Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ከሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም እስከ ግንቦት 21 ቀን 2007 ዓ.ም ያከናወናቸው ዓመታዊ የሥራ ሪፖርት እና የወደፊት ዕቅድ፤

መግቢያ

"ወአመሰ ደቂቅ አነ ወኃለይኩ ከመደቂቅ፣ ወአመሰ ልሕቁ፤ ወሠዓርኩ ኲሎ" ሕገ ደቂቅ ልጅ ሳለሁ እንደልጅ እናገር ነበር፤ እንደልጅም አስብ ነበር፤ እንደልጅም እቈጠር ነበር፡፡
ጎልማሳ ሆኜ ግን የልጅነትን ጠባይ ሽሬ አለሁ፡፡ 1ኛ ቆሮንቶስ ምዕ. 13፡11፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሰው ልጅ ስለፍቅር ኃያልነትን ይቅር ባይነት በገለጸበት አንቀጹ የሰው ልጅ በተለያዩ የዕድሜ ክልል እንደሚያልፍ በዚያው ልክ አስተሳሰቡም ጭምር እንደሚቀያየር በራሱ የሕይወት ተምሳሌት ገልጦልናል፡፡

የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መሚያም የሚመራው ወጣቱ አዲሱ ትውልድ ነው፡፡ አብዛኛው በዚህ የወጣትነት እድሜ ክልል የሚገኝ ነው፡፡የተለያዩ ምሑራን እንደሚገልጡት ወጣትነት ከልጅነት በኋላ ከጎልማስነት በፊት ያለ የዕድሜ ክልል ነው፡፡ በዚህ ዕድሜ የሚገኝ ሰው አእምሮውም አካሉም ትኩስ ነው፡፡ ትኩስ በመሆኑም ምክንያት ብዙ ሊሠራ ይችላል፡፡ ወጣት ብዙውን ጊዜ ያለበትን ተጨባጩን ዓለም ትቶ በሐሳቡ በሚፈጥረው ዓለም ውስጥ ገብቶ በዚያ ውስጥ ይዋኛል፡፡ በዚህ ዕድሜ የሚገኝ ሰው ያሉት ድክመቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡ 1ኛ ቶሎ ይበሳጫል 2ኛ ሁሉም ነገር በትክክል እንዲሠራ፣ ፍትህ እንዲኖር፣ ሰው ሀሉ እንደ ዕድሜውና እንደ ኃላፊነት ቦታው መሠረት ጨዋ፣ ቁም ነገረኛ ሐቀኛ እንዲሆን ይሻል፡፡ ጥፋት አይቶ በአስተያየት የማሳለፍ ጠባይ የለውም፡ እንዴት እንደዚያ ይሆናል ብሎ ቱግ ማለትና አጥፊውን ከፊቱ ላይ መናገር፣ ለነገ ያለማለት ሁኔታ ይታይበታል፡፡ 3ኛ ጉልበት ስላለው ለደረሰበት ጥቃት አጸፌታውን ለመመለስ ወደ ኋላ አይልም፡፡ 4ኛ አደገኛ የሆነን ነገረ እንኳ ምንም አያደርገኝም በማለት የመዳፈርና ራሱን አላስፈላጊ ለሆነ አደጋ የማጋለጥ ሁኔታ ይታይበታል፡፡ 5ኛ ያሰበው ሳይሳካለት ሲቀር ቶሎ ያዝናል፣ ቶሎም ተስፋ ይቆርጣል 6ኛ ያሰበው ሲሳካለትም በችሎታውና በዘዴው እጅግ የመኩራራትና የመደሰት መንፈስ ይታይበታል፡፡ እንዲህ የመሰለ ትውልድ ልዩ እንክብካቤና ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል፡፡

የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ በ1986 ዓ.ም ቅዱስ ሲኖዶስ አጽድቆ በሰጠው ውስጠ ደንብ ምዕራፍ ሦስት ቁጥር 17 /ከሀ-ረ/ የተዘረዘረው መሠረት በማድረግ የሰንበት ት/ቤቶች ሁለገብ አገልግሎት ይበልጥ እንዲጠናከርና በሁሉም ዘንድ ተደራሽ አገልግሎት ለማድረግ ከማዕከል ከመንበረ ፓትርያርክ ጀምሮ እስከ ወረዳና አጥቢያ ድረስ ሰፋፊ አደረጃጀትና የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ወይም ትስስር (Networking) በመፍጠር ዘመኑን ለመቅደም በሚያስችል መልኩ አመርቂ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡

ይኸው የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነትም ሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ወጥ የሆነ ሥርዓተ አገልግሎት እንዲኖር ለማድረግ ከፍተኛ የሆነ ጠቀሜታ እንዳለው መምሪያው ባደረገው የግምገማ መርሐ ግብር ለማወቅ ችሎአል፡፡ መምሪያው የወጣቶችን መምሪያ እንደመሆኑ መጠን ሁሉም ወጣቶች ሰንሰለታዊ ግንኙነትና ሕብረት እንዲኖራቸው በየደረጃው ከመንበረ ፓትርያርክ ጀምሮ እስከ አጥቢያ ድረስ የሰ/ት/ቤቶች ጠቅላላ ጉባኤ ፈጥረው ልምዳቸውን የሚለዋወጡበት፣ ችግራቸውን በጋራ መፍትሔ የሚፈልጉበት መንገድ ማመቻቸት ዘመኑ የሚጠይቀው ወሳኝ ምዕራፍ ስለሆነ ከመንበረ ፓትርያርክ ማለት ከሀገር አቀፍ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ጀምሮ እስከ ወረዳ አቀፍ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ድረስ ቃለ ዓዋዲውና በቅዱስ ሲኖዶስ የጸደቀው የማደራጃ መምሪያ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት በማድረግ በየደረጃው አደረጃጀቶች እንዲኖሩ ተደርገዋል፡፡

እስከ አሁን ድረስ ያሰገኘው ጠቀሜታ ሲታይም እጅግ ተስፋ ሰጪ እና ለወደፊት የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ የሚያመላክት ነው፡፡

ዘመኑ የቴክኖሎጂ ዘመን እንደመሆኑ መጠን ወጣቱ ደግሞ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ባለቤት ስለሆነ ይህንን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ሀገር አቀፋዊ ግንኙነቱና አንድነቱ አጠናክሮና ጠብቆ እንዲሄድ ለማድረግም ከሰ/ት/ቤቶች በተገኙ ምሁራን ባለሙያዎች ለሁለት ዓመታት የተደከመበት መሪ ዕቅድ /ስትራቴጂክ ፕላን/ ተዘጋጅቶ ቅዱስ አባታችንና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም ከየአኅጉረ ስብከቱ የመጡ የሰ/ት/ቤቶች ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በዓመታዊ የሰ/ት/ቤቶች መደበኛ ጉባኤ ላይ በይፋ ካጸደቀ ሁለት ዓመታት አልፎአል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የወላይታ፣ ኮንታና ዳውሮ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የበላይ ሊቀ ጳጳስ፣ የስልጤ ጉራጌ ሐድያና ከንባታ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት
ክቡራን የየመምሪያው እና የየድርጅቶች ኃላፊዎች
ክቡራን ጥሪ የተደረገላችሁ የዚህ ጉባኤ የክብር እንግዶች
ክቡራን የ50 አኅጉረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች ኃላፊዎችና ከመላ ሀገሪቱ የተወከላችሁ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ተቀዳሚ ምክትልና ምክትል ሰብሳቢዎች
ክቡራን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራትና ገዳማት የሰንበት ት/ቤቶች ሊቃነ መናብርት፤
በአጠቃላይ በዚህ ጉባኤ የተገኛችሁ ወንድሞችና እኅቶች
እንኳን ለ4ኛ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ አደረሰን አደረሳችሁ፡፡ እንኳን ደህና መጣችሁ


ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሐዋርያዊት፣ ታሪካዊትና ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያን በመሆንዋ መንጋዋን ለመጠበቅ ያለባት ኃላፊነትም በዚሁ መጠን ስፋትና ጥልቀት ያለው መሆኑ በግልጽ ይታወቃል፡፡

በተለይም በአሁኑ ዘመን በመላው ዓለም በሰው ልጅ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ከባድና ውስብስብ የሆኑ ችግሮች በተደቀኑበት ወቅት የወጣቱ የአገልግሎት አድማስ ስፋትና ጥልቀት እያገኘ የመሄዱ ጉዳይም ግዴታ ሆኗል፡፡ በሁሉም አቅጣጫ እየተደረገ ያለው ጥረት በወጣቱ መጻኢ ሕይወት ዕድል ላይ የተስፋ ብርሃን እየፈነጠቀ ያለ ብሩህ እንቅስቃሴ ነው፡፡

በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ 37,332 አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ከ20,000,000 በላይ ወጣቶች እንዳሉ የሚገመት ሲሆን፣ እስከ አሁን በ8610 አብያተ ክርስቲያናት በሥርዓት ተመዝግበው አገልግሎት በማግኘት ላይ ያሉ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ወጣቶች ግን 2,701,253 እንደሚያህሉ ጥናቱ ያመለክታል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ገና ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅብን ሁኔታው በግድ እያመለከትን ነው፡፡ ዛሬ እንደ ድሮ ሁሉም የእኛ ነው ብሎ መቀመጥ እራስን ከማዘናጋት ውጭ ትርጉም የለውም፡፡ ትርጉም የሚኖረው ሁሉም በተሰማራበት ሠርቶ ውጤታማ ሆኖ ወጣቶቹንና ምእመናንን ወደ ቀድሞ ክብራቸው እንዲመለሱና የቤተ ክርስቲያናችን ክብርና ልዕልና ሲጠብቅ ነው፡፡ የመምሪያው ዓላማውና ተልዕኮውም ይሄን ማሳካት ነው፡፡

የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ራዕይ

በሀገርና ከሀገር ውጭ ባሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ተቋማት አባል የሆኑና ለመሆን የተዘጋጁ አዳጊ ሕፃናትና ወጣቶች በቤተ ክርስቲያኒቷ የሃይማኖት ዶግማና ሥርዓት የተኮተኮቱ፣ ሃይማኖቱ የሚያዘውን አኗኗር የሚጠብቁ፣ የሚያስጠብቁና በየዘመናቸው ለክርስትና መከፈል የሚገባውን የመንፈሳዊ ተጋድሎ ዋጋ በመክፈል ከትውልድ ወደ ትውልድ ክርስትናን ከነ ሙሉ መገለጫዎቹ ጋር የሚያሸጋግሩ ክርስቲያኖችን ማፍራት፤

የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ተልዕኮ

1. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ በየደረጃው በተዋቀሩ የመምሪያው ተቋማት ለሚታቀፉ ሕፃናት፣ ወጣቶችና ጎልማሶች በትምህርተ ሃይማኖት፣ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፣ በኢትዮጵያና በዓለም የክርስትና ታሪክ በቤተ ክርስቲያን የአብነት ትምህርት ቤቶች በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ምሥጢራዊ አፈጻጸም በተቀደሰ ትውፊት ላይ ወጥነትና ተከታታይነት ያለው እውቀትን ማስተላለፍ፤

2. ለሕፃናትና ለወጣቶች የሚሰጠው ትምህርት በአሰጣጡ በአደረጃጀቱና በዘዴው ዘመኑን በሚዋጅ መልኩ እየተሻሻለ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ተልዕኮና የማደራጃ መምሪያውን ራዕይ የሚያሳካ በሚሆንበት መልኩ የተቃኘ ማድረግና መቈጣጠር፤

3. ወጣቶችን ከቤተ ክርስቲያኒቷ ትምህርት ሥርዓትና የክርስቲያናዊ ማንነት መገለጫ ከሆኑት ማኅበራዊ መስተጋብርና አኗኗር፣ ጠባይና ሥነ ምግባር የሚያስወጡ የየዘመናቱን ኢ-ክርስቲያናዊ ለውጦች በመከታተል በክርስቲያናዊ ትምህርት መታገልና ወጣቶችን ከመነጠቅ መጠበቅ እንዲሁም ይህንን ተጋድሎ ማስጠበቅ የሚችልና ለመጭው ትውልድ ፅኑ የሆነ ተቋማዊ መሠረት መጣሉን ማረጋገጥ፤

4. ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት፣ ከክርስቲያናዊ ወላጆች ትውፊት፣ ከማኅበረሰቡ ኢትዮጵያዊ የክርስትና አኗኗርና ፍልስፍና ይልቅ በዘመናዊ መገናኛ ብዙሃንና በዘመናዊ ትምህርት ስርጭት የበለጠ የተጋለጡትን የዘመናችንን ሕፃናትና ወጣቶች የሚመጥንና ክርስቲያናዊ ማንነትን የሚያስጠብቅ አዳዲስ ስልቶችንና ዘዴዎችን በመዘርጋት ክርስቲያናዊ ማንነትን ከጥፋት መታደግ፤

የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እሴቶች

1. በቅድስና ምሳሌ የሆነ አስተዳደራዊ አገልግሎት፡- ተቋማዊ አገልግሎት በይዘት፣ በአኗኗርና በድርጊት ቅድስናን የሚመሰክር ለሕፃናትና ወጣቶች እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ በማለት አምላካችን ያዘዘንን ትዕዛዝ የሚተረጒም መሆኑን የሚያረጋግጥ፤

2. ፅናትና ምስክርነት፡- በጊዜውም ያለጊዜውም በክርስቲያናዊ ማንነት መፅናትን በተግባር የሚተረጒምና የተጋድሎ ምሳሌ የሆነ ውሳኔ አገልግሎትና ተግባራዊ ምስክርነት፤

3. በፍቅር የሆነ አገልግሎት፡- በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉትን ለማፅናት የሌሉትን በትምህርትና በኑሮ ምሳሌነት ለማምጣት እየተጉ ለሁሉም ፍቅርን መስጠት፤

4. ዘመኑን መቅደም፡- ክርስቲያን ወጣቶች ኢ-ክርስቲያናዊ እሴቶች ላይ የቆመ ነገር ግን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመረዳት እየተፋፋመ በሚገኘው ሉላዊነት አንፃር ዓለሙን ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ አድርጉ የሚለውን የክርስቲያናዊ ሉላዊነት አምላካዊ ትዕዛዝ በሚፈጽሙት ላይ የተደቀነውን የክርስቲያኖችን ፈተናዎች የመቋቋሚያ አቅም እንዲያዳብሩ ማስቻል፤

5. ክርስቲያናዊ ኃላፊነት፡- ከእውነትን መንገድ የወጣ የወጣቶችን ውሎ ፍፁም በሆነ ትጋት ቁጥጥር በማድረግ የመልካም ሥነ ምግባር፣ የታታሪነት የሀገርና የሰው ልጆች ፍቅር ምሳሌ መሆን፤

መሪ እቅድ ፤የተናጥልና የወል ፍጻሜ አላማዎችና ግቦች--------------------------------
ቁልፍ ጉዳይ 1፡ የሰንበት ት/ቤትና የሰንበት ት/ቤት አባላትን ብዛት በቁጥርና በጥራት መጨመር፤ --------
ቁልፍ ጉዳይ 2፤ የሰንበት ት/ቤትን አስተምህሮ ፣የአገልግሎት ስፋት፣ ጥራትና ተደራሽነትን ማሻሻል -------
ቁልፍ ጉዳይ 3 ፤ የሰንበት ት/ቤት ተsማዊ ይዘት ወጥነት -----------------------------------------------
ቁልፍ ጉዳይ 4፤ የሰንበት ት/ቤት የአስተዳደር ወጥነትና የፋይናንስ ሥርዓት ዝርጋታ ---------------------
ቁልፍ ጉዳይ 5፤ ራስን ማስቻልና ልዩ ልዩ የልማትና የበጎ አድራጎት ሥራዎችን መንደፍ ------------------
ቁልፍ ጉዳይ 6፤ የወጣቶችን መንፈሳዊና ሁለንተናዊ ልማት በሚመለከት የምርምርና ጥናት ዝግጅት ሥራ መሥራት -------
ቁልፍ ጉዳይ 7 ፤ በየደረጃው የሚገኙ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባዔያትንና የመምሪያውን ርእይ ከግብ ለማድረስ የሚያስችሉ ሕጋዊ
ማእቀፎችን ተንትኖ ለቅዱስ ሲኖዶስ ማቅረብ ነው፡፡

የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ይህንን ዓላማው ለማሳካት በ2007 ዓ.ም፤

1. ሀገር አቀፍ አደረጃጀት በመላ ሀገሪቱ አደራጅቷል፤ ያልተቋቋመባቸውም እንዲቋቋምባቸው ብርቱ ጥረት እያደረገ ነው፡፡
2. የአምስት ዓመታት መሪ እቅድ ከ2005 እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ በመላ ሀገሪቱ ተግባራዊ እያደረገ ነው፡፡
3. በድረ ገጹ ለመላ ዓለም ምእመናን እያስተማረ
4. የ2007ዓ.ም እና የ2008ዓ.ም ዝርዝር የአፈጻጸም መርሐ ግብር ማውጣት በመላ ሀገሪቱ ተግባራዊ ሆኖአል፡፡
5. የሪፖርት አቀራረብ መመሪያ ለ60 አኅጉረ ስብከት ማዳረስ ተግባራዊ ሆኖአል
6. የ2007ዓ.ም በዓለ መስቀል እና በዓለ ጥምቀት ማክበር ተግባራዊ ሆኖአል
7. የተለያዩ ጉባኤያትና ሥልጠናዎች ስብሰባዎች አካሂዷል፡፡
8. እቅዱን በአግባቡ መሠራቱን የሚገመግምበት የግምገማ ሠነድ አዘጋጅቷል
9. የሰንበት ት/ቤቶች አደረጃጀት እስከ ወረዳ ድረስ አውርዷል
10. የቅዱስ ፓትርያርኩ ሐዋርያዊ ጉዞ እና አገልግሎት የቤተ ክርስቲያናችን ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴን፣ ማሕበራዊ አገልግሎት በዌብ ሳይቱ ዓመቱ ሙሉ ለመላ አለም አሰራጭቷል
11. የሥርዓተ ትምህርት እና መዝሙረ ማህሌት መጻሕፍትን በተሳካ ሁኔታ አሳትሞ፤
12. በመላ ሀገሪቱ ተሰራጭቷል

1. የፋይናንስ አሠራር ረቂቅ ተዘጋጅቶ ውይይት ላይ ይገኛል፣ ወደ ተግባር ለመግባት ያዘገየው አዳዲስ የጠቅላይ ቤተ ክህነትና አጥቢያዎች የሒሳብ አሠራር በለውጥ ላይ መሆኑ
2. የዛሬን ሥራ ጨምሮ አደረጃጀት ከሞላ ጎደል ተከናውኗል
3. የ2006 ዓ.ም የ2007 ዓ.ም ዝርዝር የደርጊት መርሐ ግብር የያዘ በአጠቃላይ 69 ገጽ የያዘ በሀገር ውስጥ ለሚገኙ ለ51 አኅጉረ ስብከት በውጭ ዓለም ለሚገኙ 9 አኅጉረ ስብከት በድምሩ ለ60 አኅጉረ ስብከት አሠራጭቷል፡፡
4. በአ.አ 2006 እና 2007 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም አድባራት ማለት የበዓላት አከባበር ዝግጅት ወጥ የሚሆንበት ጥረት ተደርጓል፣ ይህ ልምድ ተገምግሞ በሁሉም ሀገረ ስብከቶች የተሻለ አንዲሆን የዚህ የቀጣይ ዓመት እቅድ አካል ሆኖአል፤

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርከ ጠቅላላ ጽ/ቤት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ በድረ ገጽ በኩል የፈጸማቸው አገልግሎት በተመለከተ፤
ድረ ገጹ የተቋቋመለት ዋና ዓላማ፤

የቤተ ክርስቲያኒቷ መሠረታዊ አስተምህሮዎች ወቅታዊ የሆኑ ሐዋርያዊ አገልግሎቶች ወቅቱንና ሰዓቱን ጠብቆ ለምዕመናን በማዳረስ ምዕመናን ዘመን የወለደውን ይህንን ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ትምህርት ቤተ ክርስቲያናቸውን የበለጠ እንዲረዱና ከአሉባልታ የጸዳ የቤተ ክርስቲያናቸው ሐዋርያዊ የአገልግሎት ድምጽ /አንደበት/ በአግባቡ አንዲታተሙ በማድረግ እውነታውን በሚገባ ተረድተው በአገልግሎታቸው ይበልጥ እንዲጸኑ ለማድረግ ነው፡፡

ድረ ገጹ ያስገኘው ጠቀሜታ

ድረ ገጹ ከተከፈተ ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ድረ ገጾችና ብሎጎች ይተላለፍ የነበረው የወሬ አሉባልታና የውሸት ፕሮፖጋንዳዎችን ረግጦና በልጦ መረጃና ማስረጃን አስደግፎ እውነትን በማስተላለፍ በዓለም ዙሪያ የሚገኘው ሕዝባችን እውነተኛ መረጃ በመስጠት እውነቱን ከቤተ ክርስቲያን አንደበት እንዲያዳምጥ በማድረግ የመረጃ ሚዛኑን በመድፋት የውሸትና የአሉባልተ ድረ ገጾች እንዲጋለጡ አድርጎአል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎንም የቤተ ክርስቲያኒቷ ሐዋርያዊ አገልግሎትና ወቅታዊ እንቅስቃሴ በተመለከተ በአግባቡ ለሕዝቡ እንዲዳረስ በማድረጉ ዙሪያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ ሃያ ምርጥ ድረ ገጾች የሚያስብል ጠቀሜታ አስገኝቷል፡፡

የቅዱስ ፓትርያርኩ ሐዋርያዊ አገልግሎትን በተመለከተ

ይህንን የማደራጃ መምሪያው ሕጋዊ ድረ ገጽ ቅዱስ ፓትርያርኩ በተለያየ ጊዜ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ያደረጉትን ሐዋርያዊ አገልግሎት ዓበይት በዓላትን አስመልክተው ያስተላለፉትን ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ በሰፊው አስተላልፎአል፡፡ በተጨማሪም ወጥነት ያለው አገልግሎት ለማስፈን ያስተላለፏቸውን ሰርኩለር መመሪያዎች በሙሉ በጽሑፍ በምስልና በድምጽ ወምስል /በቪድዮ/ መልኩ አስተላልፏል፡፡

በመሆኑም ዋና ዋናዎቹ በድምጽ ወምስል /በቪድዮ/ ከተላለፉት መካከል
- የ2007 ዓ.ም የዘመን መለወጫ የእንኳን አደረሳችሁ አባታዊ መልዕክት
- የመስቀል ደመራ ሙሉ የበዓሉን አከባበርና የቅዱስ ፓትርያ ትምህርታዊና ቃ ምዕዳን
- የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በተመለከተና የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ

በጽሑፍና በምስል የተላለፉትን በተመለከተ

ከላይ የተዘረዘሩትን የቅዱስ ፓትርያርኩ ሐዋርያዊ አገልግሎቶች በሙሉ በጽሑፍና በምስል /በፎቶ/ የተደገፈ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም በቅዱስ ፓትርያርኩ የሚተላለፉትን የሰርኩለር መመሪያዎች ወቅቱንና ሰዓቱን ጠብቀው እንዲተላለፉ በማድረግ ከአገልጋይ ጀምሮ አስከ ምዕመን ድረስ በአስቸኳይ መመሪያውን እንዲያውቀና ተግባራዊ እንዲያደርጉ ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሌሎች ግሎጎችና ዌብሳይቶች የሚጻፉ የስሕተት መረጃዎች እውነታዎችን ማለትም እስከነ መረጃና ማስረጃ በማውጣት የመረጃ ሚዛኑን በተቻለ መጠን እንዲጠበቅ አድርጓል፡፡

ከዚህም በተጨማሪም የመልእክት ዓምድ ራሱን ችሎ በመክፈት በድምጽ በምስልና በጽሑፍ የዋና ሥራ አስኪያጅ የምክትል ሥራ አስኪያጅና በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኗ መሪዎች የሚያስተላልፉትን መልእክቶች በማስተላለፉና ምዕመናንም የመሪዎቻቸው መልእክት በሕጋዊ መንገድ እንዲያውቁ በማድረግ የነበረውን የውሸት ዌብ ሳይቶች በማጋለጥ የመረጃ ሚዛኑን ለማስተካከል ተችሏል፡፡

ትምህርተ ሃይማኖት በተመለከተ

ከሊቃውንት ጉባኤ የሚጻፉ የቤተ ክርስቲያናችን መሠረታዊ አስተምህሮዎች ለሕዝቡ በአግባቡ እንዲደርስ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በዚህም ከትምህርተ ሃይማኖት ጽንሰ ሐሳብ ጀምሮ እሰከ አእማደ ምሥጢር ድረስ በሊቃውንት ጉባኤ እየተዘጋጀ መንፈሳዊ ዕውቀት የሚሰጡ ትምህርቶች በዌብሳይቱ አርታእያን እየተመረመሩ በመሰራጨት ላይ ይገኛሉ፡፡

ሰንበት ት/ቤቶችን በተመለከተ

የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የከፈተው ዌብሳይት በዋናነት የሀገርና የቤተ ክርስቲያን ተረካቢ የሆነው ወጣቱ ትውልድ ማዕከል አድርጎ ነው፡፡ በመሆኑም የተለያዩ የጥበብ እውቀት ያላቸው የሰንበት ት/ቤቶች ምሁራን ጥበባዊ በሆነ መልኩ የሚያዘጋጁት መንፈሳዊ ኪነ ጥበብ የወጣቶች ትምህርትና የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች እየተመረመሩ በመሠራጨት ላይ ይገኛሉ፡፡

ገዳማትን በተመለከተ

ዓለም አቀፍ ክብርና አድናቆትን ያተረፉ ገዳማቶቻችን በዓለም የሚገኘው ሕዝብ ተመልክቶ በገዳማት ዙሪያ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው የተለያዩ የገዳማት ታሪኮችን የሚሰተናገድበት ዓምድ ከፍቶ ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ያሉትን ገዳማቶቻችን በማስተዋወቅ ለዓይ እንገኛለን፡፡

የተለያዩ ገዳማትን የተመለከቱ የምሁራን ጽሑፎችም እየተመሩ በመሠራጨት ላይ ይገኛል፡፡

ዜናዎችን በተመለከተ

በየጊዜው የሚፈጸሙ የቤተ ክርስቲያኒቷ ሐዋርያዊ አገልግሎት እና ወቅታዊ እንቅስቃሴን በሚመለከት ወቅቱን ጠብቆ ለምእመናን እንዲዳረስ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

በአንጻሩ በተለያዩ የውሸት ዌብሳይቶችንና ብሎጎችን የሚጻፉ ውሸቶች መልስ በመስጠት ሁሉንም መረጃ በማስደገፍ በመሠራጨት ላይ ይገኛል፡፡

የቅዱስ ፓትርያርኩ መልእክቶች ትምህርቶችና ቃለ ምዕዳኖች እንዲሁም ሐዋርያዊ ጉዞዎች በጽሑፍ በድምጽና በምስል እንዲወጣ በማድረግ ምዕመናን የቤተ ክርስቲያናቸውን ሐዋርያዊ እንቅስቃሴ በወቅቱ እንዲያገኙ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ያጋጠመው ፈተናዎች፤

- የበጀት እጥረት፡-

ይህም ማለት ማደራጃ መምሪያው በሚያቀርበው ዓመታዊ እቅድና የበጀት ጥያቄ የሚፈቀድለት የበጀት መጠን ሥራው ለማሳካት ከሚቀርበው እቅድ ጋር የማይመጣጠን መሆኑ፤ ከዚህም የተነሳ በሀገር አቀፍ የወጣ የሥልጠ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር ለማጠፍ ተገዷዋል፤

• ብቁ የሆነ የሰው ኃይል አለመመደብ፤
• የመልካም አስተዳደር እና የፍትሕ እጦት የፈጠረው ችግር፤

ሀ/ ወጣቶች በየቦታው እየተንገላቱና እየታሰሩ ናቸው፤
ለ/ ሕጋዊ የወጣት ሰንበት ትምህርት ቤት እያለ ከመዋቅር ውጭ የደብር አለቃ ጸሐፊ በተጓዳኝ የጽዋ ማሕበራት እያደራጁባቸው ነው፤
ሐ/ የሰንበት ትምህርት ቤት ሥራ አመራር መብታቸው በሕግ አግባብ ሲጠይቁ ከአጥቢያ እስከ ሀገረ ስብከት ድረስ ያሉ ኃላፊዎች ችግራቸውን ተረድተው በአግባቡና በወቅቱ አይፈቱላቸውም፤
የማሕበራት ወሰን የለሽ እንቅስቃሴና ጣልቃ ገብነት በወጣቶች ላይ፤

- የመከፋፈል ዝንባሌ እንዲያዳብሩ ማድረጉ
- በአሁን ጊዜ እንደየራሳቸው ግንዛቤና ፍላጎት ማሕበር አድርገው የተደራጁ ከ86000 ደርሰዋል፡፡ እነዚህም ማኅበራት ከአጥቢያ እስከ ላዕላይ መዋቅር ከወጣቱ እስከ መድረኩ ያለው አገልግሎት ላይ የሚያደርጉት ተፅእኖ ገንቢና ኦርቶዶክሳዊ እንዲሆን የሚያስችል ስልት፣ መመሪያና አቅም የለንም፡፡

ለእነዚህም ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች ወደ ጠቃሚ የአደረጃጀትና አስተዋጽኦ የማድረግ ዕድል እንዳይለወጥ አዝጋሚ ከሚያደርጉ ሁኔታዎች መካከል የሚከተሉት ታይተዋል፡፡


1. የሰንበት ት/ቤቶችን ጠቀሜታ በአግባቡ ያልተረዱ ወይንም ባላቸው የተዛባ ግንዛቤ ምክንያት ለሰ/ት/ቤት ወጣቶች ጥላቻ ያላቸው አለቆችና ካህናት፤
2. አንዳንድ የሰንበት ት/ቤቶችን እድገት ከቤተክርስቲያን ሌሎች አገልግሎቶች አንጻር ተገቢ ትኩረት የማይሰጡ ወይንም የተለየ ፍላጎት ያላቸው የስብከተ ወንጌል ኃላፊዎችና ሰባክያን ትብብርም ድጋፍ መንሳት፡፡ ከዚያም አልፎ ወላጆችና የአጥቢያ ሠራተኞች አዎንታዊ አመለካከት እንዳይኖራቸው ማድረግ፤
3. የምእመናን ግንዛቤን በተገቢው ደረጃ ባለማሳደጋችንና የሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን አካላት ከንስሐ አባቶች እስከ ከፍተኛ ኃላፊዎች ድረስ የሰ/ት/ቤቶችን ልዩና የተሻለ አማራጭ እስካሁን ያላበጀንለት የቤተ ክርስቲያናችንን ቀጣይነት ላይ ከፍተኛ ሚና ያለው ተቋም ለመደገፍ አለመነሳሳት፤
4. ሰ/ት/ቤቶች አባላት የወጣቶች ስብስብ በመሆኑ የተለያዩ ከኦርቶዶክሳት ቤተ ክርስቲያን ውጭ የሆኑ አካላት ሁሉ ትኩረታቸውን ያርፍባቸዋል፡፡ ከዚህ የተነሳ ወጣቶች በተለያየ አካላትና በዘመናዊ ተቋማት ተቋሟዊና ስነ ልቦናዊ ጣልቃገብነት ናቸው፡፡

ችግሮችን ለመፍታት የተወሰዱ የመፍትሔ አቅጣጫዎች፡-

 •  ግልጽ የሆነ የወጣቶች ራዕይና እስትራቴጂ ማስቀመጥ፣ ይኼንን በየሀገረ ስብከቱ እንዲታወቅ ማድረግ፤
 • ሀገር አቀፍ ጠቅላላ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት፣ ሀገረ ስብከት አቀፍ ጠቅላላ የሰንበት ትምህርት ቤት አንድነት ጉባኤ፣ ወረዳ አቀፍ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ጠቅላላ የሰንበት ትምህርት ቤት አንድነት፣ አጥቢያ አቀፍ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አደረጃጀት ማጠናከር፤
 • አደረጃጀቱን ለመምራት የሚያስችል የውስጥ መመሪያ በቅዱስ ሲኖዶስ አጽድቆ ተግባር ላይ ማዋል /ጸድቆ በተግባር ላይ ውለዋል/፤
 •  የ2006 ዓ.ም እና የ2007 ዓ.ም ዝርዝር የድርጊት መርሐ ግብር ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ድረስ በማውረድ እንዲሰሩ ተሞክሯል፣ ይህ ግን ጠንከር ያለ ግብረ መልስና ትምህርት እየተወሰደ የማሻሻል ምክክር ሊደረግበት ይገባል፤
 • የሁሉም የሰንበት ትምህት ቤቶች አደረጃጀቶች የሥራ እንቅስቃሴ በማዕከል ሆኖ መቈጣጠርና መከታተል እንዲቻል የሀሳብ ልውውጥና ስልት መንደፍ ሲሆን በተለይ የትምህርትና የመዝሙርን ወጥነት ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለው አንደኛው ጥረት ነው፡፡

2008 ቅድሚያ የሚሰጣቸው ተግባራት

1. ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ኃላፊዎች ጋር ጉባኤ በማካሄድ የመጀመሪያውን እ ማስተዋወቅና የአጭር ጊዜ የሥራ ዝርዝር አፈፃፀም ላይ ትብብር መጠየቅ፣ ለሚመለከታቸው ሁሉ ደብዳቤ መጻፍ መመሪያ እንዲሰጥ ማድረግ፤
2. የጥናት መጠይቆችን፣ ፎርሞችን ማዘጋጀት፣ የመረጃ አሰባሰብና የምንጭ መረጣ ፕሮቶኮሎችን መወሰን፣ መረጃ ለሚሰበስቡ አባላት ፕሮፋይል ማዘጋጀትና ሥልጠና መስጠት፣
3. በየወረዳው /አጥቢያው ያሉ የኢኮኖሚ እድሎች ምዝገባ
a. የቤተ ክርስቲያን የልማት ጅምሮች
b. ኦርቲዶክሳዊ ቅናት ያላቸው ባሀብቶች ዝርዝር
c. ወጣቶችን ክህሎት እውቀት የማሳደግ ዕድሎች
4. በየአጥቢያው ያሉ ቤተሰቦች ልጆቸው በጾታ፣ዕድሜ በትምህርት ደረጃ ከንስሐ አባቶቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት መመዝገብ፤
5. የሰ/ት/ቤት አባል ያልሆኑ፣ ያልሆኑበት ምክንያት ሃይማኖታዊ ኢኮኖሚያዊ ሌሎች ምክኒያቶችን የቅሬታ ምንጭ ምን ቢሻሻል ወጣቶችና ሕፃናት ወደ ቤተ ክርስቲያን እንደሚልኩ መጠየቅ፤
6. አሁን ባሉበት ሁኔታ ሰ/ት/ቤቶች በየአጥቢያው ያላቸው አመቺ የመማሪያ ሁኔታና መሟላት የሚገባቸው ነገሮችን መመዝገብ መተንተን
7. የኑሮ ችግር ያለባቸው ወጣቶችና ሕፃናት ያለባቸውን ችግር መጠን በችግሩ መጠን ምላሽ መስጠት የሚያስችል የአካባቢ አቅም ይህን አቅም እንዴት ማስተባበር እንደሚቻል ማጥናት፤
8. የሥነ ምግባር ቁጥጥርና ምክር ሰጭ ግብረ ኃይል በመሆን በፈቃደኝነት አገልግሎት የሚሰጡ ግለሰቦችን ማነጋገርና ስማቸውን ማንነታቸውን መመዝገብ፤
9. በአሁኑ ጊዜ የበየሰ/ት/ቤቶች በሥራ ላይ ያለው የትምህርትና የሥልጠና ይዘቶች ያላቸው ጽሑፎችን ኮፒ ማሰባሰብና በሚገባው ዘርፍ ከፋፍሎ በፋይል መላክ፤
10. አሁን በየሰንበት ት/ቤቶቹ የሚዘመሩ በካሴትና በሲዲ የታተሙትን መዝሙሮችን ርዕስና ዘማሪ ዝርዝር በአጥቢያውና በአካባቢው ተደርሰው የሚዘመሩትን ስከነ ስንኛቸው ጨምሮ መመዝገብ
11. የሰ/ት/ቤት አባላት ትምህርት ጨርሰው ሥራ ባለማግኘታቸው የተቀመጡ ልዩ ፈጠራ እያላቸው መተግበር ያልቻሉትን የተለያዩ ራስን የመርዳ ጥረት የሚያደርጉትን ዝንባሌዎቻቸውን የሚያሳይ መረጃ መሰብሰብ፤
12. የሰ/ት/ቤት ለሥራ የደረሱ ወጣት አባላት አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሁኔታን ለማሻሻል ሊደግፉ የሚችሉ በየአከባቢው ያሉ እድሎችን መመዝገብ፤
13. የምግባረ ሠናይ ልምዶች የተጠቃሚ ብዛት፣ የዚህ አገልግሎት መጨመር ወይንም መቀነስ ሁኔታ የሚያይ ጥናት /መረጃ/ ለወደፊቱ ምን ማድረግ እንደሚቻል የሚጠቁም ተጨባጭ ሁኔታ፤
14. በየአከባቢው ያሉ ተቋማዊ ማኅበራዊና የእውቀትና የተለያዩ አቅሞችን ለምሳሌ ጊዜ መስጠት የሚሉ መምህራን ሙያቸውና ሊሰጡት የሚችሉ የጊዜ መጠን ለወጣቶችና ሕፃናት አገልግሎት መስጠት የሚችሉና ፈቃደኛ የሆኑ በክርስትናቸው ርቱዕነት የሚመሰገኑ የማይጠረጠሩ አገልጋዮች ብዛትና መስጠት የሚችሉት አገልግሎት ኢኮኖሚያዊ ድጋ መስጠት የሚሉ ፈቃደኛ ግለሰቦች ወይንም የተደራጁ ቡድኖች በአቅማቸው መንፈሳዊ እንጂ ድብቅ አጀንዳ የሌላቸው መመዝገብ፤
15. በ2007ዓ.ም ያልተፈጸሙ የድርጊት መርሐ ግብር የ2008ዓ.ም የሥራ አካል ሆኖ ተፈጻሚ ማድረግ
16. በተዋረድ ከላይ እስከ ታች መዋቅር መሠረት ማስተባበር
17. የመዝሙረ ማኅሌት መጽሐፍ ወደ ድምጽ መለወጥ /መቅረጽ/
18. 2ኛ ዙር የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት
19. የታተመው ሥርዓተ ትምህርት ወደ ተለያዩ ቋንቋዎች መተርጎም
20. በመላ ሀገሪቱ ሥልጠናና ግምገማ ማካሄድ የሚሉ ናቸው፡፡

ማጠቃላያ፤

የቀረውንም ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብደኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሐሳብ ነው 2ኛ.ቆሮ. ምዕ. 11፡28
በአሁን ጊዜ ከምንም በላይ መምሪያው የሚያሳስበው የምዕመናንና የወጣቶችን ክርስቲያናዊ ሕይወት እና ኑሮ ነው፡፡ በአሁን ጊዜ የማይመለከታቸው አካላትና ምናልባትም ቦታውን ይመራሉ ተብለው በየቦታው የተመደቡ አንዳንድ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ወጣቱ ለሚያነሳው የመብት ጥያቄ ቀጥታ መልስ ከመስጠት ይልቅ የተለያዩ የስም ማጥፋት ስም በመስጠት ወጣቶችን መክሰስና ማንገላታት ተግባራቸው ሆኖአል፡፡ ይህ የተሳሳተ አመለካከት መቅረት አለበት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ወጣቶች በሕግ የተደራጁ ለሀገር እና ለልማት ወደር የሌላቸው እንጂ እንጀራ የጠራቸው አገልጋዮች አይደሉም፡፡ መምሪያው ሁሉ እንዲያውቀው የሚፈልገው የሚያደራጃቸው ወጣቶች የሕዝብ ልጆች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች እንጂ የማንም ማሕበር ደጋፊም አይደሉም፡፡ ማንም በፈለገው መጠን የሚያሽከረኩሯቸው አይደሉም፡፡ በራሱ የሚያስብ በራሱ የሚመራ የሀገርና የቤተ ክርቲያን ተረካቢ ብቁ ዜጋ ነው፡፡ በተሳሳተ አቅጣጫ የሚያስቡ የቤተ ክርስቲያን አካላት ካሉ መምሪያው ትክክለኛ አቅጣጫ እንዲይዙ ይጋብዛል፡፡ ሐዋርያው ከላይ እንደገለጸው መምሪያው የሚያሳስበው የወገን ድህነት የወጣቶች ከሥነ ምግባር መውጣት፣ በሀገር ሠርቶ ማደግ ሲቻል ወደስደት የሚያመራው ወጣት እንዴት በጋራ ሆኖ ችግሩ መቋቋም ይቻላል በሚለው ጉዳይ ስለሆነ ከወጣቶች ጋር ተከታታይ ውይይት በማድረግ ለውጥ እንዲመጣ ይሠራል፡፡

"ስብሐት ለእግዚአብሔር ለአብጽሐነ እስከ ዛቲ ሰዓት"
መምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ኃላፊ
ግንቦት 21 ቀን 2007 ዓ.ም
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ

 

 

የፎንት ልክ መቀየሪያ