Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፤

 

 • ክቡር ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር
 • ክቡር አቶ ሙሉጌታ ሚኒስትር ዲኤታ
 • የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፤
 • በአጠቃላይ በዚህ ዓቢይ የሰላም ኮንፈረንስ ላይ የተገኛችሁ ሁሉ፤

የሰላም አምላክ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ጉባኤ ተገኝተን የሰላምና መቻቻል መልእክት ለማስተላለፍ ስለፈቀደልን ምስጋና፣ አምልኮትና ክብር ለእርሱ ይሁን ፡፡

ኅሣሣ ለሰላም ወዴግና፤ ሰላምን አጥብቀህ ፈልጋት፣ ባገኘሃትም ጊዜ ተከተላት እንጂ አትለያት (መዝ 33፡14)


ሁላችንም እንደምናውቀው የሰላም አምላክ እግዚአብሔር ፍጥረታትን ሲፈጥር በሕይወት፣ በነጻነትና በደስታ እንዲኖሩ ነው፤


የሕይወት፣ የነጻነት፣ የደስታና የብልጽግና ዋስትና ሰጭ ደግሞ ከፈጣሪ የተገኘች ሰላም ናት፤ ሰላም ሰውን ብቻ ሳይሆን ከሰው ጋር ያሉ እንስሳት፣ ዓራዊት፣ አዕዋፍ፣ ዓሣት፣ ዕፅዋት፣ አዝርእት፤ ነፍሳት ወዘተ ሁሉ ይፈልጓታል ፡፡
ከዚህም ሌላ ሰማዩም ምድሩም ሰላምን ይፈልጋል፤ ምክንያቱም ሰላም ከሌለ ሁሉም ተጎጂዎች ናቸውና፤


ዛሬ የሰማዩ አየር በአየር ብክለት እየተጎዳ ሰላምን አጥቶአል እየተባለ በየጊዜው ሲነገር እንሰማለን፤


ምድርም እንደ ልብስ የሚያገለግሏት ዕፅዋት እየተመነጠሩ ባዶ ወደ መሆን እየተቃረበች ስለሆነ በተፈጥሮ መዛባት ሰላምን አጥታለች እየተባለ ነው ፡፡


ሰማይና ምድር በዚህ ኩነት ሰላምን ሲያጡ የሚኖሩባቸው ፍጥረታት በአጠቃላይ ሰላምን አጥተው ይሰቃያሉ ፡፡


ከዚህ እውነት ተነሥተን ስናስተውል ሕያዋንም ሆኑ ግኡዛን፣ ሰማያውያንም ሆኑ ምድራውያን ፍጥረታት ሁሉ የሰላም ተጠቃሚዎች መሆናቸውን እንገነዘባለን ፡፡


እግዚአብሔር የሰላም አምላክ ነው ሲባል የተጠቀሱ ፍጥረታት ሁሉ ገንዘቦቹ ናቸውና፣ ያመጣቸውም በሕይወት እንዲኖሩ እንጂ በሰላም እጦት እንዲጠፉ አይደለምና፣ ሰላም እንዲያገኙ አምላካዊ ፈቀዱ ከመሆኑም ባሻገር እርሱ ራሱ በባህርዩ ሰላምና ፍቅር ስለሆነ ነው፡፡ (1ዮሐ. 4፡16)


ሰዎች በበደላቸው ብዛት ሰላም እንዲደፈርስ ባደረጉ ጊዜም ሰላምን ለመመለስ ሲል በሰው መካከል በተገኘ ወቅት ‹‹ወሰላም በምድር፤ በምድርም ሰላም ይሁን›› ብለው መላእክት መዘመራቸው እግዚአብሔር ለሰላም የሰጠው ዋጋ ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ የሚያመለክት ነው (ሉቃ.2፡14)


ለሰላም ሲባል አምላክ ሰው ሆኖአል፣ ለሰላም ሲባል አምላክ በሥጋ ሞቶአል፣ በዚህም ሰማይንና ምድርንም አስታርቆ ሰላምን አድርጎአል፤ ‹‹ወገብረ ሰላመ በደመ መስቀሉ፤ ለዘበሰማይ ወለዘበምድር፣ በሰማይና በምድር ያሉትን በመስቀል ላይ ሆኖ ባፈሰሰው ደሙ ሰላምን አደረገላቸው (ቈላ 1፡20)

 

- ክቡር ሚኒስትር!

- ክቡራን እንግዶች!


ኃላፊነት ያለባችሁ አካላት ዛሬ በዚህ ስፍራ ስለሰላምና ስለመቻቻል ጠቃሚነት ለመወያየት ይህን ዓቢይ ጉባኤ ስታዘጋጁ የእግዚአብሔር ልዩ መልእክተኞችና አገልጋዮች ሆናችሁ እንደመጣችሁ እንቈጥራለን፤


የሰላምና የመቻቻል ህልውና ለአንድ ማኅበረሰብ በእምነቱም ሆነ በኑሮው ምን ያህል ትልቅ ዋጋ እንዳለው፣ የሚያመጣውም ለውጥ ምን ያህል ግዙፍ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከምንም ጊዜ በላይ የተገነዘበበት ወቅት ዛሬ እንደሆነ በተግባር አስመስክሮአል፡፡


ይህ ሰላምና መቻቻል እስከተጠበቀ ድረስ የተወጠነውና ሊወጠን የታሰበው ሁሉ እውን የማይሆንበት ምክንያት ይኖራል ብለን አንገምትም፡፡


ስለሆነም ሰላም የቤተ ክርስቲያን ተቀዳሚ ተልእኮ እንደመሆኑ መጠን ለሰላም መጠበቅና ተቻችሎ በአንድነት ለመኖር በሚደረገው ጥረት ሁሉ ቤተ ክርስቲያናችን በግንባር ቀደም ተሰልፋ የሚጠበቅባትን ከማድረግ ወደኋላ እንደማትል በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን ፡፡


ሰላምና መቻቻል ለሰው ልጅ ያላቸው ጠቀሜታ ላይ ጥያቄ ያለው ሰው ይኖራል ብለን አንገምትም፤


ይሁንና ደጋግመን መነጋገር ያለብን የሚመስለን ሰላምን እንዴት እንጠብቅ? መቻቻልን በኅብረተሰቡ ውስጥ እንዴት እናስርፅ? የሚለውን ነው ፡፡


ሁሉም እንደሚያውቀው ሰላም ስለተፈለገች ብቻ እንዲሁ የምትገኝ አይደለችም፤ ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ጌታችን እንኳ ሰላምን ለማምጣት የመስቀል መሥዋዕትነትን አስፈልጎታል፤


ጌታችን እንኳ ለሰላም መረጋገጥ መሥዋዕትነት የሚያስፈልገው ከሆነ እኛም ለሰላም ሲባል መሥዋዕትነት መክፈል እንደማይቀርልን ጥርጥር የለውም፡፡


በተጨባጭ እንደምናየውም አሁን ያገኘነው ሰላም በመሥዋዕትነት እንደተገኘ ሁላችንም እናውቃለን ፡፡


ዛሬም ልጆቻችን ለጎረቤት ሀገር ወገኖቻችን ሰላም ሲሉ መሥዋዕትነት በመክፈል ላይ እንደሆኑ የምንዘነጋው አይደለም፤


የአሁኑ ጥያቄአችን ለሰላም መሥዋዕትነት መከፈል ያለባቸው ጥቂት ወገኖች ብቻ ናቸውን? ወይስ በኃላፊነት የተቀመጡ ባለሥልጣኖች ብቻ ናቸውን? የሚለውን ነው፤


ይህ በፍጹም ሊሆን አይችልም፤ ሁሉም ሰው ይልቁንም የሃይማኖት መሪዎችና አገልጋዮች ከማንም በላይ ቀድመው የሰላም ጠበቆችና አምባሳደሮች ሊሆኑ ይገባቸዋል፡፡


ካህናቶቻችን በጸሎት ጊዜ ‹‹ሰላም ለኵልክሙ፤ ሰላም ለሁላችሁ ይሁን›› በማለት በተደጋጋሚ የሚያስተጋቡት ኃይለ ቃል በተግባርም ቀድመው ሊፈጽሙት ይገባል፡፡


ሰላም ከውጭ ተገዝቶ ወይም ተጎትቶ የሚመጣ ቁሳዊ ነገር አይደለም፤ ሰላም ከኅሊናችን ውስጥ መንጭቶ በአእምሮ ዳብሮ በተግባር የሚገለጽ ነገር ነው ፡፡


እኛ ካህናት ሰላምን በምድር ላይ ለማስፈንና ለመጠበቅ ከሁሉ በፊት ጌታችን ‹‹ቅድመ አውጽእ ሠርዌ ዘሀሎ ውስተ ዓይንከ ወእምዝ ትሬኢ ኃሠረ ዘውስተ ዓይነ ቢጽከ፤ አስቀድመህ በዓይንህ ውስጥ ያለውን ምሰሶ አውጣ፤ ከዚህ በኋላ በወንድምህ ዓይን ያለውን ጉድፍ ታወጣለህ›› ብሎ ያስተማረውን መሪ ቃል አድርገን መውሰድ አለብን ፡፡


ስለ ሰላም ነገር ሌላውን ለማስተማርና በሌላው ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረን ለማድረግ አስቀድመን እኛው ራሳችን ሰላምን በውስጣችን ማረጋገጥ አለብን ፡፡


እውነት ለመናገር ዛሬ በሰላም ውለው በሰላም የሚያድሩ የቤተ ክርስቲናችን ሹማምንቶች፣ ሠራተኞችና አገልጋዮች ስንት ናቸው? ይህስ ለምን ሆነ? ብለን ብንጠይቅ ብዙ ነገሮች በውስጣችን እንዳሉ እኛው እናውቀዋለን ፡፡


ታዲያ ይህን በውስጣችንና በጓዳችን ያለውን ሰላምና መቻቻል ሳናረጋግጥ ወደውጭ ወጥተን ሰላምን ብንሰብክ ማን ነው የሚሰማን? የዚህ መድኃኒቱስ ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ በዚህ ጉባኤ የተካሄደው ውይይት ግንዛቤን ያስጨብጣል ብለን እንጠብቃለን ፡፡

የዚህ መድኃኒት መገኛ ከባድና ገንዘብ የሚከፈልበት ባይሆንም ኅሊናን የማሳመንና የማስወሰን ከባድ ጀግንነትን ግን ሳይጠይቅ አይቀርም ፡፡ እርሱም ‹‹በቃ በውስጣችን ሰላምን እናስፍን የሚለው ቁርጥ ውሳኔ ይጠይቃል፤ ይህ እንዲሆንም እንጠብቃለን››የውስጣችን የሰላምና የመቻቻል ጠንቅ የሆኑት፤


- ግልጽነትና ተጠያቂነት፣ የሌለው አሠራር፤
- ሕግንና ሥርዓትን ማእከል ያላደረገ የሥራ አፈጻጸም፤
- የሕዝብንና የቤተ ክርስቲያንን ሳይሆን የራስን ጥቅም ማስቀደምና ወዘተ የመሳሰሉ አስተሳሰቦች የውስጥ ሰላማችንን ለማናጋት እየተፍጨረጨሩ ነው፤ እነዚህን ታግለን ለማስተካከል ወደ ቁርጥ ውሳኔ የሚያደርሰውን የኅሊና መሥዋዕትነት ይጠይቀናል፡፡


ይህንን መሥዋዕትነት በድል ካጠናቀቅን የሰላም አለቆች መሆናችን በተግባር ይረጋገጣል፡፡

 

በመጨረሻም

 

ሰላምና መቻቻል የሃይማኖታችንና የሀገራችን ህልውና ማረጋገጫዎች፣ የዕድገታችንና የብልፅግናችን ከለላዎች ናቸው፤ እነዚህን ለማስፈንና ለመጠበቅም መጀመር ያለብን ከውስጣችን ስለሆነ በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ መልካም አስተዳደርን በማስፈን፣ ግልፅነትና ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ የቤተ ክርስቲያናችንና የሕዝብ ሉዓላዊነትን ያለማወላወል በማስቀደም፣ ብክነትንና ዝርክርክነትን በመፀየፍ፣ እኛ አስቀድመን የመምሰል ሳይሆን የመሆን አለቆች ሆነን ሰላማችንን የመጠበቅ ተልእኮአችንን እንድንወጣ አደራ በማለት አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡


እግዚአብሔር ይባርካችሁ፤ ይቀድሳችሁ፤
አሜን!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ነሐሴ 30 ቀን 2007 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

የፎንት ልክ መቀየሪያ