Get Adobe Flash player

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣...

35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

በመምህር ዕንቈባሕርይ ተከስተ ዘመናትን በዘመናት የሚተካ እግዚአብሔር አምላክ 2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስን አሳልፎ ለ2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ አደርሶናል፡...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

በመምህር ሙሴ ኃይሉ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ...

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ ...

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

በገዳሙ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መርቀዋል፡፡ በመምህር ሙሴ ኃይሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳ...

 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

  Thursday, 27 October 2016 06:16
 • 35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ተጠቃቀ፡፡

  Tuesday, 25 October 2016 06:40
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሃገሪቱ ጸሎት እንዲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መመሪያ አስተላለፉ፤

  Thursday, 15 September 2016 11:54
 • ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

  Thursday, 15 September 2016 11:50
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጐበኙ፡፡

  Wednesday, 07 September 2016 09:51

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም.

በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 በተደነገገው መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የመክፈቻው ሥርዓተ ጸሎት ከተፈጸመበት ከጥቅምት 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ የተለመደውን ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባን በማካሔድ፣

 • ለቤተ ክርስቲያናችንና ለኅብረሰተባችን የሚጠቅመውን፣
 • ለሀገርና ለዓለም ሰላም የሚበጀውን አጀንዳ በማመቻቸት በስፋትና በጥልቀት ተወያይቶ የሚከተለውን ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ወቅታዊውን የሀገራችንን የሰላም ሁኔታ አስመልክቶ
"ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር"
"ኢትዮጵያ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያውያት እጆቻቸቸውን ወደ እግዚአብሐር ይዘረጋሉ" ይላል ነቢየ እግዚብሔር ዳዊት (መዝ. 67፣31)
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ክፍለ ዓለም፣ በአፍሪካ ቀንድ በሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ በዓባይ ሸለቆ ዙሪያ በቀይ-ባሕር አካባቢ የምትገኝ ሀገር ናት፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ የነጻነት፣ የአንድነት ዕድሜ የተቈጠረላት በዚህም ረዥም የነጻነትና የአንድነት ዕድሜዋ ብዙ አገልግሎት ያበረከተች ሰፊ ታሪክ ያስመዘገበች ሉዓላዊት ሀገር ናት፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ ባሳለፈችው ረዥም ዘመኗ በርካታ ደጋግ መልካም ሥራና ስም የነበራቸው ታላላቅ ሰዎች አልፈውባታል፡፡ ለታሪኳ፣ ለቅርሷ፣ ለባህሏ፣ ለዕድገቷ፣ ለድንበሯ ለአንድነቷ፣ ለነጻነቷ፣ ለክብሯ በሚገርም ወኔና ጀግንነት ደማቸውን ያፈሰሱላት፣ አጥንቶቻቸውን የከሰከሱላት ጀግኖች እንደነበሩአት አሁንም እንዳሏት በታሪክ ተመዝግቧል፡፡
ይህም በመሆኑ ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን በዘመናቸው እርስ በርሳቸው በመከባበር የተራበውን በማብላት፣ የተጠማውን በማጠጣት፣ የታረዘውን በማልበስ፣ ያለማውን በማልማት፣ ቤት የእግዚአብሔር ነው በሚል አገራዊ ትውፊት እንግዳ እየተቀበሉ እግር እያጠቡ ቤት ያፈራውን ተካፍለው በመብላት ተከባብረው በመኖር የታወቁ ደጋግ አባቶች ልጆች መሆናችን ይታወቃል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለአያሌ ዘመናት የኖሩባትና አሁንም የሚኖሩባት በአርአያነት ልትጠቀስ የሚገባት ብቸኛ ሀገር መሆኗ ከማንም ግንዛቤ የተሰወረ አይደለም፡፡
ይሁንና በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን፡-

 • የሰዎች ሕይወት እየጠፋ መሆኑ፣
 • የአገር ሀብትና ንብረት እየወደመ መታየቱ፣
 • ከነበሩበት እና ከኖሩበት ቦታ የሕዝቦችን ፍልሰት ማስከተሉ፣
 • በእነዚህም እየታዩ ባሉ ችግሮች ምክንያት በሰላማዊው ኅብረተሰብ ዘንድ ከፍተኛ ስጋት እየሰፈነ መምጣቱና ልማታዊ ሥራዎችም ሊስተጓጐሉ እንደሚችሉ መገንዘብ ተችሏል፡፡

ስለዚህ የዚሁ የጥቅምቱ 2009 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በአገሪቱ እየታየ ባለው የሰላም ችግር ላይ በሰፊው በመወያየትና በመነጋገር የሚከተለውን መግለጫ አውጥቷል፡፡


1ኛ. በአገራችን ውስጥ ለአገራችን ዕድገት ሲባል ምላሽ የሚያሻቸው ጥያቄዎች አሉን የሚሉ ወገኖች ሁሉ እንደ ጥንት አባቶቻችን ኢትዮጵያዊነትን በተላበሰ፣ በሰከነና በተረጋጋ ሁኔታ ጥያቄያቸውን ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል እንዲያቀርቡ፣
2ኛ. መንግሥት በአንድ አገር ውስጥ ለሚኖሩና ለሚያስተዳድራቸው ዜጎች እንደቤት ኃላፊና ልጆቹን እንደሚያስተዳድር መሪ እንደመሆኑ መጠን በሰከነና በተረጋጋ መልኩ ከዜጎች የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በአግባቡ በመፈተሽና በማጥናት ለአገርና ለወገን የሚጠቅመውን ምላሽ እንዲሰጥባቸው ለሕዝቡ የገባውንም ቃል በተግባር አውሎ በሥራ እንዲተረጉም፣
3ኛ. የነገድ፣ የሃይማኖትና የጾታ ልዩነት ሳይኖር ለጋራ ሕልውና፣ ለጋራ ልማትና ለጋራ ብልጽግና ለሀገራችን ኢትዮጵያና ለጐረቤት አህጉር ብሩህ ተስፋ ሰንቆ እንደሚመጣ የተነገረለት የሕዳሴው ግንባታ ፕሮጀክት ኢትዮጵያዊነቱን እያስመሰከረ ስለሆነ እንዲሁም በዘመናችን የምንታወቅበት ዓቢይ ታሪካችን የአባይ ሕዳሴ ግንባታ ግድብ የመሆኑን ያህል አሁንም ፕሮጀክቱ ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ በማንኛውም አቅጣጫ በሁሉም ወገን ያለ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በአንድነት ለግንባታው በመሰለፍ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ፣
4ኛ. ባለፈው ዓመት በነበረው የዝናም እጥረት ምክንያት በአገራችን ደርሶ የነበረው ድርቅ በመንግሥትና በመላው ኢትዮጵያዊ ሙሉ ድጋፍ ያለምንም የውጭ ርዳታ ችግሩን መወጣታችን ይታወቃል፡፡
ሆኖም በቀጣዩ ዜጐችን ለረሀብና ለስደት የሚዳርግ እንዲህ ዓይነት አስከፊ አደጋ በአገራችን እንዳይከሰት አገራችን እግዚአብሔር ባደላትና በሚያድላት የተፈጥሮ ፀጋ ምድሪቱን እየተንከባከብን ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ለልማቱ በመነሳት ምርታማነትን በማሳደግ ለዕድገት እንድንበቃ ተግተን የሥራ ባህላችንን ልናዳብር ይገባል፡፡
5ኛ. ሥር ነቀል የግንባታ ሥራ እየተካሔደባት ያለች ሀገራችን ኢትዮጵያንና ጥቅሞቿን በማይጻረር በሰላማዊ መንገድ ተቀራርቦ በክብ ጠረጴዛ የጋራ ውይይት በማካሔድ ችግሮችን መፍታት አግባብነት ያለው አሠራር ስለሆነ የሀገር ጉዳይ የጋራና የውስጥ ጉዳይ እንጂ ድንበር ተሻጋሪ እንዳልሆነ በአገሪቱ የሚገኙ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ግንዛቤን ወስደው የበኩላቸውን ድርሻ መፈጸም ይችሉ ዘንድ የራሳቸው የሆነውን አመለካከት ይዘው ሀገሪቱን ከሚመራው መንግሥት ጋር በክብ ጠረጴዛ እንዲወያዩ፣
6ኛ. ቀደምት አበው ኢትዮጵያውያን ዐረፍተ ዘመን እስከገታቸው ድረስ ሀገራቸውን ጠብቀው ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ታሪክ ለቀጣዩ ታሪክ ተረካቢ ትውልድ ማቆየታቸው የሚታወቅ ነው፡፡

ከዚህ አንጻር ወጣቱ ትውልድ ከቀደምት አበው የወረሰውን ትውፊት በመከተል፡-

 • ለሀገራችን የሚጠቅሙትን፣
 • ለልማትና ለሰላም የሚበጁትን፣
 • በሀገር ውስጥ ያሉ እና ከሀገር ውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን አንድነትና ኅብረት የሚጠናከርበትን ሁኔታ በመሻት የበኩሉን ድርሻ ማበርከት ይጠበቅበታል፡፡

7ኛ. አገራችን ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ራሷን ከወራሪ ጠላት በመከላከል ነጻነቷንና ክብሯን፣ ሰላሟንም ጭምር ጠብቃ ይዛ የቆየች መሆኑ ይታወቃል፡፡
ሆኖም ግን በየዘመናቱ የውጭ ወራሪዎችና ጣልቃ ገቦች አገጣሚዎችን እየተጠቀሙ ሕዝቧን ሰላም ለመንሳት ሙከራ ሲያደርጉ እንደቆዩና በመንግሥትና በሕዝቡ አንድነት አስፈላጊው አገራዊ ጥበቃ እየተደረገ ሳየሳካላቸው በነጻነት ኑራለች፡፡
አሁንም በአገራችን እየታየ ያለው የሰላም መታጣት አንዳንድ የውጭ ጣልቃ ገቦች እጅ እንዳለበት በርካታ አመላካች ሁኔታዎች እየታየ ሲሆን እነዚህ ከአገራችን ውጭ በአገራችን ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ ሰላም የሚነሱ የውጭ ዜጐች * ከአጥፊ ተልእኳቸው እንዲገቱ ቤተ ክርስቲያን አጥብቃ በማሳሰብ ድርጊቱን ትቃወማለች፡፡
8ኛ. ቤተ ክርስቲያናችን ለአገራችን ኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ባለውለታ በመሆን ሕዝቡን የሰላም ወንጌል በማስተማር የተጣላ በማስታረቅ የተለያየውን አንድ የማድረግ ተልእኮዋን በመፈጸም የቆየች እንደመሆኗ አሁንም ዕለት በዕለት ከምታከናውነው መንፈሳዊ አገልግሎት ባልተናነሰ መልኩ ከቅዱስ ሲኖዶሱ ጀምሮ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በሕጓና በሥርዓቷ መላው ካህናትና አገልጋዮች በዕለተ ሰንበት ለሚገኘው ሕዝበ ክርስቲያን፣ በማታ ጉባኤ፣ በወርኃዊና ዓመታዊ በዓላት ሁሉ ሕዝበ ክርስቲያኑ በሥነ-ምግባር ታንጾ በፈረሃ እግዚአብሔር በግብረ-ገብነት ለአገሩ ሰላምና ለሕዝቡ አንድነት ተባብሮ እንዲቆም የሚያስችል ትምህርት እንዲሰጡ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መመሪያን ያስተላልፋል፣
9ኛ. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እስከዛሬ ባደረገው ስብሰባ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ተዘጋጅቶ በቀረበው የ2009 ዓ.ም. በጀት ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡

10ኛ. ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም. በተካሄደው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የቀረበው የጋራ መግለጫ ላይ ተወያያቶ አንዳንድ ማሻሻዎችን በማድረግ የ2009 ዓ.ም. በጀት ዓመት የሥራ መመሪያ በማድረግ አጽድቋል፡፡
11ኛ. ለተዋሕዶ ሃይማኖታቸው ለሀገራቸው ልዕልናና ነጻነት በ1928 ዓ.ም. ከአርበኞች ጎን በመሆን ለሀገራቸው ነጻነት ጠንክረው እንዲዋጉ ሲያስተምሩ በነበረበት ወቅት በኢጣልያ ፋሽስታዊ መንግሥት በጎሬ ከተማ በ1929 ዓ.ም. በግፍ በሰማዕትነት የተገደሉት ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ሰማዕት ተብለው እንዲጠሩ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ወስኗል፡፡
12ኛ. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከጥቅምት 12 – 16 ለአምስት ቀናት ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም በቤተ ክርስቲያኒቱ ልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ሲወያይ ሰንብቶ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ስብሰባውን በዛሬው እለት አጠናቋል፡፡

 

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም
ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

የፎንት ልክ መቀየሪያ