች እንጨት ነበረች፣ የሰው ልጅም የሚበላውና የሚጠጣው ሳይቸግረው የሚለብሰውም አጥቶ ሳይታረዝ ከተከለከለችው እንጨት ፍሬ ቀጥፎ በላ፡፡ (ዘፍ 3፥6 - 7)ሙስና በገነት ተጀመረ ቅጣቱም በዚያው ተፈጸመ፡፡

በዚህ ጊዜ እንዲኖርባት ከተፈቀደችለት ምድረ ገነት ተገድዶ ወጥቶ በኃዘንና በችግር መኖር ግድ ሆነበት ሆኖም ጥፋቱን አምኖ ፈጣሪውን በይቅርታ (በንስሐ) ጠየቀ እግዚአብሔርም እንደ በደለኝ ልበድለው የማይል ሩህሩህና አዛኝ፣ ቸር ታጋሽ በመሆኑ ፀፀቱን ተቀብሎ ከወገንህ ተወልጄ ወደ ቀደመ ክብርህ እመልስሃለሁ የሚለውን ቃል አበሠረው፡፡

ይህንንም የተስፋ ቃል እየደጋገሙ የሚያበስሩና የሰው ልጅም ትክክለኛውን መንገድ ይዞ እንዲጓዝ የሚያመለክቱ ቅዱሳት መጻሕፍት እንዲጻፍለት ስለፈለገ እና ሕግም በማስፈለጉ ሕግ አምላካዊ ተበጀለት፡፡ (ዘጸ፡ 20፥3 -17)
በዚህም መሠረት ይህንኑ አምላካዊ ሕግ በሥራ ለመተርጎም ያመች ዘንድ ብዙ ሊቃውንት መጻሕፍትን ጽፈዋል ለቁጥር በሚያዳግት መልኩ ብዙም ታትቶአል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዓቢይ ርእስ አድርጋ የምትይዘውም የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ከአንድ ጸሐፊ ጥያቄ ቀርቦለት በሰጠው መልስ መሠረት በማድረግ ነው፣ ይኸውም "አፍቅሮ ለእግዚአብሔር አምላክ በኩሉ ልብከ ወበኩሉ ኃይልከ አፍቅር ቢጸከ ከመ ነፍስከ" ማቴ. 22፥34 – 40፡፡ ምክንያቱም አንድ ሰው ፍቅረ እግዚአብሔርና ፍቅረ ቢጽ ከአለው የሥነ ምግባር ጉድለት ሊታይበት አይችልም፡፡

ሲጀመር ጀምሮ ግን ሥነ ምግባር ስንል ምን ማለታችን ነው ከቃሉ ንባብ ስንነሣ ሥነ ምግባር ማለት ከሁለት ጣምራ ቃላት የተገኘ የግዕዝ ቃል ሲሆን ሥን የሚለው "ሠነየ" አማረ መልካም ሆነ ከሚለው ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ያማረ መልካም የሆነ ማለት ነው፡፡ ምግባር የሚለውም "ገብረ" ሠራ ፈጠረ አከናወነ ከሚለው ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ምግባር ማለት ደግሞ ሥራ ፈጠራ ክንውን ማለት ነው በአንድነት በመናበብ ሥነ ምግባር የሚለው የጣምራ ቃል ንባብም በሁለት መልኩ ይፈታል፡፡

ሀ/ በተነባቢ ሲፈታ በሥራ ማማር የሥራ መልካምነት ማለት ሲሆን፣
ለ/ በቅጽል ሲፈታ ደግሞ ያማረ ሥራ፣ መልካም ሥራ፣ መካም የሥራ ክንውን ማለት ይሆናል፡፡

የሥነ ምግባር መጽሐፍ የጻፉት ደራሲ ብላታ ወ/ጊዮርጊስ ወ/ዮሐንስም ስለ ቃላቱ ሲያብራሩ ሃይማኖትና ሥነ ምግባር የእግዚአብሔር የወግ ዕቃዎች ናቸው ሰዎችም የእግዚአብሔር የወግ ዕቃ ጠባቂዎች ናቸው" በማለት ገልጸውታል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም የሥነ ምግባር ባህርይን ገልጻ ለማስፋፋትና ሥነ ምግባርንም ለተከታዮችዋ ስታስተምር ሙስናን መጠየፍና መልካም ሥራውንም ማስፋፋት ማለት ማንም ሰው ራሱን ከክፉ ተግባር በመለየትና በመጠን መኖርን የሚገልጽ ከውስጥ የሚወጣና የሚታይ ተግባር መሆኑን ግልጽልጽ አድርጋ በአጻፈቻቸው የሥነ ምግባር መጻሕፍቶችዋ ዘወትር ታስተምራለች፡፡

በአጠቃለይ ሥነ ምግባር የሰውነት ባህርይ ገላጭ በመሆኑ፡-

• የታላቅነት ነጸብራቅ፣
• የሕይወት መሠረታዊ ሕንፃ፣
• የማንነት መለኪያ ቁልፍ ምሥጢርም ነው፣ ትላለች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማንኛውም ሰው ፍጡር እንደመሆኑ መጠን በተሰጠው የአዕምሮ ግዕዛን /የማወቅ ነፃነት/ ክፉ የሆነውን ተግባር ከደጉ ተግባር መለየት የሚችል ታላቅ ክቡር ፍጡር በመሆኑ ከሁሉም በፊት የፈጣሪውን ሁሉን ቻይነት ማወቅ ለቀጣዩ ሥነ ምግባራዊ ሕይወት አስተዋጽኦ ይኖረዋል ትላለች፡፡

ለዚህም ነው ከላይ በርእሱ ፍቅረ እግዚአብሔር ካለ ሥነ ምግባር አይገድም የተባለው፣ በዚህም መሠረት ሰው ሊተገብራቸው የታዘዙትን ሥነ ምግባር በመባል የሚታወቁትም በርካታ ግብረ ገባዊ ሕይወትን የሚያመለክቱና የሚጠቁሙ ሌሎች ሥነ ምግባራትን በውስጣቸው የሚያቅፉ ከመሆናቸውም የተነሣ በታላቅነት ስያሜ የተሰየሙት ስምንት ሲሆኑ እነርሱም፡-

ሀ/ ራስን መቆጣጠር፣
ለ/ ኃላፊነትን ማወቅ፣
ሐ/ ጥበብን መማር፣
መ/ ቅን ፍርድን መፍረድ፣
ሠ/ ደግነትን ማብዛት፣
ረ/ እምነትን ማጠንከር፣
ሸ/ ተስፋን ማለምለም፣
ቀ/ ፍቅርን መያዝ ናቸው፡፡

እነዚህም ዐበይት ሥነ ምግባርም በሦስት ንኡሳን ክፍሎች እንደገና ይመደባሉ ይኸውም በይበልጥ አፈጻጸማቸውን በመመልከት ይሆናል፡፡

እነሱም፡-

1. የግል ሥነ ምግባር
- ራስን መቆጣጠር፣
- ታታሪነትን ማብዛት፣
- ጥበብን መማር፣
እነዚህም በአብዛኛው ተጠቃሚው ሰው በራሱ ሕይወት ለራሱ የሚተገብራቸውና ለሌላም አርአያ ለመሆን አንድ ግለሰብ የሚፈጽማቸው ተግባራት ናቸው፡፡
2. የጋራ ሥነ ምግባር፣ የሚሆኑ ደግሞ
- ቅን ፍርድ፣
- ደግነት የመሳሰሉት ሲሆን የጋራ ሥነ ምግባራትም አንድ ግለሰብ ለሀገሩ ለወገኑ ለሰው ዘር በሙሉ የሚፈጽማቸው ተግባራት ናቸው፣ እነዚህ በጎ ምግባራትም
- ሰብአዊነትን፣
- እኩልነትን፣
- ነፃነትንና በአዕምሮ ዳኝነት መታገዝን ያንፀባርቃል፡፡
3. ሃይማኖታዊ ሥነ ምግባር የሚባሉም፣
እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር፣ የመሳሰሉት ሲሆኑ፣
እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ሃይማኖታዊ ሥነ ምግባራትም ሰው ፍጡር እንደመሆኑ መጠን ለፈጣሪው አክብሮት በመስጠት የሚገልፃቸው የእምነት ምግባራት ናቸው፡፡ ይህንኑ ያጠቃለለ ሥነ ምግባራዊ ገጽታም ከዚህ በማስከተል እንመለከታለን ይኸውም፡፡

ራስን መግዛት

ራስን መግዛት ውስጣዊ ሕሊናን መቆጣጠር የሚያስችል ወይም ልዩ የውስጥ ችሎታ ነው ይኸውም ራስን ለዚህ ታላቅ ተግባር ብቁ ለማድረግ የተለየ ልምምድን ይጠይቃል ራስን መግዛት በሰው ላይ ዘላቂ ለውጥ እና ጠቃሚ ልምድን ለማስገኘት ይረዳልና ራስን ከአጉል ልምድ መለየቱ ራስን የመግዛት ፍፁማዊ ትርጉምን ያንፀባርቃል፡፡

በአብዛኛውም በምኞት ብቻ እንዳንወሰንና ውጤታማ ለመሆን ራስን በሚገባ መጠን መቆጣጠር ወይም ማረጋጋትና አቅምን መለካት አስፈላጊ ሲሆን ይኸው ደግሞ ታላቅነትን ይገልጻል የሥን ምግባር ትርጉም ሰው መሆኑንም ያሳውቃል የራስ መግዛት ዋና ትርጉሙም በሥነ ልቡናዊ ሕይወት አንፃር ሲታይ ራስን ከክፉ ተግባራት መለየት ወይም የቆራጥነት ሕይወት መያዝንም ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቱያንም ወርቃማ ከሆነው መጽሐፍ ቃል መካከል ለሥነ ምግባር ግንባታ ማስፋፋት ከምትጠቀመው አንዱ "ሰዎች ሊያደርጉልህ የምትፈልገውን ድርጊት አንተም እንዲሁ አድርግላቸው ወይም ሰዎች ሊያደርጉብህ የማትፈልገውን ደርጊት አንተም አታድርግባቸው" የሚለው ነው፡፡ (ማቴ. 7፥12)

ሰዎች ብዙውን ጊዜ በሌሎች ሰዎች ላይ ክፉ ነገር የሚያደርጉት ራቸውን ከመውደዳቸው የተነሣ ነው፣ አምባገነንነት /ዲክታተርነት/ ሰውን መጨቆን የመሳሰሉ ክፉ ተግባራት የሚከሰቱት በራስ ወዳድነት ምክንያት ነው፡፡ ማንም ሰው ለራሱ በጎ ነገርን እንጂ ክፉ ነገርን አይመኝም ወይም አያደርግም፣ ጌታ ግን ፍቅረ ቢጽን ነው ያስተማረው፣ ፍቅረ ቢጽ ማለት ደግሞ እኛ ሰዎች ስንወዳቸው እንደ ሰዎች አካሄድ እኛንም ሲወዱን ብቻ አይደለም የፍቅር ውጤት እና ደስታ የሚኖረውም ከመስጠት ውስጥ እንጂ ከመቀበል ውስጥ አይደለም ትላለች ቤተ ክርስቲያናችን ሌሎች ሲያፈቅሩን አፍቃሪ የሆንን የሚመስለን ብዙ ጊዜ ቢሆንም ፍቅር ግን መስጠት ነው እንጂ መቀበልን ብቻ የሚወክል አይደለም፡፡

ለሰማያዊ አባት ያለንን ፍቅር የምንገልጸው እርሱ የወደዳቸውን የሰው ልጆች በመውደድ ነው ሰዎች ስንል ምንም ሰው የእግዚአብሔር ውለታ ትልቅ ነው የት አግኝተን እንመንልስለታለን ብንል እግዚአበሔር ከምናያቸው ፍጥረቶች ጋር ነውና ለእነርሱ መልካም ሥራ ከሠራን ለእርሱ መልካም ሥራ ማድረጋችን ነው፡፡/ዮሐ 4.7፡12/

በዓለም ላይ ብዙ ኃይሎች ቢኖሩም ፍቅር ግን ከማንኛውም ተፈጥሮአዊና ሰው ሠራሽ ኃይል ይበልጣል /መ.ኃ. 8፡6-7/ የፍቅር ጣዕም የሚታወቀው የእግዚአብሔር ፍቅር ሲታወቅ ነው ምክንያቱም እግዚአብሔር ራሱ ፍቅር ነውና /1ኛ ዮሐ. 4፡8/ በእርግጥ ፍቅር የሚባለው ሁሉ እግዚአብሔር ነው ለማለት ግን አይደለም ምክንያቱም ዓለም ስለ ፍቅር ትናገራለች ነገር ግን ዓለም እግዚአብሔርን አታውቅም ለማወቅም ፈቃደኛ አይደለችም፡፡

ስለዚህ እግዚአብሔር በማይታወቅበትና በማይከበርበት ስፍራም ፍቅር ሊኖር በፍጹም አይችልም በትእዛዝ ደግሞ ፈጽሞ ማፍቀር አይቻልም ምክንያቱም የፍቅር ምንጩ እግዚአበሔር እንዴት እንደወደደን ስናውቅ ብቻ ነው የሚታወቀው፡፡

እርሱን ማፍቀር የምንጀምረውም ሰዎችን መውደድ ስንችል ብቻ ነው ምን ጊዜም የፍቅር መነሻው እግዚአብሔር ነውና ስለሆነም ፍቅር ከሁሉም በላይ እውነትን ይፈልጋል እውነትና ፍቅርም አይነጣጠሉም እውነተኛ ፍቅር የሚያስወድደውም የሰውየውን ቁመና፣ መልክ፣ አለባበስ፣ ሥልጣንና ገንዘብ ሳይሆን ራሱን ሰውየውን ነው፡፡

ሰው በመሆኑም ብቻ ነው፣ ቁመናውና መልኩ ሥልጣንና ገንዘብ ቋሚ አድራሻዎቹ አይደሉምና ነው የሰው ቋሚ አድራሻው ሰው የመሆን እና እርሱነቱ ነውና እርሱነቱ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ አለ ይኖራልም፡፡

ነገር ግን ያፈቀርናቸው ሰዎች የከዱን የሉም እኛም ሰዎች ነንና ብዙዎችን ከድተን ይሆኛል፣ባለን እድሜም የሚወዱንን እየሸሸን የጠሉንን ስናሳድድ ከሁለት ያጣ ሆነን ነው የምንኖረው፣ ብዙ ፍቅር ስለገፋን ብዙ ፍቅሮችም ተሰብረውብናል ይሄ በሰው ልጅ የሚታይ እውነት ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በተለይ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ስለ ሥነ ምግባር እና የሙስና አስከፊነት ሁልጊዜ ከሚናገሩት በተጨማሪ በአንድ ወቅት ካስተላለፉት መመሪያና መልእክት በመውሰድ እንመልከት፣

"ሁላችንም እንደምናውቀው እዚህ ቅዱስ ስፍራ የሰበሰበችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፣ መሪያችንም መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እኛን የሰበሰበችበትም ምክንያት አምላካዊ ሰማያዊ፣ ዘለዓለማዊ፣ ዓላማ እንዳላት የምንዘነጋው አይደለም፡፡

የቤተ ክርስቲያናችን ዋና ዓለማም ወንጌለ መንግሥተ ሰማያትን ማስተማርና መንፈሳዊ አገልግሎትን ለእግዚአብሔርና ለሕዝበ ክርስቲያኑ ማበርከት ነው፡፡"

የቤተ ክርስቲያናችንን ተልእኮም ሳይዛባ፣ ሳይፋለስ፣ ፈሩን ሳይለቅ፣ በነበረበት ለማስቀጠል የመንበረ ሐዋርያት ወራሾች የሆኑት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትም በየዓመቱ ሁለት ጊዜ በቋሚነት እየተሰበሰቡ፣ ስለ አጠቃለይ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ እየገመገሙ እየመከሩ እየወሰኑ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እምነትዋን ሥርዓቷን እንዲጠብቁ ቅዱሳን አበው በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ደንግገዋል፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤም ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ተከትሎ የሚካሄድ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም እምነትዋን /ዶግማዋን/ ቀኖናዋን፣ ታሪኳን ጠብቃ የቆየች ጥንታዊት የሃይማኖት ተቋም መሆንዋንም በዓለም ታሪክ የታወቀ ሐቅ ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደርም የመልካም አስተዳደር ጉድለት እና የሙስና አስከፊነት እንዲሁም የሥነ ምግባር እጦት አለ በመባሉ ምእመናኑ በቤተ ክርስቲያኒቷ አመራር ላይ ቅሬታና እምነት ማጣትን እያሳደረ ሁኔታውም እየተባባሰ ሲሄድ ይታያል፡፡ ስለሆነም ታሪክ እንዳይፈርድብን ካህናቱንና ምዕመናኑን በማስተባበር አስቸኳይ የእርምት እርምጃ መውሰድ እጅግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡የሀገሪቱ መንግሥትም ሙስናን ለማጥፋት የፀረ ሙስና ኮሚሽን አቋቁሞ በሚታገልበት ጊዜም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሙስና በፍጹም መታየት የለበትም፡፡

የቤተ ክርስቲያናችንን ስም ለመጠየቅ ክብርዋን ለማደስ እንዲቻል እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች አባቶች ኃላፊዎች እና አገልጋይ ካህናት ሠራተኞች በሙሉ ለሕዝበ ክርስቲያኑ አርአያና ምሳሌ በመሆን ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲኖረን ያስፈልጋል፡፡የሚከተሉት ሥር ነቀል የለውጥ እርምጃዎችም በቆራጥነት ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማሳሰብ እወዳለሁ" ካሉ በኋላ ከሊቃነ ጳጳሳት፣ ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም ከምእመናን የተውጣጡ አባላት የሚገኙበት "የመልካም አስተዳደር የፀረ ሙስና ዓቢይ ኮሚቴ" እንዲቋቋም ሆኖ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ሁኔታውን እየመረመረ ስንዴውን ከእንክርዳድ ለይቶ እንዲያቀርብ ማድረግና እንክርዳድ ሆነው በሚገኙት ላይም አስተማሪ የሚሆን ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ነው በማለት የሰጡት ማስገንዘቢያ ለሃይማኖት ተቋማትና ለተከታዮቻቸው ብቻ ሳይሆን ይህንን የሰማና ያነበበ ሁሉ ከመገረምና ከማድነቅም አልፎ ማነቃቂያ ምሳሌ ሆኖታል፡፡ ከግለሰብ ጀምሮ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የመንግሥት ያልሆኑና የግል ድርጅቶች የተለያዩ መንፈሳዊና መንፈሳዊ ያልሆኑ ማህበራት እንዲሁም መላ የቤተ ክርስቲያንዋ ሠራተኞች ከቢሮ ሠራተኛ ጀምሮ እስከ አፃዌ ኆኀት ድረስ የት ነው ያለነው ምንስ እየሠራን ነው በማለት ቆም ብሎ እንዲያስብ አድርጎታል እንላለን"፡፡

ማጠቃለያ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መልካም ሥነ ምግባርንም ለማስፋፋትና ሙስናን ለመከላከል በመርህ የምታስቀምጠው እግዚአብሔርን አምኖ ማፍቀርና ሰውንም ከልብ መውደድ ነው እነዚህ ሁለት ወጋግራዎች በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ ከአሉ ሙስና አይኖርም በአጠቃላይ የሥነ ምግባር ጉድለት አይታይም ብላ ለተከታዮቿ ታስተምራለች አቋሟም ነው፡፡ ምክንያቱም ለገንዘብ እንዳንስገበገብም ገንዘብ፣ ከእግዚአብሔር በታች ነው የሥነ ምግባር ጉድለት እንዳይታይብንም ምን አጣን ብለን ነው አስፈላጊው ሁሉ እና የሕይወታችን ዋስትና ሳይቀር በሙሉ ከእግዚአብሔር እጅ አለ፡፡የመድኅን ዋስትናችን እግዚአብሔር ነው፡፡

ለምሳሌ እኛ ወዳጆች እንዳይከዱን ለማድረግ በኃይል ለመከላከል ሥልጣን የለንም፣ ነገር ግን ወዳጆቻችን በከንቱ ቢከዱን እንኳ የማይከዳ እግዚአበሔር ወዳጃችን ምሥጢራችንን የሚያውቅልን ገመናችንን የሚሸፍንልን ለዘለዓለም የማይከዳ ወዳጅና አፍቃሪ አባት አለን፡፡

ስለዚህ እንደዚህ ያለ ሁሉንም አሟልቶ የያዘ አፍቃሪ አምላክ፣ ሰጥቶ የማይፀፀት አፍቅሮ የማይጠላ አባት እያለ ሥነ ምግባርን በማጉደልና ሙስናን በመፈጸም ላይ አማኞች እንዳይገኙ ዘወትር የቅዱሳን መጻሕፍት ቃላትን መሠረት በማድረግ መልካም ሥነ ምግባርን በማስፋፋትና ሙስናን በመከላከል ረገድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቱያን ያላት ተሞክሮ ወደር የለውም ለወደፊትም ሳይቋረጥ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርካችን ጀምሮ (በጠነከረ) አቋም አበው ሊቃነ ጳጳሳትም ጭምር በቅኔውም፣ በጽሑፍም፣ በኮሌጅም ሁሉ በየስብከተ ወንጌል መድረኩና በየዓውደ ምሕረቱም የምትናገረውና የምታስነግረው ብዙ ቢሆንም ለግንዛቤ ያህል ከብዙ በጥቂቱ ከሙሉ በከፊሉ ከዚህ በላይ የተጻፈውን አጠናቅረን ያቀረብን መሆኑን ስንገልጽ በታላቅ አክብሮት ነው፡፡

አለበለዚያማ እንደመጀመሪያው ሰው የሚበላው ሳያጣ ከተከለከለው የዕንጨት ፍሬ ቀጥፎ እንደበላ እኛም በዚህ ዘመን ያለነው ሁላችንም የምንጠጣውና የምንበላው ሳናጣ ያልተፈቀደልንን ገንዘብ (ሀብትን) ቀምተን ከበላን ትልቅ ዕዳ በደል ስለሆነ መጠንቀቅ ያስፈልገናል፡፡ ለሁሉም ከክፉ ርቀን መልካውን ሥራ ሠርተን ለመመስገን እንድችል የፈጣሪያችን ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ርዕሰ ደብር መሐሪ ኃይሉ
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት
ዋና ሥራ አስኪያጅ
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ

የፎንት ልክ መቀየሪያ