Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

እስክንድር ገ/ክርስቶስ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የምሥራቅ ትግራይ ጉብኝታቸውን በይፋ ለማከናወን ጥቅምት 25 ቀን 2008 ዓ/ም ውቅሮ ከተማ ሲደርሱ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ የውቅሮ ከተማ ነዋሪዎች፣ ካህናት ፣ ወጣት የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎችና የከተማዋ ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

በውቅሮ ከተማ ደብረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን አቀባበል ለማድረግ ለተሰበሰቡ ምዕመናን ቅዱስ ፓትርያርኩ ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት በውቅሮ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ በተገኙበት በአሁኑ ጊዜ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ላደረገላቸው ደማቅ አቀባበል አመስግነው ይህንን እንግዳ ተቀባይነታቸውንና ለሃይማኖታቸው ያላቸውን ቀናኢነት አጠናከረው እንዲቀጥሉበት መክረዋል፡፡

አምላኩ እግዚብሔር የሆነ ሕዝብ ንዑድ ክቡር ነው፣ በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የሚያምን ሕዝብ ንዑድ ክቡርነው ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩ የውቅሮ ከተማ ሕዝብ በእምነቱ በመጽናት የእግዚአብሔርን ረድኤትና በረከት በማግኘቱ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል፡፡

Picture 003 Picture 013 Picture 015 Picture 018 Picture 021 Picture 027 Picture 031 Picture 037 Picture 040 Picture 045 Picture 083 Picture 118 Picture 139 Picture 144 Picture 175 Picture 193 Picture 196 Picture 204 Picture 211 Picture 238 Picture 239 Picture 257 Picture 266 Picture 268 Picture 273 Picture 275 Picture 276 Picture 291 Picture 294 Picture 307 Picture 310 Picture 312 Picture 317 Picture 334 Picture 344 Picture 384 Picture 390 Picture 399 Picture 467 Picture 488 Picture 491 Picture 493 Picture 605 Picture 610 Picture 662 Picture 683 Picture 685 Picture 691

ዛሬ በዚህ ከተማ የተመለከትነው የሃይማኖት ጽናትና የአባቶች አክብሮት እናንተ ከአባቶችሁ የወረሳችሁት በመሆኑ ልጆቻችሁም ይህንኑ የእናንተን ጽናት በመውረስ ሃይማኖታቸውን ጠባቂ እና አክባሪ እና ባህሉን ጠባቂ በመሆን መጪው ትውልድ ሃይማኖቱን አክባሪ እና ባህሉን ጠባቂ በመሆን ይታነጽ ዘንድ ለልጆቻችሁ ስለ ሃይማኖታችሁ ምንነትና ጽናት በርትታችሁ ማስተማር ይገባቸኋል ካሉበኋላ ካህናትም ወጣቱ ትውልድ በሕገ እግዚብሔር በፍቅርና በአንድነት መኖር ይችል ዘንድ ዘወትር ማስተማር ይጠበቅባችኋል ብለዋል፡፡

በዚሁ እለት በአጽቢ ወንበርታ ወረዳ ክልሻ እምኒ በተግለ የገጠር ቀበሌ በመላው ዐለም በኤልኒኖ ተጽዕኖ ከተከሰተው የአየር መዛባት ጋር ተያይዞ የምግብ እጥረት የገጠማቸውን አካባቢዎች ተዛውረው የተመለከቱት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ሕዝቡ አካባቢውን ሳይለቅ ከመንግሥት አካላት ጋር በመነጋገር በጊዜያዊነት የገጠመውን ችግር መቋቋምና በትዕግስት ማለፍ እንደሚገባው ጠቁመው ቤተክርስቲያንም ይህ ወቅታዊ ችግር ይፈታ ዘንድ በጸሎተ ምሕላ ልዑል እግዚብሔርን ከመለመን በተጨማሪ ቅዱስ ሲኖዶስ በወሰነው መሠረት አስፈላጊውን ሁሉ ለመፈጸም መዘጋጀቷን ገልጸዋል፡፡

የቅዱስ ፓትርያርኩን ወደ አካባቢው መምጣት የተመለከቱ የአጽቢ ወንበርታ ከተማ በርካታ ነዋሪዎችም ለቅዱስ ፓትርያርኩ ደማቅ አቀባበል ያደረጉ ሲሆን ቅዱስነታቸውም በአጽቢ ወንበርታ ደብረ ገነት ቅድስት ሥላሴ ገዳም ለተሰበሰቡ ምዕመናን ትምህርትና ቡራኬ ሰጥተዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ በትምህርታቸውም በገዳሙ የሚገኙ ጥንታዊያን ቅርሶች ለመጠበቅና ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ እንዲሁም ጥንታዊውን ቤተክርስቲያን በዘመናዊ የሕንጻ ጥበብ ለመተካት የአጽቢ ወንበርታ ሕዝብ የሚያደርገውን ጥረት አድንቀው የጀመራችሁትን ሕንጻ ቤተክርስቲያን በማጠናቀቅ ቅርሶቻችሁን በአግባቡና በተገቢው መንገድ በመጠበቅ አደራችሁን በብቃት መወጣት ይጠበቅባችኋል ብለዋል፡፡በገዳሙ ለሚሠራው አዲስ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ግንባታም የአንድ መቶ ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል፡፡

በአጽቢ ወንበርታ ወረዳ ውስጥ የሚገኘውን የደበረ ዓላማ አሲራ መቲራ ቅድስት ማርያም ገዳምን የጐበኙት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በገዳሙ አበምኔት በአባ ገ/መድህን ገ/ጊዮርጊስ የቀረበውንና የገዳሙን አመሠራረትና ታሪክ የሚገልጽ ሪፓርት አዳምጠዋል፡፡

የገዳሙ አበምኔት አባ ገ/መድህን ገ/ጊዮርጊስስም በሪፓርታቸው የገዳሙን ጥንታዊነት፣ ታሪካዊነት፣ እንዲሁም በልማት ራሱን ለመቻል ያደረገውን ጥረትና ያሳካቸውን ለኬቶች በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን በገዳሙ በቀጥታ የሚረዱ ከ8000 በላይ ወላጅ አልባ ሕፃናትም እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡ ገዳሙ ለሚያደርገው ጠንካራ የልማት እንቅስቃሴም ከወረዳ እስከ ፊዴራል መሥሪያ ቤቶች ተገቢው እውቅናና ሽልማት የተሰጠው መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የገዳሙ የራስ አገዝ ልማት ያመጣው ውጤት ያላስደስታቸው አንዳንድ ማኀበራት ነን ባዮች የገዳሙን መልካም ሥራ ለማጠልሸት ሌት ተቀን ሲደክሙ ይውላሉ ያሉት አበ ምኔቱ እኛ ግን ገዳማዊ ሥራችንን በመከናወን ለውጤት መብቃት መቻላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

ቅዱስነታቸውም ሪፓርቱን ካደመጡ በኋላ ባሰሙት አባታዊ ንግግር ይህንን ታላቅ ገዳም ከአባቶቻችሁ ተረክባችሁና ጠብቃችሁ ለትውልድ ለማስተላለፍና ቅድመ ታሪኩ ተጠብቆ እንዲቆይ እንዲሁም በልማት ሥራው የተዋጣለት እንዲሆን ለማድረግ ያደረጋችሁት ጥረት የሚደነቅና የሚመሰገን ነው ብለዋል፡፡

ይህ ገዳም ችግረኛ ሕጻናትን ለማሳደግና ለመርዳት ያደረገው ጥረትና እያደረገ ያለው ሥራ የሚመሰገንና ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ነው ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩ ይህን አይነት የተቀደሰ ተግባር ማከናወን ደግሞ ከገዳማዊያን መነኰሳትና መነኰሳይያት የሚጠበቅ ነው በዚህ ልትቀጥሉበት ይገባል ብለዋል፡፡

የዚህ ታላቅ ገዳም አበምኔት አባ ገ/መድህንም ይህን ገዳም በማስፋፋት፣ በማጠናከርና የውጤታማ የልማት ሥራዎች ባለቤት እንዲሆን በማስቻል ረገድ ያከናወኗቸው ሥራዎች ሁሉ የሚመሰገኑና ተገቢው እውቅና ሊሰጣቸው የሚገባ ነው ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ሥራ የሚሰራ ሰው መፈተኑ ስለማይቀር በሥራዎቻችሁ መካከል የሚገጥሟችሁን አሉባልታዎች በመናቅ እና ለአሉባልተኞች በመተው ጠንክራችሁ መሥራትና አሉባልታ ከሥራ እንደማይበልጥ በተግባር ማሳያነት ይጠበቅባችኋል ሲሉ መክረዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ጥቅምት 26 ቀን 2008 ዓ/ም በውቅሮ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘውን የደብረ ነገስት አብርሃ ወአጽስሐ ገዳምን ጐብኝተዋል፡፡
ገዳሙን ለመጐብኘት ከብፁዓን

አበው ሊቀነ ጳጳሳት ፣ ከጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅና የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አሰተዳዳሪዎች ጋር በደብረ ነገስት አበሃ ወአድብሐ ገዳም የተገኙት ቅዱስነታቸው በገዳሙ የሚገኘውን የጥንታዊ ቅርሶች ማስቀመጫ ሙዚየምን ተዛውረው ጐብኝተዋል፡፡

በገዳሙ አውደ ምሕረትም የገዳሙ አገልጋይ ካህናት ፣ የአካባቢው ሕዝበክርስቲያን በገዳሙ አቅራቢያ የሚገኝ የዘመናዊ ት/ቤት ተማሪዎች ለቅዱስነታቸው ደማቅ አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን የገዳሙ ሊቃውንትም ቅኔ እና ያሬዳዊ ዝማሬ ያቀረቡ አቅርበዋል፡፡ የገዳሙ ዋና አስተዳዳሪም የገዳሙን አመሠራረትና ታሪክ በማስመልከት ሰፊ ገለጻ አድርገዋል፡፡

ገዳሙ የሚገኝበትን አካባቢ የሚያስተዳድሩት አቶ ገ/ሚካኤል /አቦሐዊ/የቅዱስነታቸውን ሐዋርየዊ ጉብኝት በማስመልከት ንግግር አድርገዋል፡፡ በንግግራቸውም የቅዱስ ፓትርያርኩ ጉብኝት ለአካባቢያቸው ብሎም ለወረዳውና ለክልል ትግራይ ትልቅ በረከት መሆኑን ገልጸው በተለይም በአሁኑ ወቅት በትግራይ አንዳንድ አካባቢዎች በኤልኒኖ አለማቀፋዊ የአየር ተጽፅኖ ምክንያት በድርቅ የተጐዱ ወገኖችን በመጐብኘታቸውና በመባረካቸው ከፍተኛ ደሰታ የተሰማቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህ በበረሃማነቱ የሚታወቀው ቦታ በሕዝቡ ብርቱ ጥረት ለምላሜን እንዲላበስ በመደረጉ ዓለም አቀፍ ትኩረትና ማግኘት ችሏል፡፡ ያሉት አቦ ሃዊ ቀደምት አባቶቻችን አብርሃ ወአጽብሐ በዘመናቸው ሀገራቸውን በዓለም አቀፍ መድረክ ያስተዋወቁበትን ታሪክ በዘመናችን በሰራነው ውጤታማ አካባቢን የመለወጥ ሥራ ለማስተዋወቅና በዓለም መድረክ በአዲስ መልክ የመገናኛ ብዙሃን ርዕስ ማድረግ በመቻላችን ከፍተኛ ደሰታ ይሰማናል ብለዋል፡፡

በማያያዝም በድርቅ የከረመው ዘመናችን የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን ጉብኝት ተከትሎ ከፍተኛ ዝናብ በማግኘታችን ቦታው መልሶ የማገገም ዕድል ገጥሞታልና እንኳን ደስ ያላችሁ በማለት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩና የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጉብኝት በመንፈስ ቅዱስ የሚመራና የበረከት መሆኑን በማረጋገጣችን ከፍ ያለ ደስታ ይሰማናል በማለት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ለተሰበሰበው ሕዝበ ከርስትያን አባታዊ መመሪያና ትምህርት ሰጥተዋል ቅዱስነታቸው በቃለምዕዳናቸው እንደገለጹት የአብርሃ ወአጽብሐ ገዳም ጥታዊና ታሪካዊ መሆኑን ገልጸው የሁቱ ወንድማማች ነገስታታ ታሪክ በመላው ኢትዮጵያ የሚታወቅና የሚደነቅ ሲሆን በዘመናቸው ሁለቱ ነገስታት በመላው ኢትዮጵያ ታላላቅ ውቅር አብያት ክርስቲያናትና ሕንጻዎችን በማነጽ የሚከበርና የሚደነቅ ሥራ ሰርተው አልፈዋል ብለዋል፡፡

እነዚህን ታላላቅ አብያተ ክርስቲያናትን ያነጹ ነገስታት የሠሯቸው ሥራዎች በመላው ዓለም የሚደነቁ ሲሆኑ ታሪካቸውም እስከ ምድር ፍጻሜ ድረስ ሲዘከር ይኖራል ያሉት ቅዱስነታቸው እነዚህ ደጋግ ነገስታት የሠሯቸውን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና ትተዋቸው የሔዱትን ቅርሶች ተንከባክባችሁ እና ጠበቃችሁ የምትኖሩ እናተ ወገኖቸችን የታሪክ ባለቤትና ጠባቂ በመሆናችሁ ልት ደሰቱ ይገባችኋል ብለዋል፡፡

ዛሬ በዚህ ገዳም በተገኘንበት ጊዜ የተደረገልን አቀባበል አስደሳችና የሚያስመሰግን ነው ያሉት ቅዱስነታቸው እጅጉን በረሃማነት የሚታይበትን አካባቢ ለመለወጥ የጀመራችሁትን ዛፍ የመትከል ተግባር አጠናክራችሁ መቀጠል ይገባችኋል፡፡ ካሉ በኋላ ዛፎች የምድር ደም ስሮች ናቸው አንድ ሰው የደም ሥሩ ከተቆረጠ ዋጋ እንደሌለው ሁሉ ዛፎችም ከተቆረጡ መሬት ሥሯ ስለሚቆረጥ ዋጋ የላትም፡፡ ስለሆነም የምድርን ልምስሜ ለመመለስ የዛፎች መኖር ወሳኝ መሆኑን ተገንዝባችሁ ዛፎችን በመትከልና በመንከባከብ የከፈላችሁት መስዋዕትነት ለልጆችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ ኑሮ መሻል የሚኖረው ሚና እጅግ ከፍተኛ ስለሆነ የጀመራችሁትን የልማት ሥራ አጠናክራችሁ ቀጥሉ ብለዋል፡፡

ይህንን በማጠናከርም በዓለም ሙቀት መጨመር ምክንያት የተከሰተውን ድርቅ መከላከል እንደሚቻል የጠቆሙት ቅዱስነታቸው በአሁኑ ጊዜ የተፈጠረውን የድርቅ ችግር ከመንግስት ጋር በመሆን ለመከላከል ጥረቱ የሚቀጥል መሆኑን ጠቁመው ቤተክርስቲያን የተፈጠረው የድርቅ ችግር እንዲወገድ ጠንክራ ትጸልያለች ብለዋል፡፡ ለገዳሙ ካህናትም የ30,000 ብር ድጐማ ያደረጉ ሲሆን የብር መስቀላቸውም በገዳሙ በቅርስነት ተመዝግቦ እንዲቀመጥ ለገዳሙ አስተዳዳሪ አስረክበዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ የአብርሃ ወአጽብሐ ገዳም ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ አዲግራት ባቀኑበት ጊዜ በየመንገዱ ፣ በየመንደሩ ፣ በተለይም ደግሞ በእደጋ ሐሙስ ከተማና በአዲግራት ከተማ መግቢያ አካባቢ የተደረገላቸውው ደማቅ አቀባበል የሕዝቡ ብዛትና የአቀባበል መርሐ ግብሩ ስፋት በየትም ታይቶ የማይተወቅ ከመሆኑም በተጨማሪ የምስራቅ ትግራይ ነዋሪ ሕዝብ በአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ወቅት ያሳየው ጨዋነት፣ ለአባቶቹ ያለውን ፍቅር የገለፀበት ከመሆኑም በላይ የቅዱስ ፓትርያርኩንና የብፁዓን አበው ሊቀነ ጳጳሳትን መኪናና ልብስ በመዳሰስ ሰውነቱን እያበሰ በደስታ ሲፈነጥዝ ለተመለከተው ሕዝቡ በሃይማኖቱ የቱን ያህል እንደሚኰራ እንደሚመካና በጽናት እንደሚቆም ያሳየ ነበር፡፡ በዚሁ ወቅትም የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትየስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቀ ጳጳስ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖትን የምሥራቅ ትግራይ ዞን ሐዋርያዊ ጉዞን በማስመልከት የትግራይ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ተስፋ ሥላሴ ካህናት ፣ ምዕመናንና በካቶሊክ ቤተክርስቲያን የሚማሩ ተማሪዎች ከአዲግራት ከተማ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

የአዲግራት ከተማ ሕዝበ ክርስቲያንን የአቀባበል ሥነ ሥርዓትን በመቀላቀል የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የክልል ትግራይ ሊቀ ጳጳስ፣ የቤተክርስቲያኒቱ የሥራ ኃላፊዎችና ምዕመናን የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን ፎቶግራፍ በመኪናዎቻቸው ላይ በመለጠፍና ተማሪዎቻቸውም በሰልፍ ሥነ ሥርዓት ቅዱስነታቸውን እንዲቀበሉ በማድረግ በቅዱስነታቸው የአዲግራት ከተማ ሐዋርያዊ ጉብኝት የተሰማቸውን ደሰታ ገልጸዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ተስፋ ሥላሴ የክልል ትግራይ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስና የካቶሉክ ቤተክርስቲያን ካህናትም በአዲግራት ደብረ መድኃኒት መድኃኒት ዓለም ቤተክርስቲያን የቅዳሴ ቤት ማክበር ሥነ ሥርዓት ላይ በመገኘት በሕንጻ ቤተክርስቲያኑ ግንባታና የምረቃ ሥነ ሥርዓት የተሰማቸውን ደስታና ለቤተክርስቲያናችን ያላቸውን አጋርነት አረጋግጠዋል፡፡

ማምሻውን ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩና ለብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ክብር የምሥራቅ ትግራይ ሀገረ ስብከት ባዘጋጀው የዕራት መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የትግራይ ክልል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲየን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ተሥፋ ሥላሴ በቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉዞ የተሠማቸውን ልባዊ ደስታ በራሳቸው በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንና በዕምነቱ ተከታይ ምዕመን ስም ገልጸው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጋር በልማት ሥራዎች በጋራ የሚያከናውኗቸውን ተግባራት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ በዕምነቱ ፣ በማንነቱ፣በባህሉ እና በታሪኩ ኰሩ ሆኖ መኖር እንዲችል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ያበረከተችው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚገመት እንዳልሆነ የተናገሩት ብፁዕነታቸው በዛሬው ዕለት በቅዱስነትዎ የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ በመታደም የቅዱስነትዎን በረከት በማግኘታችን ከፍተኛ ደሰታ ይሰማናል ካሉ በኋላ ለቅዱስነትዎና ለቤተክርስቲያኒቱ ያለንን አክብሮትና ፍቅር ለመግለጽ ያዘጋጀነውን ሥጦታ እንዲቀበሉን በማክበር እንጠይቃለን በማለት ለቤተክርስቲያን አገልግሎት የሚውል የወርቅ ፅዋ ለቅዱስ ፓትርያርኩ አበርክተዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩም ሥጦታውን ከተቀበሉ በኋላ ባሰሙት አባታዊ ንግግር ለተደረገላቸው አቀባበልና ሥጦታ በማመስገን ከካቶሊክ ቤተክርስያን ጋር ያለንን የሃይማኖት ልዩነት ጠብቀን በዜግነታችን እና በክርስቶስ ልጅነታችን በዋና ዋና የልማት ሥራዎች ዙሪያ በጋራ በመሥራት ለክርስቶስና ለሰው ልጅ ደስታን የሚሰጥ አገልግሎት ማበርከት ይበቅብናል ብለዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ተስፋ ሥላሴ ከአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ጀምሮ በሕንጻ ቤተክርስቲያኑ ቡራኬ ላይም ሆነ በዚህ የእራት መርሐ ግብር ላይ ከእኛ ጋር በመሳተፍ የቤተክርስቲያናችን አጋርነትዎን በማሣየትዎ በአዲግራት ከተማ አቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይም እርሰዎ እና የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተከታይ ካህናቶች፣ ምዕመናንና ተማሪዎቻችሁ ላደረጉልን አቀባበል እና ለተሰጠን ስጦታ ምስጋናችን ላቅ ያለ መሆኑን እንገልጻለን ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ በምሥራቅ ትግራይ ዞን ቆይታቸው እጅጉን ደስተኛ መሆናቸውን የተናገሩት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በሕዝበ ክርስቲያኑ የሚታየውን መነቃቃት በመጠቀም ለልማት ማትጋትና የበለጠ ውጤታማ ሥራ እንዲሰራ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው በተለይም ድህነት ፣ ድንቁርናና ረሀብን ከሀገሪቱ ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ረገድ ሕዝበ ክርስቲያኑ የሚጠበቅበትን ሁሉ በጽናት መወጣት ይችል ዘንድ ጠንክሮ ማስተማር ይገባል፡፡ በማለት በአንዳንድ የትግራይ ወረዳዎች የተከሰተውነ ወቅታዊ የድርቅ አደጋ ለመከላከልና ለመቋቋም ከጸሎት ምህላ ጀምሮ አስፈላጊውን ሁሉ በመፈጸም የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል በማለት መልዕከታቸውን አጠናቀዋል፡፡

ከዚህ የሥጦታ ልውውጥ መርሐ ግብር ቀደም ብሎ በአዲግራት ከተማ በምሥራቃዊ ዞን ሀገረ ስብከት ሥር የሚገኘው የአዲግራት ደብረ መድኃኒት መድኃኔ ዓለም ቤተክርስቲያን ቅዳሴ ቤት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ተባርኰ የተመረቀ ሲሆን ቅዱስ ፓትርያርኩ ሕንጻ ቤተክርስቲያኑን ባርከው ከመረቁ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት ይህ ሕንጻ ከተራ ቤትነት ወደተቀደሰ ቤተክርስቲያንነት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሃይማኖታዊ ቀኖና መሠረት ተለውጧል፡፡ስለሆነም የአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን በገንዘቡ፣ በእውቀቱና በጉልበቱ ባሳነፀው ቤተክርስቲያን ሥጋ ወደሙ በመቀበል፣ ክርስትና በመነሳትና አስፈላጊውን መንፈሳዊ አገልግሎት ሁሉ በማግኘት ሊጠቀምበት ይችላል በማለት የቤተክርስቲያኑን መመረቅ በይፋ አብሥረዋል፡፡

የእግዚአብሔር ቤት የሚሰራው እግዚአብሔር እራሱ በመረጠው ቦታና ጊዜ እንደሆኑ ሁሉ ቤተክርስትያንን መሥራት የሚችሉም ባለቤቱ የመረጣቸውና የፈቀደላቸው ብቻ ናቸው የሉት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ለዚህ የተመረጣችሁና የተባረካችሁ ልጆቻችን እናንተም መድኃኔ ዓለም ፈቅዶላችሁ ይህን የመሠለ ቤተክርስቲያን ሰርታችሁ ለምረቃ አብቅታችኋልና እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል፡፡

አሁን ባስመረቅነው ሕንጻ ቤተክርስቲያን ውጤት ስንዘናጋ ወደፊት ሊሰሩ የሚገባቸው በርካታ ገቢ ማስገኛ ሕንጻዎች እና ሌሎች የልማት ሥራዎች ሊኖሩ እንደሚገባ ግልጽ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ታታሪውና ሥራ ወዳዱ የአዲግራት ሕዝበ ክርስቲያን እንደወትሮው ሁሉ በአንድነት ተባብሮ ሌላ ተዐምር ሊሰራ እንደሚችል የፀና እምነት አለን፡፡ በማለት በቀጣይነት ሊሰሩ የሚገባቸውን የልማት ሥራዎች ጠቁመው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በማናቸውም ልማታዊ ሥራዎቻችሁ ሁሉ ከጐናችሁ በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ የምታደርግ መሆኗን እናረጋግጣለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲዎስቆሬዎስ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቀደም ብለው ባደረጉት ንግግር በአዲግራት ሕዝበ ክርስቲያን መዋጮ ተገነባው የደብረ መድኃኒት መድኃኔ ዓለም ቤተክርስቲያን ለምረቃ በመብቃቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፡፡ ቤተክርስቲያኑ የመጀመሪያው የክርስትና ታሪክ ባለቤት በሆነው በክልል ትግራይ ምሥራቃዊ ዞን በአዲግራት ከተማ ጥንታዊ የሆነ ታሪኩን በጠበቀ መልኩ የተሰራ በመሆኑ ከቤተ ጸሎትነቱ ባሻገር ከአንድ ምዕተ ዓመት በኋላ የሀገር ቅርስ /የትውልድ ቋሚ መታሰቢያ/ሆኖ የሚኖር ነው ብለዋል፡፡

ይህንን የመሰለ ሕንጻ ቤተክርስቲያን በገንዘብ በእውቀትና በጉልበታችሁ የገነባችሁ የከተማችን ነዋሪዎች ሁሉ ምስጋና ይገባችኋል፡፡ ያሉት ብፁዕነታቸው ይህን ታሪክ በዘመናችን በመሥራታችሁ የሃይማኖታችሁ ፍሬና የምልካም ሥራችሁ ማረጋገጫ ማኀተም ከሆነው ከዚህ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ጋር ባለውና በሚመጣው ትውልድ ስትታሰቡ ትኖራላችሁ ካሉ በኋላ በዚህ የኪነ ጥበብ እድገታችን ጐልቶ በታየበት የሕንጻ ቤተክርስቲያን ሥራ ለበረከት በጠራናችሁና የእግዚአብሔር ፈቃድ በአደረባችሁ ልዩ ጥረት ተጠናቆ ቅዳሴ ቤቱ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቡራኬ ለመከበር በመብቃታችን በድጋሚ እንኳን ደስ ያላችሁ እያልን በሥራው ሁሉ የረዳን እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን በጐ ሥራችንና ለስሙ ያላችሁን ፍቅር የማይረሳ ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን ዋጋችሁን ይክፈላችሁ በበረከት ይባርካችሁ በማለት መልዕክታችውን አጠቃለዋል፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የክልል ትግራይ ካቶሉካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ተስፋ ሥላሴን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የአዲግራት ከተማና የአካባቢው ምዕመናን የተገኙ ሲሆን የሕንጻ ግንባታውን ከፍጻሜ ለማድረስ 5,000,000.00/አምስት ሚሊየን ብር/ወጪ መደረጉንና የአዲግራት ነዋሪ ሕዝብ በዘመቻ መልክ በየመንደሩ በመደራጀት ከፍተኛ የጉልበት እና የግንባታ ማቴሪያል አቅርቦት አስተዋጽኦ ማበርከቱን በምረቃ በዓሉ ላይ ሪፓርታቸውን ያቀረቡት የሕንጻ ሥራ ኮሚቴ ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡ በዚህ እለትም የቤተክርስቲያኑ የሰንበት ት/ቤት ለሚያሰራው አዳራሽ እና ሀገረ ስብከቱ ለሚያስገነባው ባለ 5 ፎቅ ሁለገብ ሕንጻ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የምሥራቅ ትግራይ ሀገረ ስብከት የጉብኝታቸው አንዱ አካል የሆነውን የአዲግራት ዮንቨርሲቲን ጥቅምት 27 ቀን 2008 ዓ.ም ምሽት ላይ ጐብኝተዋል፡፡

የዩንቨርሲቲውን አጠቃላይ ይዞታ ፣ የተማሪዎችን ዶርምተሪና የመመገቢያ ቦታዎችን በመኪና በመዘዋወር የተመለከቱት ቅዱስነታቸው ዩንቨርሲቲው የሚጠቀምበትን የዘመናዊ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል እና ማዕከሉ የሚሰጠውን ሳይንሳዊ ጥቅም ተመልከተዋል፡፡ በባለሙያዎችም ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

የአዲግራት ዩንቨርሲቲ ዲን ዶ/ር ዓለም በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት የቅዱስ ፓትርያርኩና የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጉብኝት ለዩንቨርሲቲው ማሕበረሰብ መነቃቃትን የሚፈጥር በመሆኑ በታላቅ አክብሮትና ደስታ የሚመለከቱት መሆኑን ገልጸው ዩንቨርሲው ከኤርትራና ከሱማሊያ ለተፈናቀሉ ሰዎች የመማር እድልን በመፍጠር ሀገራቸው ሰላም በሚሆንበት ወቅት ለሀገራቸው እድገት የበኩላቸውን የሚወጡበት ሁኔታ መፍጠሩን ጠቁመው ዩንቨርሲቲውም ከሌሎች የሀገሪቱ ዩንቨርሲቲዎች የሚለይባቸውንና ውጤታማ እየሆነባቸው ያለውን የትምህርት ዘርፍና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመዘርዘር ለቅዱስ ፓትርያርኩ ገልጸዋል፡፡

ቅዱስነታቸውም የአዲግራት ዩንቨርሲቲን ተዛውረው በመመልከታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ተማሪዎችና መምህራን እንዲሁም የዩንቨርሲቲው ዲን ለቅዱስ ፓትርያርኩና ለብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ያደረጉትን የክብር አቀባበል በአድናቆት እንደሚመለከቱትና ከፍ ያለ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል፡፡

የአዲግራት ዩንቨርሲቲ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደራጀና የተሟላ የትምህርት ተቋም በመሆኑ ለመማር ማስተማር ሥራው ከፍተኛ ጠቃሜታን ይሰጣል፡፡ ያሉት ቅዱስነታቸው በተለይም ለሁለቱ ጐረቤት ሀገራት ስደተኞች የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ በማድረግ የጐረቤትነት ግዴታችንን መወጣታችሁ የሚያስመሰግንና የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡

መንግሥት ይህ ትውልድ በዘመናዊ የኢንፎርሜሽን ኰመኒመሻን በተደራጀና የዓለም የሥልጣኔ መገለጫ በሆኑ የትምህርት ግብዐቶች በተሟላ መልኩ ዕውቀት እንዲጨብጥ ለማድረግ እያደረገ ያለው ጥረት ለሀገሪቱ ዕድገትና ሥልጣኔ ወሳኝ በመሆኑ የሚደነቅ ነው ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩ ይህ እድል የተሰጠው ወጣቱ ትውልድ የተፈጠረለትን በጐ አጋጣሚ በአግባቡ መጠቀምና ለውጤት መብቃት አለበት ብለዋል፡፡

ከአዲግራት ዩንቨርሲቲ የጉብኝት መርሐ ግብር በመቀጠል በአዲግራት ደብረ ፀሐይ ቅ/ሥላሴ ቤተክርስቲያን በዩንቨርሲቲው ተማሪ ለሆኑ ወጣቶች ቅዱስ ፓትርያርኩ ቃለበረከትና ቡራኬ ሰጥተዋል፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩ ለተማሪዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት በተሟላና በዘመናዊ እንዲሁም በሰፊ ት/ቤት በመማራችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ካሉን በኋላ ከእናንተ በፊት ትምህርት ይማሩ የነበሩ ወገኖቻችሁ ባልተሟላና ባልተደራጀ የትምህርት ማዕከል ውስጥ በብዙ ድካም ከገቡ በኋላ በተለያዩ ችግሮች ትምህርታቸውን መቀጠል፡፡ የማይችሉበት ደረጃ ላይ በመድረስ ችግር ላይ ይወድቁ ነበር እናንተ ግን ዘመናችሁ የተባረከ በመሆኑ በዘመናዊ ግብዐት በተሟላ የትምህርት ማዕከላት የመማር እድል ስለገጠማችሁ ፈጣሪያችሁን በማመስገን ትምህርታችሁን በአግባቡ መከታተልና ለሀገራችሁና ለቤተክርስቲያናችሁ ልማት የምትሰሩ እንድት ሆኑ አደራ እላለሁ፡፡ በማለት ምክር ለማስዋል፡፡

ውድ ልጆቻችን ዛሬ በዩንቨርቲቲያችሁም ሆነ በመንገድ ማካፊያው ግራና ቀኝ ተሰልፋችሁ የእኛን መምጣት ስትጠባበቁ የነበራችሁና የክብር አቀባበል ያደረጋችሁልን ሁሉ የሃይማኖታችሁን ጽናት በተግባር ያሳያችሁ በመሆናችሁ ምስጋና ይገባችኋል ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩ እኛም የእናንተን ሃይማኖተ ጠንካራነት ባየን ጊዜ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል ልዑል እግዚአብሔር ፀጋና በረከቱን ያድላችሁ ተምራችሁ ለቤተክርስቲያናችሁ እድገት የምትተጉ ያድርጋችሁ በማለት ባርከዋቸዋል፡፡

የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ እግዚብሔርን መፍራት እንደሆነ የጠቆሙት ቅዱስነታቸው በፈሪሐ እግዚብሔር የታነጻችሁና በእውቀት የበለፀጋችሁ በመሆን ለሀገርና ለወገን የሚጠቅም ሥራ የምተሰሩ መሆን ትችሉ ዘንድ ትምህርታችሁን በአግባቡና በሥነ ሥርዓት መማር ይገባችኋል በማለት አባታዊ መልዕክታቸውን አጠናቀዋል፡፡

ተማሪዎቹም የቅዱስነታቸውን አባታዊ መመሪያ በሆታና በእልልታ የተቀበሉ ሲሆን ለቅዱስነታቸው እና ለብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የእንኳን ደህና መጣችሁ ርችት ተኩሰዋል፡፡

በምሥራቅ ትግራይ ሀገረ ስብከት በውቅሮ ፣ በአጽቢወንበርታ ፣ በአሲራመቲራ ፣ በአብርሐ ወአጽብሐ ፣ በእደጋ ሐሙስ ፣ በአዲግራት ከተማና በአዲግራት ዩንቨርሲቲ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የአቀባበል መረሐ ግብር በሰልፍ የወጣው የሕዝብ ክርስቲያን ቁጥር እጅጉን ከፍተኛ በመሆኑ የቅዱስነታቸውን ሐዋርያዊ ጉዞ የተሳካ እንዲሆን ያደረገ ሲሆን ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን እንዲሁም ቅዱስነታቸውን ተከትለው በምሥራቅ ትግራይ ዞን የተጓዙ የልዑካን ቡድንን ያስደመመና ያስደሰተ የአቀባበል ሥነ ሥርዓት መሆኑ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሲገለጽ የቆየ የቅዱስነታቸው የሐዋርያዊ ጉዞ ልዩ ትዝታ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለመገለጽ እንወዳለን፡፡

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የምሥራቅ ትግራይ ሀገረ ስብከት ሐዋርያዊ ጉብኝት የተወለዱበትን፣ የተማሩበትን እና በደግርግ ዘመነ መንግሥት ከ2,500 በላይ ወገኖችና ከ20,000.00 በላይ እንሰሳት በቦንብ ተደብድበው መሥዋዕት የሆኑበትን የሐውዜን ከተማን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡ አባታዊ ቡራኬና ቃለምዕዳንም ሰጥተዋል፡፡

ጥቅምት 28 ቀን 2008 ዓ.ም ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ፣ ከጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች ፣ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎችና የደብር አስተዳዳሪዎች ጋር በመሆን በወልዋሎ ቁሸት ደብረ ብርሃን ቅዱስ ቂርቆስ በሚባል ጥንታዊ ገዳም የተገኙት ቅዱስነታቸው ተወልደው ባደጉበት መንደርና ክርስትና በተነሱበት ገዳም ተሰብስበው ለጠበቋቸው በርካታ ምዕመናንና አገልጋይ ካህናትን ከባረኩ በኋላ አባታዊ ቃለምዕዳንና ትምህርት ሰጥተዋል፡፡

ቅድስነታቸው በደብረ ብርሃን ቅዱስ ቂርቆስ ቤተክርስቲያን ለተሰበሰቡ ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት ሃይማኖታችሁን፣ ታሪክና ባህላችሁን ጠብቃችሁ የደረሰባችሁን መከራና ችግር ተቋቁማችሁ በመቆየታችሁ ምስጋና ይገባችኋል፡፡በዚህ ቤተክርስቲያን የሚገኘውን ቅርስ በሚገባ በመጠበቅ እና ለመጪው ትውልድ ለማሰተላለፍ በመቻላችሁም ልትደሰቱ ይገባችኋል፡፡ ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩ እናንተ ከአባትና አያቶቻችሁ የተረከባችሁትን ታሪክ ፣ ባህልና ሃይማኖታችሁን ጠብቃችሁ እንደቆያችሁት ሁሉ ልጆችና የልጅ ልጆቻችሁም ሃይማኖታቸውን ፣ ታሪክና ባህላቸውን ጠብቀው መኖር ይችሉ ዘንድ በሚገባ ልታስተምሯቸውና ልተመክሯቸው ይገባል ብለዋል፡፡

ከረጅም ዘመን በኋላ ወደተወለዱበትና ወደአደጉበት ሀገር መመለሳቸውን ያስታወሱት ቅዱስ ፓትርያርኩ ከዘመናት በኋላ ለመገናኘት በመብቃታችን እንኳን ደስ ያላችሁ ካሉ በኋላ በልጅነታቸው ላገለገሉበት ቤተክርስቲያን ለአምስቱ ልዑካን የመቀደሻ ልብስ እና አንድ የእጅ የብር መሰቀላቸውን ለገሰዋል፡፡ቅድስ ቂርቆስ ቤተክርስቲያንን ጨምሮ በወልዋሎ አካባቢ ለሚገኙ 8 አብያተ ክርስቲያናትም ለእያንዳንዳቸው አሥር ሺህ ብር ለግሰዋል፡፡

በመቀጠልም ቅዱስነታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ የተማሩበትን የማርያም ሰውና ገዳምን የጐበኙ ሲሆን በገዳሙ ሲደርሱ የገዳሙ አበምነት ካህናት ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች እና የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ በቅዱስነታቸው መልካም ፈቃድ ትምህርት የሰጡት የቅዱስነታቸው የልዩ ጽ/ቤት ኃላፊው ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ ሰፊና ጥልቅ ትምህርት የሰጡ ሲሆን በትምህርታቸውም ችግር ፣ ርሐብ ፣ ጦርነት ፣ ቸነፈር የማይፈተው የትግራይ ሕዝብ ይህን የመሰለ በረሃማ አካባቢ በማልማትና መሬቱ መልሶ እንዲያገግም በማድረግ ከፍተኛ የልማት ሥራ እየሠራ መሆኑን ስንመለከት ቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በአጠቃላይ ከቅዱስነታቸው ጋር የመጣን በሙሉ በታሪክ ሰሪነታችሁ በልማት አርብኝነታችሁና በቅርስ ጠባቂነታችሁ ኮርተናል ብለዋል፡፡

አካባቢን ማልማት ልማትን ማስፋፋትና ማጠናከር ቅርስን መጠበቅ ፣ በሃይማኖት መጽናትን ከወላጆቻችሁ ተምራችሁ ለልጅ ልጆቻችሁ ለማውረስ እያደረጋችሁት ያለው እንቅስቃሴ ሁሉ የሚያስደስት እና የሚያኰራ ነው ያሉት ክቡር ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ በመጽፍ ቅዱስ ምድርን አልማት ተብሎ በልዑል እግዚአብሔር የተሰጠንን አምላካዊ ትዕዛዝ እንዲሁም በላብህ ጥረህ ግረህ ብላ የሚለውን አምላካዊ ቃል በተግባር የፈጸማችሁና በመፈጸም ላይ ያላችሁ በመሆናችን ተደስተናል ብለዋል፡፡

ልማትን ማጠናከር ፣ መሥራት፣ መለወጥና አካባቢን በመጠበቅ ሀገራችንን ማልማት ይጠበቅብናል በማለት ስለአካባቢ ልማት ብሎም ስለሀገር ልማትና በውጤቱም ሕዝብ ምን ያህል ተጠቃሚ እንደሚሆን ጠንካራ መልዕክት ያስተላለፉት ክቡር ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ በትግራይ አንዳንድ አካባቢ የሚታየው በዓለም አቀፉ የኤልኒኖ ተጽዕኖ የተፈጠረውን የምግብ እጥረት ለመቋቀም እንደምትችሉ ጽኑ እምነት አለን ካሉበኋላ ከዚህ በፊት ደርግን ታግላችሁ በመጣል አሁን ደግሞ ድህነትን ለመጣል ያደረጋችሁት ተጋድሎና ያስመዘገባችሁት ውጤት የድርቁን አደጋ በመቋቋም ክፉውን ቀን እንደምታሳልፉት ማረጋገጫ ነው፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩም ለገዳሙ የብር መስቀልና ለአምስቱ ልዑካን መቀዳሻ የሚሆን አልባሳትን እንዲሁም 10,000.00ብር ለገዳሙ ለግስዋል፡፡

በዚሁ እለት በቅዱስነታቸው የተጐበኘው የሐውዜን ከተማ ሕዝብ ሲሆን ቅዱስነታቸው ሐውዜን ከተማ ከመድረሳቸው 10 ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ ካህናት፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ፣ሚሊሻዎች ፣ በአጠቃላይ የከተማዋ ነዋሪዎች በአውቶቡስ፣ በሚኒባስ፣ በሞተር ሳይክልና በእግር በማጀብ ከፍተኛ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ በሀውዜ ደብረ ሃዋዝ ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን ከሀገረ ሽማግሌዎች በተወከሉ አባላት ስለሃውዜን ከተማ አመሠራረት፣በደርግ ዘመን ስለደረሰበት የቦንብ ጥቃትና መስዋዕትነት ለቅዱስ ፓትርያርኩ ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

በዚሁ ጊዜ በሐውዜን ደብረ ሃዋዝ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰበው ሕዝብ ትምህርትና ቃለምዕዳን የሰጡት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በድህነት ላይ የሚኖርን፣ የዕለት ኑሮውን ለማሸነፍ ላይታች የሚል ፣ በገበያ ውስጥ የዕለት ጉርሱን ለመሸመት፣ ለመሸጥና ለመለወጥ የሚሯሯጥን ሕዝብ በሚግ አውሮፕላን በመታገዝ በቦንብ መፍጀት የግፍ ግፍ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ያኔ የነበረውን ጊዜ ያየ ዛሬ በመላ ሀገሪቱ በስውዓቱ መሰዋዕትነት እየተመዘገበ ያለውን ልማትና ውጤቱን ሲያይ ደስተኛ ነው፡፡ ይህን በመስዋዕትነት የተገኘን ሰላም ጠብቀን ሃይማኖታችንን ማስፋፋትና ልማትችንን ማፋጠን እንደሚገባን በገንዘብ ከመንግስት ጐን በመሆን ሀገራችንን ማልማት ይጠበቅብናል ካሉ በኋላ የሃውዜን ከተማ ሕዝብ ይህንን አውቆ አካባቢውን ለማልማትና ለመለወጥ የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡

በቤተክርስቲያኑ ለሚሰራው ሕንጻ ቤተክርስቲያን የ30,000.00ብር ድጋፍ ያደረጉት ቅዱስነታቸው ሕዝቡ ሃይማኖቱን ፣ ባህሉን ፣ ቅርሱን ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚደረገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል አደራ ብለዋል፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩ የደርግ ሰማዕታትን መታሰቢያ ሐውል በመጐብኘት ጸሎት ያደረጉ ሲሆን በማግስቱ ጠዋትም በደረግ አውሮኘላን የተደበደበውን ቦታ ተዛውረው ተመልክተዋል፡፡ በዚህም የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የምሥራቅ ትግራይ ሀገረ ስብከት ሐዋርያዊ ጉብኝት ተጠናቋል፡፡

የፎንት ልክ መቀየሪያ