Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት"የቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ አስተሳሰብ ማበልፀግ" በሚል ርዕስ ለጠቅላይ ቤተክህነት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ለአዲስ አበባ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ያቀረቡት ትምህርታዊ ቃለ ምዕዳን

በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!

"ምክር ሠናይት ለኩሉ ዘይገብራ" ለሚፈጽማት ሰው መመካከር መልካም ናት

የተከበራችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን

የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች

 • በአዲሱ ዓመት በማስመልከት በአሠራራችን፣ በምእመናን አያያዛችንና ተመሳሳይ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መወያየት አስፈላጊ ነው ብለን በማሰባችን እንድንገናኝ ሁኗል።

 • ውይይት መልካም ነው። የእግዚአብሔር ቃልም የሚያስተምረን መመካከር ፤ መረዳዳትና መወያየት እጅግ አስፈላጊ እንደ ሆን ነው፡፡ ምክንያቱም ውይይት ግንዛቤን ያሰፋል፡ ለአንድ ዓላማ ያነሳሳል፤ ፍቅርና ሰላም ያሰፍናል፡ አንድ አመለካከት ይፈጥራል፣ መንገድ የሳተም ይመልሳል፣ የወደፊት አቅጣጫም ያስተካክላል።

 • ዛሬ የምንወያይበት ርእሰ ጉዳይ የቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ አስተሳሰብ ለማበልፀግ ነው።

የቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ አስተሳሰብ ማበልፀግ ለምን እንፈልጋለን ወይም ለምን እንዲኖር እንገደዳለን? ብንል?

ዘመን ይለወጣል፤ በዘመን ውስጥ የሚኖር ሰውም አስተሳሰቡ እንደየሁኔታው ይለወጣል። ይህ ለውጥ በአዎንታዊ ጎኑ እድገት ሲሆን በአሉታዊ ጎኑ ደግሞ ውድቀት ሊያስከትል ይችላል። ዘመን በመለወጡ እነዚህ ሁለት ነገሮች ሁልጊዜ አሉ። እኛም ለለውጡ አስተዋፅኦ አለን።

እኛ ለአዎንታዊ ለውጡ የምናደርገው አስተዋፅኦ የመሪ ድርሻ ይዘንና ሕዝቡን አንቀሳቅሰን ነው ? ወይስ እንዲሁ እንደ ነገሩ በተገኘ አጋጣሚ አጋጣሚውን እየመሰልን ? ብለን ልንጠይቅ ይገባናል፡፡በተለይ ደግሞ አዲስ አበባ ያለን የቤተክርስቲያን መሪዎች ይህ ጥያቄ በአንክሮ ልናየው ይገባል።

ቤተክርስቲያናችንና ሀገራችን በእናንተና በምእመናን ጸሎትና ጠንካራ ሥራ ፣ በመላ ሕዝባችን ጥረት እድገትዋና ሰላምዋ እውን እየሆነ ነው። ይህም በበለጠ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ለዚህም ታላቁን ድርሻ የያዝነው እኛው ነንና ጠንክረን ልንቀጥልበት ይገባናል፡፡


ዘመኑን ሳንዋጅ ቀርተን እንዲሁ እያዘገምን፤ አሠራራችን ለሀገርና ለወገን በሚጠቅም ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው መንገድ በሳል የሆነ አመራር የማንሰጥ ከሆነ ሳናስበው ራሳችንንና የምንመራውን ሕዝብ አደጋ ላይ ልንጥል እንችላለን፡፡

እናንተ የምታስተዳድርዋት በአዲስ አበባ የምትገኘው ቤተክርስቲያን ብንመለከት ከተማዋ የአፍሪካ የፖለቲካ መዲና፣ የዓለም አቀፍ የዲፕሎማት መነሃሪያ፣ የአፍሪካ የኢንቨስትመንት ማእከል ናት።

በተጨማሪ የብዙ ሙሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ ደራስያን፤ ተቺዎችና ተመሳሳይ ሥራ የሚሠሩ ሰዎች የሚገኙባት ዓለም አቀፍ ከተማ ሆናለች።

በከተማዋ የሚኖሩ ምእመናንና የምእመናን ልጆችም በትምህርትና በኑሮ እየበለፀጉ ናቸው፡፡ በመሆኑም ለውጡ በሚፈጥረው እድገት ስለ አሠራራችን በቂ እውቀት አላቸው ከውጭ የሚመጡ ሰዎችም ታላቅዋን ቤተክርስቲያን ከብዙ አቅጣጫ ይመለከቷታል፤ ጥንታዊት ስለሆነችም የዳበረ አሠራር እንደሚኖራት ይጠብቃሉ።

ስለዚህ ዘመኑ ጠንካራ በሁሉም ዘንድ የተከበረ የቤተክርስቲያን መሪና አገልጋይ ይፈልጋል። ምእመናንና ምእመናትም ታማኝ፣ ንጹሕ፣ በሳል፣ ስለነገሮች ሁሉ ቀድሞ የሚያስብና የሚያቅድ ፣ ስለቤተክርስቲያን ዕለት ዕለት የሚጨነቅና ጸጋ እግዚአብሔር የበዛለት ካህንና አገልጋይ ይፈልጋሉ፡፡

ራሳችንን ለመፈተሽ አንዳንድ ተጨባጭ ጥናቶችንና ኩነቶችን እንመልከት

ከሃይማኖታዊ ገጽታ ስናየው

 • ጥንታዊት፣ ተሪካዊት ሐዋርያዊትና ዓለም ዓቀፋዊት ፣ ለሀገር ብዙ አስተዋፅኦ ያደረገች የታላላቅ አባቶች መሪዎች መፍለቂያ የሆነች ቤተክርስቲያን አለችን፡

 • የብዝኃ ሕይወት መገኛም ናት

 • በአባቶቻችን ትጋት ያገኘናቸው ምእመናን በቁጥር የሚቀንሱበት ሁኔታ ተከሥቶአል፡፡

ለምሳሌ ባለፉት አሥር ዓመታት ብቻ በአዲስ አበባ 7 በመቶ ቀንሷል፤ ኦሮምያ 10% ቀንሷል፡፡ ደቡብ ክልል 7.8 በመቶ ቀንሷል፡፡ ይህ አኃዝ አሁንም እየቀጠለ እንጂ እየቀነሰ አይደለም። የምእመናን ቁጥር የመቀነስ ጉዳይ በአሉታዊ ጎኑ ሃይማኖታዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ለውጥ ያስከትልብናል፡፡

 • ሃይማኖታዊ ተልእኮአችንን መሠረት አድርገን ብንመለከት ወደ መንግስተ እግዚአብሔር የምናቀርበው ሕዝብ እያጣን መሆኑ ያሳያል፡፡

ከኢኮኖሚያዊ ዓቅም አኳያ ስንመለከት


የቤተክርስቲ ያን ሀብት እየቀነሰ ይሄዳል፤ ስለዚህ የሚዘጉ አብያተ ክርስቲያን እየበዙ ይሄዳሉ። ይህም እየታየ ያለው ነው፡፡

ከማኅበራዊ ገጽታ አንጻር ስናየው፤

የቤተክርስቲያን እሴቶች በሀገሪቱ የነበራቸውን ጠቀሜታ ይቀንሳሉ፤ ጥንታውያን እሴቶቻችን እየቀነሱ ከሄዱ የሃይማኖታችንና የሀገራችን መሠረታዊና ማኅበራዊ እሴቶች ይጎዳሉ፡፡ ይህ ወርቃማ ባህላችን ከተጎዳ ደግሞ ጭካኔ፣ ስግብግብነት፣ ስንፍና ወንጀል ይበዛሉ። ፈሪሃ እግዚአብሔር ይቀንሳል ብሎም ይጠፋል። የትውልዱ ሥነ ምግባር ይጎዳል። ይህም እየታየ ያለ አደጋ ነው።

የተጋረጡብንን አደጋዎች በመንፈሳዊ ኃይል ለመመከት ሃይማኖታችንንና መልካሙ ታሪካችንን በመጠበቅ ወደ ራሳችን መመልከት ግድ ይለናል። ምክንያቱም አደጋ ላይ እየጣሉን ያሉ ችግሮች አስቀድመን በመለየት መፍትሄ ማስቀመጥ የወቅቱ የቤተክርስትያን ጉዳይ ስለሆነ ነው።

እዚህ ላይ አንድ ጉዳይ ላንሣ

አንዳንድ ሰዎች ችግራችንን ግልፅ አድርገን እንወያይ ስንላቸው ሌሎች ሃይማኖቶች በኛ ላይ ሊዘባበቱ ይችላሉና ዝም ማለት ይሻላል ብለው ይመክራሉ። ይህ አባባል ምን ማለት ነው ብለን እንየው;;


1ኛ) በመመካከር ልናገኘው የምንችለው መፍትሔ እንዳናገኝ በችግር ውስጥ እየተሽከረከርን እንድንኖር ያደርጋል
2ኛ) በምንፈጥረው መፍትሔ ቤተክርስቲያን ለምእመናንና ለሕዝብ የምትሰጠው የተሻሻለ አገልግሎት እንዳይኖር ያደርጋል
3ኛ) የቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ ስራ በዘመኑ ስልት እንዳይቃኝና ሃይማኖታችን እንዳይስፋፋ ያደርጋል
4ኛ) የቤተክርስቲያንን ሃብትና ንብረት ያለምንም ቁጥጥርና የሚሰበስቡና የሚዘርፉ አንዳንድ ግለሰቦችና ማኅበራት ዝርፍያቸው አጠናክረው እንዲቀጥሉ ያስችላል
5ኛ) በዚህ ዘመን ማናቸውም የሚደረግ ነገር ሁሉ ለሕዝብ ያልተደበቀ በመሆኑምእመናን በየቀኑ እያዘኑበት ያለ ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡

ስለዚህ ችግራችንን ይዘን ዝም እንድንል የሚመክሩን የቤተክርስቲያን መሻሻልና መጠናከር የማይፈልጉ ወይም የችግሩን አሳሳቢነት ያልተረዱ ከማለት በቀር ሐሳቡ ዘላቂ ችንገርን ከመፍታት አንጻር መልስ የለውም፡፡

የብልሹ አሠራር አደጋ፣

በቤተክርስቲያን ቋንቋ ብልሹ አሠራር ማለት ትምህርተ ወንጌልን የሚጻረር አሠራር መፈጸም ማለት ነው።
በዝርዝር ስንመለከተው

 • ፍትህ ማጉደል፣ ፍትህንም ለማጉደል መደለያ (ጉቦ) መቀበል፣ በዘር፣ በአካባቢ በመደራጀት ንጹሑን ሰው መበደል፡ ያልደከሙበትን የሕዝብን ሀብት ያለ አግባብ ማባከን፡

 • ለምእመናን ትጉና መልካም አርአያ አለመሆን

 • ከራስ በላይ ለቤተክርስቲያንና ለሀገር አለመቆርቆር ፤ ዋነኛ የአደጋው መገለጫዎች ናቸው፡፡

ካለን ተጨባጭ ልምድ ለማስረዳት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ከአምስት በላይ ከሚሆኑ አድባራትና ገዳማት የተውጣጡ ምእመናንና ካህናት መልካም አስተዳደር አጥተናል በሚል በሰልፍ መጥተዋል

የአቤቱታው ጥቅል ይዘት ስንመለከተው

 • በቤተክርስቲያን የተሰጠው ኃላፊነት ተጠቅመው ለራሳቸው ጥቅም የሚሯሯጡ አንዳንድ ሰዎች መኖራቸው በአንዳንድ ቦታዎች ብቻ ሳይሆን በመዋቅር ውስጥ እንደሰንሰለት ተያይዘው ለራሳቸው ጥቅም የሚሰሩ ግለሰዎች መበራከት

 • ይህ ብዙዎች አስተዳዳሪዎች ባይወክልም በኃላፊነት ያሉ አንዳንድ ሰዎች የሚፈፅሙት በመሆኑ ለቤተክርስቲያን ቀጣይ ህልውና አደጋ እየሆነ መምጣቱ

 • ከሁሉም በላይ ምእመናን ከቤተክርስቲያን እጅግ የላቀ መንፈሳዊ ተግባር ስለሚጠብቁ ይህ ባልሆነበት ጊዜ ምእመናን ክፉኛ የመንፈስ ስብራት እየደረሰባቸው እንደሆነ ይታያል፡፡

መዋቅራዊ አሠራር ያለመጠበቅ አደጋ

 • ቤተክርስቲያን ግልፅ የሆነ መዋቅር ያላት ስትሆን በቤተክርስቲያን ስም የሚደራጁ ማኅበራትና ግለሰቦች መዋቅሩን ይፈታተናሉ

 • በቤተክርስቲያን ስም የሚንቀሳቀሱ ማኅበራት በቤተክርስቲያን ስም ከቤተክርስቲያን መዋቅራዊ ቁጥጥር ውጭ የሚንቀሳቀስ ሀብትና ንብረት ማካበት ፈፅሞ የተከለከለና በከባድ ወንጀል የሚያስጠይቅ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ እየተስፋፋ መሄዱ፡፡

 • በዚህ ወቅት የሚታየው የማኅበራት ዝንባሌም ሀብት ማካበት፣ለቤተክርስቲያን ብቻ የተፈቀደውን አሥራትና በኩራት ወደ ራሳቸው መሰብሰብ፣ ከቤተክርስቲያን እውቅና ውጭ ቤተክርስቲያንን በሚተካ መልኩ የውጭና የሀገር ውስጥ ሥራዎችን በሌለ ሥልጣን መሥራት

 • በሰበሰቡት ሀብት አባቶችን መከፋፈል፣ አልፎም የቤተክርስቲያን አገልጋዮችን ማሾም፤ ማሻርና ማስፈራራት ላይ መድረሳቸው ይህ አካሄድ ለአንዲት ቤተክርስቲያን ጥንካሬና ሕልውና ፍጹም አደጋ ነው።

 • በቤተክርስቲያን ስም ያለአግባብ ሀብትና ንብረት ያካበተ ማንኛውም ኃይል ባስፈለገ ጊዜ እምቢተኛ በመሆን ቤተክርስቲያንን ለመከፋፋፈል ሊዳርጋት ይችላል። ይህም ሌላው ትልቁ አደጋ ነው።

 • ሌላው አደገኛው ነገር ሕግና ስርአት የማይቆጣጠረው ማኅበር ጽንፈኛ አሸባሪ የመሆን እድሉ የሰፋ ነው። ምክንያቱም ሁሉንም መንገዶች ለራሱ ጠቅም ብቻ እንዲዉሉ ይፈልጋልና። በዓለማችን የምናየውና ንጹሐንን እየጎዳ ያለው ትዕይንት ሃይማኖታዊ ሽፋንን ይዞ ነው እንጂ ሃይማኖት ፀረ ሰላም ሆኖ አይደለም። ስለዚህ ሁላችንም ይህንን ያልተገባ አካሄድ ሥርዓት እንዲይዝ በአቋም ልንቃወመው ይገባል።

በመጨረሻ

ከላይ በዝርዝር የተመለከትናቸውን መሠረተ ሐሳቦች ለቤተክርስቲያንና ለሀገር የማይበጁ በመሆናቸው እያንዳንዳችን ራሳችንን በመፈተሽና በማፅዳት ችግሩን በዘላቂነት ለማስወገድ በሚደረግ ጥረት ሁላችንም የድርሳችንን እንድንወጣ በማሳስብ ይህ ውይይት ዓመቱን ሙሉ በተከታታይ ከሚመለከታቸው የቤተክርስትያን አካላትና ምእመናን እንደሚካሄድ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

ስለሆነም ምንም ጊዜም የማይቀለበስና የማይሸራረፍ የቤተክርስቲያናችን ልዕልና ንጽሕናና ቅድስና ሐቀኝነተና ፈሪሃ እግዚአብሔርን ተላብሰን በምናደርገው የማያቋርጥ እንቅስቃሴ በየስፍራው በኃላፊነት የምትገኙ ኃላፊዎች ከቅድስት ቤተክርስቲያናችን ጎን በጽናት እንድትሰለፉ አበክረን ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር ይባርካችሁ ይቀድሳችሁ

አሜን!!

 

የፎንት ልክ መቀየሪያ