Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

በሀገረ ስብከቱ ለሚታነጹ አራት ሕንጻዎች የመሠረት ድንጋይ አኖሩ

እስክንድር ገ/ክርስቶስ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ ከተማ በአሶሳ የታነጸውን የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያንን ቅዳሴ ቤት ለማክበርና ሕዝቡን ለመባረክ ኅዳር 10 ቀን 2008 ዓ.ም አሶሳ ሲደርሱ የክልሉ አፈ ጉባኤ አቶ ፍቃዱ ታደሰ እና የክልሉ ፕሬዝዳንት ተወካይ ብፁዕ አቡነ ሔኖክ የምዕራብ ወለጋ ፣ የቄለም ወለጋና የአሶሳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ስምኦን የምሥራቅ ወለጋ እና የሆሮጉድሩ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በአሶሳ አየር ማረፊያ በመገኘት አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
በአሶሳ አየር ማረፊያ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በተደረገው ደማቅ የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ የክልሉን የብሔር ብሔረሰብ አልባሳት የለበሱ፣ የበርታ ብሔረሰብ የእስልምና እምነት ተከታዮች በክልሉ የብሔረሰብ ሙዚቃ በመተጀብ የታላቀ መሪነት አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ ከመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከልም የፕሬዝዳንቱ ተወካይ ፣ የክልሉ አስተዳርና ፀጥታ ኃላፊ፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ኃላፊ፣የክልሉ ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ የክልሉ የርዕሰ መስተዳድና ካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ እና የክልሉ የባሕልና ቱሪዝም ኃላፊ ተገኝተዋል፡፡

Picture 159 Picture 163 Picture 166 Picture 170 Picture 197 Picture 203 Picture 236 Picture 260 Picture 262 Picture 290 Picture 319 Picture 345 Picture 372 Picture 378 Picture 379 Picture 396 Picture 402 Picture 413 Picture 424 Picture 432 Picture 434 Picture 443 Picture 480 Picture 494

ለቅዱስነታቸው ክብር ከአየር ማረፊየው እስከ ከተማው ብሎም የአቀባበል መርሐ ግብር እስከ ተዘጋጀበት መንበረ ስብሐት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ድረስ ካህናት ፣ የከተማዋ ነዋሪዎች ፣ ምዕመናንና ምዕመናት ፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በአውቶቡስ ፣ በሚኒባስ ፣ በባጃጅና በሞተር ብስክሌት በመታጀብ በከፍተኛ ድምቀት አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡


በመ/ስ/ቅ/ማርያም ቤተክርስቲያን በተከናወነው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይም ያሬዳዊ ወረብ በሊቃውንት የቀረበ ሲሆን የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በክልሉ አፈ ጉባኤ በአቶ ፍቃዱ ታደሰ ተደርጓል፡፡ አቶ ፍቃዱ በንግግራቸውም ቅዱስነትዎ የተለያዩ ብሔር ብሐረሰቦችና የተለያዩ ሃይማኖቶች በመከባበርና በመቻቻል ወደ ሚኖሩበት አሶሳ ከተማ እንኳን በደህና መጡ ካሉ በኋላ ኢትዮጵያ ሀገራችን የተለያዩ የሃይማኖት ተከታዮች የሆኑ ብሔር በብሔረ ሰቦችና ሕዝቦች መኖሪያ እንደሆነች ይታወቃል ከነዚህም መካከል ክልላችን አንዱ እንደመሆኑ መጠን የሁሉም ሃይማኖት ተከታዮች በፍቅር ፣ በመተሳሰብ ፣ በመቻቻልና በመደጋገፍ ለሀገር ግንባታ በጋራ በመረባረብ ላይ ይገኛሉ፡፡
በዚህም መሠረት ለደወፊቱ ይህንን ጠንካራ የመቻቻል፣ የመተሳሰብና የመደጋገፍ ባህላችንን ይበልጥ በማጐልበት የአብሮነታችን አደጋ የሆኑትን የአክራሪነትና የሽብርተኝነት አመለካከትና ተግባራትን በጋራ ትግል መቀልበስና ለሀገራችን ዕድገት በጋራ መረባረብ ይገባል ብለዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ሔኖክ የምዕራብ ወለጋ፣ የቄለም ወለጋ እና የአሶሳ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በበኩላቸው በእኛ በልጆችዎ የተደረገልዎትን መንፈሳዊ ጥሪ ተቀብለው ለዚህ ህዝብና ሀገረ ስብከት ታላቅ አክብሮት በመስጠት ከዚህ ቦታ በመገኘትዎ ከፍ ያለ ምስጋና እያቀረብኩ እንኳን በሰላም መጡልን ለማለት እወዳለሁ ብለዋል፡፡
የአሶሳ ሕዝበ ክርስቲያን የአባቶቹን ፈለግ ተከትሎ በእኩልነት ተፈቃቅሮና ተከባብሮ የሚኖር ሕዝብ በመሆኑ ቅዱስነትዎና ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያስተላልፋቸውን መመሪያዎች ተከትለው በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና በሀገረ ስብከቱ የሚሰጣቸውን አቀጣጫ በመቀበል ታሪክ እየሰሩ ያሉ ናቸው ብል ማጋነን አይሆንብኝም ያሉት ብፁዕነታቸው ይህን ለማለት የተገደድኩት በመሃል ሀገር ከሚሰሩ ሥራዎች ባልተናነሰ በዚህ ጠረፍ ቦታ ያከናወኗቸው በርካታ የአብያተ ክርስቲያናት ግንባታና የልማት ሥራዎች ለቅዱስነትዎና ለቅዱስ ሲኖዶስ ትልቅ ተስፋ ሆነው ስለተገኙ ነው ብለዋል፡፡
ለሀገረ ስብከቱ የልማት ሥራ ጥንካሬ እንደ ማሳያ የሚሆነውም ዛሬ በቅዱስነትዎ ተባርኮ ለአገልግሎት የሚበቃው የአሶሳ መ/ስ/ቅዱስ ገብርኤል ሕንጻ ቤተክርስቲያን አንዱ በመሆኑ ይህን የመሰለ አኩሪ ሥራ እየሰራ ያለውን ሕዝብና ልጆችዎን እንዲያመሰግኑ እጠይቃለሁ በማለት ንግግራቸውን አጠቃለዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ በበኩላቸው የክልሉ መንግሥት አፈ ጉባኤ ፣ የፕዚዝዳንቱ ተወካይ ፣ የካቢኔ አባላትና የከተማዋ ሕዝብ በአየር ማረፊያ በመገኘት ለአደረጉላቸው ደማቅ አቀባበል በተለይም የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑት ወገኖቻችን በአየር ማረፊያ በሙዚቃ የታጀበ አቀባበል፡፡ ማድረጋቸውን አድንቀው በራሣቸውና በኢትዮትያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስም አመስግነዋል፡፡
ሃይማኖትና መንግሥት በሕገ መንግሥቱ መለየየታቸው ግልጽ እንደሆነ የጠቀሱት ቅዱስ ፓትርያርኩ ሁላችንም የምንመራው ሕዝብ አንድ ስለሆነና በአንድ ሀገር የሚኖር ስለሆነ ለምንኖርባት ሀገር ሰላም ፣ ፍቅር ፣ አነድነትና ልማት በጋራ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ካሉ በኋላ ሕዝቡ ለሥጋዊ ፍላጐቱ መሳካት ከመንግሥት ጋር በጋራ እንደሚሰራው ሁሉ ለመንፈሳዊ ሕይወቱ ስንቅ ለመቋጠር የሚያስችለውን ትምህርት ከሃይማኖት አባቶቹ በማግኘት በሰላም በፍቅርና በአንድነት እንዲኖር ከማድረግ ባሻገር በሥነ ምግባር በመታነጽ የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ግዴታ ለመወጣት እንዲችል ቤተክርስቲያን አጥብቃ መሥራት እንደሚጠበቅባት በመገንዘብ ስብከተ ወንጌልን የማስፋፋት ሥራዋን በማጠናከር ላይ ትገኛለች ብለዋል፡፡
በመንበረ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የተገኙትና ታቦተ ሕጉን ከመቃኞ አዲስ ወደ ተሠራው ሕንጻ ቤተክርስቲያን አስፈላጊው መንፈሳዊ ቡራኬ በማከናወን ያስገነቡት ቅዱስ ፓትርያርኩ በቤተክርስቲያኑ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ለተገኙ ምዕመናን ሰፊ ትምህርትና ቡራኬ ሰጥተዋል፡፡
ይህን የመሰለ ዘመናዊና ውብ ሕንጻ ቤተክርስቲያን በገንዘባችሁ ፣ በእውቀታችሁና በጉልበታችሁ በማነጽ ለምረቃ ያበቃችሁ ሁላችሁም እንኳን ደስ ያላችሁ ካሉ በኋላ ይህ ሕንጻ በዛሬው ዕለት በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ተባርኰ ከተራ ሕንጻነት ወደ ተቀደሰ ቤትነት በመለወጡ እንኳን ደስ ያላችሁ፡፡ይህ ሕንጻ ቤተክርስቲያን የምታስቀድሱበት፣ ልጆቻችሁና የልጅ ልጆቻችሁ ክርስትና የሚነሱበት ፣ በሥርዓተ ተክሊል የሚዳሩበት፣ ሥጋ ወደሙ የምትቀበሉበትና ወንጌል የምተማሩበት በመሆኑ እንኳን ለምረቃ በዓሉ አደረሳችሁ ካሉ በኋላ በቤተክርስቲያኑ የሚታዩ ቀሪ የልማት ሥራዎች ተጠናቀው እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡
እነሆ ዛሬ የእግዚአብሔር በረከትና ቸርነት በዚህ ቤት ስለሚያድር ሁላችሁንም ይቀድሳል ይባርካል ያሉት ቅዱስነታቸው ልመናችሁ ቅድመ እግዚአብሔር እንዲደርስ ፣ መንፈሳዊ አገልግሎት ሁሉ እንድታገኙበት ይህን የመሰለ ሕንጻ በመገንባታችሁ በድጋሚ እንኳን ደሰ አላችሁ እላለሁ ብለዋል፡፡
በማግስቱ ኅዳር 11 ቀን 2008 ዓ.ም አዲስ በተሠራው ቤተክርስቲያን በመገኘትና ሥርዓተ ቅዳሴውን በመምራት ቀድሰው ያቆረቡት ቅዱስነታቸው በአውደ ምሕረቱ በመገኘት የሕንጻ ቤተክርስቲየኑን ምርቃት ሥነ ሥርዓት በማስመልከት የተዘጋጀውን መርሐ ግብር ተከታትለዋል፡፡
በምረቃ በዓሉ ላይ ከክልሉ ብሔር ብሔረሰቦች መካከል የክልሉ ተወላጅ የሆኑ ወገኖች
1ኛ. ሰው ያለእግዚአብሔር መኖር አይችልም ከዚህ በኋላ ወደ ኋላ አንልም እናንተም እንዳትለዩን
2ኛ. ከዚህ ድረስ መጠታችሁ ስለአያችሁን ከፍተኛ የደስታ ስሜት ፈጥሮብናል፡፡
3ኛ. ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ ወረዳ እየተፈለግን በመሆኑ ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል
4ኛ. እንደምንፈለግ በማየታችን ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል፡፡
5ኛ. ስለ እምነታችን በቋንቋችን የሚያስተምረን ያስፈልገናል፡፡የሚሉ መሠረታዊ መልዕክት የያዙ ባነሮችን በመያዝ በበዓሉ ላይ ታድመዋል፡፡
በዚሁ ጊዜ ከወረዳ የመጡ ወጣቶች በጉሙዝ ቋንቋ መዝሙር ያቀረቡ ሲሆነ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ 40,000 የጉሙዝ ብሔረሰብ አባላት ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን መቀላቀላቸውና 18 አብያተ ክርስቲያናትም እንዲታነጹላቸው መደረጉን ተገልጾአል፡፡
በዚሁ ጊዜ ወጣቶች የብሔረሰቡ አባላት በባነር ያስተላለፉአቸው መሠረተዊ መልዕክቶች ምላሽ ማገኘት የሚገባቸው መሆናቸውን የተገነዘቡት ቅዱስ ፓትርያርኩ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ለሚሰለጥኑበት ት/ቤት ግንባታ የሚውል የ50,000.00 ብር ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን ብፁዕ አቡነ እንጦንስና ብፁዕ አቡነ ማትያስ እያንዳንዳቸው የአንድ ሺህ ዶላር ስጦታ አድርገዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ሙሴም አንድ ሺህ ዩሮ በመለገስ ለብሔረሰቡ ተወላጆች ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ሔኖክ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ከክልሉ ብሔረሰቦች መካከል ክርስትና የተነሱ ቅስናና ዲቁና የተቀበሉ ወገኖች መኖራቸውን ጠቁመው በቋንቋቸው የሚያሰተምራቸው እንዲያገኙ ያቀረቡትን ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ባለ3 ፎቅ የአብነት ት/ቤት ለማስገንባት ቦታ መዘጋጀቱን ፣ የመሠረት ድንጋይ ለማስቀመጥ መታቀዱንና ለግንባታ የሚያስፈልገው ገንዘብ በስፓንሰር መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
ቅዱስነታቸው በአሶሳ ከተማ ተገንብቶ የተመረቀውን ሕንጻ ቤተክርስቲያን የካቴድራልነት ማዕረግ የሰጡ ሲሆን በካቴድራሉ ሊገነባ ለታሰበው ባለ አራት ፎቅ ሁለገብ ሕንጻ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ብሎም የመ/ስ/ቅ/ማርያም ቤተክርስቲያን ለሚያስገነባው ባለ 4ፎቅ ሁለገብ ሕንጻ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡በተያያዘ ዜና ቅዱስ ፓትርያርኩ በአንዚ/መ/ገ/መድኃኔ ዓለም ቤተክርስቲያን ለሚያሰራው ሕንጻ ቤተክርስቲያን የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጡ ሲሆን በቤተክርስቲያኑ ለተሰበሰበው ሕዝበ ክርስቲያን በክቡር ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ የቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጸሐፊ ሰፊ ትምህርት ተሰጥቷል፡፡
ክቡር ንቡረዕድ ኤልያስ አብርሃ በትምህርታቸው ሕዝቡ ሃይማኖቱን ጠንቅቆ እንዲያውቅ፣ ለሃይማኖቱ መስፋፋት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ልጆቹ በሃይማኖታቸው የሚኮሩ ፣ ለሃይማኖታቸው የሚቆረቆሩ እና ሃይማኖታቸውን ለማስፋፋት ሌት ተቀን የሚደክሙ መሆን እንዲችሉ ወላጆች የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ማበርከት እንደሚገባቸው በማስገንዘብ ሰፊ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩም ዛሬ መሠረት ያስቀመጥንበት የሕንጻ ቤተክርስቲያን ሥራ በአግባቡ ተከናውኖ ሥራው በሚፈለገው ጥራትና ፍጥነት ተሰርቶ ለውጤት ይበቃ ዘንድ ገንዘብ ፣ዕውቀት፣ ሐሳብና ጉልበታችሁን በማስተባበር ለውጤት ታበቁት ዘንድ አደራችን የፀና ነው ብለዋል፡፡
በዚሁ ሰፊና ምቹ ቦታ ላይ ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን በመስራት የቤተክርስቲያኒቱን የገቢ ምንጭ በማሳደግ የመልአከ ኃይል እንየውን የረጅም ጊዜ ሕልምና ፍላጐት ለማስካት የበኩላችሁን ማበርከት ይጠበቅባችኋል ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩ በዚህ ቦታ ከእናንተ ከልጆቻችን ጋር በመገናኘታችን የተሰማንን ደሰታ ለማስተላለፍ እወዳለሁ ብለዋል፡፡ በክልላችሁ ብሎም በሀገራችን ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የሀገራችንን ልማት ማፋጠንና የተጀመረውን ድህነትን የማጥፋት ሥራ በየ ችሎታችን በመደገፍ ሀገራችንን ማሣደግና በመንግሥት በኩል የሚደረገውን ጥረት መደገፍ ይገባናል፡፡ በማለት ስለ ሰላምና ልማት አሥፈላጊነት ሰፊ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡
ኅዳር 12 ቀን 2008 ዓ.ም በአሶሳ ሀገረ ስብከት በጽርሐ አርአያም ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ዓመታዊ ክብረ በዓሉን ያከበሩት ብፁዕ ወቀዱስ ፓትርያርኩ የቤኒሻንጉል ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር በመሆን ሲሰሩ የነበሩትን አቶ አብዱል አህመድ ኢብራሂምን በማጥመቅ የቤተክርስቲያን ልጅ እንዲሆኑ አድርገዋቸዋል ስመ ክርስትናቸውም ኃ/ሚካኤል ተብለዋል፡፡
አቶ አብዱል አህመድ በወቅቱ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንና የቤተሰቦቻቸው ቅርበት ሥር የሰደደና በ1950ዎቹ አካባቢ የሚጀምር መሆኑን ጠቁመው በተለይም መልአከ ኃይል እንየው ወደ አሶሳ ለአገልግሎት በመጡ ጊዜ በአቶ አብዱል አህመድ አባት ቤት ማረፊያ ተሰጥቶአቸው የቤተክርስቲያኒቱን ሥራ ሲያከናወኑ እንይቆዩ ጠቀመው መልአከ ኃይል እንየው ቤተክርስቲያኒቱን ለማስፋፋትና ለማጠናከር፣ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትን ለመከፈትና ወንጌልን ለማስፋፋት ያደርጉት የነበረው ጥረት የአቶ አብዱል አህመድን ቀልብ የሳበና የክርስትና ህይወትን እንዲናፍቁ ያደርጋቸው እንደነበር ጠቁመዋል፡፡
አቶ አብዱል አህመድ ኢብራሒም ባለቤታቸውና ልጆቻው ክርስቲያኖች ሲሆኑ እርሳቸውም በመንፈስና በህሊና የክርስትና እምነት አራማጅ ሆነው መቆየተቸውን ጠቁመው ጊዜው ሲደርስና እግዚብሔር ሲፈቀድ እነሆ ክርስትና ተነስቼ ኃይለ ሚካኤል ለመባል በቅቻለሁ ብለዋል፡፡ በዛሬው ዕለት እጅግ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል ያሉት አቶ አብድል አህመድ ይህች ቀን ዳግመኛ የተፈጠርኩባትና በአዲስ ሕይወት አዲስ ኑሮ የምጀምርባት የተባረከች ቀን ናት ካሉ በኋላ አዲስ አበባ በትምህርት ላይ የሚገኙት ልጆቻቸው ይህን ዜና ሲሰሙ በጣም እንደተደሰቱና ማመን እንደተቸገሩ ገልጸውልናል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩም አቶ አብዱል አህመድና ባለቤታቸውን ከባረኩ በኋላ የክርስትና ሕይወታቸው የተቀና እንዲሆን ዘወትር ወደ ቤተክርስቲያን በመመላስ ፣ መማርና ማሰቀደስ እንደሚገባቸው መክረው በቅርቡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጠያቂነት በዓለም መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር ወጪ በኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማበር አሳታሚነት በድምጽ የተዘጋጀውን የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት በሽልማት ያበረከቱላቸው ሲሆን በድምጽ የተዘጋጀውን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን በማድመጥ እውቀታቸውን እንዲያበለጽጉ እንደሚረዳቸው ተናግረዋል፡፡
በጽርሐ አርአያም ቅ/ሚካኤል ቤተክርስቲያን በተዘጋጀው መርሐ ግብር ላይም ክቡር ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጸሐፊ ሰፊ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡በትምህርታቸው ማጠቃለያ ላይም እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ሊያነሳና ነጮች በመዝገበ ቃላታቸው ላይ የድህነትና የርሀብ ተምሳሌት አድርገው ያስቀመጡትን ሊፍቅ በቤኒሻንጉል አካባቢ አባይ እንዲገደብና ኢትዮጵያንም ወደ ቀደመ ገናናነቷ ሊመልስ ጊዜው የፈቀደ መሆኑን ጠቁመው እግዚአብሔር በፈቀደው ጊዜ በመንግሥት በኩል ለሚካሄደው የልማት ሥራና የሀገር ግንባታ ሥራዎች ዙሪያ ሕዝቡ የሚጠበቅበትን ሁሉ መፈጸም እንደሚገበው መክረዋል፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩም በዓሉን ለማከበር ለተሰበሰበው ሕዝበ ክርስቲያን ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ በመስጠት የዕለቱ በዓል ተጠናቋል፡፡ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በጉብኝታቸው ማጠቃለያ ወቅት በአሶሳ ወረዳ አምባ አንድ ሆህ ገነተ ማርያም የሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ ገዳምንና በዘመናዊ መንገድ የተደራጀውን ጸበል ቤት ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን በጸበል ቤቱ ለሚገነባው ሕንጻ ቤተክርስቲያንም የመሠረት ድንጋይ አሰቀምጠዋል፡፡ ገዳሟንም አጽንተዋል፡፡በገዳሟ መከናወን ስለሚገባቸው ዋና ዋና ሥራዎችም መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
በመቀጠልም ቅዱስ ፓትርያርኩ በሀገረ ስብከቱ የተገነባውን 5 የመኝታ ክፍሎችና አንድ አዳራሽ ያለው የካህናት ማሠልጠኛ መርቀው የከፈቱት ሲሆን ቅዱስ ፓትርያርኩ ሀገረ ስብከቱ በክልሉ ቋንቋ የሚያስተምሩ ወጣቶችን በማሰልጠን የክልሉን ሕዝብ በቋንቋው የመማር ዕድል ለማረጋገጥ እያደረገ ያለውን ጥረት ያደነቁ ሲሆን ተቋሙ በተሟላ ሁኔታ ሥራዎችን ማከናወን ይችል ዘንድ ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በሀገረ ስብከቱ ቆይታቸው በሀገረ ስብከቱ እየተከናወኑ ያሉት ተስፋ ሰጪ የልማት ሥራዎች እጅጉን እንዳስደሰታቸው የገልጹት ቅዱስ ፓትርያርኩ ይህ ሁሉ ውጤት ሊመዘገብ የቻለው በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ፣ በሥራ አስኪያጁና በሥራ ኃላፊዎች መካከል መናበብ በመኖሩ መሆኑን ጠቁመው ወደፊትም በጋራ ለቤተክርስቲያን እድገት እያከናወናችሁ ያለውን ልማታዊ ሥራ አጠናክራችሁ መቀጠል ይገባችኋል ብለዋል፡፡
የቅዱስ ፓትርያርኩን ሐዋርያዊ ጉብኝት መጠናቀቅ ተከትሎ በ12/03/2008 ዓ.ም ማታ ላይ ለቅዱስ ፓትርያርኩና ለብፁዓን አበው ሊቀነ ጳጳሳት እንዲሁም ለጠቅላይ ቤተክህነት ልዑካን ክብር በተዘጋጀው የእራት መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የክልሉ ም/ቤት አፈ ጉባኤና ከፍተኛ የክልሉ አመራሮች በቅዱስነታቸው ጉብኝት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው በሌሎች የክልሉ ዞኖች ቅዱስነታቸው ጉብኝት እንዲያደርጉና ቡራኬ እንዲሰጡ ጋብዘዋቸዋል፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩም የአሶሳ ከተማ ኢትዮጵያዊያን በጋራ በመሆን የሀገራቸውን ልማት ለማረጋገጥና ድህነትን ለመሰናበት በጥቅሉ የኢትዮጵያን ገጽታ ለመለውጥ የህዳሴውን ግድብ የሚገነቡበት ክልል በመሆኑ ሁለንተናዊ እድገት በማስመዝገብ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው ሁላችንም በየተሰማራንበት ሆነን ለሀገር ልማት መሥራት ይጠበቅብናል በማለት በሀገረ ስብከቱ ፣ በመንግስትና በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል አመስግነዋል፡፡
ኅዳር 13 ቀን 2008 ዓ.ም የአሶሳ ይፋዊ ጉብኝታችውን ያጠናቀቁት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በክልሉ መንግሥት የቁርስ ግብዥ የተደረገላቸው ሲሆን ወደ አዲስ አበባ በሚመለሱበት ጊዜ የክልሉ ም/ፕሬዝዳንት አምባደር ምስጋናው አድማሱ እና የክልሉ አፈ ጉባኤ አቶ ፍቃደ ታደሰን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በአሶሳ አየር ማረፊያ በመሸኘት የክብር አሸኛኘት አድርገውላቸዋል፡፡

የፎንት ልክ መቀየሪያ