Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

 • ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት
 •  የተከበሩ ....
 • ክቡራን አምባሳደኖችና ኮር ዲፕሎማቶች
 • የተከበራችሁ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን
 • የተወደዳችሁ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች
 • በአጠቃላይ በዚህ ዓቢይ በዓል የተገኛችሁና በየአካባቢው ሆናችሁ በዓሉን በማክበር ላይ የምትገኙ ሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ

በማየ ጥምቀት አማካኝነት ሀብተ ጽድቅንና ሀብተ መንፈስ ቅዱስን ያደለን እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ለሁለት ሺሕ ስምንት ዓመተ ምሕረት በዓለ ጥምቀተ ክርስቶስ በሰላም አደረሳችሁ፡፡

‹‹ወይደልወነ ከመ ንፈጽም ኵሎ ጽድቀ፤ እንግዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናል›› (ማቴ.3፡15)

ከሁሉ በፊት በዓለ ጥምቀቱን ስናከብር ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀበት ዕለት በቃልም ሆነ በድርጊት የፈጸማቸውንና ያስተማራቸውን ነገራተ ጽድቅ ሁሉ በልዩ ተመስጦና አንክሮ በማስታወስ ልናከብር ይገባል፡፡

ጌታችን በዚህ ቀን ከተናገራቸው ዓበይት ነገሮች አንዱ ‹‹ጽድቅን ሁሉ ልንፈጽም ይገባናል›› የሚለው ቃል ነው፤ ይህ መለኮታዊ ቃል ሰዎች በጥምቀት ሱታፌነት የእግዚአብሔርን ጽድቅ የሚያገኙበት ከመሆኑ አንጻር የማይታለፍ ጉዳይ እንደሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዮሐንስ አስረግጦ የተናገረው ኃይለ ቃል በመሆኑ የበዓሉ ዓቢይ ርእሰ - ትምህርት ነው፡፡

Picture 069 Picture 070 Picture 071 Picture 072 Picture 073 Picture 076 Picture 077 Picture 078 Picture 083 Picture 087 Picture 091 Picture 100 Picture 102 Picture 108 Picture 110 Picture 113 Picture 114 Picture 116 Picture 118 Picture 124 Picture 137 Picture 154 Picture 211 Picture 217 Picture 419 Picture 432 Picture 434 Picture 446 Picture 483 Picture 4o8

በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው ምግባረ ጽድቅ በሰማያውያኑም ሆነ በምድራውኑ ፍጡራን እንዲሁም በሥራዎቻቸው ሁሉ እጅግ አስፈላጊ ናት፤ ነገሮች ፈራቸውን ለቀው ወደመተረማመስ፣ ወደ ዓመፅ፣ ወደ ግጭት፣ ወደ ክፋት፣ ወደጭካኔ፣ ወደ ፍርድና ቅጣት እንዲያመሩ የሚገደዱበት ዋና ምክንያት ጽድቅ ስትዘነጋ ነው ፡፡

ጽድቅ የእግዚአብሔር ባህርይ መገለጫ፣ የሥራውና የፍርዱ መለኪያ ሚዛን ናት፤ የውሳኔውም ቀዋሚ ድንበር ናት፤ ጽድቅ ከእግዚአብሔር ባህርይ ውጭ የሆነች ባዕድ ነገር ሳትሆን፣ የባህርይ ገንዘቡ ሆና የኖረችና የምትኖር ናት፡፡

ፍጡራን ከጽድቅ መንገድ ሲወጡ ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሁሉ ይቋረጣል ወይም ይቆማል፤ ፍጡራን ከጽድቅ መንገድ ሲወጡ ጽድቅ ራስዋ ትወቅሳቸዋለች፣ ካልተመለሱም ትፈርድባቸዋለች፣ ትቀጣቸውማለች፡፡

ጽድቅ የእግዚአብሔር ባህርይ መገለጫና የፍርዱ መሣሪያ ስለሆነች ከእርሱ ተነጥላ አትታይምና ክፉውን ሁሉ ትጠላለች፤ እስከ መጨረሻም ትዋጋለች እንጂ፣ ከክፉ ነገር ጋር አትተባበርም፤ ፈጽማም አትስማማም ፡፡

ፍጡራን ከጽድቅ ጋር ሲጣሉ ከእግዚአብሔር ጋር በቀጥታ ይጣላሉ፤ ለዚህ አስረጅ የሚሆኑ ብዙ ፍጡራን አሉ፤ በተለይም ከቀዳማውያን ፍጡራን ወገን የሆነው መልአክ እርሱም ሳጥናኤል ‹‹ወሐሰት ርእሰ ዓመፃ፤ ሐሰት የዓመፅ ሁሉ ራስ ናት›› ሲል ቅዱስ መጽሐፍ እንደተናገረ የዓመፅ ሁሉ ራስ የሆነችው ሐሰትን መርጦና ወዶ ከጽድቅ ጋራ በተጣላ ጊዜ በቀጥታ ከእግዚአብሔር ጋር ተጣልቶአል፤ (መዝ.26፡12፤ ዘፍ.3. 1-16፤ ማቴ.4፡10፤)፡፡

ከጽድቅ ጋር መጣላት ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት እንደመሆኑ መጠን ከቅጣት ማምለጥ አይቻልምና ጽድቅ ራስዋ አጥፊን የመቅጣት ኃላፊነት ስላለባት አጥፊውን ፍጡር እርሱም ሳጥናኤልን ቀጥታለች፤ (ዘፍ. 3፡14፤ ቈላ.2፡15፤ ራእ. 12፡9፤)፡፡

ከጽድቅ ጋር የተጋጨ ሌላው ፍጡር የሰው ሁሉ አባት የሆነው አዳም ነው፤ እግዚአብሔር ጻድቅ ነውና የሚሰጠው ትእዛዝ ሁሉ ከጽድቅ ጋር የሚስማማ እንጂ የሚቃረን አይደለም፡፡

በመሆኑም አዳም ያለዓቅሙ አምላክነትን ሽቶ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን የጽድቅ ትእዛዝ ስለተላለፈ ጽድቅ ወቀሰችው፤ ፈረደችበት፤ ቀጣችውም፤ በዚህም ምክንያት አዳም ከጽድቅ ጋር በመጋጨቱ እርሱም፣ ልጆቹም በአጠቃላይ ተቀጡ፤ (ዘፍ. 3፡16-24፤ ሮሜ.5.12-14) ፡፡

ነገር ግን ጽድቅ አስተዋይ ናትና በጭፍን ሳይሆን በትክክል ትፈርዳለች፤ ጽድቅ የሳጥናኤልና የአዳም ጥፋት ልዩነት እንዳላቸው አልዘነጋችም፤ ጽድቅ የሳጥናኤል ኃጢአት ሌላ አሳሳችና ገፊ ሳይኖረው በራሱ ነጻ ምርጫና ፍላጎት በሐሰት የፈጸመው ከባድ ጥፋት እንደሆነ ታውቃለች፡፡

ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሳጥናኤል ወይም በግሪክ ስሙ ዲያብሎስ የስሕተት የዓመፅና የሐሰት ምንጭ መሆኑን ሲገልጽ ‹‹እውነት በእርሱ ስለሌለ በእውነት አልቆመም፤ ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፤ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና›› ብሎአል፤ (ዮሐ. 8፡44)፡፡

በሌላ በኩል አዳም ጥፋትን ሊፈጽም የቻለው እንደ ዲያብሎስ ከራሱ አንቅቶ ወይም ሆን ብሎ ሳይሆን አምላክ ትሆናለህ በሚል ቅስቀሳ በዲያብሎስ ተገፋፍቶ እንደሆነ በግልጽ ተቀምጦአል፤ (ዘፍ.3. 1-5 ራእ.12፡9)
ስለሆነም የአዳም ጥፋት ከዲያብሎስ ጥፋት የተለየ በመሆኑ በምሕረት እንደሚታይ ጽድቅ ራስዋ ተስፋን ሰጠች፤ ተስፋውም ጽድቀ እግዚአብሔርንና ፍትሐ እግዚአብሔርን በማይቃረን መልኩ እንደሚፈጸም በረጅሙ አናገረች፤ (ዘፍ.3፡15፤ 22፡17፤ ኢሳ.53፡11፤ ኤር. 23፡5-6) ፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚነግሩን ጻድቅ ሳይሆኑ ጻድቅ ከሆነው እግዚአብሔር ጋር መገናኘት አይቻልም፤ (2ቆሮ.6፡14-16፤ ሮሜ.3፡20-24)፡፡

በመሆኑም ሰው ወደ እግዚአብሔር ሊቀርብ የሚችለው ጽድቅን ሲያገኝ ብቻ ነው፤ በዚህ ውስጥ መሠረታዊ ጥያቄ ሆኖ ሊነሣ የሚችለው ዓቢይ ነገር ሰው እንዴት ጽድቅን አግኝቶ ጻድቅ ሊሆን ይችላል? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡

ቅዱስ መጽሐፍ ለዚህ ጥያቄ መልስ አለው፤ ይኸውም ሰው ጽድቅን ሊያገኝ የሚችለው በዋናነት ከእግዚአብሔር በሚያገኘው ወይም በሚሰጠው ጸጋ እንጂ በራሱ ጥረት ብቻ አይደለም የሚል ነው፤ (ሮሜ.3፡21-22) ፡፡

የደሴተ ቆጵሮስ ኤጲስ ቆጶስ የነበረው ሊቁ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በቅዳሴው ይህንን አስመልክቶ ሲናገር ‹‹ወሶበ ርእየ ከመ ኢበቊዐ ለአድኀኖ ዓለም ደመ ኵሎሙ ነቢያት ዘተክዕወ ዲበ ምድር እምደመ አቤል ጻድቅ እስከ ደመ ዘካርያስ ወልደ በራክዩ ፈነወ ለነ ወልዶ መድኅነ፤

ማለትም ከጻድቁ አቤል ደም ጀምሮ እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የነቢያት ሁሉ ደም ዓለምን ለማዳን ወይም ለማጽደቅ እንዳልበቃ ባየ ጊዜ አዳኝ የሆነው ልጁን ላከልን›› ብሎአል ፡፡

ከዚህ አንጻር ከጽድቀ እግዚአብሔር በስተቀር ሌላ ማጽደቂያ ያልተገኘለት የሰው ልጅ የእርሱ ጽድቅ ለእኛ ተቆጥሮልን በእርሱ የጽድቅ ስጦታ ጻድቃን እንሆን ዘንድ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመሥዋዕትነት ተሰጠን፤(2ቆሮ.5፡21)፡፡

በእርሱ መሥዋዕትነት በተገኘው ቤዛነት የእርሱ ሕይወት ለእኛ ተሰጠ፤ የእኛ ሞት ደግሞ ለእርሱ ሆነ፤ የምሥራቃውያን ዓምደ ሃይማኖት የሆነው ሶርያዊው ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬም ይህንን ሲገልጽ ‹‹ዘዚአነ ሞተ ነሥአ ወእንቲአሁ ሕይወተ ወሀበነ፤ የእኛን ሞት እርሱ ተቀበለ፤ የእርሱን ሕይወት ደግሞ ለኛ ሰጠን›› ብሏል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹ወበእንተ ኃጣውኢነ ውእቱ ተሰቅለ ዲበ ዕፅ በሥጋሁ ከመ ያውጽአነ እምኃጣውኢነ ወበጽድቁ ያሕይወነ፤ ማለትም እርሱ ስለ ኃጢአታችን በዕንጨት ላይ በሥጋው ተሰቀለ፤ ከኃጢአታችን ነጻ ያወጣን ዘንድ፣ በእርሱ ጽድቅም ያድነን ዘንድ ብሎአል›› (1ጴጥ. 2፡24) ፡፡

ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ‹‹አነ ውእቱ ፍኖተ ጽድቅ ወሕይወት፣ የሕይወትና የጽድቅ መንገድ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ይድናል›› ብሎአል፤ (ዮሐ.14፡6)

መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹ጸጋሰ ወጽድቅ በኢየሱስ ክርስቶስ ኮነ፤ ጸጋና ጽድቅ በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ›› በማለት ያረጋገጠው ይህንኑ ነው ፤ (ዮሐ. 1፡17) ፡፡

እንግዲህ ሰው ጽድቅን ሊያገኝ የሚችለው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ቤዛነት እንደሆነ በዚህ ሁሉ እንገነዘባለን፤

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት !

የጽድቅ መገኛው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቢሆንም ለሰው ሊሰጠው የሚችል በሱታፌ ሃይማኖት ወምግባር እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ይናገራሉ፤

ጌታችን ሊጠመቅ ወደ ዮሐንስ በመጣ ጊዜ ‹‹ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናል›› ሲል የተናገረው ቃል በሱታፌ ጥምቀት ምክንያት የሚገኘው ጽድቀ እግዚአብሔርን ሲያመለክት ነበረ፡፡

ጽድቀ እግዚአብሔር በአንድ ጊዜ ተሰጥቶ የሚጠናቀቅ ሳይሆን በጥምቀት ተጀምሮ በእግዚአብሔር ጸጋና በሰው ሱታፌ እያደገ ሄዶ በዳግም ምጽአተ ክርስቶስ በግልጽ የሚታይና የሚፈጸም ነው፡፡

ጌታችን ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናል ማለቱ እርሱ በመምህርነትና በመሪነት፣ ሰው በተጠምቆ ሱታፌነት፣ እግዚአብሔር አብ በጽድቅ ሰጪነት እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም በአንጽሖና በአክብሮ፣ የሚገናኙበት የጽድቅ መንገድ ምሥጢረ ጥምቀት መሆኑን ሲያመለክት ነው ፡፡

ሰው ከመጠመቁ በፊት ጽድቅን አያገኝም፤ አይሰጠውምም፤ ምክንያቱም ኃጢአተኛ ነውና፤ ነገር ግን ከጥምቀት በኋላ በተሳትፎ - ጥምቀት የእግዚአብሔርን ጽድቅ ይሰጠዋል፡፡

ከዚህ በኋላ የጽድቅ ሕይወት አንድ ብሎ ይጀምራል፤ በይቀጥላልም ሰው በሱታፌነቱ ከእግዚአብሔር ጋር ሆኖ በሃይማኖት ብቻ ሳይሆን በሥነ ምግባርም ጭምር ጽድቅን እያሰፋና እያሳደገ ከሠላሳ ወደ ስድሳ፣ ከስድሳ ወደ መቶ ደረጃ ያደርሳል፤ ከበዓለ ጥምቀት የምንማረው ዓቢይ ሃይማኖታዊ ትምህርት ይህ ነው (ማቴ.13፡23)፡፡

እዚህ ላይ ክርስቲያኖች ሁሉ ሊገነዘቡት የሚገባ ዓቢይ ነገር እግዚአብሔር በሁሉም ነገር አሳታፊ አምላክ መሆኑን ነው፤ እግዚአብሔር ምንም እንኳ የሚሳነው ነገር የሌለና ሁሉን የሚችል አምላክ ቢሆንም፣ በሥራው ሁሉ ፍጡራንን በአጠቀላይ፣ በተለይም ሰው የሥራው ተሳታፊ እንዲሆን በተፈጥሮ ሳይቀር ጸጋውን አብዝቶ ሰጥቶታል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ሕይወት ያላቸው ፍጡራን ሁሉ በዘር እንዲባዙ ማድረጉን እናውቃለን፤ ሆኖም መባዛት ያለተባትና እንስት ተሳትፎ እንዲሆን አላደረገውም፤ ቀጣይ የሆነ ዘር ወይም ትውልድ እንዲኖር የተባትና የእንስት ፆታዊ ተሳትፎ ወይም ውሕደት የግድ ያስፈልጋል፤ ይህ የሚያሳየው እግዚአብሔር በሥራው አሳታፊ አምላክ መሆኑን ነው ፡፡

የሰው ጽድቅም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ እግዚአብሔር ጽድቅን በጸጋው ቢሰጥም ያለሰው ተሳትፎ ግን የሚገኝ አይደለም፤ የእግዚአብሔርን ጽድቅ ለማግኘት ሰው የግድ ማመን አለበት፣ የግድ መጠመቅ አለበት፣ የግድ መቊረብ አለበት፣ የግድ በሥነ ምግባር አጊጦ መኖር አለበት፣ በሌላ አገላለጽ በሃይማኖትና በሥነ ምግባር ጸንቶ መኖር አለበት፣ ማለት ነው፤ ይህ ከሆነ ሰው በጽድቀ እግዚአብሔር ተሳትፎ አድርጎአል ማለት ነው፤ በመሆኑም ሰው በዚህ ብቻ ጻድቅ ሆኖ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይችላል፡፡

በሃይማኖት ላይ የሥነ ምግባር ተሳትፎ ከሌለ ግን ጽድቅ የለም፤ ጻድቅ መሆንም አይቻልም፤ ሥነ ምግባር ከሌለ ሃይማኖቱ ራሱ የሞተ ይሆናል ማለትም ጽድቅን አያስገኝም ተብሎ ተጽፎአልና፤ ጽድቅም ከሌለ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ የለም ይህ ደግሞ የሞት ሞት ነው (ያዕ.2፡18-26፤ ማቴ25፤1-46)፤፡፡

በዚህ ክርስቶሳዊ አስተምህሮና ሐዋርያዊ ትውፊት መሠረት ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ነገረ ድኅነትን በተመለከተ ሃይማኖትና ሥነ ምግባር የማይነጣጠሉና የአንድ ሳንቲም ገጽታዎች እንደሆኑ በማስረገጥ ሰው ሃይማኖትና ሥነ ምግባርን ጠብቆ በመኖር ይጸድቃል ብላ ታስተምራለች ፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናትና ምእመናን !

ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅን ሁሉ ለመፈጸም በፈለገ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ በተጠመቀበት ዕለት የተላለፈው መለኮታዊ ትምህርት ሰው ሃይማኖትንና ሥነ ምግባርን አንድ አድርጎ መያዝ እንዳለበት የሚያመለክት ነው፤

በዕለተ ጥምቀት ቃል በቃል የተላለፈው የእግዚአብሔር አስተምህሮ ‹‹ይህ ልጄ ነው፤ የሚላችሁን ስሙ›› የሚል ነው፤ (ማቴ3፡17፤ 17፡5)

ከዚህ መለኮታዊ ቃል እንደምንገነዘበው ‹‹ይህ ልጄ ነው›› የሚለው ኃይለ ቃል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር መሆኑን አምነን እንድንቀበል የሚያስገነዝብ ሲሆን ይዘቱ ሃይማኖትን ይመለከታል፤ (ዮሐ.1፡3)

‹‹የሚላችሁን ስሙ›› የሚለው ቃል ደግሞ ሃይማኖትንና ሥነ ምግባርን የሚመለከት ሆኖ ጌታችን ‹‹በእኔ እመኑ፤ በአባቴም እመኑ፤ መልካም የሠሩ ወደዘላለም ሕይወት፣ ክፉ የሠሩ ግን ወደ ዘላለም ኵነኔ ይሄዳሉ›› በማለት ሃይማኖትንና ሥነ ምግባርን የጽድቅ ምሰሶ አድርጎ ያስተማረውን ሰምተን በተግባር እንድንፈጽም የሚያስገነዝብ ኃይለ ቃል ነው፤ (ዮሐ. 14፡1፤ 5፡29)፡፡

በመሆኑም ታላቁና ተወዳጁ የጥምቀት በዓላችን ዛሬ ስናከብር የሃይማኖትና የሥነ ምግባር ዋና መገለጫ የሆነውን ‹‹ፍቅረ እግዚአብሔርና ፍቅረ ቢጽን (ባልእንጀራ መውደድን)›› በሕይወታችን ዘመን ሁሉ በተግባር ለመፈጸም ቃል በመግባት ሊሆን ይገባል፡፡

እግዚአብሔርን መውደዳችንን የምንገልፀው ለቅዱስ ቃሉ ታዛዥ በመሆን ብቻ ነው፤ ባልጀራችንን መውደዳችን የምንገልፀው ደግሞ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ‹‹ያለውን ለሌለው ያካፍል›› ብሎ ያስተማረውን በመቀበልና በተግባር በመፈጸም ባልንጀሮቻችንን እንደራሳችን አድርገን በመውደድ ነው ፡፡

ዛሬ ብዙ ባልንጀሮቻችን የሚለብሱትና የሚጎርሱት፣ የሚጠጡትም ጭምር አጥተው በከባድ ችግር ላይ እንደሚገኙ እየሰማንና እያየን ነው፡፡

በመሆኑም ለነዚህ ባልንጀሮቻችን ወገናዊና ወንድማዊ የሆነ ድጋፍ ይዘን በወቅቱ በፍጥነት ልንደርስላቸው ይገባል፤ ይህም ሌላው የበዓለ ጥምቀት ዓቢይ አስተምህሮና ተቀዳሚ መልእክት ነው ፡፡

 • በዓለ ጥምቀት ተራራው ዝቅ ይበል፤ ጎድጓዳው ይሙላ፤ ሁሉም ትክክል ይሁን እያለ እኩልነትን፣
 • በደመወዛችሁ ኑሩ እንጂ ማንንም አትቀሙ እያለ ግብረ ሙስና መጸየፍን፣
 • ነፍስ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይመልከት እያለ በሃይማኖት መዳንን፣
 • ለንሥሐ የሚሆን ሥራ ሥሩ እያለ የሥራና የአእምሮ ልማትን፣
 • ግብር ሰብሳቢውም፣ ወታደሩም፣ ፈሪሳዊውም፣ ሌዋዊውም፣ ሕዝቡም ሁሉ በአንድነት በማገናኘት አንድነትን፣
 • የሰላም ምልክት በሆነች በነጭ ርግብ አምሳል መንፈስ ቅዱስን በመግለጽ ፍጹም ሰላምን ያስተማረን፣ የሃይማኖት፣ የልማት፣ የእኩልነት፣ የአንድነትና የሰላም መምህራችን ነው ፡፡
 • ስለሆነም ጽድቀ እግዚአብሔርን በሃይማኖትና በሥነ ምግባር ተቀብለን፣ የልማት ሥራችንን አጎልብተን፣ የአንድነት፣ የሰላም፣ የእኩልነት፣ የመከባበር፣ የመተማመንና የወንድማማችነት ነባር ዕሤቶቻችንን ጠብቀን የተራቡ ወገኖቻችንን በማገዝና በመርዳት በዓሉን ልናከብር ይገባል፤ ጽድቅን ሁሉ ልንፈጽም ይገባናልና ፡፡
 • በመጨረሻም

 • ጥምቀት ማለት በመንፈስ ቅዱስ መታደስ ማለት ስለሆነ በዓለ ጥምቀቱን ስናከብር ሀገራችንን በልማትና በሰላም - ሕዳሴ ለመገንባት የጀመርነው ሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን መርሐ ግብር በተያዘለት አቅጣጫ በስኬት ለማጠናቀቅ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የሚገኙ መላ ኢትዮጵያውያን በሁሉም የሥራ መስክ በትጋትና በንቃት እንዲረባረቡ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን ፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ

መልካም በዓለ ጥምቀት ያድርግልን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አሜን
ጥር 11 ቀን 2008 ዓመተ ምሕረት
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

የፎንት ልክ መቀየሪያ