Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

በመ/ር ዕንቈባሕርይ ተከስተ

የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ኃላፊ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን

ከጥቅምት ፰- ፲፩ ቀን ፳፻ወ፰ ዓ/ም ድረስ የተካሔደው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርሰቲያን መንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የ፴፬ኛው መደበኛ ስብሰባ

ቃለ ጉባኤ

ዐቢይ ጉባኤው በቃለ ዐዋዲው ምዕራፍ ሁለት አንቀጽ ዐራት፣ ንኡስ ቁጥር ዐራት መሠረት የተቋቋማና በዓመት አንድ ጊዜ የሚደረግ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ነው፤ በዚህ ዓመት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያትክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ርዕስ መንበርነት፤ በብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የመንበረ ፓትያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የወላታ ኮንታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የጉባኤው መሪነት የተካሄደ ፴፬ኛውመደበኛ ስብሰባ ነው፡፡

፩. የጉባኤው መደበኛ አባላትና ተሳታፊዎች

 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያትክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ የጉባኤው ርዕሰ መንበር
 • ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የመ/ፓ/ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የወላታ ኮንታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የጉባኤው መሪ
 • ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የጉባኤው አባል
 • ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የጉባኤው አባላት
 • ዶ/ር አባ ኃ/ማርያም መለሰ የጠቅላይ ቤተክህነት ም/ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የጉባኤው አባል
 • ክቡር ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጸሐፊ የጉባኤው አባል
 • የጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያና የድርጅት ኃላፊዎች፣ልማትና
 • ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽንና፣ የሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳዮች፣የከፍተኛ መንፈሳዊ ኮሌጆች ኃላፊዎች፣ .........የጉባኤው አባላት
 • የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፣ ምክትል ሥራ አስኪያጆች፣
 • የካህናት፣ የምእመናን፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ የሰበካ ጉባኤ፣
 • የስብከተ ወንጌል፣ ተወካዮች የጉባኤው አባላት
 • በውጭ ሀገር የኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ተወካዮች፣ የጉባኤው አባላት
 • የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የክፍል ኃላፊዎች፣ የጉባኤው አባላት
 • የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣
 • የሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቃነ መናብርት፣ የጉባኤው ተሳታፊዎች
 • የማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል አመራር አባላት የጉባኤው አባላት
 • በጉባኤው እንዲሳተፉ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የጉባኤው ተሳታፊዎች

በአባልነትና በተሳታፊነት ተገኝተዋል፡፡

፪. የጉባኤው በጸሎተ ቡራኬ መከፈት

በጉባኤው መርሐ ግብር መሠረትና አስቀድሞ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠ/ጽ/ቤት በተላለፈው ጥሪ መሠረት ከመላው ዓለም የመጡ የአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አባላትና ተሳታፊዎች በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ስብከተ ወንጌል መሰብሰቢያ አዳረሽ በመገኘት ጥቅምት 8 ቀን 2008 ዓ/ም፣ ከጠዋቱ 2-3 ድረስ እየተመዘገቡ በአዳራሹ የተዘጋጀላቸውን ቦታ ይዘዋል፡፡ በመቀጠልም በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ መሪነት የጉባኤው ርዕሰ መንበር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያትክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጋር በመሆን የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ሰንበት ትምሀርት ቤት አባላት፤

 አሰርጓካ ለኢትዮጵያ በስብሐት በሃሌሉያ

ማትያስ ፀሐይ ለኢትዮጵያ
ማትያስ ፀሐይ ለቤተ ክርስቲያን (የሚለውንና) 

ባርከኒ አባ መፍቀሬ ሕፃናት ማትያስ
አስመ አንተ ሰባኬ ወንጌል ሐዲስ
ሰባኬ ወንጌል ማትያስ

የሚሉ ጣዕመ ዝማሬዎችን በማሰማት ቅዱስነታቸውን አጅበው ወደ አዳራሹ ሲገቡ ጉባኤው በታላቅ አክብሮት ተቀብሏዋል፡፡ በመቀጠልም በቅዱስነታቸው አባታዊ አመራር የካህናት አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ በመጋቤ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዘማርያም ቅዱስነታቸውን በማስፈቀድ፣ የጉባኤውን አባላት ለጸሎት በማዘጋጀት በቅዱስነታቸው ጸሎተ ቡራኬ ውዳሴ ማርያም፣ መልክዐ ማርያምና መልክዐ ኢየሱስ ታድሎ ከመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ልብሰ ተክህኖ ለብሰው በተገኙ ልዑካን ለእለቱ የተዘጋጀው ምስባክና ጸሎተ ወንጌል ደርሷል፡፡

ለዕለቱ የተመረጠው ምስባክም፡

ስምዓነ አምላክነ ወመደኀኒነ
ተስፋሆሙ ለኩሎሙ አጽናፈ ምድር
ወለእለሂ ውስተ ባሕር ርሑቅ አቤቱ አምላካችንና መድኀኒታችን ሆይ ስማን
ለምድር ዳርቻዎች ተስፋቸው አንተ ነህ
በሩቅ ባህር ውስጥ ላሉትም (እንዲሁ)

የሚለው ነው፡፡ (መዝሙር 64 ፡ 5) የተወሰደው ምስባኩ ተሰምቶ ጸሎተ ወንጌል ተደርሶ፤ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 18፡18-21 የሚገኘው "አማን እብለክሙ ዘአሰርክሙ በምድር ይከውን እሱረ በሰማያት፣ ወዘፈታሕክሙ በምድር ይከውን ፍቱሐ በሰማያት፣ ወአዲ እብለክሙ ለእመ ኀብሩ ክልኤቱ አው ሠለስቱ እምኔክሙ በውስተ ምድር በእንተ ኵሉ ግብር ዘሰአሉ ይትገበር ሎሙ በኀበ አቡየ ዘበሰማያት እስመ ኀበ ሀለው ክልኤቱ ወሠለስቱ ጉቡኣን በስምየ ህየ እሄሉ ማእከሌሆሙ" ትርጉም፡ "እውነት እላችኋለሁ በምድር ያሰራችሁት በሰማያት የታሰረ ይሆናል፣ በምድርም የፈታችሁት በሰማያት የተፈታ ሆናል፤ ዳግመኛም ከእናንተ ሁለቱ ወይም ሦስቱ በምድር ላይ ስለሚለምኑት ሥራ ሁሉ ቢተባበሩ በሰማያት አባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል፣ እላችኋለሁ ሁለቱ ወይም ሦስት በስሜ ተሰብስው ካሉበት እኔ ከዚያ በመካከላቸው እኖራለሁ" የሚለው ቃለ ወንጌል ለጉባኤው ዐቢይ መርሕና ትምህርት ሁኖ እንዲያገለግል በቅዱስነታቸው ተነቦና ጸሎተ ኪዳን ተደርሶ ጉባኤው በይፋ ተከፍቷል፡:

፫. በደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ሰንበት ትምህርት ቤት የቀረበ ያሬዳዊ መዝሙር

ሰላም ለክሙ ኦ! አፍላገ ወንጌሉ ለክርስቶስ
በጽባሕ ሐውጽዋ ለቤተ መቅደስ፣ ለቤተ ክርስቲያን

የሚለው ወረቡ በወጣቶቹ ተዘምሯል፡፡

፬. የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግሮችና የመርሐ ግብር ትውውቅ

ሀ. የክብር ሊ/ማ ፋንታሁን ሙጨ የመርሐ ግብር ትውውቅና መልእክት

የጉባኤው መክፈቻ ጸሎትና የሰንበት ትምህርት ቤት የመዝሙር ምስጋና ከቀረበ በኋላ አስተባባሪው መ/ካ ኃይለ ሥላሴ መድረኩን ለክቡር ሊ/ማ ፋንታሁን ሙጨ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ አስረክበዋል፡፡ ክቡር ሊ/ማ ፋንታሁንም ጉባኤውን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ሰላምታ ካቀረቡ በኋላ የ34ኛውን አጠቃላይ ሰበካ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ በተከታታይ ቀናት የሚኖሩትን መርሐ ግብሮች አስተዋውቀዋል፡፡ በመቀጠልም በዜህ ጉባኤ ልናስበውና በጥልቀት ልንገነዘበው የሚገባው ያለፈው ዓመት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በልዩ ልዩ ዘርፎች በመልካም አስተዳደር፣ በገቢ ዕድገት፣ በአሠራር ዘመናዊነት መልካም እምርታ ያሳየችበትና እስከ ዛሬ ያላነበሩን የሒሳብ አያያዝ አሠራር በአዲስ መልክ የጀመርንበት ተቋርጦ የነበረውን ስምሪት የጀመርንበት በመሆኑ እና በሌሎችም መስኮች ወደ ጥሩ ምዕራፎች የተሸጋገርንበት ዘመን ነው ካሉ በኋላ ይህ ሲባል ሁሉ ነገር የተስተካለከለ ነው ለማለት ሳይሆን በአንዳንድ አካባቢዎች የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሲኖዶሳዊ ማዕከላዊነት የጣሱና የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ የአበውን አመራር አንቀበልም የሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች እያደጉ መምጣታቸው፣ ዕውቅና ባላቸውም ሆነ በሌላቸው አካላት እየታገዙ የቤተ ክርስቲያንን ሉዓላዊነትና የአንድነት ሕልውና የሚፈትኑ ክስተቶች መታየት ሁላችንም እያሳሰበ የመጣ ሲሆን ሳይቃጠል በቅጠል እንደሚባለው አባቶቻችን በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ትኩረት ሰጥተው መፍትሔ እንያበጁለት የምናሳስበብበት አጋጣሚ መሆኑን፣ ምን እንኳ በበጀት ዓመቱ የገቢ ዕድገት ቢታይም የልማት ዕድገት መታየት በሚገባው ደረጃ እየታየ ባለመሆኑ ሁላችንም ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ንብረት ለማፍራት በልማቱ በኩል ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበው ከጋምቤላ ብሔራዊ ክልል፣ በሥራ አስኪያጁ አማካኝነት ከአምስቱ የክልሉ ነባር ብሔረሰቦች ተወክለው የመጡ፡-

1. አቶ ኰንግ የመኩዮ ወረዳ አስተዳደር
2. አቶ ጋርንጅ የዋንትዎ ወረዳ አስተዳደር
3. አቶ ጃን የጃሳዎ ወረዳ አስተዳደር
4. አቶ አሙሉ ኡቻራ የክልል መንግሥት ዲያስፖራ ቢሮ ኃላፊ
5. አቶ ሴንገ ኰርወ የክልል መንግሥት የንግድ ቢሮ ኃላፊ
6. አቶ ዋጂኒ የመጀዋንግ ዞን አፈ ጉባኤ
7. ወ/ሮ ኒያራ የጋምቤላ ከተማ የሴቶች ጉዳይ ኃላፊ ለጉባኤው በማስተዋወቅና ከቅዱስነታቸው ቡራኬ እንዲቀበሉ ካደረጉ በኋላ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር እንዲያደርጉና ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን ለጉባኤው ቃለ ቡራኬ እንዲያስተላልፉ እንዲጋብዙላቸው መድረኩን አስተላልፈዋል፡፡

ለ. የብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክትና ቅዱስነታቸው አባታዊ ቡራኬን እንዲያስተላልፉ መጋበዝ፤

ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ንግግራቸውን "ብርሃን ዘሰደዶ ለጽልመት፡ ወማሕቶት ዘአብርሃ ለኵሉ ዓለም፡ ወመሠረት ዘኢያንቀለቅል፡ ንድቅ ዘኢይትነሠት፡ ሐመር ዘኢይሠበር፡ መዝገብ ዘኢይሠረቅ፣ አርዑት ሠናይ ወጾር ቀሊል፡ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ኃይሉ ወጥበቡ ለአብ፡፡ (ትርጉም፡ ጨለማን ያሳደደው ብርሃን፡ ዓለም ሁሉ ያበራው ፋና፡ የማይነዋወጥ መሠረት የማይፈርስ ግንብ፡ የማይሰበር መርከብ፡ የማይሠረቅ ማኅደር፡ ያማረ ቀንበርና የቀለለ ሸክም እርሱ ለአባቱ ኃይሉ ጥበቡም የሚሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡" በማለት ከሊቁ የአቡነ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ መጽሐፈ ሰዓታት በመጥቀስ ንግራቸውን የጀመሩ ሲሆን፣ ለሠላሳ ዐራተኛው አጠቃላይ ሰበካ ጉበኤ መደበኛ ስብሰባ በተላለፈላቸው ጥሪ መሠረት የተገኙ አባላትንና ተሳታፊዎች ሁሉ እነኳ ደህና መጣችሁ በማለት የጉባኤውን ቃለ ጉባኤ መዝጋቢዎች በማሰየምና በማጸደቅ ቅዱስነታቸው ለታላቁ ጉባኤ አባታዊ ቃለ በረከት እንዲያስተላልፉ ጋብዘዋል፡፡

፭. የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያትክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ቃለ ቡራኬ

ቅዱስ ፓትርያርኩ ለሠላሳ ዐራተኛው አጠቃላይ ሰበካ ጉበኤ ያደረሰንን እግዚአብሔርን በማመስገን የጉባኤውን አባላትና ተሳታፊዎች እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት በመክፈቻው ያስተላለፉት ቃለ ቡራኬ ‹‹ቃለ እግዚብሔር ቃል ንጹሕ፣ የእግዚአብሔር ቃል ንጹሕ ቃል ነው›› (መዝ.11፡6) የሚለውን መዝሙር በመጥቀስ የሚጀመር ሲሆን የቃለ ቡራኬው ዋና ይዘት የቤተ ክርስቲያን ውስጣዊ ሕልውና መሠረቷ፣ የውስጥ ጽናቷ፣ የውጭ ቅጽሯ፣ አስትንፋሷ፣ ሥራ ኃይሏ፣ የሉዐላዊነቷና ክብሯ ምንጭ ሕያው ሆነው ቃለ እግዚአብሔር መሆኑ፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቃለ እግዚአበሔር መድረሻ መሆኗ፣ የዛሬው መሰብሰባችንነ በዚህ ወቅት የምናደርጋቸው ሥራዎች ሁሉ የቃለ እግዚብሔር ውጤቶችና ፍጻሜዎች መሆናቸው፣ በዓለም ውስጥ እጅግ ሀብታምና ኃያል የሆነ ማን ነው? ተብሎ ቢጠየቅ ትክክለኛ መልስ ሊሆን የሚችለው ቤተ ክርስቲያን መሆኗ፣ በአሁኑ አመት ከፍተኛ የመባል የገቢ ዕድገት ማሳየታቻን እጅግ የሚያስደስት መሆኑንና ይሁን እንጅ የምእመናን ዕድገትስ የት ነው ያለው የሚለውን መጠየቅ እንደሚገባን፣ የጊዜው እየጨመረ የመጣውን የምእመናን ወደ ልዩ ልዩ እምነቶች የመፍለስ ሁኔታ ልናጤነው እንደሚገባ፣ በመግለጽ ዓቢይ ጉባዔው በሁለት ዓበይት የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንዲነጋገርባቸው ጠቁመዋል፣ እነሱም፡-

 • ምእመናንን የመጠበቅ ተልእኮ በሚገባ እየተወጣን አይደለምና ባዶአችንን ከመቅረታችን በፊት ለተደራጀና ለድንበር የለሽ ትምህርተ ወንጌል ብንነሣ፤
 • የአስተዳደር ሥራችን ለምእመናን ኅሊና እንቅፋት እየሆነ ነውና የሃይማኖቱን መርሕ ጠብቀን አስተዳደራችን የሕግ የበላይነትን ያረጋገጠ፣ ግልጽ፣ ተአማኒና ተጠያቂነትን ያሰፈነ የምእመናንን ልብ የሚያረካ፣ ምእመናን በቤተ ክርስቲያናቸው ኵራት እንዲሰማቸው የሚያስችል አሠራር ብናረጋግጥ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ እንችላለን፤

የሚሉ ሲሆኑ የሰበካ ጉባኤ ዋና ምንጭ ምእመናን መሆናቸውን አውቀን በዚህ ዙሪያ በሰፊው እንሥራ፤ ቢቻል አሁን አለን ከምንለው የላቀ የምእመናን ቁጥር በበለጠ ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ፣ ባይሆን ደግሞ ባለበት ጠብቆ ለማቆየት በርትተን መሥራት ይጠበቅብናል ፡፡ በማለት ቃለ ቡራኬ አስተላልፈዋል፡፡

ከዚህ አንፃር ቅዱስነታቸው ያስተላለፉት ቃለ ቡራኬ፣ መልእክትና መመሪያ ካለው እጅግ ማራኪና አስተማሪ ይዘት፣ በጉባኤው አባላትና ዘንድ አጥንትን ዘልቆ የገባ የማይረሳና ታሪካዊ በመሆኑ የቃለ ቡራኬው ሙሉ ይዘት የዚህ ቃለ ጉባኤ አካል እንዲሆን ጉባኤው ተስማምቷል፡፡

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያትክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ቃለ ቡራኬ ሙሉ ይዘት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን፡፡

ሁሉን ፈጥሮ የሚገዛ አምላካችን እግዚአብሔር ያለፈውን የ2007 ዓ.ም. የሥራ ዘመን በሰላም አስፈጽሞ በአዲሱ የ2008 ዓ.ም. ልንሠራው የሚገባንን ሥራ ለመሥራት አንድ ላይ ስለሰበሰበን ከሁሉ በፊት እርሱን እያመሰገን እንኳን ለሠላሣ ዐራተኛው ዓመታዊ መደበኛ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በሰላም አደረሳችሁ እንላለን ፡፡
‹‹ቃለ እግዚብሔር ቃል ንጹሕ፣ የእግዚአብሔር ቃል ንጹሕ ቃል ነው›› (መዝ.11፡6) ስለ ቃል አንሥተን ስንመረምር በፍጡራን ዘንድ የተለያዩ ቃላት እንዳሉ ከቅዱስ መጽሐፍ እንመለከታለን፡፡ ከነሱ መካከል የተወሱትን ለመጥቀስ የአዕዋፍን ቃል ‹‹ቃለ ማዕነቅ›› የውሀን ቃል ‹‹ቃለ ማያት ብዙኅ›› የደመናትን ቃል ‹‹ቃለ ወሀቡ ደመናት›› እየተባለ በቅዱስ መጽሐፍ ተጽፎአል፡፡ ከምድራውያን ፍጡራን ሁሉ የተሻለ ቃለ ሰብእም እንዳለ ሁላችን የምናውቀው ጉዳይ ነው ፡፡ ነገር ግን ከዚህ ሁሉ የበለጠና ሕያው የሆነው ቃል የእግዚአብሔር ቃል ነው፤
ቃለ እግዚአብሔር በሰማይም ሆነ በምድር ያሉትን ማለትም የሚታዩትንና የማይታዩትን ሁሉ የፈጠረ፤ ኃይላተ ሰማያት ወምድር ጸንተው የሚኖሩበት፣ ሁሉን የሚያሳልፍ እንጂ እርሱ የማያልፍ ቃል ነው፤ የእግዚአብሔር ቃል እውነት እንጂ ሐሰት የማይቀላቀልበት፤ ኃይል እንጂ ድካም የማይፈራረቅበት በመሆኑ ንጹሕ ቃል ይባላል ፡፡ በዚህ ዓለምም ሆነ በወዲያኛው ዓለም የእግዚአብሔር ቃል ያልተናገረለት ፍጡር የለም፤ ይሁን እንጂ የእግዚአብሔር ቃል ከሁሉም በላይ አብዝቶ የተናገረላት ብትኖር ቤተ ክርስቲያን ብቻ ናት፣
በተለያየ ኅብረ ትንቢት ወአምሳል፣ በተለያየ ኊልቈ ሱባዔ ወቀመር ተጽፎ የሚገኘው ቃለ እግዚአብሔር የመጨረሻ መዳረሻው ቤተ ክርስቲያን ናት፤ ቤተ ክርስቲያን በጥንተ ፍጥረት ከመጀመሪያ ጀምሮ ነበረች፤ ከዓለም ፍጻሜ በኋላም የእግዚአብሔር መንግሥት ርእሰ ከተማ ሆና ማኅለቅት በሌለው ኊልቈ ዘመን ትቀጥላለች ፡፡
የእግዚአብሔር ቃል በብሉይ ኪዳን ስለ ቤተ ክርስቲያን ሲናገር ‹‹ይሰግዱ ለኪ ኵሎሙ ነገሥታተ ምድር ወይልሕሱ ፀበለ እግርኪ፤ ወትሰመይ ጽዮንሃ ሀገረ እግዚአብሔር፤ ወአስተጋብኦሙ ለውሉድኪ በውስቴትኪ፣ ያመጽኡ አምኃኪ እምርኁቅ ብሔር ወነገሥት ክብረ ሊባኖስ›› ብሎአል ፡፡ ይህም ማለት ሁሉም የምድር ነገሥታት ላንቺ ይሰግዳሉ፤ የእግርሽንም ትቢያ ይልሳሉ፤ አንቺ የእግዚአብሔር ከተማ ጽዮን ነሽ ትባያለሽ፤ ልጆችሽን በአንቺ ውስጥ እሰበስባቸዋለሁ፤ መባውን፣ ቀዳምያቱን፣ ዐሥራቱን፣ በኵራቱን ከሩቅ አገር ይዘውልሽ ይመጣሉ፤ ነገሥታትም የሊባኖስን ክብር ያመጡልሻል ማለት ነው ፡፡ (ኢሳ. 49፡23) በውስጧ ሆነው ሲያገለግሉ የሚኖሩ ልጆችዋም ‹‹ወይትወኃውሁ በአዝማን ዘአልቦ ኊልቁ፤ ፍጻሜ በሌላቸው አዝማነ መንግሥተ ሰማያት ሲመላለሱ ይኖራሉ›› ተብሎ በተነገረላቸው ቃል መሠረት ማኅለቅትና ፍጻሜ በሌለው ሕይወት በውስጧ ለዘላለሙ በደስታና በክብር ይኖራሉ ፤
እንግዲህ የእግዚአብሔር ቃል ይህን ሁሉ የተናገረው ለንጽሕትና ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ነው፤ ዛሬ በዚህ ዓቢይ ጉባዔ እግዚአብሔር የሰበሰበን ኃይል ‹‹ልጆችሽን በአንቺ ውስጥ እሰበስባቸዋለሁ›› ብሎ ከዛሬ ሁለት ሺሕ ሰባት መቶ ዓመታት በፊት የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ነው፤ ዛሬ መባውን፣ ቀዳምያቱን፣ በኵራቱን፣ ዐሥራቱን፤ ወይም በዘመናችን አነጋገር የሰበካ ጉባኤ አስተዋጽኦውን ከሩቅ አገር ይዘን ወደዚህ የመጣንበት ምክንያት ‹‹መባሽን ከሩቅ ይዘውልሽ ይመጣሉ›› የሚለው የእግዚአብሔር ቃል አስተምሮን ነው፤ ይህ ሕያውና የማይታበል ቃል ዛሬም በእኛ ውስጥ ሥራውን እየሠራ የሚገኝ በመሆኑና እኛም የቃሉ መሣሪያ ሆነን በመገኘታችን እጅግ፤ ደስ ሊለን ይገባል፡፡
በዓለም ውስጥ እጅግ ሀብታምና ኃያል የሆነ ማን ነው? ተብሎ ቢጠየቅ ትክክለኛ መልስ ሊሆን የሚችለው ቤተ ክርስቲያን ናት የሚለው መልስ ነው ፡፡ እርግጥ ነው፤ ቤተ ክርስቲያን ለሰዎች ኃይል ቀርቶ ለሰይጣንና ለሠራዊቱ እንኳ የማትበገር ኃያል ናት፤ በዚህም የእግዚአብሔር ቃል ‹‹ወአናቅጸ ሲኦል ኢይኄይልዋ፣ የሲኦል በረኞች ሰይጣንና ሠራዊቱ አያሸንፉአትም›› ብሎ ተናግሮላታል፤ ይህ ቃል የማይሸነፍ ኃያልና ንጹሕ የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ እነሆ ጠላቶቿ ሁሉ እየተሸነፉ እርስዋ ግን በድል አድራጊነት በዘመኑ ሁሉ ወደፊት እየገሠገሠች ከዘመናችን ደርሳለች፤ ወደፊትም በዚሁ ትቀጥላለች ፡፡
በሌላም በኩል ቤተ ክርስቲያን እጅግ የበለፀገች ባለሀብት መሆንዋን የእግዚአብሔር ቃል ሲናገር ‹‹ወይበውእ ኀቤኪ ብዕለ አሕዛብ፤ የሕዝቡና የአሕዛቡ ብዕል ወዳንቺ ይገባል ›› ይላል፡፡ቤተ ክርስቲያን ይህ ቃል መሠረተ ሀብቷ ሆኖ አስገዳጅ ምድራዊ ኃይል ሳይኖር በቃሉ ቀስቃሽነት ብቻ ሕዝበ እግዚአብሔር የሆኑ ክርስቲያኖች ያላቸውን በደስታ፣ በፈቃደኝነትና በልግስና ዐውደ ምሕረቷ ድረስ እየመጡ ከከበረው የወርቅ ጌጥ ጀምሮ ስጦታውን በየዓይነቱ ሲያፈሱላት ይኖራሉ ፡፡ እንግዲህ ይህን ሁሉ በዓይናችን እየተመለከትን የምንገኝ እኛ ‹‹በአማን ኢይሔሱ ቃሎ ዘነበበ፣ በእውነት የተናገረውን ቃል አይዋሽም›› ብለን እርሱን ከማመስገን ጋር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነን ልንፈጽመው የተሰጠንን ተልእኮ በደስታ፣ በፈቃደኝነት፣ በትጋትና በቅንነት ከመወጣት በቀር ሌላ ምን ሥራ ሊኖረን ይችላል ፤
ከዚህ ተነሥተን ስናይ እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን የተናገረው ቃሉን እንዳላጠፈብን እናረጋግጣለን፡፡ በአንጻሩ ደግሞ እኛስ ቃላችንን አክብረናል፤ ወይስ አጥፈናል፤ የሚለውን መመርመር ከእኛ ይጠበቃል ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ያለው የቤተ ክርስቲያናችን ገቢ በቂ ነው ባይባልም ቤተ ክርስቲያናችን በሰበካ ጉባኤ መደራጀት ስትጀምር ገቢዋ በመቶ ሺሕ ብር ደረጃ የነበረው ዛሬ ወደመቶ ሚሊዮኖች መድረሱ በሀገር አቀፍ ደረጃ አጠቃላይ ሲታይ ደግሞ ወደ ቢሊዮኖች መድረሱ ትልቅ ዕድገት ነው፤
ነገር ግን የምእመናን ዕድገትስ የት ነው ያለው የሚለውን አይተነዋል ወይ?፤ በዚህ በኩል ያለው ዕድገት የኋልዮሽ መሆኑ የማያውቅስ በመካከላችን ይኖር ይሆን? ይህን ችግር በሚገባ ተገንዝበንና በቁጭት ተነሣሥተን ነገሩን ለመቀልበስ ያደረግነው ሙከራስ ይኖር ይሆን? ለዚህ ጥያቄአችን ከዚህ ጉባኤ መልስ እንፈልጋለን ፡፡
መቼም ቢሆን ተልእኮአችን ሰማያዊ እንጂ ምድራዊ እንዳይደለ ሁላችንም እናውቃለን፤ ሰማያዊውና ታላቁን ተልእኮአችን በተገቢው ሁኔታ ለመወጣት ከኅሊና መቈርቈር ጀምሮ እስከ ኅልፈተ ሕይወት የሚዘልቅ የመሥዋዕትነት ዋጋ እንደሚጠይቅ ምንጊዜም አንዘነጋውም፤ ይህ መሥዋዕትነት ብዙዎቹ የሃይማኖት መስተጋድላን አባቶቻችን ያለፉበት ስለሆነ ለኛ ለቤተ ክርስቲያን ልጆች አዲስ አይሆንም ፡፡
ይሁንና እኛ ባለንበት በአሁኑ ዘመን ከፍተኛ መሥዋዕትነትን እየጠየቀን ያለው የደምና የሕይወት መሥዋዕትነት ሳይሆን ራስን የመካድ ወይም ያልተገባ ጥቅምን የመጸየፍና ኃላፊነትን በሚገባ ለመወጣት የመነሣሣት ጉዳይ ነው ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንን ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር ስናነጻጽር በቊጥር እጅግ የላቀ የውሉደ ክህነት ብዝኅነት ያላት ስትሆን ‹‹ታላቁን የቅዱስ ወንጌል ተልእኮን›› ለውሉደ ሰብእ በማዳረስ ረገድ ያለን ውጤት ግን አናሳ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ባህርን አቋርጦ፣ ድንበርን ተሻግሮ፣ እስከ ጽንፈ ምድር ተጉዞ፣ አስተምሮና ያላመነውን፣ አሳምኖ የቤተ ክርስቲያን ልጅ ማድረጉ ይቅርና በሀገር ውስጥ ያሉትን ወገኖች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አሰባስቦ ምእመናንን ማብዛት ብዙ ያልተሄደበት እንደሆነ ማወቅ አለብን ፡፡ ከሁሉም በላይ የሚያስቆጨው ደግሞ ትናንት ቤተ ክርስቲያን ‹‹ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና›› ሰጥታ በአባልነት የተቀበለቻቸው ልጆችዋ ዛሬ እናት ቤተ ክርስቲያናቸውን እየካዱ ወደሌላው ጎራ የመቀላቀሉ ጉዳይ እጅግ በጣም እየናረ መምጣቱን ነው ፡፡
የምእመናን ፍልሰት በየጊዜው እየጨመረ የመሄዱ መነሻ ምሥጢር ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ ቤተ ክርስቲያናችን በአጽንዖት ልታጤነው ይገባል፤ በዚህ ዙሪያ የሚታየው ክፍተት ፈጣን ምላሽ በመስጠት መግቻ ካላበጀንለት ነገ ከባድ የሃይማኖትና የታሪክ ወቀሳ ማስከተሉ እንደማይቀር ልብ እንበል ፡፡ ለመሆኑ ምእመናን ከቤተ ክርስቲያናችን እየወጡ ወደ ሌላ ካምብ ለመግባት ለምን መረጡ? የሚያስተምራቸው ካህን አጥተው ነው? የቤተ ክርስቲያናችን ትምህርተ ሃይማኖት ክፍተት ኖሮት ነው? የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር የማያረካ ሆኖ ነው? የካህን እጥረት ስላለ ነው? ወይስ ሌሎች ከእኛ የተሻሉ ሆነው ስለተገኙ ነው፤? የዚህ ሁሉ መልስ በእያንዳንዳችን ኅሊና ውስጥ ቁልጭ ብሎ ስለሚታወቅ የጥያቄው መልስ ለእናንተው ሰጥተናል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ ዓቢይ ጉባዔ በሁለት ዓበይት የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንዲነጋገርባቸው ሳንጠቁም አናልፍም ይኸውም፡- ምእመናንን የመጠበቅ ተልእኮ በሚገባ እየተወጣን አይደለምና ባዶአችንን ከመቅረታችን በፊት ለተደራጀና ለድንበር የለሽ ትምህርተ ወንጌል ብንነሣ፤ የአስተዳደር ሥራችን ለምእመናን ኅሊና እንቅፋት እየሆነ ነውና የሃይማኖቱን መርሕ ጠብቀን አስተዳደራችን የሕግ የበላይነትን ያረጋገጠ፣ ግልጽ፣ ተአማኒና ተጠያቂነትን ያሰፈነ የምእመናንን ልብ የሚያረካ፣ ምእመናን በቤተ ክርስቲያናቸው ኵራት እንዲሰማቸው የሚያስችል አሠራር ብናረጋግጥ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ እንችላለን፤ ይህ ሲሆን ነው የሰበካ ጉባኤ ዓላማ ግቡን የሚመታው በእርግጠኝነት ለመናገር እንደ ጌታችን አስተምህሮ ሕጻናትን፣ ወጣቶችንና አዋቂዎችን በአግባቡ ጠብቃ የምትኖር ቤተ ክርስቲያን ለሃይማኖት ቅሰጣ አትጋለጥም ፡፡
ስለሆነም የሰበካ ጉባኤ ዋና ምንጭ ምእመናን መሆናቸውን አውቀን በዚህ ዙሪያ በሰፊው እንሥራ፤ ቢቻል አሁን አለን ከምንለው የላቀ የምእመናን ቁጥር በበለጠ ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ፣ ባይሆን ደግሞ ባለበት ጠብቆ ለማቆየት በርትተን መሥራት ይጠበቅብናል ፡፡
በመጨረሻም ይህ ዓለም አቀፋዊ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ከየአቅጣጫው የሚቀርቡትን ሪፖርቶች በመገምገም፣ ለበጀት ዓመቱ ሥራችን መሠረት የሚሆኑ የዕቅድ አመላካች አስተያየቶችና ሐሳቦችን በማስቀመጥ፣ እንደዚሁም የሀገራችንን የሕዳሴ ጉዞ በተያዘለት መርሐ ግብር መሠረት ግቡን እንዲመታ ሕዝቡን ለማነሣሣት ቃል በመግባት የሚጠበቅበትን ሁሉ እንዲያደርግ መልእክታችንን በቤተ ክርስቲያን ስም እናስተላልፋለን፤ እግዚአብሔር ጉባኤያችንን ይባርክ ይቀድስ፡፡

አሜን፤ ወስብሐት ለእግዚአብሔር

፮. የብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ያቀረቡት አጠቃላይ ዘገባ

የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዘገባን የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም መለሰ ያነበቡት ሲሆን፣ በሪፖርቱ ቅድስት ቤተክርስቲያን በየዓመቱ በሃይማኖታዊ፣ መንፈሳዊና ማበራዊ ዘርፎች የምታከናውናቸው ዐበይት ተግባራት ፣የተመዘገቡ ውጤቶችና ያጋጠሙ ችግሮች እንዲሁም ላጋጠሙ ችግሮች የተሰጡ የመፍትሔ ሐሳቦችና የወደፊት እቅዶች በዓመት አንድ ጊዜ በሚካሔደው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ እየቀረቡ ከተመከረባቸውና የውሳኔ ሐሳብ ከቀረበባቸው በኋላ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ እንዲያርፍባቸው በማድረግ የቤተክርስቲያኒቱ ዓመታዊ በጀትና ዕቅድ እንዲጸድቅ እየተደረገ ሲሠራ እነሆ ለ34ኛ ጊዜ መሆኑን ለዚህም ያበቃን ልዑል እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን በማለት፣ በ2007 ዓ.ም በተለያዩ አህጉረ ስብከት የተፈጠሩ የሥራ ላይ አለመገባባቶች በሊቃነ ጳጳሳት ሰብሳቢነት በሚካሔዱ ጉባኤያት አማካኝነት እየታዩ ውሳኔ እንዲያገኙ የተደረገ መሆኑን፣ በየአህጉረ ስብከቱ የተላለፉ ውሳኔዎችም ተግባራዊ በማድረግ የተረጋጋና ውጤታማ የሥራ ዘመን ያለፈ መሆኑ፣ በሑሳብ አሠራር ሂደትም ዘመናዊ የአሠራር ሂደትን የተከተለ ዜዴ ተግባራዊ መሆኑና አሠራሩ ማዕከላዊነትን እንዲጠብቅ መደረጉ፣ በልማትና በገቢ አሰባሰብ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን፣ በርካታ የአቅም ግንባታ ሥራዎች ሥልጠና መካሄዳቸው፣ ተቋርጠው የነበሩ ሥምሪቶች በተሻለና በሥልጠና ታግዘው መከናወናቸውን እንደመግቢያ በመግለጽ፣ አሠራራችንና አደረጃጀታችንም ዘመኑን በሚዋጅ በግልጽነት እና በተጠያቂነት መርሕ ላይ እንዲመሠረት በማድረግ የቤተክርስቲያኒቱን ተጠቃሚነትና የሕዝበ ክርስቲያኑን ፍላጐት የሚያሟላ ሥራ በመሥራት የምናከናውናቸው ሥራዎች ሁሉ በተቋም ደረጃ ውጤት ሊያመጡ የሚችሉ እንዲሆኑ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት መደረግ እንዳለበት በማሳሰብ በ2007 ዓ.ም በጠቅላይ ቤተክህነት ደረጃ በየመምሪያውና በየድርጅቱ የተከናወኑትን ዋና ዋና የሥራ አፈጻጸም ሪፓርት ከዚህ እንደሚከተለው አቅርበዋል፡፡
በ2007 በጀት ዓመት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን በተመለከተ፡ ቅዱስነታቸው በ2007 ዓ.ም የበጀት ዓመት ለበርካታ አብያተ ክርስቲያናት የገቢ ማስገኛ፣ የወጣቶች ሰንበት ትምህርት ቤቶች ሕንፃዎች፣ ለስብከተ ወንጌል አዳራሾች፣ የአዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት ሕንፃዎች፣ ትምሀርት ቤቶች ግንባታ፣ ሙዚየሞችና ለመሳሰሉት፣ የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጣቸው፤ ግንባታቸው የተጠናቀቁ አብያተ ክርስቲያናትን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ የአህጉረ ስብከት ጽ/ቤቶችን፣ በዘመናዊ መንገድ የተገነቡ የአብነት ትምህርት ቤቶችን፣ መርቀው በመክፈትና ቀድሰው በማቁረብ እንዲሁም በገቢ ማስገኛዎችና የምረቃ መርሐ ግብር ላይ አባታዊ ቡራኬ ምክርና መመሪያ ማስተላለፋቸው፤ ለጉባኤው በአጽንዖት የተገልጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በታላላቅ በዓላት በልዩ ልዩ ዓመታዊ ክብረ በዓላት፣ አጽዋማት፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤያት፣ በአጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፣ በኮሌጆች የምረቃ በዓላት፣ በታላላቅ ብሔራዊና መንፈሳውያን በዓላት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት በመላው ዓለም ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በዓለም አቀፍ ብዙኀን መገናኛዎች መልእክት በማስተላለፍ፤ በልዩ ልዩ ዓለም አቀፍና ሀገር ዘቀፍ ጉባኤዎች ላይ በመገኝት አባታዊ መልእክቶችንና የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ ትምሀርት በማቅረብ፣ ቃለ ቡራኬና ቃለ ምዕዳን በመስጠት የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ድምጽ በሀገር ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም እንዲሰማ ማድረጋቸው ጉባኤው በአድናቆት ተቀብሎታል፡፡ ከዚሁ ጋርም የቅዱስነታቸው ሁለተኛ ዓመት በዓለ ሲመትም በከፍተኛ ድምቀት መከበሩ ለጉባኤው ተገልጧል፡፡
በተለይም ባለፈው ዓመት ውስጥ ትልቁና ዓቢይ ጉዳይ ከነበሩት ውስጥ በሊቢያ የተሰው ኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖችን በተመለከተ ቅዱስነታቸው ዜናው በተሰማበት ተመሳሳይ ቀን የነበረባቸውን ዓለም አቀፍ ጉብኝት በመሠረዝ፣ ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትን አስቸኳይ ጥሪ በማስተላለፍ ሰብስበው በሊቢያ በተሰውት ንጹሐን ክርስቲያኖች የተፈጸመውን አሰቃቂ ግድያ አውግዘዋል፡፡ ሚያዚያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም ለተሰውት ወገኖች ጸሎተ ፍትሐት እንዲደረግ በሰጡት መመሪያ ሚያዝያ 15 ቀን 2007 በቅድስት ሥላሴ ጸሎተ ፍትሐት በማድረግና በመስቀል አደባባይ በተደረገው ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የተሰውት ወገኖች ሰማዕታት ተብለው እንዲጠሩ በቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑን በመግለጽ ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን መልእክት ማስተላለፋቸው፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አሁንም ደማቸውን ሳይቀር የሚሰውሏና ለሐዋርያዊ ትምህርቷ ባዶ እጃቸውን ሁነው የጦር መሣሪያና በያዙና ፊታቸውን በተሸፈኑ አረመኔዎች ፊት እውነተኛ ምስክሮች የሚሆኑ ወጣቶች ያሏት መሆኗን ለመላው ዓለም ማሳወቃቸው ጉባኤው ከፍ አድናቆቱንና አክብሮቱን ለቅዱስነታቸውና ለቅዱስ ሲኖዶስ ግልጧል፡፡
በማያያዝም ቅዱስነታቸው ሚያዝያ 27 ቀን 2007 ዓ.ም ርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤ ባለ ዐሥራ አንድ ነጥብ መግለጫ በማዘጋጀት በመገናኛ ብዙሃን ማስተላለፋቸው፣ ግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም በአስተዳደር ጉባኤ በመገኘት ለሰባት ዓመታት ያህል ተቋርጦ የነበረውን የሰበካ ጉባኤ ስምሪት እንዲቀጥል አባታዊ መመሪያ መስጠታቸው፣ ሰኔ 28 ቀን 2007 በተማሩበት ጭህ ገዳም በመገኘት አባታዊ ቡራኬና ቃለምዕዳን ማስተላለፋቸው እንዲሁም በበጀት ዓመቱ ለበጐ አድራጊ ድርጅቶች ለታማሚዎች ፣ለነዳያን፣ ለእንግዶች፣ ለገዳማትና አድባራት ማጠናከሪያና ማስፋፊያ፣ ለሙዚየሞች ከ1.5 ሚሊየን ብር በላይ መለገሳቸው ለጉባኤው ተገልጧል፡፡
የውጭ ግንኙነት መምሪያ የቅዱስነታቸው መዋዕለ ፕትርክና በሚያስተላልፉት አባታዊ ጥሪና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጥረት መሠረት ከእናት ቤተ ክርስቲያን ተለይተው የቆዩ አጥቢያዎች ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መመለሳቸው የታየበት ከመሆኑም በላይ፣ በበጀት ዓመቱ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ በግብፅ፣ በሱዳንና በቤይሩት ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉዞዎች መደረጋቸውና በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ጉዳያቸው እንዲጣራ የተደረጉ የውጭ ሀገራት አህጉረ ስብከትን ጉዳይ መከታተሉ፣ አገልጋይ እንዲላክላቸው የጠየቁ አህጉረ ስብከቶች አገልጋይ እንዲላክላቸው በቅዱስ ሲኖዶስ አስወስኖ አገልጋዮች መላኩ፤ ከውጭ ሀገራት የመጡ ኢትዮጵያውያንን ግንኙነት ማስፈጸሙና ከውጭ ሀገራትና አዲስ አበባ ከሚኖሩ የውጭ ሀገራት ኤምባሲዎች የተደረጉ ግንኙነቶችን በአግባቡ ማካሔዱ፣ በከፍተኛ ደረጃ ልዩ ክትትልና ማስተካካያ ሊደረግበት የሚገባው የውጭ ሀገር ቤተ ክርስቲያን በአብዛኛው የምትመሠረተው በስደተኞች በመሆኑ፣ ቤተ ክርስቲያን ሳታውቃቸው በሄዱበት ቦታ እናገለግላለን የሚሉ ሰዎች በሰደት የሚኖሩ ምእመናን ሕይወት ችግር ላይ መዳረጋቸው፣ በውጭ ሀገር ያለውን መንፈሳዊ ሕይወት ለመምራት የሚችል ከሀገሮቹ የውሥጥ ደንብ ጋር የሚጠጣም መመሪያ ባለመኖሩ፣ ችግር ከመፍጠሩ ባሻገር ክፍተቱት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም አዲስ አበባ ያለው የቤተ ክረስቲያኒቱ ማዕከል አይመራንም ሲኖዶስ አያዘንም በሚል የማፈንገጥ ድርጊቶች እያደጉ መምጣታቸው፣ የቤተክርስቲያኒቱን ተቋማዊ አደረጃጀት ለፖለቲካ፣ ለንግድ፣ ለግልና ለቡድን ጥቅም ለማዋል የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች መበራከታቸው፣ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመላው ዓለም ስፋታ የምትገኝ በመሆኑ የውጭ ግንነቱ መጠናከር እና ልዩ ትኩረት ማግኙት እንደሚገባው መምሪያው ለሚመለከተው የቤተ ክርስቲያኒቱ አካል ማሳወቁ ለጉባኤው ያሳውቃል፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ቤተ ክርስቲያን በዓለም መድረክ ከሌሎች አብያተ ክርስተያናት ጋር ያላት ግንኙኑነት እየተጣናከረ መምጣቱ፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ ከሮም ካቶሊክ፣ ከአንግሊካን፣ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ኤቫንጀሊካል አብያተ ክርስቲያናት ጋር የምታደርገው ዓለም አቀፍ ውይይተ መቀጠሉ፣ በሀገር ውስጥ ከልዩ ልዩ እምነቶ ጋር በጋራ የምታደረገው የሰላምና የልማት ተሳትፎ መጠናከሩ ለጉባኤው ያሳውቃል፡፡
የአስተዳደር መምሪያ በ2007 ዓ.ም የበጀት ዘመን አቅዶ ሊሠራ ያሰባቸውን ተግባራት በተገቢው ሁኔታ ማከናወኑ፣ በዚህም መሠረት 279 መግለጫዎችን፣ ማስታዎሻዎችን፣ አስተያየቶች አጥንቶ አመራር እንዲሰጥባቸው ማድረጉ፤ 104 ሠራተኞች ተዘዋውረው እንዲሠሩ ማድረጉ፣ 79 የኮሌጆች ምሩቃን እንዲመደቡ ማድረጉ፤ የልደት የጋብቻ የሙትና የትምህርት ማረጋገጫ ሰነዶችን በመስጠት ተገቢውን ክፍያ በመቀበል ገቢ ማድረጉ፤ በመጋዘን የነበሩ ንብረቶች እንደሁኔታቸው እንዲሸጡ በቅርስነት እንዲቀመጡና እንዲወገዱ ማድረጉ፤ የሠራተኞችን ማኅደር በመመርመር በክብር በጡረታ እንዲሰናበቱ መደረጉ፤ ግዥዎች ሥርዓቱንና ሕግን በጠበቀ መንገድ እንዲፈጸሙ፣ የጥገና ሥራዎችና እድሳቶች እንዲከናወኑ መደረጉ፤ ተገልጧል፡፡
የሊቃውንት ጉባኤ በበጀት ዓመቱ የግእዙ መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ጥራዝ እንዲታተም በቅዱስ ፓትርያርኩ በታዘዘው መሠረትና የግእዙ ሐዲስ ኪዳን 2ኛ ማጣራት ተደርጎለት ለሕትመት እየተዘጋጀ መሆኑንና ከልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ስለፀበልና ኤች/አይ/ቪ፣ ስለጽንስ ማቋረጥና ስለወሊድ መቆጣጠሪያ፣ ስለደም መስጠትና መቀበል፣ ስለ ዓይን ብሌንና ኩላሊት ልገሳ በቀረበው ጥያቄ የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምህሮ የሚገልጽ መልስ መሰጠቱ፤ በመናፍቅነት የተጠረጠሩ ሦስት የመንፈሳዊ ኮሌጆች ደቀ መዛሙርትና ሰባክያነ ወንጌል ትምህርት ላይ የቀረበውን መረጃ በጥንቃቄ ተመልክቶ የውሳኔ ሐሳብና አስተያየት ማቅረቡ፣ ከልዩ ልዩ ደራስያንና ግለሰቦች ቀርበው የተመሩ ጽሑፎችን መርምሮ ካሴቶችን አዳምጦ የማስተካከያና ሐሳብ ማስተላለፉን ጉባኤው ተቀብሎታል፡፡
የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ሦስት ዓይነት ቅጾች አሳትሞ ማሰራጨቱ ከአህጉረ ስብከት የሚላኩ ሪፖርቶችንና ቅጾችን በመቀበልና በማገናዘብ ወደ ቅጽ -መ- ማሸጋገሩ፤ ለ33ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በልዩ ልዩ ማወዳደሪያ ላሸነፉ አህጉረ ስብከት የ98,000.00/የዘጠና ስምንት ሺህ ብር/ የህዳሴውን ግድብ ቦንድ ገዝቶ መሸለሙ፤ የሰበካ ጉባኤ ዓላማን ለማጠናከር በምዕራብ ጎጃም፣ በሶማሌ፣ ደ/ም/ሥ/ትግራይና በሽሬ እንዳሥላሴ አህጉረ ስብከት ስምሪት በማድረግ ሥልጠናዎችና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ማከናወኑ፤ ከተለያዩ አህጉረ ስበከት በሰበካ ጉባኤ ዙሪያ የቀረቡ ማመልከቻዎች ላይ መግለጫዎች እንዲቀርቡ ማድረጉ፣ በተጨማሪም ከዋናው መሥሪያ ቤት የተላለፉ መመሪያዎችና ትዕዛዞች በመምሪያው በኩል ተፈጻሚነት እንዲያገኙ፣ ለሰባት ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን ስምሪት እንዲጀመር 50 ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንን በማስማራት ለ46 አህጉረ ስብከት ሴሚናር እንዲሰጥ ማድረጉ ተገልጧል፡፡
የካህናት አስተዳደር መምሪያ በበጀት ዓመቱ ሊቀውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ በአበይት በዓላት ካህናትና መዘምራንን በማስተባበር የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ 2ኛ ዓመት በዓለ ሢመትን ጨምሮ ዓበይት በዓላት በታላቅ ድምቀት እንዲከበሩ አድርጓል፡፡
የበጀትና ሒሳብ መምሪያ በነደፈው የገቢና ወጭ ዕቅድ መሠረት ሒሳቡን ገቢና ወጭ ያደረገ መሆኑ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በራሳቸው ሒሳብ የሚያንቀሳቅሱ መምሪያዎች ሒሳባቸው በአንድ ቋት እንዲሆን፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሒሳብ የደብል ኢንትሪ ሒሳብ አሠራርን በመከተል በዘመናዊ መንገድ እየሠራ መገኘቱ፣ ለመምሪያውን ሠራተኞች የብቃት ማሻሻል ሥልጠናዎችን መስጠት፣ የሠራተኞች ደመወዝ ክፍያና የቤትና ሕንፃዎች አስተዳደር ድርጅት የቤት ኪራይ አሰባሰብ በባንክ እንዲሆን ማድረጉን ጉባኤው በአድናቆት ተቀብሎታል፡፡
የገዳማት መምሪያ ከቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤትና ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የተመሩለትን ጉዳዮች በጥንቃቄ መርምሮ ተገቢውን አሰተያየትና የውሳኔ ሐሳብ ማቅረቡ፣ አበምኔቶችና እመምኔቶች ስልጠና ለመሰጠት ዝግጅት ማድረጉን፤ ገዳማት የቱሪስት መስሕብና የምርምር ማዕከላት እንዲሆኑ፣ ከግልና ከማኀበራት ተረጅነት ወጥተው ራሳቸውን እንዲችሉ መነኰሳት በዓታቸውንና አገልገሎታቸውን አጽንተው ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆኑ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑ ለጉባኤው ተገልጧል፡፡
የቅ/ጥ/ቤ/ወመዘክር መምሪያ ለተጠቃሚዎች አገልግሎት መስጠቱ ለሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ተመራማሪዎች ደብዳቤና ለአንድ የጥናት ጽሑፉ ማስተካከያ መስጠቱ፤ ቅርሶች እንዲመለሱና የቅርስ ቀሳጢዎች ሕጋዊ ውሳኔ እንዲያገኙ እየሠራ መሆኑ ለጉባኤው ተገልጧል፡፡
የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ፡ በ44 አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት፣ በታላላቅ ዓመታዊ በዓላት፣ በየአብይ ጾምና በጾመ ፍልሰታ በልዩ ልዩ የውጭ ሀገርና የሀገር ውስጥ አህጉረ ስብከት ስምሪት ማድረጉ በመምሪያው ኃላፊነት የሚዘጋጁ የሕትመት ውጤቶች ጊዜያቸውን ጠብቀው እንዲታተሙና እንዲሠራጩ መደረጉ፣ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ስርጭትን ለማቋቋም የሚያስችለውን ጥናት ለቅዱስ ሲኖዶስ አቅርቦ ከጸደቀ በኋላ፣ ሥራ አመራር ቦርዶችን መሰየሙ ለጉባኤው ተገልጧል፡፡
የቁልቢ ንዋየ ቅድሳት ማደራጃ አንድ መኪና መግዛቱን የገለጸ ሲሆን ፣ ገቢ በሚገኝባቸው በዓላት ቀን ከዋናው መሥሪያ ቤት ፈቃድ ሳያገኙ በሀገረ ስብከቱ ፈቃድ ልመና የሚያካሒዱና ገንዘብ ሚሰበስቡ ተቋማት በቤተ ክርስቲያኒቱ ገቢና ማዕከላዊ ሥራ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እየፈጠሩ መሆኑንና ሥጋት እንዳደረበት በመግለጽ መፍትሔ እንዲሰጥ አሳስቧል፡፡
የዕቅድና ልማት መምሪያ በመምሪያዎችና ጽ/ቤቶች ተዘጋጅቶ የቀረበውን ዕቅድ ወጥ በሆነ መንገድ በማዘጋጀት በአስተዳደር ጉባኤ እንዲገመገምና ሥራ ላይ እንዲውል ማድረጉ፣ ከስፖንሰር በተገኘ ድጋፍ ልማትና ቤተክርስቲያን የሚል መጽሔት አሳትሞ በነፃ በማሰራጨት የቤተክርስቲያኒቱ የልማት ሥራዎች ያለበትን ደረጃ የተለያዩ አካላት ግንዛቤ እንዲያገኙ ማድረጉ፣ በተለይ በመንገድ ዳር በቤተ ክርስቲያን ስም የሚደረጉ ልመናዎች ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግባቸው ተገቢ የሆነ ሥራ በመሠራትና ጸሎትና አምልኮት የሚፈጸምባቸው ሥዕላትና ንዋየ ቅድሳት መለመኛ ያደረጉ 15 ሰዎች በሕግ እንዲጠየቁ፣ ንብረቶቹም እንዲወረሱ ማድረጉ ጉባኤውን ያስደሰተ ሲሆን በዘላቂነት የመንገድ ዳር ልመናው የሚቆምበትን ሒደት ለመፍጠርም እየተሠራ መሆኑ በጉባኤው አድናቆት አግኝቷል፡፡ መምሪያው ለልዩ ልዩ ደብዳቤዎች የሰጠው ተገቢ መግለጫ፣ በ51 አህጉረ ስብከት 534 አብያተ ክርስቲያናት የግንባታ ፈቃድ እንዲያገኙ ያደረገው ጥረት፣ የልማት ሥራዎችን በአግባቡ በመዘገብ ያስመዘገበው ስኬት፣ በይበልጥም ሕገ ወጥ ሙዳየ ምጽዋቶችን ጉዳይና በቤተክርስቲያኒቱ ስም በልዩ ልዩ መንገድና በየመንገዱ በመኪና እየዞሩ የሚለምኑ ወገኖችን በተመለከተ ጉዳዩ ቤተ ክርስቲያንን አቅም ከማዳከም ባሻገር ቀኖናዋንም የጣሰና ክርስቲያናዊ ባለመሆኑ የቤተ ክርስቲያን ቀኖናዊ ውሳኔ ብቻ ሳይሆን ሕጋዊ ርምጃ ለማስወሰድ የሚያደርገውን ጥረት ጉባኤው በከፍተኛ ድጋፍ ተቀብሎታል፡፡
የትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ፡ በበጀት ዓመት የቤተክርስቲያኒቱ አንጡራ ሀብት ለሆኑት የአብነት መምህራን ቅዱስነታቸው በተገኙበት "ትንሣኤ ለአብነት ትምህርት ቤቶችና መምህራን" በሚል ርዕስ 1000 ለሚጠጉ የአብነት መምህራን አውደ ጥናት በማድረግ በምሁራን ጥናታዊ ጽሑፎች እንዲቀርቡ ማድረጉ፣ ወደ አብነት ትምህርት ቤቶችና መንፈሳውያን ኮሌጆች የሚገቡ ደቀመዛሙርት የመግቢያ መሥፈርት ተምረው ሲጨርሱ የሥራ ዋስትና እንዲያገኙ መሥራቱንና ተጨማሪ ጥናት ማቅረቡን፣ የኮሌጆች ምሩቃን ደቀ መዛሙርት እንዲመደቡ ማድረጉ፣ በአጠቃላይ ስለ አብነት ትምህርት ቤቶች፣ መምህራንና ደቀመዛሙርት የሚደርገው ጥረት ለቤተ ክርስቲያን ዘላቂ ሕልውና አማራጭ የለሽ ሊበረታታና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው በመሆኑ ጉባኤው በከፍተኛ አድናቆት ተቀብሎታል፡፡
የቁጥጥር አገልግሎት በበጀት ዓመቱ የጠቅላይ ቤተክህነት መምሪያዎች፣ ድርጅቶችና ኮሌጆች የገቢና ወጪ ሒሳብ ተመርምሮ ውጤቱ ለበላይ አካል ማቅረቡን፣ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ገዳማትና አድባራት ሒሳብ ከሀ/ስብከቱ ሠራተኞች ጋር በመሆን ኦዲት ማድረጉን፣ ዋናው መ/ቤት ለኦዲት ሥራ የሚያስፈልገውን ወጪ በመሸፈን ኦዲት መደረጉና እያደረገ መሆኑ፤ በተጨማሪም የማበረ ቅዱሳን ጽ/ቤት በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት በዋናው መ/ቤት ዕውቅና ባላቸውና ለቁጥጥር በሚያመች መልኩ በታተሙ ሞዴላ ሞዴሎች ከዋናው ማዕከል እስከ ንዑስ ማዕከላት ድረስ እንዲጠቀሙ ማድረጉን፣ ለጉባኤው ተገልጧል፡፡ በበጀት ዓመቱ ኦዲት ከተደረጉ መካከል የፋይናንስ ሕግና ደንብን ተከትለው የሠሩ አህጉረ ስብከቶች ሲዳማ ጌዲኦ አማሮና ቡርጂ ዞኖች ሀ/ስብከት ጽ/ቤት፣ የሰማን ሸዋ ሰላሌ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት በየዓመቱ የኦዲተሮችን የውሎ አበልና ትራንስፓርት ወጭ መሸፈኑ የሰ/ም/ ዞን ሽሬ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት የቃለ አዋዲውን ደንብ በመከተል የገቢና ወጪ ሒሳብ በአግባቡ ጠብቆ ለልማት እንዲውል በማድረግ ለሌሎች አርዓያነታቸው እንዲገለጽ ማፈለጉን ተገልጧል፡፡
የአልባሳት ማደራጃ መምሪያ፡ ከአልባሳት፣ ካባና አክሊል፣ ከመፆርና የእጅ መሰቀል፣ ከመጎናጸፊያና ቀጸላ፣ ከበሮ መቋሚያ ተዘጋጅቶ ለገብያ በማቅረብ ገቢ ማድረጉ ለጉባኤው ተገለጧል፡፡
የተቸገሩ አብያተ ክርስቲያናት፣ በአይነትና በጥሬ ከሰበሰበው ከዚሁ ገንዘብ ወጭ በማድረግ የመቀደሻ አልባሳት ፣ መጎናጸፊያ ፣ ጥላ ፣ ዕጣንና ጧፍ፣ዘቢብ እንዲሁም ለተለያዩ ድርጅቶች ድጋፍ ፣ለአህጉረ ስብከቶች፣ ለበዓል መዋያ፣ ለግለሰቦች ርዳታ፣ ድጋፍ በማድረግ ኃላፊነቱን መወጣቱ ጉባኤው በአድናቆት ተቀብሎታል፡፡
የትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅትን የሚያሳትማቸው መጻሕፍት ተፈላጊነታቸው እያደገና በጣም እየጨመረ መምጣቱ፣ እና የቅድስት ቤተ ክርስቲያኒቱን ማዕከላዊነት በመጠበቅ ረገድም የገንዘብና የንብረት ገቢና ወጪ ደረሰኞችን ፣ የክርስትናና የጋብቻ የምስክር ወረቀቶችን፣ የካህናትና የምዕመናን መታወቂያ ካርዶችን፣ የምእመናን መመዝገቢያ ቅጾችን ፣ ማህተሞችንና ቲተሮችን የመሳሰሉትን ሁሉ በየጊዜውና በየወቀቱ በማሳተምና በማሰራጨት ለቤተክርስቲያኒቱ የሚሰጠውና የሚያበረክተው አገልግሎት ትልቅ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ በ2007 በጀት ዓመት 38,000 ቅዱሳት መጻሕፍት ፣614,330 ሞዴላ ሞዴሎች ፣ ማህተሞችና ቲተሮችን መሠራጨታቸው ተገለጧል፡፡
የቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ፡ በበጀት ዓመቱ በሰርተፊኬት፣ በመደበኛ በዲኘሎማ፣በድግሪ ፣ በማስትሬት ፣ በሐዲስ ኪዳንና በብሉይ ኪዳን ትርጓሜ መጻሕፍት እንዲሁም በኤክስቴንሽንና በርቀት በዲግሪና በዲኘሎማ ደረጃ እያስተማረ መሆኑ፣ በበጀት ዓመቱ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ 126 ደቀ መዛሙርት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ በተገኙበት በዲግሪ በዲኘሎማ በሰርተፊኬት ማስመረቁ፤ ለኮሌጁ የትምህርት የሞጅል ዝግጅቶች ፣ አርቲክሎች የጥናትና ምርምር ሥራዎች ማዘጋጀቱ፣ ሲምፖዝየም ማካሄዱ፣ ኮሌጁ የዘመናዊ ሐሳብ አሠራር ተጠቃሚ መሆኑና የአጸደ ሕጻናት ግንባታ ተጠናቆ ሥራውን መጀመሩ፣ የባለ 5 ፎቅ ሕንጻም ግራውንዱ ሙሉ በሙሉ ያለቀ ሲሆን በሰኔ ወር 2007 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አባታችን መሠረቱ የተቀመጠው ባለ 10 ፎቅ ሕንጻም ግንባታው እንዲጀመር ማድረጉ ጉባኤው በከፍተኛ አድናቆት ተቀብሎታል፡፡
የትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤትን ከነበረበት ዝቅተኛ ደረጃ ለማንሣት እተደረገ ያለው ጥረት እጅግ ከፍተኛ ሲሆን ማተሚያ ቤቱ በበጀት ዓመቱ የሕትመት ቁሳቁስ በክምችት በመያዝ ከፍተኛ ለውጥን እያስመዘገበ መገኘቱ፣ 308.000 ብር ለጡረተኞች መክፈሉ፣ ከዚህ በተጨማሪ ሥራ አቁሞ የነበረውን ዲጂተል መቁረጫ፣ ከጥቅም ውጭ ሁነው የነበሩ ሁለት ማሽኖችን በአስተማማኝ ሁኔታ በዝቅተኛ ወጪ ማስተገኑና ወደ ሥራ መመለሱ፣ ለሠራተኞችን የአቅም ግንባታ ሥልጠናና የልምድ ልውውጥ እንዲኖራቸው ማድረጉ፣ የሕትመት ጥራት ለመጠበቅ የሚያደርው ጥረት ውጤታማ እንዲሆንና የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖረው እያደረገ ያለውን ግስጋሴ ጉባኤው በአድናቆት ተቀብሎታል፡፡
ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ አንጋፋና የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት መፍለቂያ እንደመሆኑ በ2007 ዓ.ም የበጀት ዓመት ከኮሌጁ በሥነመለካት ትምህርት በሠርተፊኬት፣ በዲኘሎማና ፣ በዲግሪና በድህረ ምረቃ ፕሮግራም ትምህርት እየሰጠ መገኘቱ፣ የኮሌጁ የአካዳሚክ አቅም ለማሳደግ 10 መምህራንን በድህረ ምረቃ ማስመረቁ፣ የበጀት ዓመቱ ተመራቂ የቀንና የማታ ተማሪዎችን በታላቅ ድምቀትና ሥነ ሥርዓት በቅዱስ ፓትርያርኩ ማስመረቁ፣ በርቀት ትምህርት በሀገር ውስጥና በውጪ እያስተማረ መሆኑ፣ ቤተ መጻሕፍቱን እያጠናከረ እንደሚገኝ በተለይም የኮሌጁን አቅም በማሳደግ ወደ ዩኒቨርስቲ ለማሳደግ እያስጠና መሆኑና የገቢ አቅሙን ለማሳደግም በኮሌጁ እየተገነቡ ያሉት ሕንፃች ጉባኤው በታላቅ አድናቆት ተቀብሎታል፡፡
ጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል እደ ጥበብ ማሠልጠኛ ድርድት በድርጅቱ ለሚገኙ ሠራተኞች በተለየዩ የሙያ ዘርፎች ስልጠና ተሰጥቷል ፣ከመንበር ጀምሮ ለቤተክርስቲያን መገልገያ የሚያገለግሉ በእደ ጥበብ በሚመረቱ ንዋየተ ቅዱሳትን እየመረተ የቤተ ክርስቲያኗን ዶግማ፣ ቀኖናና ትውፊት በጠበቀ መልከ እየሠራ ለገበያ በማቅረብ ቤተክርስቲያን እንድትገለገል ማድረጉና ባለው ክፍት መሬት ላይ ተጨማሪ የገቢ ማስገኛ ለመሥራት በባለሞያ ፕሮጀክት ማስቀረፁ፣ የይዞታ ማረጋገጫ ለመረከብ ክትትል ማድረጉ ጉባኤው ተቀብሎታል፡፡
የሕግ አገልግሎት መምሪያ ከዋና ሥራ አሥኪያጅና ከምክትል ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም መምሪያዎችና ድርጅቶች የቀረቡለትን የሕግ አስተያየትና መግለጫ መልሰ መስጠቱ፣ በጐሬ ከተማ ለሚቆመው የብፁዕ አቡነ ሚካኤል ሐውልት ሥራ ተጨማሪ የውል ሕግ እንዲስተካከል ማድረጉ፣ ውሎች ማዘጋጀቱ፣ በመደበኛ ፍ/ቤት በከሳሾች በቀረበው የተለያዩ ክሶች ከፍተኛ ኪሳራ ሊያስከትሉ የነበሩትን ከ14 በላይ የሆኑ የተለያዩ መዝገቦች በበቂ ሁኔታ ተከራክሮ በማስወሰን ከፍተኛ ውጤት ማምጣቱ ጉባኤው በከፍተኛ አድናቆት ተቀብሎታል፡፡
መንፈሳዊ ፍርድ ቤት፣ ተጠሪነቱ ለቀዱስ ሲኖዶስ ሆኖ እንዲሠራ በ2007 ዓ.ም ተሻሽሎ በወጣው ሕገ ቤተክርስቲያን አንቀጽ 22/1/ለ ላይ የተደነገገ በመሆኑ ከምንጊዜም በላይ ተጠናክሮ እየሠራ መሆኑ፣ በሥር ፍ/ቤት በተሰጡ ውሳኔዎች ላይ ቅሬታ አለን በሚል በይግባኝ ደረጃ 22 መዝገቦች መታየታቸውን ከዋናው መ/ቤት ሠራተኞች በሕመም በጡረታ በተለያዩ ምክንያቶች የውክልና አገልግሎት በመስጠት የተጣለበትን ኃላፊነት መወጣቱን ጉባኤው ተቀብሎታል፡፡
የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ካሌጅ፣ በበጀት ዓመቱ በብሉይና በሐዲስ ትርጓሜ እና በሴሚናር 240 ደቀ መዛሙርትን፣ በቀኑና በማታው የትምህርት ክፍለ ጊዜ ያሰለጠናቸውን ደቀ መዛሙርት በብፁዕ ወቅዱሰ ፓትርያርክ ማስመረቁ በቀንና በማታው ክፍለ ጊዜ ከ800 በላይ የሆኑ ደቀ መዛሙርትን ተቀብሎ በማስተማር ላይ መሆኑና ልዩ ልዩ መጻሕፍትን መግዛቱ ደቀ መዛሙርቱ የኮምዩተር እውቀት እንዲኖራቸው ለማስቻል ስልጠና እየሰጠ መገኘቱ ጉባኤው ተቀብሎታል፡፡
የሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ በበጀት ዓመቱ ለ896 ሕፃናት የመኪና፣ የምግብ፣ የአልባሳት፣ የጤና፣ የመንፈሳዊ ሥነ ልቡናና የትምህርት መሣሪያዎች ድጋፍ ማድረጉ፣ በ15 ሕፃናት መርጃ ማዕከላት ለምግብና ለመሠረታዊ ወጭ ወረኃዊ የገንዘብ ድጎማ፣ ነፃ የሕክምና አገልግሎትና ፣የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲያገኙ 309 ወጣቶች በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች 293 ወጣቶች ደግሞ በተለያዩ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ገብተው ትምህርትታቸውን እንዲከታተሉ የገንዘብ ድጎማ ማድረጉ፣ ማዕከሉ በሐዋርያው ጳውሎስ ፣ በደብረ ታቦር ፣ በመቀሌ ፣ውቅሮ፣ ኮረም፣ በጎባ፣ በገነተ ኢየሱስ፣ በፈለገ ሕይወት የሕፃናት መርጃ ማዕከላት የማስፋፋት ሥራ መሥራቱና 1304 ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ መሆኑ ሲገለጽ፤ ለ60 እናቶች ልዩ ልዩ ሥልጠና 261 ሕፃናት የገንዘብና የአልሚ ምግብ ድጋፍ ማድረጉ፤ ለ10 የኤች አይቪ /ኤድስ/ እና የቲቪ በሽተኞች ተጨማሪ አልሚ ምግብ እና ለተለያዩ ችግሮች ለተጋለጡ 50 ሕፃናት የገንዘብ ድጋፍ ማበርከቱ፣ በአካባቢ ንጽህና አጠባበቅ ዙሪያ ለ4624 የሕፃናት አሳዳጊዎች ስልጠና መስጠቱና ለ100 ሕፃናት ብርድ ልብስ ለ202 ሕፃናት የንጽህና መጠበቂያ የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ጉባኤው ሰምቶ ተቀብሎታል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የልማትና ክርስቲያን ተራድኦ ኮሚሽን ከተመሠረተ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በሚያካሂዳቸው የልማት ፕሮግራሞችና አሳታፊ እንቅስቃሴዎች በየደረጃው የሚገኙ የክልልና የወረዳ መንግሥት አሰተዳደርና የሚመለከታቸው ሴክተር ቢሮዎች እንደዚሁም ተጠቃሚው ማኅበረሰብ ኮሚሽኑ አንደኛ የተቀናጀ የገጠር ልማት ፕሮግራም፡ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ክብካቤ፣የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ምንም ገቢ ለሌላቸውና አነስተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተጨማሪ የገቢ ምንጭ በመፍጠርና እንደዚሁም የንጹህ ውሃ አቅርቦትን የሕፃናትን ሥርዓተ አመጋገብንና በሽታን መከላከል ጨምሮ የተለያዩ ማበራዊ ተጠያቂነትን ጽንሰ ሐሳብ ግንዛቤ እንዲያዳብርና በማበራዊ ሕይወቱም እንዲጠቀምበት በማድረግ፣ 11 ፕሮጀክቶች በአማራ ፣ በትግራይና በኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ተካሂደው በርከት ያሉ ተግባራት ተከናውነው 280,582 ሕዝብ ተጠቃሚ ማድረጉን፣ ሁለተኛ በንፁህ ውሃ አቅርቦት ፣ የአካባቢ ጽዳትና ንጽህና አጠባበቅ ፕሮግራም፡ ለተጠቃሚዎች የውሃ አቅርቦትን በመጠንም ሆነ በጥራት ማሻሻልና የንጽህና ሽፋንን መጨመርና በጽዳትና የአካባቢ ንጽህና አጠባበቅ ላይ የተሻለ ግንዛቤ በመፍጠር 4 ፕሮጀክቶች በአማራ፣ በትግራይና በኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በጠቅላላው 216,524 ሕዝብ ተጠቃሚ ማድረጉን፣ ሦስተኛ፡ ኮሚሽኑ የኤች አይቪ ኤድስ ችግር በሀገሪቱ ውስጥ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ባለማቋረጥ ዘርፈ ብዙ የሆኑ የኢኮኖሚ፣ ማበራዊና የሥነ ልቡና አገልግሎት ድጋፍ በመስጠት የላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ መገኘቱንና በዚህም 6 ፕሮጀክቶች በልዩ ልዩ ክልሎች 2.3 ሚሊዮን ሕዝብ ተጠቃሚ መሆኑን፣ አራተኛ፡ በስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ድጋፍና ክብካቤ ፕሮግራም 2 ፕሮጀክቶች በትግራይ፣ ጋምቤላ ፣ ሶማሌና አዲስ አበባ ክልሎች በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በማካሄድ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾችን መሠረታዊ ፍላጎቶች ሊያሟሉ የሚችሉ የምግብ፣ የልብስ ፣ የጤና የትምህርትና የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች መስጠት ተግባራትን ማከናወኑና ከተሰጠውም አገልግሎት በጠቅላላው 222,000 ሰዎች ተጠቃሚ ማድረጉን ሲገልጽ ጉባኤው የኮሚሽኑን የልማትና የማኅበራዊ አግልግሎ ተግባራ በአድናቆት ተቀብሎታል፡፡
የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደና ልማት ድርጅት፣ በ2007 ዓ.ም የበጀት ዓመት ሊሰበስብ ካቀደው ውስጥ ብር 28,691,794.70/ሃያ ስምንት ሚሊየን ስድስት መቶ ዘጠና አንድ ብር ከሰባ ሣንቲም/ በመሰብሰብ የእቅዱን 94.8 ፐርሰንት ማሳካቱን፤ ከተከራዮች ጋር በተደረገ ስምምነትም ብር 4 ሚሊዮን የሚፈጅ እድሳት ማድረጉንና የኪራይ ጭማሪ በበጀት ዓመቱ በመደረጉም 4 ሚሊየን ብር ተጨማሪ የኪራይ ገቢ ማግኘቱ ለጉባኤው ተገለልጧል፡፡ በባንኮ ዲሮማ እየተገነባ ያለው ሕንጻ 70 ፕርሰንት መድረሱን፣ የይዞታ ካርታን በሚመለከት በአራዳ ክፍለ ከተማ 156 ቤቶች፣ በጉለሌ ክፍለ ከተማ 29 ቤት በድምሩ 185 ቤቶች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲያገኙ እየተሠራ መሆኑን፣ ከቻይና ኩባንያ ጋር በአራት ኪሎ አካባቢ ለማልማት የታሰበውን ቦታ በተመለከተ የማስተር ኘላኑን ስኬማቶክ ዲዛይን ግምቱ 3,500,000.00 /ሦስት ሚሊየን አምስት መቶ ሽህ ብር/ በአባ አርክቴክት/ኃ/የተ/የግ/ማህበር በነጻ ለቤተክርስቲያን ተጠንቶ እንዲበረከት ማድረጉን፣ የቤቶችና ሕንጻዎች አስመላሽ ኮሚቴም በአዲስ አበባ በአሮጌ ቄራ አካባቢ ባለ 23 ክፍልች ሆቴል እንዲመለስ ማድረጉን፣ የተገለጸ ሲሆን፣ የሕዝብ ተወካይ ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲሁም የኦሮሚያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በቢሮነት የሚገለገልበትና የፊንፊኔ ዱካ ሆቴል ሕንጻዎች የካሳ ግምት ተብሎ ብር 71,051,517.80/ሰባ አንድ ሚሊየን ሃምሳ አንድ ሺህ አምስት መቶ አሥራ ሰባት ሺህ ብር ከሰማኒያ ሣንቲም/ ገቢ ሆኖ የማይንቀሳቀስ አካውንት ተከፍቶለት እንዲቀመጥ መደረጉንና ካሣ ተቀብለንባቸዋል በተባሉት በአራቱ ሕንጻዎች ምትክ ሕንፃ መሥሪያ ቦታ 1ኛ ደረጃ 22,856 ካሬ ሜትር ቦታ ለመረከብ በዝግጅት መሆኑ በመግለጽ ድርጅቱ አሁንም ያልተመሰሉ ቤቶች በአዲስ አበባ ከተማ 285፤ በሐረር ከተማ 25 ቤቶችና ሕንጻዎች መኖራቸውን ገልጾ የማስመለሱ ጉዳይ ክትትል እየተደረገበት መሆኑን፣ በዳግማዊ ምኒሊክ ት/ቤት ፊት ለፊት ያሉት በቤት ቁጥር 1166-1669 የተመዘገቡት ባለ 12 ፎቅ ሕንፃዎችና መለስተኛ ሕንጻ እንዲመለስ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ የቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ባያገኝም ጉዳዩ ፍትሐዊ አለመሆኑን ኮሚቴው ለቅዱስ ሲኖዶስ በማስረዳትና ማስረጃዎችን በማደራጀት ቤቶቹ የሚመለሱበትን ሒደት እየተከታተለ መገኘቱ በላሊበላ ከተማ በተለምዶ 7 ወይራ ሆቴል በመባል የሚታወቀው ሆቴል ጉዳይ እልባት አለማግኘትና በድሬድዋ ከተማ ከሚገኙት 23 ቤቶች መካከል ለድሬደዋ ደ/ም/ቅ/ሚካኤል ቤተክርስቲያን ያለ ቅዱስ ሲኖዶስ ትዕዛዝ 5 ቤቶች መሰጠቱ በበጀት ዓመቱ ከታዩ ችግሮች መካከል መጥቀሱን ለጉባኤው የተገለጹ ሲሆን ጉባኤው የተገለጸውን ሪፖርት ተቀብሎ ሊሠሩ የሚገባቸው እንዲሠሩ ሐሳቡን በድጋፍ ገልጧል፡፡
የሰንበት ትምህርት ቤቶች መምሪያ፡ አደረጃጀቱን በማጠናከር ከመላው ሀገሪቱ ካሉ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ጋር የተጠናከረ ግንኙነት መጀመሩ፣ ለ60 አህጉረ ስብከት የሪፖርት አቀራረብ መመሪያ ፣ የግምገማ ሰነድ ማሰራጨቱ፣ የ2007 ዓ/ም መስቀል በዓል በድምቀት ማክበሩ፣ ሥልጠናዎች ማካሄዱ፣ የዌብሳይት አገልግሎቱን ማጠናከሩ፣ በጉጉት ሲጠበቅ የኖረውን የሰንበት ትምህረት ቤቶች ማስተማሪያና የመዝሙር መጽሐፍ በተሳካ ሁኔታ አሳትሞ ማሰራጨቱ ጉባኤው በአድናቆት ተቀብሎታል፣ ይሁን አንጅ መምሪያው የበጀት እጥረት፣ የመልካም አስተዳድርና ፍትሕ እጦት፣ የትኩረት ማጣት፣ እና የማኅበራት ወሰን የለሽ ጣልቃ ገብነት በበጀት ዓመቱ የነበሩበት ችግሮች መሆናቸው በጉባኤው እንዲታወቅ ጠይቋል፡፡
ማህበረ ቅዱሳን በልዩ ልዩ አህጉረ ስብከት ገዳማት፣ አድባራትና አብያተ ክርስቲያናት፣ የአብነት ትምህርት ቤቶች 19,014,016.80/አሥራ ዘጠኝ ሚሊየን አሥራ አራት ሺህ አሥራ ስድስት ብር/ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን፣ ከየአህጉረ ስብከት ለጠየቁ 38 አብያተ ክርስቲያናት የሕንጻ ዲዛይን እና የልማት ሥራዎች ኘሮጀክት ጥናት በነፃ አጥንቶ መስጠቱት፣ ጠረፋማ የሆኑትን አህጉረ ስብከትን በመለየት ትምህርተ ወንጌል መስጠቱና 13776 ሰዎችን እንዲጠመቁና 6 አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነጹላቸው ማድረጉን፣ በትምህርት ተቋማት ወጣቶችን እያስተማረ እንዳለና የተወሰኑትን መርጦ የአብነት ትምህረት እንዲያገኙ መድረጉና በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት በትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት በታተመ የገቢ መሰብሰቢያ ደረሰኝ በመጠቀም ላይ መሆኑን ለጉባኤው ተገልጧል፡፡
የበጀት ዓመቱን አጠቃላይ ገቢን አስመልክቶም በሪፖርቱ በበጀት ዓመቱ ከሃምሳው አህጉረ ስብከት ብር 59,116,899.68/ሃምሳ ዘጠኝ ሺህ አንድ መቶ አሥራ ስድስት ሺህ ስምንት መቶ ዘጠና ዘጠኝ ብር ከስልሳ ስምንት ሣንቲም/ገቢ የተደረገ ሲሆን ከአምናው ጋር ሲነጻጸር የብር 13,984,494.26/አሥራ ሦስት ሚሊየን ዘጠኝ መቶ ሰማኒያ አራት ብር ከሃያ ዘጠኝ ሣንቲም/ብልጫ ማስመዝገቡ ጉባኤው እጅግ ከፍ ባለ ድጋፍ ተቀብሎታል፡፡
በ2007 ዓ.ም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ብር 66,668,379.25/ ስልሳ ስድስት ሚሊየን ስድስት መቶ ስልሳ ስምንት ሺህ ሦስት መቶ ሰባ ዘጠኝ ብር ከዘጠና አምስት ሣንቲም/ገቢ ማድረጉና ከአምናው ጋር ሲነጻጸት የ16432074.68/የአሥራ ስድስት ሚሊየን አራት መቶ ሠላሳ ሁለት ሺህ ሰባ አራት ብር ከስልሳ ሣንቲም/ ብልጫ ማስመዝገቡ ጉባኤው እጅግ ከፍ ባለ ድጋፍ ተቀብሎታል፡፡
በ2007 ዓ/ም በሃምሳው አህጉረ ስብከት ብር 125785279.95/አንድ መቶ ሃያ አምስት ሚሊየን ሰባት መቶ ሰማኒያ አምስት ሺህ ሁለት መቶ ሰባ ዘጠኝ ብር ከዘጠና አምስት ሣንቲም/ ገቢ መሆኑንና ከአምናው ጋር ሲመዘዘን የብር 30,416,568.94/ሰላሳ ሚሊየን አራት መቶ አሥራ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ስልሳ ስምንት ብር ከዘጠና አራት ሣንቲም/ብልጫ ማስመዝገቡ ጉባኤው እጅግ ከፍ ባለ ድጋፍ ተቀብሎታል፡፡
ከዚህ አጠቃላይ ገቢ ውስጥም ብር 5,381,655.29/አምስት ሚሊየን ሦስት መቶ ሰማኒያ አንድ ሺህ ስድስት መቶ ሃምሳ አምስት ብር ከሃያ ዘጠኝ ሣንቲም/በልማት ገቢ የተደረገ ሲሆን በዘርፉ ጠንክሮ መሥራት የሚገባ በመሆኑ የተለየ ትኩረት ሊሠጠው የሚገባ መሆኑ፣ በ2007 ዓ/ም ይህ የገቢ እድገት ሊመዘገብ የቻለው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና በየደረጃው ያሉ የሥራ ኃላፊዎች ጠንክረው በመሥራታቸው በመሆኑ ወደፊትም ይህንን ዕድገት አስጠብቆ የበለጠ ዕድገት ለማስመዝገብ ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባ ጉባኤው በከፍተኛ ድጋፍ ተቀብሎታል፡፡
በተያያዘም በበጀት ዓመቱ በገቢ ራሳቸውን ያልቻሉ 19 አህጉረ ስብከት የተመዘገቡ ሲሆን ባለፈው ዓመት በገቢ ራሳቸውን ያልቻሉ ሆነው ከተመዘገቡት 23 አህጉረ ስብከት አራቱ ማለትም ሰሜን ኦሞ /ጋምጐፋ/፣ ጅማ፣ ምዕራብ ሐረርጌ እና ወላይታ አህጉረ ስብከት ራሳቸውን በመቻላቸው ጉባኤው በከፍተኛ ድጋፍና አድናቆት ተቀብሏል፡፡
በመጨረሻም የብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ዘገባም ቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ የምታስመዘግበውን ሁለንተናዊ እድገት አስደናቂ ሲሆን የበለጠ እንዲስፋፋ፣እንዳጠናከርና ውጤታማ እንዲሆን ሥራዎች ሁሉ በዕቅድ እንዲከናወኑ ውጤቶቻቸው እንዲገመገም በማድረግ ዘመኑን የዋጀ ሥራ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆን እንደሚገባ፣ በማለት በድጋሜ እንኳን ለ34ኛው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በሰላም አደረሳችሁ በማለትና ጉባኤው የተቃናና የተሳካ እንዲሆን የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ያደረገውን ጥረት በማድነቅ በ2007 በጀት ዓመት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ጽ/ቤት የተከናወኑ ዋና ዋና የሥራ አፈጻጸም ዘገባ ወይም ሪፓርት አጠናቀዋል፡፡

7. ከመላው ዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሰ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አህጉረ ስብከት ለጉባኤው የቀረቡ የ2007 ዓ/ም ሥራ አፈጻጸም ዘገባዎች

7.1 በሀገር ውስጥ አህጉረ ስብከት

ሀ. በሀገር ውስጥ ካሉ አህጉረ ሰብከት የተጠቀሱ ችግሮች

1. በአንዳንድ አህጉረ ስብከት ሰበካ ጉባኤን ለማጠናከር የቤተ ክርስቲያን ዘርፈ ብዙ ገቢ ለማሳደግ በሚደረጉ ጥረቶች ቃለ ዓዋዲ አለመሻሻልና ዕውቅና አለማግኘት መመሪያን አንቀበልም በሚሉ አካላት ምክንያት ውዝግቦች መፈጠራቸው፤
2. በቡድንም ሆነ በግል ተደራጅተው በቃለ ዐዋዲው መመሪያ መሠረት አንሠራም የሚሉ አስተሳሰቦች፣ ተቃውሞዎች፣ እንቅፋቶች መፈጠራቸው፤ በየደረጃው ለሚሰጠው ለቤተ ክርስቲያቱ ሕግና ደንብ ከለላ ማጣትና የቤተ ክርሰቲያኒቱ ሕግ ዕውቅና የሌለው መሆኑ በተለያዩ አህጉረ ስብከት በመልካም አስተዳደርን ፍትሕ ማጣት ምክንያት መሆን፤
3. በቃለ ዓዋዲው መመሪያ መሠረት በየአጥቢያው ራሱን ችሎ ሰበካ ጉባኤ እንዲቋቋም አስተዳደራዊ ውሳኔ ሲተላለፍ የግል ጥቅምን ታሳቢ በማድረግ፣ በየደብሩ ሰበካ ጉባኤ እንዳይቋቋም፣ እና ነባሩ እንዳይለወጥ ምእመናንን ተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በማድረግ ለቤተ ክርስቲያን አስተዳዳረዊ መዋቅር ተቀዋሚ ሁኖ መነሣት፤
4. የቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ ጥንካሬና ወጥ የሆነ ተጠያቂነት ያለው አስተዳደር መመሪያና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ወቅቱን ባገናዘበ መልኩ አለመውጣትና ሠራተኛውም በሥራ ድርሻው የሚጠየቅበትና የሚገመገምበት አለመሆን፤
5. የፋይናንስ ሥርዓት ወጥና ሰፊ በሆነ መንገድ ተዘጋጅቶ፣ የፍይንናስ አጠቃቀምና የድርሻ አከፋፈል መመሪያን በማጠቃለል በመመሪያ መልክ ተሰናድቶ ባለመገኝቱ ልዩ ልዩ ክፍተቶች መክፈቱ፤
6. ከሰባት ዓመት በፊት ተቋርጦ የነበረው ሥምሪት ቤተ ክርስቲያን በተልእኮዋ ላይ እንዳትወያይ አድርጓት የቆየ ቢሆንም እንደገና መጀመሩ እጅግ የሚያስደስት ቢሆንም በዘንድርው ዓመት የተካሄደው የሰበካ ጉባኤ ዓመታዊ ሥምሪት ቀጣይ መሆኑ እና አለመሆኑ አለመረጋገጡ፤
7. በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ባሉ የገጠር አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የዲያቆናት፣ የካህናትና የሰባክያነ ወንጌል እጥረት ከፍተኛ በመሆኑ ምእመናን መንፈሳዊ ፍላጎት በበቂ ሁኔታ ማሟላት አለመቻል ፣ ጉዳዩም ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው ምእመናን ፍልሰት ምክንያት መሆኑ፤
8. የተለያዩ ብሔር ብሔረሰበች ባሉበት፣ የኦርቶዶክስ ምእመናን ቁጥር አነስተኛ በሆነበት ሥፍራ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በአካበባው ቋንቋ መስጠት በተፈለገው መጠን አለመቻሉ፤ አሁንም ለበርካታ ምእመናን ወደ ሌላ እምነት ፍልሰት አሳሳቢና አፋጣኝ መልስ የሚጠይቅ መሆኑ፤
9. በየብሔር ብሔረሰቡ ተወላጆች ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ለማሰልጠን የተሸለ ሁኔታ አለመፈጥር ያሉትንም በየቦታው አዘዋውሮ ለማሰማራት የበጀትና የመሠረታዊ ፍላጎቶች ማሟያ አቅም አለመኖሩ፣ የሌሎች ቅደመ ዝግጅቶች አለመደረጋቸው ትኩረት እንዲሰጠው መጠየቁ፣
10. የልማት ሥራዎችን ያለ ዕቅድና በቂ ጥናት አለማከናወን ሊያደርስ የሚስችለው ጉዳት ሳይገመገምና ቅድመ ዝግጅት ሳይደረግ ማከናወኑ በሥራ ላይ የነበሩ ሰዎች ሕይወት ማለፍና መቁሰል መፈጠሩ ወደፊት ለሚደረጉ ሥራዎች ትምሀርት የሰጠ መሆኑ፤
11. በአንዳንድ ወረዳዎች በአማሌቃውያን አማካኝነት ሦስት አብያተ ክርስቲያናት ለማቃጠል ሙከራ መደረጉን
12. በርካታ ነባር የካህናት ማሰጠልኛዎች ትኩረት ተሰጥቶአቸው ቋሚ በጀት ተመድቦላቸው አገልግሎት ለመስጠት አለመቻላቸው፣ ወደ ከፍተኛ ደረጃ አለመሸጋገራቸው ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮቿን የአቅም ግንባታ ሥልጠና፣ ወቅታዊ ግንዛቤ መፍጠሪያ እና በልዩ ልዩ ቋንቋዎች የሚያስተምሩ ሰባክያነ ወንጌልን ለማፍራት አለመቻላቸው፤
13. በአህጉረ ስብከቶች ልዩ ጥረትና በግለሰቦች ድጋፍ የተቋቋሙና እተቋቋሙ ያሉ ማሰልጠኛ ተቋማት እና በዘመናዊ መንገድ እየተገነቡ ያሉ የአብነት ትምህርት ቤቶች ቤተ ክርስቲያቱ በባለቤትነት ተረካባ አሰስፈላጊው የበጀትና የአስተዳዳር አደራጃጀት ባለመከናወኑ አንዳንዶቹ ለችግርና ለጉዳት እተጋለጡ መሆናቸው፣
14. በልማት ሥራ ስም አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናነት ከሚያገኙት ገቢ በቃለ ዓዋዲው ድንጋጌ መሠረት የፐርሰንት ክፍያ ለመፈጸም ፈቃደኛ አለመሆን ይህንኑም ያስፈጽማሉ ብለው ያመኑባቸውን ኃላፊዎች ከሕዝብ ጋር በማጣልትና በማጋጨት የይነሱልን ጥያቄ በማስተባበር የግጭት መፍጠር ሥራ እየሠሩ መገኝት፣
15. አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ተጠናክረው በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች በጽንነፈኝነትና በአክራሪነት የተፈረጁ ግለሰቦች በተለይ የሰንበት ትምሀርት ቤተ ወጣቶችንና ታዳጊዎችን በጋብቻና በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች በማታለል ሃይማኖታቸውን እያስለወጧቸው ስለሚገኙ መፍትሔ ቢፈለግ
16. ርዳታ እንሰጣለን በሚል ስም አሳዳጊ የሌላቸውና በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ያሉ ሕፃናትን ነፃ የትምህርት ዕድል እንሰጣለን፣ በሚል ሰበብ ወደ ልዩ ልዩ እምነትቶች በማስገባትና በአርዮሳዊ ትምህርት በማነፅ ቤተ ክርስቲያንን ተረካቢ የማሳጣት ሥራ እየተሠራ ስለሆነ መፍትሔ ቢፈለግ፣
17. በሀገረ ስብከት ደረጃ በሚሾሙ አካላት የአመራር ብቃት ማነስና በችግር አፈተት ላይ ችሎታና ብቃት አለመኖር አማካኝነት በሀገረ ስብከት በሚገኙ ሠራተኞች መካከል በሚፈጠረው አለመግባባትና ጎራ ለይቶ በመናቆር እና አሉባልታ በመንዛት በሚጠፋው የሥራ ጊዜ ከአጥቢያ ጀምሮ አስከ ሀገረ ሰብከት ደረስ ሊሞሉ የሚገባቸው የገንዘብና የሰው ኃይል ቅጾች በተገቢው ጊዜ ሞልቶ ለማቅረብ ችግር ያጋጠመ መሆኑ፤
18. በመልካም አስተዳደር እጦት ደረጃቸውን ጠብቀውም ሆነ ሳይጠብቁ በመጡ አቤቱታዎች በዋናው መሥሪያ ቤት ከታዩ በኋላ በክፍሉ ሊቀጳጳስ ሰብሳቢነት ታይቶ መፍትሔ ይሰጥ ተብሎ ሲላክ ባለጉዳዩን መልሶ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መላክ አናስተናግድህም ብሎ መላክ (የመመሪያወችና የውሳኔዎች አለመከበር)
19. በዝምድና በቤተሰብነትና በቀረቤታ ስም ወይም ምክንያት የብፁዓን አበው ሊቃነ ጰጳሳት የስም ቲትር ለሕገ ወጥ አገልግሎት ያለአግባብ ውሎ መገኘትና አስተዳደራዊ መናጋትን ማስከተሉ፣
20. ሕገ ወጥ ሰባክንና አጥማቂዎች ነን የሚሉ ግለሰበች ከሀገር አቀፍነት ወደ አለም አቀፍነት አልፈው ተርፈው ፅላት አስቆፍረን አውጥተናል እያሉ ምእመናንን የሚያወናብዱ፣ የየአህጉረ ሰብከቶችን የአመራርና የልማት ሥራ የሚያደናቅፉ የሐሰት ወሬዎችንና ጽሑፎችን የሚያዘጋጁ ለዋናው መሥሪያ ቤትም አቤቱት የሚያቀርቡ አደራጅተው በመላክ ሁከት የሚፈጥሩ፣ ያልተሠራ ተሠራ ብለው የሚያስነግሩ መኖራቸው፣ በቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ተልእኮ ዕንቅፋትና መፍጠራቸው፤
21. የካህናትና የሊቃውንት መፍለቂያ፣ የበርካታ ቅርሶች ማኅደር፣ በሆኑት የሀገራችን ክፍሎች ሳይቀር፣ ከዐሥራ ሁለት አብያተ ክርስቲያናት በላይ በአገልጋይ ካህናት እጥረት ሙሉ በሙሉ የተዘጉ መሆናቸው፣ ዐሥራ አምስት አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ አንድ ካህን ብቻ ያላቸው መሆኑ፣ የቅርስ ጥበቃና፣ የምእመናን አገልግሎት መታጎሉ አሳሳቢነት፣
22. በሰበካ ጉባእ አባላት ምርጫ ወቅት የአጥቢያ አባላት ያልሆኑ ሰዋችንና በምርጫ የራሳቸውን ፍላጎት ለሟሟላት የሚጥሩ ግለሰቦችና ቡድኖች እየተፈጠሩ መምጣት
23. በተፈጠረው የአየር ለውጥ ምክንያት በወቅቱ በተፈጠረው ድርቅ ምክንያት በድርቁ በተጎዱ አህጉረ ስብከት፣ የሚገኙት አድባራት፣ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት ምእመናን መገኘታቸው
24. በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ ገዳማትና አድባራት ያለው ሠራተኛ ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ለማስተናገድ አለመቻሉ
25. ከመላው ሀገሪቱ ፈልሰው በሚመጡ አገልጋየች አማካኝነት በሀገረ ስብከቱ የሥራ ፈላጊ ቁጥር ከአቅም በላይ መሆኑ
26. በልዩ አለመግባባቶች አማካኝነት በርካታ የአድባራትና ገዳማት ሠራተኞች መታገድ
27. የዐሥራት ገቢ አለመሰብሰብና አሁንም ገቢው በሙዳይ ምጽዋት የተመሠረት መሆኑ
28. መዋቅርንና ቃለ ዓዋዲውን ያልጠበቁ አደረጃጀቶች እየተበራከቱ መምጣት እና ለዚህም በቂ ቁጥጥር አለመኖሩ
29. የተለያዩ ፍልጎቶች ያሏው ኃይሎች ቤተ ክርስቲያንን የመታገያ መድረክ በማድረግ የሚፈጥሩት ችግር ለቤተ ክርስቲያንን ሰላምና መረጋጋት ጠንቅ መሆንና በመዋቅራችን ውስጥ ያለውን የሰው ኃይል ችግር ዙሪያ በበቂ ሁኔታ ግንዛቤ አለመኖር

ለ. በውጭ ሀገራት ካሉ አህጉረ ሰብከት የተጠቀሱ ችግሮች

1. በልዩ ልዩ ምክንያት በሰርግም በልደት ወደ ውጭ ከሔዱ በኋላ ከቤተ ክርስቲያን ለአገልግሎት ተልከን ነው በማለት እፈጠሩ ያለው ችግር
2. የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋማዊ አደረጃጀት ለፖለቲካ፣ ለንግድ፣ ለግልና ለቡድን ጥቅም ለማዋል የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች መበራከታቸው፣
3. ግብረ ሰዶም
4. ከመንበረ ፓትርያርክ ጋር የሚኖሩ ግንኙነቶች ፈጣንና ቀልጣፋ አለመሆን እንዲሁም በመንበረ ፓትርያርክ የውጭ ግንኑነት መምሪያ አለመጠናከር
5. በውጭ ሀገር ለሚኖሩ የውጭ ሀገር ተወላጅ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ምእመናን ትኩረት ማጣት እና አቅም ማነስ
6. በእንግሊዝ ሀገር እንደ ለንደን ደብረ ጽዮን ባሉ ቦታዎች ጽንፈኛ ቡድኖች ከሠላሳ ዓመት በላይ የቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረት የነበረውን ሕንፃ ይገባናል በማለት የቤተ ክርስቲያን በር በፖሊስ በር እስከማሰብር የደረሱበት ሂደት መፈጠሩ
7. ቤተ ክርስቲያን የማታውቃቸው አገልጋዮች በውጭ ሀገር የትምሀርት ተቋማትና የወንጌል መድረኮችን በቤተ ክርስቲያን ስም እያስፋፉ መገኘታቸው

7.2. አበረታች ዘገባዎች

ሀ. በሀገር ውስጥ ባሉ አህጉረ ስብከት

1. ምንም እንኳ የምእመናን ወደ ልዩ ልዩ እምነቶ መፍለስ ከፍተኛ ቢሆንም በአንዳንድ አህጉረ ስብከት የሚታዩ የተጠናከሩ የስብከተ ወንጌል አገልግሎቶች ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አማናዊ ትምህርተ ሃይማኖት መምጣታቸው፣
2. በአንዳድን አህጉረ ስብከት የታዩ የአዳዲስ ሕንፃዎች ጽ/ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የገቢ ማስገኛ ህንፃዎች ግንባታና የነባር ታሪካውያን ሕንፃች እድሳት መኖራቸው፣
3. ከፍተኛ ገንዘብ ወጭ ተደርጎባቸው የተሠሩ የአዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት ግንባታ መከናወንና በበጀት ዓመቱ ተጠናቀው መመረቃቸው እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች ለሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የመሰብሰቢያ አዳራሾች ተገንብተው መመረቃቻ፣
4. ለመልክም አስተዳደር፣ ስለ ጤና፣ ስለ አካባቢ ጥበቃ፣ ስለ አክራሪነት እና ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች የካህናት ሥልጠና መኖሩ፣
5. ለሰንበት ትህርት ቤት ወጣቶች ልዩ ልዩ ሥልጠናዎች መሰጣቸውና፣ እንደ አሰፈላጊነቱም ትምህርት አበ ነፍስ በመስጠት ለወጣቶች አበ ነፍስ መመደባቸው፣
6. በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ያዘጋጀው የማስተማሪያ መጽሐፍ እና የመዝሙረ ማኅሌት ማውጫ በወጥነት መዘጋጀቱና ተግባራዊ መሆኑ፤
7. አንዳንድ አህጉረ ስብከት ነባርና በቅርስነት ለተመዘገቡ ቦታዎች ምትክ አዲስ ቦታ በመሰጠቱ የሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና ለመሥራት ቦታ መረከብ
8. ከማዕከል የሚዘጋጁ የቅዱሳት መጻሕፍት፣ ጋዜጦች መጽሔቶች፣ ልዩ ልዩ ሰነዶችና ቅጾች በአግባቡና ማእከላዊነቱን በጠበቀ መንገድ መሰራጨታቸው
9. ለተቸገሩ አብያተ ክርስቲያንተ የተመደበው እርዳታ ለታለመለት ዓላማና ግብ መዋሉ ለወደፊቱም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ዕቅድ መኖሩ፣
10. በራስ አገዝ ልማት ለቤተ ክርሰቲያን ዘላቂ የሆኑ ጥቅምና ሀብት የሚስገኙ ሕንፃዎች (የብፁዓን አባቶች መልካም ሐዋርያዊነትና የሥራ ተነሳሽነት መዘክርም ስለሆኑ) በየሀገረ ስብከቱ እየተሠሩ (በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዐምደ ብርሃን በምእመናን ሕሊና ዘለዓለም ዝክር ናቸውና)፣ መሆናቸው
11. ለአብነት መምህራን ትምህርት ቤቶችን ለማስፋፋትና ለማጠናከር ሲባል ወርሐዊ አበልና ድጎማ መሰጠቱና ለደቀ መዛሙርቱም አቅም የፈቀደውን ድጋፍ መደረጉ
12. በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ሕይወታቸው ላለፉና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ቁስለኞች ቤተ ክርስቲያን አቅሟ የፈቀደውን ድጋፍ ማድረጓል
13. በሊቢያ በርሐ ስለክርስትና ሃይማኖታቸው ሰማዕትነትን የተቀበሉ ወጣቶች ቤተ ሰቦች ድጎማ መደረጉና በቅዱስ ሲኖዶስ በታዘዘው መሠረት ጸሎቱ መድረሱ
14. ስለ መልካም አስተዳደር ሥልጠና መሰጠቱ ከቤተ ክርስቲያንተልእኮና አገልጋዮችን ከመሰብሰብ አንፃር ከጠቅላይ ቤተ ክህነት በተለኩ ልዑካን መሰጠቱን፣ ስለሆነም በአንዳንድ አህጉረ ስብከት በበጀት ዓመቱ በመልካም አስተዳደር እጦት የተነሣ የተፈጠረ የአፈጻጻም ችግር አለመኖሩ
15. የገንዘብ ብክነትን ለመቆጣጠር፣ በሙዳየ ምጽዋት ቆጠራ፣ በሥዕለት አቀባበል፣ ላይ የሚገኘውን የቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረት የባንክ ባለሙያዎች ጭምር በመታገዝ ገንዘብ በቀጥታ ወደ ባንክ ገቢ የሚደረግበት አሠራር በአንዳንድ አህጉረ ስብከት መጀመሩ
16. አንዳንድ አህጉረ ስብከት በሰለጠኑ የሒሳብ ባለሙያዎች በመታገዝ የሂሳብ አያያዝ አሠራራቸውን ከነጠላ ሂሳብ አያያዝ ወደ ሁለትዮሽ የሂሳብ አያያዝ ለማሸሸጋገር ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ፈቃድ አግኝተው ሰነዶችን በማዘጋጀት ላይ መሆናቸው

ለ. በውጭ ሀገር ባሉ አህጉረ ስብከት

1. የቅዱስነታቸው የውጭ ሀገር ሐዋርያዊ ጉዞ መሠረት ከልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከሩ፣.
2. ብፁዓን አባቶች ሰፊ የሆኑ አህጉረ ስብከቶች በሐዋርያዊ ጉዞ እየተዘዋወሩ ማስተማር፣ መቀደስና ማጽናናት፣ ሥልጣነ ክህነትንም መሥጠት ደረጃ ላይ መድረስ
3. ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ቀኖናዊ ሥርዓት በመጣስ እንደ ተሐድሶ አደረጃጀቶች ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን መዋቅራዊና ሲኖዶሳዊ አደረጃጀትና የምሥጢራት አፈጻጸም ባለመከጸል ገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት በማቋቋም በይፋ ተሐድሶን የሚያስፋፉ አገልጋዮችን በመምከር ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት እንዲገቡ ማድረግ
4. አብዛኛዎቹ በውጭ የሚኖሩ ወጣቶችን በማሰባሰብ የሰንበት ትምሀርት ቤቶችን ማጠናከር
5. ቤተ ክርስቲያን በውጭ ሀገራት ባለችበት ቦታ ሁሉ ለስደተኞች ድጋፍ ማድረጓ
6. በውጭ ሀገራት የሚኖሩ የኢትዮጵያ ቆንሲላዎች ጋር በመሆን በየሀሮቹ ያሉ የኢትዮጰያውንን ችግሮች ለመፍታት መቻላቸው
7. ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር በተለይም ከኦሬንታል አብያተ ክርስቲያናት ጋር በትብብር የመሥራት ተግባር መኖሩ


የጉባኤው የጋራ መግለጫ

እኛ ከጥቅምት ፰- ፲፩ ቀን ፳፻ወ፰ ዓ/ም ድረስ የተካሔደው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርሰቲያን መንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የ፴፬ኛው መደበኛ ስብሰባ የጉባኤ አባላትና ተሳታፊዎች በጉባኤው ከተሰሙት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት አባታዊ የሥራ መመሪያና ቃለ ቡራኬ፣ የብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅና በሀገር ውስጥና በውጭ ካሉ አህጉረ ስብከት ዓመታዊ የሥራ ዘገባ በመነሣት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ሲኖዶስ እንዲመክሩባቸውና በየአህጉረ ስብከቱ ተግባራዊ እንዲሆኑ ከዚህ ቀጥሎ ያለውን የጋራ መግለጫ አውጥተናል፡፡

 

1. ቅዱስ ፓትርያርኩ ለሠላሳ ዐራተኛው አጠቃላይ ሰበካ ጉበኤ ያስተላለፉትን ቃለ ቡራኬና አባታዊ የሥራ መመሪያ ሙሉ በሙሉ ተቀብለን ተግባራዊ ለማድረግና የሚጠበቅብንን ለመወጣት ዝግጁ መሆናችንን ቃል እንገባለን፤
2. በቅዱስነታቸው ቃለ ቡራኬ ከተላለፉት መሠረታዊ መልእቶች ውስጥ ቅዱሰነታቸው ዓቢይ ጉባኤው ትኩረት ሰጥቶ እንዲወያይባቸው ያሳሰቧቸወን፡- አንደኛ፤ ምእመናንን የመጠበቅ ተልእኮ በሚገባ እየተወጣን አይደለምና ባዶአችንን ከመቅረታችን በፊት ለተደራጀና ለድንበር የለሽ ትምህርተ ወንጌል ብንነሣ፤ ሁለተኛ፤ የአስተዳደር ሥራችን ለምእመናን ኅሊና እንቅፋት እየሆነ ነውና የሃይማኖቱን መርሕ ጠብቀን አስተዳደራችን የሕግ የበላይነትን ያረጋገጠ፣ ግልጽ፣ ተአማኒና ተጠያቂነትን ያሰፈነ የምእመናንን ልብ የሚያረካ፣ ምእመናን በቤተ ክርስቲያናቸው ኵራት እንዲሰማቸው የሚያስችል አሠራር ብናረጋግጥ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ እንችላለን፤ በማለት የሰጡትን መመሪያ በተግባር ለመለወጥ ቃል እንገባለን፤
3. የቅዱስ ሲኖዶስን ሉዓላዊነት የሚጋፉ ለቤተ ክርስቲያን ማእከላዊ አመራር አንታዘዝም የሚሉ፤ ቤተ ክህነት ምን አገባው? ሀገረ ስብከት ምን አገባው? ቅዱስ ሲኖዶስ ምን አገባው? በጠቅላላው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ምን አድርጎልናል? በሚል የማደናገሪያ ስልት መዋቅርን የሚንዱ ችግሮች በከፍተኛ ፍጥነትና ብዛት በተደራጀና በተጠና ስልት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር እያደጉ ስለሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እንዲወያይበትና መፍትሔ እንዲሰጠው ለዘመናት ፀንቶ የቆየውን የቤተ ክርስቲያንን መዋቅር እንዲያስጠብቁ በከፍተኛ ስሜት እንጠይቃለን፣
4. በሁሉም አህጉረ ሰብከት የታየው የብፁዓን አባቶች ሐዋርያዊ ጉዞ እጅግ ውጤታማና ለምእመናን ጥንካሬ፣ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው ስለሆነ ተጠናክሮ እንደቀጥል እንጠይቃለን፤ በእኛም በኩል የሚገባንን ለማድረግ ቃል እንገባለን፣
5. በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁና በማደራጃ መመሪያ የተገለጹት የሁለትዮሽ የሒሳብ አያያዝ (ደብል ኢንትሪ)፣ ሥርዓት የፈይናንስ ማእከላዊነት በማረጋገጥ፣ የአገልጋዮችን የሥራ አቅም ብልጽግና በማሳደግ፣ ብክነትን በማስወገድ፣ ከፍተኛ አስተዋጽ ያለው ስለሆነ፣ ከብዙ ጊዜ ማሳሰቢያ በኋላ ተግባራዊ መሆኑ ጉባኤውን አስደስቷል፤ ይኽ አሠራር በቀጣይነት በየደረጃው እስከ ታችኛው የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ድረስ ተግባራዊ እንዲሆን፣ ይልቁንም አሠራሩ ዘመኑ አሁን የደረሰበትን የሥልጣኔ ደረጃ መሠረት በማድረግ፣ በኔት ወርክ ተሣሥሮ፣ በሥልጠና ተደግፎ ግልጽና ተጠያቂ በሆነ መንገድ ተግባራዊ እንዲደረግ ወጥና ቀጥ ያለ አመራር እንዲሰጥ እየጠየቅን እኛም ለተግባራዊነቱ የድራሻችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን፤
6. ተቋርጦ የነበረው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ሥምሪት መጀመሩ ጉባኤውን እጅግ ያስደሰተ ሲሆን ሥምሪቱ እጅግ በተጠናከረ መንገድ፣ አስተማማኝ የሆነ የራሱ በጀት ተመድቦለት፣ በሥልጠና እና በተደረጃ ውጤት ተኮር በሆነ መንገድ እንዲቀጥል የበኩላችን ለማድረግ ቃል እንገባለን፤
7. የታየው የገቢ እድገት ጉባኤውን እጅግ ያስደሰተ ሲሆን ከበጀት እድገቱ ጎን ለጎን በልማት ሥራዎች ለቤተ ክርስቲያን ቋሚ ንብረት ለማፍራት የቀደሙት አባቶች ሠርተው እንደወረሱን ሁሉ ቋሚና ዘላቂ ንብረት ለቤተ ክርስቲያን ለማትረፍ በልማት ለመትጋት ቃል እንገባለን፤
8. በብፁዓን አባቶች ባደረጉት ጥረት፣ ምእመናንና ካህናትን በማስተባበር የሚያካሂዷው የልማትና ለቤት ክርስቲያን ንብረት የማፍራት፣ ዘላቂ ገቢ የማስገኝት ሥራ ለሚመሯው አህጉረ ስብከቶችም ሆነ ተቋማት ሕልውና ዋስትና፣ ለብፁዓን አባቶችና አብረዋቸው ለደከሙ የሥራ ኃላፊዎች የድካማቸው መዘክር ስለሆኑ ንብረቶቹ በየአህጉረ ስብከቱና በዋናው መሥሪያ ቤት ባህር መዝገብ በአግባቡ ተቆጥረውና ተመዝግበው እንዲያዙ እንጠይቃለን፣ ለአፈጻጸሙም የበኩላችን ለማድረግ ቃል እንገባለን፤
9. ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋትና የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ በተፈለገው መጠን ለማዳረስ ብቃትና ታዛዥነት ያላቸው አገልጋዮች እጥረት ትልቅ እንቅፋት ስለሆነ የአገልጋዮችን እጥረትና በተለይም በልዩ ልዩ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ቋንቋዎች የሚስተምሩ መምህራነ ወንጌል በጥራትና በቁጥር ለማሳደግ የበኩላችን ለማድረግ ቃል እንገባለን፤
10. የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን ከዐውደ ምኅረት ባሻገር በማረሚያ ቤቶች፣ በጤና ማእከላት በመሳሰሉት ለማደረስ በተለይም ዘመኑ በሚፈቅደው በብዙኅን መገናኛ (በሚዲያ) በመታገዘ በመላው የቤተ ክርስቲያንን ድምጽ በራሷ በኩል ማእከላዊነቷን ጠብቆ ለማሰማት የሚደረገውን ጥረት ከልብ በመደገፍ ለተግባራዊነቱ የበኩላችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን፤
11. ለስብከተ ወንጌል እንቅፋት የሆኑ የሕገ ወጥ ሰባክያንን፣ ሕገ ወጥ አጥማቂ ነን ባዮችን እና መዋቅር ያልጠበቁ፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ክብር የሚያስነቅፉ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት እስከ አሁን ከተሠራ በይበልጥ ለመሥራት ቃል እንገባለን፤
12. በየጊዜውና በየዘመኑ ወቅቱ እንደሚፈቅደው መጠን መሠረቱን ሳይለቅ ሲሻሻልና ሲዳብር የኖረው ቃለ ዐዋዲው አሁንም በይበልጥና በጥራት የሕግ ጸባይ በመያዝ፣ ለሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር መንግሥታት ተቀባይነት በሚያገኝ መልኩ፣ መሻሻሉን ሁሉም የሚጠብቀው ስለሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት በተለይ እስከ አሁን ያልተደረገው የውጭ አህጉረ ስብከት ያሉ አብያተ ክርስቲያናትን ማዕከል ባደረገ መልኩ ጊዜ ሳይሰጠው ተዘጋጅቶ እንዲሻሻል በአጽንዖት እየጠየቅን ለሚደረገው ሁሉ የበኩላችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን፤
13. ለማሰልጠኛዎችና ለአብነት ትምህርት ቤቶች እየተሰጠ ያለው ትኩረት ከምን ጊዜው በላይ የተሻሻለ ቢሆንም በተቀናጀና ማእከላዊነቱን በጠበቀ መልኩ እንዲደራጅ፣ በጀት ያልተመደበላቸው በጀት እንዲያገኙ፣ በበጎ አድረጊ ምእመናን የተሠሩት ሁሉ በማእከል እውቅና እየተሰጣቸው የቤተ ክርስቲያን ባለቤትነት እንዲያገኙ እየጠየቅን ቅዱስ ሲኖዶስ በተለይ ለአብነት መምህራንና ለደቀ መዛሙርቶቻቸው ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ በታላቅ አክብሮት እንጠይቃልን፤
14. ለሰንበት ትምህርት ቤቶች አደረጃጀት የተሰጠው ትኩረት፣ ልዩ ልዩ ሥልጠና እና የሥርዓተ ትምህርት ከመዝሙር መጽሐፍ ጋር ተዘጋጅቶ መሠራጨቱ ወጣቶችን በወጥነት ለማስተማርና በሃይማኖትና በምግባር ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ጉባኤ ያመነበት ሲሆን ሂደቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ በመምያሪው በኩል የቀረቡት ችግሮች በተለይም ከልዩ ልዩ የወጣትና የጎልማሶች ማኅበራት ያለው ተጽዕኖ አንዲቆም፣ የወጣቶች የሰንበት ትምህርት ቤት ቆይታ የዕድሜ ገደብ እንዲከበር በቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ እንዲሰጥ እንጠይቃለን፤
15. በቅርስ ጥበቃና ምዝገባ በተመለከተ በአንዳንድ አህጉረ ስብከት የታየው ከመንግሥት ጋር የተቀናጀ የቅርሶች ምዝገባ፣ የቅርሶች ማስመለስ፣ የሙዚየሞች ማደራጀት ለቅርሶች ዋስትና ቢሆንም ሁሉም ጥረቶች የቤተ ክርስቲያኒቱን የቅርስና የታሪክ ባለቤትነት በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይና ወቅታዊ መመሪያ እንዲሰጥ በታላቅ አጽንዖት እንጠይቃልን፣
16. ወደ መናፍቃንና ወደ ኢ-አማንያን ለሚፈልሰው የምእመናን ቁጥር አስተዋጽኦ የሚያደርገው፣ ለአገልጋዮች ዋስትናና ከለላ ማጣት ለቤተ ክርስቲያን የወደፊት ሕልውና ከፍተኛ ስጋት የሆነው የመልካም አስተዳደር እጦትንና ሙስንና ለመቅረፍ በሥልጠና የታገዘ ሥራና ሠራተኛን በማገናኝት ላይ ያተኮረ፣ ትግሮችን በመፍታት ብቁ አገልጋዮችን ለማፍራት ያለመ የመልካም አስተዳደርን ለማስፈን ቅዱስ ሲኖዶስ ልዩ ትኩረት እንደሰጠው እጠየቅን፣ ለተግባራዊነቱ የበኩላችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን፣
17. በተፈጠረው የአየር ለውጥ ምክንያት በወቅቱ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት በተጎዱ አህጉረ ስብከት፣ የሚገኙት አድባራት፣ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት ምእመናን በርካታ በመሆናቸው ቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ መፍትሔ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር እንዲሰጠው እንጠይቃለን፡፡
18. በልማት፣ በአረጋውያን እንክብካቤ፣ ወላጆቻውን ያጡ ሕፃናትን በማሳደግ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በማኅራዊ አገልግሎትና ለወገን ደረሽነት፣ አብያተ ክርስቲያናትን በማሳነጽ፣ ቋሚና ዘላቂ ንብረትን በማስፋፋት የሚደረጉ ጥረተችን ሁሉ ለመደገፍ ቃል እንገባልን፣
19. የቤተ ክርስቲያናችን አስተደደር ሲኖዶሳዊ መሆኑ ይታወቃል፣ ይሁን እንጅ በአንዳንድ አካባቢዎች እንደ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አብያተ ክርስቲያናት ከሲኖዶሳዊ መዋቅር የወጣ፣ ቀኖናዊና ትውፊታዊ ያልሆነ ኢ-ኦርቶዶክሳዊ ገለልተኛ አደረጃጀት በመፍጠር ምእመናን የሚያደናግሩ አካላት ዙሪያ ቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲያበጅለት እየጠየቅን ለተግባራዊነቱ በኩላችንን ሁሉ ለማድረግ ቃል እንገባልን፤
20. በውጭ ሀገር የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉዞ የቤተ ክርስቲያንን ዓለም አቀፋዊነት የሚያረጋግጥ በመሆኑና በውጭ ያሉትን አህጉረ ስብከት የሚያጠናክ በመሆኑ ቀጣይነት እንዲኖረው እጠየቅን፣ በዚሁ ረገድ ከኦሬንታል አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያለው ግንኑነት እንዲጠናከርና በተለይም ከግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር ያለው ግንኙነት በሚገባ እንዲተኮርበት በታላቅ አጽንዖት አንጠይቃለን፤
21. በአሁኑ ጊዜ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመላው ዓለም የሰፋችና እና ከራስዋ ምእመናን አልፎ የውጭ ሀገር ተወላጅ ካህናትና ምእመናን ያፈራች በመሆኑ የውጭ ግንኙነት ሥራዋ ዓለም አቀፋዊ ይዘቷን እንደጠበቀ እንዲጠነክርና እንዲስፋፋ ቅዱስ ሲኖዶስ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው በታላቅ አጽንዖት አንጠይቃለን፤
22. በሊቢያ በርሐ ስለክርስትና ሃይማኖታቸው ሰማዕትነትን የተቀበሉ ወጣቶች አስመልክቶ የተደረገው ሲኖዶሳዊና ቀኖናዊ ውሳኔ የተቀበልን ሲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ ሰማዕታትን የሚስቡ ከሰማዕታት ዋና ያገኛሉ የተባለውን በመከተል የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ ቃል እንገባለን፤
23. የእግዚአብሔርን ሕግና ትእዛዝ የተፈጥሮን ወሰን በማለፍ በታላላቅ ሀገሮች ድጋፍና ተጽእኖ እየተስፋፋ ያለውን የግብረ ሰዶምን በደል በመቃወም ቤተ ክርስቲያን ድምጽዋን ለዓለም ማሰማት እንዳለባት እየጠየቅን ጥያቄውን ከአሁን በፊት ያስተጋቡ ብፁዓን አባቶች ላደረጉት ጥረት ልባዊ ድጋፋችንንና አጋርነታችን ለመስጠት ሃይማኖታዊ ቀኖናዊ ግዴታችን ስለሆነ ምእመናን በትምሀርተ ወንጌል በማነጽ ዜጎቻችንን ለመጠበቅ ቃል እንገባለን፤

የፎንት ልክ መቀየሪያ