Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51
 • ቅዱስነታቸው የተለያዩ የሀይማኖት መሪዎችና የመንግስት ባለሥልጣናትን አነጋግረዋል፤

                                                       በመምህር ሙሴ ኃይሉ እና በመምህር ዳንኤል ሠይፈ ሚካኤል

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትየጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዳግማይ ትንሣኤን በዓል ምክንያት በማድረግ ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ሐዋርያዊ ጉብኝት አደረጉ፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን አስከትለው ረቡዕ ሚያዝያ 26 ቀን 2008 ዓ.ም ምሽት ላይ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ ብዛት ያላቸው ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ ኃላፊዎች እንዲሁም የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ከፍተኛ አሸኛኘት ያደረጉላቸው ሲሆን በእስራኤል ቴልአቪቭ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱም በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ክቡር አቶ ህላዌ ዮሴፍ እና የኤምባሲው ሠራተኞች፣ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም፣ የገዳሙ መጋቢ አባ ፍስሐ፣ እና የገዳሙ ማኅበረ መነኮሳት፣ የኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት እና ብዛት ያላቸው ምዕመናን ከፍተኛ መንፈሳዊ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

Picture 019 Picture 041 Picture 065 Picture 073 Picture 093 Picture 097 Picture 104 Picture 108 Picture 112 Picture 158 Picture 324 Picture 331 Picture 335 Picture 350 Picture 352 Picture 357 Picture 539 Picture 548 Picture 582 Picture 590 Picture 628 Picture 629 Picture 680 Picture 732

በአየር ማረፊያው ልዩ የእንግዳ መቀበያ ሳሎን ዕረፍት በማድረግም በወቅቱ ለተሰበሰበው ሕዝብ አባቶችን አክብሮ መቀበል እና ሲሄዱም አክብሮ መሸኘት የቆየ የኢትዮጵያውያን መልካም ባህል መሆኑን ገልጸው ይህንን ባህል መሠረት በማድረግ በዚህ ሌሊት እዚህ ድረስ መጥታችሁ አባቶቻችሁን በመቀበላችሁ እጅግ ልትመሰገኑ ይገባችኋል በማለት በራሳቸውና በብፁዓን አባቶች ስም ምስጋና እና ቡራኬ ሰጥተው የአየር መንገድ አቀባበል መርሐ ግብር ፍጻሜ ሆኖአል፡፡

ከአየር መንገድ መርሐ ግብር በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትያርኩ እና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በቀጥታ ወደ ደብረ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ገዳም በማምራት በገዳሙ ላይ በመገኘት ጸሎተ ኪዳን በማድረስ ወንጌል ከተነበበ በኋላ የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም ባስተላለፉት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት "ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ለረጅም ጊዜ በሊቀ ጵጵስና ዘመንዎ ወደ ደከሙበት ገዳምዎ እኛን ገዳማውያን ልጆችዎን ለመባረክና ጥንታውያን ገዳማቶቻችንን ለመጎብኘት እንኳን ደህና መጡልን፡፡ የቅዱስነትዎ መምጣት ለገዳማችን ትልቅ ክብርና ሞገስ ነው፤ በመንግስትም ሆነ በወንድሞቻችን የሃይማኖት መሪዎች ዘንድ ተሰሚነታችንን ይጨምራል፤ ችግራችንንም ይነገራል፣ ይደመጣል፤ ይህም ለገዳማችን ትልቅ በረከት ስለሆነ በቅዱስነትዎ መምጣት በጣም ደስ ብሎናል፤ ራሳችንም እንደ እድለኞች እንቆጥረዋለን ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ቃለ ቡራኬና ቃለ ምዕዳን እንዲሰጡ ጋብዘዋቸዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በበኩላቸው ከሦስት ዓመታት በኋላ ተመልሰን ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ገዳማችን በመምጣታችን በጣም ደስ ብሎናል፡፡ እናንተም አባቶቻችን ይመጣሉ ብላችሁ በሌሊት ከአየር ማረፊያ ጀምራችሁ ላደረጋችሁልን አቀባበል በጣም ልትመሰገኑ ይገባችኋል፡፡ የኢትዮጵያ ጥንታውያን ቅርሶች የሆኑት ገዳማቶቻችንን በብዙ መከራ እና ሰማዕትነት ጥንታውያን ርስታችሁን አጥብቃችሁ እየጠበቃችሁ ላላችሁ ባለ አደራ ልጆቻችን ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው፤ እግዚአብሔር ከለፈው ይበልጥ ጽናትንና ፍቅርን ሰጥቶ ምናኔያችሁን አክብራችሁ ለትልቅ ክብር እንድትበቁ የሁላችንም ምኞት እና ጸሎት ነው በማለት ገዳማውያኑን አመስግነዋል፡፡

ሐሙስ ሚያዝያ 27 ቀን 2008 ዓ.ም

ሐሙስ ሚያዝያ 27 ቀን 2008 ዓ.ም በታላቁ የዴር ሱልጣን ገዳማችን ላይ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት በጎልጎታ ይዞታ ያላቸው የሁሉንም አብያተ ክርስቲያናት ፓትርያርኮች እና መሪዎች በተገኙበት ቅዱስ ፓትርያርኩ ጎልጎታ ከመድረሳቸው በፊት ከመኪና ወርደው ከሁሉንም የአርመን፣ የግሪክ፣ የላቲን፣ የኮፕት፣ የፍራንሲስካን ፓትርያርኮች እና መሪዎች ጋር መንፈሳዊ ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ በከፍተኛ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ክቡር አቶ ህላዌ ዮሴፍ እና የኤምባሲው ሠራተኞች፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን የቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ተሳላሚዎች በተገኙበት ከፍተኛ መንፈሳዊና ይፋዊ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

በዚህም ቦታ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጰጳሳትም ቅድሚያ በሌሎች ይዞታዎች ላይ የሚገኙ መድኀኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን፣ የተገነዘበትን፣ የተቀበረበትን፣ የተነሣበትን... ሁሉንም ዞረው ከተሳለሙ በኋላ በጎልጎታ ውስጥ የሚገኘው የራሳችን መድኃኔዓለም ገዳም ገብተው ጸሎተ ኪዳን አድርሰዋል፡፡ በገዳሙም ክቡር አምባሳደርና የኤምባሲው ሠራተኞች፣ የገዳማችን መነኮሳት እና መነኮሳይያት እንዲሁም ከኢትዮጵያና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በመገኘት በእልልታ፣ በጭብጨባና በመዝሙር የአቀባበል መርሐግብሩ ደማቅ እና በቦታው ከተለመደ ሥርዓት ለየት ያለ ትርጉም እንዲኖረው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

በዴር ሱልጣን መድኃኔ ዓለም ገዳም ላይ አስቀድመው ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ካደረጉ በኋላ አባ ገብረ ሥላሴ የተባሉ የገዳሙ አባት ቅዱስነታቸው ወደ ኢትዮጵያ ከሄዱ ጀምሮ ያለውን የዴር ሱልጣን ነባራዊ ሁኔታ ገለጻ አድርገው ለዕለቱ ያዘጋጁትን ቅኔም ለቅዱስነታቸው አበርክተዋል፡፡ የአባ ገብረ ሥላሴ ቅኔ ተከተሎም ሌሎች ሊቃውንት ምስጢር እየሳባቸው የተሰማቸውን ደስታ በቅኔ ገልጸዋል፡፡ በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በገዳሙ ለተሰበሰቡት ካህናት፣ መነኮሳት እና ምዕመናን ትምህርተ ወንጌል ቃለ ምዕዳንና ቃለ ቡራኬ አስተላልፈዋል፡፡

ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታውያን ገዳማት የኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆኑ የአፍሪካውያን ሁሉ ተጠቃሽ ምልክቶች መሆናቸውን ታሪካዊ ዳራውን በማንሳት ሰፊ ገለጻ አድርገዋል፡፡ በመሆኑም እነዚህ የማንነታችን፣ የጥንታዊነታችን አሻራዎችና ምስክሮች የሆኑ ገዳማቶቻችን የሃይማኖት ብቻም ሳይሆን የሀገርም ሀብት፣ መመኪያና ቅርስም ጭምር ናቸው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የድኅነት ሥራውን ፈጽሞ ካረገ በኋላ ኢትዮጵያውያን መናንያን ከሀገራቸው በግብፅና በሱዳን በረሃ እያቋረጡ በመምጣት ለተባሕትዎ ብለው የሠሯቸው ገዳማት መሆናቸውን አስታውሰው የቦታው የርስትነት ይዞታ ግን ከንግሥት ሳባ ጀምሮ ለኢትዮጵያውያን ነጋድያን (ተሳላሚዎች) ማረፊያ ተብሎ የተሰጠ ከመሆኑም በላይ ከዚያን ዘመን ጀምሮም በከፍተኛ ትጋት እና ቁርጠኝነት ተጠብቆ የኖረ ቅርስ መሆኑን በሰፊው ገልጸዋል፡፡

ይህ ጥንታዊ የኢትዮጵያውያን ርስት እንደ አባቶቻችሁ ሁሉ ይዞታችሁን አጽንታችሁ፣ ምናኔያችሁን አስምራችሁ የምትኖሩ መነኮሳት ልጆቻችንም ቤተ ክርስቲያን ሁሌም ቢሆን ትኮራባችኋለችና ከፍ ያለ ምስጋናም ይገባችኋል፤ አሁንም ደግሞ በበለጠ መልኩ ይህንን አገልግሎታችሁን አጠናክራችሁ መቀጠል ይኖርባችኋል፡፡ ከኢትዮጵያም ሆነ ከመላ ዓለም በረከት ለማግኘት ወደ ቅድስት ሀገር የምትመጡ ልጆቻችን ምዕመናንም እንዲህ ተሰባስባችሁ በዚህ መገኘታችሁ ከመሳለማችሁ በተጨማሪ ጥንታውያን የሃይማኖታችሁ ምልክቶች የሆኑ እነዚህ ገዳማትን በዕውቀታችሁ፣ በገንዘባችሁ እና በጉልበታችሁ በመደገፍ ደጀን ስለሆናችሁ ከፍተኛ ምስጋና ይገባችኋል፡፡ ይህን ሁሉ እንኳ ባታደርጉ እዚህ መገኘታችሁ ብቻ ገዳሙ ከጀርባው የሚጠብቀው ብዙ ህዝብ እንዳለ ለምስክርነት የሚያገለግል በመሆኑ ለገዳሙ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው በማለት ሰፊ ቃለ ምዕዳን በማስተላለፍ መርሐ ግብሩ በጸሎት ተጠናቋል፡፡

ከዴር ሱልጣን መድኃኔዓለም ገዳም ጸሎትና ቃለምዕዳን በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርኩና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የኢትዮጵያ አምባሳደር፣ የአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ጵጵስና አዳራሽ ላይ የሻይ ቡና መስተንግዶ ተደርጎላቸዋል፡፡ በዚህ መስተንግዶ ወቅት በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ክቡር አቶ ህላዌ ዮሴፍ ባስተላለፉት መልእክት የኢትዮጵያ ኤምባሲ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራቸው ዋና ዋና ሥራዎች ውስጥ በዋናነት በኢየሩሳሌም የሚገኙ ጥንታውያን የኢትዮጵያ ገዳማት ቅርስነታቸውን ታውቆ ይዞታቸውን እንዲጠበቁ በማድረግ ዙርያ ሰፊ ሥራዎች ተሠርቶአል፡፡ የዚህ ገዳማችን ቁልፍ ችግር፤ ችግሩ በሁሉም የሚመለከታቸው አካላት (በሃይማኖት እና በመንግስት ኃላፊዎች) ዘንድ ታውቆ ትኩረት አለማግኘቱ ላይ ነው፡፡ የዚህ ገዳም ችግር የሚታወቀው በእነዚህ አባቶች መነኮሳት እና በኤምባሲው ብቻ ነው፤ በዚህ ደግሞ በትክክል ችግሩ ምን እንደሆነ ተለይቶ ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ሊያመጣ አልቻለም፡፡ ስለዚህ ኤምባሲው ከእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ተደጋጋሚ ውይይት እና ከፍተኛ የሆነ ቅሬታ አቅርበናል፤ ይሁን እንጂ እንፈታለን ከማለት የዘለለ ምንም መፍትሔ ሊሰጡን አልቻሉም፡፡ ስለሆነም ኤምባሲው እንደ አቅጣጫ የወሰደው ነገር ቢኖር ይህ ችግር በሁሉም ዘንድ እንዲታወቅ ማድረግና ሁሉም ባለድርሻ አካላት (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ የኢትዮጵያ መንግስት እና ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ) በጉዳዩ ላይ ሰፊ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ ባቀድነው መሠረት አጠናክረን እየሠራን እንገኛለን፡፡ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቀው በማለት በኢትዮጵያ ቴሌቪዢን በተደጋጋሚ ፕሮግራም እንዲሠራለት በማድረግ፣ መንግስትም ወደ እስራኤል ሀገር ለሥራ የሚመጡ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናትም ገዳሙ እንዲጎበኙ በማድረግና ችግሩን በማስረዳት ከአቻ የእስራኤል ባላሥልጣናት ጋር እንዲወያዩበት በማድረግ፤ አሁን በቅርቡ እስራኤል ለመጎብኘት የመጡት የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሚኒስቴር ወ/ሮ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ገዳሙን እንዲጎበኙና ችግሩን በአግባቡ እንዲረዱት በማድረግ ትልቅ ሥራ ተሠርቶአል፡፡ አሁንም በቅርቡ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ከፍተኛ የእስራኤል ባላሥልጣናት ወደ ኢትዮጵያ ስለሚሄዱ ይህንን የዴር ሱልጣንን ጉዳይ በአጀንዳነት እንዲያዝ አቅርበን ተፈቅዶልን ለውይይት አጀንዳ ተይዞዋል በማለት ማብራራያ ሰጥተዋል፡፡

በመቀጠልም ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም የገዳማቱንና የገዳማውያኑን ችግር አስመልክተው መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ብፁዕነታቸው የዴር ሱልጣን ገዳም ጉዳይ ሰፊ እና ዘመናት የተሻገረ ውስብስብ ችግር በመሆኑ ከገዳሙ አቅም በላይ ሆኖ በአባቶች መነኮሳት ላይ ትልቅ ችግር እያስከተለ ይገኛል፤ የዚህ ዋንኛ ምክንያትም ቅድም ክቡር አምባሳደሩ እንደገለጹት አንድ ነገር ሲገኝ እዚሁ ገዳሙ ለብቻው ይጮኻል ትንሽ ረገብ ሲል ደግሞ ይተዋል፤ ስለሆነም የዚህ ጥንታዊ ቅርሳችን ችግር ዘለቄታዊ በሆነ መንገድ መፍትሔ እንዲያገኝልን ቅዱስነትዎ ለመንግሥት ባለሥልጣናት ከፍተኛ ማሳሰቢያ ሰጥተውልን የኢትዮጵያ መንግስት እና የእስራኤል መንግስት ተወያይተውበት ዘመናት እየተሻገረ የመጣውን የዴር ሱልጣን ጉዳይ አንድ እልባት ማግኘት አለበት በማለት ከገለጹ በኋላ በግብጻውያን ወንድሞቻችን እየደረሰብን ያለውን ችግር ግን በጣም የሚያሳዝን መሆኑንና በእነርሱ ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ኢትዮጵያውያን መናንያን በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከውሻ ማደሪያ ባነሰ ቤት ውስጥ እንዲኖሩ እየተገደዱ እንደሚገኙ ልብን በሚነካ ሁኔታ በግብፃውያን በኩል እየተፈጸመባቸው ስላለው መከራ ሰፋ አድርገው በመግለጽ ንግግራቸውን አጠናቀው ቅዱስነታቸውን ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ እንዲሰጡ ጋብዘዋቸዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ በበኩላቸው የኢየሩሳሌም ገዳማት ችግር በተለይ የዴር ሱልጣን ችግር የቆየ ችግር መሆኑን ገልጸው ከዚህ በኋላ የሁለቱም ሀገር መንግሥታት በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥተው ተወያይተውበት ዘላቂ ሰላም መፈጠር ይኖርበታል፡፡ ከግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር በሌላ በኩል መልካም ግኑኝነት ያለን ቢሆንም በዚህ በዴር ሱልጣን በኩል ግን ሁሌም በግጭት ላይ ነን ያለነው፤ ስለሆነም አሁን መንግስትም ይሄ ገዳም የሃይማኖት ብቻም አይደለም፤ የሀገርም ቅርስና ይዞታ ስለሆነ በሀገራችን እንደሚገኙ ጥንታውያን ቅርሶቻችን እነዚህም ያላቸውን የታሪክና የሃይማኖት ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ትኩረት ሰጥቶ ከሚመለከተው አካል ጋር ተነጋግሮ በዚህ ገዳም ላይ ዘላቂ የሆነ ሠላም እንዲፈጠር የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል፤ ቤተ ክርስቲያንዋም የበኩልዋን ድርሻ መወጣት አለባት፤ ሁሉም የየድርሻውን ከተወጣ የማይፈታ ችግር አይኖርም በማለት ሰፊ ታሪካዊ ትንተና በማቅረብ ጭምር መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ እያደረገው ያለው በጎ ሥራ የሚያበረታታና ለወደፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆን እንደሚገባው አሳስበው እስካሁን አምባሳደሩ ላደረጉት ጥረት ከፍተና ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡ ቅዱስነታቸው አሁንም ደግመው ደጋግመው ገዳማውያኑ አሁንም እንደትላንት በርትታችሁ ገዳማትሁን ጠብቁ፤ ይዞታችሁን አትልቀቁ፤ ከትላንት ዛሬ ይሻላል፣ ከዛሬ ደግሞ ነገ የተሻለ እንደሚሆን እንጸልያለን፤ ስለዚህ ችግሩንም መከራውን ታግሳችሁ የአባቶቻችሁን አደራ ለአፍታ እንኳ ልትዘነጉት አይገባም በማለት መነኮሳቱን መክረዋል፣ አበረታትተዋል፡፡                     

ዓርብ ሚያዝያ 28 ቀን 2008 ዓ.ም

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ማኅበረ መነኮሳትን ሰብስበው አነጋግረዋል፡፡ በመርሐግብሩ መጀመሪያ ላይ የገዳሙ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡ ብፁዕነታቸው የገዳሙን ችግር ዘርዝረው በማንሣት ይህ የገዳሙ የቆዩና አዳዲስ ችግሮች መፈታት የሚችሉት በዋናነት በቅዱስነትዎ እና በቅዱስ ሲኖዶስ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ከተሠራ ብቻ ነው በማለት ያለውን ነባራዊ ሁኔታ አስረድተዋል፡፡ ብፁዕነታቸው የገዳሙ ችግር ብለው ከዘረዘርዋቸው ውስጥ በቅድሚያ ዘመን እየተሻገረ የመጣው የዴር ሱልጣን ጉዳይን አንስተዋል፤ በዴር ሱልጣን ላይ በግብጻውያን ወንድሞቻችን እየደረሰብን ያለው ችግር ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም፤ በዚህ በሃያ አንድኛው ክፍለ ዘመን ውሻ እንኳ የጌታዋን ቤት እንድትጠብቅ ተብሎ ያማረ ቤት እየተዘጋጀላት በሚገኘው በዚህ ዘመን የእኛ አባቶች ግን መብራት እና ውኃ እንዳይገባላቸው፣ የሚኖሩበት ቤት እንዳይታደስ... እያደረጉት ያሉት ጭካኔ የተሞላበት ተጽዕኖ ይህ ነው የማይባል ነው፡፡ ስለሆነም የዴር ሱልጣን ጉዳይ ቅዱስነትዎ በዋናነት ትኩረት ሰጥተዉት በቅዱስ ሲኖዶስ አስወስነው ከመንግሥት ጋራ ተመካክረው ሥርዓት እንዲይዝ ካልተደረገ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ነው ያለነው በማለት እያንዳዱ ክስተት በመዘርዘር አስረድተዋል፡፡ በእስራእል መንግሥት በኩልም ከሀያ ዓመት በላይ የኖሩ መነኮሳት ቪዛ ለማሳደስ ስንጠየቅ ሆን ተብሎ በዋናነት የዴር ሱልጣን ታሪክን ጠንቅቀው የሚያውቁ መነኮሳት እነዚህ ስለሆኑ አባርሩልን እየተባበሉ ከኮፕቶች ጋር እየተመሳጠሩ ቪዛ እንዳይሰጥ በሕግ የተሰጠንን መብት እየተነፈግን ነው ሲሉ ምሳሌዎችን አንስተው ለአባቶች አስረድተዋል፡፡ እዚህ ብንጮኽ ምንም ምላሽ አጥተናል፤ ስለዚህ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኖ ከመንግስት ጋር ተመካክሮ መልስ እንዲሰጠን ስንል በገዳሙ ስም ቅዱስ አባታችንን እጠይቃለሁ በማለት የመክፈቻ ንግግራቸውን አጠናቅቀዋል፡፡

የገዳሙ መጋቢ አባ ፍስሐ በበኩላቸው ተመሳሳይ የሆነ ሐሳብ በማንሳት የገዳሙ ችግር የሚባሉት ጠቅሰው ለቅዱስ ፓትርያርኩና ለብፁዓን አባቶች አስረድተዋል፡፡ በዋናነት ካነሡት ሐሳብ አሁን የተያዘው አቅጣጫ በተለይ የዴር ሱልጣን ታሪክ በደንብ የሚያውቁ መነኮሳት በዚህም በዚያም ተብሎ ከዚህ ሀገር እንዲወጡ በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ለማሳያ የአባቶችን ስም በመጥቀስ የገጠማቸውን ችግር በማንሣት አስረድተዋል፡፡ ግብጻውያን በሚሠሩት ሴራ አብዛኛዎቹን ሰዎች በሙስና ውስጥ ለውስጥ በመደለል የተለያዩ በደሎች በእኛ ላይ እንዲደርስብንና ተማርረን ሀገር ለቀን እንድንሄድ ከዚያም እነርሱ ቦታውን ያለ ምንም ተቃውሞ ለመውረስ ከፍተኛ ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙ የቪዛ አሠጣጥ ችግሩን ምሳሌ በማቅረብ አስረድተዋል፡፡

ሌሎች አባቶች መነኮሳት የማኅበሩ አባላትም በቅዱስ ፓትርያርኩ ተፈቅዶላቸው እንደዚሁ ያላቸውን ችግር አስመልክተው ሁሉንም ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡ የሁሉንም ሐሳብ ተጠቃልሎ ሲታይ "በግፍ ከፍተኛ በደል እያደረሱብን ያሉ ግብጻውያን ሁሌም ቢሆን ከላይ መንግስታቸውም ሆነ ቅዱስ ሲኖዶሳቸው አይዞአችሁ፣ በርቱ፣ አለንላችሁ... ስሚሏቸው ነው፡፡ እኛም ከ90 ሚልዮን በላይ ኢትዮጵያዊ ወገን እያለን፣ መንግስት እያለን፣ ቅዱስ ሲኖዶስ እያለን ልንበረታታና ድጋፍ ልናገኝ ይገባናል፤ እነርሱም እንደልባቸው እውነትን በውሸትና በገንዘብ እየቀበሩ ሌትና ቀን ችግር እያደረሱብን ያሉ ምንም አያመጡም፣ እዚሁ እንደተለመደው ጮኸው ይቀራሉ እያሉ ነው፤ ታድያ እንዲህ እየተባልን እና ግፍ እየተፈጸመብን የምንኖረው እስከመቼ ነው፤ እኛ የተለየ ነገር ይደረግልን አላልንም ነገር ግን ለሁሉም አብያተ ክርስቲያናት በእስራኤል መንግስት ዘንድ የተሰጠ መብት እንዴት እንነፈጋለን፤ እኛ ብዙ ጊዜ በምሬት የምናቀርበውን ቅሬታ ሳይሰማ እነርሱ የሚያቀርቡት የሐሰት ውንጀላ በአስቸኳይ ይቀበሏቸዋል፡፡ እንግዲህ እየሠራ ያለው እውነት ሳይሆን ገንዘብ ነው፤ ስለዚህ ቅዱስ ሲኖዶስ ግልጽ የሆነ ውሳኔ ወስኖ ከመንግስት ጋራ ተመካክሮበት መፍትሔ እንዲሰጠን የሚሉ በዋናነት ይገኙበታል፡

ከዚህ በመቀጠል ሁሉንም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጰጳሳት በየተራ በቀረበው የገዳሙ ዘመን የተሻገሩ እና ወቅታዊ ችግሮች ላይ ሰፊ ግንዛቤ መጨበጣቸውንና ከእነርሱ የሚጠበቀውን ሁሉ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ገልጸው ነገር ግን እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ አሁንም ተጠናክሮ ያለውን ችግሩ ተቋቁማችሁ የአባቶቻችሁ፣ የሀገራችሁን የቤተ ክርስቲያናችሁን አደራ በርትታችሁ መወጣት ይገባችኋል በማለት አደራ ጭምር አበረታትተዋቸዋል፡፡

በመጨረሻ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩክ በበኩላቸው በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና በማኅበረ መነኮሳቱ በኩል የተነሡ ችግሮች ከጥንት ጀምሮ የነበሩ መሆናቸውን ታሪክ እየጠቀሱ አስረድተው አሁን ስለተነሱት ጉዳዮችም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት የዚህ ገዳም ችግር እንዲፈታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የሚቻለውን ሁሉ በማድረግ ላይ እንደሚገኙና ለወደፊትም ይህንን ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ለማኅበሩ አስረድተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ቅዱስነታቸው ታሪክ ጠቅሰው ትላንት አባቶቻችን የሚበሉት የሚጠጡት እንኳ ሳይኖር የዕለት ጉርስ እየለመኑ ነው ይዞታውን ጠብቀው ያቆዩት ከትላንትናው የአባቶቻችን ዘመን አሁን እኛ እንሻላለን፤ ዛሬ ገዳማችን ራሱን ችሎ እየተዳደረ ነው፤ ይህንንም ማየታችን ትልቅ ጸጋ ነው፤ ከዛሬ ደግሞ ነገ እግዚአብሔር የተሸለ ያደርገዋል ብለን እናምናለን፡፡ ስለዚህ መናንያን ልጆቻችን የቆየ ገዳማዊ ጥንካሬችሁን ጠብቃችሁ ገዳማችሁን አገልግሉ፤ እኛም ሁላችን ከጎናችሁ ነን፤ ቅዱስ ሲኖዶስም ከጎናችሁ ነው፤ የቀረቡት ጥያቄዎች ግን ለቅዱስ ሲኖዶስ እንደ መነሻ ሆነው እንዲያገለግሉ መጀመሪያ ዘርዝራችሁ በጽሑፍ ላኩልን ከዚያ ቅዱስ ሲኖዶስ ተወያይቶ አንድ ውሳኔ ላይ ይደርሳል በማለት መክረው ጉባኤውን በጸሎት ዘግተዋል፡፡

ቅዳሜ ሚያዝያ 29 ቀን 2008 ዓ.ም       

ሚያዝያ ቅዳሜ 28 ቀን 2008 ዓ.ም ቅዱስነታቸውና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ በደብረ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ገዳም በመገኘት ጸሎተ ኪዳን አድርሰው ሥርዓተ ቅዳሴውንም መርተዋል፡፤ በመጨረሻም ከተለያዩ ክፍለ ዓለማት ለመሳለም የመጡ ምዕመናን በተገኙበት ሰፊ ትምህርተ ወንጌል፣ ቃለ ምዕዳንና ቃለ ቡራኬ ሰጥተዋል፡፡

እሁድ ግንቦት 29 ቀን 2008 ዓም

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትየጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመሆን ሚያዝያ እሁድ 29 ቀን 2008 ዓ.ም የዳግማይ ትንሣኤን በዓል በደብረ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ገዳም አክብረዋል፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩ እና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ከሌሊቱ በ10 ሰዓት በገዳሙ የተገኙ ሲሆን ቅዱስ ፓትርያርኩ ጸሎተ ኪዳን አድርሰው ቀድሰው በማቁረብ ምዕመናንን ባርከዋል፣ አስተምረዋል፣ ቃለ ምዕዳንንም አስተላልፈዋል፡፡

ከሰዓት በኋላ በኢትዮጵያ የኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት ቀደም ብሎ አስፈቅዶ በያዘው የእራት መርሐ ግብር መሠረት በተዘጋጀውን ስፍራ በመገኘት በድርጅቱ መሪነት ከመላ ሀገራችን ኢየሩሳሌምን ለመሳለም የመጡት ልጆቻቸውን መክረዋል አስተምረዋል፡፡ በዚህ መርሐ ግብር ላይ ወ/ሮ እግዚእ ኃረያ የተባሉ የራሽያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አማኝ በኢየሩሳሌም ለሚገኘው ገዳማችን በ2006 ዓ.ም 30 ሺህ ዶላር፣ በ2008 ዓ.ም 50 ሺህ ዶላር በመለገስ ላደረጉት ክርስቲያናዊ ድጋፍ በገዳሙ ስም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ከፍተኛ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል፡፡

ሰኞ ግንቦት 1 ቀን 2008 ዓ.ም

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ዓመታዊ የእመቤታችን ድንግል ማርያምን በዓል ልደት በደብረ ገነት ኪዳነ ምሕረት ገዳም በመገኘት ከሌሊቱ በ10 ሰዓት ጀምሮ ጸሎተ ኪዳንና ጸሎተ ቅዳሴውን መርተው፤ ዕለቱን አስመልክቶ ትምህርት፣ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ አስተላልፈዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ በዚህ ቀን የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ፓትርያርክ በኢየሩሳሌም ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ጋር በጽ/ቤታቸው በመገኘት ውይይት አድርገዋል፡፡ የቅዱስነታቸው መልእክት በዋናነት ያተኮረው፡- "ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን..." የሚል የምስራች ምስክርነት በማስቀደም የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ የሁላችንም የክርስቲያኖች ጥንታውያን የእምነት ምልክቶቻችን ተጠብቀው እንዲኖሩ በማድረግ በኩል ሰፊ ድርሻ ያላት መሆንዋን ታሪክ ጠቅሰው አስረድተዋል፡፡ አያይዘውም በኢየሩሳሌም ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ መሳካት ላይ የግሪክ ቤተ ክርስቲያን የማይናቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አመላክተው ይህንኑ ያላት መልካም ዕድል በመጠቀም በሁሉም አብያተ ክርስቲናያት ዘንድ ተጠብቆ የቆየውን ሰላማዊ ግኑኝነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል፡፡ የኢትዮጵያ ገዳማት አስመልክተውም በዴር ሱልጣን አካባቢ የሚፈጠሩት ችግሮች በመፍታት ዙርያ ለገዳማውያኖቻችን የምታደርጉትን ቀና ትብብር ከልብ እያመሰገንኩ ለወደፊትም ወቅታዊ ችግሮች በሚነሱበትም ይሁን ዘላቂ መፍትሔ በሚያስፈልግበት ጊዜ ሁሉ የሚቻላችሁን እንደምታደርጉ በመተማመን ነው በማለት ንግግራቸውን አጠቃልለዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ በበኩላቸው የክርስቶስ ትንሣኤን አስመልክተው ሠላምታ ከሰጡ በኋላ እንኳን ወደ ቤትዎ በሰላም መጡ በማለት ንግግራቸውን ጀምረዋል፡፡ በመቀጠልም ኢየሩሳሌም የዓለም የክርስቲያኖች የእምነት ማዕከል መሆንዋን ገልጸው ይህንን መሠረት በማድረግ ሁሉም በአንድ አካባቢ ተሰባስበው ሲኖሩ በፍጹም መከባበርና ፍቅር መሆን እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ ይሁን እንጂ የዴር ሱልጣን አካባቢ ያለው የቆየ ችግር እስካሁን መፈታት አልቻለም፤ በሕግ እና በእልህ ምናልባት ላይፈታ ይችላል፤ በሰላምና በፍቅር እንዲሁም የጋራ መግባባት ካለ ግን የማይፈታ ችግር የለም፤ እኛም አሁን በተለይ በእናንተ እና በግብጻውያን መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ከምንግዜም በላይ ተዘጋጅተናል፤ የእስራኤል መንግስትም ይህንኑ ችግር በአስቸኳይ እንድንፈታ አሳስቦናል፤ ቅዱስነትዎም በገዳምዎ ለተመደቡት አዲስ ሊቀ ጳጳስ ከእኛ ጋራ እንዲተባበሩ ያሳስቡልን በማለት ለዘላቂ ሰላም እንደሚሠሩ በማረጋገጥ ንግራቸውን ፈጽመዋል፡፡      

በመቀጠል ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ወደ ቤተ ልሔም በመሄድ ደብረ ሰላም ኢየሱስ ገዳምን ጎብኝተዋል፡፡ የገዳሙ ነባር ይዞታና አዳዲስ የተሠሩ ሥራዎችን ከጎበኑ በኋላም ይዞታን በመጠበቅ እንደገና እንዲህ ዓይነቱ ተጨማሪ ሥራን መሥራት የሚያስመሰግን ሥራን ያከናወኑ መናንያን በከፍተኛ አባታዊ ምክርና ምስጋና አበረታትተዋል፡፡ 

ቅዱስ ፓትርያርኩ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው በመቀጠል አልዓዛር ወደሚገኘው ምሰካበ ቅዱሳን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም በመሄድ እዚያ በገዳሙ ለረጅም ጊዜ አገልግለው አሁን በገዳሙ በመጦር ላይ የሚገኙ አረጋውያን ጎብኝተው ከክፍላቸው የማይወጡትን በመጀመሪያ በየክፍላቸው እየዞሩ ከጎበኟቸው በኋላ ሌሎች ሁሉንም ተሰባስበው አዳራሽ ላይ አብረው ለግንቦት ልደታ ያዘጋጁትን የገዳም ንፍሮ ከተሳተፉ በኋላ ለሁሉም ገዳማውያንና አረጋውያን ትምህርተ ወንጌል፣ ቃለ ምዕዳንና ቃለ ቡራኬ በመስጠት አበረታትተው ወደ ማረፊያቸው ወደ ደብረ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ገዳም ተመልሰዋል፡፡  

ማክሰኞ ግንቦት 2 ቀን 2008 ዓ.ም

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ እና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ዴር ሱልጣን ገዳም ተመልሰው በመሄድ አጠቃላይ የገዳሙ አሁን ያለበት ሁኔታና ያለው መሠረታዊ ችግሮች በእግራቸው በመዘዋወር ሁሉንም ቦታዎች ይዘታቸውና ያላቸውን ወቅታዊ የእድሳት ችግር አንድ በአንድ በመጎብኘት በሚገባ ተረድተዋል፡፡ በዚሁ ዕለት ከሰዓት በኋላ ቅዱስነታቸው በማረፊያቸው በተዘጋጀው በልዩ የእንግዳ መቀበያ በመሆን ከተለያዩ ክፍለ ዓለማት የመጡ የኢየሩሳሌም ተሳላሚዎች ተቀብለው በማነጋገር ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጥተዋል፡፡

ረቡዕ ግንቦት 3 ቀን 2008 ዓ.ም

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመሆን የገዳሙ መነኮሳትን ሰብስበው የግማሽ ቀን ውይይት አድርገዋል፡፡ የውይይቱ መርሐ ግብር በብፁዕ አቡነ ዕንባቆም የኢሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ ከተገለጸ በኋላ መርሐ ግብሩ በብቅዱስ ፓትርያርኩ መልእክት የተጀመረ ሲሆን ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው ውስጥ የሐዋርያዊ ጉዞው ዋና ዓላማ ገዳማቱን ለመጎብኘት፣ ያለውን ችግር በአካል ተገኝተን ለመረዳት፣ ከማኅበሩ ጋር እንዲህ ተሰባስበን ለመወያየት እንደመሆኑ መጠን ተሰባስቦ መወያየት መፍትሔ ያመጣል፤ ስለሆነም ዛሬ የተሰባሰብንበት ዋና ምክንያት የቤተ ክርስቲያናችን ሚድያ መጀመርን በተመለከተ ይሆናል በማለት ጀምረው የሚድያ አስፈላጊነት እና የሚያስገኘውን ጠቄሜታ አስመልክተው ሰፊ የሆነ መግለጫ ካቀረቡ በኋላ አባቶች ሊቃነ ጳጳሳትም ሐሳብ እንዲሰጡበት ብለው ዕድሉ የሰጧቸው ቢሆንም መጀመሪያ የጋራ የሆነ ሰፊ ግንዛቤ እንዲኖር የሚዲያው ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር ዳንኤል ሠይፈሚካኤል አጠቃላይ መግለጫ እንዲሰጡ ታዘው ሰፊ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡

መምህር ዳንኤል ሠይፈ ሚካኤል በመግለጫቸው ከሁሉ አስቀድሞ የመገናኛ ብዙኅንን አስፈላጊነት በመረዳት በቅዱስ ፓትርያርኩ አሳሳቢነትና መሪነት ቅዱስ ሲኖዶስ ሰፊ ጥናት በማድረግ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የራስዋ የሆነ የመገናኛ ብዙኀን ሥርጭት አገልግሎት እንዲኖራት በ2006 ዓ/ም ርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤ መወሰኑ፤ ከዚያም ጀምሮ ውሳኔውን ወደ ተግባር ለመለወጥ ልዩ ጥረት በማድረግ፣ የራሱ የሆነ ቦርድ እንዲኖረው፣ ከዚያም ድርጅቱን ማዋቀር መቻሉንና፣ የራሱ የሆነ ዓመታዊ በጀት መወሰኑን፣ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የሥራው ሁሉ ዋና አካል የሆነውን የሳተላይት ሥርጭት ድርጅት በመላው ዓለም ሰፊ ጥናትና ዳሰሳ በማድረግ መምረጥ መቻሉን በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

በመቀጠልም የመገናኛ ብዙኀን በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው የሚንቀሳቀሱ፣ ትውልድን በመቅረጽ፣ መረጃን በማሰራጨት፣ መልካም ገጽታን በመገንባት፣ መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ፣ ሃይማኖታዊም ሆነ ማኅበራዊ ጉዳዮችን ከአንዱ የዓለም ጥግ ወደ ሌላው ዳርቻ ያልምንም እንከንና እንቅፋት በጥራትና በብቃት በማሰራጨት ወደር የለሽ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ተቋማት በመሆናቸው፤ ይህንኑ መንገድ ተጠቅሞ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ዓላም፣ ትምህርተ ሃይማኖት፣ ቀኖና፣ ታሪክ፣ መንፈሳዊ ሕይወት፣ ማኅበራዊ አስተዋጽኦ፣ ሥነ ምግባር፣ የቅዱሳን ሕይወትና የሰማዕታት ተጋድሎ፣ የቅዱሳት መጻሕፍት ጥናትና የመሳሰሉትን በየትኛውም ሀገርና ቦታ ለሚኖሩ ለሕፃናት፣ ለወጣቶች፣ ለአዋቂዎች በየትኛው ሰዓት  (24 ሰዓት) አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ በአሁኑ ጊዜ ጥናቱ ተጠናቆ፣ አብረውን የሚሠሩትን ድርጅቶች መርጠን ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችለው ቅድመ ሁኔታ መሟላቱን በሰፊው ዘርዝዋል፡፡     

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የመገናኛ ብዙኀን ሥራ በአንድ ተቋም ብቻ የሚሠራ ሳይሆን ብዙ ትብብርና ትሥሥር የሚያስፈልገው፣ በመላው ዓለም ያለችው የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አካላት በሙሉ የበኩላቸውን ማድረግ እንደሚገባቸው በተለይ በኢየሩሳሌም የሚገኙ የኢትዮጵያ ገዳማት ሊያበረክቱት የሚችሉትን አስተዋጽኦ ገለጸ አድርገዋል፡፡ ከዚህም በመቀጠል፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የየበኩላቸውን አስተያየት የሰጡ ሲሆን የገዳሙ ማኅበረ መነኰሳት አመራሮችና አባላትም በሙሉ በየተራ እየተነሡ ያላቸውን ድጋፍና ትብብር በከፍተኛ ስሜትና ተቆርቋሪነት ገልጸዋል በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ፓርትያርኩ መርሐ ግብሩን በጸሎት ዘግተዋል፡፡

ሐሙስ 04 ቀን 2008 ዓ.ም

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ሐሙስ ግንቦት 4 ቀን 2008 ዓ.ም የአርመን ፓትርያርክ በኢየሩሳሌም እና የፍራንሲስካን የበላይ ኃላፊ በኢየሩሳሌም ጋር ተገናኝተው ተነጋግረዋል፡፡ ቅዱስነታቸው አስቀድመው ከፍራንሲስካን የሃይማኖት ኃላፊ ጋር የተገናኙ ሲሆን ቀደም ሲል በሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት በኢየሩሳሌም የነበረውን መልካም ግኑኝነት እና ትብብር መነሻ በማድረግ ሰፊ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን በኢየሩሳሌም ለሚገኝ ገዳማችን ለሚደረገው ትብብርም በራሴና በገዳሙ ስም በጣም ማመስገን እወዳለሁ በማለት ቀጣይም የተለመደው ትብብር እንዳይላቸው በመጠየቅ አመስግነዋል፡፡ የፍራንሲስካን ኃላፊም በበኩሉ ከኢትዮጵያ ገዳም መነኮሳት እና ምዕመናን ጋር የቆየ መልካም ግንኑኝነት እንዳላቸው ገልጸው ይህንኑ ትብብርም እንዲሁ ተጠብቆ እንደሚቀጥል ለቅዱስ ፓትርያርኩ ቃል ገብተውላቸዋል፡፡

ለአርመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ በኢየሩሳሌምም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ባደረጉት ንግግር የአርመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግኑኝነታቸው ከመጀመሪያው ምእተ ዓመት የሚጀምር መሆኑንና ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌምም በሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ከፍተኛ ትርጉም ያለው ስፍራ መሆኑን ገልጸው በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የሚገኙ የሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት ገዳማውያን የቆየ የትብብር እሴት ለቀጣይ መልካም ግኑኝነት መሠረት የሚጥል ስለሆነ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡      

የአርመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ በበኩላቸው ከዚህ በፊት በሊቀ ጵጵስና ለረጅም ጊዜ ያገለግሉበት ገዳም ተመልሰው በመምጣታቸው በጣም መደሰታቸውን ገልጸው ይኸው የቆየ ክርስቲያናዊ ግኑኝነታችንን አጠናክረን ለሁሉም ምሳሌ መሆን ይኖርብናል ብለው የቅዱስ አባታችን ምኞትና ፍላጎት በመጋራት ንግግራቸውን ከፈጸሙ በኋላ የስጦታ ልውውጥ ተደርጎ መርሐ ግብሩ ተጠናቋል፡፡

ዓርብ ግንቦት 5 ቀን 2008 ዓ.ም

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመሆን ኢያሪኮ ድረስ በመሄድ ቅድስት ሥላሴ ገዳምን ጎብኝተው፣ በገዳሙ ላይ ጸሎተ ኪዳን አድርሰው፣ ገዳሙን በማገልገል ላይ ያሉ መናንያንም አበረታትተው ተመልሰዋል፡፡ በዚሁ ዕለት በተጨማሪም ከሰዓት በኋላ በእስራኤል የሚገኙ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ በልዩ የእንግዳ መቀበያ ሳሎን ተቀብለው በማነጋገር ቡራኬና ቃለ ምዕዳን ሰጥተዋቸዋል፡፡

 •  ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ከእስራኤል መንግሥት ባለሥልጣናትና የሥራ ኃላፊዎች ጋር ያደረጉት ውይይት

 

ቅዳሜ ግንቦት 6 ቀን 2008 ዓ/ም ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር ያደረጉት ውይይት

በእስራኤል የቱሪዝም ሚንስትር በቅዱሳት መካናት የሚደረጉ ጉብኝቶችንና መንፈሳዊ ጎዞዎችን ማስተዋወቅ፣ ማበረታታትና የጎብኝዎችን ምቾት መጠበቅ የመሳሰሉትን ሥራዎች የሚያከናውን መሥሪያ ቤት ሲሆን በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በርካታ ቱሪስት ከሚጎበኛቸው ቅዱሳት መካናት አንዱ የሆነው በዴር ሱልጣን የኢትዮጵያ ገዳም ከዋና ዋናዎቹ የቱሪስቶችና የመንፈሳዊ ተጓጓች መዳረሻዎች አንዱ ነው ነው፡፡ ቅዱስነታቸው በዴር ሱልጣን ለዘመናት የቆየውን ችግር ለመፍታት ዓላማ ባደረገው ጉዞአቸው ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ለሚደረጉት ውይይቶች አስቀድሞ መርሐ ግብር የተያዘለት የቱሪም ሚንስትርን ግንቦት 7 ቀን 2008 ዓ/ም አግኝተው ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡ በዚሁ ውይይታቸው ከቱሪዝም ዘርፍ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቅድስተ ሀገር የሚገኙ ጥንታውያን ገዳማት መብት ስለሚከበርበት ሁኔታ አሳስበዋል፤ ከቱሪዝም ሚንስትሩ ጋር በተደረገው ውይይት አብረው የተገኙት የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን መሠረተ ልማት ዳይሬክተር፣ የቱሪዝም ቅስቀሳና ማስታወቂያ ዳይሬክተር፣ ምክትል ሚንስትር፣ በገዳማቱ አካባቢ ስላለው መሠረታዊ ችግር በጥልቀት አስረድተዋል፡፡ በውይይቱ ወቅት በእስራኤል ኢትዮጵያ ኤምባሲ አማባሳደር ሕላዌ ዮሴፍም ተገኝተዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት የቱሪዝም ሚንስቴሩ ቅዱስነታቸውን እንኳን ደህና መጡ በማለት በመምጣቸው የተሰማቸውን ደስታ ከገለጹ በኋላ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ከቀድሞው በተለየ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ቅድስት ሀገር የሚያደርጉት መንፈሳዊ ጉዞ የሚያስደስት ቢሆንም በቅርቡ ባሉን መረጃዎች ደግሞ የመቀነስ ሁኔታ እንዳለው፣ በኢትየጵያ መንግሥት በኩል ለቱሪዘም ከተሰጠው ልዩ ትኩረት አንፃር በቅርቡ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት የባህልና ቱሪዝም ሚንስትር ሜኒስቴር ኢ/ር አይሻ ሙሐመድ በኢየሩሳሌም እስራኤል ጉብኝት ማድረጋቸውን የጠቀሱ ሲሆን የእሥራኤል መንግስትም ለዚሁ ዘርፍ ልዩ ትኩረት በማድረግ ጉብኝዎች በነፃነት በሁሉም የቱሪስ መዳረሻዎች ተገቢውን ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ሥርዓት ፈጽመው ጉብኝታቸውን እንዲፈጽሙ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን በማስታወቅ በዚህ ረገድ ለሚፈጠሩ ችግሮች ሁሉ የሚንስቴር መሥራያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግና ኢትዮጵያውያን እስራኤልን እንዲጎበኝ እንደሚያበረታቱ አስታውቀዋል፡፡

የሚንስትሩን የእንኳን መጡና የመግቢያ ንግግር አስከትለው ቅዱስነታቸው ባደረጉት ንግግር በመጀመሪያ የሚንስትር መሥሪያ ቤቱ ለዚህ ስብሰባ ያሳየውን ፈቃደኛነት፣ ባለሥልጣናቱም ጊዜያቸውን ሰጥተው ለውይይቱ ፈቃደኛ በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፤ ከሁሉ አስቀድሞ መናገር የምፈልገው የኢትዮጵያና የእሥራኤል ግንኙነት ከንግሥተ ሳባ የኢሩሳሌም ጉብኝት ጀምሮ የቆየና ያለማቋረጥ ለረጅም ዘመናት የዘለቀ የሦስት ሽህ ዓመት ታሪክና ትውፊት መሆኑን፣ በክርስትና ዘመንም ከልደተ ክርስቶስ ጀምሮ ምእመናን ይህንኑ ነባር ትውፊትና ክስቲያናዊ ሥርዓት በመከተል ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌምን የመጎብኘት ልምድ እንዳደበሩ፣ በተለይ በትንሣኤ ሰሞን፣ ልዩ የሆነ የመንፈሳዊ ጉዞ ወደ ኢየሩሳሌም ማድረግ ነባር ባህል መሆኑን ገልጸው፣ ይሁን እንጅ በአሁኑ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም የሚመጡ ምእመናን ቁጥር እያደገ ቢሆንም በቀድሞ ጊዜ በትንሣኤ ብቻ የነበረው በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከመላው ዓለም በመነሣት ዓመቱን ሙሉ ወደ ቅድስት ሀገር ጉብኝት የሚደረጉ ሲሆን ሁሉም ተጓዦች የሚያነሡት ጥያቄ በዴር ሱልጣን ያለውን ችግር በመሆኑ ለዚህ ጉዳይ የእስራኤል መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መፍትሔ ሊሰጠን ይገባል በማለት አሳስበዋል፡፡

ቅዱስነታቸው በአጽንዖት እንዳሳሰቡት በዴር ሱልጣን ኢትዮጵያውያን የሚኖሩበት ጥንታዊ ገዳማቸው እጅግ የተጎሳቆለ የተረሣና ትኩረት የተነፈገው ከመሆን ባሻገር "በእስራኤል እንደዚህ ዓይነት ቦታ አለ ወይ?" የሚያስብል ነው፤ ብለዋል፡፡ የቦታውን አስከፊ ጉስቁልና በእውነቱ መንግሥትንም የሚያስነቅፍ፣ በየትኛውም የሠለጠነ የዓለም ክፍል ፈጽሞ በማይገኝ ሲሆን ለዚህ መሠረት የሆነው በኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ወንዶሞቻችን መሠረት የለሽ ክስና ያላተቋረጠ በደል መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ፓትርያርኩ እንዳሉት ይህንን ቦታ ኢትዮጵያውያን ራሳቸው ለማሳደስ ፍላጎቱና አቅሙ ቢኖራቸውም ካሳደሳችሁት ሙሉ ባለቤት ትሆናላቸሁ በማለት በሃይማኖት የሚመስሉን የራሳችን ኦርቶዶክሳውያን ወንድሞቻችን ይከሱናል፤ እነሱ እንዳያሳድሱት ደግሞ ቦታው የእነሱ አይደለም፤ ለዚህ መፍትሔው ራሱ የእስራኤል መንግሥት ራሱ እንዲያሳድሰው ማድረግ ነው በማለት ለችግሩ መፍትሔ የሚሉትንም ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

በመቀጠልም እንደ እሥራኤል ሁሉ ኢትዮጵያም እንደ ርዕሰ አድባራት አክሱም ጽዮን፣ የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ ጎንደር የነገሥታት ቤተ መንግሥታትና አብያተ ክርስቲያናት፣ የጣና ሐይቅ ገዳማት፣ ከፍተኛና ዝቅተኛ ቦታዎች፣ ለጎብኝዎች ማራኪ የሆኑ በርካታ ጥንታውያን የቅድመ ክርስትናና የክርስትና ዘመን ታሪካዊ ቦታዎች፣ ቅርሶችና የተፈጥሮ ሀብቶች ባለቤት ስለሆነች እስራኤላውያን ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ጥሪ እንደሚያስተላፉ ለዚህም የሚንስትር መሥሪያ ቤቱ የበኩሉን ቅስቀሳ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

በውይይቱ የተገኙት አምባሳደር ሕላዊ ቅዱስ ፓትርያርኩ ላቀረቡት ጥያቄ አጽንዖት በመስጠት ችግሩን የሚፈታ ጠንካራ ዕቅድ እንደሚያስፈልግ፣ በቦታው መሠረታዊ የሆኑ የመብራት፣ የውሃ፣ የንፅሕና መጠበቂያ፣ ለኑሮ አመች የሆኑ አገልግሎቶች፣ መሠረተ ልማቶች ማሟላት ተገቢ መሆኑን፤ የቦታው መጎሳቆል በርግጥም እጅግ አስከፊ መሆኑን ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ይሁን እንጅ የኢትዮጵያውያን ፍላጎት የእስራኤል መንግሥትን የስታተስኮ መመሪያ ለማስቀየር ወይም የተለየ በጎ አድርጎት እንዲደረግላቸው ሳይሆን ገዳሙ አሁን ባላበት ሁኔታ ቢያንስ ተገቢው ጥገናና መሠረታዊ ሁኑታዎች ተሟልተውለት በአደራ የጠበቁት ጥንታዊ ቦታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ የተነሣው ሁለተኛ ችግር ለቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የመግቢያና ለአገልግሎት የመኖሪያ ቪዛ ችግር መሆኑ በተለይ በገዳም ለሚያገለግሉት መነኰሳት ከፍተኛ ተጽዕኖ መፍጠሩን ቅዱስነታቸው አሳስበዋል፡፡ ከዚሁ በማያያዝ የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢየሩሳሌምን በጣም እንደሚወድ ወደ ኢየሩሳሌም ለመምጣት የሚያበረታታውና የሚቀሰቅሰው ሳይኖር ለመምጣት ከፍተኛ ፍላጉ,ጎት እንዳለው በእስራአል መንግሥት በኩል ደግሞ ሕዝቡ መጥቶ የሚጎበኛቸውን ጥንታውያን ይዞታዎቹን ደኅንነት ጊዜ ሳይወስድና ችግሩ ወደከፋ ደረጃ ሳይደርስ ማስጠበቅ እንደሚገባ በአጽንዖት አሳስበዋል፡፡  

የቱሪዝም ሚንስቴሩ ምንም እንኳ አንዳንዶቹ ጉዳዮች በቀጥታ የሳቸውን የሚንስትር መሥሪያ ቤተ በቀጥታ የሚመለቱ ባይሆንም እንደ መንግሥት የማንንም ችግር የመፍታት ኃላፊነት ያለብን መሆኑ የተነሣውን ችግር ለሚመለከተው የመንግሥት መሥሪያ ቤተ በማስረዳት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡ ከዚሁ አያይዘው እንደገለጹት መንግሥት የሁሉን ሰው ችግር በፍትሐዊና አግባብ ባለው መንገድ የመፍታት ኃላፊነት ስላለበት የአንድ ሰው እንኳ አቤቱታም ቢሆን ብታሳውቁን ለመፍታት ዝግጁ መሆናችንን እንገልጻለን ብለዋል፡፡

ሰኞ ግንቦት 8 ቀን 2008 ዓ/ም ቅዱስነታቸው ከእስራኤል ፕሬዝዳንትና ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ያደረጉት ውይይት

ቅዱስታቸው ከእስራኤል ፕሬዝዳንት ሚ/ር ሩቨን ሩቭሊን ጋር በነበራቸው ውይይት በኢትዮጵያና በእሥራኤል መካከል ከንግሥተ ሳባና ንጉሥ ሰሎሞን ጀምሮ ከሦስት ሽህ ዓመታት በላይ የቆየ በዓለም ታሪክ ረጅሙ የእምነት፣ የባህል፣ የማኅበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደነበር፣ ይህንኑ መሠረት በማድረግ በርካታ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ወደ ኢየሩሳሌም በመጓዝ የማያቆርጥና ጠንካራ ግንኙነትን እንደመሠረቱ ለክቡር ፕሬዝዳንቱ አሳውቀዋል፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዘው ቅዱስነታቸው እንደገለጹት ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ በየዓመቱ ወደ ኢየሩሳሌም መንፈሳዊ ጉዞ እንደሚያደርጉ ከዚህም የተነሣ በርካት ንብረቶችን፣ ቤተ መቅደሶችንና ገዳማትን በእስራኤል ምድር በልዩ ልዩ ጥንታውያን ቦታዎች ለመመሥረት መቻላቸው፣ ይሁን እንጅ በአንዳንድ እንደ ዴር ሱልጣን ባሉ እጅግ ጥንታውያን ይዞታቸው ላይ እየደረሰባቸው ያለውን የመብት ጥሰትና የትኩረት ማነስ እጅግ እያሳዘናቸው እና ስሜታቸውን እየጎዳ ከመገኙቱ ባሻገር የኢትዮጵያን ሕዝብና ምእመናንን እያሳሰበ መሆኑን አጥብቀው አሳስበዋል፡፡

በዴር ሱልጣን ኢትዮጵያውያን ሁለት ሽህ ዘመን ያስቆጠር ታሪክ ያላቸው ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የቦታው ከሌሎች ቦታዎች ተለይቶ አለመታደስና እጅግ አሳዛኝ በሆነ ጉስቁልና ላይ መሆኑ ከግብጽ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን መሠረት የሌለው የይዞታ ጥያቄ ምክንያት በተፈጠረው አለመግባባት ችግሩ ሊባባስ በመቻሉ ላይ ውይይቱ ያተረኮ ሲሆን ቅዱስነታቸው በዚህ አለመግባባት የእስራኤል መንግሥት አፋጣኝ መፍትሔ ካልሰጥ ያልተጠበቀ ችግር ሊያስከትል ከመቻሉ በላይ የእስራኤልን መንግሥት ሊያስነቅፍ እንደሚችል አጥብቀው አሳስበዋል፡፡

ክቡር ፕሬዝዳንት ሩቨን ሩቭሊን በበኩላቸው ቅዱስነታቸውን እንኳን ደህና መጡ በማለት ከተቀበሉ በኋላ በርግጥም በታሪክና በቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚታወቀው በኢትዮጵያና በእስራኤል መካከል እጅግ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ወዳጅነት መኖሩ ይህንንም ጠብቆ ማቆየት አስፈላጊ መሆኑን፣ ከዚህ በተጨማሪ በዴር ሱልጣን ያለውን ችግር እንደሚያውቁት ቅዱስነታቸው ችግሩን በቀጥታ በማንሣታቸው መደሰታቸውን፣ በበኩላቸው በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለው ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የእስራኤል መንግሥት ፍላጎት መሆኑ፣ ከዚህ በተጨማሪ የእስራኤል መንግሥት አቋም በሃይማኖትና በፈጣሪ ስም የሚደረግን ማናቸውን ዓይነት ጭቆናና ማደናገር ፈጽሞ እንደማይቀበል፣ ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት በፍትሕና በእኩልነት የእምነት ሥርዓታቸውን በተፈቀደላቸውና ባላቸው ቦታ መፈጸም እንዳለባቸውና መብታቸው መሆኑን እንሚያምን፣ ለዚህም ቆርጦ እንደሚሠራ ብፁዕ ቅዱስ አቡነ ማትያስ ላነሡት ጥያቄም በፍትሕና በሰላማዊ መንገድ አፋጣኝ መልስ እንደሚሰጥበት አረጋግጠዋል፡፡ 

የኢየሩሳሌም ከንቲባ ጽ/ቤት ተወካዮችን፣

በቅዱስ ፓትርያርኩ የከንቲባ ጽ/ቤት ውይይት ላይ የተገኙት ምክትል ከንቲባው፣ የከተማ ዕቅድ ጉዳዮ ተጠሪ፣ የታሪካዊ ሕንፃዎች ጥገናና እንክብካቤ ዳይሬክተር አብረው ተገኝተዋል፡፡ በዚሁ ውይይት በኢየሩሳሌ ከተማ በርካታ ታሪካዎ ቦታዎች የሚመለከተው የከንቲባ ጽ/ቤት ወይም የማዘጋጃ ቤቱን ሲሆን ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጥገናና እንክብካቤ ስለሚያስፈልጋቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች ሰፊ ዳሰሳ ያደረገ ውይይት ተደርጓል፤ ከዚሁ ጋር በማያያዝ ሕንፃዎችን በማደስ ሂደት መፈጸም ስላለባቸው ቅደመ ሁኔታዎች ውይይት ተገርጓል፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በእስራኤል ከአንድ ሽ ዓመት በላይ ያስቆጠሩ ይዞታዎች እንዳሏቸው፣ እነዚህን ለማደስና፣ የመኖሪያ ሁኔታቸውን ለማሻሻል ፍላጎት ቢኖርም በርካታ ውስብስብ ችግሮች መኖራቸውን በመግለጽ በዴር ሱልጣን የኢትዮጵያ ገዳም ያለውን ከፍተኛ ችግር፣ በዮርዳኖስ ያለውን የቅድስት ሥላሴ ቤተ መቅደስ ተደራሽነት፣ በሌሎችም ቦታዎች ያሉትን ችግሮች አስረድተዋል፡፡ 

ምክትል ከንቲባውና የጥንታውያን ሕንፃዎች ጥገና ባለሙያዎቹም በጉዳዩ ላይ ያለውን ትኩረት በሰፊው ያብራሩ ሲሆን የዴር ሱልጣን ሁኔታ በጥንታዊው የኢየሩሳሌም ከተማ ክልል ውስጥ በመሆኑና ካለው አሳሳቢነት በማእከላዊ የእስራኤል መንግሥት እንክብካቤ ሥር ከመሆኑ አንፃር ከከተማው ማዘጋጃ ቤት አቅም በላይ ቢሆንም ችግሩን በአግባቡ በማስረዳትና ለሚመለከተው አካል በማሳሰብ ረገድ የበኩላቸውን እንደሚወጡ፤ ሲናገሩ ከዚህ በተጨማሪ እስራኤላውያን በግብጽ ሀገር በፈርዖን ቀንበር ሲገዙ ኑረው እግዚአብሔር ለአብርሃም በተስፋ ወደ ሰጠው ምድረ ርስት በኢያሱ መሪነት ዮርዳኖስን ተሻግረው ሲገቡ የተሻገሩበት ቦታ ነው ተብሎ የሚታመነው በዮርዳኖስ አካባቢ ያለውን ታሪካዊ መካን ለማስተካከል የሚደረገውን ጥረትና እንቅስቃሴ በተመለከተ በዓረብ መንግሥታትና በእስራኤል መንግሥት መካከል እንደአውሮፓውየን ዘመን አቆጣጠር ከጁን አምስት እስከ ዓሥር ድረስ በተደረገው የስድስቱ ቀን ጦርነት ምክንያት በዮርዳኖስ ወንዝ አቅራቢያ የተቀበሩት ቦምቦች ለደኅንነት ሥጋት በመሆናቸው ለብዙ አሥርት ዓመታት በአካባቢው ያሉ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት አቋርጠው ከዘመን ብዛት የተነሣ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑና ከእነዚህ ጥንታውያን አብያ ክርስቲያናት ውስጥም አንዱ በእቴጌ መነን የተሠራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅድስት ሀገር ገዳማት አንዱ ነው፡፡ ይሁን እንጅ በቅርቡ የእስራኤል መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የተቀበሩትን ቦምቦች ሳይፈነዱና በፍንዳታው በሚፈጠረው ያልተጠበቀ ችግር በአብያተ ክርስቲያናቱ ላይ ጉዳት ሳያደርሱ የማጽዳት መርሐ ግብር እንደነደፈና ወደ ተግባር እንደሚገባ አረጋግጠዋል፡፡    

የእስራኤል መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሚኒስቴርንና የሚንስትር መሥሪያ ቤቱ የሃይማኖት ጉዳዮች ኃላፊዎች ጋር ያደረጉት ውይይት

በእስራኤል መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚንስትር መሥሪያ ቤት ሥር የሃይማኖት ተቋማት በሚመለከት የሚፈጸሙ ተግባራትን የሚያከናውን የሃይማኖት ጉዳዮች ዳይሬክተር ቢሮ ሲኖር በቅዱስነታቸው ጉብኝት ወቅት ትኩረት ተሰጥቶና ከፕሮቶኮል ዋና ኃላፊው መ/ር ሙሴ ኃይሉ ጋር በሚደረጉ መርሐ ግብር ዝግቶች መሠረት ውይይት ካደረጉት ባለ ሥልጣናት ውስጥ የዚሁ ክፍል ኃላፊ ጋር የተደረው ውይይት አንዱ ነው፡፡ ኃላፊዋ ደብረ ገነት ኪዳነ ምሕረት ገዳም ተገኝተው ውይይቱን ያካሔዱ ሲሆን በውይይቱ ኃላፊዋ በዴር ሱልጣን ገዳም በሁለቱ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት (በኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን) መካከል ያለው ልዩነት በአስቸኳይ መፈታት ከተቻለ የዴር ሱልጣን ዕድሳት በአፋጣኝ በእስራኤል መንግሥት ሊፈጸም እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጅ ችግሩን ለመፍታት በሁለቱም ወገናች ዝግጅት ሊኖር እንደሚገባ የራሳቸውን አመለካከት አቅርበዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ ኃላፊዋ ለውይይቱ ፈቃደኛ ሁነው ጽ/ቤት ድረስ በመምጣቸው ደስተኛ መሆናቸውን ይሁን እንጅ የዴር ሱልጣን ጉዳይ የምንለሳለስበት እና የምንደራደርበት ጉዳይ አለመሆኑን በሁሉም ዘንድ ሊታወቅ እንደሚገባው፣ ሌሎቹ የራቸው ያልሆነውን ለመውሰድ፣ መብታቸው ባልሆነ ቦታ መብታችን ይከበር በማለት ሲደራደሩ እኛ የራችንን ይዞታና መብት አሳልፈን ለማንም አንደማንሰጥ ልታውቁልን ይገባል፤ እኛ ከእስራኤል መንግሥት የምንጠብቀው ትክክለኛ ፍርድን ነው፡፡ ፍትሕን መስጠት ከተቻለ በታሪክ ተወቃሽና በትውልድ ዘንድ ትዝብት ውስጥ ከመግባት እንድንድ ያደርገናል፡፡ 

ኃላፊዋ በታሪክ ብዙ ጉዳዮች ያሉ ቢሆንም ታሪካዊ የሆኑትን ነገሮች ለጊዜው አቆይተን አሁን ባለው ሁኔታ አካባቢው ለኑሮ ምቹ እንዲሆን፣ መሠረታዊ ፍላጎቶች እንዲሟሉለት ሕንፃው ጥገና እንዲደረግለት በእስራኤል መንግሥት በኩል ከፍተኛ ፍላጎት ያለ መሆኑን፣ ይህ ሁኔታ ሳይሟላ ቀርቶ ግን በሰው ላይ የሚደርሰው ችግር የበለጠ የሚያሳስብ እንደሆነ በመግለጽ በበኩላቸው የኢትዮጵያና የግብጽ በእስራኤል አምባሳደሮች ባሉበት የሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት በኢየሩሳሌም ያሉ ኃላፊዎች በተገኙበት ውይይት ቢደረግ የሚል ሐሳብ እንዳላቸው ለቅዱስነታቸው አቅርበዋል፡፡

በዚህም የውጭ ጉዳዩ መሥሪያ ቤቱ ችግሩን ለመፍታት ያቀረበው በእውነተኛ ታሪካዊና ፍትሐዊ መሠረት ላይ የተመረኮዘ፣ አድሎአዊ ያላሆነ፣ የኢትዮጵያን ጥንታዊ ይዞታ የሚያስከብር፣ የኢትዮጵያውያንን ደኅንነትና መብት ቅንጣት ታክል የማይነካ፣ አባቶቻችን ያወረሱንን ብዙ ሀብት ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት እኛ ሳናውቅ በግፍና በግድ የተወሰደ ቢሆንም የተረከብነው እና በይዞታችን ሥር ያለውን ግን ለማንም አሳልፈን እንደማንሰጥ ከግምት ውስጥ ያስገባ ከሆነ፣ ሌላው የተሰጠውን መብትና ነፃነት ለእኛ የማይነፍግ ከሆነ በእኛ በኩል ለውይይት ዝግጁ መሆናችንንና ይህም በይፋ ሊገለጽንልን እንደሚገባ አሳውቀዋል፡፡

ቅዱስነታቸው ከሃይማኖት ሚንስትር ሚኒስቴር ዳቪክ አዞላይ ጋር ያደረጉት ውይይት 

በቅዱስነታቸው ጉብኝት መርሐ ግብር ተይዞላቸው ውይይት ካደረጉት የመንግሥት ባለሥልጣናት አንዱ የእስራኤል የሃይማኖት ሚንስትር ነው፡፡ የሃይማኖት ሚንስትሩ ዳቪክ  ኦዝላይ ጋር ባደረጉት ውይይትም ሚኒስትሩን በሚመለከተው በሃይማኖት ተቋማት መካከል የሚነሡ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት እንዲቀጥል፣ በዴር ሱልጣን የኢትዮጵያ ገዳም ለዘመናት የቆየው ችግር በበየጊዜው በማባበልና በሽንገላ የሚታለፍ አለመሆኑን፤ ችግሩ ሳይፈታ ቀርቶ ለሚደርሰው መጠነ ሰፊ ጉዳት ከአሁኑ መፍትሔ ማፈላለጉ ተገቢ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡

ቅዱስነታቸው ጉዳዩን ከማሳሰብና መፍትሔ እንዲሰጠው ከማድረግ ባሻገር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ከመሆናቸው በፊት በኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ ሁነው ሁለት ጊዜ እንደሠሩ በእነዚህ ዐሥር ዓመታት በሚደርሱ ጊዜያት ሁሉ "ችግሩን እንፈታዋለን" ከሚል የተስፋ ቃል የዘለለ ምንም የተሠራ ሁኔታ እንደሌለ፤ አንዳንድ ጊዜም ከእኛ ይልቅ መብትና ታሪካዊ ማስረጃ ለሌላቸው ችግሩን በዋናነት እየፈጠሩብን ላሉት ለሌሎች መሠረት የለሽ መብት ለሚጠይቁ ሰዎች የማድላት አዝማሚያም እያየን እንደሆነ ይህንን ጉዳይ እስከመጨረሻው እንደሚከራከሩበትና መብታቸውን አሳልፈው ለማንም እንደማይሰጡ፣ በጽኑ አቋም አስታውቀዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ የኢየሩሳሌምና የዴር ሱልጣን ጉዳይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ወይም የኢትዮጵያውያን ብቻ ጉዳይ ሳይሆን የመላው አፍሪካውያን ጉዳይ መሆኑን በገለጽበት ወቅት እንዳስረዱት፣ አባቶቻቸን ከምሥራቅ አፍሪካ በረሀና ባህር አቋርጠው ከፊሎቹ በረሀብ፣ ከፊሎቹ በአውሬ ሕይወታቸውን አጥተው የተረፉት ከዚህ ሀገር ደርሰው ቅዱሳት መካናትን ተሳልመው፣ ለኢየሩሳሌምና በዙሪያው ላለው ቅድስና ባላቸው ልዩ ፍቅር ለትውልድ የቆየ መታሰቢያ ቤትና ቦታ ገዝተው ያቆዩት ቦታ እንኳንስ አሁን በሰለጠነው ዓለም ማንም በሚረዳው ሁኔታ ይቅርና በኢየሩሳሌም ማእከላቸው አድርገው መካከለኛ ምስራቅን ይገዙ በነበሩ ገዥዎች ሳይቀር የተመሰከረ ስለሆነ ዛሬ በእኛ ትውልድ የኢየሩሳሌም ይዞታ አናስነጥቅም፣ ይዞታችንን እናስከብራለን፣ እኛ አሁን የምንጠይቀው አቢይ ጉዳይ በይዞታችን ላይ ማንም ማዘዝ የለበትምና ይዞታችን ለነዋሪዎቹ መናንያን የድኅንነት ሥጋት ሳይሆን፣ ሳይፈርስና ጉዳት ሳይደርስ በፊት ይታደስልን ወይም እንድናድስ ፈቃድ እንዲሰጠን ጥያቄአችንን በጽኑ አቋም እናቀርባለን በማለት ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡

ከይዞታው ጥያቄ በተጨማሪ የሃይማኖት ጉዳይ ሚንስትሩን የሚመለከተው ሌላው ማሳሰቢያ የእስራኤል መንግሥት በሀገሩ ለሚኖሩ የአብያተ ክርስቲያናት አገልጋዮች ያልተከለከለንና ምንም ዓይነት ተጨባጭ መረጃ ወይም ምክንያት ሳይኖር ኢትዮጵያውን አገልጋዮች ላይ እየተደረገ ያለው ተጽዕኖ የሚመለከት ነው፡፡ በዚህም ሚንስትሩ ጉዳዩ በአስቸኳይ እርማት እንደሚደረግበትና መፍትሔ እንደሚሰጠው ቃል ገብተዋል፡፡ ሚኒስትሩ በማስከተልም የሃይማኖት መሪዎች የሆኑ አባቶችን የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በሀገሮችና በሕዝቦች መካከል የቆየ መልካም ግንኙነቶችን የሚያጠናክሩ አዳዲስ መልካም ግንኙነቶች ለመመሥረት ምክንያት የሚሆኑ ሊሆኑ ይገባልና የቅዱስነትዎ እስራኤል ድረስ መጥተው የቤተ ክርስቲያንዎን ጉዳይ ለማስፈጸም ከሚያደርጉት ጥረት በተጨማሪ ወደ ሀገርዎ ሲመለሱም የእስራኤል አምባሳደር እንዲሆኑ እንፈልጋለን በማለት ያለቸውን መልካም ፍላገት ገልጸዋል፡፡ ቅዱስነታቸውም ሚንስቴሩ "የእስራኤል አምባሳደር ይሁኑልን" ካሉት ሐሳብ ጋር በተያያዘ እኔን በኢትዮጵያ ላለው መልክም ግንኙነት አምባሳደር እንደሆን ስትጠይቁኝ እኔ ደግሞ እርስዎን በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር እንዲሆኑልን እጠይቃለሁ በማለት በጎ ምላሽን ሰጥተዋል፡፡

በቀጣይም በዚሁ የሚንስትር መሥሪያ ቤት ሥር የሃይማኖት አገልግሎት የሚሰጡ አባቶችን የመኖሪያ ፈቃድ አሰጣጥ ዙሪያ ያሉ የመብት ማስከበርና ዋስትና ወደፊት ለሚመጡ አባቶችም ሊደረግ የሚገባውን የመግቢያና የአገልግሎት ፈቃድ አሰጣጥ በተመለከተ ወሳኝ የሆነ ውይይት የተደረገ ሲሆን ፈቃድ ሰጩ አካል ያለምንም ምክንያትና ተጨባጭ ማስረጃ በአገልጋይ መነኰሳት የቆይታ ፈቃድ ዙሪያ ጫና እንዳይፈጥር የሚያሳስብ መልእክቶችን ቅዱስነታቸው አስተላልፈዋል፡፡ የቢሮው ኃላፊዎችም በጉዳዩ ያላቸውን ስምምነትና ባለፉት ጥቂት ጊዜያት ለተፈጠሩት ችግችም ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡   

በመጨረሻም ቅዱስነታቸው በእሥራኤል ያደረጉት ሐዋርያዊ የሥራ ጉብኝት አጠናቀው ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ በእስራኤል ቴል አቪቭ ቤን ጎንዩን አውሮፕላን ማረፊያ በእስራኤል ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም፣ በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ አምባሳደር ሕላዌ ዮሴፍ፣ የኢየሩሳሌም ገዳማት መጋቢ ፍሥሓ ጽዮንና የገዳማቱ መነኰሳትና ምእመናን አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል፡፡

በአሸኛኘቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ መንግሥት አምባሳደር ሕላዌ በሰጡን ቃለ ምልልስ ቅዱስ ፓትርያርኩ በእስራኤል ያደረጉት ሐዋርያዊ የሥራ ጉብኝት በኢትዮጵያና በእስራኤል ሕዝቦችና መንግሥታት መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ፣ ታሪካዊ ግንኙነት የሚያጠናክር፣ በኢየሩሳሌም የሚገኙ የኢትዮጵያ ይዞታዎች አካባቢ ያሉ ችግሮችን ከፍተኛ ትኩረት እንዲያገኙ የሚያደርግና በእስራኤል ልዩ ከተሞች ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መንፈሳዊ ጥንካሬን በመስጠት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ኤምባሲም በዴር ሱልጣን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች በማስከበርና ችግሮችን ከእስራኤል መንግሥት ጋር በመወያየት ጠንክሮ እንደሚሠራ፣ እስከ አሁንም በተለይ ችግሩ ልዩ ትኩረት እንዲያገኝ ማስተዋወቁ ትልቁን ቦታ ስለሚይዝ ሁኔታውን በማስተዋወቅ ሥራ እየሠራ መሆኑን፣ ከኢትዮጵያ ለጉብኝትም ሆነ ለከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ወደ እስራኤል የሚመጡ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ወደ ኢየሩሳሌም ዴር ሱልጣን ይዞታ በመምጣት ቦታዎቹን እንዲጎበኙ ኢትዮጵያውያን መነኰሳት አባቶች በእስራኤል ሀገር ያቆዩልንን ሀብት አንዲያውቁ በማድረግ ከፍተኛ ኃላፊነትን እየተወጣ ከመሆኑ ባሻገር የዴር ሱልጣን ጉዳይ የኢምባሲው ዓመታዊ ዕቅዶች ውስጥ በየዓመቱ ሳይካተት የተረሳበት ጊዜ እንዳልነበረ አስታውቀዋል፡፡ 

ቅዱስነታቸው ግንቦት 9 ቀን 2008 ዓ/ም አዲስ አበባ ሲገቡ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያው ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን ቅዱስ ፓትርያርኩ ወደ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ሲደርሱም የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ኃላፊዎችና የድርጅቶች ሥራ አስኪያጆች እንዲሁም መላ ሠራተኞች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ኃላፊዎችና ሠራተኞ ልዩ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

 

                          ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የፎንት ልክ መቀየሪያ