በሃይማኖት ጉዳይ የተሳሳተና ሚዛናዊ ያልሆነ መረጃ መስጠት ይቁም፡፡

"ዕንቁ" መጽሔት ቅጽ 4 ቁጥር 55 ሕዳር 2004 ዓ/ም በፊት ለፊት ገጽ "አስደንጋጩ የክርስቶስ ፊልም ከጀርመን-ላሊበላ" በሚል ርእስ በተለይ ፊልሙ እንዲሠራ ከቤተ ክህነት ፈቃድ ተሰጥቷል የሚል ዘገባ ማውጣቱ ይታወቃል ፡፡

ፊልሙ ሃይማኖትን፣ትውፊትን፣ባሕልንና መልካም የሕዝብ አኗኗርን የሚቃረን ክርስትናንም የሚነቅፍ ይዘት ያለው በመሆኑ ጉዳዩን አስመልክቶ ለሕዝብ ተገቢ መረጃ መስጠቱ ባልከፋ ነበር፡፡ ነገር ግን የተሳሳተና ሚዛናዊነት የጎደለው መረጃ ከፍተኛ ጉዳት ስለሚያስከትል ጋዜጠኞች ጥንቃቄ ማድረግና ሙያዊ ሥነ ምግባርን መከተል ይኖርባቸዋል፡፡ ሊቃውንት ጉባኤ ፣ጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በጉዳዩ ዙሪያ ተጠይቀው የተሟላ ዘገባ ማቅረብ ሲቻል ጠ/ቤተ ክህነት ባልተጠየቀበት ሁኔታ ጉዳዩን እንደ ፈቀደ ብሎም ቸል እንዳለው በማስመሰል ሕዝብን የሚያሳስት መረጃ ማውጣት ተገቢ ካለመሆኑም በላይ ሊቃውንት ጉባኤን በጣም አሳዝኗል፡፡

በተለይ ሊቃውንት ጉባኤ ፊልሙ በዐጸደ ቤተ ክርስቲያን በአድባራትም ሆነ በገዳማት ከዚህም በላይ በማንኛውም ቦታ ተቀረጾ ለሕዝብ መቅረብ የለበትም ሲል የሰጠውን የውሳኔ አሳብ፣ቅዱስ ሲኖዶስም የጉባኤውን ጥናትና የውሳኔ አሳብ መሠረት በማድረግ ፊልሙ እንዳይቀረጽ የወሰነውን ውሳኔ፤ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ወደ ጎን በመተው፣ጉባኤ ሊቃውንትና ቅዱስ ሲኖዶስ 13 ማስተካከያ አሳቦች ሰጥተዋል፤በማለቱ እንዲሁም ጉባኤው ጽሑፉን መርምሮ የውሳኔ አሳብ ለማቅረብ ዐምስት ቀናት ብቻ የወሰደበት ቢሆንም ዐራት ወራት ፈጅቶበታል በማለት የተሳሳተ መረጃ ለሕዝብ በመድረሱ ይህን መረጃ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ አስፈልጓል፡፡

በቁጥር ል/ጽ/565/279/03 በቀን 8/11/ 2003 ዓ/ም ለሊቃውንት ጉባኤ የተጻፈ ደብዳቤ ደርሶት ጉባኤው የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ከ11/11/2003-15/11/2003 ዓ/ም ለዐምስት ቀናት ባደረገው ተከታታይ ስብሰባ 80 ገጾች ያሉትን የፊልም ጽሑፍ መርምሮ በ15/11/2003 ዓ/ም ለቅዱስ ሲኖዶስ የውሳኔ አሳብ አቅርቧል፤ በቀረበው የውሳኔ አሳብ መሠረትም ቋሚ ሲኖዶስ ጳጉሜን 1/2003 ዓ/ም ባደረገው ስብሰባ የቀረበው የፊልም ጽሑፍ፤

1.የክርስቶስን ቅዱስ ወንጌል በአገባቡ የማይገልጽና የማይተረጉም በመሆኑ

2.የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት፣ትውፊትና ታሪክ ያልጠበቀ በመሆኑ

3.የክርስቶስን አምላክነት፣መከራ መስቀሉን፣ ሕማሙን፣ ሞቱንና ትንሣኤውን ዝቅ አድርጎ በማሳየት የቀረበ ሆኖ በመታየቱ

4.ከቤተ ክርስቲያናችን ቀኖናና ትውፊት ውጭ መሆኑን የሊቃውንት ጉባኤ አጥንቶና ወስኖ ባቀረበው መሠረት ፊልሙ እንዲሠራ በሚስ ብርጊት ማርያ ሜየር የቀረበውን ጥያቄ አልተቀበለውም ሲል ወስኗል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የጠ/ቤ/ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ በቁጥር 7403/2789/2003 በቀን 18/11/2003 ዓ/ም ለትግራይ ምሥራቃዊ ዞን ሀገረ ስብከት ጽ/ቤትና ለሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በጻፉት ደብዳቤ ፊልሙ እንዳይሠራ፣ ቀረጻ ተጀምሮ ከሆነም እንዲቆም ይደረግ ዘንድ አሰታውቀዋል፡፡

ጳጉሜን 4 ቀን 2003 ዓ/ም ቋሚ ሲኖዶስ የወሰነውን ውሳኔ ለጠ/ቤ/ ክህነት ጽ/ቤት በሸኝ ደብዳቤ የላከ ሲሆን ጠ/ቤ/ክህነት በበኩሉ መስከረም 4 ቀን 2004 ዓ/ም ለጀርመን ኢምባሲ፣ መስከረም 11 ቀን 2004 ዓ/ም ደግሞ ለሁሉም አህጉረ ስብከት የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ በደብዳቤ አስታውቋል፡፡ በዚህም ምክንያት ፊልሙ እንዳይሠራ መከልከሉን አረጋግጠናል፡፡

ይህ ሁሉ ተሠርቶ ሳለ ጠ/ቤተ ክህነት ጉዳዩን አስመልክቶ የሠራውን ሥራ ጠይቆ ተገቢና ሚዛናዊ የሆነ መረጃ ለሕዝብ ማቅረብ እየተቻለ የተሳሳተና ሚዛናዊነት የጎደለው መረጃ ለሕዝብ በመቅረቡ ብዙ ሰዎች ጉዳዩን አስመልክቶ ጥያቄ በማቅረብ ላይ ናቸው፤ ምእመናን ትክክለኛውን ነገር ተረድተው ከሐሰተኛ ወሬ ራሳቸውን ይጠብቁ ዘንድ ጉባኤው ያሳስባል፡፡

እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን ከክፉ ነገር ይጠብቅ!

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ጉባኤ

ሕዳር 28 ቀን 2003 ዓ/ም

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

 
የፎንት ልክ መቀየሪያ