Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

ፆታዊ ጥቃትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በማስመልከት በኢትዮጵያ የሀይማኖት ጉባኤ ምክንያት በተዘጋጀው ሀገር አቀፍ ጉባኤ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ያስተላለፋት መልእክት እና ቃለ ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
አሜን!!

 • ክቡራን የሃይማኖት መሪዎች፤

 • ክቡራን ሚኒስትሮች፤

 • ክቡራን ዲፕሎማቶች፤

በአጠቃላይ በዚህ ሀገራዊ የምክክር መድረክ የተገኛችሁ የጉባኤው ተሳታፊዎች በሙሉ፡፡

ከሁሉ አስቀድመን በዚህ ሀገራዊ የምክክር መድረክ ላይ ተገኝተን በሴት ልጆቻችን እየደረሰ ባለው ኢ-ሃይማኖታዊና ኢ-ሰብአዊ አሳዛኝ ድርጊት አባታዊ ምክርና መልእክት ለማስተላለፍ በመብቃታችን ከሁሉ በላይ የሆነውን አምላካችን እግዚብሔርን እናመሰግነዋለን፡፡

ወኢይከውን በኀበ እግዚእ ብእሲት ዘእንበለ ብእሲ ወብእሲ ዘእንበለ ብእሲት፤ በጌታ ዘንድ ሴት ያለ ወንድ፣ ወንድም ያለ ሴት አይሆንም፤ (1ኛ ቆሮ. 11፡11)

ሁላችንም እንደምናውቀው ሕይወት ያላቸው ፍጡራን ሁሉ ዘራቸውን ሲያስጠብቁና ሲያስቀጥሉ የሚገኙት በሁለቱም ፆታዎች አማካይነት ነው፤ ከሁለቱ አንዱ ከሌለ የሕይወት ቀጣይነት ሊኖር አይችልም፤

 

Picture 040 Picture 045 Picture 047 Picture 051

በጌታ ዘንድ ሴት ያለ ወንድ ወንድም ያለ ሴት አይሆንም ብሎ ሐዋርያው ያስተማረበት ዋናው ምክንያት፣ ከሴትና ከወንድ ህልውና ውጭ ሕይወት እንዲጠበቅና እንዲቀጥል በጌታ ዘንድ በጥንተ ፍጥረት ያልተፈቀደ መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡

ሴትና ወንድ ሁለቱም በጋራ የሐብለ ሕይወት አስቀጣይ ምክንያት መሆናቸው ቢታወቅም፣ ከሁለቱ እሪና ወይም እኩልታ የተገኘው ሕይወታዊ ፍጡርን መግቦ፣ ተንከባክቦና ጠብቆ የማብቃት ተግባር ግን ከ70% በላይ ሊያስብል በሚችል ደረጃ የሴቷ ድርሻ ሆኖ እንደሚገኝ አሌ የማይባል ሐቅ ነው፤

የእናት ምግብና ከማኅፀን ጀምሮ አካለ መጠን እስኪደርስ ድረስ ይዘልቃል፤ በዚህ የሕይወት ዕድገት የእኅት፣ የአያት፣ የአክስት ወዘተ. እንክብካቤና ጥበቃም ከእናት ቀጥሎ ሁለተኛውን ደረጃ ይዞ የሚኝ ነው፤ ለዚህም ይመስላል አባታችን አዳም እናታችን ሔዋንን ሔዋን ብሎ የሰየማት፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ እንደተረጐመው ሔዋን ማለት "የሕያዋን ሁሉ እናት" ማለት ነውና፤ (ዘፍ. 3:20)

ሔዋን የሚለው ስም ለመጀመሪያዋ እናት መሰጠቱ ሕይወትን መግቦ ተንከባክቦና ጠብቆ ለተሟላ ሰብእና የማብቃት ኃላፊነት በአብዛኛው ለሴት እናቶችና እኅቶች በተፈጥሮ የታደለ መሆኑን በሚገባ ያንፀባረቀና አጉልቶ ያሳየ መሆኑን ሰዎች ሁሉ በተለይም ወንዶች ልጆቻችን ልብ ሊሉት ይገባል፡፡

ታላቁ መሪ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ "እናት ሕይወት ልትሰጥ ሕይወት ማጣት የለባትም" ብለው የተናገሩት ታሪካዊ ንግግር ከቅዱስ መጽሐፍ አስተምህሮ ጋር በእጅጉ የተስማማ ስለሆነ እዚህ ላይ መጥቀሱ ተገቢ ነው፡፡

ይሁንና ዛሬ እየተሰማ ያለው ነገር ማለትም ሕይወት ሰጭ የሆኑ እኅቶቻችንን መድፈር ብሎም መግደል ዝም ብለን እንደተራ ነገር አልፈነው የምንሄድ ከሆነ፣ ቀጣዩ ዕድል ከሕግ ውጭና ብልሹ የሆነ ማኅበረ ሰብ ሀገራችን እንድትሸከም ማድረግ ይሆናል፤ በዚህም የሕይወት ጣዕም ወደ መራራነት ይለወጣል፡፡

ነገር ግን ይህ እንዳይሆን እያንዳንዱ ወንድ ልጅ ዛሬ የሚመካባት ሕይወት አምራና ጉልበት ፈጥራ ለመገኘት የበቃችው በእናትና በእኅት ልዩ እንክብካቤ እንደሆነ በአጽንኦት ሊገነዘብ ይገባል፡፡

ወንድ ልጅ የሆነ ሁሉ ምርጥ ምርጡን አጉርሳና አልብሳ ያሳደገችውን እናት፣ ምኑን ከምኑ አጥባና አጽድታ፣ አዝላና ስማ ወንድሜ አያለች አቆላምጣ ያሳደገችውን እኅት ቆም ብሎ ውለታዋን ሊያስብ ይገባል፤

ይህንንም ሲያስብ የግል እኅቱን ብቻ ሳይሆን ሴት ልጅ የሆነችውን ሁሉ እንደማኅበረ ሰብ ተንከባካቢ አድርጎ ማሰብ ይገባል፤ ከዚህም ተነሥቶ ለሴት ልጆች ሁሉ ልዩ ክብርና ፍቅር ማሳየት አለበት፤ ሕይወትን ልትሰጥና ልትንከባከብ በፈጣሪ የታደለች ሴት ልጅ ጭካኔ በተሞላበት አድራጎት ከቶ ልትደፈርና ሕይወቷን ልታጣ አይገባም፡፡

ይህን አድራጎት የሚፈጽሙ ሰዎች ከኃጢአት ሁሉ የበለጠና የተደራረበ ኃጢአት እየፈጸሙ እንደሆነም መገንዘብ አለባቸው፤ ይህንን የሚያደርጉ ሁሉ አትመኝ፣ አታመንዝር፣ አትግደል የሚሉትን ሕገጋተ እግዚአብሔር በአንድ ጊዜ በመጣስ የእግዚአብሔርን ቁጣ እያነሣሡ እንደሆነም ሊያስተውሉ ይገባል፡፡

የሴቶች እኅቶቻችን ተግባር የማኅበረ ሰቡን ጨቅላ ሕይወት ተንከባክቦ ለምልአተ ሕይወት ማብቃት ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ ማኅበረ ሰብ ቤት ውስጥም ሕይወትን ብርሃናዊት እንድትሆን የሚያስችል ልዩ ጸጋ እንዳላቸው ለማስገንዘብ ቅዱስ መጽሐፍ "ከቀይ ዕንቀC እጅግ ትበልጣለች" (ምሳ. 31:10) ብሎ መስክሮላቸዋል፡፡ ታዲያ ዕንቀCን አክብረው ይይዙታል እንጂ ይሰብሩታል ወይ?

ቅዱስ መጽሐፍስ እነሱን ዕንቀC ማለቱ በእጅጉ እንድናከብራቸው፣ እንድንከባከባቸውና እንድንወዳቸው ፈልጎ ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? ወንድ የሆነ ሁሉ የሴት ጥገኛ መሆኑንስ እንዴት ሊዘነጋ ይችላል? ስለዚህ የማኅበረ ሰባችን አኗኗር ፍጹም ጤናማ ይሆን ዘንድ የሴቶች ሰብአዊ መብት በወሳኝ መልኩ መከበር አለበት ፡፡

ክቡራንና ክቡራት እንግዶች፤

ሀገራችን ኢትዮጵያ የአማንያን፣ የመልካም ሥነ-ምግባርና የመልካም ባህል ሀገር እንደሆነች ሊዘነጋ አይገባም፤ ምንም እንኳ በሀገሪቱ ውስጥ የተለያዩ እምነቶች ቢኖሩም፣ የሴት ልጅ ክብረ ሰብእናን አስመልክቶ ያላቸው አስተምህሮ የተለያየ አይደለም፡፡

ከሞላ ጎደል የሁሉም አስተምህሮ ያለፈቃድ አይደለም ያለ ሕጋዊ ጋብቻ የሚፈጸም ሩካቤ ኃጢአት መሆኑን ሁሉም ያሰምሩበታል፡፡ ይሁንና በአሁኑ ጊዚ የዓለም ሉላዊ (ግሎባላይዜሽን) ግንኙነት ባመጣው መቀራረብ ብዙ ጎጂ ባህሎች ወደ ሀገራችን እየገቡ ሃይማኖታዊውንና ቅዱሱን ባህላችን እየተፈታተኑት እንደሚገኙ ግልጽ ነው፡፡

ዛሬ በሀገራችን እየተፈጸሙ እንደሆኑ የሚደመጡት አስጸያፊና አስነዋሪ ድርጊቶች ሁሉ ሕገ እግዚአብሔርንና፣ ሕገ ተፈጥሮን በማፋለስ እንዲሁም የጋብቻን ክቡርነት በማዛባት ማኅበረ ሰባችንን ለመበከል በተለይም ሴት ልጆቻችንን ለመድፈርና ብሎም ለመግደል ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሆነ በብዙ መልኩ እየታየ ነው፡፡

በመሆኑም ለማኅበረ ሰባችን ጉዳት እንጂ ጥቅም የማያመጡትንና ከነባሩና ከቅዱሱ ሥነ-ምግባራችንና ባህላችን የሚያራርቁን የውጭ ባህሎችና ድርጊቶች ማኅበረ ሰቡ አምርሮ እንዲታገላቸው ሁላችንም በጋራ መንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሴት ልጆቻችን ላይ የሚደርሰውን የመደፈርና የግድያ ተግባር ሁሉ አጥብቃ የምትኮንነውና የምታወግዘው ከመሆኑም በላይ ይህንን አረመኔያዊ ተግባር በሀገሪቱ እንዳይፈጸምና ሥር እንዳይሰድ በሚደረገው ጥረት ሁሉ በግንባር ቀደም ተሰልፋ ለሴት ልጆቻችን መብት መከበር የሚጠበቅባትን ለማድረግ ዝግጁ መሆንዋን በዚህ ጉባኤ ፊት ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን፡፡

በመጨረሻም

ኢትዮጵያውያን የሆናችሁ ወገኖቻችን ሁሉ በተለይም ነገ ሀገሪቱን በልማት፣ በመልካም ሥነ-ምግባርና በተቀደሰ ባህል ትመራላችሁ ብለን የምንጠብቃችሁ ወጣት ወንዶች ልጆቻችን ከሁሉም በላይ የተቀደሰውን የሀገራችን ሃይማኖታዊ አስተምህሮ አንግባችሁ በሰብአዊ መብት ይልቁንም በሴት መብት አከባበር ላይ ትኩረት ሰጥታችሁ በሙሉ ዓቅማችሁ እንድትንቀሳቀሱ፣ እንደዚሁም የሀገራችን ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች ሥነ-ምግባሮችና ባህሎች የማይፈቅዱአቸውን ጎጂና መጤ ልምዶች በጽናት በመቋቋም በዳበረ አስተሳሰብ በሰብአዊ መብት አከባበርና በማኅበራዊ ኑሮ እጅግ የበለፀገ ማኅበረ ሰብ ለመገንባት በሚደረገው ያላሰለሰ ጥረት የበኩላችሁን እንድትወጡ አባታዊ መልእክታችንን አደራ ጭምር እናስተላልፋለን ፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ ይቀደስ
አሜን!!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ታሕሣሥ 8 ቀን 2007 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

የፎንት ልክ መቀየሪያ