ማኅበረ ቅዱሳን የኦዲት ምርመራን አስመልክቶ ለጠቅላይ ቤተክህነት የጻፈው ደብዳቤ አግባብነት የሌለው መሆኑን ተገለጸ፡፡
ለቤተክርስቲያን ሁለገብ አገልግሎት ድጋፍ ሰጪ እንዲሆን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር የተቋቋመው ማኅበረ ቅዱሳን ለ19 ዓመታት ያህል በቤተክርስቲያንዋ የሒሳብ ምርመራ /ኦዲት/ተደርጐ የማያውቅ ብቸኛ አካል መሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡ ማኅበሩ በበኩሉ በውጭ ኦዲተሮችም ጭምር እንዳስመረመረ ቢገልጽም መረጃዎች እንደሚያስረዱት ግን ማህበሩ በውጭ ኦዲተር የተመረመረው የአንድ ዓመት ሒሳብ ብቻ እንደሆነ ነው፡፡ ይህም ቢሆን እንደጥሩ ጅምር በመቈጠር ቤተክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ሒሳቡ እንዲመረመር ባለሙያዎች አወዳድሬ እመድባለሁ ስትል፡-ማኅበሩ በበኩሉ በራሱ በውስጥ ኦዲተሮች እንደሚመረመርና በውጭ ኦዲተሮችም ጭምር እንደአስፈላጊነቱ እንደሚያስመረምር ገልጾ በቤተክርስቲያንዋ በኩል የሚደረግ የሒሳብ ምርመራ (ኦዲት)ግን እንደማይቀበል ከቃልም ባለፈ በጽሑፍ እምቢታውን ሲገልጽ መቆየቱ በዚሁ ገልጸን እንደነበር ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጂ ጠቅላይ ቤተክህነቱ ከማኅበሩ የተጻፈለትን ደብዳቤ በአግባቡ ከተመለከተ በኋላ ማኅበሩ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር የተቋቋመ በመሆኑ ከጠቅላይ ቤተክህነቱ የሚሰጡትን መመሪያዎች ማክበርና መታዘዝ ሲገባው በራሳችን እንጂ በቤተክርስቲያንዋ የሚደረግ የሒሳብ ምርመራ ለመቀበል ያስቸግረናል በማለት የጻፈው ደብዳቤ አግባብነት የሌለውና መዋቅሩን ያልጠበቀ መሆኑን ገልጾ አሁንም ማኅበሩ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤቱ ገለልተኛ በሆኑ ወገኖች ኦዲት እንዲደረግ የማዘዝ ስልጣን ያለው መሆኑ ተገንዝቦ በተለያየ ዘዴ ከማመካኘት ይልቅ በመታዘዝ ሒሳቡን በአግባቡ እንዲያስመረምር፤ የቁጥጥር መምሪያም ይህንን ሂደት ተከታትሎ አሁንም እንዲያስፈጽም በጻፈው ደብዳቤ አስታውቋል፡፡ የተከበራችሁ አንባቢዎች ጠቅላይ ጽሕፈት ቤቱ ለማኅበሩ የጻፈው ደብዳቤ ከዚህ ቀጥለን አቅርበናል፡፡
